ለአሸናፊነት መገዛት በተሰኘው መጽሐፍ ውስጥ ከሚገኙ በርካታ ወርቃማ አባባሎች መካከል የሰው ልጅን በሥነ ምግባር ሳይኮተኩቱ አዕምሮውን በትምህርት ማበልጸግ ለማኅበረሰብ ጠንቅ የሆነ ትምህርት መስጠት ነው የሚለው አንዱ ነው። ይህንን አባባል የሚመለከት ማንኛውም ሰው አይናቸውን ጨፍነው ፎቶ የሚያነሱትን፣ ፈጣሪያቸውን መፍራት የተዉቱን እና የዓለም የተፈጥሮ ሕግጋትን እንዲሁም በፍጹም ለአፍታም ቢሆን ሊዘነጉ የማይገባቸው ሰው ከመሆናችን ጋር የተቆራኙ የሥነ ምግባር መርሆችን የረሱ እና የናቁ ምዕራባውያንን ማስታወሱ የማይቀር ነው፡፡
ምዕራባውያን የአያሌ እውቀቶች አመንጭ ባለቤቶች መሆናቸው የማይታበይ ሐቅ ነው። እውቀታቸው ግን በሥነ ምግባር የተገራ ነው ለማለት ፈጽሞ አያስደፍርም። ይህንን ስል በአመክንዮ እንጂ እንዲሁ በግብዝነት ስላለመሆኑ በርካታ ምክንያቶችን ማቅረብ ይቻላል። ነገር ግን ሁሉንም ማቅረብ ስለማይቻል ሁለት አመክንዮችን በወፍ በረር እነሆ።
አንደኛው አመክንዮ Enlightenment እየተባለ ከሚጠራው በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፈረንሳይ ተጀምሮ በሂደት መላ አውሮፓን አዳርሶ ወደ ሌሎች አገራት የተስፋፋውን የምሑራን እንቅስቃሴ ይቃኛል። በ17ኛው እና በ18ኛው ክፍለ ዘመን በአውሮፓ የተካሄደው ምሁራን እንቅስቃሴ (Enlightenment) አውሮፓዊያን ስለ አምላክ ፣ ተፈጥሮ እና የሰው ልጅ ያላቸውን አስተሳሰብ በምዕራቡ ዓለም ሰፊ ተቀባይነት ካለው እና በኪነጥበብ፣ በፍልስፍና እና በፖለቲካ አስተሳሰቦች ጋር አቀናጅተው አብዮታዊ እድገቶችን ያነሳሱበት ወቅት ነው ።
በዚህ ወቅት አውሮፓውያን በማኅበራዊ እና የተፈጥሮ ሳይንስ የተመነደጉበት ጊዜ ነበር። ይሁን እንጂ በማኅበራዊ እና የተፈጥሮ ሳይንስ አውሮፓውያን እንዲመነደጉ ያስቻሉ የእውቀት ቀንዲል አባታቶች ተብለው በአውሮፓ የተለየ የክብር ማማ ላይ የተቀመጡ አያሌ ምሑራን ሁሉም በሚያስብል ደረጃ በፈጣሪ መኖር አያምኑም ነበር። በፈጣሪ መኖር የማያምን ደግሞ ፈጣሪ ፈጥሯቸዋል የሚባሉት ሰዎች ሊላበሷቸው የሚገቡ የሥነምግባር መርሆችን ማለትም መተባበር ፣ መዋደድ ፣ መከባበር ፣ ለሌሎች ጥቅም ራስን መስዋዕት ማድረግ ወዘተ የመሳሰሉትን ሥነ ምግባራት ይዘነጋሉ። ሁሉንም ለእኔ ብቻ ማለት ይጀመራል፡፡
ለእኔ ብቻ የሚል አመለካከት ከተጀመረ ደግሞ ሰዎች መጠፋፋትን ይጀምራሉ። መጠፋፋት ካለ ደግሞ ሳይቀድመኝ እንዴት ልቅደመው ይቀጥላል። በ17ኛው እና በ18ኛው ክፍለ ዘመን የተካሄደው የአውሮፓ ምሑራን እንቅስቃሴ (Enlightenment) ይዞት የመጣው ይህንን ሌሎችን አጥፍቼ እኔ ብቻ ልኑር ፡ በሌሎች ልፋት እኔ ብቻ ልጠቀም ፤ ሌሎች ሞተው እኔ ብቻ ልብላ ፤ ሌሎች ታርዘው እኔ ብቻ ልልበስ አይነት አስተሳሰቦች ናቸው ።
