የዓለም ጤና ድርጅት ውስጥ በአስር አገራት በአራት አሕጉራት ለ21 ዓመታት በመዘዋወር አገለግለዋል፤ የአፍሪካ ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርም በመሆን ሰርተዋል:: በድምሩ ለ 42 ዓመታት ዓለምን በመዞር አንቱ የሚያሰኙ ሥራዎችን በጤናው ዘርፍ አከናውነዋል::
ከዛም ወደ አገራቸው በመመለስ “ለደግ ሚድ ዋይፈሪ ኮሌጅ” ን በመመስረት ችግረኛ ሴቶችን በትምህርት ለመደገፍ እየሰሩ ነው:: በዚህም በርካታ ውጤቶችን አምጥተዋል:: እኛም ለዛሬ የዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ልዩ እትማችን እንግዳ በማድረግ የሕይወትና የስራ ልምዳቸውን እንዲያካፍሉን የጋበዝናቸው ዶክተር ትዕግስት ግርማ ናቸው::
ዶክተር ትዕግስት ግርማ ማናቸው?
ዶክተር ትዕግስት ውልደታቸው አዲስ አበባ ከተማ አሮጌው አውሮፕላን ማረፊያ አካባቢ ነው፤ አውሮፕላን ማረፊያውን ተንተርሶ የነበረው ሜዳ ደግሞ ለዶክተር ትዕግስትና እህት ወንድሞቻቸው እንዲሁም ለሰፈር እኩዮቻቸው መቦረቂያ ነበር:: ለቤተሰባቸው የመጀመሪያ ልጅ የሆኑት ዶክተር ትዕግስት በብዙ እንክብካቤ ውስጥ ነው ያደጉት::
ነገር ግን ይህ እንክብካቤ አብሯቸው የቆየው ወንድማቸው መንክር እስከሚወለዱ ድረስ ብቻ ነበር፤ የመንክር መወለድ በቤት ውስጥ ትልቅ ስሜትን ፈጠረ:: ወንድ ልጅ ማግኘታቸው ትልቅ ደስታን ሰጠ:: ይህ ሁኔታ ደግሞ ብዙ እንክብካቤዎችን ባለፉት ዶክተር ትዕግስት ላይ የመረሳት ስሜትን አጫረ:: ይህም ቢሆን ግን ዶክተር ትዕግስት ከልጅነታቸው ጀምሮ ልባም ስለነበሩ የቤተሰቦቻቸውን ትኩረት ለማግኘት የተጠቀሙት ዘዴ በትምህርታቸው ጎበዝ መሆንን ነው::
ይህ ሃሳባቸውም ተሳክቶላቸው ይማሩበት ከነበረው የሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤት የደረጃ ተማሪ በመሆን የቤተሰባቸውንም የመምህሮቻቸውንም ፍቅርና እንከብካቤን ለማግኘት ቻሉ::
ዶክተር ትዕግስት በአዲስአበባ ሊሴ ገብረማርያም የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በቀጥታ ያመሩት ወደፈረንሳይ አገር ነበር:: ዶክተር ትዕግስት ፈረንሳይ አገር ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የነበራቸውን ቆይታ ሲገልጹ “በአገራችን የመማር ማስተማር ሂደት የለመድነው ሁሉም ተማሪ ለሥነ ሥርዓት ተገዢ ሆኖ መምህራኖቹን አክብሮ ሲማር ነው፤ እዛ የገጠመኝ ነገር ግን ፍጹም የተለየ ነበር::
በሄድኩበት ዩኒቨርሲቲ 1 ሺ 500 ተማሪ ነው ያለው ፤ እነዚህ ሁሉ ደግሞ ከፈለጉ መምህሮቻቸው ላይ እንቁላል ይወረውራሉ ፤ ይጮሃሉ፤ ይረብሻሉ ፤ እኛ በዚህ መካከል ግራ ተጋብተን ትምህርቱም እጅግ ከባድ ሆኖብን ነበር “ ይላሉ::
