የካቲት ወር የአፍሪካውያን ወር ይባላል። ይህን ወር የአፍሪካውያን ወር ያሰኘው ብቸኛ ምክንያት የዓድዋ ድል ነው። ነጮች አፍሪካውያንን በግፍ በሚረግጡበት፣ በባርነት በሚገዙበት፣ ያሻቸውን ያለከልካይ በሚፈፅሙበት በዚያን ወቅት “እምቢኝ! ሀገሬን በቅኝ አላስገዛም” ብሎ በጀግንነት የተነሳ፣ ተነስቶም የቅኝ ገዢዎችን በትር በሀይል መስበር የተቻለበት ወር የካቲት ነው።
የአውሮፓ ሀገራት አፍሪካን በተቀራመቱበት ዘመን ጣሊያንም ኢትዮጵያን ቅኝ ግዛቷ ለማድረግ መንገድ የሚከፍትላትን የውጫሌ ውል ከአፄ ምኒልክ ጋር ውጫሌ ከተማ ላይ በተወካይዋ አንቶሌኒ መሰረት ተዋዋለች። ከተደረገው ውል አንቀፅ 17 ግን የአማርኛ እና የጣሊያንኛ ትርጓሜው የተለያየ ነው። ይህም በታወቀ ግዜ አንቀፅ 17 ይቅር ቢባልም ጣሊያኖች አሻፈረኝ በማለታቸው የጦርነቱ አይቀሬነትም ተረጋገጠ።
የጣሊያን መንግሥት በተወካዩ አማካይነት ኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ሲያውጅ አፄ ምኒልክ የጣሊያንን በጦር መሳሪያም ሆነ በስልጣኔ ከፍ ማለቱ ሳያሸብራቸው ‹‹ቴዎድሮስ በመቅደላ ዮሐንስ በመተማ የሞቱላትን ሀገር እኔም ደሜን አፍስሼ ነፃነቷን አስጠብቃለሁ። እሞትላታለሁ›› ብለው አዋጅ አወጁ… ‹‹….የሀገሬ ሰው ከአሁን ቀደም የበደልኩህ አይመስለኝም፤ አንተም አላስቀየምኝም። ጉልበት ያለህ በጉልበትህ ዕርዳኝ፤ ጉልበት የሌለህ ለልጅህ ለሚስትህ ለሃይማኖትህ ስትል በሐዘን ዕርዳኝ። ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ፤ አልተውህም። ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም..ዘመቻዬ በጥቅምት ነው እና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታ ድረስ ወረይሉ ከተህ ላግኝህ።›› አዋጁን ተከትሎ ህዝብ ከዳር እስከ ዳር ተመመ። እቴጌይቱ እንዳሉት ደረቱን ለጥይት እግሩን ለጠጠር ሰጥቶ ሀገሩን ከጠላት ሊታደግ የኢትዮጵያ ህዝብ ከዳር እስከ ዳር ነቅሎ ተነሳ።
ዕለቱ የዓድዋ ድል 126ኛ ዓመት የሚከበርበት የሚዘከርበት ኢትዮጵያውያንም አንገታችንን ቀና እድርገን ስለ ድላችን የምናወራበት በቀጣይ ስለሚጠብቁን የቤት ሥራዎች ተመካክረን በተለያዩ መስኮች ላይ ድል አድርገን አገራችንን ዳግም ቀና የምናደርግበት ዕለት እንደመሆኑ ልዩ ጊዜ ነው። የዛሬው እንግዳችን በጅማ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ከተቦ አብዲዮ ሲሆኑ የታላቁ የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያንን በአንድነት የማሰባሰቡ አንደምታ ላይ አነጋግረናቸዋል።
አዲስ ዘመን፦ ኢትዮጵያ በታሪኳ ከተለያዩ አገራት ጋር ጦርነት አድርጋለች። ከአውሮፓ ከመጡ ወራሪዎች ጀምሮ አፍሪካዊቷ ግብጽ በተለያዩ ወቅቶች ኢትዮጵያ ላይ ወረራ አድርጋም ነበር። እንደው ኢትዮጵያ ያደረገቻቸው ጦርነቶች ምክንያቱ ከምን የመነጨ ነው?
