መቸም ከ”ነገር በምሳሌ ጠጅ …” ጀምሮና ጨምሮ ሀሳብን በፈሊጥ (ዛሬ በፍልጥም አልሆነ የሚሉ አሉ) መግለጽ እንደ አበሻ የተሳካለትና የተካነበት ያለ አይመስልም። ለዚህ ደግሞ መረጃና ማስረጃው የትየለሌ ሲሆን አንዱም “የጉሎ ዘይት …” ነው።
እርግጥ ነው በንባብም ይሁን በንግግር አልፎ አልፎ ብቅ ሲል ይታያል እንጂ “የጉሎ ዘይት …” በቃላት ገበያ ላይ ዘወትር የሚከሰት፤ በሽ በሽ የሆነ ፈሊጥ (“ምሳሌያዊ አነጋገር” ማለትም ይቻላል) አይደለም።
ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ እሱ የሚገለጥበት ድርጊት እራሱ ተዝውታሪ አለመሆኑ ነው። ለምሳሌ “የጉሎ ዘይት አጠጣው/ አጠጡት” ሲባል የሰማንበት ጊዜ አለ፣ ካለስ ምን ያህል ጊዜ? ብለን ለማጣራት ብንሞክር የምናገኘው ውጤት መኖሩን ከመናገር ያለፈ በቁጥርም ሆነ በመረጃና ማስረጃ የሚነግረን አናገኝም።
ለምን? ሥራው እራሱ ለአድራጊውም ለተደራጊውም ምቾትም ሆነ ሰላምን ስለማይሰጥ ነው። መግቢያችን እንደ ርእሳችን ግልፅ ነው። በመሆኑም የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል እንዲሉ የዘይት ነገርም የባሰ ነውና ከምግብ ማጣፈጫነት ወደ ከንፈር ማውዣነት ከመሸጋገሩ በፊት አንዳንድ ሀሳብ መለዋወጥ ያስፈልጋልና ወደ’ዛው እናዝግም።
እንደ አለመታደል ሆኖ ያለንበት ዘመን የተወደደውን ከመናገር ያልተወደደውን (ካለ) መናገሩ የቀለለበት ነው። አሁንም እንደ አለመታደል ሆኖ የጨመረውን ከመናገር ያልጨመረውን (አሁንም ካለ ነው) መዘርዘሩ የሚመረጥበት ክፉ ዘመን ነው። ሻጭና ገዥ እጅና ጓንት ሆነው እንዳልነበሩ ሁሉ፤ ደንበኝነት በ”ደንበኛ ንጉስ ነው” እንዳልተገለፀ ሁሉ፤ መግዛትም ሆነ መሸጥ መሰረቱ እምነትና ማተብ እንዳልነበሩ ሁሉ . . . ዛሬ በተቃራኒው እየሆነ የሚታይበት ዘመን ነው ይህ ዘመን።
የዚህ ጽሑፍ አንባቢ በዘይት አልባ ሆዱ “ምን አይነት ዘመን ነው ዘመነ ቁርንጮ ….” እያለ ቢያንጎራጉር፤ በ”ነበር” ቢቆዝም፤ ወይም “በእያሱ ዳቦ ነው ትራሱ”ን ቢያስታውስ በምንም መንገድ ሊወቀስም ሆነ ሊከሰስ አይችልምና ቢያደርገው ያስኬደዋል።
በ”አምስት ሊትር ዘይት 1000 ብር”ም ቢማረር እንደዛው።ኧረ ከዚህም ከፍ እንዳይል በሉኝ። ዘንድሮ “ምን ምን ተወደደ?” ሲባል መልሱ “ምን ያልተወደደ ነገር አለ” ከሆነ ሰንብቷል። “ምን ምን ጨመረ?” ሲባል “ምን ያልጨመረ አለ” ከሆነ ጊዜው ዛሬ ሳይሆን ቆየ። ልዩነቱ የአሁኑ ባለ ዘይቶች ደንበኞቻቸውን የጉሎ ዘይት ማጠጣት መሻታቸው (ወይም፣ እያጠጡት መሆናቸው ነው።
