ትውልዳቸው ምዕራብ ሸዋ ዞን ሜታ ሮቢ ወረዳ ጠለታ የምትባል ቦታ ነው:: እናት እና አባታቸው ለአገራቸው ሲታገሉ የኖሩ እና በትግል ውስጥ ያለፉ ናቸው:: የእናታቸው አባት ተሰማ ገዳሙ በጣሊያን ወረራ ጊዜ ትልቅ ጀብድ ፈጽመዋል:: ጣሊያንን አታለው ለወገን ከ50 መትረየስ በላይ ማስገኘት ችለዋል:: በዛ ጊዜ ባይማሩም የፈጠራ ሰው በመሆናቸው ፎቅና ድልድይ ለመሥራት የበቁ ኢንጂነር ናቸው:: አባታቸው ብሩ በዳሳም በጣሊያን ወረራ የተሳተፉ ሲሆን፤ ወረኢሉ ላይ ወሎ ውስጥ ትልቅ ተጋድሎ ፈጽመዋል:: ይህንን እና ሌሎችም የብዙ ጀግኖችን ታሪክ እየሰሙ ‹‹እንደነሱ በሆንኩ እያሉ›› ያደጉት የዛሬዋ የሴቶች ቀን እንግዳችን ሉላ ጉራ በሚባል ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል::
በኢንጪኒ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመለስተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል:: የከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ ሆለታ ገነት ትምህርት ቤት ጀምረው፤ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በ1983 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከፍተኛ ሰባት ትምህርት ቤት የ11ኛ ክፍል ተማሪ ሆነው ኢህአዴግ አገሪቱን ሲቆጣጠር ትምህርታቸውን አቋርጠዋል:: በደርግ ጊዜ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ በኦነግ ይተላለፉ የነበሩ የአፋን ኦሮሞ የሬዲዮ ፕሮግራሞችን ያዳምጡ የነበሩት እኚሁ ሴት፤ ከኦነግ ወደ ኦህዴድ ያመጣቸው ሞቷል ተብሎ ለ17 ዓመት ተስካር ሲበላበት የነበረው አብሮ አደጋቸው የአጎታቸው ልጅ የኦህዴድ መሥራች ሆኖ ቤተሰቡን ሲቀላቀል እርሳቸውንም አሳመናቸው:: ከአብሮ አደጋቸው ጋር በመሆን አብረው ኦህዴድ ውስጥ ሆነው መሥራት ጀመሩ::
በ1984 ዓ.ም ትምህርታቸውን ሲቀጥሉ በአንድ ጊዜ አምስት ወረዳን እንዲያስተዳድሩ ሥልጣን ተሰጥቷቸው ነበር:: ማዕከላቸውን ሰንዳፋ አድርገው ጂዳ፣ አሌልቱ፣ አቢቹ እና ሌሎችንም ወረዳዎች ሲያስተዳድሩ ቆይተዋል:: በዛን ጊዜ ሥልጣን የተሰጣቸው ወይዘሮዋ በኦሮሚያ ክልል ፍቼ፣ አምቦ እና ሌሎችም አካባቢዎች ላይ ምክትል ቢሮ ሃላፊ እስከ መሆን ደርሠዋል:: በ2008 ዓ.ም የፓርላማ አባል ሆነው በመመረጥ ወደ ፌዴራል መጥተዋል:: በወረዳ፣ በክልል እና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆነውም ብዙ ሠርተዋል::
በፌዴራል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ እና የሰራተኛ እና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው አገልግለዋል:: በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የመሬት አጠቃቀም ዕቅድ ፖሊሲ ዝግጅት የነበሩት ወይዘሮ ወርቅነሽ ብሩ፤ ለውጡ ሲመጣ ደግሞ በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የኢትዮጵያ ቤተ መንግሥቶች አስተዳደር ላይ ሲሰሩ ቆይተዋል::
