የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል እንደሚባለው የትምህርት ነገርም ፋታ አይሰጥም። እንዳወያየ፣ እንዳነጋገረ፣ እንዳጨቃጨቀም ጭምር ነው ዘመናትን የዘለቀው፤ ይቀጥላልም። አዎ፣ የትምህርት ነገር፣ ባጭሩ፣ የሁሉም ነገር እናትና አናት ነው። ያለትምህርት ማንም፣ ምንም የለም ቢባል “እንዴት ሆኖ?” ሊያስብል የሚችል ጉዳይ አይደለም። በተለይ በአሁኑ ዘመናዊም ሆነ ድህረ-ዘመናዊ፤ ወይም መጪው ዘመን ያለ ትምህርት፣ ያለ እውቀት …. ለአፍታም እንኳን ሊታሰብ የሚችል አይደለም። ባጠቃላይ የትምህርት ነገር፣ እጓለ ዮሐንስ በ”የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ”ያቸው “ትምህርት፣ ትምህርት፣ ትምህርት …” እንዳሉት ነውና ወደ ዛሬው አስደሳች ርዕሰ-ጉዳያችን እንዝለቅ።
የዛሬው ጽሑፋችን መነሻ የ2013 ዓ.ም 12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ውጤት ይፋ መሆኑን ተከትሎ፣ በተለይ በትምህርት ተቋማት፣ መምህራን፣ ተማሪዎችና ቤተሰቦቻቸው አካባቢ ከልብ እያነጋገረ ያለው ማትሪኩላሽንና ውጤቱ ነው።
የትምህርት ሚኒስቴር አገር አቀፍ የትምርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ባለፈው ሳምንት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ በሁለት ዙር የተሰጠው 2013 ዓ.ም 12ኛ ክፍል ለአገር አቀፍ ፈተና ከተመዘገቡት 617ሺህ 991 ተማሪዎች መካከል 599ሺህ 003 (96.9%) ፈተናውን መውሰዳቸውን ገልጿል።
የሲቪክስ ፈተና በሁሉም ትምህርት ቤቶች በሚባል ደረጃ የውጤት መመሳሰልና ግሽበት በመታየቱ ምክንያት የፈተና ውጤት ለዩኒቨርሲቲ መግቢያ መወዳደሪያነት እንዳያገለግል መወሰኑን የገለፀው ኤጀንሲው ተማሪዎች የግልም ሆነ የመንግሥት የከፍተኛ ትምህርትን ለመከታተል ለመግቢያነት የሚያገለግሉ የትምህርት ዓይነቶችን አጠቃላይ አማካይ ነጥብ 50% እና በላይ ማምጣት እንደሚጠበቅባቸውም ተናግሯል። የፈተናው፣ ተፈታኞችና ውጤቱ አጠቃላይ ይዞታ ይህ ሲሆን፤ በዚሁ ጉዳይ ላይ በተናጠል አርአያ የሆኑ ትምህርት ቤቶችና ተማሪዎች ያሉ ሲሆን አንዱም “ኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ቀዳማዊ ምኒልክ ሳይንስ ሼርድ ካምፓስ” መሆኑ እየተነገረ ነው። በመሆኑም እኛም ወደ’ዚሁ አራት ኪሎ ወደ’ሚገኘው ተቋም በመሄድ በኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር መምህርና የካምፓሱ ርዕሰ መምህር (ፕሪንሲፓል) ከሆኑት አቶ አቤል ጫላ ጋር ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን:- በቅድሚያ ለቃለ መጠይቅ ስለተባበሩን እናመሰግናለን። ወደ ዋናው ጉዳያችን ከመግባታችን በፊት ስለ ትምህርት ቤቱ አመሠራረት ባጭሩ ቢነግሩን።
