የዓድዋ የድል በዓል የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፣የመላው አፍሪካውያን ኩራት ነው ። ይህ የጥቁር ሕዝቦች ተምሳሌት የሆነው ድል 126ኛ ክብረበዓሉ ላይ ሲደርስ አንዴ እየደመቀ፣ሌላ ጊዜ ደግሞ እየደበዘዘ ነበር። ተለዋዋጭ የሆነ ነገር ቢያጋጥምም ታሪኩና ድሉ ትልቅ በመሆኑ ሁሌም ይከበራል። ይህን የድል በዓል ከወቅታዊ የአገራችን ሁኔታ ጋር በማያያዝ ከኢትዮጵያ አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ጋር ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን:- የዓድዋ በዓል በየዓመቱ ይከበራል። ይሄ ምን አንድምታ አለው ?
ልጅ ዳንኤል ጆቴ:- የዓድዋ ድል በዓል በብዙ መልክ በተምሳሌትነት ይገለጻል። በአገር ወዳድነት፣ በአንድነት፣ በመተባበር፣ በጀግንነት፣ ወራሪውና ፋሽስቱ የጣሊያን ጦር ኢትዮጵያን በኃይል ሊወርር በመጣበት ወቅት አፄ ምኒልክ ለሕዝባቸው ጥሪ ሲያቀርቡም ሲሆን፣ነጋሪት አስጎስመው የክተት ዘመቻ ሲያወጁ ዓመልህን በጉያህ ነበር ያሉት። ይህ የሚያስገነዝበው የውስጥ ችግር እንኳን ቢኖር አገርን ማስቀደም፤ በአንድነት ሆኖ በኃይል ሊወርር የመጣን ጠላት እንደአመጣጡ እንዲመለስ ማድረግ እንደሚገባ ነው። በወቅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ በሚባል ደረጃ ረሀብ ገብቶ ነበር።
ከብቶችም አልቀው ነበር። ረሀቡ በአየር ንብረት መዛባት የተከሰተ ሲሆን፣ከብቶቹ ያለቁት ደግሞ ከሕንድ አገር ከብቶች መጥተው ስለነበር ከብቶቹ በሽታ እንዳለባቸው ሳይታወቅ እንዲቀላቀሉ ተደርጎ ተላላፊው በሽታ ሁሉንም ጨረሳቸው። በመሆኑም ገበሬው እርሻ የሚያርስበት በሬም ሆነ የወተት ላም ስላልነበረው ልጆቹን ወተት ማጠጣትና መመገብ ባለመቻሉ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ወድቆ ነበር።
በተጨማሪም ወረርሽኝ በሽታ ገብቶ ነበር። በተለያየ ምክንያትም የእርስበርስ ግጭቶች በርትተው ስለነበር እነዚህ ሁሉ የተደራረቡ ችግሮች አገርን ሊወርር ለመጣ አካል ምቹ እንዳይሆን ነበር የምኒልክ ማስጠንቀቂያ አዘል ጥሪ። ***‹‹ወስልተህ ትቀርና ማርያምን ትጣላኛለህ›› ነበር ያሉት። ጥሪያቸውን ተቀብለው ከሰሜን፣ ከደቡብ፣ ከምዕራብ፣ ከምስራቅ፣ ከየአቅጣጫው ጦር አደራጅቶ ያላከ የአገር አስተዳደር አልነበረም። ከየአቅጣጫው የተመመው ጦርም ከስፍራው ተገኝቶ ጠላትን መፋለሙን ተያያዘው። ይህ ሁሉ የሕዝቡን አስተዋይነት፣ ብልህነት ያሳያል።
