የጀግንነት እና የነጻነት ተምሳሌት አገር ኢትዮጵያ! በየጊዜው አገርን ብሎም ዓለምን የሚያስደምም ጀብዱ የፈጸሙ ጀግኖችን መፍጠር መታወቂያዋ ነው። ልጆቿ ለአገራቸው ህልውና መስዋዕትነት መክፈልን እንደ ጽድቅ ይቆጥሩታል። በጠላት መረገጥን አምረረው ይጠየፋሉ። ስለአገራቸው ለመሞት ለማይክሮ ሴኮንድም ያህል ማሰብ አይፈልጉም።
ኢትዮጵያውያን ጉልበት ስላላቸው እና ሁኔታዎች ስለተመቻቸው ብቻ በማን አለብኝነት ተገፋፍተው በታሪካቸው ሉዓላዊ አገርን በወረራ ለመያዝ ሙከራ አደረጉ ሲባል ተሰምቶ አይታውቅም። መታወቂያ ግብራቸውም አይደለም። ይሁን እንጂ ወቅቶችን እና ሁኔታዎችን እየጠበቁ በሚመጡ የውጭ እና የውስጥ ኃይላት ዳር ድንበራቸውን በመጣስ ተደጋጋሚ ወረራዎችን ተፈፅሞባቸዋል።
በዚህ ወረራም ህልውናቸው ሲፈተን በተደጋጋሚ አይተናል። ዳሩ ግን የግዛታቸውን አንድም ስንዝር እነካለሁ የሚል እና ህልውናቸውን የሚፈታተን ጥጋበኛ ሲመጣ ጥጋቡን በልኩ ማስተንፈስን ያውቁበታል። በማን አለብኝነት ሊደፍራቸው የሚመጣን ኃይልም ለመሬት ማዳባሪያነት በመቀየር ረገድ የሚስተካከላቸው የለም። ይህ በታሪክ ቅብብሎሽ የታየ ጥሬ ሐቅ ነው። ከመቶ ሃያ ስድስት ዓመት በፊት የተካሄደው ዓድዋ ጦርነት የኢትዮጵያውያን አልደፈር ባይነት ሁነኛ ማሳያ ነው።
ከዓድዋ ጦርነት ጋር ተያይዞ በደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ እና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር እንዲሁም የአለቃ ገብረሃና የባህል ጥናት ዳይሬክቶሬት አስተባባሪ ከሆኑት አቶ መሠረት ወርቁ ጋር ቆይታ አድርገናል። መልካም ንባብ ይሁንላችሁ።
“ኢትዮጵያ በውጭ ኃይሎች በተደረገ ተደጋጋሚ ወረራዎች ለብዙ ዘመናት በጦርነት ውስጥ እንድታልፍ ተፈርዶባት ቆይቷል” የሚሉት የታሪክና የቅርስ አስተዳደር መምህሩ ፤ በተለይ በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ የግንባታ ሂደት ውስጥ የኢትዮጵያን አንድነት የሚጠሉ ኃይሎች ደካማ እና የተበታተነች አገር እንድትሆን በመፈለግ በተደጋጋሚ ወረራ ማንሳታቸውን የጠቁማሉ። ለአብነት ያህል በጉራዓ ፣ በጉንደት ፣ በዶጋሊ ፣ በዓድዋ ወዘተ ተደጋጋሚ የወረራ ሙከራዎች ተደርገዋል። የውጭ ወራሪዎች በራሳቸው ማድረግ ሳይችሉ ሲቀርም አሸባሪውን ሕወሓት የመሰሉ አገር ጠል የባንዳ ስብስብ ቡድኖችን በመጠቀም ኢትዮጵያን የማፍረስ ሥራ ሲሠሩ ቆይተዋል። አሁንም እየሠሩ ይገኛሉ። ትህነግ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የፈጸመው ወረራም ምዕራባውያን እያደረጉት ለሚገኘው ለእጅ አዙር ጦርነቱ ሁነኛ ማሳያ ነው ።
በዓድዋ ጦርነት ኢትዮጵያውያን የተፋለሙት የውጭ ወራሪውን ጣሊያንን ነው ያሉት አቶ መሠረት ፤ በህልውና ዘመቻው ግን ኢትዮጵያውያን የተፋለሙት የውጭ ተልዕኮን ያነገበን የአገር ውስጥ ባንዳን መሆኑን አመላክተዋል። ሁለቱ ጦርነቶች አንድ የሚያደርጋቸው ወራሪ ቡድኖቹ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሱ መሆናቸው ነው። ሌላው አንድ የሚያደርጋቸው ደግሞ አገሬ ተነካች፣ ተደፈረች በማለት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ወራሪ ቡድኖችን ለመመከት እና ለመፋለም ያሳየው ትብብር እና አንድነት መሆኑን ጠቁመዋል።
