በሕይወት ጉዞ ውስጥ አስተሳሰብ ትልቁን ቦታ እንደሚይዝ ማንም የሚያምንበት ጉዳይ ነው።ምክንያቱም አስተሳሰብ ሰውን ቤትንና አገርን ይለውጣል።ይህ ሆነ ማለት ደግሞ ሕይወት ሙሉ ይሆናል። በፍቅር የተገነባ ማንነትን ያላብሳል። ለሥራ ያነሳሳል። በሌሎች ከመቅናትም ይታደጋል። ምክንያቱም በራስ ላብ ማደግን ያስተምራልና። ወደ አሸናፊነትም የሚያስጉዘን ጥርጊያ መንገድ ነው። ትናንት እንደ አገር አሸናፊ የሆነውም በቀና አመለካከታችንና ሥራችን መሆኑን ማንም ሊክደው አይችልም።
ዛሬም ያ እንዲሆን በዚህ ስብዕና መሰራት እንዳለብን እሙን ነው።በተለይ አሁን አገራችን ያለችበትን ችግር ለመፍታት አስተሳሰባቸው ቀና የሆኑ ሰዎች ያስፈልጉናል።በመሥራት የሚያምኑና ለአገራቸው የሚሰስቱት ነገር የሌላቸውም እንዲሁ።ከእነዚህ መካከል ደግሞ ለዛሬ ‹‹የሕይወት ገጽታ አምድ›› እንግዳችን ያደረግናቸው ዶክተር ሃብተማርያም አባተ አንዱ ናቸው።ብዙ የሕይወት ተሞክሮም አላቸው።ልምዳቸውም ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም።ነገር ግን አባይን በጭልፋ ቢሆንም ከሕይወታቸው ትማሩ ዘንድ ቀነጫጭበን እንድታነቧቸው ጋበዝናችሁ።
ተማሪው ልጅ
ፍቅርንና ፍትህን አብዝተው ከሚወዱ ልጆች መካከል ናቸው።እንዲያውም ሰው ሰላም ካላላቸው ያኮርፋሉ።ስለዚህም መልሰው ሰላም ካልተባሉ ያዝናሉና ሰላም አለማለትን ምርጫቸው አድርገዋል።በሌላ በኩል በባህሪያቸው ተጨዋችና የብዙ ተሰጥኦ ባለቤት ሲሆኑ፤ በተለይ ሙዚቃ፣ እርሻ፣ ቴአትር፣ ስፖርት በዋናነት በትምህርትቤት የሚሳተፉባቸው ስለነበሩ እነዚህ ላይ የተለየ ችሎታ ነበራቸው። በተለይ ቴአትር ላይ ልዩ አቅም እንደነበራቸው ያስታውሳሉ።ቴዎድሮስን ሆነው የሠሩትንም መቼም አይረሱትም።
ከስድስት ዓመት በላይ በእናታቸውና አባታቸው ቤት ያልቆዩት ባለታሪካችን፤ አብዛኛው የልጅነት ጊዜያቸውን ያሳለፉት በአርሲ ከተማ ታላቅ ወንድማቸው ቤት ነው።በእዚያ ደግሞ ብዙ ልምድን አካብተዋል።አብዛኛው ማንነታቸውም በወንድማቸው የተሠራው ለዚህ ነው።እርሱ የልጅነት መምህራቸው የዛሬ ሕይወት ቀያሺያቸው ነው።እርሳቸውም ቢሆኑ ጥሩ ተማሪ እንደነበሩ አይረሱትም።ምክንያቱም በባህሪም ሆነ በሥራ የእርሱን ባህሪ ቀድተው ይዘው አድገዋልና ነው።
በአንድ ትምህርት ቤት ቢበዛ ዓመት ያህል ነው የሚቆየው።ለዚያውም ሥራውን እስኪያጠናቅቅ ድረስ።ዋና ሥራው ወቅቱ ትምህርት ቤቶችን የማስፋፋት ዘመቻ ያለበት በመሆኑ ዳይሬክተር ሆኖ የተመደበ ሁሉ ይህንን የማድረግ ግዴታ አለበት።በዚህም ትምህርትቤቶችን በማስፋፋት ዙሪያ አርሲ ክፍለአገር ላይ አሻራቸውን ካሳረፉ መካከል ይጠቀሳል።ይህ ደግሞ ለእርሳቸው አገር ወዳድነትን፣ ሥራ አፍቃሪነትንና ለፍቶ ማደርን አስተምሯቸዋል።ተክል ተክሎ የመብላትና ራስን የመገንባትም ያህል አድርገው ነው በሚሠሩት ሁሉ የሚደሰቱትም።ልፋቱ ለራስም ለአገርም የሚበጅ እንደሆነ እንዲያምኑ ሥራቸውን ለማከናወን ያገዛቸው የታላቅ ወንድማቸው ምክር እንደነበርም አይዘነጉትም።
