ዓድዋ ግዙፍ ታሪክ ነው። በእርግጥ ስለዓድዋ በዓመት አንዴ ለቀናት በዓሉ ይዘከራል። አውደ ጥናቱ ፣ ሲምፖዚየሙ፣ የኪነጥበብ ዝግጅቱ ፣ የአደባባይ ትርኢትና የመሳሰሉት ፣ ጥናታዊ ሥራዎችና ውይይቶች በስፋት ይካሄዱበታል። በእዚህ በኩል እነዚህ ክንውኖች ምን ያህል ተሰንደው ተቀምጠዋል የሚለው እንዳለ ሆኖ ሀብታም ነው። በስሙም አንድ ድልድይና አደባባይ እንደተሰየመለት ይታወቃል። ዓድዋ ድልድይ ዓድዋ አደባባይ ሲባል ይሰማልና።
ታሪኩን በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በመላ ዓለምም በየቤተ መጽሐፍቱ ማግኘት ይቻላል። በዓድዋ ላይ ጥናት ያደረጉ እንደሚሉት ግን ዓድዋ ገና ብዙ ሊጻፍ የሚችል ታሪክ አለው። ከዓድዋ ድል ጋር የሚያያዙ ፎቶ ግራፎች ፣ የጦር መሣሪያዎች ፣ አልባሳት፣ ወዘተ በተበታተነ መልኩ ነው የሚገኙት። እነዚህን ቅርሶች የተለያዩ ተቋማት አቆይተዋቸዋል። አሁን ግን ቢያንስ ምስላቸው በሚገባ ተደራጅቶ ሊቀመጥ ይገባል። ይህ ብቻ ትልቅ ሥራ ነው።
ዓድዋ ትልቅ ታሪክ እንደመሆኑ ይህን የሚዘክሩ ሙዚየሞች፣ አብያተ መጻሕፍትና የተለያዩ መዘከሪያዎች ወዘተ ያስፈልጋሉ። ይህ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም እንዲሁም በቅኝ ግዛት ውስጥ ሲማቅቁ ለነበሩ የዓለም ሕዝቦች በሙሉ ታላቅ የትግል እርሾ በመሆን ያገለገለና ዛሬም ድረስ ጎላ ብሎ የሚጠቀስ ታሪክ እስከ አሁን ከፍ ብሎ የሚታይ መዘከሪያ አልተሰየመለትም፤ አልተገነባለትም።
በዘመነ ኢሕአዴግ አንድ ሰሞን ጦርነቱ በተካሄደበት ዓድዋ በዓሉ በዓድዋ በደማቅ ሥነሥርዓት ማካሄድ ተጀምሯል፤ ይህ አንድ ለውጥ ነው። በዚያው በአድዋ የአድዋ ድልን የሚዘክር የፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ይቋቋማል ተብሎ የመሠረት ድንጋይም ተጥሎ ነበር። ሀሳቡ ወደ መሬት ሳይወርድ እንዲሁ እየተንከባለለ አለ።
በዚያው በኢሕአዴግ ዘመን በአዲስ አበባ አድዋን ለመዘከር በቦሌ ክፍለ ከተማ አንድ የአራዊት ማቆያ / ዙ/ ይገነባል ተብሎ የመሠረት ድንጋይም ሳይቀመጥ እንዳልቀረ የሰማሁ መሰለኝ። ይህ ሰፊ ስፍራ ተይዞለት የነበረ ፕሮጀክት ውሃውም አልሞቀ።
ዓድዋ አሁንም በዓመት ለአንድ ሰሞን ብቻ ከሚዘከርበት ሁኔታ የተሻገረ መዘከሪያ ያስፈልገዋል። ይህን የተገነዘበው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በእዚህ ሥራ ተጠምዷል። የዓድዋን ሙዚየም ማዕከል መገንባት ውስጥ ከገባ ወደ ሁለትና ሶስት ዓመታት ተቆጥረዋል።
የዓድዋ ማዕከል በአዲስ አበባ እንብርት ላይ መሐል አራዳ ጊዮርጊስ፣ አዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት እና ዳግማዊ ምኒሊክ ሐውልት አጠገብ፣ በጥንታዊ መጠሪያው ሲኒማ ዓድዋ በነበረበት ስፍራ ላይ እየተገነባ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ቦታው በራሱ ለዓድዋ ይገባዋልና ትልቅ ሀሳብ ነው።
ግንባታውን የሚያከናውነው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግዙፍ ፕሮጀክቶች ጽሕፈት ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ምሬሳ ልክሳ እንዳሉት፤ በ3 ነጥብ 3 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ይህ ግንባታ በ4 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ነው የሚከናወነው።