ለዚህም አንዱ ሁነኛ ማሳያ ደግሞ ከ1884-1885 ዓ.ም በአገረ ጀርመን የተካሄደው የበርሊን ኮንፈረስ እየተባለ የሚጠራው ነው። ይህ ደግሞ ሁለተኛው አመክንዮ ነው። በበርሊን ኮንፈረስ አውዳሚ መሣሪያ የመሥራት እውቀት ያዳበሩት አውሮፓውያን አውዳሚ መሣሪያቸውን ተጠቅመው አውዳሚ መሣሪያ የሌላቸውን አፍሪካውያንን ለመቀራመት የተሰበሰቡበት ነው ። በዚህም ኮንፈረስ አውሮፓውያን በመካከላቸው ምንም አይነት ጸብ ሳይፈጠር አፍሪካን እንዴት አድርገው መቀራመት እንዳለባቸው መከሩ፡፡
መክረውም አልቀሩ! ሰብዓዊነትን በዘነጋ አኳኋን አፍሪካውያንን ተቀራመቱ። በዚህ ጊዜ ክፉ ከተመከረባቸው የአፍሪካ አገራት አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ ክፉ የመከረችባትን ጣሊያን የዛሬ 126 ዓመት በዓድዋ ተራሮች በተዘጋጀው ግብዣ ላይ መላ አውሮፓውያንን አስተማሪ የሆነ ግብዣ ለክፉ መካሪዋ ጣሊያን ጋብዛ በመጣችበት አግባብ አስተናግዳ መለሰቻት።
የዛሬ 126 ዓመት በዓድዋ ተራሮች ጣሊያንን እንደ አመጣጧ አስተናግዳ የመለሰችው ኢትዮጵያ ለሌሎች አፍሪካ አገራት ነጻነታቸውን በጉልበታቸው ማስመለስ እንደሚችሉ የማሳያ ችቦ ለኮሰች። ኢትዮጵያን በአርያነት የተከተሉ አፍሪካውያን አገራት ከሰንደቅ ዓላማቸው ጀምሮ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በማስመሰል ለነጻነታቸው ተዋደቁ። ኢትዮጵያን መሆን ባይችሉም እንደ ኢትዮጵያ ግን ማድረግ ቻሉ። ነጻነታቸውንም አገኙ።
በአድዋ የታየው የኢትዮጵያውያን አርአያ መሆን ልምድ አሁን ላይም ምዕራባውያን አፍሪካን ብሎም ሌሎች አገራትን በእጅ አዙር ቅኝ ለመግዛት በሚጋጋጡበት ሰዓት የምዕራባውያንን የእጅ አዙር የቅኝ ግዛት እንደማይቀበሉ በሁለት ዐቢይ ጉዳዮች ፍንትው አድርገው ማሳየት ችለዋል።
አንደኛው ኢትዮጵያውያን ዓባይን ሲገነቡ በነበረው ውጣ ውረድ ላይ ነው ። ኢትዮጵያ ገና ከጅምሩ በዓባይ ላይ ግድብ ልሠራ ነው ስትል «ቄሰ ገበዙ ለጎረሱ አቃቢቱ አገሱ» እንዲሉ የዓባይ ውሃ ተጋሪ አገራት ምንም ባላሉበት ሁኔታ አሜሪካ እና የጥፋት መለከት ነፊዎቿ ምዕራባውያን ግብጽን ለማስደሰት ስለምን በዓባይ ላይ ግድብ ይገደባል ሲሉ ተደመጡ። ምዕራባውያን አፍሪካንም ሆነ የዓረቡን ዓለም ለማጥፋት ሲሹ የጥፋት ድግስ መደገሻ ማጀት የሆነችው ግብጽም ስለምን ዓባይ ይገነባል በማለት ያዙኝ ልቀቁኝ አለች። የሰማት ኢትዮጵያዊ አላገኘችም እንጂ።
ዓባይ እንዳይገደብ መላላጥ የጀመሩት ምዕራባውያን ለግድቡ መገንቢያ የሚሆን ብድር ኢትዮጵያ ማግኘት እንዳትችል የብድር መገኛ በሮቹን በሙሉ ክርችም አድርገው ዘጉ። የዓድዋ ድል አድራጊ ልጆች መደፈርን አምረረው ይጠላሉና ዓባይን በራሳቸው ለመገንባት ሆ ! ብለው ተነሱ። ግድቡንም ይገነቡት ያዙ።