ፕሪንሲፓል አቤል:- ከ2008 ዓ.ም በፊት ይህ ግቢ በፊት ቀዳማዊ ምኒልክ በሚል የሚታወቅ አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነበር። ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ግን “ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ቀዳማዊ ምኒልክ ሳይንስ ሼርድ ካምፓስ” አሁን “ኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ቀዳማዊ ምኒልክ ሳይንስ ሼርድ ካምፓስ” በሚል በዩኒቨርሲቲው ሥር ሆኖ ተቋቋመ። ለትምህርቱ መጀመርና ለሳይንስ ትምህርቶች ትኩረት የመስጠቱ ጉዳይ መነሻው እስራኤል አገር ይኖሩ የነበሩ፣ ማርክ ጌልፈንድ የተባሉ ግለሰብ ናቸው። ግለሰቡ እስራኤል አገር ያሉ ቤተ እስራኤላውያን (ኢትዮጵያውያን) ለሳይንስ ትምህርት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው፣ ልዩ ትኩረትም እንደ’ሚሰጡና ከፍተኛ ውጤትም እንደሚያመጡ ይመለከታሉ። ከዚህ በመነሳት ’ኢትዮጵያ የሳይንስ አገር፣ የሳይንስ ማዕከል ነች ማለት ነው። እዛ ለዓለም የሚተርፉ ሳይንቲስቶችን ማፍራት ይቻላል’ የሚል ድምዳሜ ላይ በመድረስ፤ ፕሮጀክት በመቅረፅና ወደ’ዚህም በመምጣት የሳይንስ ዝንባሌ ያላቸውን ወጣቶች በመመልመል ትምህርቱ መሰጠት ተጀመረ። ፕሮጀክት ነበርና ከሁለት ዓመት በኋላ ፕሮጀክቱ አለቀ። ነገር ግን በወቅቱ የነበሩት ተማሪዎች በተፈተኑት ትምህርት በሙሉ “ኤ” (ስትሬት “A”) ያመጡ ስለነበሩና ኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ይህ ፕሮግራም መቆም የለበትም በማለት ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ሙሉ ለሙሉ ተረክቦት ለአገር በሚበጅ መልኩ ሥራው እንዲቀጥል ተደረገ። በአሁኑ ሰዓት 290 ተማሪዎችን ያስተናግዳል። አነሳሱ ባጭሩ ይህን ይመስላል።
አዲስ ዘመን:- ምን አይነት ተማሪዎችን ነው የምትቀበሉት?
ፕሪንሲፓል አቤል:- የምንቀበላቸው ተማሪዎች ከአዲስ አበባ እና አካባቢው ሆነው 8ኛ ክፍልን በከፍተኛ ውጤት ያጠናቀቁና ለሳይንስ ትምህርት ከፍተኛ ዝንባሌ ያላቸው ናቸው። የምንመርጣቸው ማስታወቂያ በማውጣትና በእሱው መሠረት እንዲወዳደሩ በማድረግ ነው። ይህን ስል ግን ውጤት ብቻውን ወደ እዚህ ካምፓስ ያስገባል ማለት አይደለም። ወደ እዚህ ተቋም ለመግባት በርካታ መስፈርቶች የሚያስፈልጉ ሲሆን ከሥነ ምግባር ጀምሮ ያሉት ሁሉ ይታያሉ። ከሁሉም በላይ ደግሞ ካምፓሱ የሚያዘጋጀውን የመግቢያ ፈተና ማለፍ ያስፈልጋል። እነዚህን (መግቢያ ፈተና 75%፣ የሚኒስትሪ ውጤት 15%፣ ቃለ-መጠይቅ 10%) ያሟላ ተማሪ ነው ወደ’ዚህ የሚገባው።
አዲስ ዘመን:- የካምፓሱ አሁናዊ ይዞታው ምን እንደሚመስል ቢነግሩን?