እኛ የለመድነው የትምህርት ክብርና እነሱ ለትምህርት የሚሰጡት ቦታ ፍጹም የተለያየ ነበር፤ የሚሉት ዶክተር ትዕግስት በዛ ላይ ውድድር ነበር፤ በሌላ በኩል ደግሞ 1 ሺ 500 ተማሪ መካከል ወደ ሕክምና የሚገባው 150 ተማሪ ብቻ ነው:: የቀረው ጥርስ ህክምና እንዲያጠና ነበር የሚሆነው:: ዶክተር ትዕግስት ደግም የጥርስ ሕክምናን አልፈለጉትም::
የእናታቸውም ሆነ የእሳቸው ህልም ሀኪም መሆን ነበር ግን ትምህርት ቤቱ ደግሞ ጥርስ ህክምና ካልገባሽ ነጻ የትምህርት እድል (ስኮላርሽፕ) ይቋረጣል አላቸው:: በዚህ መካከል ግን የጥርስ ሕክምናውን ለሶስት ወራት ከተማሩ በኋላ ስላልተስማማቸው ማቋረጥን መረጡ::
በዚህ ምክንያት ነጻ የትምህርት እድላቸውን አጡ:: በጣም ችግር ውስጥ ገቡ:: ብዙ ከባድ ጊዜያትንም ስለማሳለፋቸው ይናገራሉ:: ከብዙ የችግር ወራት በኋላም ስራ አገኙ:: ምንም እንኳን ዶክተር ትዕግስት ከውልደታቸው ጀምሮ የቤት ሥራ በተለይም ደግሞ ቤት መወልወልን ሞክረውት ባያውቁም ሕይወታቸውን በፈረንሳይ አገር ለማቆየት ያገኙት ብቸኛው አማራጭ ቤት ወልዋይ ሆኖ መስራትን ነበር:: ሆኖም ይህ ስራ ለእርሳቸው የሚሆን አልሆነም፤ ከባድ ሆነባቸው::
ጥቂት ወራት እንደሰሩም መልቀቂያ ለማስገባት በሄዱበት ጊዜ አይ ወደማታ ፈረቃ ቀይረንሻል የሚል የምስራች ሰሙ:: ማታ የቀኑ አይነት ከባድ ሥራ ባለመኖሩም ደስተኛ ሆኑ::
ነገር ግን ዶክተር ትዕግስት አንዱ በር ሲዘጋ ሌላውን የሚያንኳኩ ጠንካራ ሴት ስለነበሩ መጀመሪያ ትምህርታቸውን ሲያቋርጡ ዓለም ላይ ላሉ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሙሉ ደብዳቤ ልከው ነበርና ከካናዳና ከሴኔጋል መልስ መጣላቸው:: አሁንም ቢሆን ግን ነገሩ ሁሉ አልጋ በአልጋ አልሆነም፤ በተለይም ካናዳ ሄዶ ለመማር 25 ሺ ዶላር ተቀማጭ አስፈለጋቸው::
እሱ እንደማይሆን አወቁ፤ ሴኔጋል መመዝገቢያ ካለሽ መጥተሽ መቀጠል ትችያለሽ መባላቸው ቢያስደስታቸውም ወደማያውቁት አገር መሄድ ደግሞ ሌላው ከባድ ነገር ነበር:: ይሁንና በቆራጥነት ወደ ሴኔጋል ዳካር ሄደው በአገራቸው የለመዱትን አይነት ትምህርት ጀመሩ:: ትምህርት ላይ ሆነውም ከፈረንሳይ አገር አጠራቅመው ይዘውት የመጡት ገንዘብ በማለቁ ትምህርታቸውን እየሰሩ ለመማር ሞከሩ፤ በዚህ መካከል ደግም ሴኔጋል አገር የተዋወቋቸው ደጋግ ሴኔጋላውያን የተለያዩ ሥራዎችን ይፈልጉላቸው፣ ያሰሯቸውም ጀመረ::
ነገር ግን ዛሬ ለደረሱበት ደረጃ ብሎም ህልማቸውን ለማሳካት ያስቻላቸው የሴኔጋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሰጧቸው የትምህርት እድል ነው:: “የሴኔጋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ይናገሩ የነበሩት ፈረንሳይኛ ብቻ ነበር::
