የኢትየጵያን ዋና ከተማ የሆነችው አዲስ አበባ እጅ እና እግሯን ጠርንፈው ከተበተቧት ችግሮች መካከል ዋነኛው የመኖሪያ ቤት አቅርቦት እጥረት ነው። በየዕለቱ እየጨመረ ያለው የቤት ፍላጎት ከአዝጋሚው አቅርቦት ጋር ሲወዳደር ልዩነቱ በፍፁም ሊቀራረብ የሚችል አይመስልም።
በዚህ ሳቢያ የከተማው ነዋሪ በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያለው እና የመንግሥት ሠራተኛው በከፍተኛ ችግር ውስጥ ይገኛል። ተገንብተው ተጠናቀዋል የሚባሉት የጋራ መኖሪያ ቤቶችም ቢሆኑ የጥራት ችግር እንዳለባቸው ተደጋግሞ ይገለፃል። ለዚህ በመንስኤነት የሚቀርቡት በዘርፉ ላይ ያለው የሥነምግባር ጉድለት፤ የሥራ ዕድል ፈጠራ በሚል ሰበብ ጥራትን ግምት ውስጥ አለማስገባትና የአቅም ችግር ተጠቃሾች ናቸው። እነዚህ ችግሮች ለምን ኖሩ፤ ከመኖራቸው አልፈው እንዴት ሥር ሠደዱ በማለት በአዲስ አበባ አስተዳደር ቤቶች ልማት ቢሮ የቤት ልማት ትግበራ እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ክትትል ዳይሬክተር ኢንጂነር ኪያ በሬቻን አነጋግረን እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።
አዲስ ዘመን፡- የቤት ግንባታ ዋነኛው ዓላማው ምንድን ነው?
ኢንጂነር ኪያ፡- ዋነኛ ዓላማው ቤት ፈላጊዎችን የቤት ባለቤት ማድረግ ነው። በዚህ ውስጥ ቤቶችን ማስተዳደር የሚያስፈልጉ ጉዳዮች ካሉም ማስተዳደርም ይካተትበታል።
አዲስ ዘመን፡- የቤት ግንባታ እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ግንኙነታቸው እንዴት ይገለጻል?
ኢንጂነር ኪያ፡- የቤት ግንባታ ላይ ከሚንቀሳቀሰው ሃብት እና ከሚሳተፈው ሰው አንፃር በርካታ የሥራ ዕድል ይፈጥራል። ቤት ልማት ሲባል ግንባታ ነው። ብዙ ተጓዳኝ ሥራዎችም አሉበት። የጫኝ አውራጅ ሥራ፤ የጥበቃ ሥራ ሌላው ቀርቶ ሠራተኞችን የማቅረብ ሥራ እና ሌሎችም ሥራዎች በብዙ ዘርፍ መታየት የሚችሉ የሥራ ዕድሎች ያሉበት ዘርፍ ነው። አንድ ሕንፃን በተለያየ ዘርፍ ከፋፍለን ስንመለከተው ከግንባታው እስከ መጨረሻው ተጠናቆ ቁልፍ እስከ ማስረከብ ድረስ ያለው ሒደት በርካታ ዘርፎችን የሚነካካ እና በዛ ዘርፍ ደግሞ ሰዎችን አደራጅቶ እና ዕድል ሰጥቶ ሥራ መሥጠት የሚችል ዘርፍ ነው። ግንባታ ማለት ውድ እና ብዙ ገንዘብን የሚያስወጣ ነው። በዛ በኩል የሚገኘውን ሃብት በዛው የሥራ ዕድል ፈጥሮ ሃብት ለማከፋፈል የሚስያችል ዘርፍ ነው የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር የቤት ግንባታ እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ጭራሽ የማይነጣጠሉ ተደርገው እየተወሰዱ ነው። እንደውም ዋነኛ ዓላማው ለተጠቃሚው ቤት ማስገኘት ሳይሆን ዓላማውን የሳተ ይመስላል እየተባለ ነው። በእዚህ ላይ የእርሶ አስተያየት ምንድን ነው?