ፕሪንሲፓል አቤል:- እንዳልኩህ ቀደም ሲል የጠቀስናቸው ግለሰብ ድጋፍ ማድረጋቸውን አቁመዋል። አሁን ካምፓሱ ሙሉ ለሙሉ በመንግሥት በጀት (በኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ በጀት ማለት ነው) የሚተዳደርና በዩኒቨርሲቲው አመራር ስር ሲሆን ማንኛውም ነገር የሚሟላለት ከዚሁና በዚሁ ተቋም ነው። የካምፓሱ መምህራን ዝቅተኛው የትምህርት ደረጃ ሁለተኛ ዲግሪ (ኤምኤ) ሲሆን ከዛም በላይ የትምህርት ደረጃ ባላቸው መምህራን (ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምሩ ጭምር) ነው ትምህርቱ የሚሰጠው። ከመምህራኑ የሚጠበቀው የትምህርት ደረጃ ብቻ ሳይሆን ከሥነ ምግባር ጀምሮ ለሙያው ያላቸው ትጋትና የማስተማር ፍላጎት ሁሉ ከግምት ውስጥ ገብቶ ነው ቅጥር የሚካሄደው። በመሆኑም ካምፓሱ የነገ አገር ተረካቢ ትውልድ መፍጠርን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ነው እየሠራ ያለው። በተለይም የተመሰከረላቸው ዓለም አቀፍ ሳይንቲስቶችን ማፍራት ላይ ነው ትኩረቱ። ከዚሁ አኳያም እስካሁን በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነው።
አዲስ ዘመን:- ስንተኛችሁ ነው ማትሪክ ስታስፈትኑ?
ፕሪንሲፓል አቤል:- ሶስተኛችን ነው።
አዲስ ዘመን:- ውጤታችሁስ እንዴት ነበር?
ፕሪንሲፓል አቤል:- እኛ የተማሪ መውደቅ አይደለም ዝቅተኛ ውጤት የሚያመጣ ተማሪም አላጋጠመንም። ምናልባት እኛ ጋር ያለው ዝቅተኛ ሌላ ጋ ቢሄድ ከፍተኛ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ዘንድሮ ዝቅተኛው ውጤት 529 ነው። ይህ ምናልባት ሌላ ተቋም ቢሆን ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም። በ2012 ዓ.ም 75 ተማሪዎችን አስፈትነን 21ዱ ከ600 በላይ፤ ከ30 በላይ የሆኑት ደግሞ ከ500 በላይ ውጤት ነው ያመጡት። ስለዚህ ተማሪዎቻችን ስመ ጥር ናቸው። ይህ ደግሞ ይታወቃል።
አዲስ ዘመን:- ወደ ዘንድሮው ፈተናና ውጤቱ እንምጣ፤ እንዴት አገኛችሁት?
ፕሪንሲፓል አቤል:- እኛ እንደ ጠበቅነው ነው ያገኘነው። የተማሪዎቻችን ውጤት ከአዲስ አበባ አይደለም ከመላ አገሪቱ ከፍተኛው ሲሆን፣ እየመራም ነው። ዘንድሮ አጠቃላይ 78 ተማሪዎች ለፈተና ተቀምጠው 42 ተማሪዎች ከ600 በላይ ወጤት ያስመዘገቡ (አላዛር 659፣ ናታኒም 651) [ሳምንት ሁለቱንም በዚሁ አምድ እንግዳችን አድርገን እናቀርባቸዋለን] ሲሆን ዝቅተኛው ውጤት 529 ነው። ከፍተኛው (ከ700) ደግሞ 659 ማለት ነው። የዘንድሮው ተማሪዎቻችን ውጤት ይህንን ይመስላል። በጣም የሚያስደስት ውጤት ነው። ወደ ፊት የበለጠ እንድንሠራ የሚያበረታታን ውጤት ነው ያመጡት። ይህ ብቻም አይደለም። ተማሪዎቻችን በሁሉን አቀፍ እውቀትም ጎበዞች (ሁለ-ገብ ማለትም ቨርሳታይ) ናቸው፤ ለምሳሌ አንድ የሚወስዱት ዓለም አቀፍ ስታንዳርድን የጠበቀና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመወዳደርና የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ለመግባት የሚያስችል ፈተና አለ። ከፍተኛ ውጤት ነው የሚያመጡት። ለምሳሌ አላዛር ተካ ገመቹ ይህንን ፈተና ተፈትኖ ከ1600 1585 ነው ያመጣው። እዚህ ድረስ ናቸው የኛ ተማሪዎች።
አዲስ ዘመን:- ካምፓሳችሁ ለዚህ ውጤት ለመብቃቱ ምስጢሩ ምንድን ነው ይላሉ?