እነ ዶክተር ቤት ብዙም ሥራ የለም።ይሁን እንጂ ከብት ማገድን አጥብቀው ስለሚወዱ ከእረኞች ጋር በመሄድ ተግባሩን ይፈጽሙ ነበር።ወንድማቸው ጋር ከሄዱ በኋላ ደግሞ ከብት ማገዱን ሆነኝ ብለው ሳይሆን ከብቶቹ ለእርድ በመጡበት ወቅት ስለሚወልዱ የተወለዱትን በመንከባከቡ ዙሪያ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ።በተመሳሳይ የሚኖሩበት የትምህርት ቤቱ ግቢ ሰፊ በመሆኑ በእርሻ ትምህርት ያዳበሩትን እውቀት በተግባር ይተረጉማሉ።አትክልትና ፍራፍሬን በስፋት ያመርቱናም ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች በመሸጥ ለትምህርት ቤቱ ገቢ ያስገኛሉ።ከዚያም የተወሰነ ፐርሰንት ይሰጣቸውና የትምህርት ወጪያቸውን ይሸፍናሉ።በዚህ ደግሞ መምህሮቻቸው በጣም ይወዷቸዋል።
ትምህርት
መምህሮቻቸው በብዙ ነገራቸው የሚደሰቱባቸው ልጅ ነበሩ። ምክንያቱም በእውቀትም በቅልጥፍናም ጥሩ አቅም ነበራቸው። በተለይ በእጅ ጽሑፋቸውና በሚያመጡት ያልተጠበቀ ውጤት ሁልጊዜ እንደተደነቁባቸው ነው። በዚህም ሁሉም ከሌሎች ተማሪዎች ለየት አድርገው ያዩዋቸዋል፤ ይንከባከቧቸዋልም። ለሰነፍ ተማሪዎች ማስተማሪያ ጭምር ያደርጓቸዋል።
በጭላሎ አውራጃ ኮፈሌ መለስተኛ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሁለተኛ ክፍል በመግባት ትምህርታቸውን የጀመሩት ባለታሪካችን፤ ቀድመው የቄስ ትምህርትና ለሦስት ወር ያህል ታላቅ እህታቸው ጋር መርሳ ከተማ መርሳ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በ1961 ዓ.ም በመግባት ተምረዋል።በሁሉም ክፍል ላይ የተሻለ ተማሪ ሲሆኑ፤ ለዚህም ማሳያው ከሦስት ወር ትምህርት በኋላ በቀጥታ ሁለተኛ ክፍልን እንዲቀላቀሉ መሆኑ ነው።ሁለተኛ ክፍልንም ቢሆን እንዲሁ ከአራት ወር በላይ አልቆዩበትም።ሦስተኛ ክፍል ገብተው ነው ትምህርታቸውን የቀጠሉት።
እስከ አራተኛ ክፍል በኮፈሌ የተማሩት እንግዳችን፤ ቀጣዩን ትምህርታቸው ያደረጉት በዚያው በአርሲ ክፍለአገር አርባጉጉ አውራጃ አሰኮ ትምህርት ቤት ነው።አምስተኛና ስድስተኛ ክፍልን ተምረውበታልም።ትምህርት ቤቱ በላይነህ ተብሎ የሚጠራን ጎበዝ ተማሪ አስረስተው አርአያነታቸውን ያስመሰከሩበት ቦታም ነው።ከዚያ ወደ ጉና የተጓዙ ሲሆን፤ እዚህ ደግሞ የተማሩት ከታላቅ ወንድማቸው ጋር በመሆን ነው።ሰባተኛ እና ስምንተኛ ክፍልን በዚያ ተከታትለውበታል።ይሁን እንጂ ስምንተኛ ክፍል ሳሉ ለተወሰነ ወራት ትምህርታቸው ተቋርጦ ነበር። ምክንያቱም የ1966 ዓ.ምቱ የአብዮት ፍንዳታ ረብሻ የፈጠረ በመሆኑ ወደ ቤተሰባቸው እንዲሄዱ አድርጓቸዋል።ነገር ግን ተመልሰው ትምህርታቸውን እንዲያጠናቅቁ ሆነዋል።
ዘጠነኛ እና አስረኛ ክፍል ደግሞ የተማሩት አቦምሳ አርበኞች ትምህርት ቤት ሲሆን፤ ትምህርቱን በአግባቡ ማጠናቀቅ ያልቻሉበት ጊዜ ነው።ምክንያቱም ጊዜው ተማሪው ወደ ትግል የገባበትና ፓርቲ ውስጥ የገባበት ጊዜ በመሆኑ እርሳቸውም አንዱ ስለነበሩ ትምህርታቸውን እያቆራረጡ እንዲቀጥሉ ሆነዋል።ችግሩ ደግሞ ደሴ እንዲሄዱና እንዲማሩ ከማድረጉም በላይ የትምህርት መስክ ምርጫቸውን አዛብቶባቸዋል።11ኛ እና 12ኛ ክፍልን በወይዘሮ ስሂን ትምህርት ቤት ሲማሩም በትምህርትቤቱ የሚያስተምረው ወንድማቸው የትኛው ላይ ዝንባሌ እንዳላቸው ያልተረዱትና አርትን እንዲመርጡ ያደረጓቸውም ለዚህ ነው።ይህ ደግሞ የሚፈልጉትን ዩኒቨርሲቲና ትምህርት መስክ እንዲያገኙ አላደረጋቸውም።