ኢንጂነር ኪያ፡- ዓላማውን ስቶ የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ብቻ አተኩሯል የሚለው ትክክል አይደለም። ዓላማውን ለማሳካት እና ቤቱን ለተጠቃሚው ለማስተላለፍ መገንባት አለበት። ሲገነባ ደግሞ ራሱን የቻለ በርካታ ሂደቶችን ያልፋል። በዛ ሒደት ውስጥ የሥራ ዕድል ይፈጥራል። ዓላማውን ስቷል ማለት ግን ሌላ ነው። ጭራሽ ቤቱ አይገነባም፤ አይተላለፍም ማለት ነው። ስለዚህ ግንባታው መገንባት አይችልም ከተባለ የሥራ ዕድልም አይኖርም። ቤት ማልማት እና ለቤት ፈላጊ ማስተላለፍ እስካለ ድረስ የሥራ ዕድል መፈጠሩ አይቀርም። የቤት ልማት በዚህ ደረጃ ዓላማውን ስቶ የሥራ ዕድል መፍጠር ብቻ መሆን አይችልም። ይሔ ዓላማውን ስቷል የሚባለው ነገር መስተካከል አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ዓላማውን ስቷል ያስባለበት ምክንያት የቤት ፍላጎት እና አቅርቦቱ መካከል ሰፊ ልዩነት መኖሩ ነው። ካለው ፍላጎት አንፃር እየተሠራ ያለው እጅግ ውስን መሆኑ፤ ይህንን ለማለት ምክንያት ሆኗል። ከአቅርቦት እና ከፍላጎት አንፃር ምን ይላሉ?
ኢንጂነር ኪያ፡- የከተማው የመኖሪያ ቤት ፍላጎት በቀጥታ ከከተማው ሕዝብ ጋር የሚያያዝ ነው። የሕዝብ ቁጥር ሲጨምር የቤት ፍላጎት ያድጋል። ይሔ የማይቀር ነው። እንደውም የፍላጎቱ መጠን እየቀነሰ ይሔዳል የሚል እምነት የለኝም። ከተማው በሰፋ እና ወደ ከተማ የሚገባው ሰው ቁጥር ሲጨምር ኅብረተሰቡ የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ይኖረዋል። ፍላጎቱን ተንተርሶ አቅርቦቱም በዛው ልክ ማደግ አለበት። ይሔ እውነታ ነው። ትክክለኛ ስትራቴጂም ነው።
በእርግጥ ፍላጎቱ እና አቅርቦቱ መካከል ያለውን ልዩነት ቢያንስ ማጥበብ ያስፈልጋል። አሁን ከተማችን ላይ ፍላጎቱ ከፍተኛ ነው። አቅርቦቱ ደግሞ በጣም አዝጋሚ ነው። ይሔ መሬት ላይ ያለ ሐቅ ነው። ይሔ ለምን ተፈጠረ ከተባለ ከከተማዋ ዕድገት ጋር የተያያዘ ጉዳይ ነው። የኅብረተሰቡ ቁጥር ሲጨምር ፍላጎት መጨመሩ አይቀርም። የእኛ ግን አቅርቦት በሚፈለገው ልክ ስላልሆነ መሃል ላይ ያለውን ክፍተት በጣም አስፍቶታል። ከፍተኛ ፍላጎት አለ። ይህንን የምንረዳው እና የምንቀበለው ጉዳይ ነው።
አዲስ ዘመን፡- እዚህ ላይ አቅርቦቱ እና ፍላጎቱ በስፋት የተራራቀበት የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም፤ የቤት ልማት ዓላማውን ስቷል እስከማለት ያደረሰው ቤቶቹ በፍጥነት እና በጥራት በውጪ አልሚዎች በብዛት ለመገንባት እየተቻለ፤ የሥራ ዕድል ለመፍጠር በሚል ሰበብ ዕድሉን ለአገር ውስጥ ተቋራጮች ብቻ በመሰጠቱ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ። እዚህ ላይ ምን ይላሉ?