እኔ ደግሞ ፈረንሳይኛውን ወደ እንግሊዝኛ እየተረጎምኩ ከሌሎች እንግዶች ጋር እንዲግባቡ የማድረግ ስራ ስሰራ ባልጠበኩት አጋጣሚና ሁኔታ ሰውየው ወደ እኔ ቀርበው ስላለሁበት ሁኔታ ከየት እንደመጣሁ ጠየቁኝ፤ እኔም ኢትዮጵያዊ መሆኔን፤ ለትምህርት ሴኔጋል እንደሄድኩና ነጻ የትምህርት እድል ስለሌለኝ እየሰራሁ ለመማር መገደዴን ነገርኳቸው፤ ወዲያው የነጻ ትምህርት እድል እንዲሰጠኝ ጻፉልኝ:: በዛም ትምህርቴን ተምሬ በማጠናቀቅ ዛሬ ያለሁበት ደረጃ ላይ ደረስኩ” በማለት ሁኔታውን ያስታውሳሉ::
የሥራ ዓለም ጅማሮ
ዶክተር ትዕግስት ከጅምሩም በትምህርታቸው ትጉ የነበሩ በመሆኑ በሰው አገርም ሴትነትን ጥቁር መሆንን ተቋቁሞ ውጤታማ መሆን ለእሳቸው ብዙ ከባድ አልነበረም::
በዚህም ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ በሕከምናው ዘርፍ በመሰማራት ሀኪም ሆነው በተለያዩ የአፍሪካ አገራት በመዘዋወር ነው የሥራን ዓለም አንድ ብለው የተቀላቀሉት:: ኋላም የሥራ ትጋታቸው ለማወቅና በየጊዜው እራሳቸውን ከመለወጥ ያላቸው ተነሳሽነት ተደማምሮ ከፍ ወዳለ የሥራ መስክ ለማምራት ዓመታትን መጠበቅ አልጠየቃቸውም::
ወደ ዓለም ጤና ድርጅት በመቀላቀል ከፍ ያለውን የሥራቸውን ደረጃ ጀመሩት፤ በዚህ ድርጅት ውስጥ 21 ዓመታትን ከትንሽ የሥራ ደረጃ ጀምሮ እስከ ዳይሬክተር ደረጃ ባሉ ሃላፊነቶች ሴትነታቸውም ሆነ ጥቁርነታቸው ሳያንበረክካቸው መስራታቸውን ይናገራሉ:: ከዛም በመቀጠል በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ጤና ቢሮ ተጠሪ በመሆን የመጀመሪያዋ ሴት እንዲሁም ጥቁር በመሆን ሰርተዋል:: በእነዚህ የሥራ ጊዜያት ደግሞ በተለይም ሴትነታቸው ብዙ ውጣ ውረዶችንም እንዲያልፉ እንዳስገደዳቸውም ይናገራሉ::
እኔ ባለሁበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ብዙ ፈተናዎች አሉ የሚሉት ዶክተር ትዕግስት እነዚህን ነገሮች ለማለፍ ግን የራስ ጥንካሬ ብሎም ከመጀመሪያ ጀምሮ በቤተሰብ ውስጥ ያለ አስተዳደግ ወሳኝ መሆኑን ያብራራሉ::
“እኔ ለቤተሰቤ የመጀመሪያ ልጅ ነኝ ፤ እናቴ ከፍተኛ የሆነ የሕክምና ፍቅር የነበራት ከመሆኑም በላይ ነርስ የመሆን ህልም ነበራት፤ ነገር ግን 10 ክፍል ስትደረስ አባቷ ስለዳሯት ህልሟን መኖር አልቻለችም:: እሷ ያጣችውን የህክምና ትምህርት በእኛ ሴት ልጆቿ ለማግኘት ትፈልግ ስለነበር ሁሌም ስለ ህክምናና ዶክተር ነበር የሚወራልን ፤ አባታችንም ይህንን በእጅጉ ይደገፍ ስለነበር በትምህርታችን ላይ ከፍተኛ ትኩረት እናደረግ ነበር:: በቤተሰቡ ውስጥ ካለን አራት ሴት ልጆች ሶስታችን ዶክተር ነው የሆነው “ ይላሉ::