ከየአቅጣጫው የተሰባሰበው ጦር የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪ ነበር። አንዱ የሌላውን ቋንቋ አይሰማም። አይናገርምም ነበር። ሃይማኖቱም እንዲሁ የተለያየ ነበር። ሁሉም አፄ ሚኒልክ የሚባሉ ንጉሥ እንዳላቸው ያውቃሉ። ንጉሡም ለአገራቸው ለመሞት የተዘጋጁ ነበሩ። በቋንቋ አለመግባባቱ፣በእምነትም መለያየቱ፣በዘር አንድ አለመሆኑ አገሩን ከጠላት እንዳያድን አላደረገውም። ወገን እንደ ጠላት ዘመናዊ የጦር መሣሪያ የታጠቀ አልነበረም። በቤቱ የሚጠቀምበትን ስለት ይዞ ነበር ሆ ብሎ የተነሳው። ወደ ግዳጅ ሲሄድም የራሱን ስንቅ ይዞ ነበር። እንዲህ ባለው ሁኔታ ነበር በአንድ ልብ ሆኖ ተግባብቶ ለአገሩ ደሙን አፍስሶና አጥንቱን ከስክሶ ጠላትን አሳፍሮ ወደ መጣበት የመለሰው።
አንድነትና ኅብረቱ፣አገር ወዳድነቱ ነው ለድል ያበቃው። የዓድዋ ድል ላይ እንዲህ ነው ኢትዮጵያዊነት የታየው። ዓድዋ ላይ በተደረገው ጦርነት የእቴጌ ጣይቱ ሚና ከፍ ብሎ ይነሳል። ሴቶች ለጦር ተዋጊው ስንቅ እንዲያዘጋጁ፣ቁስለኛውንም አንስተው እንዲረዱ በማድረግ ጦርነቱንም በመምራት ጭምር ትልቅ ገድል የፈጸሙ ጀግና ናቸው። ምን ያህል ብልህ ሴት እንደነበሩ ከማሳያዎቹ አንዱ ወራሪዎቹ የጣሊያን ተዋጊ ወታደሮች የውሃ ጥም እንደማይችሉ አስቀድመው ያውቁ ስለነበር ውሃ የሚገኝበትን ስፍራ ሁሉ በኢትዮጵያ ጦር እንዲከበብ በማድረግ ጀግንነት ፈጽመዋል።
ሌላው ሳይነገር መታለፍ የሌለበት። የውጭ የሚመስል ነገር ግን ኢትዮጵያውያን የሚጠቀሙበት የራሳቸው ሕግ አላቸው። የተማረከ የጠላት ጦር አይገደልም። ኢትዮጵያውያኑ የማረኳቸውን የጣሊያን ወታደሮች በደንብ እያበሉ ተንከባክበው ነበር የሚጠብቋቸው። እንደውም አንድ ምርኮኛ ስለሚስቱና ልጁ ታሪክ ሲያወራላቸው እንደለቀቁት በታሪክ ይታወሳል። በኢትዮጵያ ባህል ምርኮኛ ይከበራል። ይህን ታሪክ የሰሙ ፈረንጆች በሁኔታው ተገርመው ግራ በመጋባት ስሜት ኢትዮጵያውያን አፍሪካውያን አይደሉም ለማለት የበቁት።
ያ ጦርነት ምን ፈጠረ ሲባል። መላ አፍሪካን፣በቅኝ ግዛት ውስጥ የነበረውን ሁሉ አናጋው። ጥቁሮች ስለ ኢትዮጵያ ጆሮአቸውን ሰጥተው ማዳመጥ ጀመሩ። ከቅኝ ግዛት ተላለቅቀው ነፃነታቸውን ያገኙ ካሬቢያን፣አሜሪካን አገር የሚገኙ፣ሌላው ቀርቶ ዓረቦችና ቻይኖች ጭምር የነጭ መንግሥት ኃይልን ማሸነፍ ማለት ለኢትዮጵያ ይቻላልን መንፈስ ሰጥቷታል። ፓን አፍሪካኒዝም ያኔ ነው የተጀመረው። ከዓድዋ ጦርነት ድል በኋላም ቢሆን አፄ ኃይለሥላሴ አፍሪካውያን ቢሰባሰቡ፣አንድ ሆነው የኢኮኖሚ አቅማቸውን ቢያጎለብቱ ማንም እንደማይነካቸውና እንደማይደፍራቸው በመናገር አፍሪካውያን አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ ብዙ ጥረት አድርገዋል።
