የትናንቱ ትውልድ በአድናቆት፣ የዛሬ ልጆች በትዝታ ስሟን እያነሳሱ የሚያደናንቋት ድምጻዊት ሂሩት በቀለ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በፊት ይህንን የእኛን ወቅት በሚገባ የሚገልጽ አንድ ዘመን አይሽሬ ዜማ ማንጎራጎሯ ይታወሳል፤
“ሃሳብ እሹሩሩ ውረድ ከጀርባዬ፣
መሸከም የማይችል አፈር ነው ስጋዬ::
በትካዜ ባህር መንፈሴ ተውጦ፣
ሃሳብን ታቅፌ አጠባለሁ ጡጦ::
በሃሳብ በትካዜ አእምሮዬ ዞሮ፣ በመኖር ላይ አለሁ እንቆቅልሽ ኑሮ::” ይህቺ ድምጻዊት ዘመኗን በሚገባ ኄሳበት፤ ለእኛም ዘመን እንደ ትሩፋት ያሸጋገረችልን ይህ ዜማ እንደ ቀድሞው ዘመን ዛሬም ለዘፈን ምርጫ ውድድር ቢቀርብ በሚሊዮኖች ድምጽ አሸናፊነትን ሊጎናጽፍ እንደሚችል ጥርጥር የለውም::
ድምጻዊት ሂሩት ሆይ! ረጅም ዕድሜን ያድልልን:: በአንድ ወቅት በቤትሽ ተገኝቼ ስንጨዋወት ይህንን ዜማ እንድታንጎራጉሪ ባለመጠየቄ ቆጭቶኛል:: ወይ ነዶ! አለ አሉ ዕድል ያመለጠችው ጀግና::
የዘመናችን ሃሳብ እሹሩሩ፤
እኛ የዛሬዎቹ የኢትዮጵያ መልኮች ግራ ገብቶንና ግራ ተገባብተን ፈጣሪን ራሱን ሳይቀር ግራ ያጋባንበት፣ እንዴትና ስለምን ሊሆን ቻለ ለሚሉት ጥያቄዎቻችንም መልስ ያጣንባቸው በርካታ ጉዳዮቻችን እንቆቅልሽ ሆነውብን “ሰማይ ምድሩ” ዞሮብናል – ይህንን የብሶት መንደርደሪያ የሃሳብ እሹሩሩ “አንድ” ብለን በመቁጠር ንባባችንን እንቀጥል::
“ጦርነትን እንደ ባህል የወረስነው” ፈቅደንና ወደን ይሁን ወይንም ፈጣሪ ራሱ የዕጣ ክፍላችን እንዲሆን ፈቅዶና ወዶ ያድርገው ለጊዜው መልሱን ስላልደረስንበት ግር እንደተሰኘን አለን – ሁለተኛው የሃሳብ እሹሩሯችን መሆኑን እያስታወሰን ወደፊት እንቀጥል:: ድርቅና ርሃብ በየአሥር ዓመቱ እየጎበኙን ስለምን እንደ ቱሪስት መዳረሻ እንደሚንሸራሸሩብን ወይንም በፈቃዳችን እንጋብዛቸው እንደሆን እንጂ ብቻ እስከ ዛሬ ድረስ መልስ የሚሰጠን ምሥጢር ፈቺ አላገኘንም – ሦስተኛው የሃሳብ እሹሩሯችን መሆኑን ልብ ይሏል::
አምነንና ፈቅደን ብቻም ሳይሆን በግድ እንድናምናቸው ጭምር “አስገድደውን” መንበረ ሥልጣኑ ላይ ፊጥ ያሉት ፖለቲከኞቻችንና ሹማምንቶቻችን እርካቡን ከተቆናጠጡ በኋላ በተጨባጩ የምድር ኑሯችን ላይ ሳይሆን በማይጨበጠው አየር ላይ እያንሳፈፉ ከዳቦ ይልቅ ተስፋ በማስገመጥ “ተኖረና ተሞተ” በሚል እሹሩሩ እንድንቆዝም ፈርደውብናል::
መከራን እንደ እመጫት “ጡጦ እያጠባን” በእህህ ቀን መግፋታችን ልክ እንደነሱ የተመቸን መስሏቸው ከሆነም ተራራ የሚያህል ስህተት መሳሳታቸውን ቢያውቁት መልካም ይሆናል – ይህንን እሹሩሩ በአራተኛነት እንመዝግበው::