በትራንስፖርት ሚኒስትር በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የመድህን ፈንድ አስተዳዳሪ ሆነው ሠርተዋል:: ሠላም ሚኒስቴርም በተመሳሳይ ደረጃ ሲሰሩ የቆዩ ሲሆን፤ አሁን ደግሞ በባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው::
በሃላፊነት ቦታ ላይ እየሰሩ ጎን ለጎን ትምህርታቸውን የቀጠሉት ወይዘሮ ወርቅነሽ፤ በማኔጅመንት ዲግሪ ይዘዋል:: በተቋም አመራር (ኦርጋናይዜሽናል ሊደርሽፕ) ተጨማሪ ሁለተኛቸውን የመጀመሪያ ዲግሪ አግኝተዋል:: ከአንድ የእንግሊዝ ዩኒቨርሲቲ በትራንስፎርሜሽናል ሊደርሽፕ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ይዘዋል:: ከባለቤታቸው ጋር አብረው አድገው፤ አብረው ተምረው በሃላፊነት ቦታ ላይ አንዳንዴ ሃላፊ እና ምክትል ሆነው ሠርተዋል:: አብረው ተምረው ተመርቀዋል::
ከልጅነታቸው ጀምሮ የሰሙትን ለማወቅ የሚፈልጉትን በትንንሽ ወረቀቶች ማስታወሻ በመያዝ ያስቀምጡ የነበሩት ወይዘሮ ወርቅነሽ፤ አሁን ደግሞ ከሚኒስትር ዴኤታነቱ ጎን ለጎን መጽሃፍ በመጻፍ ላይ ይገኛሉ:: በቅርቡ ከሚታተመው የብዙ ጀግኖችን ታሪክ የያዘው በአማርኛ እና በኦሮሚኛ ከተፃፈው ባለ 400 ገፅ መጽሃፍ በተጨማሪ ሌሎች ስድስት የሚደርሱ መጽሐፍትን ጀምረዋል:: ከባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር የባህል እና ቋንቋ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ወርቅነሽ ብሩ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እነሆ ብለናል::
አዲስ ዘመን፡- በፍጥነት ተቋማትን ይቀያይራሉ:: አንዳንዴ ራስዎም የተቋማት ቱሪስት ነኝ ይላሉ:: እዚህ ላይ ውጤታማነትዎ እንዴት ይገለፃል?
ወይዘሮ ወርቅነሽ፡– አንድን መሥሪያ ቤት ተረድቶ ሥራ መጀመር ቀላል አይደለም:: የመሥሪያ ቤቱን አዋጅ ደንብ እና መመሪያ ማወቅ እና ቶሎ ሁሉንም አውቆ መምራትን ይጠይቃል:: ይህንን ለመሥራት ብዙ ነገሮችን በአንድ ጊዜ የማየት ችሎታ አስፈላጊ ነው:: በእርግጥ ሴቶች ነገሮችን በተለያየ አቅጣጫ በማየት በፍጥነት ተረድቶ የመሥራት ብቃት አላቸው:: አንዲት ሴት እርጉዝ ሆና እንጀራ እየጋገረች ወጥ ትሰራለች:: የልጆችን ጩኸት እየሰማች ባሏንም ልጆቿንም ትንከባከባለች:: በዚህ ውስጥ የሴቶች አዕምሮ ሰፊ ነው:: ሁሉን ነገር ይችላል:: ስለዚህ እኔም በየሔድኩበት በፍጥነት ተቋማትን በመረዳት ውጤታማ ሥራዎችን ሠርቻለሁ:: ምክንያቱም ሴት ነኝ:: ሴት ፈጣን እና በአንድ ጊዜ ብዙ ነገር መሥራት የምትችል ናት:: በዚህም ውጤታማ ነኝ::
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካም ሆነ የሥልጣን የሴቶችን ተሳትፎ እንዴት ያዩታል?