ዓድዋ ላይ በተደረገው ጦርነት ጠዋት ተጀምሮ ምሽት ላይ አለቀ የሚባለው ብቻ አይደለም መታወስ ያለበት። ጦርነቱ በአምባላጌ፣በእንዳስላሴ፣መቀሌና በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተለያዩ አካባቢዎች የተካሄደ ሲሆን፣ስማቸው በታሪክ የሚታወስ ጀብድ የፈጸሙ ጀግኖች የተሳተፉበት ነው። እንዲሁ በአሸናፊነት አሸነፍን ተብሎ ብቻ የሚነገር አይደለም ። በውስጡ ብዙ የሚታወሱ ነገሮች አሉ። ውስጠ ሚስጥሩ ሳይጻፍና ሳይነገር እንደዚሁ ለብዙ ዓመት ታልፏል። በጣሊያን ሀገር ሳይቀር ቪቫ ምኒልክ እየተባለ የሚነገርለት የምንኮራበት የድል በዓል ነው።
አዲስ ዘመን:- ኢትዮጵያ በተለያየ ጊዜ ጠላቶች አያጧትም። ለምንድነው?
ልጅ ዳንኤል ጆቴ:- ቆንጆ ሴት ሁሉም የሚፈልጋት? ኢትዮጵያም እንደ ቆንጆ ሴት የምትፈለገው በውስጧ ብዙ ሀብት ይዛለች። ለም አገር ናት። የራስዋ ቋንቋና ሃይማኖት፣ፊደልና የቀን መቁጠሪያ እንዲሁም ታሪክ አላት። የሃይማኖት፣ የዘርና ቋንቋ ልዩነት ሳይኖር በመተሳሰብና በመረዳዳት በሰላም የሚኖርባት አገር መሆኗ በዓለም ይታወቃል። ነጮቹ የዓባይ መነሻ ኢትዮጵያ እንደሆነች ያውቃሉ። የዓባይ መነሻ ኢትዮጵያ ከሆነች ይህችን አገር ሁሉም ይፈልጓታል።
ይህ ብቻም አይደለም። ማዕድን አላት። የውጭዎቹ የእምነት፣የትምህርትና የተለያየ አጀንዳ ይዘው ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ኢትዮጵያ ያላትን የአየር ፀባይ ሳይቀር ሀብቷን ዓባይ ከየት ተነስቶ የት እንደሚደርስ ያጠናሉ፡ ፡በእርምጃቸው ሁሉ ሳይቀር ልኬት ይጠቀማሉ። ሌላው ቀርቶ በእርሻ ወይንም በድንበር በሕዝቦች መካከል መቃቃር እንኳን ቢኖር ምክንያቱን ያጠናሉ። የሚፈልጉትን ዓላማ ለማሳካት ለመጠቀም ስለሚረዳቸው ይሄን ያደርጋሉ ። የኢትዮጵያ ሕዝብ እርስበርሱ ይጋጫል፣ወረርሽኝና ረሀብ አለ ብሎ በደካማ ጎን ለመግባት ሲጠቀሙ ይስተዋላል። ይሁን እንጂ እስከ ዛሬ አልተሳካላቸውም። ምክንያቱም የውጭ ተጽዕኖ ሲመጣ ኢትዮጵያውያን አንድ ናቸው። የአገራቸውን ጥቅም አሳልፈው አይሰጡም። ዳር ድንበራቸውን አያስደፍሩም። አይንበረከኩም።
አዲስ ዘመን:- ኢትዮጵያውያን ከውጭ የመጣን ወራሪ በአንድ ሆነው በመመከት ይታወቃሉ። አንድ የሆነ ሕዝብ እርስበርስ በመጋጨት ለምን ሰላሙን ያደፈርሳል?