በቤት ውስጥ ለወንድና ለሴት መጠነኛም ቢሆን ልዩነት ነበር የሚሉት ዶክተር ትዕግስት ያም ቢሆን ግን እኛ ሴቶቹ እንድንጠክር አደርጎናል ብለዋል:: ዛሬ ላይም በዚህ አስተሳሰብ ውስጥ ያሉ ካሉ ፍጹም የተሳሳተ መሆኑን ሊገነዘቡ ብሎም ሴትም ወንድም እኩል ከታዩ አስፈላጊው ነገር ከተሟላላቸው ያሰቡበት ሊደርሱ እንደሚችሉ መገንዘብ ያስፈልጋል ባይ ናቸው:: እኔ ሥራዬን ለብዙ ዓመታት የሰራሁት በተባበሩም መንግሥታት የዓለም ጤና ድርጅት ውስጥ ቢሆንም እዛም ብዙ እኩልነት የለም::
ሴት ሆነሽ በልጠሽ ከተገኘሽ ጫናው ብዙ ነው:: በመሆኑም ከመጀመሪያ ሥራዬ ጀምሮ ብዙ ትግል አድርጌያለሁ:: ለምሳሌ መጀመሪያ ሥራ ስጀምር የአንድ ሕክምና ተቋም የተላላፊ በሽታዎች ሕክምና ክፍል ሃላፊ ነበርኩ:: የሆስፒታሉ ዳይሬክተር ደግሞ ወንድ ነው::
ነገር ግን ይህ ሰው በራሱ የሚተማመን አይደለም:: በመሆኑም እኔን ወደታች ሊያደርገኝ በጣም ብዙ ጥረት አድርጓል:: ግን እኔም በቀላሉ የምሰበር ባለመሆኔ ብዙ ታግዬ አሸንፌዋለሁ:: በመሆኑም ሴት ከሆንሽ አርፈሽ ስራሽን መስራት ብቻ ሳይሆን ብዙ ትግልም ይጠበቅብሻል::
ሴትነታችን ከምንም ሊገድበን አይገባም:: ሴቶች በራሳችን ትልቅ ህልም ሊኖረን ይገባል:: ያንን ህልም ደግሞ ለመኖር ብዙ መስራት በሕይወት ውስጥ ከባድ ውሳኔዎችን መወሰን ያስፈልጋል:: እኔ በሕይወቴ ብዙ ከባድ ሃላፊነቶችን ወስጃለሁ::
ሌላው ለሴቶች ወሳኝ የሆነው ነገር በራስ መተማመን ነው:: ይህ ግን ምናልባትም በቀላሉ የሚሆን አይደለም፤ በተለይም ኢትዮጵያውያን አስተዳደጋችንም ለዚህ የተመቸ አይደለም::
በነገራችን ላይ እኔ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰዎች ፊት ቆመሽ ንግግር አድርጊ ስባል የተሰማኝን ፍርሃት እስከ አሁን አልረሳውም:: በሂደት ግን ራሴን እያስተማርኩ በራሴ መቆም እንደምችል እያወኩ ስመጣ ሁሉም ነገር ለቆኛል:: ይህንን ካላደረግን ግን አስተዳደጋችን በተለይም ለሴቶች በጣም ዝግ ነው:: በመሆኑም ሴቶች ያለንን አቅም አውጥተን ካላሳየን ስለራሳችን አፋችንን ሞልተን መናገር ካልቻልን ማንም አያስታውሰንም::
ለደግ ሚድዋይፍ ኮሌጅ
ዶክተር ትዕግስት ያላቸውን የሥራ ልምድ እንዲሁም በሥራ ዘመን ያፈሩትን ሀብት ቋጥረው ከ 42 ዓመት የውጭ አገር የትምህርትና የስራ ቆይታ በኋላ ወደአገራቸው ነው የገቡት:: ወደ አገራቸው የገቡት ደግሞ ዝም ብለው ለማረፍ ሳይሆን ለአገራቸው በተለይም በትምህርት ዘርፉ ሴቶችን ከፍ ወዳለ ደረጃ ሊያሻግር የሚችል አንድ ነገር ለማበርከት ነው::