ወይዘሮ ወርቅነሽ– መጀመሪያ አካባቢ በዞን አመራር ውስጥ የሴቶች ቁጥር በጣም ትንሽ ነበር:: በዞን ደረጃ ብቻዬን የሆንኩበት ጊዜም ነበር:: ነገር ግን በሒደት ብዙ ሥራዎች በመሠራታቸው የሴቶች ማህበር፣ ሴቶች ሊግ፣ ሴቶች ፌዴሬሽን እየተባለ የተለያየ አደረጃጀቶች መፈጠራቸው፤ ሴቶች ወጥተው እንዲናገሩ በሥራ እና በሥልጣን ላይ በስፋት እንዲሳተፉ ማድረግ አስችሏል::
ሴት የደጅ ብቻ ሳይሆን የቤቷም ሥራ እንደግዴታዋ ይወሰዳል:: ከሥራ ገብታ ልብሷን ቀይራ ስትንደፋደፍ ባል የእግር ውሃ እየጠየቀ የቴሌቪዥን ዜና ያያል:: ይሔ ልዩነት ያመጣል:: በሂደት ግን ሴቶች ራሳቸውን እንዳይጎዱ እና በፖለቲካው እንዲሳተፉ ወደ አመራር እንዲመጡ ግፊት ተደርጓል:: ከእያንዳንዷ ቅንጣት ጀምሮ ስለሴቶች ታግያለሁ:: በኦሮሚያ የቤተሰብ ሕግ ሲወጣ የተመራጭ ሴቶች ፎረም ፕሬዚዳንት ነበርኩ:: የቤተሰብ ሕጉ ሲወጣ ጋብቻ ላይ ጋብቻን ሳይከለክል ዘሎ አለፈው:: በሕግ የታለፈ ነገር እንደተፈቀደ ይቆጠራል:: ‹‹በንጉሱ ዘመን እንኳ ጋብቻ ላይ ጋብቻ መፍቀድ ተገቢ አይደለም ተብሎ በሕግ ሠፍሮ ነበር አሁን ለምን ይዘለላል ? ›› በማለት ተከራክሪያለሁ::
የክልሉ ምክር ቤት ላይ ሴቶችን አስተባብሬ ከፍተኛ ክርክር ተካሂዷል:: በቀጥታ ስርጭት ይተላለፍ የነበረው የምክር ቤት ውሎ በክርክሩ ምክንያት ስርጭቱ ተቋረጦ ነበር:: በወቅቱ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መአዛ አሸናፊ ድጋፍ አድርገውልኛል:: በዚያ ሳቢያ ‹‹አንቺ አመዱን ቡን አድርገን ጪስ ማስነሳት አለብን›› ብለሻል በመባል ትልቅ ግምገማ ተካሔዶብኛል:: ብከራከርም ብዙዎቹ ሴቶች ተናግረው እንደመቃወም ሳያሳውቁ በመውጣታቸው:: በድምፅ ብልጫ ሕጉ ጋብቻ ላይ ጋብቻን ሳይከለክል ለጊዜው አልፎታል:: ሆኖም አላቋረጥኩም፤ እስከ ፌዴራል ድረስ ሔጄ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በአስቸኳይ ጉባኤ ጠርተው ጋብቻ ላይ ጋብቻ መፈፀም እንዲከለከል ትዕዛዝ አስተላልፈው ሕጉ ተሻሽሏል::
በራሴ በኩል ሴት ብሆንም የቤቴን ሥራ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካውንም ሆነ የሃላፊነት ቦታውን ሥሠራ እስከዛሬ ቆይቻለሁ:: ሕገመንግሥት ማርቀቅ ላይ ነፍሰጡር ሆኜ ከየክልሉ ተሰባስበው በዋቢ ሸበሌ ከተቀመጡ ሴቶች ጋር አብሬ ስሠራ ነበር:: በቤተመንግሥት ውስጥ ስሠራ በዛ የነበረው ስቃይና መከራ ይታወቃል:: በምን ዓይነት ሰዎች የተከበበ እንደነበር ይታወቃል:: ሁሉም መሣሪያ የያዙ ነበሩ:: ስምንት ጊዜ የግድያ ሙከራ ተደርጎብኛል::
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ከተቃወሙት መካከል ከሚኒስትሮች ከካቢኔ ውስጥ አንድ እኔ ብቻ ነበርኩኝ:: ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ያለ ሰው እንዴት የመንግሥትን አዋጅ ይቃወማል? በሚል እኔ ብቻ ሳልሆን ድርጅቴ እና ክልሌ ጭምር ብዙ ተብለዋል:: ከለውጡ በኋላም ቢሮዬ ድረስ ሊገድሉኝ መጥተዋል:: ነገር ግን በፈጣሪ ሃይል በተለያዩ ዘዴዎችም ተርፌያለሁ::
አዲስ ዘመን፡- አሁንም ድረስ የሴቶች ሥልጣንም ሆነ የፖለቲካ ተሳትፎ ውስን ነው:: እርስ በእርስ የመደጋገፍ ክፍተት አለ:: ይህን ያህል የግድያ ሙከራ እስከማድረስ የዘለቀ ፈተናን ማለፍ የቻሉት እንዴት ነው?
