የኢትዮጵያ ሆቴል አትሌቲክስ ክለብ የትጥቅ እና የስፖርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገለት። ድጋፉን ያደረገው የሚስትቡሽ ኮርፖሬሽን ለድጋፉ ከ1ነጥብ8 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንዳደረገበትም ታውቋል።
ወጣትና ተተኪ አትሌቶችን ለስፖርቱ ምቹ ከሆኑ ስፍራዎች በማውጣት በስልጠና ደግፎ ለአገር ከሚያበረክቱ ክለቦች መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ሆቴል አትሌቲክስ ክለብ ሲሆን፣ ክለቡ በሆቴሉ በጀት የሚንቀሳቀስ ነው።
ድጋፉን የተረከቡት የኢትዮጵያ ሆቴል ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሉቀን ዓለሙ ድጋፉ ክለቡ ተተኪ አትሌቶችንም ለማፍራት ለሚያደርገው ጥረት እንደሚያግዝ እና ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጠቁመዋል።
ክለቡ ባለፉት ዓመታት በሆቴሉ በጀት ድጋፍ ሲደረገለትም ቆይቷል። በተያዘው በጀት ዓመት በሚስትቡሽ ኮርፖሬሽን 1ነጥብ8 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የትጥቅ እና ቁሳቁስ ድጋፍ የተደረገለት ሲሆን፣ ድጋፉ በሁለት ዙር የሚፈጸም ነው፤ በመጀመሪያው ዙር ለአትሌቶች ውድድር ትጥቆች፣ የውድድር ወጪ እንዲሁም የቢሮ መገልገያ ቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል። በሁለተኛው ዙር ደግሞ ለአትሌቶች የሚሆኑ የቤት ውስጥ መለማመጃ የሚሆኑ ማሽኖች፣ የመም የውድድር መሮጫ ጫማዎችን ያካተተ ነው።
ድጋፉን ያስረከቡት የኮርፖሬሽኑ ማናጀር አኪማሳ አሳኮ፤ ተቋማቸው ለክለቡ ድጋፍ በማድረጉ ደስተኛ መሆኑን አስታውቀዋል። ተቋሙ በሚያደርገው የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ወጣት አትሌቶችን እንደሚደግፍ ጠቅሰው፣ ወጣቶቹ ሕይወታቸው ተቀይሮ አገራቸውንም ወክለው በተለያዩ ውድድሮች ለመሳተፍ ለሚያደርጉት ጥረት እንደሚረዳ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሆቴል አትሌቲክስ ክለብ በምዕራብ ጎጃም ዞን ሰከላ ወረዳ ግሽአባይ ከተማ መቀመጫውን አድርጎ የተቋቋመ ክለብ ነው። ለስፖርቱ ምቹ እና የስመ ጥር አትሌቶች ምንጭ በመሆን ይታወቃል። ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ወጣት አትሌቶችን በማቀፍ ሲያሰለጥን ቆይቷል። ክለቡ ከ160 በላይ ተተኪ አትሌቶችን በማፍራት ለሌሎች ክለቦችም ግብዓት መሆን እንደቻለ ተጠቁሟል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን የካቲት 24/2014