በዚህም የሴት እህቶቻችንን በተለይም ለአቅመ ሄዋን ከደረሱ ጀምሮ በወሊድ እንዲሁም ከወሊድ በኋላ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለመጋራት የአቅማቸውን አበርክተውም ችግሩን በተወሰነ መልኩም ቢሆን ለመፍታት በማሰብ የሚድዋይፈሪ ኮሌጅ ማቋቋምን ምርጫቸው አደረጉ:: በዚህም ራሳቸውን ሴቶቹን በማስተማር ለውጥ ለማምጣት እየጣሩም ይገኛሉ:: ዶክተር ትዕግስት ስለ ለደግ ሚድዋይፈሪ ኮሌጅ ይህንን ይላሉ “ለደግ ሚድዋይፈሪ ኮሌጅ ከክልል የሚመጡና ከፍለው መማር የማይችሉ ሴቶችን በሚድዋይፈሪ የትምህርት መስክ የሚያስተምር ነው:: ሴቶቹ ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ ተመልሰው ወደመጡበት አካባቢ በመሄድ እህቶቻቸው በወሊድ እንዳይሞቱ እያደረጉ ነው::
ወደፊትም የልህቀት ማዕከል እንዲሆን እንፈልጋለን”:: አሁን ኮሌጁ ውስጥ ከአፋር፣ ከሱማሌ፣ ከጋምቤላ፣ ከቤኒሻንጉል እንዲሁም ከሌሎች ክልሎች ወጣት ሴቶች እየመጡ እውቀት እያገኙ በገጠር ያሉ እህቶቻቸው የሕይወት መድህን እየሆኑ ነው:: በዚህ ኮሌጅ ለመማር የሚያስፈልገው 12ኛ ክፍልን ማጠናቀቅ እንዲሁም የትምህርት ሚኒስቴር ያስቀመጠውን የኮሌጅ መግቢያ ነጥብ መሟላት የመክፈል አቅም የሌላቸው መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ ብቻ ነው::
በነገራችን ላይ የመክፈል አቅም ያላቸውም ቢሆኑ ተመጣጣኝ የሆነ ክፍያን እየከፈሉ ትምህርታቸውን በመማር ላይ ሲሆኑ በአሁኑ ወቅትም ከአንድ መቶ በላይ ተማሪዎች በኮሌጁ ይገኛሉ::
ኮሌጁ ይላሉ ዶክተር ትዕግስት እስከ ዛሬ ይተዳደር የነበረው እኔ ለዓመታት ለፍቼ ባመጣሁት ገንዘብ እንዲሁም ከውጭ በምናገኘው እርዳታ ነበር:: አሁን ላይ ግን የእኔም ገንዘብ አልቋል፣ እርዳታውም ሁሌ የሰው ፊት የሚያሳይ በመሆኑ ኮሌጁን በአግባቡ ሊረዳ የሚችል እንዲሁም ተማሪዎች የሥራ ላይ ልምምድ ሊያደርጉበት የሚችሉበት ደረጃውን የጠበቀ የእናቶችና የሕጻናት የህክምና ማዕከል በኮሌጁ እንዲኖር ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች በመሰራት ላይ ስለመሆናቸው ይናገራሉ::
በኮሌጁ የሚማሩት ሴቶች
“በኮሌጁ ትምህርታቸውን ለመከታተል ከተለያዩ ክልሎች የሚመጡ ሴቶች መጀመሪያ ሲመጡና ኋላ ትምህርታቸውን አጠናቀው ሲሄዱ የሚኖራቸውን ነገር ሳይ በጣም እደነቃለሁ::
አስገራሚ ለውጥም ነው የሚታይባቸው፤ በጣም የሚገርመው ነገር እዚህ በቆዩባቸው ዓመታት የሚያዳብሩት በራስ መተማመን ከፍተኛ ነው ፣ ይህ ደግሞ ለዘላቂው የሕይወት ጉዟቸው ወሳኝ ስለሚሆን በበኩሌ ህልሜ እንደተሳካ ነው የምቆጥረውም” ይላሉ ዶክተር ትዕግስት::
የቤተሰብ ሁኔታ