በተለይ አሁን ላይ የተደረገው የህልውና ማስከበሩ ጦርነት የውጭ ጣልቃ ገብነት በግልጽ የተስተዋለበት እና ኢትዮጵያ ደካማ እና የተሽመደመደ ኢኮኖሚ እንዲኖራት ለማድረግ ታቅዶ የተሠራበት እና በተሽመደመደ ኢኮኖሚ ደግሞ የውጭ ኃይላት ፍላጎታቸውን ማስፈጸም በከፍተኛ ደረጃ ሲንቀሳቀሱ የተስተዋለበት መሆኑን አመላክተዋል።
የዓድዋ ጦርነትን ኢትዮጵያውያን ድል ባደረጉበት ወቅት ጎረቤት አገሮች ሙሉ በሙሉ የአውሮፓ አገራት ነበሩ። በዚህም ኢትዮጵያ አውሮፓ ውስጥ የምትኖር አንድ ትልቅ አገር ትመስል ነበር። ምክንያቱም በሰሜን ጣሊያን፣ በምስራቅ ፈረንሳይ ፣ በምዕራብና ደቡብ ምዕራብ ደግሞ እንግሊዝ ፣ በደቡብ ምስራቅ ደግሞ ጣሊያን ያዋስኗት ስለነበር። ይህ የሆነው እንደ ኢትዮጵያ አፍሪካውያን ሉዓላዊነታቸውን መጠበቅ ባለመቻላቸው ነበር።
እንደ አቶ መሠረት ገለጻ፤ ኢትዮጵያውያንን ለዓድዋ ድል ያበቃቸው ሁለት ሁነኛ ምክንያቶች ነበሩ። አንደኛው ንጉሡ ምኒሊክ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታውን የተረዱበት መንገድ አለመዛነፉና ትክክል መሆኑ ነበር። አጼ ምኒሊክ በአጼ ቴዎድሮስ ቤት ከማደጋቸው ጋር ተያይዞ ብዙ የአመራር ጥበቦችን መማር ችለዋል። ከዚህ ባሻገርም በአጼ ዮሐንስ ዘመነ መንግሥት አጼ ምኒሊክ የሸዋ ገዥ ሆነው ሳለ አጠቃላይ ዓለም አቀፉን ሁኔታ በሰከነ መልኩ የመመልከት እድሉ ነበራቸው። ከውጭው ዓለም ጋር የመገናኘትም አጋጣሚም ተፈጥሮላቸው ነበር። በመሆኑም በወቅቱ “ዓለም የት ላይ ነች” የሚለውን በሚገባ ግንዛቤው ነበራቸው ።
ሁለተኛው ዐቢይ ምክንያት ደግሞ አጼ ምኒሊክ የውጭውን አጠቃላይ ሁኔታ ከመረዳት ባለፈ ዘመናዊት ኢትዮጵያን ከመገንባት ጋር ተያይዞ የአካባቢ ገዥዎች እርስ በርስ እና እንዲሁም የአካባቢ ገዥዎች ከንጉሡ ጋር ከፍተኛ ቅራኔ ውስጥ ነበሩ። ይህን የነበረ የእርስ በርስ አለመግባባት «አመልህን በጉያህ ስንቅህን በአህያህ» በማለት የፈቱበት ብልሃት እና የአካባቢ ገዥዎችን አስተባብረው ወደ ዓድዋ የዘመቱበት ጥበብ ለድል አብቅቷቸዋል።
የታሪክና የቅርስ አስተዳደር መምህሩ አቶ መሠረት እንደሚናገሩት፤ የዓድዋ ጦርነት ለኢትዮጵያውያን በሁለንተናዊ መልኩ በርካታ መልካም አጋጣሚዎችና እድሎችን ይዞ ብቅ ያለ ነበር። ይሁን እንጂ ድሉ የፈጠረልንን መልካም አጋጣሚዎች ያህል መጠቀም አልቻልንም። ምናልባትም “ምንም” ለማለት ስለሚከብድ እንጂ ዓድዋ ድል ይዟቸው ከመጣቸው እድሎች አንጻር እኛ ኢትዮጵያኖች የተጠቀምነው ዜሮ በመቶውን ነው፡፡
“ዓድዋን ድል የተጠቀምነው ጦርነት በሚገጥመን ግዜ ‘አባቶቻችን ተዋግተው አገር አስቀጥለዋል’ ለሚል ወኔ መቀስቀሻነት ብቻ ነው” የሚሉት አቶ መሠረት፤ አንድና ብቸኛ ነገር የተሠራው የኢትዮጵያውያን የህዳሴ ግድብ በራሳቸው ለመገንባት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ላይ እንደ አንድ ማስተባበሪያ አጀንዳ መጠቀም መቻሉን እንደሆነ ይገልፃሉ።
