በሙያቸው ሲቪል መሐንዲስ ናቸው። የፖለቲካ ሳይንስ ምሑርም ናቸው። የተወለዱት ደሴ ከተማ ልዩ ስሙ ሜጠሮ በተባለ ሥፍራ ነው። ጦሳ ተራራ ላይ ባለው በአባታቸው እርሻ ላይ እየቦረቁ ፤ የወሎዋን መዲና ሕዝብ ፍቅር እየኮመኮሙ አድገዋል።
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በእቴጌ መነን ትምህርት ቤት ገብተው መከታተል ቢጀምሩም አባታቸው በልጅነታቸው በማረፋቸው አሰብ ያሉ ዘመዶቻቸው ጋር ተላኩ። አስፋ ወሰን በተባለ ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን እስከ ስድስተኛ ክፍል ቀጠሉ። 7ኛ እና 8ኛ ክፍል ደግሞ አዲስ አበባ መጥተው ፍሬሕይወት በተባለ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።
ከፍተኛ ውጤት ስለነበራቸው በምርጫቸው ተግባረ-ዕድ ትምህርት ቤት ገብተው ለአራት ዓመታት ንድፍ ተማሩ። የተማሪዎች ኮንግረስ አባል ሆነው ከዛው ከተግባረ-ዕድ ዲፕሎማቸውን አገኙ።
በሲቪል ኢንጅነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪቸውን እንዲሁም በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን የማስተርስ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አግኝተዋል። በሙያቸው ካገለገሉባቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች መካከልም ግብርና ሚኒስቴር፤ የዱር ሙጫና እጣን ኮርፖሬሽን ይጠቀሳሉ። በተለያዩ የግል የኮንስትራክሽን አማካሪ ድርጅቶች ውስጥ ተቀጥረው በንድፍ ሥራና በማኔጀርነት ሠርተዋል።
በመቀጠልም የራሳቸውን የኮንስትራክሽን ንግድ ፈቃድ አውጥተው ወደ ኢንቨስተርነት ገብተዋል። እንግዳችን በዚህ ብቻ አልተወሰኑም፤ የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ ኮንትራክተሮች ማኅበርንም በመመሥረትና ማኅበሩን በፕሬዚዳንትና በምክትል ፕሬዚዳንትነት መርተዋል።
በርካታ የፖሊሲ ግብዓቶችን በማኅበሩ አማካኝነት ለመንግሥት በማቅረብ የዜግነት ግዴታቸውን የተወጡ ሰውም ስለመሆናቸው ይነሳል። በማኅበሩ አማካኝነት በአገር ልማት እንዲሁም በከተማ ፅዳት ላይ ባበረከቱት የጎላ አስተዋፅኦም ይታወቃሉ።
በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በመሳተፍ የሚታወቁት እኚሁ ሰው በአሁኑ ወቅት የራሳቸው ድርጅት ውስጥ የማማከር አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ። በታላቁ ህዳሴ ግድብ የሕዝብ አስተባባሪ ምክር ቤት አባል በመሆን ከፍተኛ የማስተባበር ሥራ ሲያከናውኑ ቆይተዋል።
ከዚሁ ጎን ለጎን የኢትዮጵያ አሠሪ ፌዴሬሽኖች ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ። በቅርቡ ደግሞ በአገራዊ የምክክር መድረኩ እጩ ሆነው ከቀረቡ ሰዎች አንዱ የነበሩ ሲሆን ምንም እንኳን ለኮሚሽኑ ከተመረጡት አመራሮች ውስጥ ባይካተቱም ከ40ዎቹ ምልምሎች ውስጥ በመሆን ከፍተኛ ድምፅ አግኝተው ነበር።
አዲስ ዘመን፡- የልጅነት ጊዜዎ ምን እንደሚመስል ይንገሩንና ውይይታችንን እንጀምር?
ኢንጅነር ጌታሁን፡- እኔ ተወልጄ እስከ ስድስት ዓመቴ ያደኩት ደሴ ከተማ በተለምዶ ሜጠሮ በተባለ አካባቢ ነው። ቤተሰቦቼ ሙስሊሞች ናቸው። ነገር ግን ከክርስቲያን ማኅበረሰብ ጋር ተቀላቅለን በመኖራችን ልዩነቱ አይታየኝም ነበር።
ክርስቲያኑ መስጊድ ሄዶ መድረሳ ይማራል፤ ሙስሊሙም ቄስ ትምህርት ቤት ይማራል። እነዚህ የእምነት ተቋሞች የስብዕና መሠረት እንድይዝ አድርገውኛል ብዬ አምናለሁ።
ያደግነው የሁለቱንም የሃይማኖት በዓላት በእኩል መንገድ እያከበርን ነው። ለምሳሌ ጳጉሜን 5 ቀን ሌሊት ከክርስቲያን ወገኖቻችን ጋር ወንዝ ሄደን እንጠመቅ ነበር። ቤተሰቦቻችን እንደባህል ሆኖ ለዘመናት ይዘውት የኖሩት ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የቆየ እሴት ነው።