ልጅ ዳንኤል ጆቴ:– ግጭቱ የእርስ በርስ ነው ብሎ አፍ ሞልቶ ለመናገር ያስቸግራል። ኢትዮጵያ እንደሌለች አድርጎ ለማየት የሚፈልግ የተወሰነ ክፍል አለ። የኢትዮጵያ ታሪክ ከአክሱም ስልጣኔ ስለመምጣቱ ታሪክ ምስክር ነው። በመሆኑም እንደሕዝብ ግጭት የሚፈልግ የለም። ነገር ግን የእከሌ ብሔር የእከሌ አካባቢ መሪ ነው በማለት የእናንተ የነበረውን እነእከሌ ወይንም እከሌ ወሰደው የሚል ትምህርት ትውልድ ውስጥ በመንዛት ቂምና ቁርሾ እንዲፈጠር በማድረግ ተፈቃቅሮ የኖረው ሕዝብ እንዲለያይ የተደረገበት አቅጣጫ ነው እርስበርስ ግጭት እየተባለ የሚነገረው።
ፖለቲካው ተለውጧል። ትናንት ያልነበረ ነገር ዛሬ ላይ እየተስተዋለ ነው። የኮሚኒዝም ሥርዓት በሚራመድበት ጊዜ ግብጾች እንዲፋፋም ይፈልጉ ነበር። አሜሪካኖች ደግሞ አይፈልጉትም። አሜሪካን በገንዘቧ፣በቴክኖሎጂዋ ስለምትመካ ኃያል ሆና ሁሉንም መግዛት ትፈልጋለች። በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያን መያዝ ትፈልጋለች። ኢትዮጵያን መያዝ የሚፈልጉበት ዋና ምክንያት ለቀይባህር ስትል ነው። ቀይባህር ለመጓጓዣ ወሳኝ በመሆኑ የጦር መሳሪያን ጨምሮ የተለያዩ ነገሮች ለማጓጓዝ ይጠቅማል።
ኢትዮጵያን መቆጣጠር ሳይሆን፣ኢትዮጵያን ካፈረሱ እሽ ጌታዬ ብሎ የሚታዘዝ መንግሥት ይኖራል። እስካሁን ይህን ፍላጎታቸውን የሚያሟላላቸው መንግሥት ማግኘት አልቻሉም። አፄ ኃይለሥላሴ አልተመቿቸውም። አፄ ኃይለሥላሴ እነርሱ ሳይፈጠሩ በፊት በእንግድነት አውሮጳ የሄዱ መሪ ናቸው። ጥቁር ዝቅተኛ ሥራ ሲሠራ እንጂ መሪ አላዩም። በአንደበተ ርዕቱነታቸውና ለነገሮች ችኩል አለመሆናቸው በብዙዎች ይታወቃሉ። በመሆኑም በነጮች በኩል ትልቅ ከበሬታ የተሰጣቸው መሪ ናቸው። ግን ደግሞ በመሪነት ስልጣናቸው ላይ እንዲኖሩ አይፈልጉም። እርሳቸውን ከስልጣናቸው ለማስነሳት ብዙ ተሞክሯል። የደርግ መንግሥት ሥልጣን ከመያዙ በፊት ኩዴታ ተፈጸመ። ግን ሳይሳካ ቀርቶ በመሪነት ሥልጣናቸው ለጥቂት ዓመታት ቆዩ ። በድጋሚ በደርግ መንግሥት በተደረገባቸው ሙከራ ከስልጣናቸው ለመውረድ ችለዋል።
አሜሪካን ወደ ኢትዮጵያ ብዙ ሰላዮችን ትልክ ነበር። በማስተማር ሰበብ ፒስኮር እየተባሉ ወደ ኢትዮጵያ ይመጡ የነበሩ ሁሉ ስለላ ነበር የሚሠሩት። ገጠር ውስጥ ሕዝቡን ተመሳስለው አብሮ በመኖር የአካባቢውን ባህል ጨምሮ እያንዳንዱን ነገር ነበር የሚያጠኑት። የደርግ መንግሥትንም ለመጣል ተመሳሳይ ነገር ነበር ያደረጉት። ደርግን ለመጣል ሶማሌን ነበር ያስነሱበት። ኢዲዩ፣ሕወሓት የመሳሰሉ በአገር ውስጥ የተቋቋሙ ድርጅቶች ደግሞ በውስጥ ሆነው መንግሥትን አዳከሙ። ይሄ ሁሉ የሚያሳየው እነርሱ እንደልባቸው የሚያሽከረክሩት የሚታዘዝ መንግሥት ለመመሥረት ያላቸውን ፍላጎት ነው። እንዲህ ባለው የውጭ ጣልቃ ገብነት ነው እርስበርስ ሽኩቻው በዝቶ የኢትዮጵያ ትልቅነት እንዲጠፋ እየተደረገ ያለው።
