በአገራችን ኢትዮጵያውያን እንኳን መኖራቸውን የማናውቃቸው፤ ብናውቃቸው ደግሞ በአግራሞት እጃችንን አፋችን ላይ የሚያስጭኑ ቁጥራቸው እጅግ በርካታ የሆኑ አስደናቂና አስገራሚ ቅርሶች በጥንታዊ ሙዚየሞቻችን በአብያተ ክርስቲያናት፣ ገዳምት እና መስጂዶች ውስጥ ይገኛሉ።አንዳንዶቹን በዓይናችን እያየናቸው ስለመሆኑ ሁሉ ለማመን እንቸገራለን።
እነኝህን አስደማሚ ቅርሶች የሚመለከት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በአክሱም እና በላልይበላ ቅርሶች ላይ ብቻ አዕምሮውን ቸንክሮ ሌሎች ቅርሶቻችንን ማየት እንዳንችል ከተራራ የገዘፈ፣ እንደቋጥኝ የከበደ፣ ከውቂያኖስ የሰፋ እና የጠለቀ ደባ የፈጸመብን አንዳች ኃይል መኖሩን ይገነዘባል።
ለማወዳደር ባይሆንም በደቡብ ጎንደር ዞን በሚገኙ ገዳማት እና አብያተ ክርስቲያናት ያየኋቻው ቅርሶች ብቻ ከእነአክሱም እና ላልይሊበላ የሚበልጡ እንጂ የሚያንሱ አይደሉም።በደቡብ ጎንደር ዞን እጅግ በርካታ ቅርሶች ተመልክቻለሁ። እጅግ ያማሩ እና የሚያስደንቁም ናቸው።ቅርሶቹ ቀልብን ከመሳባቸው የተነሳ ለአፍታም እንኳን ቢሆን ዓይኖቻችንን እንድንከድን ፈቃድ አይሰጡንም።
ውድ አንባቢያን ለዛሬው በደቡብ ጎንድር ዞን በታች ጋይንት ወረዳዎች በምትገኘው የቤተ ልሄም ገዳም ከተመለከትኳቸው ቅርሶች የተወሰኑትን ብቻ በወፍ በረር ላስቃኛችሁ።
በታች ጋይንት ወረዳ ቤተልሄም ገዳም በርካታ የሆኑ አስደናቂ እና ምንአልባትም እያየናቸው እንኳን ለማመን የሚከብዱ ቅርሶች ይገኛሉ። ሁሉንም ቅርሶች በዛሬው ዝግጅት ላይ ብቻ በዓይነት እና ብዛት ለመጥቀስ መሞከር እንደትልቅ ድፍረት የሚያስቆጥር ይሆናል።
የጨው አጥር
የሰው ልጅ የሚመገበውን ምግብ ለማጣፈጥ ከሚጠቀማቸው ንጥረ ነገሮች መካከል ጨው በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሽ ነው።በተለይ እኛ ኢትዮጵያኖች ለጨው የተለየ ቦታ እንሰጠዋለን። ለወጥ መስሪያ፣ ለበርበሬ፣ ለቡና መጠጫ፣ ወዘተ ጨውን በስፋት እንጠቀማለን።በታች ጋይንት ወረዳ በምትገኘው የቤተልሄም ገዳም ጨውን ከምግብነት ባለፈ ለገዳሟ ህልውና ማስጠበቂያ የሚሆን አጥር ተሠርቶበት እናያለን።
ገዳሟ ሰፊ እና ረጅም ቁመት ባለው አጥር ዙሪያዋን የተከበበች ናት።ዙሪያዋን የከበባት አጥር የተሠራው ደግሞ ከጥርብ ድንጋይ እና የአሞሌ ጨው እንዲሁም ኖራ ተቀላቅሎ ነው።የገዳሙ አጥር የአጼ ዳዊት ልጅ በሆነችው ድል ሞገሳ በአስራ አራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደተሠራ የደብሩ አስተዳዳሪ እና የድጓ ምስክር መምህር የሆኑት ሊቀ ምሁራን አባ ይትባረክ ካሳዬ ይገልጻሉ።