የሙስሊሙም በዓል ሲከበር በተመሳሳይ መንገድ ክርስቲያን ወገኖቻችን ጋር አብረን እናከብራለን። የአንተ፤ የእኔ የሚባል ነገር የለም። ታቦት እንኳን የምንሸኘው አብረን ነው። መስጊዶች ሲገነቡ የምንሠራው በጋራ ነበር። ይህ የመቻቻል እሴት ዛሬ ድረስ በጣም ይደንቀኛል።
አሁን ያለው ትውልድ ይሄንን ቢያይና የዚያን ትውልድ ትውፊቶች ቢያስቀጥል ኖሮ ብዙ ችግር ውስጥ ባልገባን ነበር። ወሎ ደግሞ በተለይ የነበርኩበት አካባቢ ኅብረተሰብ ሁለቱንም እምነቶች ፍፁም ተቀባይ ነው።
በሌላ በኩል ለእድገቴ መሠረት ጥለውልኛል ብዬ የማስበው መምህራኖቼ ናቸው። እቴጌ መነን ስንማር መደብ ተሰጥቶን እርሻ እናርስ ነበር። አትክልትና ፍራፍሬ እንተክል ነበር። ከዚህ ባሻገር ሰኞ ጠዋት ስንገባ ምንም የድሃ ልጆች ብንሆንም ልብሳችንን አጥበን፤ ጥፍራችንን ቆርጠን ንፁህ ሆነን መገኘት አለብን። የሞራልና ሥነ ምግባር ትምህርቶች ከፍተኛ ዋጋ ነበራቸው። ይህም በተለይ ለእኔ ትልቅ መሠረት ጥሎልኛል። አገራዊና ማኅበራዊ ፍቅር፤ ታላቅን
ማክበር የመሳሰሉትን ነገሮች አስተምሮን አሳድጎናል። በነገራችን ላይ ደሴ ከሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች የመጡ ሰዎች ተከባብረውና ተቻችለው የሚኖርባት ሕብረብሔራዊ ድምቀት ያላት፤ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ነች። አሰብም ዘመዶቼ ጋር ሄጄ ስኖር ያየሁት ተመሳሳይ ነው።
ኤርትራውያንን ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያውያን በሞቀ ፍቅርና አየር በሰላም የሚኖርባት ከተማ ሆና ነው ያገኘኋት። አዲስ ዘመን፡- ገና ስምተኛ ክፍል ሳሉ ወደ ውትድርና ለመግባት አመልክተው እንደነበር ሰምቻለሁ።
በእዚያ እድሜዎ ሠራዊቱን ለመቀላቀል ያነሳሳዎት ምክንያት ምን ነበር? ኢንጅነር ጌታሁን፡- አንድ የቋንቋ አስተማሪዬ ኢትዮጵያ በዓለም ድሃ ከሚባሉት አገራት ተርታ መሆንዋን በመጽሐፍ ደረጃ መፃፉን፤ የችግርና የረሃብ ተምሳሌት ተደርጋ እንደምትቆጠር ሁልጊዜ ይነግረን ነበር።
ከመምህሩ የምሰማው ነገር ሁሉ ትልቅ ቁጭት አሳድሮብኝ ነበር። ስምንተኛ ክፍል ሆኜ ውትድርና ተቀጥሬ መንግሥት ለመገልበጥ አሮጌው አየር ማረፊያ ሄድኩኝ። እዚያ ስሄድ ‹‹ ደግሞ አንተ ምንድን ነህ?›› አሉኝ። አይ ወታደር መሆን እፈልጋለሁ አልኳቸው። አንተ እድሜም ሆነ ቁመትህ ገና ነው ብለው ሲያባርሩኝ አለቀስኩኝ። ‹‹በቃ ትደርሳለህ እኮ አትቸኩል›› አሉኝ። አልቅሼ ተመለስኩኝ። ከእድሜ በላይ አስብ ስለነበረ ነስር ይበዛብኝ ነበር። አገሬ ከዓለም በኢኮኖሚ ውራ መሆንዋ፤ ፊውዳል ሥርዓቱን አገሪቱን ኋላ ማስቀረቱ ፤ ለእኔ በዚያ እድሜ ከባድ ነበር።
ተግባረ-ዕድ ከገባሁም በኋላ የተማሪዎች ኮንግረስ አባል ሆኜ የተማሪውን ንቅናቄ ተቀላቅዬ ነበር። በተለይ ወደዚያ ትምህርት ቤት ተመርጠን የገባነው ከየትምህርት ቤቱ ጎበዝ የሆንን ተማሪዎች በመሆናችን በየወሩ 25 ብር ለአንዳንድ ነገር ይሰጠን ነበር። መሐል ላይ ያ ገንዘብ ቆመ። አብዛኞቹ ከክፍለሃገር የሚመጡ እንደመሆናቸው የሚኖሩት ቤት ተከራይተው ነው። የገበሬ ልጆችም በመሆናቸው እዚህ ብዙ ወጪ አለባቸው። ብሩ ሲቆም ትልቅ ቅሬታ ተፈጠረ።
አድማ ለማድረግ አስበን የነበረ ቢሆንም የበለጠ መንግሥት ጫና ያደርግብናል ብለን ሰጋንና በራስ እምሩ በኩል ጃንሆይን ለማግኘት ቀጠሮ ያዝን። በቀጠሮ መሠረት ንጉሱ ፊት ቀረብን ጉዳያችንን አስረዳን። ጃንሆይም በጣም ተቆጥተው በአስቸኳይ እንዲከፈለን አዘዙ። በዚህና በሌሎችም የተማሪዎች እንቅስቃሴ ላይ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን አደርግ ነበር።
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ ኮንትራክተሮች ማኅበርን በሚመሩበት ወቅት የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ ዝግጅት ባከናወኑት በጎ ሥራም ስምዎት ጎልቶ ይነሳል። እስቲ አሁን ደግሞ ስለዚህ ሥራዎ ምንነት ያስረዱን?