ወይዘሮ ወርቅነሽ– ብዙ ሴቶች ወደ አመራርነት እንዲወጡ ሠርቻለሁ:: በተለያዩ አጋጣሚዎች ከተለያዩ የወደቁ ቦታዎች ያነሳኋቸው ሴትም ሆነ ወንድ እህቶች ወንድሞች እና ጓደኞች አሉኝ:: መደጋገፍ ላይ ብዙ ችግር የለብኝም:: ከብዙዎች ጋር በሥራ አጋጣሚም እደጋገፋለሁ:: ሴት ናት ተብዬ በተለየ ሁኔታ የምጋለጥበት ሁኔታ የለም:: ይሔ ጫና ከፖለቲካ ሂደቱ ጋር የተፈጠረ ነው:: ወንድም ላይ የሚያጋጥም ነው::
አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለምን ተቃወምሽ ተብለው ቢሮ ድረስ ለመግደል ሲመጡ ቀድሞ ሌላ ወዳጄ ‹‹ተጠንቀቂ ሊገድሉሽ ነው›› ብሎ ነግሮኝ ነበር:: ቢሮሽን ሳትቆልፊ አትቀመጪ ተብዬ ነበር:: ቢሮዬን ቆልፌ ተቀምጬ የማውቃቸው ደህንነቶች 11 ሰዓት አካባቢ መጥተው በርሽን ክፈቺ ብለው ሲያስገድዱኝ ‹‹ሁለተኛ ፎቅ ላይ ነኝ ድረሱልኝ የተባሉት ሰዎች ሊገድሉኝ መጥተዋል›› ብዬ ስልክ ሳናግር ትተውኝ ሔደዋል:: ከሔዱ በኋላ ቶሎ ወጥቼ ሊገድሉኝ ተልዕኮ የተሰጣቸውን ጊቢው ውስጥ ሳገኛቸው ‹‹ተነቃቅተናል አትከታተሉኝ›› አልኳቸው:: በማግስቱም በር ላይ ስፈተሽ ነበሩ:: በሰው ፊት ‹‹እባካችሁ ከገደላችሁኝ በሽጉጥ እንጂ በጨረር እንዳይሆን›› አልኳቸው:: በሃሳብ በለጥኳቸው::
ከቤተመንግሥት ወጥቼ ቢሮ ስቀይርም በድጋሚ ቢሮ ድረስ መጥተዋል:: ከዱባይ መጥተው መስቀል አደባባይ ላይ በኔ በኩል መኪናዬን ገጭተውታል:: ቤተመንግሥት ላይ የአንድ ቡድን ጥርቅሙን በማስወጣቴ እና ብዙ ጥቅማጥቅሞችን በማስቀረቴ ‹‹እርሷ ናት እንጂ ዐቢይ ምናደረገን?›› ብለው ለመግደል ሲከታተሉኝ ነበር:: ከዱባይ የመጡ ሊገድሉኝ የሞከሩት ተይዘዋል:: ቤተመንግሥት ውስጥ ሳይቀር መኪናዬን ለማቃጠል እና እኔን ለመግደል ተሞክሮ ነበር:: ስምንት ጊዜ ከሞት ሳመልጥ ቀላል አይደለም::
በመጨረሻ አጃቢ ውሰጂ ስባል ሁለት ሴቶችን ወስጃለሁ:: ነገር ግን መንገድ ስንሔድ ፍተሻ ላይ ብዙዎች ልጆች ይዤ የምሄድ ይመስላቸዋል:: የሴት አጃቢ አልተለመደም:: የሃዋሳ ጉባኤ ላይ ሳይቀር አንዳንዴ ፖሊሶች ይጠራጠራሉ:: ከዛ በኋላ ግን ቀዳማይ እመቤት ዝናሽ ታያቸውም የሴት ሹፌር ከመከላከያ ወስደዋል:: አጃቢም ሴቶችን ቀላቀሉ:: አሁን በየሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ሴቶች ተቀላቅለዋል:: በዚህም ደስተኛ ነኝ:: ሴቶች በጣም ጥንቁቅ እና ንቁ ናቸው::
አዲስ ዘመን፡- ካነሱት አይቀር በሃላፊነት ላይ ሴቶች እንዴት ናቸው?