ዶክተር ትዕግሰት ከስኬታማው የሕይወት ጎናቸው አንዱ የቤተሰባቸው ገጽ ነው:: ምንም እንኳን ባለቤታቸው በቶሎ ከዚህ ዓለም በሞት ቢለዩአቸውም በጋብቻ የወለዷቸውን ሁለት ሴት ልጆች ግን ከስኬታማው የስራ ጉዟቸው ጎን ለጎን በጥሩ ሁኔታ በማሳደግ ለቁምነገር አብቅተው ዛሬ ላይ ሶስት የልጅ ልጆችን ለማየት በቅተዋል:: “ልጆቼ ዛሬ ላይ ሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው የተማሩ የራሳቸውን ስራ የሚሰሩ አልፈውም እኔን በተለያዩ መንገዶች የሚደግፉኝ ናቸው::
ነገር ግን ልጆቼን ለብቻዬ ሳሳድግ ያለፍኩት ውጣ ውረድ ቀላል አልነበረም:: ይህንን ለማለፍ በጣም ጠንካራ ነበርኩ” ይላሉ:: ሴቶች ምንም እንኳን በሥራው ዓለም ትልቅ ሃላፊነት ላይ ቢደርሱም ልጅ ወልዶ የማሳደጉ ከባዱ ሃላፊነት ያለው እነሱ ላይ ነው:: ይህንን ሁኔታ ለማለፍ ግን ከፍተኛ የሆነ ጥንካሬ ያስፈልጋል የሚሉት ዶክተር ትዕግስት ልጆች እናት ይፈልጋሉ እናት ደግሞ ከልጆቿ ጎን ለጎን በስራዋ ውጤታማ መሆን አለባት::
ለዚህ ደግሞ የቤቱንም የውጭውንም ሥራ ፕሮግራም አደርጎ መሄድ የግድ መሆኑን ከራሳቸው ልምድ ተነስተው ይመክራሉ:: “አንዳንድ ጊዜ ሥራም ልጆችም ሲደራረብብኝ በጣም እበሳጭ ነበር:: ምክንያቱም ሥራ ላይ ብዙ ፈተና አለ፣ እንኳን ደከም ብለሽ ጠንክረሽም ብዙ ፈተና አለ፤ በመሆኑም ሴቶች ሥራና ቤታቸውን ለይተው በመንቀሳቀስ ከዛም ጠንካራ በመሆን በሥራቸውም በቤተሰባቸውም ውጤታማ መሆን ይችላሉ፤ ነገር ግን ሥራ ብለው ቤቱን ከተውት ወይም ቤት ብለው ሥራቸውን ችላ ካሉት ውጤቱ ጥሩ አይሆንም” ይላሉ::
ተስፋ አለመቁረጥ- የስኬት ሚስጢር
ዶክተር ትዕግስት እንደሚሉት ተስፋ አለመቁረጥ የስኬት ቁልፍ ሚስጢር ነው:: በጭራሽ ተስፋ አልቆርጥም፤ እንኳን እኔ የትኛዋም ሴት ብትሆን ተስፋ መቁረጥ የለባትም:: ወድቆ መነሳት መሸነፍ ማሸነፍ ያለ ነው:: ሁሌም ቢሆን ነገ ጥሩ ቀን ይመጣል ማለትን መልመድ እጅግ አስፈላጊ ነው::
እውነት ለመናገር ለሴቶች ተስፋ አለመቁረጥ ትልቅ የስኬታማነታቸው ሚስጢር መሆኑን መረዳት አለባቸው:: ከላይም ብዬዋለሁ፤ ምን ጊዜም ሴቶች ሥራና ቤታቸውን መለየት አለባቸው:: እኔ መለያየት ሳልችል ብዙ ተቸግሬ ነበር፤ ኋላ ላይ ግን ቤቴንና ስራዬን ስለይ ያገኘሁት ለውጥ እንዲህ በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም ይላሉ:: “ሥራ ላይ ብዙ ብስጭት አለ ፤ ፈተና ይደራረባል፤ ነገር ግን ቤቴ ስገባ ሁሉንም እርግፍ አድርጌ በመተው የቤቴና የልጆቼ እሆናለሁ::
ሃሳቤንም ትኩረቴንም ልጆቼና ቤቴ ላይ አደርጋለሁ:: በእርግጥ ይህንን ማድረግ ቀላል አልነበረም:: መለማመዱ ግን በጣም መሰረታዊ ነገር ነው”::
በአማርኛ መጽሐፍ ስለመጻፍ?