በወይዘሮ ስሂን ትምህርትቤት ሲማሩ አዲስ ቢሆኑም ተአምር የሠሩ ናቸው።ይህንን ዕድል የሰጣቸው ደግሞ የሂሳብ ትምህርት ውጤታቸው ነው።ሳይንሱ ላይ ትልቅ አቅም ነበራቸው።በ15 ደቂቃ እስከ ቦነሱ መልሰውት መቶ አስራ አምስት አምጥተው ያውቃሉም።በዚህም ሁሉም ተገርሞባቸው ነበር።ይህ ውጤታቸው ወንድማቸውን ጨምር ያስደመመና ያናደደም እንደነበር ያስታውሳሉ።ከአርት አስወጥተው ሳይንሱ ላይ ሊቀይራቸውም ሞከረው ነበር፤ አልተሳካም እንጂ።
ቀጣዩ የትምህርት ጉዟቸው ሀረማያ ላይ ያቆያቸው ሲሆን፤ ሳይመርጡት ተመርጠው የገቡበት ነው።መግቢያ ውጤታቸው ከሦስት ነጥብ በላይ የሆኑ ስምንት ልጆች መካከል ቢሆኑም ሳይንሱን ትተው ወደ አርቱ እንዲገቡ በተገደዱበት ጊዜም ያገኙት ነው።እናም ስድስት ኪሎ ገብተው ኢኮኖሚክስ ማጥናትን የሚፈልጉት ዶክተር ሃብተማርያም ብዙ ተፈትነው ዩኒቨርሲቲውን ተቀላቅለዋል።የመጀመሪያው በሱማሌ ጦርነት ዩኒቨርሲቲው ተዘግቶ ቆይቶ ስለነበር ተመራቂ ተማሪዎች መውጣት ባለመቻላቸው ከሦስት ነጥብ በላይ ውጤት ያላቸው 100 ተማሪዎች ብቻ እንዲገቡ ተደረገ። ተመራጮቹ ደግሞ ከእርሳቸው በስተቀር የሳይንስ ተማሪዎች ስለሆኑ እርሳቸውንም ግድ የሳይንስ ተማሪ እንዲሆኑ ያስገደዳቸው ነው።
ከእንደገና ትተውት የቆዩትን ትምህርት እንዲያጠኑም ሆኑ።በዚህም በተለይም የመጀመሪያ ዓመቱ እጅግ ከባድ ሆኖባቸው ነበር።ይሁን እንጂ እጅ ሳይሰጡ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግሪካልቸራል ኢኮኖሚክስ ትምህርት መስክ የጠበቁትን ያህል ውጤት ባይመጣላቸውም ትምህርታቸውን ማጠናቀቅ ችለዋል።ከዚያ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከስድስት ዓመት የሥራ ላይ ቆይታ በኋላ እንግሊዝ አገር በሚገኘው ሪዲንግ ዩኒቨርሲቲ በመግባት በአግሪካልቸራል ኤክስቴንሽን የትምህርት መስክ ተመርቀዋል።
ከተወሰነ ዓመት የሥራ ላይ ቆይታ በኋላ ዳግም ትምህርታቸውን ለመጀመር የቻሉት ዶክተር ሃብተማርያም፤ ሦስተኛ ዲግሪያቸው በሚዲያና የልማት ኮሙኒኬሽን ትምህርት መስክ ተከታትለዋል።የተማሩበት ዩኒቨርሲቲ ደግሞ ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ነው።ከዚያ በኋላ 11ኛ ክፍል ላይ ከአንዱ ወደ አንዱ መቀያየር ያመጣባቸውን ጣጣ ያውቁታልና እየሠሩበት ያለውን የትምህርት መስክ በመቀጠል የተለያዩ ሥልጠናዎችንም ወስደዋል።አሁንም ቢሆን ይህንኑ ሙያቸውን በተለያየ መልኩ እያጎለብቱ እንደሆነም አጫውተውናል።
ግብርናን ያልለቀቀው ሥራ
እንግዳችን ላለፉት 30 ዓመታት ማለትም ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ጨርሰው ከእንግሊዝ ከተመለሱ በኋላ የትምህርት መስኩን ብቻ ሳይሆን አለቃቸውን ጭምር ቀይረው አያውቁም።ይህ መሆኑ ደግሞ ሥራቸው ውጤታማ እንዲሆን አስችሏቸዋል።የግብርና ስትራቴጂዎችን፣ ፖሊሲዎችን እና የተለያዩ ፐሮጀክቶችን፣ ፕሮግራሞችን በመቅረፅ ከ30 ዓመታት በላይ የኢትዮጵያን ግብርና በማሳደግ ትልቅ አስተዋፅኦን እንዲያበረክቱም ያገዛቸው በዚህ መልኩ መጓዛቸው እንደሆነ ያወሳሉ።ሰዎች በአንድ ሙያ መስክ ላይ ስፔሻላይዝድ ሲያደርጉ በአቅምም በጉልበትም በእውቀትም የተሻሉ ይሆናሉና ይህንን አውቀው ተግባራትን መከወን አለባቸውም ይላሉ።