ኢንጂነር ኪያ፡- አሁን የሥራ ዕድል መፍጠር ከአቅርቦት ጋር ቀጥታ ግንኙነት አለው ተብሎ ሲታሰብ ከውጪ የሚመጡትን ካምፓኒዎች ከመከልከል ጋር ተያይዞ ሊፈጠር የሚችለውን የአቅርቦት መጠን ቀንሶታል ወደሚለው ለመሔድ አንደኛ የውጪ አልሚዎች ምን ያህል ጠይቀዋል፤ በቤት ልማቱ ላይስ ምን ያህል ፍላጎት አላቸው የሚለው መታየት አለበት። በተለይ እንደኛ ተቋም አነጣጥረን የምንቀሳቀስለት ቡድን አለ። ዝቅተኛ ገቢ ያለው የኅብረተሰብ ክፍልን ታሳቢ አድርገን እንገዛለን። ይህን ኅብረተሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ ወጪ ቆጣቢ የሆኑ ቤቶችን መገንባት ዓላማችን ነው። ምክንያቱም ለኅብረተሰቡ የምናስተላልፈው ወጪ ቆጥበን ከተንቀሳቀስን ብቻ ነው። ያለ በለዚያ ዓላማችን ግብ አይመታም።
በከፍተኛ ወጪ ከተገነባ በትክክል ለኅብረተሰቡ ቤቱን ተደራሽ ማድረግ ይከብደናል። ከዛ አንፃር ስናየው የውጪ አልሚዎች እኛ አልምተን ልናስተላልፍ በምንችለው ዋጋ ምን ያህል ሊሠሩ ይችላሉ? ብለን መጀመሪያ መስፈርቱን ማየት አለብን። በዛ ደረጃ በዝቅተኛ ዋጋ ወይም በተመጣጣኝ ዋጋ የመጣ ምን ያህል አለ? እኛ ለኅብረተሰቡ ለማስተላለፍ በምናስበው ዋጋ እየቆጠበ ያለው ኅብረተሰብ በሚጠብቀው ዋጋ አልምቶ ወደ ሥራ ሊገባ የሚችል አሁንም ቢሆን አልሚ ካለ የግድ የውጭ ወይም የግድ የውስጥ አልሚ ተብሎ የተዘጋ በር የለም።
አሁን ላይ ቀርፀን እየሔድንበት ያለው የግል እና የመንግሥት አጋርነት (ፒፒፒ) ወይም በሽርክና ማንኛውም አልሚ አቅም ፈጥሮ መምጣት የሚችል ካለ እንደውም ብዙ ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥረን፤ ከእርሱ ጋር ለማልማት ዝግጁ መሆናችንን ገልፀን ለውጪ አልሚዎች በራችንን ክፍት አድርገናል። ለውጭ ብቻ ሳይሆን ለአገር ውስጥ ባለሃብትም አቅም ፈጥሮ ለሚመጣ ሰው የተለያዩ የግብር ጥቅሞችን መንግሥት ለመፍቀድ እንዲሁም የመሠረተ ልማት አቅርቦትንም ለማቅረብ ፈቃደኛ ነው። ይህን ሁሉ ሂደት ሔደን ከእነርሱ ጋር በመዋዋል ልማት ላይ ተሳትፈው እንዲሰሩ ብዙ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
ሞዳሊቲ እና የአሠራር ሥርዓት ተቀርጸዋል። ምናልባት ለአገር ውስጥ ተቋራጭ አምራቾች ብቻ እንዲሳተፉ ታስቦ ለሌላው ተዘጋ ተብሎ የሚታሰበው ነገር አሁን ትክክል አይደለም። ምክንያቱም ሌሎች አማራጮችን የከተማ አስተዳደሩ እየከፈተ ነው።