በተለየ ሁኔታ የአገራችን የንግድና የሰላም ሚኒስቴር መ/ቤቶች ስማቸውና ተግባራቸው አልጣጣም ብሎ አንዱ ለዕለት ጉርሳችንና ለማባያው ዘይት እንኳን ግድ ሲያጣ፤ ሌላው ስም እንጂ ግብር ተነፍጎት በሰላም ጠኔ እንቅልፍ አጥተን ማደራችን የቆረቆራቸው አይመስልም:: የቢሮዎቻቸው ሕንጻዎች ተውበው፤ መሪዎቻቸው በከረቫት ዘንጠው የትራዤዲና የኮሜዲ ተውኔት ሲተውኑብን እየሳቅን ስናለቅስ በቴያትራቸው ተማርከን ከመሰላቸው ተሞኝተዋል::
ከዛሬው አዝማሚያቸው እንደምናስተውለው ተውኔታቸው ለወደፊቱም ቢሆን ይገባናል ብለን ተስፋ አናደርግም:: ምክንያቱም ግርታው ከእለት ወደ እለት እየባሰበት እንጂ ሲሻሻል አላየንም – አምስተኛው እሽሩሩ ነው::
እብሪተኞቹ የአመጽ ልጆች በነጋ በጠባ በሚጭሩት ሽብር እየተሳቀቀች የሀዘን ማቋን ከገላዋ ላይ ለማውለቅ የተሳናት አገሬ እንባዋን ወደ ፀባኦት እየረጨች ስታነባ አብረን አንብተናል::
መፍትሔ አመንጪ መስለውን ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ሙሉ ቀን ተገትረን ውለን የመረጥናቸው “እንደራሴ ተብዬዎችም” ከመከራችን ይታደጉናል ብለን ተስፋ ስናደርግ፤ በፓርላማው ወንበር ላይ ተመቻችተው እንደተቀመጡ በአርምሞ ተውጠው ዝምታን መምረጣቸው በእጅጉ ተስፋችን እንዲቆስል ምክንያት ሆነዋል::
“ዐይነ ስውር ልጅ የወለደች እናት፤ ልጇን ቦጋለ ብላ ትጠራዋለች” እንዲል የራሳችን አገራዊ ብሂል እንቶኔን ምርር ብለን ብናዝንባቸው ቢያንስ እንጂ በዝቷል ተብሎ አያስቆጣም:: የመስማትን አቅም የሚቀንሰው የዕድሜ ፀጋ ብቻ ሳይሆን የሕዝብ ኡኡታ ሲበዛ ለካንስ የመንግሥትም ጆሮ ይደነቁራል – ስድስተኛው የሃሳብ እሹሩሩ ምዕራፍ ላይ ደርሰናል::
“ሀዘንሽ ቅጥ አጣ፤ ከቤትሽ አልወጣ…” እንዲል ወግ ጠራቂው የእኔው ሕዝብ፤ የአገራችን መከራና አበሳዋ መቼና እንዴት ከጀርባዋ ላይ እንደሚንከባለል ቀን ቆጥሮ፣ ዘመን ሰፍሮ የሚተነብይ ባለ ራእይ አጥቶ ተቸግሯል:: የቤታችን አሳርና ፍዳ ያነሰ ይመስል ጡንቸኞቹ የዓለም መንግሥታት በርሃብና በድህነት የሰለለውን እጃችንን ለመጠምዘዝ ሌት ተቀን የፍልሚያ ሸማ ካልተጣጣልንና ካልለየልን በማለት በመልእክተኞችና በሚዲያ ወረራ እያጨናነቁ ፋታ ነስተውናል::
“ምን እጅ አለው የእሳት ሰደድ፤ አያውቅም ክንዳችን እንደሚያነድ” እያልን እንደ አፄ ቴዎድሮስ እንዳንፎክር እንኳን ወኔውም ይሁን አቅሙ ወይንም ኅብረታችን ኮስምኖ ሁላችንም አኩራፊ ሆነን ቋንቋችን ተደበላልቋል::
መሆን ወይንም አለመሆን፤ እዚህ ላይ ነው ችግሩ፣
የዕድል ፈተና አለንጋ፣ ሲወናጨፍ ወስፈንጥሩ፤
በሃሳብ ግርፊያ መሰቅየቱ፣ ችሎ ታፍኖ ማደሩ፣
ወይስ የመከራን ማዕበል ተጋፍጦ ጦርን ከጦሩ፣
ተጋትሮ ወግቶ ድል መምታት እስኪነቀል ከነሥሩ፣
የቱ ነው [የሀገር] ክብሩ?