ሥራቸውን አሀዱ ብለው የጀመሩት በጎንደር ከተማ በእርሻ ሥራ አመራር ባለሙያነት ሲሆን፤ አንድ ዓመት ከስድስት ወር ያህል አገልግለውበታል።ከዚያ የጎንደርና የጎጃም ክፍለአገሮች በአንድነት ሆነው እንዲሠራባቸው ቀጣና ጽሕፈት ቤት በመቋቋሙ ሰሜን ምዕራብ ቀጣና ውስጥ በእርሻ ሥራ አመራር ሙያቸው ባለሙያ ሆነው እንዲሠሩ ሆኑ።ከተወሰነ ወራት በኋላም ፔዛንት አግሪካልቸር ዴቨሎፕመንት በሚባል ፕሮጀክት ላይ ኃላፊ ሆነው ወደማገልገሉ ገቡ።ምርጥ ተብለው የሚጠቀሱ 47 ወረዳዎች ላይ በምግብ ራስን ለመቻል ፕሮግራም ተቀርጾ የዓለም ባንክ የሚረዳው ነበርና እርሱን አስተባብረዋል፣ መርተዋልም።ይህም ባህር ዳር ላይ የከተሙበት ሲሆን፤ ለአገራቸው በሙያው ብዙ ጥቅም ያስገኙበት እንደነበረ ያነሳሉ።
በሙያቸው ከኢትዮጵያ አልፈው በተለያዩ አገራትም ልምዱን በማካፈል ድህነትን ለመዋጋት ብዙ ለፍተዋልም።ምክንያቱም ቦታውን ሲይዙት ከቴክኖሎጂ እስከ ትግበራው ድረስ ብዙ ልምድ ቀስመዋል፤ የምርምር ሥራን ከውነዋል። በዚህም ወደ ዋና መሥሪያቤት ተዛውረው የአገሪቱን ግብርና ሊመሩ ይገባል ተብለው ታመነባቸው። የሠሩት ጥናት በደረሳቸው በወሩም ነው ዝውውር ሳይጠይቁ አዲስ አበባ የገቡት። የግብርና ዘዴ ማስፋፊያ መምሪያ (አግሪካልቸራል ኤክስቴንሽን) ክፍል ውስጥ ከፍተኛ ባለሙያ በመሆንም ማገልገል የጀመሩትለዚህ ነው።
ሁለት ዓመት ሳይሞላቸውም የሞያሌ አውራጃ አስተዳዳሪ ሆነው ተሹመው እንደነበር ያጫወቱን እንግዳችን፤ ሙያቸውን መልቀቅ አይፈልጉምና አልሄዱም።ይልቁንም ለትምህርት የሚሄዱበትን መስመር መዘርጋትና ማፋጠናቸውን ተያያዙት።ዕድል ቀንቷቸውም ለትምህርት ሄዱ።ከትምህርት መልስ በኋላ የላካቸውን መስሪያቤት ሦስት ወር ላልሞላ ጊዜ ካገለገሉ በኋላ የሳሳካዋ ግሎባል 2000 ፕሮጀክት ከግብርና ሚነስቴር ጋር በቅርበት ይሠራ ነበርና እርሳቸው ዋና አካል (ፎካል ፕርሰን) ሆነው ደርበው እንዲሠሩ ተደረጉ።ለስድስት ዓመት ያህልም በቦታው ላይ ቆይተዋል።
ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ጨርሰው ሲመጡ ደግሞ ያስተማራቸው ተቋም ምቹ ሁኔታን ባለመፍጠሩና ስላልተቀበላቸው እርሱን ሳያገለግሉ ግብረ ሰናይ ድርጅት ውስጥ እንዲገቡ ሆኑ።ይህም ዋና ሥራ አስፈፃሚ በመሆን ለሰባት ዓመት ያህል ያገለገሉበት ሲሆን፤ በዘላቂ መሬት ልማት አጠቃቀም የተባለ መስሪያቤት ነው።ጎን ለጎንም በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው የአየር ንብረት ለውጥ ድርድር ላይ ከፍተኛ ሥራ የሰሩ ነበሩም።