ዶክተር ከተቦ ፦ የእነዚህ ሁሉ ወረራዎች ምክንያቶች ብዙ ሊሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን ዋናው የቅኝ ግዛት ፍላጎት ነው። የበላይነትን የማስፈን ሁኔታ ነው። ሌላው ግን አንዳንድ ጊዜ ሃብት በራሱ እርግማን ወይም ምርቃት የሚሆንበት ሁኔታ ስላለ ከዛ ጋር ተያይዞም የሚመጡ ችግሮች አሉ። ለምሳሌ የአባይ ወንዝ ሁኔታ፣ ከቀይ በባህር ጋርም ስትራቴጂክ የሆነን ቦታ የመያዝ ሽሚያ አለ። በተለይም ከግብጾች ጋር የሚያያዘው ከዚህ ጋር ነው። ግብጾቹ እንግዲህ 1875 እና 1876 ዓ.ም በጉንደትና በጎራ ተሸንፈው ኋላም ሀረር ላይ በ1875 እና በ1876 ዓ.ም ቢይዙም አልተሳካላቸውም።
ከዛ በኋላ የመጣው ጠንካራው የአውሮፓ አገር ጣሊያን ነው። ጣሊያን የመጣው ለቅኝ ግዛት ነው። አገሪቱ እንደ አንድ አገር የተዋሃደችው በጣም ዘግይታ በ1871 ዓ.ም ነው። እናም የተነሳችው በቁጭት ከመሆኑም በላይ ያላት የሌላትን ሃይል አሰባስባ ወደ ኢትዮጵያ የመጣችው ለቅኝ ግዛት ነው።
ቅኝ ግዛት ሲባል እንግዲህ ከጥቅም ጋር የተያያዘ ነው። የቅኝ ግዛት ሂደቶች የሚደረጉት ዞሮ ዞሮ የራሳቸውን የበላይነት በሌላው ላይ ጭነው የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ እና የማህበራዊ ጥቅማቸውን ከማስከበር አንጻር ነው።
አዲስ ዘመን ፦ ኢትዮጵያ እነዚህን ወረራዎች በአሸናፊነት መወጣቷስ አንደምታው ምንድን ነው?
ዶክተር ከተቦ ፦ ዋናው ነገር ለአለም ያሳየነው አንድ ላይ ከቆምን ምንም የሚቸግረን ነገር አለመኖሩን ነው። ታሪክ ማለት የጋራ ትውስታ ነው። የጋራ ትውስታ ሆኖ ደግሞ ለወደፊቱ ከጥንካሬያችንና ከድክመታችን ተምረን የወደፊት ስትራቴጂያችንን የምንቀይስበት መንገድም ነው። እነዚህን ጦርነቶች በድል መወጣት ትልቁ ምስጢር በአንድነት መቆማችን ነው። በሌላው ጊዜ ውስጥ ውስጡን በተለያዩ ምክንያቶች የሚጣሉ ህዝቦች የውጭ ጠላት ሲመጣ አንድ ላይ ሆነው መከላከላቸው ለድል ያበቃቸዋል። ስለዚህ እኛም ይህንን ድል ለማስመዝገብ የቻልነው በአንድነት በመቆማችን ነው።
ከዓድዋ በፊት በግብጾችም በሌሎችም የተቃጡትን ወረራዎች በድል ማጠናቀቅ ተችሏል። ነገር ግን የዓድዋው በጣም ትልቅ ከመሆኑ አንጻር ይህንን ትልቅ ግዙፍ ድል ማስመዝገብ የተቻለው ህዝቦች ከምዕራብ እስክ ምስራቅ ፣ ከሰሜን እስከ ደቡብ ሁሉም በአንድነት መቆምና መከላከል በመቻላችን ነው። ይህ ባይሆን ኖሮና ተበታትነን ብንቀር ኖሮ ምንም ማድረግ አይቻልም ነበር። ሚስጥሩ አንድነት ነው። የሚያመለክተው ለአንድ አላማ የውስጥ ችግርን ለሌላ ጊዜ አቆይቶ በአንድነት መቆም ውጤታማ እንደሚያደርግ ነው ።
አዲስ ዘመን ፦ ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ስሟን ከፍ አድርገው ካሳዩ የጦር ታሪኮች አንዱ ዓድዋ ነው። ይህ ድል ለኢትዮጵያውያን ብሎም ለተቀሩት ጥቁር ህዝቦች የሚኖረው አንደምታ እንዴት ይገለጻል?