ፕሪንሲፓል አቤል:- እንደምታየው ካምፓሳችን ሁሉ ነገር የተሟላለት፣ ይህ ቀረሽ የማይባል አይደለም። ብዙ የሚጎድሉት ነገሮች አሉ። ነገር ግን ውጤት ደግሞ ሁሉ ነገር ስለተሟላም ስላልተሟላም አይደለም። ቢሟላ ጥሩ ነው። በእንደኛ አይነት አገር ሁሉንም ማሟላት ይከብዳል። በሂደት እንጂ ባ’ንዴ ሊሆን የሚችል አይደለም። በመጀመሪያ ደረጃ አንድ ተማሪ ለውጤት የሚበቃው ከራሱ፣ ከውስጡ ከሚመጣ የጋለ ፍላጎትና ውጤታማነትን የመሻት ጉዳይ ነው። በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የምናየው ይህንኑ ነው። ብዙ ጎበዝና ለዩኒቨርሲቲ የሚበቁ ተማሪዎች የሚወጡት ሁሉ ነገር ከተሟላለት የትምህርት ተቋም አይደለም። ነገር ግን ካላቸው ልዩ ፍላጎትና ከሚያደርጉት ልዩ ጥረት የተነሳ ለከፍተኛ ውጤት ሲበቁ፤ ከአገርም አልፈው ለዓለም ሲተርፉ እያየን ነው። የእኛ ተማሪዎችም ውጤት ከዚሁ አኳያ ሊታይ የሚችል ነው። ከፍተኛ የሆነ የማወቅ፣ የመማር፣ ውጤታማ የመሆን ፍላጎት አላቸው። በመሆኑም በዛው ልክ የሚጥሩ ተማሪዎች ናቸው ያሉን። ዩኒቨርሲቲው ለተማሪዎች ልዩ ትኩረት መስጠቱ፣ የአስተዳደር ሠራተኞች ለተማሪዎቹ ልዩ እንክብካቤ ማድረጋቸው፣ በመምህራን በኩል ይህ ቀረ በማይባል መልኩ ነው የመማር-ማስተማሩን ተግባር ማከናወናቸው፤ ከተማሪዎቻቸው የሚቆጥቡት አንዳችም ነገር አለመኖሩ ሁሉ ለዚህ፣ ለተማሪዎቻችን ከፍተኛ ውጤት መብቃት ራሱን የቻለ አስተዋፅኦ አድርጓል። ሁሉም አካላት ያላቸውን ሁሉ ለተማሪዎቻቸው የሚያውሉ ናቸው። በአስተዳደር በኩልም እንደዛው ነው። ቤተሰብም ያለ ምንም ማቋረጥ ክትትል ያደርጋል። የተማሪዎቻችን ወላጆች በልጆቻቸው ጉዳይ በጣም ስሱ ናቸው። ልጆቹ አንድ ክፍለ ጊዜ እንኳን ሳይማሩ ካሳለፉ ወይ በአካል መጥቶ፣ አልያም ስልክ ደውሎ ምክንያቱን የሚጠይቅ ወላጅ ነው ያለው። የዚህ ሁሉ ድምር ነው እንግዲህ ተማሪዎቻችንን ለዚህ ውጤት የበቃቸው። በዋናነት የራሳቸው ጥልቅ ፍላጎትና ብርቱ ጥረት።
አዲስ ዘመን:- ከዚህ ከማትሪክ (አጠቃላይ ፈተናው) ውጤት ባሻገር ስለ ቀደምት ተማሪዎቻችሁ ሁኔታ የምታውቁት ነገር አለ? ክትትል አላችሁ፣ እንደው ምን ያህል ስኬታማ እንደሆኑ ለማወቅ ማለቴ ነው?