ወይዘሮ ወርቅነሽ– በጣም ጠንቃቆች ናቸው:: በሃላፊነት የኖርኩ ሰው ነኝ:: ወንዶችንም አውቃለሁ:: ወንዶች ሰነፍና ዝንጉ ናቸው ማለቴ ሳይሆን የሴቶች ጥንቃቄ የበለጠ ነው:: በተለያየ ጊዜ ያጠናናቸው ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሴቶች ጠንቃቆች ናቸው:: ይህንን ማንም ቢሆን የሚመሠክረው ነው:: መኪና እንኳ ሲገዛ ሴት በጥንቃቄ ስለምትይዝ ሴት የያዘችው መኪና ተፈላጊ ነው:: በተቋም ውስጥም ሴቶች በብዛት ሌባ አይደሉም:: ሁሉም ንጹህ ናቸው ማለት ባይቻልም ሴቶች ወደ ከባድ ሌብነት የሚገቡበት ሁኔታ እጅግ ውስን ነው:: ሴቶች በብዛት በሃላፊነት ስሜት ለአገር እና ለሕዝብ ያስባሉ::
ሴቶች ከጊዜ በኋላ ወደ ሥራ እና ሥልጣን በመምጣታቸው ትንሽ ነገር ሲያጠፉ ይጎላል:: ወንድ ብዙ አጥፍቶ ሳይነገር፤ የሴቷ አገር ምድር አዳርሶ በሁሉም ይታወቃል:: በጣም ጥንቃቄ ታደርጋለች:: ሪፖርት እንኳን አጠናቅቀን እናቀርባለን:: ቤት እንጀራ እና ወጥ ሳይበስል እንደማናወጣው ሥራው ላይም የበሰለ ነገር ይዘን ለመቅረብ እንሞክራለን:: አጠናቀን ካልሠራን እንደወንዱ አንታለፍም፤ እኛም እጅ አንሠጥም::
አዲስ ዘመን፡- እርሶ በፖለቲካው ውስጥ ሲሳተፉ ስምንት ጊዜ ግድያ ተሞክሮቦታል:: ልጆች እና ቤተሰብ አልዎት:: የቤተሰብዎ እርሶን ማጣት ሙሉ ቤተሰቡ ሊበተን የሚችልበትን ሁኔታ ይፈጥራል:: በዚህ ምክንያት እንዴት ከፖለቲካው ዓለም ራስዎን አላገለሉም?