ዶክተር ከተቦ፦ ዓድዋ የሚጠራው የድሎች ሁሉ የበላይ በመባል ነው። ለኢትዮጵያም የሚታየው እንደዛ ነው። ታሪካዊ ፋይዳውም በጣም ብዙ ነው። ለአውሮፓውያን በተለይም ደግሞ ለጣሊያን የቅኝ ግዛት ህልሟ የመከነበት ትልቅ ሽንፈት ነው። በዚህ ደግሞ ጣሊያን ብቻ ሳትሆን የደነገጡት ነጮች በሙሉ ናቸው። አፍሪካውያንን እስከ ዓድዋ ድል ድረስ የሚጠሩት የጨለማ አህጉር ብለው ነበር። ዓድዋም በአፍሪካ አዲስ ሀይል የመነሳቱን ሁኔታም ቁልጭ አድርጎ ያሳያቸውም ነው። በመሆኑም ለጥቁሮች አንደምታው በጣም ብዙ ነው። ለነጮች ደግሞ የሆነው በተቃራኒው ነው። ለመላው የዓለም ጥቁር ህዝቦች እንደ ትልቅ ድል ተወስዷል።
ከጥቁርም አልፎ ጃፓኖች እ.ኤ.አ በ1905 ከራሽያ የገባችበት ጦርነት ከዓድዋ ጋር በማነጻጸር እንዴት ጥቁሮች ነጮችን ድል ሲያደርጉ እኛስ እነዚህን” ቢጫ” ህዝቦች ማሸነፍ ያቅተናል በማለት ለድል በቅተዋል። ለሌሎችም ማለትም ጭቆና ለበዛባቸው ህዝቦች ለምሳሌ ደቡብ አፍሪካ፣ አሜሪካ፣ የፓን አፍሪካኒዝም መነሻ ሁሉ ከዓድዋ ድል በኋላ የመጣ ነው።
ሌሎች አለም አቀፍ ተቋማትም ከድሉ በኋላ በኢትዮጵያ ስም ተቋማታቸውን ሲሰይሙ ተስተውለዋል። በተለይም ቤተክርስቲያኖችን ሰይመዋል ፤ በመሆኑም ድሉ የአፍሪካውያን ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር ህዝብ ድል ነው።
በዋናነት እንደ ኢትዮጵያ ደግሞ በመጀመሪያ ደረጃ ኢትዮጵያ ነጻ አገር ናት ብለን የምንለው ትልቁ ምክንያት ዓድዋ ነው። ከዚህ የመነጩ ደግሞ በርካታ ነገሮች አሉ። ለምሳሌ ኢትዮጵያ ከውጭ አገር ጋር በቀደምትነት ግንኙነት የመሰረተችው በዓድዋ ምክንያት ነው። ከዛም መጀመሪያ ጣሊያን ፣ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ፣ ጀርመን ፣አሜሪካን ሌጋሲዮናቸውን(ኤምባሲዎቻቸውን)በኢትዮጵያ በመክፈት ነጻነቷን አረጋገጡ። የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢ ሲ ኤ) በ 1958 ዓ.ም የተከፈተው፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (ኦ ኤ ዩ) በ1963 ዓ.ም የተከፈተው በዓድዋ ድል ምክንያት ነው።
የዓድዋ ተምሳሌት እንሆናለን። እንደ ኢትዮጵያ እኛም እናሸንፋለን በማለት አብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት ሰንደቅ አላማ አደራደሩ ይዘበራረቅ እንጂ ሁሉም መነሻቸው አረንጓዴ ፣ ቢጫና ቀይ ነው። የኢትዮጵያ ድንበር በአለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነትን ያገኘው ማግኘት የጀመረው በዓድዋ ምክንያት ነው። በመሆኑም ዓድዋ ለኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ቅርጽ የሰጣት ያስከበራት ለጥቁሮች ሁሉ የክብር ምንጭ የሆነ ነው።
አዲስ ዘመን ፦ ኢትዮጵያ ለዓድዋ ድል የበቃችበትን ምስጢር እርስዎ እንዴት ይገልጹታል?