የቤተልሄም ገዳም አጥር አስገራሚ የሚያደርጉት የራሱ መገለጫዎች አሉት።አንደኛው አጥሩ በአንድ ቀን ተጀምሮ በአንድ ቀን ያለቀ መሆኑ ነው።ሁለተኛው ደግሞ የአጥሩ ግማሽ የሚሆነው አካሉ ከጨው መሠራቱ ሲሆን፤ ሌላው እና ሦስተኛው ደግሞ አጥሩ በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ይሠራ እንጂ ምንም ዓይነት የእርጅና ምልክት ሳያሳይ እስከዛሬ ድረስ እንደ አዲስ መቀመጥ መቻሉ ነው።
የደብሩ አስተዳዳሪ የገዳሟ አጥር ከጨው መሠራቱን ሲነግሩን ለማመን ተቸገርን።በጥፍራቸው ኖራውን ፋቅ ፋቅ አደረጉ።ኖራው ተፈረፈረ።በኖራው ውስጥ ተቀብሮ የነበረው አሞሌ ጨው ብቅ አለ።ጨውንም በጥፍራቸው ፋቅ ፋቅ አደረጉ በምላሳቸውም ቀምሰው አሳዩን።የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጠኞችንም እርሳቸው እንዳደረጉት በጥፍራችን ከአጥሩ ላይ ፍቀን እንድንቀምስ አዘዙን። እኛም በጥፍራችን ከአጥሩ ላይ ፍቀን ቀመስነው።ጨው ነው! እየቀመስነው እውነታውን ግን አምኖ መቀበልና ማመን አቃተን።
እውነት ለመናገር ይህን የጨው አጥር የተመለከተ ማንም ሰው እንዴት በጨው አጥር ይሠራል ? ማለቱ አይቀርም ።እንዴትስ አጥር የተሠራበት ጨው በክረምት ወቅት ሟሙቶ አጥሩ ሊፈርስ አልቻለም? ብሎ መጠየቁ የማይቀር ነው።ነገር ግን የጥንታዊ ኢትዮጵያውያን ጥበብ አስደናቂ ነው። በክረምት ዝናብ በበጋው ፀሐይ የማይፈርስ ለመፍረስም ስጋት ያልሆነ ከጨው ክምር የቤተ ክርስቲያን አጥር መሥራት ችለዋል። ማስተዋልና ጥበብን በብልሀት የያዙ አባቶች ይህን አስደናቂ ሥራ ሠርተው አቆይተውናል።
ይህ የድንጋይ ጨው ቤተ ክርስቲያኗ ከተሠራችበት አካባቢ ከሚገኝ ወንዝ እንደተገኘም የደብሯ አስተዳዳሪ ነግረውናል።መጽሐፈ ኢሳያስ አንድምታው ላይ እንደተመላከተው እነዘሩባቤል እና እዮሲያስ ግንባቸውን በጨው ይሠሩት እንደነበር ያስታውሳሉ። ልጅ እያሉም ይሄን ታሪክ ከትንቢተ ኢሳያስ ላይ ሲያነቡ እጅጉን ይገረሙ እንደነበር ይገልጻሉ። የኋላ ኋላ ግን ምስጠሩ ሲገባቸው የቤተልሄም ገዳምም በዚያመልኩ እንደተሠራች መገንዘባቸውን ይናገራሉ።
አሁን ላይ የጨው አጥሩ በፍየሎች፣ በጎች እና ከብቶች እየተላሰ እና እየተበላ ቅርሱ ለከፍተኛ ችግር ተጋልጦ ይገኛል።
የድንጋይ አትሮንስ
ከጨው አጥሩ በተጨማሪም ቤተልሄም ገዳም ውስጥ እጅግ በርካታ የሆኑ ለዓይን ማራኪ እና ቀልብን ሰራቂ የሆኑ ቅርሶች ይገኛሉ።ከእነኝህ መካከል በሊቁ ቅዱስ ያሬድ ከድንጋይ የተሠራው የመጽሐፍት ማንበቢያ አትሮንስ አንዱ ነው።ይህ አትሮንስ ከአለት የተፈለፈለ ሲሆን ውብ እና ማራኪም ነው።