ይህን የኢትዮጵያውያንን ትብብር የተመለከቱ ምዕራባውያን የነገይቱን የሰለጠነች ኢትዮጵያን አሰቡ። ይበልጡኑም ደነገጡ። ከግድቡ ጋር ተያይዞ የወደፊቷን ያደገች ኢትዮጵያ ያሰቡ ምዕራባውያን በቀጠናው የሚኖራቸውን ጥቅም ምን ሊሆን እንደሚችል በማሰብ ብርክ ያዛቸው። በራሷ ወጭ ግድቧን የምትገነባዋን ኢትዮጵያን ምክንያት እየፈለጉ ቁም ስቅሏን ያሳይዋት ያዙ። በኢትዮጵያ ላይ ያልተገባ ጫና ማሳደር ሥራዬ ብለው ተያያዙት።
በዓለም ላይ የሰላም ስጋት የሆኑ ጉዳዮችን እንዲፈታ ታስቦ የተቋቋመው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም የምዕራባውያን ተልዕኮ ማስፈጸሚያ አሽከርነቱን በግ ልጽ በማሳየት ግድቡን ወይም ልማቱን እንደስጋት ቆጥሮ ጉዳዩን በተደጋገሚ በጸጥታው ምክር ቤት እንዲታይ አደረገ።
ሴራን ቀድመው የሚረዱት የዓድዋ ድል ወራሽ የሆኑት ኢትዮጵያውያን ግን ከአቋማቸው ፍንክች ሳይሉ ቀሩ። አባቶቹ በዓድዋ ተራሮች በደማቸው የጻፉትን ደማቅ የጀግንነት አሻራ የአሁኑ ትውልድም በዓባይ ላይ አስመሰከረ። በዚህም የአሁኑ ትውልድ የትኛውንም አይነት ጫና ከየትኛወም አቅጣጫ የደረሰበት ቢሆንም ጫናዎችን በሙሉ መክቶ እና ተቋቁሞ ግድቡን ገደበ። የዓድዋ ልጅ ከግድቡም እሸት መቅመስ ጀመረ።
አሜሪካ እና ምዕራባውያን ልማታችንን ሊያደናቅፉ ሞክረው ሳይችሉ ሲቀሩ፤ ዓለምን በቅኝ ግዛታቸው እንዲያስተዳድሩ ሕጋዊ እውቅና የሰጠው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እሳት ልሶ እሳት ጎርሶ፤ ፍርደ ገምድልነቱን በአደባባይ ያለምንም ይሉኝታ አሳየ።
ኢትዮጵያ ወደ አሰበችው የእድገት ጎዳና እንዳትገባ ለማድረግም ሁሉንም አማራጭ የእድገት ጎዳናዎችን በሙሉ በሾህ ሞሏቸው። በመንገዳችን ላይ የተከሰከሰውን እሾህ ስንለቅም ምዕራባውያን እኛን በሁለተናዊ መልኩ ለማጥፋት በማሰብ እና እድገታችንን እንዳናፋጥን ለማድረግ በመወሰን ሕወሓት የተባለ መርዛማ እሾህን በመንገዳችን ላይ ነሰነሱ።
የዓድዋ ድል ወራሽ ልጆችም አሸባሪውን ሕወሓት አይቀጡ ቅጣት ቀጡት። ምዕራባውያን ያላሰቡት ስለገጠማቸው በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማድረግ ተነሱ። አደረጉትም! ነገር ግን ምዕራባውያን ሊፈጥሩብን የነበረውን ጫና በበቃን ወይም (no more) ዘመቻዎች በዜሮ አባዝተው ምዕራባውያን ሴራ ለዓለም ሕዝቦች አሳዩ። ይህ የበቃ ዘመቻ ሁለተኛነት የሚጠቀስ የእዚህ ዘመን ኢትዮጵያውያን ለመላው ዓለም ባርነትን በመጠየፍ ረገድ በአርያነት እንዲጠቀሱ ያስቻለ ተግባር ነው።