በዋናነት የሚፈለገው ማልማት የሚችሉ ሰዎችን አምጥቶ አልምቶ ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ነው። ነገር ግን መሠረታዊ ነገሩ ግቡ ዝቅተኛውን ማኅበረሰብ የሚጠቅም መሆን አለበት። ዋጋው ተመጣጣኝ ሊሆን የግድ ነው። በዚህ ግንባታ ተጠቃሚ የሚሆነው አካልን ታሳቢ ማድረግ ያስፈልጋል። ይህን መሠረት አድርጎ ሥራ ለመሥራት የሚፈልግ ማንኛውም አልሚ በግብዣ መሥራት የሚችልበት ሁኔታ አሁንም እየተፈጠረ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የሥራ ዕድል ፈጠራው ላይ ከተቋራጭ አንፃር ብቻ ሳይሆን ለተቋራጩ የሚቀርቡ ብሎኬት የሚያመርቱ አሉ። ጥራቱም ላይ ተፅዕኖ የፈጠረው የሥራ ዕድል ፈጠራ ተብሎ ወደዛ ትኩረት የተሰጠበት ሁኔታ በመኖሩ ነው ይላሉ። በእዛ ላይ የእርስዎ እምነት ምንድን ነው?
ኢንጂነር ኪያ፡- መንግሥት ለዜጎቹ የሥራ ዕድል የመፍጠር ኃላፊነት አለበት። የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ይሄ የቤት ልማት ኢንዱስትሪ ብቻ ሳይሆን በመንግሥት አስተባባሪነት የሚገነቡ ፕሮጀክቶች ላይ የሥራ ዕድል መፍጠር ኃላፊነት ነው። በግንባታው ሂደት ላይ በተለይ በከተማ ውስጥ የሥራ ዕድል አናሳ ከሆነ የሥራ ዕድል ይፈጠራል። ነገር ግን ጥራት ከተባለ ደግሞ ራሱን የቻለ የጥራት ቁጥጥር አካል አለ። በቤት ግንባታ ላይ ባለሙያው የጥራት ቁጥጥር የሚያደረገው የግንባታ ቦታ ሳይት ድረስ በመገኘት ነው። ክትትል የሚደረግበት የራሱ መንገድ አለው።ይሔ ለተቋራጭ ሲሆን፤ ለማኅበር ሲሆን የሚለይበት ሁኔታ አይኖርም።
በእርግጥ የሥራ ዕድል ትስስር ይፈጠራል። የክትትል እና የጥራት ቁጥጥር ባለው ሥርዓት ይቀጥላል። ጥራትን የሚያጓድሉ ነገሮች መንስኤያቸው በአሠራር ሥርዓቱ ላይ የሚፈጠሩ ክፍተቶች ናቸው። ሳይታሰቡ የሚያጋጥሙ የጥራት ክፍተቶች ይኖራሉ። የእኛም ፕሮጀክቶች ላይ የጥራት ጉድለት አይተናል። ይህን እያየን እየገመገምን ነው። ነገር ግን የጥራት ጉድለት እንዳይፈጠር እያጠናከሩ መሔድ እንጂ ግዴታ የሥራ ዕድል ስለተፈጠረ ወይም ማኅበራት ስለሠሩት የጥራት ጉድለት ያጋጥማል ማለት አይቻልም። እንዲህ መታሰብ የለበትም።
ጥራት ላይ የራሱ የቁጥጥር ሥርዓት አለው። ያለውን አጥብቆ የአሠራር ሥርዓት ፈትሾ ማጠናከር እንጂ ሥራ ዕድል በራሱ ችግር ሆኖ የሚመጣበት ሁኔታ አይኖርም። ምክንያም የሚደራጁት የማኅበር አባላት በራሳቸው አቅም ያላቸው የተማሩ እና ስልጠና የወሰዱ እና ስለጥራቱ ግንዛቤ ይኖራቸዋል ተብሎ ይታሰባል። ስለዚህ እነርሱን እያገዙ መሔድ ይገባል። የጥራት ጉድለትን የሚያመጣው የአሠራር ሥርዓቱ ላይ ያለው ክፍተት መሆኑን ማወቅ ተገቢ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ዘርፉ ላይ አንዱ የሚጠቀሰው ችግር ጥራት ብቻ ሳይሆን የሥነ ምግባር ክፍተትም ነው። ከላይ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ በማኅበር ተደራጅተው ከሚሠሩ ከብሎኬት አምራቾች ጀምሮ እስከ ተቋራጮች እንዲሁም አጠቃላይ ከመንግሥት የቤት ልማት ፕሮጀክት ጋር ተያይዞ ያሉ የተለያዩ ግለሰቦች ሲሚንቶ ከመስረቅ ጀምሮ ያለውን ሌብነት እንዴት ያዩታል?