ኢንጅነር ጌታሁን፡- የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ወደ አፍሪካ ኅብረት ሊቀየር ዝግጅት ሲደረግ በወቅቱ የሊቢያ መሪ የነበሩት ሙሐመድ ጋዳፊ ‹‹ኢትዮጵያ ቆሻሻ ናት፤ ለአፍሪካ ኅብረት መቀመጫነት አመቺ አይደለችም›› እያሉ ሲያሳምኑ ስሰማ ከፍተኛ ቁጭት ተፈጠረብኝ።
በአገሪቱ ያሉትን ኮንትራክተሮች ሁሉ ሰበሰብኩና በእኛ ጊዜ ፤ በእኛ ትውልድ ታሪካችን፤ ቅርሳችንና መታወቂያችን የሆነውን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዴት ከዚህ ተነስቶ ሲሄድ ዝም እንላለን? ዋናው ችግሩ ምን እንደሆነ እንወቅና እንቅረፍ አልኳቸው። ሁሉም ደስ አላቸው።
ስለዚህ ያለንን ሃብት ፤ አቅም ሁሉ አሰባስበን የኅብረቱ መቀመጫ ከዚህ እንዳይሄድ ማድረግ አለብን አልኳቸው። ሁሉም ተስማሙ። ገንዘብና ማሽኖችን ሁሉ አዋጣን፤ በእኔ ሰብሳቢነት ኮሚቴ በማዋቀር የሚሠሩ ሥራዎችን ለየን። በዚያ መሠረት በዋናነት ከተማዋን ማፅዳት አለብን በሚል የከተማዋ እምብርት የሚባሉና ተስብሳቢዎቹ በሚያዘወትሩባቸው የከተማዋ አካባቢዎች ሁሉ እየተዘዋወርን አፀዳን። አሮጌ የሚባሉ አካባቢዎችን ቆርቆሮ ገዝተን አጠርናቸው።
ቀለም ቀብተን አስዋብናቸው። በተመሳሳይ የመንገድ አካፋዮችን ቀለም ቀባን። አስፋልቶቹን በሙሉ አፀዳን። የተቆፋፈሩ መንገዶችን ከቢሾፍቱ ቀይ አሽዋ አምጥተን ደፈን ቀይ ምንጣፍ አስመሰልነው።
ይህ ሁሉ ሲሆን የመንግሥት ሰዎች አያውቁም ነበር። በኋላ በወቅቱ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ የነበሩ ዶክተር ካሚል የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ የነበሩትን ዶክተር አርከበን ይዘው መጡ። እኔ ደግሞ አሁን ስካይላይት ሆቴል የተሠራበት ቦታ ቆሻሻ መጣያ ቦታ ሆኖ ስለነበር ያንን ቆሜ እያስጠረግኩኝ ነበር። ተዋውቀውኝ እየሠራሁት ስላለው ሥራ አመስግነው ‹‹ይህንን መንግሥትና አገር ከጉድ እያወጣችሁ ነው›› አሉ። ከዚያ በእሳቸው መኪና እየዞርን የተሠራውን ሥራ ሁሉ ተመለከተን። በዚህ ምክንያት በአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ ላይ እንድንታደም እድል ተሰጠን።
ያንን ሁሉ ቅሬታ ሲያነሱ የነበሩት ጋዳፊ ለመዝናናት ሶደሬ ሄደው ነበርና ሲመለሱ በተመለከቱት ነገር ክፉኛ የተደናገጡ ይመስለኛል። ያንን የማየት እድሉ አጋጥሞኝ ነበር። የኢትዮጵያ ኮንትራክተሮች ከአፍሪካ የሥራ አጋሮቻችን ጋር በመሆን የአፍሪካ ኅብረትን የሚወክል ሐውልት እንድንሠራ እድሉን ተሰጠን። አሁን ከቦሌ አየር ማረፊያ ስንወጣ ቦሌ ድልድይ አጠገብ የተሠራው አንዱ ሐውልት በኢትዮጵያ ኮንትራክተሮች የተሠራ ሐውልት ነው።
ከዚያ ወዲህ በብዙ መንገድና የማንም ፖለቲካ ድርጅት አባል ሳንሆን ይህችን አገር በነፃ ማገዝ አለብን ብለን የተለያዩ ሥራዎችን መሥራት ጀመርን። የተለያዩ አደረጃጀቶች ውስጥ በመግባት፤ በመምራት፤ በመተባበር የበኩሌን አስተዋፅኦ አበርክቻለሁ ብዬ አምናለሁ።
ከሁሉ በላይ ይህንን ማድረግ የሚችሉት ኢትዮጵያ ያስተማረቻቸው፤ ለወግ ማዕረግ ያበቃቻቸው፤ ቅን አሳቢ ኢትዮጵያውያን ምሑራኖች ናቸው። በዚህ መሠረት የየትኛው የፖለቲካ ድርጅት አባል ያልሆነ ንፁህ ኢትዮጵያዊ አስተሳሰብ ያላቸው አባላት ያሉበት ቲንክ ታንክ ማኅበር በ2000 ዓ.ም መሠረትን።
ይህ የምሑራን ስብስብ የኢትዮጵያ፤ የሠላም፤ የዲሞክራሲ ፤ የልማት ሕዝባዊ መድረክ ይባላል። የተለያዩ የፖሊሲ ግብዓቶችን ማቅረብ ችለናል። በዚያ ምክንያት የኢሕአዴግ ጉባኤዎች ላይ በተጋባዥነት ይጠሩን ነበር። በተለይ ሀዋሳ ላይ አቶ መለስ እያሉ የተደረገው ጉባኤ ላይ ሁሉም በእቅዱ ላይ በየእናት ድርጅቶቻቸው ተመካክረውበት መጡ። የመጡት ለማፅደቅ ብቻ ነበር። ነገር ግን አቶ መለስ ‹‹ተጋባዥ እንግዶችም አስተያየት መስጠት ትችላላችሁ›› ብለው እድል ሰጡ።
ያን ጊዜ እኔ እጄን አወጣሁና አራት ወሳኝ ጥያቄዎችን አነሳሁ። አንዱ የሥነ ሕዝብ ጥያቄ ነው፤ የኅብረተሰብ ምጣኔ እቅድ እዚህ ውስጥ አላየሁም። ይሄ ነገር እቅድ ውስጥ ካልተያዘ ያለው የአገሪቱ ኢኮኖሚ አቅም ይሸከመዋል ወይ? የሚል ነው።