በአሁኑ ወቅትም ፕሮጀክቱ ተቀላጥፎ የግንባታው 75 በመቶ ተጠናቅቋል። ስትራክቸራል ሥራውም በሙሉ አልቋል። አሁን የቀለም ፤ የኤክትሮ ሜካኒካል ፤ የኤሌክትሪክ ፤ የሂፖክሲ እና ጣሪያ የማልበስ ሥራ እየሠራን ነው ይላሉ ኢንጂነሩ። ግንባታውን በተቻለ መጠን በታቀደለት ጊዜ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም ያመለክታሉ።
ግንባታው ግዙፍ ስለመሆኑ ግንባታው በሚካሄድበት ስፍራ ያለፈ ሁሉ ይገነዘበዋል። በርካታ ሕንጻዎች እንዳሉትም መረዳት አይቸገርም። ቦታውን አስቀድሞ የሚያውቅ በእዚያ ስፍራ ሁሉ ግዙፍ ሕንጻዎች እየተገነቡ መሆናቸውን ሲመለከትም ያለማንም ነጋሪ ግንባታው ግዙፍ መሆኑን ይመሰክራል።
እስኪ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ስለ ፕሮጀክቱ ይዘት በፌስቡክ ገጹ ሰሞኑን ካሰፈረው ጽሁፍ እንዋስና የግንባታው ግዝፈት ምን ያህል እንደሆነ እንመለክት።
በ3 ነጥብ 3 ሄክታር ቦታ ላይ የሚገነባው ይህ ፕሮጀክት ከ 3 እስከ 5 ወለሎች የሚኖሯቸው የተለያዩ ሕንጻዎችን አካቷል። ዋነኛው የፕሮጀክቱ አካል የዓድዋ ሙዚየም ሲሆን፣ ከዋናው ሙዚየም በተጨማሪ 400 ሰዎችን የመያዝ አቅም ያላቸው 2 የስብሰባ አዳራሾችና 250 ሰዎችን የሚያስተናግድ ሌላ አዳራሽን ጨምሮ 3 የተለያዩ የመሰብሰቢያ አዳራሾች ይኖሩታል።
ሌላኛው የፕሮጀክቱ አካል የተለያዩ ቢሮዎችና የመመገቢያ አዳራሽን የሚያካትተው ክንፍ ይሆናል። በዚህኛው የፕሮጀክቱ ክፍል ዘመኑ በደረሰባቸው መሣሪያዎች የሚደራጀውና 2000 መቀመጫዎች የሚኖሩት ግዙፍና በዘመናዊ ግብዓቶች የሚደራጅ አዳራሽ /City Hall/ ይኖሩታል።
በአንድ ጊዜ 1000 መኪኖችን ማቆም የሚያስችል የመኪና ማቆሚያ፣የታክሲ እና የአውቶቡስ ተርሚናሎች የፕሮጀክቱ ሌሎች አካላት ናቸው።
ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውልና 4000 መቀመጫ የሚይዝ ግዙፍ ሁለገብ አዳራሽ፣የቤት ውስጥ ስፖርት መጫወቻ ሜዳ፣ የህፃናት መጫወቻ ሜዳ፣በዘመናዊ መሣሪያ የተደራጀ ጂምናዚየም፣አገራዊ የዕደጥበብ ውጤቶች እና ሌሎችም የሚሸጡባቸው ሱቆች በፕሮጀክቱ አንደኛው ክንፍ የሚገኙ አገልግሎቶች ናቸው።
ከዚህ በተጨማሪ 2 ዘመናዊ ሲኒማ ማሳያዎች፣ ካፌ እና ሬስቶራንት፣ ግዙፍ ቤተ-መጽሐፍት፣ የተለያዩ ሁነቶች የሚካሄዱበት አምፊ ቲያትር፣ ከቤት ውጪ የሚዘጋጅ የኤግዚቢሽን ማሳያ ቦታ የአድዋ ‹‹00›› ኪ.ሜ.ፕሮጀክት ገፀ-በረከቶች ናቸው።
ከዚህም በተጨማሪ በግንባታው ማዕከላዊ ስፍራ ላይ ‹‹ሁሉም ከዚህ ይጀምራል›› የሚል ጽሑፍ የሚኖር ሲሆን፣ ይቺ ነጥብ ወደየትኛውም የአገሪቷ አቅጣጫ የሚደረግ ርቀት/ልኬት አንድ ብሎ የሚጀምርባት የርቀቶች ሁሉ አልፋ፣ የኪሎሜትሮች ሁሉ መነሻ ሆና ታገለግላለች። ፕሮጀክቱም ስሙን ከዚህ ተውሶ ዓድዋ ‹‹00›› ኪ.ሜ. ሙዚየም ተብሏል።
በተለይ ይህ የ00 ጉዳይ ሀሳቡ ምንድን ነው በማለት ኢንጂነር ምሬሳን ጠየቅናቸው። ሀሳቡ ሁለት እንደሆነ ገለጹልን። አንደኛው ወይም እማሬያዊ ፍቺው ከላይ የተጠቀሰው ሲሆን፣ ፍካሬያዊ ፍቺው ደግሞ የዓድዋ ዘመቻ መነሻውን ለማመልከት እንደሆነ ነው። ”የአድዋ ዘመቻን ሀሳብ እዚህ አሸንፈን ጀምረን ነው ወደ ዘመቻው የሄድነው ፤ አሸንፈንም የተመለስነው ወደዚህ ነው የሚለውን ለማሳየት ነው” አሉን።