“የዓድዋ ጦርነት ከፈጠራቸው መልካም አጋጣሚዎች መካከል የእከሌ የእከሌ ጎሳ ሳይባል ሁሉም ኢትዮጵያዊ በእኩልነት ደሙን አፍስሶ ፤ አጥንቱን ከስክሶ አንድነቱን ያሳየበትና አገሩን ከጠላት ተከላክሎ ህልውናውን ያስቀጠለበትን አጋጣሚ የተፈጠረበት ነው። ነገር ግን እኛ ኢትዮጵያውያን ከየት እንደወረስነው የማይታወቅ መጥፎ የመከፋፈል በሽታ ሊያጠፋን ሲዳደው እያየን ነው” ያሉት አቶ መሠረት ዓድዋ የፈጠረውን ዕድል መጠቀም ቢቻል ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን ይበልጥ ማጠናከር የሚችል መሆኑን ጠቁመዋል።
እንደ መምህሩ ገለፃ፤ በዓድዋ ጦርነት ንጉሡ ነገሥት አፄ ምኒሊክ ሕዝቡን አንድ አድርገው እንደመሩ ሁሉ አሁን ኢትዮጵያን የሚያስተዳድረው መንግሥት አድዋን ምሳሌ በማድረግ ዜጎች በልማት እና በድህነት ላይ በኅብረት መዝምት እንዲችል የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው። ፖሊሲ ሲቀረፅም ሆነ ሲተገበር ልማትን የሚያፋጥኑ እና የአንድነት መንፈስን የተላበሱ መሆን አለባቸው።
የአጼ ምኒሊክ የክተት አዋጅ በአሜሪካ የውትድርና ትምህርት ቤት ውስጥ እንደ አንድ የትምህርት ዘርፍ ሆኖ እየተሰጠ ይገኛል። እኛ አገር ይህን ለምንድን ነው የማንጠቀመው? የዓድዋ ጦርነት ሲባል ዓድዋን ብቻ ማየት ተገቢነት የለውም። ክተት የታወጀበት አዲስ አበባ፣ የውጫሌ ስምምነት የተፈረመበት እና ውሉ የፈረሰበት ቦታ፣ ወረኢሉን እና መሰል ቦታዎች ትልልቅ የጉብኝት ማዕከል መሆን ነበረባቸው። የጥናት እና የኮንፈረስ ማዕከል መሆን ነበረባቸው። ለዓድዋ ጀግኖች በመላው ኢትዮጵያ ሐውልቶቻቸው ሊቆም ይገባል። በዚህም ትውልድን ብዙ ማስተማር ይቻላል። ለቱሪዝም ዘርፉ ሰፊ እድል መፍጠር ይቻላል።
“እንደሚታወቀው አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት ነጻ ለመውጣት ኢትዮጵያኒዝም ፣ አቢሲኒያኒዝም ወዘተ እያሉ የዓድዋን ድል በአርአያነት እየተጠቀሙ ነበር” የሚሉት አቶ መሠረት፤ ይህን ያህል አፍሪካውያን ለነጻነታቸው ምሳሌ ያደረጉትን ጦርነት ዩኒቨርሲቲዎችን በመክፈት ትውልዱን ስለአንድነት ማስተማር ይቻል እንደነበር ያነሳሉ። በዓለም ላይ የሚገኙ ሕዝቦች ኢትዮጵያ ሲባል ተሽቀዳድመው የሚመለከቱት በአጼ ኃይለ ስላሤ እና በደርግ ሰዓት የተከሰተውን ረሃብ መሆኑን ይናገራሉ። እንደነዚህ ያሉ ገጽታን የሚያጠለሹ ሁነቶችን የሚሸፍኑ እና የጥቁሮች ነጻነት መነሻ እርሾ ጠንሳሽ መሆናችንን የሚያሳዩ ሙዚየሞች መኖር ነበረባቸው ሲሉም መስተካከል ያለባቸውን ቁልፍ ጉዳዮች በምክረ ሐሳብ ደረጃ ያስቀምጣሉ።
እንደ አቶ መሠረት፤ ወጣቱ ከአባቶቹ የተከፈለለትን ዋጋ ዞር ብሎ ሊመለከት ይገባል የሚል አቋም አላቸው። ምክንያታቸው ደግሞ ወጣቱ አድዋ ላይ በትክክል ምን እንደተከናወነ፣ ምን አይነት ጠላት መጥቶብን እንዴት አድርግን እንዳሸነፍን ፣ በታሪክ ባለሙያዎች እና ጉዳዩ በሚመለከታቸው ባለሙያዎች በትክክል ስለጦርነቱ ስልጠናዎች እና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች እየተዘጋጁ እውነታው ሊገለጽለት ይገባል። በዓድዋ ምን እንደተከፈለለት ያወቀ ወጣት በዓድዋ ጀግኖች ስም የቤተ መጽሐፍቶችን ቢገነባ፣ የመንገድ ስያሜዎችን ቢያወጣ፣ ሐውልቶች ቢቆም መልካም ነው።