የመሰዋት ማቅረቢያ ሕንፃ
በገዳሟ ከሚገኙ ቅርሶች መካከል በኦሪት ዘመን ኢትዮጵያውያን ለፈጣሪያቸው መሰዋዕት የሚያቀርቡበት የነበረ ሕንፃ ይገኛል።ይህ ሕንፃ አሠራሩን ለተመለከተ በጥንት ጊዜ የነበሩ የኢትዮጵያውያን የኪነ ሕንፃ ጥበብ ሥልጣኔ የት ደርሶ እንደነበር በቀላሉ መገንዘብ ይችላል።
ይህ ሕንፃ ከክርስቶስ ልደት በፊት የተገነባ መሆኑን የደብሩ አስተዳዳሪ እና የድጓ ምስክር መምህር የሆኑት ሊቀ ምሁራን አባ ይትባረክ ካሳዬ ያስረዳሉ።ዕድሜ ጠገቡ ሕንፃ ዛሬም ላይ በቅርብ ጊዜ የተሠራ እንደመሰለ እስከነሙሉ ግርማ ሞገሱ ይገኛል።አባቶቻችንን ሕንፃውን ሲሠሩ ድንጋይን፣ ኖሯን፣ እንጨትን እና ብረትን ተጠቅመዋል።የተጠቀሟቸውን ግብአቶች የተመለከተ ማንም ሰው በሕንፃው ጥራት እና የዚያን ዘመን እድገት መደመሙ የማይቀር ነው።
ከዚህ ጋር ተያይዞ የዚህ ውብ ቅርስ ባለቤት መሆናችንን ስንቶቻችን እናውቃለን ? ቅርሱን ለማስተዋወቅ እና ቅርሱን ተጠቅመን በሚገኙ ገቢዎችስ ሥራጥነትን ለመቀነስ ምን ያህል እርምጃዎችን ሄደናል? አባቶቻችን የሠሩትን እኛ በዚህ ዘመን መሥራት ባንችል እንኳን የአባቶቻችን የታሪክ አሻራ ለኢትዮጵያን ብሎም ለዓለም ሕዝብ ለማሳየት ወይም ለማሳወቅ እንዴትስ ተሳነን? የሚሉትን እና መሰል ጥያቄዎች ማንም ገዳሟን የጎበኘ ሰው የሚያነሳው ስለመሆኑ አልጠራጠርም።
ሌላው በገዳሟ ከሚገኙ አስገራሚ ቅርሶች መካከል በአራተኛው ክፍለ ዘመን የተሠራው የቤተልሄም ቤተክርስቲያን ሕንፃ ነው።የገዳሙ አሠራር በመጽሐፍ ቅዱስ የሚገኙ አስተምህሮቶችን መሠረት ተደርጎ የታነጸ ነው።አንድም ነገር የመጽሐፍ ቅዱስን አስተምህሮት ምሳሌ ሳያደርግ አልተሠራም።ሕንፃው እስካሁንም ድረስ አዲስ ነው።ይሁን እንጂ ጥበቃ አያስፈልገውም ማለት አይደለም።በአያያዝ ችግር ሕንፃው ለችግር እንዳይጋለጥ ከፍተኛ ጥንቃቄ ቢደረግ መልካም ነው።
በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተሠራው ደብር ካሏት አስደናቂ ነገሮች መካከል አንዱ ደግሞ በሙቀት ወቅት ነፋስ የሚሰጡ ሁለት ቬንት ሌተሮች መኖራቸው ነው።ቬንት ሌተሮቹ በኤሌክትሪክ ወይም በእንፋሎት አልያም በከሰል ድንጋይም አይሠሩም።በምን ኃይል ታግዘው እንደሚሠሩ ባይታወቅም ሙቀትን የመቀነስ አቅም እንዳላቸው ግን ሊቀ ምሁራን አባ ይትባረክ ካሳዬ ይናገራሉ።
ዓለም በዘመነበት በአሁኑ ሰዓትም እንኳን ቢሆን ቬንት ሌተርን መጠቀም ቅንጡ ሕይወት የሚኖሩ ሰዎች ማሳያም ተደርጎ ይወሰዳል።የእኛ አባቶች ግን ቀድመው የሰለጠኑ ስለነበሩ አሁን ላይ የአየር ሙቀት ማቀዝቀዣ ፈጠርን ብለው የሚመጻደቁትን አካላት በብዙ እጥፍ ቀድመው በመሳብ ያስከነዱ መሆናቸውን ያስገነዝበናል።