አዲስ ዘመን:- ምንም እንኳን ኢትዮጵያ እጇን ሰጥታ ባታወቅም፣ በውጭ ጣልቃ ገብነት ዛሬም ከትርምስ አልወጣችምና መቼ ነው ኢትዮጵያውያን ነቅተው ጣልቃ ገብነቱን ቀድመው መከላከል የሚችሉትና ዓድዋ ላይ የታየው አንድነት የሚደግሙት?
ልጅ ዳንኤል ጆቴ:- እንዴ ምን ማለትሽ ነው ይህ ጊዜማ አንድነት የታየበት ወቅት ነው። ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንድ አልሆኑም እንዴ? ነቀፌታ የተሞላበት አካሄድና ከእርሱ ፓርቲ በስተቀር ሌላ የሌለ አስመስሎ ሲናገር የነበረ ሁሉ አንድ ሆኗል። ደካማ መንግሥት ቢኖር ኖሮ ኢትዮጵያ ምን እንደምትሆን መገመት አያዳግትም። ዘመኑ ሰልጥኗል። ቴክኖሎጂ በመጠቀም የዓለምንና የአገሩን ሁኔታ ይከታተላል። በሚያገኘው መረጃም የኅብረተሰቡ ንቃተ ህሊና ከፍ ብሏል። ተኝቶ የቀረ ማኅበረሰብ አይደለም። ይሄን የምልሽ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ከተረዳ ምን ማድረግ ያውቃል። የኢትዮጵያ ሕዝብ የቱንም ያህል ደሀ ቢሆንም ኢትዮጵያዊነቱን ይወዳል። ማንነቱንም ማስነካት አይፈልግም።
የውጭ ጣልቃ ገብነትን ማስቆም አይቻልም። ፈላጊዎችዋ ብዙ ስለሆኑና ያሰቡትንም እስኪያሳኩ ድረስ ጣልቃ ገብነታቸውን ስለማይተዉ ኢትዮጵያ ከውጭ ጣልቃገብነት መቼም አትድንም። ለዚህ መፍትሔው ወይንም መድኃኒቱ ባህሏንና ታሪኳን አስከብራ፣ አንድነቷንም አጠናክራ፣ ትውልዱ ስለአገሪቱ ታሪክ እንዲያውቅ በማስተማሩ ላይ በመጠንከር በግብረገብ አገር ወዳድ ዜጋ የማፍራት ተልዕኮ መወጣት ስትችል ብቻ ነው።
አንዳንድ የምንታዘባቸው ነገሮች አሉ። ስለአገር ባንዲራ፣ ስለአገር ፍቅር ሲነሳ አንድ ዓይነት አመለካከት እየተስተዋለ አይደለም። እዚህ ላይ መጠንከር ያስፈልጋል። በተለያየ ሁኔታ ውስጥ ኑሮውን የሚመራው ሁሉ የአንድ አገር ልጅና የሚያስተሳስረው መለያ ባንዲራ አለው። ይሄን ወጣቱ እንዲያውቀው መድከም ያስፈልጋል። የውስጥ ሽኩቻ እንደማይጠቅም ያለው ነባራዊ ሁኔታ ያስረዳል። የጦርነት ትርፉ ድህነት ነው። ስለዚህ ከጦርነት ይልቅ አንድነትን አጠናክሮ ልማቱን ማፋጠን ይበጃል ነው የምለው።
አዲስ ዘመን:- በኢትዮጵያ የተረጋጋ ሰላም እንዲሰፍን ምን መደረግ አለበት ?