ወይዘሮ ወርቅነሽ- ትክክል ነው:: እዚህ ምድር ላይ በጣም ውድ አንዴ ካለፈ የማይገኝ ማንም ሰው የሚሰስታት ሕይወት ናት:: ነገር ግን ሕይወት መሆን በሚገባት ነገር ካለፈች ምንም ማለት አይደለም:: ሕዝብ ላይ የሚደርስ ስቃይና መከራን፣ ግፍን አጥፍተን ሕዝብን የሚጠቅም ነገር ማድረግ ከተቻለ አንድ ሰው እና አንድ ቤተሰብ ቢያልፍም ብዙ አያሳስብም:: ችግሩን የቀረፍኩለት ሕብረተሰብ እኔን ተክቶ ልጆቼን ያሳድጋል፤ ቤተሰቤን ይረዳል ብዬ አስባለሁ:: ለሕዝብ ራሴን ከሰጠሁ በኋላ ሕይወቴን መሰሰት አይኖርብኝም ብዬ አስባለሁ:: በመኪና እስከ ቤት ድረስ ሲከታተሉኝ ቤተሰብ ላይ ጫና ይፈጥራል:: ነገር ግን ቤተሰቦቼ አብዝተው ይደግፉኛል::
ቤተሰቦቼ ሰርተው የሚበሉ የሚያጠጡ ናቸው:: ከባለቤቴ ጋር ወደ 30 ዓመታት ስንቆይ ለአንድም ቀን ክፉ ደግ ተባብለን አናውቅም:: ባለቤቴ አምባሳደር ዳባ ደበሌ መልካም ሰው ነው:: ከባለቤቴ እናት ጋር ለ27 ዓመታት አብረን እየኖርን ነው:: በብዙ መልኩ ያግዙኛል:: የእኔ እናትም ከመኪና አደጋ ተርፋ እርሷም ከኔ ጋር መኖር ከጀመረች አራት ዓመታት ተቆጥረዋል:: ሁለቱም እናቶቻችን አብረው ይውላሉ:: በቤት ውስጥ ብዙ ሰዎች ይኖራሉ:: አንድም ቀን ሰው ተጣልቶ አያውቅም::
ግማሹ ይማራል:: ግማሹ ይሠራል:: ልጆቼ ትልልቅ ቦታዎች ደርሰውልኛል:: ሁለቱ ትልልቆቹ በስኮላርሽፕ አሜሪካን የተማሩ ሲሆን አንደኛዋ እዚህ ወርልድ ባንክ ትሰራለች:: ወንዱ ልጄም ሳይንቲስት ነው:: የፈለገው ብርን ሳይሆን አገሩን በመሆኑ የውጭ የሥራ ዕድል ትቶ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ ትልልቅ ቁምነገሮችን በመሥራት መንግሥት እና ሕዝብን እያገዘ ነው:: በድሮን ቴክኖሎጂ ታዋቂ ነው:: ታናናሾቹም ታታሪዎች ናቸው:: በአጠቃላይ አንድ ወንድ እና አምስት ሴት ልጆች አሉኝ:: ሁሉም ብርቱዎች ናቸው:: ይህንን ማንም ያውቃል::
አዲስ ዘመን፡- በአንድ በኩል ፖለቲካ እና ሥልጣን በሌላ በኩል ልጅ አሳድጎ ለውጤት ማብቃት አይከብድም?