ኢንጂነር ኪያ፡- በአጠቃላይ የግንባታ ዘርፉ ላይ የሚታይ የሥነ ምግባር ጉድለት አለ። ዘርፉን ራሱ ከብልሹ አሠራር እና ከሌብነት ለማፅዳት በርካታ ሥራዎችን ይጠይቃል። ከመንግሥትም አጠቃላይ በዘርፉ ላይ ያሉ ተዋናዮች በሙሉ ብዙ ይጠበቅባቸዋል። ይሔ የሥነ ምግባር ጉድለት ከላይ ሲገለፅ ለነበረው የጥራት ችግር መሠረታዊ መንስኤ ነው። የአሠራር ሥርዓቱ ላይ ችግር አለ ማለት አንዱ መንስኤ የሥነምግባር ጉድለት ነው።
ወደ ጥቃቅን እና አነስተኛ ብቻ ሳይሆን ወደ ተቋራጩም ቢኬድ የግብዓት አቅራቢው ላይ ሳይቀር በየትኛውም ቦታ የሥነምግባር ጉድለት ስላለ ተቋራጩም የሚሠራበት ጥራት ማኅበሩም ብሎኬትም ሆነ ፕሪካስት አምራቹ ሁሉም በሥነምግባር እየተመራ ስላልሆነ መጨረሻ ላይ ፍጥጥ ብሎ የጥራት ችግሩ እንዲታይ ያደርገዋል። ይህ ማለት ሕንፃው ላይ ክትትል እና ቁጥጥር ከሚያደርገው ባለሙያ ጀምሮ ማለት ነው።
አማካሪ ድርጅትም ሆነ የእኛ ግብአት አቅራቢን ጨምሮ በጣም በሰፊው የሥነምግባር ጉድለት አለ። አጠቃላይ ሌብነት አለ። ሌብነቱን ማጥፋት የሚያጠያይቅ አይደለም። የግድ አስፈላጊ ነው። ይህንን የምለው ቤቶች የሚዘገዩት፣ በጥራት የማይሠሩት የሥነ ምግባር ጉድለት ስላለ ነው። በዛ ላይ ያለውን ለይቶ ማስተካከል ሲቻል ችግሩ ይቃለላል። ይህንን ለማስተካከል ወደ ሥራ ተገብቷል። ሙሉ ለሙሉ ማጥፋት ባይቻል እንኳን ማሳነስ ያስፈልጋል።
ምን ሥራዎች ተጀምረዋል? ሌብነትን የምናጠፋው እንዴት ነው? ከተባለ ከጥራት አንፃር ከጊዜ አንፃር ግልፅ ብሎ እየታየ ነው። ግንባታዎች ከሚፈለገው በላይ ጊዜ እየወሰዱ እና ወጪ እያስወጡ እንዲሁም ጥራታቸው ከሚፈለገው በታች ሆነው እየተጠናቀቁ ነው። ስለዚህ ሌብነቱን ማሳነስ መቻል አለብን። ለማጥፋት መሞከራችን እና በዛው ውስጥ ማሳነስ መቻል አለብን። ከዛው ውስጥ ደግሞ የቁጥጥር ሥርዓቱን ለማስተካከል ጥረት እያደረግን ነው።
ውል እና ዲዛይን ሲዘጋጅ ተጠናቆ እንዲሔድ፤ ውሉ ላይ በትክክል የፕሮጀክቱ ሥራ እንዲቀመጥ፤ የክትትል እና የቁጥጥር ሥርዓት ላይ ጥብቅ ማሻሻያ አድርገናል። ለምሳሌ ከዚህ በፊት በነበረን ልምድ አንድ ባለሙያ አንድ መሐንዲስ ሰላሳ እና አርባ ሕንፃን ይቆጣጠር ነበር። ምን ያህል ደርሶ የመቆጣጠር ሥራውን ይወጣል ካልን የማይቻል ነው። ኣሁን ያንን ቀንሰን አንድ ባለሙያ ከአምስት እና ከአሥር በላይ እንዳይቆጣጠር እያደረግን ነው። አማካሪም ስንቀጥር በቀጣይ የምንሔድበትን እያዘጋጀን ነው። አፈፃፀማቸውን መሠረት አድርገን አንድ አማካሪ ምን ያህል ሠርቷል? ምን ያህል ለውጥ አምጥቷል? ከእኛ ጋር ሲሠራ በፊት ከነበረው ምን ያህል ለውጥ አምጥቷል? የሚለውን እያየን አማካሪ መቅጠር፤ አቅም መፍጠር፤ ተቋራጮችም አቅም ያላቸው ተቋራጮችን ለመቅጠር እየተሠራ ነው።
ተቋራጭ ስንቀጥር ከዚህ በፊት ያለብንን ክፍተት ለይተናል። በፊት ብዙ ችግሮች ነበሩ። ያንን ችግር ፈተን አሁን ላይ አቅም ያላቸው ተቋራጮችን የምንቀጥርበት ዕድል ፈጥረን የነበረውን ትርክት ማጥፋት ይኖርብናል። ደካማ ተቋራጮችን እና አማካሪዎችን ቀጥሮ ሥራ ከመበደል ይልቅ ጠንካሮቹን በተሻለ ዋጋ እያስገቡ ፕሮጀክቶችን ቶሎ ማጠናቀቅ ይገባል የሚል አቅጣጫን እየተከተልን ነው። አሁን ነባሮችን ፕሮጀክቶች እያጠናቀቅን ነው። ወደ ፊት አዳዲሶቹ ፕሮጀክቶች ላይ ተቋራጩ ራሱ ግብዓት እያቀረበ እንዲሠራ፤ ግብዓት ራሱ ካቀረበ ለጥራቱ ሙሉ ተጠያቂ የሚሆንበት፤ ለመዘግየትም ራሱ ሙሉ ተጠያቂ የሚሆንበት ሁኔታ ይፈጠራል። ከዚህ በኋላ እያንዳንዱ ላጠፋው ጥፋት ራሱ ተጠያቂ የሚሆንበት ሁኔታ ይኖራል። ያጠፋው ራሱ ይቀጣል፤ የጥራት ጉድለቱ ላይ የማስተካከያ እርምጃ ይወሰዳል። ይህንን ለማምጣት እያስተካከልን ነው።
ከዚህ በፊት ፕሮጀክቱ ለምን ዘገየ? ሲባል ክላይንቱ አላቀረበልኝም የሚል ምላሽ ይሠጣል። ግብዓት ሲቀርብ ደግሞ ተቋራጩ ሠራተኞቹን በትኗል። በሌላ በኩል የክፍያ መዘግየት ይኖራል። ተቋራጩ ራሱ የአቅም ችግር ይኖርበታል፤ ፋይናንስ ሲዘገይ ሠራተኛ ይበትናል። በድጋሚ ፋይናንስ ሲመጣ ደግሞ ሠራተኛ እስኪሰበስብ ጊዜው ይሔዳል። እነዚህ ሁሉ ሲደማመሩ ማንን ተጠያቂ ማድረግ እንደሚቻል ራሱ ግራ ይገባል። ያንን ግን አሁን ለመቅረፍ ተቋራጩ ራሱ ግብዓት ያቀርባል፤ ይሔ ደግሞ መጨረሻ ላይ የጥራትም ችግር ሲመጣ ራሱ ተጠያቂ ይሆናል። ጊዜው ከዘገየም ይጠይቃል።