ሌላኛው ጫት ከፍተኛ ገቢ ከሚያስገቡ ምርቶች አንዱ ቢሆንም ለምግብ ፍጆታ የማይውል፤ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የማያገለግል፤ ጊዜ አጥፊ፤ የእርሻ መሬቶችን ያስለቀቀ ነው። ቤቶች እየተዘጉ መቃሚያና ማደንዘዣ እየሆኑ ጤና የሚነሳ ከመሆኑ አኳያ ለምን በዚህ ዙሪያ መንግሥት አቋም አይወስድም? አልኩኝ።
ሶስተኛው የባቡር ትራንስፖርት የሚመለከት ሲሆን አራተኛው የመሬት አጠቃቀምና ፕላን ላይ የተመሠረተ ነው። እኔ ፖለቲካ ውስጥ ስለሌለው ጫና መፍጠር አልችልም፤ ግን ደግሞ በአጠቃላይ የሰጡኝ መልስ ከአንድ መሪ የሆነ ሰው የማይጠበቅ ነበር። በባቡር ትራንስፖርት ጉዳይ በሚመለከት ‹‹ አንድ የጭነት መኪና በአሁኑ ጊዜ ስንት ቤተሰብ የሚያስተዳድር ነው። ባቡር ትራንስፖርት መዘርጋት ማለት የእነሱን ጉሮሮ መዝጋት ነው›› የሚል መልስ ሰጡኝ።
በሥነተዋልዶ ላይ ደግም ‹‹አዎ በደርግ ጊዜ አንድ የሥነ ሕዝብ ጽሕፈት ቤት ተቋቁሞ ነበር፤ ማዕከላዊ ፕላን ጥጉን ይዞ ተቀምጧል፤ አሁን ምን እየሠራ መሆኑን አላውቀም›› አሉኝ። ይሁን እንጂ ሲወለድ አፍና ሆድ ብቻ ይዞ አይደለም የሚወጣው እጅግና እግር ይዞ ይመጣል። ሕዝብ ሃብት ነው ሲሉ በስብሰባው የታደመው ሁሉ አንገቱን አቀረቀረ። እኔም ብሆን እየሰጡት ባለው ምላሽ ደስተኛ አልነበርኩም።
በዚህም ሳያበቁ ‹‹ጫትም ቢሆን ባለፈው ዓመት 100 ሚሊዮን ለአገራችን ገቢ የሚያመጣ ስለሆነ እኛ መከልከል አንችልም፤ ዛሬ ላይ ደግሞ ኅብረተሰቡ ራሱ የሚጎዳውንና የማይጎዳውን ያውቃል›› ሲሉ መለሱልን። በተለይ ሥነ-ሕዝብን በተመለከተ የመለሱት ምላሽ በጣም ነበር ያሳዘነኝ ።
‹‹ የአገራችን እናቶች ዛሬ እኛ አንመክራቸውም፤ እንዳውም እኛን ያስተምሩናል፤ እንዳውም እናንተ አላያችሁም እንጂ ከእኛ የባሰ ቁጥር ያለባቸው የአፍሪካ አገራት አሉ፤ የአዲስ አበባ ሕዝብ ቁጥር 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ነው፤ እሱም ቢሆን የሚሞተውን ያህል ነው የሚወለደው›› የሚል ሁላችንንም አንገት ያስደፋ ምላሽ መስጠታቸው በጣም ነበር ያስገረመኝ።
ከሰዓት በኋላ በነበረው ስብሰባ ከእነሱ አንዱ ተነሳና በአዲስ አበባ ቆሻሻ ዙሪያ ለጠየቀው ጥያቄ ሲመልሱ ‹‹አዲስ አበባ ምንታድርግ፤ ሦስት ሚሊዮን ሕዝብ ተሸክማ!?›› ካሉ በኋላ ጠዋት የተናገሩት ትዝ ሲላቸው መልሰው ‹‹ይሁን እንጂ ጠዋት 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚሆነው አዲስ አበባ ሲሠራ ውሎ ማታ ተመልሶ ከአዲስ አበባ ይወጣል›› አሉ። ይሄ የሚያሳየው ግልፅነት ያለመኖሩን ነው።
ምሑራንን ያለማዳመጥ፤ ከምሑራን ጋር በቅርበት ያለመሥራት፤ ሁልጊዜ የፓርቲ አባል ካልሆነ በስተቀር ያለመቀበል ችግር መኖሩን ነው። የእኛ የምሑራን ፎረም በርካታ ሥራዎችን ሠርቷል። የኢትዮጵያ ሚሊኒየም አከባበር ላይ ይህንን ከሚያከብረው አካል ጋር በመተባበር ምክረ ሃሳብ በመስጠት የበኩላችን ሚና ተጫውተናል።
በከተማ ፅዳት፤ በባዕድ ባህል ወረራ፤ በተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀምና በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ በሚዲያና መድረኮችን በማዘጋጀት ተከታታይ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ሠርተናል። ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ተከስቶ በነበረበት ጊዜ መንግሥት ነጋዴውን ያስርና ያከማቹትን ይወስድ ስለነበር በዚህ ጉዳይ ላይ የውይይት መድረክ በማዘጋጀት፤ የመፍትሔ ሃሳብ በማመንጨት የዋጋ ግሽበቱ እንዲስተካከልና ችግሩ እንዲፈታ ጥረት አድርገናል።
አዲስ ዘመን፡- በአገራዊ ምክክር መድረኩ መታጨትዎት የፈጠረብዎት ስሜት ምንድን ነው? በተለይ ካለው ከፍተኛ ኃላፊነት አኳያ ቢመረጡ ኖሮ በግልዎ ፈታኝ ይሆንብኛል ብለው ያሰቡት ነገር የለም?