ይህ የተውኔት መነባንብ የተቀነጨበው ከጸጋዬ ገብረ መድኅን የኀምሌት ተውኔት ገቢር ሦስት ላይ ሲሆን አነብናቢው ገፀ ባህርይ ደግሞ ኀምሌት ራሱ ነው:: ከፑሽኪን የተዋስነው መልእክት የአገሬን ወቅታዊ ሁኔታ ፍንትው አድርጎ ስለሚያሳይ ሰባተኛው የሃሳብ እሹሩሩ ትዝብት መሆኑ ይመዝገብልን::
ሃሳብ እሹሩሩ ውረድ ከጀርባችን፤
መቼና ከየትኛው ገጽ ላይ እንዳነበብኩት ለጊዜው ግር ካለኝ ምንጭ ላይ በአእምሮዬ ከትቤ የያዝኩት አንድ ልብ ጠለቅ አባባል ሁሌም ትውስ ሲለኝ ይኖራል:: ሳይንስ ሙግት እንደማይገጥመን ተስፋ በማድረግ ጥቅሱን ላስታውስ፤ “የሰው ልጅ ያለምግብ ለአርባ ቀናት፣ ያለ ውሃ ለሦስት ቀናት፣ ያለ አየር ለስምንት ደቂቃ መቆየት ይችላል:: ያለ ተስፋ ግን ለአንድም ሰከንድ ቢሆን መኖር አይችልም::” እንግዲያውስ ጥቅሱ እውነታነት ካለው የሞራል ትምህርቱን ከኑሯችን ጋር እናገናዝበው::
የዕለት እንጀራ ብርቅ ሆኖብናል – እውነት ነው:: የምንጠጣው ምንጭም ነጥፎብናል – ትክክል:: የምንተነፍሰው የሰላም አየርም ተበክሏል – በርግጥ:: የዘረዘርናቸውን የመከራ ዓይነቶች በሙሉ ለመሸከም ብንገደድም የተስፋችን ብርሃን ጨልሞ በአረንቋ ውስጥ እንደተዘፈቅን እንዳንሞት ከቁዘማ ወጥተን መንፈሳችንን በማጀገን “ጉልበቴ በርታ! በርታ!” እያልን ልንጽናና ይገባል:: የጦርነት ማግስቱ ገበያ ጨርቁን ጥሎ አብዷል:: ኑሮውም ጦዞ አጡዞናል::
ድሆች ከመንግሥታቸው የሚጠይቁት የመጨረሻው ዝቅተኛ መብት የዕለት እንጀራ እንዲቀርብላቸው መጠየቅ ነው:: በዳቦ ጉዳይ ሕዝቡ ምሬቱ ገንፍሎ እምባው አሲድ እንዳያዘንብ መንግሥታችን ሆይ! ጨክነህ ዳቦ ለማቅረብ ትጋ:: ሕዝቡ “ጅብ ከሚበላህ ጅብ በልተህ ተቀደስ” ወደሚል ቁጣ ሳይገፋፋ በፊት የንግድ ሥርዓቱን ከላይ እስከ ታች የሚመሩት ሹመኞችና ባለሙያዎች ለእሪታው ጆሮ ቢሰጡ ይበጃቸዋል::
ከገጠር እስከ ከተማ እየተሹለከለኩ ነፍሳችንን እንደ ጎመን የሚቀነጥሱትንና ሀብታችንን እየዘረፉ የሚያፈናቅሉንን ሸማቂዎችና ምን ግዴዎች መከራ ባጎበጠው የሕዝብ ትከሻ ላይ ሌላ አበሳ ሲያሸክሙን ቸል ማለቱ አዋጭ ስልት ስላለመሆኑ ደፍረን የፍትሕ ያለህ እንላለን::
የምስኪኖች ጩኸት ብቻም ሳይሆን የትልቁ “የሕጎች አባት” የደነገገው መብትና በቅዱስ መጻሕፍት ውስጥም የፍርዱ ውጤት በሚገባ ስለተጠቀሰ መንግሥታችን ሆይ! ከተደራራቢ ፍርድ ለመዳን መሞከሩ ብልህነት ነው:: ጓያ እንደሰበረው ገልቱ ሰው “ቆይ ብቻ!” እያሉ ማነከሱ ሩቅ ስለማያራምድ ሞቱና ውድመቱ እንዲገታ መሃላቸውን በማስታወስ መሪዎቻችንን የሙጥኝ እንላለን::
ሃሳብ ከውለታ ስለማይቆጠርም “እያሰብንበት ነው” በሚሉ ሪፖርቶች ሊያደነጋግሩን ባይሞክሩ መልካም ይሆናል:: “ልብ ያለው ልብ ማድረጉ” ከእኛ ከግፉዓን ይልቅ ለእነእርሳቸው በእጅጉ ስለሚጠቅም “እሹሩሩ” እያልን ጡጡ ከምናጠባው ሃሳብ ነፃ ያውጡን ::