አምስት ሊትር ዘይት 1000 ብር። እነ ደረጀና ሀብቴ “ሙያሽ ሙያሽ ይነገርልሽ …. ይዝርዘርልሽ” በማለት በኮመዲኛ እንዳዜሙት እኛም እንጋራቸውና የነጋዴዎቻችን ደንበኞቻቸውን የጉሉ ዘይት የማጠጣትና የማሳጣት ተግባር ሊዘረዘርላቸው ይገባልና “ሙያችሁ ይዘርዘርላችሁ” እያልን እንዘረዝርላቸዋለን። በ”አምስት ሊትር ዘይት 1000 ብር” ማሳያነት። ባለሙያዎች እንደሚሉት የሰሞኑ የዘይት ዋጋ ጭማሪ በምንም አይነት መስፈርት ልክ ሊሆን የሚችል፣ በምንም አይነት ቋንቋ የሚገለፅ፣ በየትኛውም የነፃ ገበያ መርህ ሊበየን የሚችል አይደለም። ባጭሩ የሚስተዋለው ነገር “እኔ ከሞትኩ …..” እንጂ ሌላ አይደለም።
አምስት ሊትር ዘይት 1000 ብር ! ዘይት እየበላን ሳይሆን እየተያየን መተላለፍ ሆኗል። በ”ነፃ ገበያ” ስም ገበያው አቅሉን ከሳተ ቆይቷል። ነፃነት ስድነት እስኪመስል ድረስ ገበያውን ያሳበደው የነፃ ገበያ አሰራር ለነጋዴው ክብረትን ለሸማቹ ድህነትን እያወረሰ፤ ነጋዴውን ያለ ላቡ እያደለበ፣ ሸማቹን ላብና ደሙን እየመጠጠ ሲጓዝ እዚህ ስለ መድረሱ ምስክሮቹ ጥቂቶች ሳይሆኑ ሁላችንም ነን።
አሁን ደግሞ “አምስት ሊትር ዘይት 1000 ብር” የሚለው በራሱ መረጃም ማስረጃም ነውና ሃሳባችንን መሬት ያወርድልናል። የትም አገር ነጋዴ መንግሥትን ይገዳደራል። የመንግሥትን እጅ ለመጠምዘዝ ይሞክራል። የሚችለውን ሁሉ ለማድረግ ይጥራል። በአንድ ወቅት በአሜሪካም ሆኖ የነበረው ይሄው ነው። ነጋዴው በስውር የጦር ሰራዊት ሁሉ እስከ ማቋቋም፣ የመገናኛ መስመር እስከ መዘርጋት … ሁሉ ድረስ ተጉዞ ነበር።
ነገር ግን በማያዳግም ህግና ህጋዊ እርምጃ ወደ መስመር ሊገባ ችሏል። መንግሥትን የጉሎ ዘይት ከማጠጣቱ በፊት መንግሥት ቀድሞ ነጋዴውን ጋተውና ሊያስተው የነበረውን አሳተው።
በሌሎችም እንደዚሁ። ለምንና ለምን “ጥርስ አያሳዩም” የሚባል ነገር አለ፤ አዎ ! ተገቢ ባልሆነ መንገድ ጥርስ ካሳዩአቸው “ቀጥሉ” የተባሉ ያህል ነውና ተግባሩን የሚገፉበት ለእነዚህ ወገኖች ጥርስ ማሳየት (ፊት መስጠት) ተገቢ አይሆንም። ለነጋዴውም እንዲሁ ነው።
የትም አገር ነጋዴ አንድ ሲሰጡት አስር አልፎ ለመሄድ መሞከሩ የማይቀር ነው። በመሆኑም በፓርላማም ሆነ በሌላም መድረክ የሚሰጡ ንግድና ነጋዴውን የተመለከቱ አስተያየቶች አስፈላጊው ጥንቃቄ ሊደረግባቸው ይገባል። ይህ ካልሆነ ነጋዴው ምስኪኑን ሸማች የጉሎ ዘይት በማጠጣት ከማሳት አይመለስም።
