
ሩሲያ ማሪፖል እና ቮልኖቫካ በተባሉ ሁለት የዩክሬን ከተሞች ላይ ከፊል የተኩስ አቁም አወጀች፡፡
የሩሲያ የመከላከያ ሚኒስቴር አዋጁ የሰብአዊ እርዳታን ለማንቀሳቀስ የሚያስችሉ ኮሪደሮችን ክፍት ለማድረግ ያለመ ነው ብሏል፡፡ ተኩስ አቁሙ ማሪፖል እና ቮልኖቫካ በተባሉ ሁለት የዩክሬን ከተሞች ላይ የታወጀ ነው፡፡
ሩሲያ በሁለቱም የዩክሬን ከተሞች ላይ ከፊል የተኩስ አቁም ያወጀችው የሰብአዊ እርዳታ ለማንቀስቀስ የሚያስችሉ ኮሪደሮችን ክፍት ለማድረግ በሚል እንደሆነም ነው የሩሲያ የመከላከያ ሚኒስቴር ያስታወቀው፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ «በሞስኮ አቆጣጠር ከቀኑ 10 ሰዓት ጀምሮ ሲቪሎች የማሪፖል እና ቮልኖቫካ ከተሞች ለቀው እንዲወጡና የተኩስ አቁም እና የሰብአዊነት ኮሪደሮች እንዲከፈቱ በሩሲያ በኩል ከፊል ተኩስ አቁም ታውጇል» ሲልም ነው የገለጸው፡፡
የማሪፖል ከንቲባ ቫዲም ቦይቼንኮ ከተማይቱ የሩሲያ ኃይሎች ላለፉት ቀናት በተደጋጋሚ ሲሰነዝርባት በቆየ ከባድ እና ጭካኔ የተሞላበት ጥቃት «ከበባ» ውስጥ መሆኗን ከሰዓታት በፊት ገልጸው ነበር፡፡
ቫዲም ቦይቼንኮ «ማሪፑልን ከከበባ በማውጣት ሰብአዊ ችግሮች መፍትሄ የሚያገኙበት ሁሉንም መንገዶች እንፈልጋለን» ሲሉም ነበር የሰብዓዊ ቀውሱ አሳሳቢነት የገለጹት።
የማሪዮፖልን ከተማ ለቀናት በከበባ ውስጥ በቆየችበት ወቅት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ናዚ በሌኒንግራድ ከተማ ያደረገውን በሚያስታውስ መልኩ፤ የሩሲያ ጦር ኃይሎች የከተማዋ የኤሌክትሪክ፣ ምግብ፣ ውሃ፣ ማሞቂያ እና ማጓጓዣ አገልግሎት እንዲቋረጥ ማድረጋቸው ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የቪላድሚር ፑቲን ጦር በዩክሬን ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ማድረግ ከጀመረበት የካቲት 24 ወዲህ በርካታ የዩክሬይን ከተሞችን መደብደባቸው፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎችን መገደላቸው እንዲሁም በአውሮፓ ትልቁን የአቶሚክ ኃይል ማመንጫ ላይ ጥቃት መሰንዘሩ የሚታወቅ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የጀመረችው ወታደራዊ ዘመቻ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተወደደላት አይመስልም፡፡
በዚህም አሜሪካን ጨምሮ በርካታ የምዕራቡ ዓለም አገራትና አጋሮቻቸው የሩሲያ አካሄድን ለመግታት አገሪቱ ያዳክማሉ ያሏቸው በርካታ ምጣኔ ሀብታዊ ማዕቀቦች በሩሲያ ላይ እየጣሉ ይገኛሉ፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን የካቲት 27/2014