አሁን መንግሥት የሚጠየቀው ፋይናንስ ካዘገየ ብቻ ነው። ለሚዘገዩ ጉዳዮች ሁሉ እከሌ ብሎ የሚያላላክበት ዕድል አይኖርም። ለዚህ መጀመሪያ ላይ ሥራዎች ሁሉ ዲዛይን ላይ እንዲያልቁ ማድረግ ነው። ሥራዎች ሁሉ ኮንትራት ላይ እንዲያልቁ በማድረግ ከላይ እስከ ታች ተናቦ ለመሥራት እየተሞከረ ነው። በቤት ልማት ላይ ያለውን ችግር ለማቃለል ደግሞ ብልሹ አሠራርን እና የስነምግባር ጉድለትን መቆጣጠር የሚቻልበትን ሥርዓት መፍጠር የግድ ነው። ሥርዓት ሲዘረጋ ራሱ ግንባታው የሚፈልገው ሳይንሳዊ የሆኑ መንገዶችን ይከተላል። ይህ ሆነ ማለት ደግሞ ማንም ከዛ መውጣት ስለማይችል በዛው ልክ ክፍተቱ ጉልህ ሆኖ ስለሚታይ በዚህ ደረጃ በአሠራር ሥርዓት ነገሮችን ለመፍታት ጥረት ይደረግበታል። አሁን ይህንን እያደረግንም እንገኛለን።
አዲስ ዘመን፡- የውጪ ካምፓኒዎች ለምን አይገቡም በሚል ለቀረበው ጥያቄ በተመጣጣኝ ዋጋ የኅብረተሰቡን አቅም ባማከለ መልኩ የሚሠራ ካለ መግባት ይችላል ብለዋል። ነገር ግን በከፍተኛ ዋጋም ቢሆን በብዛት ቢሠራ ልክ ለአመራሮች የመንግሥት ቤቶች አስተዳደር እንዳሠራው ዓይነት ቤት ቢሠራ የአቅርቦት ክፍተት ላይ የራሱ ሚና እንደሚኖረው እሙን ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ይላሉ?
ኢንጂነር ኪያ፡- ቅድምም እንደገለፅኩት ከመንግሥት ጋር በአጋርነት የሚሠሩ ሥራዎች አሉ። አልሚዎች እንዲሳተፉ ጥሪ እያደረግን ነው። በራችን ክፍት ነው። ይዘው የሚመጡትን የቤት ልማት ፕሮጀክት የምንመዝንበት ድርጅቶቹን የመመልመያ መስፈርት አዘጋጅተን እየጠበቅን ነው። አሁን የማልማት ጥያቄ ያቀረቡ የቻይና ካምፓኒዎች አሉ። አንዱ የአዋጭነት ጥናት እያካሔደ ነው። ከዚህ በፊት ዋስ የሚባል የዓረብ ኤሜሬት ወደ 30 ሺህ ቤት እገነባለሁ ብሏል።
ማልማት የሚፈልግ አቅም አለን የሚል ከመጣ ክፍት አድርገናል። ዘርፉ በጣም ትልቅ ኢንቨስትመንት የሚጠይቅ ነው። የአገር ውስጥም ቢሆኑ የቤት ፕሮጀክቶችን ይዘው ከኛ ጋር ቢገናኙ ማመቻቸት ያለብንን ነገር አመቻችተን እኛ ላስቀመጥነው የኅብረተሰብ ክፍል ተደራሽ የሚያደርጉ ካሉ በራችንን ከፍተናል። ዕቅዳችን ውስጥም አለ። ሁሉም በመንግሥት ተሠርቶ የሚቻል አይደለም። ተሞክሯል፤ ጥሩ ሥራ ተሠርቷል። አሁን ግን የግሉ ዘርፍ ተዋናይን ማሳተፍ የግድ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በሽርክና እና በጋራ የሚኖረው የቤት ልማት ሥራ በትክክል መቼ ይጀመራል?