የኢትዮጵያ ሲቪል ሶሳይቲ ኔትወርክ ኦን ክላይሜት ቼንጅ ዋና አማካሪና 54ቱንም የአፍሪካ አገራት ያቀፈውን ፓን አፍሪካ ክላይሜት ጀስቲስ አሊያንስ ድርጅትን ተባባሪ ሊቀመንበር በመሆን ሲመሩ ቆይተዋል።በዚህም የአፍሪካ ድምፅ በዓለም መድረክ እንዲሰማ ከፍተኛ አስተዋፅኦም አድርገዋል።እንዲያውም ይህ ዓመት ራሳቸውን በጣም ባተሌ ያደረጉበት ጊዜ እንደነበርም ያነሳሉ።ምክንያቱም ማታ የዋና ሥራቸውን አጠቃላይ ተግባር ሲያከናውኑ ያድሩና ቀን ላይ በአየር ንብረት ለውጡ ላይ የተለያዩ ተግባራትን ይከውናሉ።ይህ በመሆኑም ብዙ ለውጥ እንዳስመዘገቡና አገራቸውን ብቻ ሳይሆን አፍሪካን ጭምር እንዳስጠሩም ያወሳሉ።ለአስር ዓመትም ያህል ሠርተውበታል።
ቀጣዩ የሥራ ጉዟቸው የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ሲሆን፤ የፕሮጀክት መሪ ሆነው እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ አገልግለውበታል። በእርግጥ ይህ ሲሆንም የአየር ንብረት ለውጡ ሥራቸውን ሳይተው ነበር። አምስት ዓመታትም በዚህ ሁኔታ እንዳሳለፉ ያስታውሳሉ። ከዚያ በኋላ ግን ሙሉ ጊዜያቸውን በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ውስጥ ብቻ መስራቱን ተያያዙት። በእርግጥ ይህ ኤጀንሲ ለመመስረቱ አሻራቸውን ካሳረፉ መካከል አንዱ ናቸው።ምክንያቱም ይህ መስሪያቤት ሲቋቋም በጥናት ሲሆን፤ በወቅቱ በነበሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትዕዛዝ በተመረጡ አጥኝዎች አማካኝነት ነው።ጥናቱን እንዲያጠና የተደረገው ፋኦ ሲሆን፤ አንድ የሳውዝ ኢስት ኤዥያን ተሞክሮ ያለውና አንድ የአገር ሰው ተብሎ ተመርጦም ነው ተግባሩ የተከወነው።በዚህም ከአገር ውስጥ ከተመረጡት አንዱ ሆነው ጥናቱን በተሻለ አቅም እንዲሠሩት ሆነዋል።ያላቸውን አቅም አሟጠው በመጠቀም አገር የጣለችባቸውን ኃላፊነት ተወጥተዋልም።
ለአገሬ የምቆጥበው እውቀትና ጉልበት የለም የሚሉት ባለታሪካችን፤ አገሬ ለእኔ ያወጣችውን ወጪ ያህልም ባይሆን የተቻለኝን ላደርግላት ይገባል የሚሉ ናቸው። በዚህም ውጭ ብዙ አማላይ የሥራ አማራጮች ቀርቦላቸው ሊሄዱ ፈቃደኛ አልሆኑም። በዚህም ከዓመት በፊት ባሉ ዓመታት ሁሉ አገራቸውን በሁሉም መስክ ቀን ለሌት ሳይሉ ሲያገለግሏት ቆይተዋል። ከዚህኛው ሥራ በኋላም ቢሆን አገራቸው በምትፈልጋቸው ሁሉ እየገቡ ሲያገለግሉ ነበር።አሁንም እንዲሁ ምንም እንኳን በናይጀሪያ ማዕከላዊ ባንክ ውስጥ ዓለም አቀፍ አማካሪ ሆነው ቢሠሩም በምትፈልጋቸው ጊዜ ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን አጫውተውናል።በተለያየ መልኩ እያገለገሉም እንደሆነ ነግረውናል።
በእርሳቸው እምነት የገጠር ልማት ሠራተኛ ባይሆኑም፤ እንደዩኒቨርሲቲ ባሉ አገልግሎቶች ውስጥ ገብተው ባይጽፉም ለአገራቸው በሚማሩበት ሙያ ብቻ ሳይሆን ለመማር በሚሄዱበት ሁሉ ይሠራሉ። ከዚያም አልፈው ትውልዱ እንዲያውቅና እንዲማርበት እንዲሁም አገሩን በአወቀው ልክ እንዲሠራበት ለማድረግ ሙያቸውን በሚመለከት ገና ብዙ ይለፋሉ።ለዚህም ማሳያው ሥራ ሲቀጠሩ ጀምሮ አንዳንድ የጥናት ሥራዎችን መተግበራቸው ነው። ወደ መፀሐፍትነት የቀየሯቸውም አሉ። እንዲያውም ከአራት በላይ እንደሆኑም ያነሳሉ። ከዚያ ባሻገር መጣጥፎቹ ኦን ላይን ላይ ስለሚገኙ ብዙዎች ለሥራቸው መጠቀሚያ ያደርጓቸዋል። ለዚህ ደግሞ መነሻቸውን ወደው መሥራትንና የአገር ለውጥን አድርገው መሥራት መቻላቸው እንደሆነም ያብራራሉ።