ዶክተር ከተቦ ፦ ምስጢሩ በአንድነት መቆም ነው። የውስጥ ችግር ቢኖርም እርሱን ለሌላ ጊዜ አቆይቶ ወደሚቀድመው ነገር መሄድ ነው። ለምሳሌ በወቅቱ የትግራይ ኖቢሊቲ የጊዜው ሹማምንት በ1894 ዓ.ም አካባቢ ጣሊያኖችን እናንተ ገፍታችሁ ብትመጡ እኛ ምኒሊክን አንረዳም ብለው ነበር። ነገር ግን ጦርነቱ ገፍቶ ሲመጣ የራሳቸውን ግጭት ወደጎን በመተው አዲስ አበባ ድረስ በመምጣት ለራስ መንገሻ ዮሃንስ ለአገራችን በአንድ ላይ መቆም አለብን ብለው ተቀላቀሉ።
ሌላው እዚህ ላይ የማነሳው ኤርትራዊ የነበረ ሰው ለጣሊያኖች ተከፍሎት ይሰራ ነበር። በዛ ጦርነት ላይም መረጃ ሰጪ ነበር። ነገር ግን ቅጥሩ የእነሱ ይሁን እንጂ የሚሰጣቸው መረጃ የተሳሳተ ብሎም አቅጣጫ አስቀይሮ የኢትዮጵያን አሸናፊነት የሚያመጣ ነበር። ሌላው የጊዜው መሳፍንት አርሶ አደሩ የጀግንነት ስሜቱ በጣም ከፍተኛ ነበር። እንደ ዛሬ የተንደላቀቀ ቪላ የለም። ሁሉም አገሩን ለማዳን ዝግጁ ነበር። ይህ ደግም ድሉ እንዲመጣ ከፍተኛ የሆነ አስተዋጽኦን አበርክቷል።
እናሸንፋለን በሚል በህዝቡ ውስጥ የነበረው በራስ የመተማመን ስሜት ከባድ ነበር። ይህ ቀላል ነገር አይደለም። ቤት ያፈራውን የራሱን ስንቅ ቋጥሮ፤ መኪና ባለመኖሩ በእግሩ ተጉዞ ዓድዋ ደርሷል። ይህ ሲታይ አገርን ለማዳን ሁሉም ህብረተሰብ ሴት፣ ወንድ፣ ከህጻን እስከ ሽማግሌ የነበረው የጀግንነት ስሜት፤ የዓድዋ ድል ለመገኘቱ ትልቅ መሠረት ነው።
አዲስ ዘመን ፦ ከዚህ አንጻር አድዋ ኢትዮጵያዊ አንድነትን አጠናክሯል ማለት ይቻላል?
ዶክተር ከተቦ፦ በጣም ይቻላል። አሁን እንደ ጋራ ታሪክና ድል አድርገን የምናነሳው ዓድዋን ነው። ያልተሳተፈበት የለም ማለት ይቻላል። ለምሳሌ አባ ጅፋርን፣ ኩምሳ ቦረዳ፣ ሃው ጦና ፣ ሼክ ኡጅራል ሃሰን እንዲሁም ሌሎችንም ማንሳት ይቻላል። ሁሉም ተሳትፎ አድርገዋል። እነዚህ ግዛቶች በወቅቱ ገና ወደ ኢትዮጵያ የተቀላቀሉ ናቸው። ነገር ግን ሁሉም ተነስተው የሄዱት ወደ ግንባር ነው። እናም በቁርጠኝነትና በድል ስሜት መነሳታቸው ለድል አብቅቷቸዋል። እንደውም እኮ አጼ ምኒልክ እናንተ ድንበር ጠብቁ ብለው የመለሷቸውም ነበሩ። በመሆኑም ድሉ የጋራ ነው። አንድነትን ያጠናከረ ነው። የሰሜን፣ የደቡብ፣ የምስራቅ እና የምዕራቡ ሁሉም በመሳተፉ እንደ አንድነት አርማ ማንሳት የሚቻል ግንባር ቀደም ድል ነው።
አዲስ ዘመን ፦ አትዮጵያ በዘመነ መሳፍንት ዘመን አንድነቷ ተበታትኖ፣ በየቦታው በነበሩ መሳፍንትና የጦር አበጋዞች ስትመራ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ። ከዚያ በኋላ ደግሞ መልሳ አንድ በመሆን የፋሽስት ኢጣልያን ጭምር ድል ማድረግ ችላለች። ለመሆኑ በወቅቱ ለኢትዮጵያ አንድነት መፈጠር የነበረው ዋነኛ መነሻ ምን ነበር? እውን አንድነት የመጣው በሃይል ነው ወይስ ቀድሞውንም የአንድነት ስሜቱ ስለነበረ ነው?