ወይዘሮ ወርቅነሽ– ስኬት ያለሥራ፣ ያለእንግልት እና ያለድካም አይመጣም:: ከዛ አልፎ ፈጣሪም ሲፈቅድ ነው:: እያንዳንዱ እንቅስቃሴዬ ላይ እኔ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ብሆንም ሙስሊሞች እና ፕሮቴስታንቶች ሳይቀሩ ብዙ ነገር ይነግሩኛል:: እያንዳንዱ ሂደት ውስጥ ፈጣሪ ያመለክተኛል:: ሞቶ አስከመነሳት ደርሻለሁ:: ይህንን በመጽሐፌ ውስጥ አካትቼዋለሁ:: ብዙ ጊዜ አልተኛም:: ቀን የቢሮ ሥራ እሰራለሁ፤ በብዙ ነገር ውስጥ አለሁ:: በሴት ተመራጭ ፎረም ፣ በማህበር ውስጥና ሊግ ውስጥ አለሁ:: በሚኒስቴር መስሪያ ቤት ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ኮሚቴ ሆኜ እሠራለሁ:: በአገር ውስጥ ብዙ ያልተሠሩ ሥራዎች አሉ:: ሃላፊነቴን ለመወጣት ጥረት አድርጌያለሁ:: እንደገና ቤት ስገባ እናቴ በመኪና አደጋ በመጎዳቷ ለሊት ሲያማት እሸማቀቃለሁ:: አልፎ አልፎ የሚመጡ ነገሮችን በሙሉ ችዬ በተጨማሪ ለሊት አነባለሁ፤ እጽፋለሁ::
ብዙ ጊዜ ያለፍኳቸው እና እያሳለፍኳቸው ያሉ መከራዎችን እና ስቃዮችን ሳይሆን ነገን አያለሁ:: ስለነገ ብቻ ተስፋ አደርጋለሁ:: ትልቁ እና ዋናው ሸክሜን በሙሉ ቤተሰቦቼ ያግዙኛል:: የባለቤቴ እናት እና እህት ወንድሞቼ ያግዙኛል:: የትዳር አጋሬም ለእኔ ትልቅ ቦታ አለው:: እርሱ የእኔን ቁስል ያውቀዋል:: አንድ ዓመት እና ከዛ በላይ ቤት መቀመጥ አጋጥሞን ነበር:: ያ ሁሉ ፈተና አንዱ ሲወድቅ ሌላው አይዞን ያልፋል ባይል እዚ መድረስ አይቻልም ነበር:: አንዳንዶች ጨጓራቸው ገበር አለው ይሉናል:: ዝቅ ቢሉም አፈር ልሰው ይነሳሉ እያሉ ያሙናል:: እኛ ግን ፈተና ሲኖር ችግሩን ወደ ደስታ ቀይረን መቆየት ችለናል:: ወንዶች ቶሎ ቢከፉም ሴቶች ነገን ተስፋ ማድረግ ይችላሉ:: እኔም በተስፋዬ ነገን በማየቴ ለዚህ በቅቻለሁ::
አዲስ ዘመን፡- ሴቶች ከእርሶ ምን ይማራሉ?
ወይዘሮ ወርቅነሽ- አሁን በተለይ ከለውጡ ወዲህ በሴቶች መያዝ የለባቸውም ተብለው ሕግ የወጣባቸው የሚመስሉ የተለዩ ቦታዎች ሁሉ በሴቶች ተደፍረዋል:: ከንቲባነት እና ሚኒስትርነት ጭምር በሴቶች ተይዟል:: ይህን ዕድል በደንብ መጠቀም ይገባል:: ሕዝብ እና መንግሥትን ማገልገል ያስፈልጋል:: እኛ የወጣን ሴቶች ደግሞ ሊወጡ የሚችሉ ሴቶችን በመኮትኮት ከእኛ ደረጃ በላይ እንዲደርሱ መተጋገዝ፣ መመካከር፣ አብሮ መሆን ያስፈልጋል:: ይህን ማድረግ ዝም ብሎ አይመጣም:: የቤት ውስጥ ስራ የሚቀልበትን መንገድ መጠቀም ያስፈልጋል::
ሁልጊዜ ራሳችንን ብኩን ማድረግ ሳይሆን ተረጋግተን ለራሳችን ጊዜ እየሰጠን ሚዲያ የመከታተል መጽሐፍ እና ጋዜጦችን ማንበብ ላይ ትኩረት በማድረግ አቅማችንን ማሳደግ ይኖርብናል:: ስለአገር እና ስለሥራ ማውራት ያስፈልጋል:: ከሌሎች ባለሥልጣኖች ጋር ጊዜ እንዲኖረን ማድረግ አለብን:: በሥራችን ስናጓድል ለሚመጡ ሴቶችም እንቅፋት እንዳንሆን መጠንቀቅ አለብን::
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ እጅግ አመሰግናለሁ::
ወይዘሮ ወርቅነሽ- እኔም በጣም አመሰግናለሁ::
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን የካቲት 29/2014