ከአየር ንብረት ለውጡ ድርድር ጋር በተያያዘ ሌላው ሁለት መቶና ከዚያ በላይ ሆኖ ሲመጣ ኢትዮጵያ ግን በሁለት ተወካዮች ብቻ ነው የምትወከለው።እናም ሌላው እያረፈና እየተኛ እንዲሁም ተረዳድቶ ሀሳቡን እያቀረበ በሚቆይበት ኢትዮጵያን ግን ሳይተኙና በአንድ ቀን ከ100 በላይ ሴሽኖችን እየተካፈሉ ጭምር ለአገራቸው ትልቅ ዕድል ይሰጡ ነበር።እናም እርሳቸው በመንግሥት ባይወከሉም እንደመንግሥት ሠራተኛ እየሆኑ በማገዙ ተግባር ላይ በመሳተፋቸው እንዲሁም በሚዲያው ላይ ከፍተኛ ሽፋን የሚያገኙበትን አጋጣሚ በመፍጠር ሥራቸው ኃይል እንዲኖረው ማድረጋቸው አንዱ ለአገራቸው ያበረከቱት ነገር እንዳላቸው የሚሰማቸው መሆኑንም ያነሳሉ።በተለይም ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስና ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን በማማከርና የአየር ንብረት ለውጡ ላይ እንዲሠሩ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በመደገፉ የተቻላቸውን ማድረጋቸው ዛሬ ድረስ የሚደሰቱበት ሥራቸው እንደነበረም አጫውተውናል።
እርሳቸው ለአገሬ አሁንም እየሠራሁ ነው የሚሉት ነገር አላቸው።ይህም ዘወትር 10 ሰዓት ተነስተው የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በሚመለከት ከሚያውቋቸው ጓደኞቻቸው ጋር በኦን ላይን በመወያየት የመፍትሄ ሃሳብ በመቀያየር በምን መልኩ አገራቸውን መደገፍ እንዳለባቸው መረጃ በመለዋወጥ ለአንድ ሰዓት ያህል ይወያያሉ።
የሕይወት ፍልስፍና
እድገት ለማምጣት ሀብታም መሆን አይጠበቅም። መሠረቱ ልዩ ፍላጎትና ተግባር ከጸና በቀላሉ ይመጣል። አገርን ለመለወጥም ሥራና ፍላጎት ብቻ እንጂ በጀት አይደለም ሀብት የሚፈጥረው።እናም ሀብት ስለሌለን በጀት ስላልተመደበልን ይህንን አልሠራንም የሚሉ ሁሉ ተሳስተዋል የሚል እምነት አላቸው። በአካባቢው ያለው መሬት፣ ጉልበት፣ እውቀት ቢጠራቀምና በሥራ ቢተረጎም ድሃ አስተሳሰብ እንጂ፣ ድሃ አገር የሚባል ነገር አይኖርም። ምክንያቱም በአስተሳሰብ የላቀ ሰው ያለውን ነገር ያያል፤ ባለው ላይ ተመሥርቶ ለማልማት ይታትራል።ከዚያም ሀብቱን ያትረፈርፋል የሚለው አቋማቸው ነው።
አገርንም ሆነ ሕዝብን የሚያተልቀው ገንዘብ ሳይሆን ሥራ ነው። ትንሹን ይዞ በቅንጅትና ሰውን በሚለውጥ መልኩ ከተሠራበት የማይጠራቀም ገንዘብ አይኖርም። ለዚህ ደግሞ ያለንን መጠቀም፤ በሕብረት መሥራትና ለለውጥ በፍላጎት መነሳት አስፈላጊ እንደሆነም ያምናሉ። በተጨማሪ በራስ መተማመንም በሥራ የሚተረጎም ሀብትን ይሰጣል ብለው ያስባሉ።
የእርሳቸው አለቃም ከአለቃቸው የወሰዱት ተሞክሮም ለእርሳቸው ሌላው የሕይወት ፍልስፍና ነው።እነዚህ መርሆች ሦስት ሲሆኑ፤ የመጀመሪያው በሙያህ እስከ ጫፍ ድረስ ዝለቅ፤ እወቀውም የሚል ነው።ሁለተኛው በሙያህ ጠንካራ ሠራተኛ ሁን የሚል ሲሆን፤ ሦስተኛው በሙያ ባለቤትነትህ አንቱ ብቻ መባል ሳይሆን አንቱነትን ሊያላብሱ የሚችሉ ሥራዎችን መከወን ነው።እነርሱም ማቀድ፣ መጻፍና መተግበር እንዲሁም ሥራው መሬት መድረሱን ማረጋገጥ የሚሉ ናቸው።