ዶክተር ከተቦ ፦ ይህ ምናልባት ጥናት ሊያስፈልገው ይችል ይሆናል። ነገር ግን እዚህ ላይ አሁን የምናውቀውን ድንበር የከለሉት ፈረንጆች ናቸው። ከዛ በፊት ህዝባችን በንግድ በጋብቻ በተለያዩ ነገሮች ይተሳሰር ነበር ። እንደዚህኛው ዘመን ኮሚኒኬሽን ኢንተርኔት ወይም ሌሎች የግንኙነት መንገዶች አልነበሩም። ግን ደግሞ ግንኙነቱ በጣም ጠንካራ ነበር።
ይህ ጠንካራ ግንኙነት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን እንደ አህጉርም ጠንካራ ነበር። ፈረንጆች መጥተው ህዝቡን ሳያማክሩ አንተ ወደ ሱዳን አንተ ደግሞ ወደ ጅቡቲና ኬንያ በማለት ከፋፈሉት እንጂ ህዝቡ ቢጠየቅ ኖሮ ሌላ ታሪክ ይፈጠር ነበር። እንደ ሆር ኦፍ አፍሪካ አንድነትም ነበር። ህዝቡ በቋንቋም የተሳሰረ ነበር ። በነገራችን ላይ እኮ ዛሬ ድረስ ኦሮሚኛ የሚነገርባቸው የአፍሪካ አገራት አሉ። በተመሳሳይ ሶማሌኛ እኛን ጨምሮ በጅቡቲና በተለያዩ አገሮች ይነገራል። ይህ እንግዲህ ለድሉም ለአንድነቱም ከፍተኛ የሆነ አስተዋጽኦ አድርጓል ማለት ይቻላል።
አዲስ ዘመን ፦ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያዊነት እየደበዘዘ የብሔር ማንነት እየጎላ መጥቷል የሚሉ ብዙዎች አሉና ይህ ሁኔታ ለኢትዮጵያ ህልውና አደጋ ይሆናል ብለው ያስባሉ?
ዶክተር ከተቦ ፦ እዚህ ላይ አንድ ቤት የሚሰራ አይጣላም የሚባል አባባል መጠቀም አስፈላጊ ነው። እኛም ሁሉንም ብንገነባ ጥሩ ነው። ማንነትም ከኢትዮጵያዊነት ጋር የሚጣላ አይመስለኝም። ሰው መጀመሪያ የሚነሳው ከቤቱ ከቤተሰቡ ነው። ሰሙን የሚያገኘውም ከእናት ከአባት አልያም ከአያት ነው። የራሱ ባህል እና ቋንቋ አለው። በሌላ በኩል ደግሞ ትንንሽ ወንዞች እንኳን ከተለያየ ቦታ ይነሱና መድረሻቸው ላይ ሲገናኙ ትልቅ ወንዝ ይፈጥራሉ። እንደዚህ ብናየው ጥሩ ነው ። ምክንይቱም በኢትዮጵያዊነት ላይ ሁሉም የየራሱ ድርሻ አለው። በመሆኑም ብሔርም ማንነትም የየራሳቸው ሚና እንዳላቸው መረዳት እንጂ አይናችንን ጨፍነን ጨፍልቀን ሌላ እንገነባለን ማለት ጥሩ አይደለም።
ምንም እንኳን ኢትዮጵያ አንድ ብትሆንም የተለያየ ባህል ሀይማኖት ቋንቋ ያለን ህዝቦች ነን። በመሆኑም እነዚህን በቅጡ ይዘን አንድ ላይ ማስኬድ ካልቻልን እንደውም አሁን ካለው የባሰ ችግር ውስጥ ሊያስገባን ይችላል።
አንድነትን የሚጠላ የለም ተባብረን እንቆማለን። አንድ ካልሆንን እንወድቃለን የሚልም የፈረንጆች አባባል አለ። ነገር ግን እንደማየው እኔ የበለጠ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል አለ። ይህ ግን ፈጽሞ አይሰራም ። መጀመሪያ ሁሉም ኢትዮጵያዊ መሆኑን መቀበል ያስፈልጋል። አልያ ግን የእኔ እበልጥ እበልጥ ድራማ ውስጥ ከገባን የሚሆነው የፉክክር ቤት ሳይዘጋ ያድራል እንደሚባለው ነው።