“አምስት ሊትር ዘይት 1000 ብር” የዚሁ አካል ካልሆነ ማለት ነው። ይህ በአንዳንድ አገራት ባሉ ነጋዴዎች የሚደረግ ሙከራ ቢሆንም (ማጭበርበር ማለታችን ነው)፣ በእንደኛ አይነቷ፣ አንድ የንግድ ዘርፍ በአንድ ሰውና እጁ ላይ ባለች አንዲት ሞባይል ስልክ በሚመራበት አገር፣ አምስት ሊትር ዘይት 1000 ብር ቢገባ ምኑ ይገርማል የሚሉ ወገኖች መኖራቸው የሚታወቅ ሲሆን፤ ይህን ይሉ ዘንድ ያስገደዳቸው ግን በህግ ተስፋ የመቁረጥ ሁኔታ ስለመሆኑ ራሱ የሃሳባቸው ድምፀቱ ይናገራልና የጉሎ ዘይት ሲግቱን ከመጋት፤ ተግቶም ከመሳት ውጪ ምን እድል አለን ማለታቸው ሁሉ ይመስላል።
ገና የዘይት ፋብሪካዎች ተመረቁ፤ ወደ ሥራም ገቡ በተባለ በዓመቱ “አምስት ሊትር 1000 ብር ገባ”ን መስማት በራሱ እንቆቅልሽ ቢሆንም (ትያትር ቢሆን ኖሮ “አብዘርድ” እንለው ነበር)፤ ትናንት ከወደ ባህር ዳር የተሰማው “በነገው ዕለት የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር በሁሉም ክፍለ ከተሞች ላይ እንዲሁም በጎንደር ከተማ መንግሥት በተመጣጣኝ ዋጋ የምግብ ዘይት እንደሚያከፋፍል ታውቋል።” የሚል የማረጋጊያ ዜና ዘላቂ መፍትሄ ይሁን/አይሁን ለባለሙያዎች እንተውና እንደ አንድ ሸማች ሆነን ስንመዝነው እየሆነው ያለው ሁሉ የእብደት እንጂ የጤና አይመስልም – አምስት ሊትር ዘይት 500 ብር ይሁን ብንል በእጥፍ ጫኑን ።
ንግድ ይሉኝታ አለው፤ ንግድ ኃላፊነት የሚሰማው የሙያ ዘርፍ ነው። ንግድ እንደ ማንኛውም የስራ ዘርፍ ሙያ ነው። በመሆኑም መርህ አለው። ደንብና አሰራር አለው። “አምስት ሊትር ዘይት በአንዴ ጭማሪ 300 ብር” ሲባል እንግዲህ እነዚህ ሁሉ ናቸው ገደል እየገቡ ያሉት ማለት ነውና ያሳዝናል።
እዚህ ላይ ችግሩን በአብዛኛው በነጋዴው ላይ ለማላከክ የተደፈረበት አቢይ ምክንያት ሌላ ሳይሆን ከሁለትና ሶስት ቀናት በፊት በሁለት ሰዓታት ውስጥ ከ700 ብር ወደ 1000 ብር መግባቱን በመታዘብ ነው።
መንግሥት ግልበጣ እስኪመስል ድረስ በዚህ ቅፅበት ይሄንን ያህል ዋጋ መጨመር የጤና ሳይሆን ሸማቹን የጉሎ ዘይት በማጠጣት ለማሳት እየተደረገ ያለ ጥረት ነውና እዚሁ ላይ ሊቀጭ፤ ሸማቹም ተጨማሪ የጉሎ ዘይት እንዳይጋት ሊደረግ ይገባል።
ካልሆነ ዘይት አይደለም ለምግብነት ወደ’ፊት ለከንፈርማውዣ ‹‹ቻፒስቲክነት›› እንኳን የማይገኝ፤ የቅንጡዎችና የቱጃሮች ቀለብ ብቻ ወደ መሆኑ ያቀናልና ጊዜ የለም። ነጋዴውም “አምስት ሊትር ዘይት 1000 ብር !” የሚለውን መፈክር ሊጥል ይገባዋል። መንግሥትም ሊያስጥለው የግድ ይለዋል። ካልሆነ ግን …..።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን የካቲት 29 /2014