ወቅታዊ ሁኔታውና እይታቸው
አሁን በአገራችን ላይ የተከሰቱት ችግሮች ትናንትም የነበሩ ናቸው። መነሻቸው ደግሞ እኩልነት፣ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የተሳሳቱ ትርክቶች፣ ማንነት፣ የአደጉ አገራት ተጽዕኖ መሆናቸውን ማንም ይገነዘበዋል።ለምሳሌ፡- እኩልነት ሲባል በሀብት፣ በብሔር፣ በጾታ ወዘተ ሊመነዘር ይችላል።እነዚህ ደግሞ ድሮም በትምህርት ቤት ጭምር የትግል መነሻዎች እንደነበሩ ይታወሳል።አሁን ሥር ሰደው በአሠራርና በአመራር ተደግፈው ዓይን አወጡ እንጂ የተለዩ አልነበሩምም ይላሉ። ለዚህ ደግሞ መድኃኒቱ ችግሮቹን ተቀብሎና አምኖ ለመፍትሄዎቹ መሥራት ነው።
በንጉሡ ጊዜ በሳል አመራርና የአገር ፍቅር ከመኖሩም በላይ አንድነት ኃይል ሆኖ ብዙ ነገሮችን በአገር ላይ ገንብቷል። ለዚህም ማሳያው ከአገር አልፎ የአፍሪካ አንድነትን ጭምር ማስተሳሰሩና የነፃነት ስሜትንም ማስተጋባቱ ነው። አገር የሚበለጽገው ሕዝብ ሲማርና ሕዝብ ሲመራ ነው የሚል አቋማቸውም በመተግበሩ አመራሩ በእውቀት እንጂ በስሚ ስሚ እንዳይሠራ እንዲሁም በራሳቸው የሚተማመኑ መሪዎች እንዲኖሩም አድርገዋል።ይህ ደግሞ የተግባር ሰው እንዲበራከት መስመር ቀዷል።በተለይም ከራሳቸው አልፈው በቅኝ ግዛት የተያዙትን አፍሪካውያንን እስከማስለቀቅ እና ፓን አፍሪካኒስቶች እንዲወለዱ ማድረጋቸው ብዙ ነገሮችን ለመቀየር ያስቻለ እንደሆነ ይገለጻል።እናም አመራር ላይ ከተሠራ ሕዝብ የተሻለ እንደሚሆን በሚገባ የታየበት ዘመን ነው። ይሁን እንጂ ከዚያ በኋላ ያሉት ዲፕሎማሲያዊውን ትተው ጦርነትን መርጠው አገርን በብዙ ነገር ፈትነዋታልም ይላሉ።
ከእርሳቸው በኋላ ያለው አመራር አገርን ከድጡ ወደ ማጡ የከተታት ሆኗል። በጥበብ የተያዘውን አመራር በጦርነት ለመፍታት ብቻ የሚጥርም ነው።በዚህም ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው የጦርነት አስተሳሰብ ዛሬን ከባድ አድርጎብናልም ባይ ናቸው።የመልካም አስተዳደር እጦት ጅማሬው ደርግ መሆኑም ለዚህ ነው።አመራሩ የአገር ፍቅር ቢኖረውም በስልጣኑ ከአገር ይበልጥ ማንም እንዲመጣበት አይፈቅድም።በዚህም የወሬ እንጂ የሥራ ሰው እንዳይኖር አድርጓል።ይህ ደግሞ የአገር ፍቅርን በእውቀትና በሥራ እንዳያግዘው በር ዘግቶበታል።በተለይም ከፍትህ እጦት ጀምሮ በርካታ ችግሮች በአገር ላይ መከራ እንዲደቅኑ ያደረገው ይህ ሁኔታ ስላልነበረ እንደሆነ ያነሳሉ፡፡
ከዚያ በኋላም ቢሆን ከ30 ዓመት በላይ ቅጥ ያጣ አመራር በመኖሩ አገር ሳይሆን ስልጣን ቦታ እንዲኖረው ተፈቅዷልና ብዙ ነገራችን ተወሰደ።ይህ ደግሞ የዛሬውን መከፋፈል፣ በግጭት ውስጥ መኖርን ወለደም፣ እንዲኖርበትም ፈረደ።በተለይ አቤት እንጂ ለምን የማይሉ ካድሬዎች ሰብስቦ መሾሙ አገር እዚህ ውጥንቅጥ ውስጥ እንድትገባ አደረጋትም ይላሉ።ስለዚህም አሁን በማንነትና በእኩልነት ሰበብ እንድንለያይና እንድንጨቃጨቅ የሆነውም ከዚህ የተነሳ ነው ባይ ናቸው።