የጥንተዊቷ ቤተልሄም ገዳም መስኮቶች በብረት የተሠሩ ናቸው።ነገር ግን የብረቶቹን ዓይነት ለይቶ ማወቅ ከባድ መሆኑን አባቶች ይናገራሉ።ከዚህ ጋር ተያይዞ ለጉብኝት ከአዲስ አበባ ወደ ታች ጋይንት ቤተልሄም ገዳም ተጉዞ የነበረውን የብረት ጥበብ ባለሙያው አቶ ዮሐንስ ግርማን ጨምሮ በርካታ የኪነ ሕንፃ ባለሙያዎች መስኮቶቹ የተሠሩባቸውን የብረት ዓይነቶች እስካሁን ድረስ ማወቅ እንዳልቻሉ የገዳሙ አባቶች ይገልጻሉ።
ይህች ገዳም በአገራችን ከሚገኙ ስመ ጥር ከሆኑ የድጓ ማስመስከሪያ ትምህርት ቤቶች ግንባር ቀደሟ ናት።የድጓ ማስመስከሪያም እንድትሆን ያዘዙት አጼ ሰርጸ ድንግል መሆናቸውን የገዳሙ አባቶች ይናገራሉ።አንድ ተማሪ የድጓን ትምህርት ተምሮ ሲጨርስ እና መጨረሱን ሲያስመሰክር አጼ ሰርጸ ድንግል ለገዳሟ ባበረከቱት ማህተም ድጓ ስለማስመስከሩ የማረጋገጫ ምልክት እንደሚደረግለት የገዳሙ አባቶች ይናገራሉ።ማህተሙም እጅግ የተለየ አስደማሚም ነው።
ስጋቶች፡- ቅርሶቹ ጥንቃቄ ካልተደረገላቸው እና በሙዚየም መቀመጥ ያለባቸው ደግሞ በሙዚየም ካልተቀመጡ ወደ ፊት በነበሩበት አስደማሚነታቸው ሊቀጥሉ እንደማይችሉ አንዳንድ ጠቋሚ ምልክቶች ይታያሉ።ለምሳሌ የጨው አጥሩ ጥንቃቄ የማይደረግለት እና በዚህ መልኩ የሚቀጥል ከሆነ በከብቶች፣ ፍየሎች እና በጎች እየተበላ ሊፈርስ እንደሚችል ማየት ችለናል።ስለሆነም ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ለቅርሱ ጥንቃቄ ቢያደርጉ መልካም ነው።
ዕድሎች፡- ወደ ፊት እነኝህን ቅርሶች በአግባቡ ጊዜ ተወስዶባቸው ለኢትዮጵያውያን እና ለዓለም ሕዝብ ቢተዋወቁ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ሰፊ የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም ባሻገር ኢትዮጵያ ከቱሪዝም ዘርፉ የምታገኘውን ገቢ በእጅጉ ማሳደግ የሚያስችል ነው።
በደቡብ ጎንደር ዞን የሚገኙ ቅርሶቻችንን ለኢትዮጵያውያን ብሎም ለዓለም ሕዝብ በማሳወቅ ለዜጎቻችን የሥራ ዕድል ለመፍጠር እና ኢትዮጵያ ከቱሪዝም ዘርፉ የምታገኘውን ገቢ በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ለመሥራት አቅዶ እየተንቀሳቀሰበት ያለውን የቅርሶች የፎቶ አውደ ርዕይ እንዲሳካ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን መወጣት ይጠበቅበታል! መልዕክቴ ነው።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን የካቲት 27/2014