እንደሚታወቀው ምዕራባውያን ከቡርኪናፋሶ እስከ ኮንጎ፤ ሩዋንዳ ፣ ብሩንዲ ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን ፣ሊቢያ እስከ ላይቤሪያ ፤ ከኢራን እስከ ኢራቅ፤ ፣የመን ፣ሶርያ ፣ኮሪያ እስከ ቬትናም አገራትን ለማፍረስ ሞከሩ። ሞክረውም የአሰቡትን አደረጉ።
በዚህም ከላይ የተጠቀሱ እና መሰል አገራት በአሜሪካ እና ሸሪኮቿ የክፋት መርዝ ተነድፈው ብዙ መከራ አሳለፉ። እስካሁንም አሜሪካ እና አጋሮቿ የክፋት መርዝ ለማሻር የሚያስችል መድኃኒት አጥተው እየተተራመሱ ያሉ አገራት ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። ይህ ሲሆን ግን ከኢትዮጵያ በስተቀር በእነ አሜሪካ የጥፋት መርዝ የተነደፉ የአፍሪካም ሆኑ የኤዥያ አገራት ዜጎች አገራቸውን በክፋት መርዝ የሚያበጣብጡት አሜሪካ እና የጥቅም ሸሪኮቿ ምዕራባውያን እንደሆኑ እያወቁ አንድም በውጭ አገራት የሚኖሩ የእነኝህ አገራት ዲያስፖራዎች NO MORE ወይም በቃ ሲሉ አልታዩም።
አሜሪካ እና አጋሮቿ በሌሎች አገራት የሞከሩትን የክፋት መርዛቸውን በኢትዮጵያም ላይ ለመድገም ሞክረው ነበር። ይሁን እንጂ በዓድዋ ተራሮች ገድል በሠሩት አባቶች እግር የተተኩ በውጭም ሆነ በውስጥ የሚኖሩ የዛሬዪቷ ኢትዮጵያውያን አሜሪካ እና የጥፋት ፈረሶቿ ምዕራባውያንን በቃ ሲሉ በአደባባይ ተደመጡ። ይህ የኢትዮጵያውያን አልገዛም ባይነት አሜሪካና እና የጥፋት ፈረሶቿን ክፉኛ አስደነገጣቸው። የማዕቀብ አይነቶችንም አዥጎደጎዱት ። አንዱን ማዕቀብ በሌላ ላይ ደረቱ፡፡
ከፍቅር፣ ፍትሕ እና እውነት ውጭ ኢትዮጵያውያን ማሸነፍ እንደማይቻል ምዕራባውያን ስለምን እንዳል ተገነዘቡ የሚመለከት ማንኛውም ሰው ከምዕራባውያን የበለጠ በዓለማችን ላይ ግብዝ እንደሌለ በቀላሉ ይገነዛባል። ከፍቅር፣ ፍትሕ እና እውነት ውጭ በጉልበት ኢትዮጵያውያንን ካሰቡት እንዳይደርሱ ሊያስቆም የሚችል ምድራዊ ኃይል እንደሌለ ከዓድዋ እስከ በቃ ዘመቻ ባለው ሂደት ለዓለም ሕዝብ አስተማሩ።
አሁን ላይ አሜሪካ እና የጥፋት ሸሪኮቿ አገራት የኢትዮጵያውያንን እያንዳንዱን እርምጃ እየቆጠሩ ያሉት በሕወሓት ዘመን እንደፈለጉ ሲያደርጓት የነበረችውን ኢትዮጵያ ከአሁን በኋላ እንደማያገኟት ስለተረዱ ነው። ይህን ተከትሎ አሁን ላይ ምዕራባውያንም ሆነ ብለው የኢትዮጵያን የስም የማጥፋት ዘመቻ ( character assassination) በመክፈት ኢትዮጵያን በሆነ ባልሆነው መውቀሱን እና መክሰሱን ሥራዬ ብለው እንደያዙት እያየን ነው።
ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ያላቸው ጥላቻ የቆየ መሆኑ እና አሸባሪው ሕወሓትም ለምዕራባውያን በአሽከርነት ሲሠራ መቆየቱን ለመረዳት በባሮን ሮማን ፕሮቻዝካ የተጻፈው እና በአርቲስት ደበበ እሸቱ ወደ አማርኛ የተተረጎው “Abessinien: Die schwarze Gefahr” ወይም «የባሩድ በርሜል» የተሰኘው መጽሐፍ ማየት በቂ ነው።
የባሩድ በርሜል ጸሐፊ የሆነው ባሮን ሮማን ፕሮቻዝካ ከኦስትሪያ በአዲስ አበባ የዲፕሎማሲ ሥራ እንዲሠራ የተላከ ዲፕሎማት ነበር። በ1926 ዓ.ም ከዲፕሎማት ሥራው እና ከዲፕሎማቲክ መብቱ ጋር የሚፃረር ተግባር ሲያከናውን በመገኘቱ ከአዲስ አበባ ተገዶ እንዲወጣ ተደረገ። ባሮን ሮማን ፕሮቻዝካ ከአዲስ አበባ መባረሩን የሚያስታውስ ማንም ሰው በህልውና ዘመቻው የመጀመሪያው ዙር ጦርነት ወቅት ከያዙት ዓላማ እና ተዕልኮ ውጭ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ እና በኢትዮጵያ መንግሥት ከኢትዮጵያ የተባረሩትን ሰባቱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞች የሚያስታወስ መሆኑን አያጠራጥርም።
በባሮን ሮማን ፕሮቻዝካ የተጻፈው መጽሐፍ አሁን ላይ ትህነግ እና የተባበሩት መንግሥታት ከምዕራባውያን ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ላይ እያሳደሩት ያለውን ተፅዕኖ ለመረዳት ስለሚያስችል መጽሐፉን በወፍ በረር ማየቱ ተገቢ ነው።
መጽሐፉ ምዕራፍ 1 ላይ “በኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄደው ምንድን ነው? ” በሚል ርዕስ ተነስቶ በርካታ ርዕሰ ጉዳዮችን ይዳስሳል። መጽሐፉ ስለ አገሪቱ መልክዓ ምድራዊ ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ኩነት ሲደሰኩር ከቆየ በኋላ ቅኝ ተገዥ ከሆነው ከሌላው ዓለም ሕዝብ የሚያገኙትን ክብርና ታዛዥነት ኢትዮጵያ ውስጥ ማጣታቸውን ሳይደብቅ ይነግረናል። ይህንን የኢትዮጵያውያን ኩራት ማኮስመን ካልተቻለ እና በቸለልተኝነት ከታለፈ ወደ ሌሎቹ የአፍሪካ አገሮች ተሸጋግሮ ዋጋ ያስከፍናል። ስለዚህ የኢትዮጵያውያን ኩራት እና የራሳቸውን ችግር በራሳቸው ለመፍታት የሚያደርጉትን ጥረት ማኮስመን እንደሚገባ ለአውሮ ፓውያን ይመክራል። አክሎም የአማራ ብሔር ለውጭ ኃይሎች ያላቸው ጥላቻ ለሁሉም የውጭ መንግሥታትና ዜጎች አሳሳቢ መሆኑን አመላክቷል። ስለሆነም የአማራ ብሔርን ከሌሎች ብሔረሰቦች ጋር በማጋጨት ኢትዮጵያን እንዳትነሳ አድርጎ ማጥፋት እንደሚቻል ይገልጻል ፡፡
ይህንን የባሮን ሮማን ፕሮቻዝካ እቅድ ለሚመለከት አሸባሪው ሕወሓት በ1968 ዓ.ም በእጅ የጻፈው ማኒፌስቶው መነሻው የባሮን ሮማን ፕሮቻዝካ መጽሐፍ መሆኑን በማያወላዳ መልኩ መገንዘብ ይቻላል ። ይህም አሸባሪው ትህነግ ከፍጥረቱ ጀምሮ የምዕራባውያን የጥፋት አሽከር መሆኑን ያመላክተናል።