ኢንጅነር ጌታሁን፡- በነገራችን ላይ በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ አሠሪ ፌደሬሽኖች ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ነኝ። በዚህም የአሠሪዎችን ብቻ ሳይሆን የመንግሥትን ድምፅ ለዓለም ማኅበረሰብ እናሰማለን። ይህ ለአገር ትልቅ ጥቅም የሚሰጠው ነው። ከጠየቅሽኝ ጥያቄ አንፃር በኮሚሽኑ አመራርነት ባልመረጥም 42 ውስጥ ገብቼ ነበር።
የጠቆሙኝና ድምፅ የሰጡኝን ማመስገን እወዳለሁ። ከዚህ በላይ ለዚህች አገርና ሕዝብ ብሰራ ደስ ይለኛል። ይህ መድረክ በአገሪቱ እንዲካሄድ አስቀድመን ጥያቄ የጠየቅነው እኛ ነን። 16 ምክረሐሳቦችን ለአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ስንሰጥ የችግሩ ባለቤት የሆነው ሕዝብ በቅርብ ተገናኝቶ፤ ሕዝባዊ የምክክር መድረኮችን በማዘጋጀት ችግሮችን እንዲፈታ መደረግ አለበት የሚል ነው። በ2009 ዓ.ም ያ ሁሉ ችግር ሲከሰት ቀድመን ምክረ ሐሳብ የሰጠነው እኛ ነን።
አሁን ምክክር እንዲደረግ መንግሥት ሃሳቡን ያቀረበው ጊዜውን ጠብቆ ነው። መመካከር የምንችለው መጀመሪያ ትልቁ ነገር ሕዝባዊ ተግባቦቶች ሲኖርና በሃሳቦች ስንቀራረብ ነው ።
ለዚህ ደግሞ መከባበር መኖር አለበት፤ ፊታችን ላይ ለውይይት እንቅፋት የሆኑትን ነገሮች ማስወገድ አለብን። ይሄ ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃም በርካታ ተሞክሮዎች አሉ። ከዚህ ቀደም እንደሚታወቀው በ1997ቱ ምርጫ የታሰሩ የቅንጅት አመራሮች እንዲፈቱ ለማድረግ በእኔ አገናኝነት ፊታውራሪ አመዴ ለማ፤ ደራሲ ማሞ ውድነህ፤ ሲስተር ሮዛና ዶክተር መኮንን የሚባሉ የአገር ሽማግሌዎች የመጀመሪያው ጠንሳሽ ሆነው ከሕወሓት አመራሮች ጋር ውይይት አደረጉ።
የታሪክ ሽሚያና ቅሚያ ነው እንጂ እነዚህ ሰዎች ባለውለታ ናቸው። ፊታውራሪ አመዴ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር ገብተው ‹‹ መሳም ያልመለሳትን ሚስት ዱላ አይመልሳት›› በማለት ሁሉ ነገር በምክክርና በፍቅር ካልሆነ በስተቀር በኃይል የሚሆን ነገር እንደሌለ በድፍረት አስረድተዋል። እነዚያ እሴቶቻችንን ይዘን የምክክር መድረክ እንዲኖር ሃሳብ ስናቀርብ ኖረናል።
ወደዚህ ፅንፍ ወደያዘ መጋፋፋት የሄድነው በቅርብ ባለመነጋገራችን ነው። በታሪኮቻችን ላይ ፤ በአብሮነቶቻችን ላይ ፤ እሴቶቻችን ላይ ወደዚህ አቅጣጫ እንድንመጣ ሌላው ቢቀር ምሑሩ ድርሻውን ባለመወጣቱ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ችግር አንፃር የዚህ የምክክር መድረክ መፈጠሩ ፋይዳው ምንድነው ብለው ያምናሉ?
ኢንጅነር ጌታሁን፡- ይሄ የምክክር መድረክ አስፈላጊነቱ በጣም ወሳኝ ነው። ተግባቦቶችን ይመጣል፤ አንድ ወደ ሆነ ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊ አቅጣጫ እንዲመጣ ያደርገናል። በአገራችን ሰላም እንዲሰፍን ያስችላል፤ ልማታችንን ያፋጥናል።
ስንወያይ፤ ስንመካከር የሚያጣሉንን ችግሮች ፈተን በሚያስማሙት ነገሮች ላይ በጋራ መቆምና መሥራት እንችላለን። ደግሞም ማንም ቢሆን በሕዝብ ውይይት የመጣን ሃሳብ አልቀበልም ሊል አይችልም። ‹‹እኔ ያልኩት ካልሆነ›› የሚለው ነገር ይቆማል ማለት ነው። ስለዚህ በምክክር ያውም ታላቅ በሆነው ሕዝብ የሚወጡ ምክረሃሰቦች ተቀባይነት አግኝተው ወደ ሥራ ሊገቡ ይገባል እንጂ በፖለቲካ ኃይሎች ማንም አይሆንም ብሎ አቋም ሊይዝ አይገባም።