እንግዲህ ከላይ እንዳየነው ይህ ማዕከል ለግዙፉ ዓድዋ በሚመጥን መልኩ እየተሠራ ያለ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው። በቦታው ተገኝቶ የሚመለከት እንደሚያስተውለው እየተገነባ ያለው ግዙፍ ፕሮጀክት ቀን በቀን እየገዘፈና ሽቅብ እየወጣ መሆኑን ነው።
ይህ ግዙፍ ግንባታ እንደ አገር ምን ጠቀሜታ አለው? አንደኛው እና ዋነኛው ጥቅም ዓድዋ የአንድ ቀን ወይም ሰሞን ትርኢት ሆኖ እንዳይቀር እና በየቀኑ የምናስታውሰው ጉዳይ እንዲሆን ማድረግ የሚያስችል መሆኑ ነው።
ድሉ የታሪክ መጽሐፍት ማድመቂያና ይህ ነው የሚባል ማስታወሻ የሌላው የአንድ ሰሞን ትርኢት ሆኖ ኖሯል። ይህ ሁኔታ በአድዋ ፓርክ ታሪክ ሆኖ ይቀራል።
የአድዋ ማዕከል አድዋ ከዓመት ዓመት የሚታወስበት ሕያው ማስታወሻ ሆኖ ተገኝቷል። በማዕከሉ ያሉት ሁሉም ነገሮች ዓድዋን ቀን በቀን እንድናስታውሰው የሚያግዙ ናቸው። ልጆቻችንን ይዘን በማዕከሉ ሙዚየም እየተንጎራደድን አባቶቻችን ምን እንደሰሩ ለማውጋት እንችላለን ፤ አልያም በማዕከሉ በሚገኝ አዳራሽ የካቲት 23ን ሳንጠብቅ ስለ አድዋ ድል ሲምፖዚየም ማዘጋጀት እንችላለን ፤ ወይም ደግሞ በማዕከሉ የቴአትር አዳራሽ ዓድዋን የሚዘክር የሥነ ጽሑፍ ምሽት ማስተናገድ እንችላለን ወዘተ…
ሁለተኛው ጉዳይ የቱሪስት መስህብ መሆኑ ነው። እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ በታሪክ ከምትታወስባቸው ነገሮች አንዱና ዋነኛው ቅኝ አለመገዛቷ ነው። ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ተጠቃሽ የዓድዋ ድል ነው። በዚህም የተነሳ ብዙ ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ታሪኩን የሚያስታውስ አንዳች ነገር ማየት ይፈልጋሉ። እስከ ዛሬ ግን ማሳየት የቻልነው ብቸኛ ነገር መሐል አራዳ ላይ የሚገኘውን የአፄ ምኒሊክ ሐውልት እና ምን እንደሆነ እንኳን ለማስረዳት የሚከብደውን የዓድዋ ድልድይ ነው። አሁን ግን በኩራት ወደ ዓድዋ ማዕከል እንወስዳቸዋለን። እዚያም ስለ ማዕከሉ ማስረዳት የሚገባንን ሁሉ ማስረዳት እንችላለን።
ሶስተኛው ማዕከሉ ለከተማዋ ተጨማሪ አንድ ሕዝባዊ ተቋም ሆኖ ያገለግላል። በዚህ ማዕከል ግንባታ የተነሳ አዲስ አበባ አሁን አንድ ተጨማሪ የቴአትር አዳራሽ ፤ አንድ ግዙፍ የመኪና ፓርኪንግ ፤ አንድ የሕጻናት መዝናኛ ፤ አንድ ተጨማሪ ጂምናዚየም ፤ አንድ ተጨማሪ ሲኒማ ወዘተ ይኖራታል ። ሌሎችም ብዙ ጥቅሞች ይኖሩታል።
ከሁሉም በላይ ግን ማዕከሉ አዲስ አበባ ላይ መገንባቱ አዲስ አበባ የሁሉም ናት የሚለውን ገንቢ ትርክት የሚያጠናክር ከመሆኑም በላይ የዓድዋ በዓልም የሁሉም ነው የሚለውን የታሪክ እውነታ ለማጽናት ይጠቅመናል።
ከእንግዲህ የዓድዋ ማዕከል አዲስ አበባ እንብርት ላይ ተቀምጧል። አዲስ አበባ ደግሞ የኢትዮጵያ እንብርት ናት፤ ሁሉም ነገር ከአዲስ አበባ ብሎም ከዓድዋ ማዕከል ይጀምራል። ስለዚህም የዓድዋ ማዕከል መነሻ እና መድረሻ ነጥባችን በእማሬም ይሁን በፍካሬ ዋጋው ከፍተኛ የሆነ የአንድነት እና የድል ማዕከላችን ነው።
(አቤል ገ/ኪዳን)
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2014