“ኧረ ምረር ምረር፤ መረር እንደቅል፣ ስላልኮመጠጠ ስላልመረረ ነው ዱባ እሚቀቀል::”
እያለ ያቅራራው ባለአገር ጥሩ ሌጋሲ ትቶልን ስላለፈ “መምረሩና መኮስተሩ” አንድም ለራስ ነፍስ፤ አንድም ለሕዝብ በረከት በእጅጉ ይጠቅማል:: ሽቅብ የላይኞቹን፣ ወደ ጎን እርስ በእርስ መሰዳደቡና በየአደባባዩ ተዋርዶ ማዋረዱ በሌላው ዘንድ የማይፋቅ ትዝብት፤ ለራስም ርኩሰት ነውና “አዋቂና አንቂ የሕዝብ ተቆርቋሪዎች እኛ ብቻ ነን” የሚሉ አውርቶ አደሮችም አደብ ቢገዙ ውለታ እንደዋሉልን እንቆጥራለን::
በቁስላችን ላይ ጨው እየነሰነሱ እንድንፈራገጥ የሚጎተጉቱን ከሆነ ግን እርግጫው የሚተርፈው ለእነርሱም ጭምር መሆኑን ቢረዱት መልካም ይሆናል:: አደባባዮቻችንንም ባልተገራ ምላስ ባይበክሉት ለሁላችንም ይበጅ ይመስለናል:: የማይበርድ እሳት ለማጋጋልም ሆነ ያልበላንን የታሪክ ወገብ እያከኩ የሚያቋስሉን የመንግሥት ሹመኞችም ሆኑ የፖለቲካ ካድሬዎች የሥልጣናቸው ወንበር የሚቆረቁራቸው ከሆነ በራሳቸው ፈቃድ ዞር ቢሉ ይሻላል እንጂ ሕዝቡን ምክንያት ባያደርጉ የተሻለ ይሆናል::
“ሁለት ባላ ተክለው፤ አንዱ ቢሰበር በአንዱ ለመንጠልጠል” አስበውም ከሆነ የተንጠለጠሉበት ቅርንጫፍ ለሁልጊዜ ተሸክሟቸው እንደማይዘልቅ የምንመክራቸው በሕዝብ ድምጽ ነው:: የማክዶናልድ ጥጋብ ያለ ስንቅ የሚያዘምታቸው “የሀገረ ያኒኪዎቹ” ሴረኞች የኢትዮጵያን ተስፋ “ቆርጦ ለመጣል” እያሴሩበት ያለውን የማዕቀብ ሰይፍ ወደ ሰገባው ቢመልሱ ለእነርሱም ለእኛም ሳይበጀን አይቀርም::
ማዕቀቡ እንዳይተገበር የሚወተውቱትና አደባባይ እየዋሉ ድምጻቸውን የሚያሰሙት ወገኖች ከዲያስፖራው ሰፈር ብቻ መሆን ያለባቸው አይመስለንም:: እኛም በአገር ቤት ያለን ባለአገሮች “ማዕቀብ ካልጣልን” ወደሚሉ አገራት የኤምባሲ ጽ/ቤቶች ጎራ እያልን ድምጻችንን ብናሰማ አይከፋም::
“እሹሩሩ” የምንልባቸው አገራዊ ሃሳቦቻችን በብዛትም፣ በይዘትም፣ በዓይነትም፣ በቅርጽም በርካታ እንደሆኑ ይገባናል:: ቢሆንም ቢሆንም ግን “ዘጠኝ ሞት መጣ ቢሉት፤ አንዱን ግባ በለው” እንዲሉ፤ የተስፋ መቁረጥ ውስጥ ተዘፍቀን በጭራሽ ልንሟሟ አይገባም:: ከእሹሩሩ ባሻገር አገሬ ታላቅ ተስፋ አላት፤ መዳረሻዋም ከፍታ ነው::
በሃሳብ በትካዜ አእምሮዬ ዞሮ፣
በመኖር ላይ አለሁ፤ እንቆቅልሽ ኑሮ::”
እያልን ከድምጻዊት ሂሩት በቀለ ጋር ማንጎራጎሩ ለስሜት ማረጋጊያ ይጠቅም ካልሆነ በስተቀር ቀጣዩ ጥረታችንን ከማጎምዘዝ ውጭ እርባና ስለሌለው ከእሹሩሩ ቁዘማችን ተላቀንና መከራን ተጋፍጠን በአሸናፊነት እንድንወጣ የዳግላስ ብእር አንባቢያንን ይማጠናል:: ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን የካቲት 30 /2014