
ከሩሲያ ዩክሬን ቀውስ ጋር በተገናኘ ስጋት የገባቸው ሩሲያውያን ወደ ጎረቤት ፊንላንድ እየተሰደዱ መሆኑ ተነገረ፡፡
ከፊንላንድ ዋና ከተማ ሄልንሲንኪ 120 ማይሎች ርቀት ላይ የምትገኘውና ከሩሲያ ጋር ድንበር በምትጋራው ቫሊማ ከተማ ውስጥ በርካታ የሕዝብ ማመላለሻዎችና የግል መኪኖች ውስጥ ያሉ ሰዎች ፓስፖርታቸውን ሲያሳዩ ተስተውሏል።
እነዚህ ሰዎች ታዲያ ዩክሬናውያን አይደሉም፤ ሩሲያውያን ናቸው። ምንም እንኳን ቁጥራቸው ከፍተኛ ባይሆንም ያለማቋረጥ ግን ይመጣሉ።
አንዳንዶቹ ከሩሲያ ለመውጣት የቸኮሉ ናቸው። ምክንያታቸው ደግሞ የቭላድሚር ፑቲን መንግሥት እየተነሳበት ያለውን ተቃውሞ ለመቆጣጠር በቅርብ ቀናት ውስጥ ወታደራዊ አስተዳደር ሊያውጁ ይችላሉ የሚል ስጋት በመፈጠሩ እንደሆነ እየተነገረ ነው።
ከሩሲያ ወደ ተለያዩ የአውሮፓ አገራት የሚደረጉ በረራዎች መቋረጣቸውን ተከትሎ ከሩሲያ ለመውጣት ያለው ብቸኛው አማራጭ በተሽከርካሪ አልያም በባቡር መጓዝ ነው።
ቢቢሲ ያነገራት ወደ ምሥራቃዊ አውሮፓ በመሸሽ ላይ የነበረች አንዲት ሩሲያዊት ሴት ማዕቀቦቹ ከመጣላቸው በፊት የአውሮፓ ሕብረት ቪዛ ማግኘቷን በመግለጽ እየሆነ ባለው ነገር ሁሉ በጣም ማዘኗን ትናገራለች።
«ዩክሬናውያን የእኛው አካል ናቸው፤ ቤተሰቦቻችን ናቸው»
ብላለች። «ልንገድላቸው አይገባም። ይህ መንግሥት እስካለ ድረስ ወደ ሩሲያ መመለስ አልፈልግም። በጣም አሳዛኝ ነው» ብላለች።
እሷ እንደምትለው አብዛኞቹ ሩሲያውያን ይህንን ጦርነት አይፈልጉትም፤ ነገር ግን ፑቲንን ተቃውመው ደግሞ እስር ቤተ መግባት እንደማይፈልጉ ታስረዳለች።
ፊንላንድ ውስጥ ልክ እንደ ዩክሬናውያን ሁሉ እንደዚህች ሴት ዓይነት ሩሲያውያን ትልቅ ኀዘኔታን እያገኙ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ሩሲያ በማንኛውም ጊዜ እንደ ፊንላንድ ያሉ ጎረቤት አገራት ላይ ጦርነት ልታውጅ ትችላለች የሚለውም ስጋት አብሮ እየጨመረ ነው።
በቅርብ በተሠራ አንድ የዳሰሳ ጥናት መሠረት አብዛኛዎቹ ፊንላንዳውያን አገራቸው የኔቶ አባል መሆን እንዳለባት የሚያምኑ ሲሆን ከጥምረቱም ከፍተኛ የሆነ ድጋፍና ጥበቃ እንደሚያገኙ ያምናሉ።
ሄልሲንኪ ውስጥ ከሩሲያዋ ሴንት ፒተርስበርግ የተነሳ ባቡር በመቶዎች የሚቆጠሩ ጭንቀት ውስጥ የገቡ ሩሲያውያንን ይዞ ደርሷል። አብዛኞቹ ባቡሮች ቀድመው የተያዙ ሲሆን የቲኬት ዋጋም ቢሆን ከዕለት ወደ ዕለት በእጅጉ እየናረ ነው።
ከሩሲያ የሚወጡ ዜጎች ይዘውት መንቀሳቀስ የሚችሉት የገንዘብ መጠን የተመጠነ ነው። የሩሲያው መገበያያ ገንዘብ ሩብል ዋጋው እየወደቀ ነው። የአገሪቱም ኢኮኖሚም ቢሆን በተጣሉት በርካታ ማዕቀቦችና እገዳዎች ምክንያት ጫና ውስጥ እየገባ ነው።
በሌላ በኩል የሩሲያው ትልቅ የነዳጅ አምራች ኩባንያ ሉኮይል የዩክሬንን ወረራ መቃወሙ ለሩሲያ መንግሥት ትልቅ ራስ ምታት ነው።
የአገሬው ወሳኝ ባለሀብቶች እና ቁልፍ ሰዎች ጀርባቸውን ለፑቲን መስጠት ከጀመሩ የመጨረሻው አማራጭ የሚሆነው ወታደራዊ አስተዳደር ማወጅ ሊሆን ይችላል።
ወደ ቱርክ ኢስታንቡል በመሄድ ላይ የነበረች አንዲት ሌላ ሩሲያዊት ሴት ለቢቢሲ በስልክ በሰጠችው አስተያየት በሶቪየት ሕብረት ወቅት ወደነበረው ዓይነት ሕይወት መመለስ እንደማትፈልግ ገልጻለች።
«30 ዓመቴ ነው። እስካሁን ድረስ በጣም አስቸጋሪ የሚባል ነገር አልተመለከትኩም። አሁን ላይ ግን ቶሎ ከሩሲያ ካልወጣሁ መቼም ቢሆን መውጣት እንደማልችል እየተሰማኝ ነው» ብላለች።
«በአንድ በኩል ይህ ጊዜ ከሩሲያ ለመውጣት ጥሩ አጋጣሚ ይመስላል። በሌላ በኩል ደግሞ ምናልባት ቤተሰብና ወዳጅ ዘመዶቼን ከዚህ በኋላ ላላያቸው የምችለበትም አጋጣሚም አለ» በማለት ስጋቷን ገልጻለች።
ፑቲን በሩሲያ ወታደራዊ አስተዳደር የሚያውጁ ከሆነ የሚፈልጉትን ነገር ያለማንም ጠያቂ በቀላሉ ማድረግ ይችላሉ።
ፕሬዚዳንቱ ከፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር በነበራቸው ውይይት በማንኛውም ሁኔታ ዩክሬንን ሙሉ በሙሉ ሳይቆጣጠሩ እንደማይቆሙ ገልጸውላቸው ነበር።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን የካቲት 27/2014