ዶክተር ትዕግስት “ትሙት ግዴለም” በሚል ርዕስ የራሳቸው ታሪክ ላይ የተመረኮዘ መጽሐፍ አዘጋጅተው ለህትመት አብቅተዋል:: ዶክተር ትዕግስት እንደሚሉት መጽሐፍ መጻፍ እንግዲህ ከባድ ሊሆን ይችላል ነገር ግን እኔ ለአገሬም ሆነ ለአገሬ ቋንቋ ትልቅ ክብር አለኝ:: የራሷ የሆነ ፊደል ያላት ብቸኛ አፍሪካዊ አገር ኢትዮጵያ ብቻ ናት::
ይህንንም ደረቴን ነፍቼ የማወራና የምኮራ ነኝ:: በመሆኑም በሥራም በትምህርትም በቆየሁባቸው አገራት ላይ ኢትዮጵያዊ ሳገኝ የማወራው በራሴ ቋንቋ ነው:: ኢትዮጵያዊ በሌሉባቸው አገራት እንኳን ስሄድ ቤተሰቤ ጋር ደውዬ አማርኛ አወራለሁ፤ ልጆቼንም አማርኛ አስተምሬያለሁ፤ በደንብ ይናገራሉ:: እነሱም ልጆቻቸውን እያስተማሩ ነው:: ቋንቋ ማንነት ነው የሚሉት ዶክተር ትዕግስት ቋንቋዬን ረስቼ እንግሊዝኛና ፈረንሳይኛ ብማር ራሴን እንደረሳሁ ነው የምቆጥረው ምክንያቱም መቼም እንግሊዛዊ ወይም ፈረንሳዊ መሆን አልችልም ::
መጽሐፉንም መጻፍ እችላለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር:: ነገር ግን ጀመርኩት፤ ጨርሼም ለኤዲተሮች ስሰጣቸው ብዙ ችግር አላገኙበትም፤ ይህም አበረታቶኛል:: በቀጣይም ሁለተኛ መጽሐፍም እያሰብኩ ነው::
ለሴቶች መልዕክት
ወጣቶች ሥራ ተሰርቶ እንደሚገኝ ሕይወት ቀላል እንዳልሆነ ዛሬ ተምሮ ነገ ሀብታም ወይም ታዋቂ ሰው መሆን እንደማይቻል ሁሉም ነገር ከብዙ ሥራ ልፋትና ትጋት በኋላ የሚገኝ መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል:: ሴቶች ደግሞ ከወንዶች የበለጠ ሁለቴ ሶስቴ ከዛም በላይ ጠንክረው መስራት መቻል እንዳለባቸው ማወቅ ያስፈልጋል:: እኔ እዚህ ለመድረሴ ብዙ ልፋት ስራ ትምህርት እንዲሁም ከወንዶች የሚደረስብኝን ጫና መቋቋም ነበረብኝ እሱን አድርጌ ነው እዚህ የደረስኩት::
ይህንን ማወቅ ያስፈልጋል:: ሴቶችም ወንዶችም የሕይወት መሪያቸው (ሞዴላቸው) እንዲሆን የሚያስቡት ሰው ሰርቶ ለፍቶ የተለወጠን እንጂ ሰርቆ ወይም አጭበርብሮ እላይ ወጥቶ የተኮፈሰን ሰው ሊሆን አይገባም:: ሴቶች ህልም አልሙ ህልማችሁ ላይ ለመድረስ ሌት ተቀን ልፉ እንዲሁም ከባባድ የሕይወት ውሳኔዎችን በራሳችሁ ወስናችሁ ማለፍን ተለማመዱ::
ይህ ከሆነ መቼም ቢሆን እናንተ ላይ የሚደርስ አይኖርም:: የእናንተ ከፍ ማለት ደግሞ በቤተሰባችሁ በልጆቻችሁ ላይ ይታያልና እህቶቼ ይህንን ስንቅ አድርጉ ብለዋል:: “ሕይወት ትግል ነው:: እኔ እዚህ ለመድረሴ ብዙ ትግሎችን አልፌያለሁ፤ በፍጹም ተስፋ ቆርጬም አላውቅም:: እህቶቼም የእኔ ተሞክሮ ከጠቀማችሁ በዚህ መልኩ መሄድ አለባችሁ”::
ዕፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን የካቲት 29 /2014