በእምነትም ዙሪያ ይመካከሩ፤ በፖለቲካ አቋም ይመካከሩ፤ በሕገ መንግሥትም ዙሪያ ይመካከሩ የሕዝብን ድምፅ መደመጥ መቻል አለበት። ኮሚሽኑ ከመቋቋሙ በፊት ካውንስል እንዲሆን ሃሳብ አቅርበን ነበር። ይህ ካውንስል 30 እና 40 አባላት ያሉበት ሆኖ እነዚህ ኮሚሽነሮች በየጊዜው ቋሚ የሆነውን ሥራ እንዲሠሩ፤ ሌላው አባል ደግሞ በየጊዜው በሚቀርቡ ጉዳዮች ላይ እየተወያየ ምክረ ሃሳቦችን እንዲለግስ፤ አቅጣጫዎችን በማየት የጎደሉትን በማማከር እንዲሠራ ቢደረግ የሚል ሃሳብ አንስተን ነበር። ምክንያቱም ይህ ኮሚሽን የተሰጠው ኃላፊነት ትልቅ ነው። የእዚህች አገር ተስፋ እዚህ ላይ ነው።
ስለዚህ የምሥራቁን ከምዕራቡ፤ የሰሜኑ ከደቡቡ ማቀራረቢያ መንገድ ማለት ነው። ስለዚህ ይህ ኮሚሽን በሰለጠነ አግባብ መመራት አለበት። በሰከነ መልኩ ሊመራም ይገባል። የተመረጡ ኮሚሽኖች በቅድሚያ አርዓያነት ያለው ማንነት እንዳላቸው በተግባር ሊያስመሰክሩ ይገባል ባይ ነኝ። እነሱ በዚያ ላይ የማስተዋወቅ ሥራ ባይሠሩም ምቹ ምህዳር ለኅብረተሰቡ እንዲፈጠር ማድረግ አለባቸው። ከዚያ ሥራው በቅንነት እንዲከናወን በተጨማሪም ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ፤ ሲቪክ ማኅበራት፤ የሃይማኖት አባቶች፤ የአገር ሽማግሌዎች መሳተፍ ፤ መደገፍ አለባቸው። ኮሚሽኑም በዚህ ዙሪያ ላይ ይሠሩልኛል ያላቸውን ሰዎች እየጠራ እንዲያማክሩት ፤ ከዚህ በፊት የነበራቸውን ልምድ እንዲያካፍሉት ማድረግ መቻል አለባቸው።
ይሁንና በሥራቸው በምንም መልኩ ጣልቃ እንዳይገባባቸው እና ጫና እንዳያሳድርባቸው መደረግ መቻል አለባቸው። ምክንያቱም ጣልቃገብነት እስካሁን የተለፋበትን ሊያበላሽ ይችላል። ለመንግሥትም፤ ለፖለቲካ ፓርቲዎችም ፤ ለእምነት ተቋሞችም ለሁሉም የምለምነው ይህንን ድሃ ሕዝብ እንየው ፤ እዚህ ያደረሰንን፣ ያስተማረንን ፣ የአገራችንን ነፃነት አስጠብቆ ያቆየንን ወገን ሁልጊዜ መከራውን አናብዛበት።
እኛ ከዚህ እናውቃለን እያልን የምንጭራቸው ነገሮች ነገ ሌላ መዘዝ እንዳይመጡ መተባበር አለብን። በዚህ አጋጣሚ እኛም ለማገዝ ዝግጁ መሆናችንን ማሳወቅ እፈልጋለሁ። አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ ሰዎች የምክክር ኮሚሽኑ መቋቋም ወቅታዊነትና በምክክሩ የሚሣተፉ አካላት ላይ ጥያቄ ያነሳሉ። በተለይም ጦርነቱ ሙሉ ለሙሉ ባልቆመበት፤ የፖለቲካ ችግሮች ባልተፈቱበት ሁኔታ አሁን ሊከናወን አይገባም ብለው ይከራከራሉ።
እርስዎ በዚህ ሃሳብ ላይ ያለዎት አቋም ምንድን ነው? ኢንጅነር ጌታሁን፡- እኔ ማንም ይሁን ማን ኢትዮጵያዊ ሃሳቡን የመግለፅ ፤ ከፅንፈኝነትና ከጦረኝነት መለስ በመድረክ ላይ ችግሩን የመፍታት መብቱ እንደሆነ አውቃለሁ። ግን በእሱ ላይ ሊደርስ የማይፈልገውን ነገር በሌላው ላይ ማድረስ እንደማይገባው ነው የማምነው።
እኔ አውቅልሃለሁ፤ እኔ ነፃ አወጣሃለሁ፤ እኔ ብቻ ነኝ የአንተ ተጠሪ ፤ ያልኩህን ብቻ ስማ የሚባል ነገር በዚህ የሰለጠነ ዘመን አይሠራም። ሁልጊዜ መሣሪያና ገንዘብ ያለው ጀብደኛ ነው፤ ትምክህተኛ ነው። ገንዘብ ስላለው በገንዘቤ እወጣዋለሁ ስለሚል፤ መሣሪያም ያለው በመሣሪያው እንደሚያሸንፍ ስለሚያምን ነው። ከጦርነቱ በፊት የአማራና የትግራይ ማኅበረሰብን ለማቀራረብ ሁሉንም ነገር ጨርሰን ጉዞ ልናደርግ ስንል ነው በመጀመሪያ ኮረና ገባ፤ ከዚያ ጦርነቱ ተጀምሮ ተስተጓጉሎ ቀረ። በእኔ እምነት ሕዝባዊ የምክክር መድረኮች የማይፈቱት ነገር የለም። ‹‹እኔ አውቅልሃለሁ›› የሚሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከዚህ ተግባር መቆጠብ አለባቸው።
መገፋፋት ለማንም አይጠቅምም፤ ለሁሉም የሚበጀው መደማመጥ ነው። አሁንም የትግራይ ወገኖቻችን ፤ በወዲህም ያለው አማራ ወገኖቻችን መላውም የኢትዮጵያ ሕዝብ በዚህ