ኢንጂነር ኪያ፡- በአጭር ጊዜ ይጀመራል። ከላይ እንደገለፅኩት የአዋጭነት ጥናት እያካሄዱ ያሉ አሉ። እነርሱ ጥናታቸውን አጠናቀው በምንፈልገው ልክ እና ዋጋ ቤቶቹን ሠርተው የሚያስረክቡን ከሆነ ውል ተዋውለን ወደ ግንባታ እንገባለን። ይህ እነርሱ አልሚዎቹ በሚሰጡን መልስ ላይ ይወሰናል። የቅድመ ዝግጅት ሥራዎቻችን የተወሰነ ጊዜ ይወስዳሉ። ወደ ፊት በጋራ እና በሽርክና መሥራት ላይ ልምድ ሲገኝ በፍጥነት ወደ ሥራ መግባት የሚቻልበት ዕድል ይኖራል። አሁን ለጊዜው በዚህ ቀን በትክክል ይጀመራል ለማለት ያዳግታል።
አዲስ ዘመን፡- የክልል መንግሥት ሠራተኞች ቤት እና ቤት መሥሪያ ቦታ የሚያገኙበት ዕድል አለ። እየተሰጣቸው ነው። የፌዴራል የመንግሥት ሠራተኞች ግን አንዳንዶቹ 2 ሺህ ብር በማይሞላ ደሞዝ በቤት ኪራይ እየተሰቃዩ ነው። ለመንግሥት ሠራተኞች በቀላል ግብዓት የሚገነቡ ቤቶች መሥራትን በሚመለከት ምን ይላሉ?
ኢንጂነር ኪያ፡- የመንግስት ሠራተኛው አንዱ የኅብረተሰብ ክፍል ነው። እዛው ውስጥ ለኅብረተሰቡ ግልጋሎት እየሠጡ ያሉ የቤቶች ልማት ሠራተኞች ራሳቸው ቤት የላቸውም። ኅብረተሰቡ እንዲረዳ የምንፈልገው ራሳችንም ችግር ውስጥ ሆነን ነው። የመንግሥት ሠራተኛውን ለይቶ የቤት ልማት ይካሔድለት የሚል ውሳኔን መወሰን የሚችሉት ከፍተኛ አመራሮች ናቸው። በእኛ በኩል ግን የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥተን የምንሠራው መጀመሪያ የ1997 ዓ.ም ተመዝጋቢዎች ቀጥሎ የ2005 ዓ.ም ተመዝጋቢዎችን ነው። የመንግሥት ሠራተኞችን በሚመለከት ፕሮጀክት ተቀርፆ ከመጣ በአንደኛው ሥርዓት ውስጥ ማሳለፍ ይቻላል። በጋራ አልሚዎች ወይም በሽርክና ውስጥ ማካተት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ እጅግ አመሰግናለሁ።
ኢንጂነር ኪያ፡-እኔም አመሰግናለሁ።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 28 ቀን 2014 ዓ.ም