እነዚህ ዕድሎች ለውጭ ጫናው በር የከፈቱ ናቸው። በአገር ውስጥ ጣልቃ ገብተው የፈለጉትን እንዲያደርጉም ፈቅደዋል። ምክንያቱም በአንድነት የምንመክትበት ጊዜ ላይ እንዳልሆንንና በራሳችን አቅም እንደማንከላከለው አውቀዋል። እናም እንደ አገር መሸነፍ የሚባል ነገር ያልታወቀባትን ለመፈተን ተነስተዋል።በተለያዩ ብሔሮች ተከፋፍላ የተለያየ አገር እንድትሆንና ብጥስጣሽ ክልሎች እንዲኖሯትም እያደረጓት ነው።በዚህም እንቢኝ ማለት ካልጀመርንና አንድነታችን ካላጠናከርን የማንመልሰው ፈተና ውስጥ እንደሆንን መገንዘብ አለብን። ለሀሳባቸው ተገዢ የሆኑ አካላትን አሁን እየሄድን ባለንበት ቅጽበት ልንሞግታቸው ይገባልም ብለዋል።እንደቀደሞው የአፍሪካ አንድነት መስራችነታችን ዛሬም ለሕዝብ አንድነት መሥራትና የተጫነብንን ተልዕኮ ማክሸፍ ይጠበቅብናልም ሲሉ ያሳስባሉ።
መልዕክት
አሁን ያለንበት ሁኔታ እጅግ አዳጋች ነው። ምክንያቱም አንድ በሆንበት ጊዜ ሊደፍሩን ያልሞከሩት አካላት ክፍተቶቻችንን ተጠቅመው ሊያጠቁን ቆርጠዋል። ሚዲያቸውን ከማሰለፍ አልፈው በኢኮኖሚ ጫና ለመፍጠርም ብዙ እየለፉ ናቸው። ከምንም በላይ በብሔር መከፋፈልን ለማስቀረት እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ስላልተመቻቸው እርሱን ለመዋጋትም የማይቆፍሩት ድንጋይ እንደሌለ በብዙ መልኩ አይተነዋል። እናም ልንደፈር የማንችልበትን ድልድይ መስራት ዛሬ ላይ ያስፈልገናልም ይላሉ።
የነጮች ሥራ ነዋሪውን በትነው ምድሪቱን የራሳቸው መዝናኛ ማድረግ ነው። አይደለም እንደ አህጉር እንድናስብ እንደ አገርም ማሰብ የለባችሁም እያሉን ነው። ለዚህ ደግሞ ተቀባዮቻቸው ብዙ ነገር በሕዝቡ ላይ አድርገዋል። ዘረኝነታቸው ዛሬም ጭምር ያለቀቃቸው በመሆኑ ቀደምት አባቶችና አመራሮች ስልታቸውን ተረድተው መፍትሄዎቹን ቀምረው የተግባር ሰው ሆነው እንደአፍሪካ አስበው መንቀሳቀሳቸው ለዛሬ የአፍሪካ ነፃነት ትልቅ አበርክቶ እንደኖራቸው ሁሉ ዛሬ ያሉትም አመራሮች ተግባራቸውን መረዳት አለባቸው። በተለይ ቀድሞ መረዳት ላይ ሊሠሩ ይገባል።መከፋፈሉንም ማስቆም ይጠበቅባቸዋል የሚለውም ሌላው መልዕክታቸው ነው።
ማህበራዊ የአስተሳሰብ ለውጥ ላይ መስራት ይገባል። ችግሮችን ከራስ ገሸሽ ከማድረግ መቆጠብና ችግሩን ተቀብሎ ለመፍትሄው መሥራት ያስፈልጋል። በተመሳሳይ የተሳሳቱ ትርክቶችን ምንጭ ማድረቅም ተገቢ ነው። ለዚህም የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑን በአግባቡ መጠቀም አስፈላጊ ነው። በተጨማሪ ተቃዋሚ ኃይሎች ዝም ብሎ ከመቃረን አስተሳሰብ መውጣት አለባቸው፤ ውሃ ቀጠነ ሊሉም አይገባም። ከዚያ ይልቅ መተማመንንና በውይይት ችግሮችን ለመፍታት መሞከር እንዲሁም ለአገር ሲባል መተውን መልመድ ይኖርባቸዋልም ሲሉ መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ።
በመጨረሻ ያነሱት ነገር ሚዲያው፣ ዳያስፖራው ከአጨብጫቢነት ወጥቶ ለአገር መሥራት አለበት የሚል ሲሆን፤ በተጨማሪ አመራሮች ከንግግራቸው የጀመረ አርአያነት ሊኖራቸው እንደሚገባም አሳስበዋል። ዘመናዊ ትምህርት የቀመሰው የሰው ኃይልን በአገር አስቀርቶ ማሠራትም ላይ ትልቅ ትግል ማድረግ እንደሚያስፈልግም ይመክራሉ።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን የካቲት 27/2014