ምዕራፍ 2 “ጥቁር መጽሐፍ የኢትዮጵያውያን የጥቃት ስንዘራ” በሚል ርዕስ ተነስቶ ነጮች ኢትዮጵያ ውስጥ ሲመጡ የሚገጥማቸውን መከራና ሰቆቃ ይዘረዝራል። ለውጭው ዓለምም ለጥቁር አሜሪካውያን ሳይቀር ኢትዮጵያ ማለት ለእንግዳ ክብር የማትሰጥ የምድር ሲዖል እንደሆነች አድርጎ ያለግብሯ ግብር እና ያለታሪኳ ታሪክ ለመስጠት ሲፍጨረጨር ይታያል ።
ይህን የኢትዮጵያን ክብር ለማውረድ ሲጣጣር የሚመለከት ማንኛውም ሰው የአሸባሪው ትህነግ እና ግብሩ ኦነግ ሸኔ የኢትዮጵያ ታሪክ የ100 ዓመት ነው ብለው ታሪኳን ሲያኮሰምኑ መመልከት የጥፋት ቡድኑ ትህነግ እና ኦነግ ሸኔ የባሮን ሮማን ፕሮቻዝካ ጽሑፍ እና የምዕራባውያን እኩይ ተልዕኮ ፈጻሚ መሆናቸውን ለአፍታም እንዳንጠራጠር ያደርጋል።
ምዕራፍ 3 “ኢትዮጵያና ሌላው ዓለም” በሚል ርዕስ ተነስቶ የውጭው ዓለም ከኢትዮጵያ ጋር ስላለው ግንኙነትና በነሱ ጉዞ ላይ ስለሚፈጥረው መሰናክል፤ ስለ አገሪቱና ሌግ ኦፍ ኔሽን ስለ መሆኗ፤ አገሪቱ ጦርነት ለማከናወን ስላላት አቅምና ስለ አገሪቱ መንግሥት የመረዳት መጠን የራሱን ውስጠ መርዛዊ ትንታኔ በመስጠት ኢትዮጵያ አፍሪካ በምዕራባውያን ዕዝ ስር ሆና እንዳትሰለጥን የተቀመጠች ደንቃራ መሆኗን በማጠቃለያው ገልጾ አውሮፓውያን አገሪቱን ልክ እንዲያስገባት መክሮ መጽሐፉን ይደመድማል።
በመጨረሻም ለዘመናት ግብፅን፣ ጣሊያንን፣ ሶማ ሊያን ወዘተ የመሳሰሉ የውጭ ወራሪዎችን ኢትዮጵያን ሲወሩ የኢትዮጵያ ጀግኖች አሳፍረው እንደመለሱ የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ። ለዚህ ሁሉ የኢትዮጵያውን ጀግንነት ዋነኛው ምክንያት እና ምንጩ ደግሞ ኢትዮጵያኖች በታሪካቸው ሁሉ ያደረጓቸው ጦርነቶች የውጭ ኃይላት ኢትዮጵያ ላይ በሚፈፅሟቸው ግፎች እንጂ ኢትዮጵያ በፀብ ጫሪነት ያካሄደቻቸው አለመሆናቸውን ያሳያል፡፡
ኢትዮጵያውያን ያደረጓቸው ጦርነቶች ስለእውነት እና ለፍትሕ የተደረጉ ጦርነቶች በመሆናቸው ብዙ ጀግኖችን አፍርተዋል። የጀግንነት ታሪክ ሕዝብ ባለቤት አድርጓታል። አሁንም በገፍ እየተፈጸሙብን ያሉ አስቸጋሪ የጠላት አካሄዶች እጅ ለእጅ ተያይዞ ማክሸፍ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ታሪካዊ ኃላፊነት ነው። ስለሆነም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከታሪክ ተወቃሽነት የሚድንበትን ታሪካዊ ኃላፊነቱን በመወጣት አገሩን ለተተኪው ትውልድ ማስተላለፍ ይጠበቅበታል መልዕክቴ ነው።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2014