ፕሪንሲፓል አቤል:- አዎ አለን። ከተማሪዎቻችን (ካሉትም ከወጡትም) ጋር የቅርብ ግንኙነት ነው ያለን። [ከተማሪዎቻቸው ጋር ሲደዋወሉ፣ በቅርብ ሲነጋገሩ …. ተመልክተናል። የተማሪዎቻቸው የእጅ ስልክ ቁጥርም በስልካቸው ውስጥ መኖሩን አይተናል። እናነጋግራቸው ዘንድ የፈለግናቸውን ተማሪዎች የእጅ ስልክ ቁጥርም የሰጡን ከስልካቸው ውስጥ ነው።] ለምሳሌ የመጀመሪያዎቹ ተፈታኞች ከፍተኛ ውጤት በማምጣታቸው ምክንያት በአሁኑ ሰዓት በጄን ዩኒቨርሲቲ (ባንግሎር፣ ሕንድ)የቴክኖሎጂ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ይገኛሉ፤ በማጠናቀቅም ላይ ናቸው። እዛም የውጤት ተማሪ መሆናቸውን እየተከታተልን ነው። ሌሎችም ብዙ አሉ። ኢትዮጵያውያን ሁኔታዎች ትንሽ እንኳን ከተመቻቹላቸው ዓለም አቀፍ ሳይንቲስት እንደሚሆኑ በየትም የታወቀ ነውና እነዛን ለማፍራት ነው እየሠራን ያለነው።
አዲስ ዘመን:- ከመማር-ማስተማሩ ተግባር ጎን ለተማሪዎቻችሁ ሌላ የምታደርጉት ነገር አለ? እንደ ተጨማሪ (ወይም ማጠናከሪያ) ማለቴ ነው።
ፕሪንሲፓል አቤል:- አዎ አለ። ለምሳሌ ታዋቂ ሰዎች መጥተው ለተማሪዎቻችን ልምዳቸውን የሚያካፍሉበት መድረክ አለ። ከተለያዩ ተቋማት፣ ከዩኒቨርሲቲዎች … እየመጡ የማነቃቂያ ንግግር ሁሉ ያደርጋሉ። እነዚህንና መሰል ተግባራትን ከመማር-ማስተማሩ ተግባር ጎን ለጎን እናከናውናለን። ይህም አንዱ ለተማሪዎቻችን ውጤታማነት የራሱን ድርሻ ያበረከተ መሆኑ አያሻማም። በቤተ መጻሕፍት፣ ቤተ ሙከራ ወዘተ ያለው ሁኔታም እንዲሁ ተማሪዎችን ውጤታማ ሊያደርግ በሚችል መልኩ ነው የተደራጀው። ከቴክኖሎጂ ተቋማት ጋር ትስስር በመፍጠር ከመደበኛው ትምህርት ባሻገር ተግባራዊ እውቀት እንዲገበዩ ይደረጋል። ከሁሉም በላይ ግን ተማሪዎቻችን ትምህርትን አጀንዳ አድርገው መሥራታቸው ነው ለዚህ ውጤት ያበቃቸው። ከእኛ ጋር በሚያደርጉት የአራት ዓመት ቆይታ የምንመለከተው ይሄንን ነው። ያለ ምንም መዛነፍ ጉብዝናቸውን ይዘው ነው የሚዘልቁት።
አዲስ ዘመን:- እስኪ ተማሪዎቻችሁን ለአንባቢያን አጠር አድርገው ይግለፁላቸው።
ፕሪንሲፓል አቤል:- ተማሪዎቻችን የተሟላ ሰብዕና ባለቤት ናቸው። ለትምህርት ቤቱ ማኅበረሰብ ሁሉ ታዛዥ ናቸው፤ ሰው አክባሪና ትሁት ናቸው። ቤተሰባዊ ግንኙነት ነው ያላቸው። እንደ እድሜያቸው አይደሉም፤ ወጣትነት ከባድ ሆኖ ሳለ ተማሪዎቻችን ግን ተቆጣጥረውት ትምህርታቸው ላይ የሚያተኩሩ ናቸው። በቴክኖሎጂ አጠቃቀማቸው የላቁና እርስ በእርስ ከመፎካከር ይልቅ መረዳዳትና መደጋገፍን የሚያስቀድሙ ናቸው። ችግሮችን ብቻ ይዘው የሚመጡ ሳይሆኑ መፍትሔዎችንም ይዘው የሚመጡ ናቸው። እርስ በእርስ በከፍተኛ ደረጃ የሚተማመኑ ናቸው። ወደ ፊት ኢትዮጵያ አገራቸውን በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ሊያስጠሩ የሚችሉ ተማሪዎች ናቸው ተማሪዎቻችን። “ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ” አሁን በአዋጅ ወደ “ኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ” ተቀይሯል፤ የትምህርት የልህቀት ማዕከል ሆኖ ይሠራል፤ በአገሪቱ የተፈጠረውን የትምህርት ስብራት ይጠግናል ተብሎ ነው የሚጠበቀውና እነዚህን ተማሪዎች እዚህም እያሉ ወይም ከዚህ ከሄዱና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከተቀላቀሉ በኋላም ድጋፉ ስለማይለያቸው የአገር አለኝታነታቸውን ይዘው የሚቀጥሉ ነው የሚሆኑት።
አዲስ ዘመን:- ጥሩ። እንደ ርዕሰ መምህርነትዎ ለተማሪዎች፣ በተለይም ከዚህ ውጤት በኋላ ወደ ተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለሚገቡ ተማሪዎች የሚሉት፣ የሚያስተላልፉት መልዕክት ይኖራል ብዬ አስባለሁ። ከዚህ አኳያ የተወሰነ ነገር ቢሉን።
ፕሪንሲፓል አቤል:- ልክ ነህ፤ ይኖራል። ተማሪዎች ምን ግዜም ቅድሚያ ሊሰጡ የሚገባው ለትምህርታቸው ነው። ራዕይ ሊኖራቸው ይገባል። ሌላው ቀጥሎ የሚመጣና ሊደረስበት የሚችል ነው። ተማሪዎች የአሁኑን እድሜአቸውን ከትምህርት ጋርና ለትምህርት ነው ማሳለፍ ያለባቸው። በዚህ የሚቆም ነገር የለም። ከዚህ ውጤት በኋላ የሚሄዱት ወደ ተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ነው። ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ በባህርያቸው ሕብረ ብሔራዊ ናቸው። ከተለያዩ አካባቢዎች፣ ባህሎች ወዘተ የሚመጡ ተማሪዎች በአንድ የሚገቡባቸው፤ በአንድም የሚኖሩባቸው ናቸው። ከዚህ አኳያ ተማሪዎቻችን ከወዲሁ ለእንደዚህ አይነቱ ማኅበራዊ ሕይወት ራሳቸውን ማዘጋጀት አለባቸው። እዚህ ያሳዩትን መከባበር፣ መደጋገፍ፣ አብሮነት … እዛም ሊቀጥሉበትና ከሌሎች ተማሪዎች ጋር በፍቅርና መተጋገዝ ሊኖሩ ይገባል። ከአካባቢያቸው፣ ከቤተሰቦቻቸው፣ ከለመዱት …. ሁሉ ተለይተው ራቅ ያለ ቦታ ሊሆን ይችላልና የሚሄዱት ይህ ማለት ምንም ማለት እንዳልሆነ ተገንዝበው፤ እንደውም ጥሩ አጋጣሚ መሆኑን ተረድተው እራሳቸውን ከሁኔታዎች ጋር አስማምተው ትምህርታቸውን መከታተል አለባቸው። ወደ ፊት አገራቸው በከፍተኛ ደረጃ የምትፈልጋቸው መሆናቸውን አውቀው ከዛ አንፃር ነው ትምህርታቸውን መከታተል የሚገባቸው። በሳይንስ ዘርፍ አገራችን ከፍተኛ የሰው ኃይል ያስፈልጋታል፤ ዓለምም ጭምር። በሌላውም እንዲሁ። ይህ ደግሞ እውን ሊሆን የሚችለው ነገ የእነሱ ከሆነው ከወጣቶች ነውና በርትተው ሊሰሩ ይገባል። ከዚህ አኳያ በተማሪዎቻችን በጣም እንተማመናለን። የ”ኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ቀዳማዊ ምኒልክ ሳይንስ ሼርድ ካምፓስ”ም እየሠራ ያለው ከዚሁ አኳያ ነው።
አዲስ ዘመን:- ለሰጡን ሙያዊ ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ።
ፕሪንሲፓል አቤል:- እኔም አመሰግናለሁ።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 28 ቀን 2014 ዓ.ም