ጦርነት ምክንያት ትልቅ ኪሳራ ውስጥ ገባ እንጂ ያተረፈው ነገር የለም። ስንት ዓመት የተገነባ ሃብት ነው ያጠፋው ? ከዚያ በላይ ውድ የሆነውን የሰው ልጅ ነው ያጣነው። ይህ ትልቅ ኪሳራ ነው። ይህ ከዚህ በኋላ ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም። ስለዚህ ሁሉም መሣሪያቸውን ማስቀመጥ ፤ በመሐላቸው እውቀቱና ክህሎቱ ያላቸውና ወገንተኛ ያልሆኑ ሰዎች ገብተው ማሸማገል፤ ወደ እርቅ መምጣት፤ መስማማት መቻል አለባቸው። እኛ እኮ በኬኒያ የሰላምና የእርቅ ኮሚሽን ላይ ሃሳብ ስንሰጥ ነበር። ምክንያቱም የኮፊአናን መልዕክተኛ እና የእኛ ፎረም አባል የሆኑት አምባሳደር ብርሃኑ ዲንቃ የኮኒያን ሰላምና እርቅ ኮሚሽን የመሩት እሳቸው ናቸው።
እኛ ጋር በየጊዜው እየተሰበሰቡ ሃሳብ እየወሰዱ ይሄዱ ነበር። ይህንንም ተሞክሮ ኢትዮጵያ ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ ስንነጋገር ነበር። ኢትዮጵያ ምሑር አላጣችም፤ ሰው አላጣችም። ግን ምሑር አግላይ ጊዜ ላይ ደርሰናል። አንድ ራሳቸውን የሚሸጡና ጥገኛ የሚሆኑ አንዳንድ ምሑራኖች አሉ። ይሄ አግባብ አይደለም። ሰው መሆን መቻል አለብን።
ሕዝባችንን ከችግር በማውጣት ማኅበረሰባዊ ግንኙነት አጠናክረን በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ ሰላም በማስፈን ለሌሎች አገራት ምሳሌ መሆን የምንችል ሰዎች ነን። የአባቶቻችንን ታሪክ ማስቀጠል አለብን። ስለዚህ የትግራይ ኃይሎችም ሆነ ሌሎች ነፍጥ ያነገቡ አካላት ጋር ያለው ችግር በውይይት የሚፈታ ነው ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- ግን ደግሞ ቁርሾ ባልበረደበት፤ የጦርነቱ ቁስል ባላገገመበት ሁኔታ እነዚህ ኃይሎች ለመደራደር ፍላጎት ባላሳዩበት ሁኔታ ምክክሩ እንዴት ውጤታማ ሊሆን ይችላል?
ኢንጅነር ጌታሁን፡- ለእኔ ይሄ አመለካከት ስህተት ነው። እስከመቼ ድረስ ነው ቁርሾው እስከሚደርቅ የሚጠበቀው? የተጎዱ ማኅበረሰብን መደገፍ፤ ካሳ መስጠት ፤ ማቋቋም ነው የሚበጀው። አለበለዚያ ያንን ሁልጊዜ እየደጋገሙ ማንሳቱ ችግሩ እየጨመረ እንዲሄድ ነው ያደረገው።
አስቀድሜ እንዳልኩሽ እኛ ይሄ እንዳይሆን በ2009 ዓ.ም ለአቶ ኃይለማርያም ከሰጠነው ምክረ ሃሳብ አንዱ እንዲህ አይነት ችግሮች ከመፈጠራቸው በፊት በሕዝባዊ ምክክር ይፈቱ በሚል ነው። ስለዚህ አሁን ብንቆይ ሌላ ቁርሾ መፈጠሩ አይቀርም። ይሄ መፍትሔ አያመጣም።
ዋናው ትልቁ ለዚህ መገፋፋት የውጭው ተፅዕኖ በመሆኑ መገፋፋትን ትተን ይቅር መባባል መቻል አለብን። የሞተ ሞቷል፤ የጠፋ ጠፍቷል፤ ልንመልሰው አንችልም። ግን ደግሞ ለተጎዱ ወገኖቻችን አስፈላጊውን ካሣና ድጋፍ ማድረግ አለብን። ይህንኑ ለማድረግ ደግሞ እኛ አንድ አገራዊ የእርዳታ መልሶ ማቋቋም ኮሚቴ መሥርተናል።
የተጎዱትን ሁሉ ለመደገፍ መንግሥት አቅም ስለማይኖረው እኛ መደገፍ አለብን ብለን ነው የተነሳነው። አሁን ድረስ ቤታቸው በመቃጠሉ ዋሻ ውስጥ የሚኖሩ አሉ። እንዳልሽው እነዚህ ሰዎች ምሬታቸው ከፍተኛ ነው። ግን እስከወዲያኛው ሐዘናቸውና ቅሬታቸውን ይዘው ሊቀጥሉ አይገባም።
ያለማወቅ ፖለቲካ ያመጣው ችግር ነው። ስለዚህ ፖለቲካ የሚፈታው በውይይት ነው። አምባገነንነት እኮ አይሠራም። ሁልጊዜ ጠበንጃና መሣሪያ ነካሽ ሆነን ልንኖር አንችልም። አንድ ቀን እኮ መሬቱ ሁሉ ሊከዳን ይችላል።
ስለዚህ ጥፋት ጠፍቷል፤ ወድሟል፤ ሰው ከመኖሪያ ቀየው ተፈናቅሏል፤ አሁንም የበለጠ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ገብተን ወደባሰ ችግር ውስጥ ከመውደቃችን በፊት በማኅበራዊ ውይይት ነገሮችን መፍታት መቻል አለብን።
ትግራይም ድረስ ሄዶ ማነጋገርና እነሱም የሠሩትን ሥራ አምነው ይቅርታ እንዲሉ፤ ከወዲህም ስህተት ተሠርቶ እንደሆነ ይቅርታ መጠየቅ መቻል አለበት። በይቅርታ ነገሮችን ማግባባት መቻል አለብን።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ አንፃር የአፍሪካ አገራት ልምድ ምን ይመስላል? ከእነዚህ አገራት ምን ተሞክሮ ልንወስድ እንችላለን ብለውስ ያምናሉ?