ልጅ ዳንኤል ጆቴ:– ሙሉ ለሙሉ ሰላም የሆነ ነገር አይጠበቅም። እንኳን እንደ ኢትዮጵያ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ የምትገኝ አገር ቀርቶ ባደጉ አገራትም ሰላም የለም። ስለሰላም የሚሰጠው ትርጉም ይለያያል። አንድ ሰው ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ሲሄድ በመንገዱ ችግር ካልገጠመው ሰላም መሆኑን ሊያረጋግጥ ይችላል። ሰላም ደግሞ ከራስ ይጀምራል። አንድ ሰው ውስጡ ሰላም ካለ ሰላም አለ። ከተማው ውስጥ ረብሻ ኖሮ ሰው በውስጡ ሰላም ካለ ያ ረብሻ ሰላም ሊነሳው አይችልም። ፍርሀትና ስጋት ነው ሰላም የሚያሳጣው። የእነዚህና ሌሎች ጥርቅም ድምር ውጤት ነው የሰላም መደፍረስ። በኢትዮጵያ የሰሜን ክፍል የተፈጠረው ችግርና ጦርነት የገዥዎች ወይንም የመሪዎች ችግር ነው።
አዲስ ዘመን:- ኢትዮጵያ በታላቁ የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያውን ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ጀምራለች ይህን እንዴት ያዩታል?
ልጅ ዳንኤል ጆቴ:– ፍፃሜ እንዳይደርስ የታሰበ ፕሮጀክት ነበር። ከአፄ ኃይለሥላሴ የአገዛዝ ዘመን ጀምሮ ሥራው እንዳይጀመር ትግል ተደርጓል። ሆኖም ግን የመንግሥት ጥንካሬ ለውጤት እንዲበቃ አድርጎታል። መሆንም ያለበት ጉዳይ ነው።
አዲስ ዘመን:- ዓድዋን እንደ አንድ መለያ ወይንም ብራንድ በማድረግ መጠቀም ይቻላል?
ልጅ ዳንኤል ጆቴ:- የዓድዋ የድል በዓል ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በደማቅ ሁኔታ መከበር ጀምሯል። ይሄ የሚያሳየው ሕዝቡ ታሪኩን ማወቅ መጀመሩን ነው። ስለዚህ የዓድዋ የመላው አፍሪካውያን ድል በመሆኑ ከኢትዮጵያ ውጭም እንዲከበር ማድረግ ማስፋት ያስፈልጋል። የአፍሪካውያንን አንድነት ያጠናክራል።
አዲስ ዘመን:- የሚያስተላልፉት ተጨማሪ መልዕክት ካለዎት ዕድሉን ልስጥዎት
ልጅ ዳንኤል ጆቴ:- የዓድዋ ድል በዓል ኢትዮጵያን አስከብሮ ያቆየ፣ በዓለም ላይ እንድትታወቅ ያደረገ፣ ኢትዮጵያን በወርቅ ቀለም ያጻፈ በመሆኑ ትልቅ ቦታ አለው። ያለኝ መልዕክት ለኢትዮጵያ መስዋዕት ሁኑ እንጂ አሳልፋችሁ አትስጡ። በማኅበራዊ ድረ ገጹ በሚጻፈውና በሚተላለፍ መልዕክት ከመነዳት ይልቅ ጠቃሚውን አገር የሚገነባውንና እንድትቀጥል የሚያደርገውን መርጦ መጠቀም ይገባል።
አዲስ ዘመን:- አመሰግናለሁ ።
ልጅ ዳንኤል ጆቴ:- እኔም አመሰግናለሁ።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2014