አዲስ ዘመን ፦ አሁን አሁን አንድ ከሚያደርጉን የጋራ ታሪኮቻችን ይልቅ የሚያለያዩን እየጎሉ ነው የመጡትና እርስዎ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
ዶክተር ከተቦ ፦ ሁሉም መስራት አለበት ባይ ነኝ። እኛም የታሪክ ሰዎች አንድ በሚያደርጉን ነገሮች ላይ ትኩረት አድርገን መጻፍ እንዳለብን ይሰማኛል። ስህተቶችም ካሉ ማረሙ መልካም ነው። ታሪክ የጋራ ትውስታ ነው። ስኬቶቻችንንና ድክመቶቻችንን በማየት ወደፊት ደግሞ የተሳካ ጉዞ እንድናደርግ ይጠቅማልና የታሪክ ሰዎች መስራት አለባቸው።
ታሪክን ከመማሪያነት ባለፈ በተለይም ባለፈው ላይ የምንጨቃጨቅ የምንጣላ ከሆነ ይህ ከፍተኛ ችግር ነው። ሊሆንም አይገባም፤ ይልቁንም በባለፈው ታሪካችን ላይ ስህተት ካለ እርሱን ተነጋግሮ ተግባብቶ አርሞ ልክ እንደ ዓድዋ ድል አንጸባራቂ ሊሆን ይገባል።
በሌላ በኩል በዚህ ዘመን ልክ አንደ ዓድዋው ሁሉ በህብረትና በአንድነት ሆነን ሆ ብለን የምንዘምትባቸው ብዙ የቤት ሥራዎች ያሉብን ነን። መንግሥት ህዝብን ካዳመጠ ህዝብም መንግሥትን ማዳመጥ ከቻለ ብዙ ማይልሶችን መጓዝ እንችላለን።
በታሪካችን ላይ መጣላት አዋጭ አለመሆኑን ከሌሎች የአፍሪካም ሆነ የሩቅ አገሮች መማር አለብን። ለምሳሌ እነ ህንድ ደቡብ አፍሪካ ሌሎችም በርካታ ቋንቋ ያላቸው በባህል የሚለያዩ ቢሆኑም አገር የመሚለው ነገር ላይ ግን አንድ ከመሆናቸውም በላይ ለአንድነታቸው ትልቅ ቦታ የሚሰጡ ናቸው ። በእኛም አገር ይህ እንዲመጣ የታሪክ ምሁራን ፖለቲከኞች እንዲሁም እናንተ የመገናኛ ብዙሃኖች ባለሙያዎች ከፍተኛ የሆነ ሥራን ልትሠሩ ይገባል።
አዲስ ዘመን ፦ ዛሬ ላይ ቆመን ከዓድዋ ድል ምን እንማር?
ዶክተር ከተቦ ፦ ከዓድዋ ድል ብዙ ነገሮችን መማር ይቻላል። በነገራችን ላይ ድል የሚገኘው በጦርነት ብቻ አይደለም። በአንድነት በፍቅርና በቁርጠኝነት ከቆምን ኢኮኖሚያችን አድጎ ወደ ፊትም እንሄዳለን ። በኢኮኖሚ ራሳችንን ካልቻልን ክብርም የለንም በመሆኑም ድል በጦርነት ብቻ አለመሆኑን ተገንዝበን በምንሰራው በእያንዳንዱ ነገር ድል ማስመዝገብ ያስፈልጋል።
በኦሮሚኛ አንድ ተረት አለ “ኦሊገለን አላገለን” ትርጉሙም ስንተባበር ነው ከውጪ የምንገባው የሚል ነው። በመሆኑም ታሪካችንን እንደ ስንቅ ወስደን ባለንበት መሰክ ሁሉ በቁርጠኝነት የሚጠበቅብንን ሰርተን ለመማለፍ መጣር ያስፈልጋል። አሁን ላይ ዓድዋን በኢኮኖሚ በማህበራዊ በጀመርነው በህዳሴ ግድብ ላይ እንኳን አሻራችንን በማሳረፍ መድገም እንችላለን።
አዲስ ዘመን ፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ ።
ዶክተር ከተቦ ፦ እኔም አመሰግናለሁ።
ዕፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2014