ኢንጅነር ጌታሁን፡- እኔ የኬኒያውም ቢሆን በሕዝብ ውይይት የተፈታ ችግር ባለመሆኑ ለእኛ ጥሩ ተሞክሮ ይሆናል ብዬ አላምንም። በተባበሩት መንግሥታትና በመሳሰሉት አካላት ለጊዜው እንዲበርድ የተደረገ እንጂ ወደፊት ሊፈነዳ የሚችል እንደሆነ ነው የሚሰማኝ።
የሩዋንዳም እንደዛው ነው፤ በመሣሪያ ኃይል አሸናፊነት የመጣ መረጋጋት ሰላም ነገ ጠዋት ይፈነዳል። ደቡብ አፍሪካ በትክክል በእርቅ ተዘግቷል ። ያሉ ቅሬታዎችም ግን አሉ፤ አሁንም ወደበለጠ መካረር ሳይሄዱ መግባባት መቻል አለባቸው። በነገራችን ላይ ውይይት፤ ምክክርና እርቅ አንድ ጊዜ ብቻ የሚከናወን አይደለም። ሁልጊዜ የሚመጡ ችግሮችን እየተፈታ መሄድ አለበት።
አንድ ጊዜ ተፈጠረ ብለሽ ልትተዪው አትችዪም። አንድ ቀን ሳይታሰብ የሆነ ቦታ ላይ ሊፈነዳ ይችላል። ስለዚህ ሁልጊዜ ጥንቃቄና ክትትል ይፈልጋል። የቱኒዚያው ጥሩ መልክ አሲይዞላቸዋል። በተረፈ ግን ሁልጊዜ ድህነት ካለ መገፋት ካለ፤ መገለል ካለ፤ አሳታፊነት ከሌለ የፈለገ ምክክር ቢኖር ውጤታማ ሊሆን አይችልም። ሊሆን የሚችለው ተግባብተን አንድ በሚያደርጉን ነገሮች ላይ መስማማት ነው። ከሁሉ በላይ ደግሞ የጋራ ቃልኪዳናችን የሆነውን ሕገ መንግስት አስተካክለን እንደ ቅዱስ መጽሐፍ ልንመራበት ይገባል።
እርግጥ ነው በጊዜ ሂደት እንደ እድገታችን ሊሻሻል ይችላል። ግን አሁን ያለውን በማስተካከልና ወጥ አመካከት ኖርን ማፅደቅ መቻል አለብን። ይህንን የምለውም ለዚህ ሁሉ ችግር የዳረገን ይሄ ሕገመንግስት ነው ብዬ ስለማምን ነው። ሕገመንግስቱ ሲፀድቅ እኔም ኢትዮጵያ ውስጥ ነበርኩኝ ግን ሃሳብ አልሰጠሁበትም። ብዙ ሰው አልሰጠም።
በፖለቲካ ተሳትፎ ነው የተሠራው። ሕዝብ አስቸግሮኛል ሲል ደግሞ ቶሎ መንግሥት መቀየር ነበረበት። ሕገመንግሥት የሁሉንም መብት የሚያስጠብቅ ፤ ሁላችንም የተግባባንበት ሰነድ ነው መሆን ያለበት። ኢሕአዴግ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ እስካሁን የዘለቀው ሕገ-መንግስት ነው። አሁንም ኅብረተሰቡ እየተገፋና እየተበደለ ነው። ስለዚህ ውሳኔውን ለሕዝቡ መስጠት ነው ያለብን ብዬ ነው የማምነው።ሕገመንግሥቱ ሁሉንም አሳታፊ ካደረገ አስቀድመን ያነሳናቸው ችግሮች ይፈጠራሉ ብዬ አላምንም። ቁልፉ ነገር ሕገመንግስቱ ማሻሻል ነው።
አዲስ ዘመን፡- በአገሪቱ ሰላም ባልሰፈነበት ሁኔታ የምክክር ኮሚሽኑ ተንቀሳቀሶ ኅብረተሰቡን ለማወያየትና ውጤታማ ሥራ ለማከናወን እንቅፋት አይሆንበትም ብለው ያስባሉ?
ኢንጅነር ጌታሁን፡- እንግዲህ መንግሥት አንድ ነገር ማድረግ መቻል እንዳለበት አምናለሁ። እነዚህ ጫካ ውስጥ ያሉትም ሆነ በሰሜኑ የአገሪቱ አካባቢ ያሉ ወገኖች ሁልጊዜ ተካረን መኖር ስለሌለብን ወደ ሰላሙ መንገድ እንዲመጡ መግባባት መቻል አለባቸው። መቶ በመቶ ባይግባቡም በከፊሉ ከተግባቡ በቀሪው ጉዳይ ላይ በሕዝብ ውሳኔ የሚወሰን ሊሆን ይችላል።
ስለዚህ እነዚህን ድርጅቶች ጥያቄያቸው ምንድን ነበር? ለምን በጊዜ አልተፈታም?
አሁንስ ለምን አይፈታም? የሚሉትን ነገሮች መረዳት ያስፈልጋል። በሕግ አግባብ እንዲተዳደሩ ማድረግ ያስፈልጋል። ጫካ መሽጎ ይሄ መንግሥት ካልወረደ ወደ ሰላም አልመጣም ካለ ደግሞ ውሳኔ የሚሰጠው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። ሕዝቡ እየተሰደደ፤ እየተራበና እየሞተ እኔ ያልኩት ካልሆነ የሚል የፖለቲካ ኃይል ሊኖር አይችልም።
በአጠቃላይ ግን በምክክሩ ሕዝቡን ባለቤት ካላደረግነው የአገሪቱ ችግሮች ሊፈቱ አይችሉም። የምናሳትፈው ግን በአንድ አካባቢ ወገንተኝነት ላይ ተመሥርተን ሳይሆን በኢትዮጵያዊነት መንፈስ ብቻ ነው።
ምሑራኖች በግላቸው ተጠራርተው የውይይት መድረክ በማዘጋጀት በምክር ለዚህ ኮሚሽን ምክረ ሃሳብ መስጠት መቻል አለባቸው።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ሥም ከልብ አመሰግናለሁ።
ኢንጅነር ጌታሁን፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን የካቲት 26 /2014