ከህዳሴው ግድብ እና ከሕወሓት ወረራ ጋር ተያይዞ ዓለማቀፋዊ ጫናዎች እየበረቱ መሆኑን የሚያነሱት የታሪክና ቅርስ አስተዳደር መምህሩ፤ በእነኝህ ዓለም አቀፍ ጫናዎች ደግሞ የራሳችን ሃብት እንዳንጠቀም እየተደረግን ነው ይላሉ። እነዚህን ጫናዎች መቀልበስ የሚቻለው የአሁኑ ትውልድ እንደ አባቶቹ ሁሉ «አመልህን በጉያህ ስንቅህን በአህያህ » በማለት ውስጣዊ ችግሮቹን በብልሃት በመፍታት እጅ ለእጅ በመያያዝ በአንድ ላይ መቆም ሲችል መሆኑን ይናገራሉ። በዚህ መልኩ የዓለም አቀፉን ጫና መመከት ከተቻለ እውነትም የአሁኑ ትውልድ “በዓድዋ ተራሮች ላይ ጠላትን ድል ማድረግ የቻሉት የእነዚያ ጀግኖች የአባቶቻችን ልጆች ነን” ማለት እንደሚችል ጠቁመዋል።
አቶ መሠረት ያነሱት ሌላኛው ጉዳይ፤ የዓድዋ ጀግኖች ለአፍሪካውያን ነጻነት ከፍተኛ አበርክቶ እንዳላቸው ነው። አፍሪካውያን ፓን አፍሪካኒዝምን ጨምሮ የተለያዩ በርካታ ንቅናቄዎችን አድርገዋል። በዚህም እንደ ኢትዮጵያ ነጻ ለመሆን ከፍተኛ ተጋድሎ አድርገዋል። የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ መሪዎች ሁለት አመለካከት ነበራቸው። የአንደኛው ቡድን አባላት ባለንበት አሜሪካ መብታችን ይጠበቅ የሚል ሲሆን ሁለተኛው ቡድን ደግሞ ወደ አፍሪካ መመለስ እቅድ የነበረው ነው። ወደ አፍሪካ እንመለስ ያለው ቡድን “ወደ አፍሪካ ስንመለስ የት ነው የምናርፈው?” የሚል ጥያቄም አንስቶ ነበር። ይህን ተከትሎም “የጥቁሮች አገር ኢትዮጵያ ስለሆነች የምንመለሰው ወደ ኢትዮጵያ ነው” ይሉ ነበር ።
“ከዓድዋ ድል ጋር ተያይዞ በርካታ አፍሪካዊ አገራት ሰንደቅ ዓላማቸውን የኢትዮጵያን እንዲመስል ጥረት አድርገዋል” የሚሉት የታሪክና ቅርስ አስተዳደር መምህሩ፤ ይህን ያደረጉት የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የነጻነት ምልክት ነው ተብሎ ተምረውት እንዳልሆነ ይገልፃሉ። ይልቁንም ኢትዮጵያ በአድዋ ስለተጠቀመችውና በዚያም እየተመራች ድል ስላደረገች እንደሆነ ይገልፃሉ።
በመሆኑም የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከኢትዮጵያውያን አልፎ መላ ጥቁር ሕዝቦች እንደ አንድ ቅርስ መሆን የሚችል መሆኑን አመላክተዋል። በሁለተኛው የኢጣሊያን ወረራ ወቅት ኢትዮጵያውያን ንጉሣቸው በአገር ቤት ባይኖሩም እንኳን ኢትዮጵያውያን ስለአገራቸው ብለው በአንድነት ቆመው መስዋዕትነትን ከፈሉ። በአንድነት ሲቆሙም ዝም ብለው አይደለም ። እናሸንፋለን የሚል የሞራል ልዕልና ከዓድዋ ተረክበው ስለነበር እንጂ። ይህ የሞራል ስንቅ የማይዳሰስ ነገር ግን ለትውልድ እየተንቦገቦገ የሚተላለፍ ትልቅ ሃብት መሆኑን ጠቁመዋል ፡፡
የዓድዋ ድል አፍሪካን አንድ በማድረግ ትልቅ ሚና ነበረው ያሉት አቶ መሠረት፤ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መቀመጫው አዲስ አበባ እንዲሆን ያደረገው አንዱ ምክንያት ኢትዮጵያውያን ለጥቁር አፍሪካውያን የነጻነት ምሳሌ መሆን መቻላቸው እንደነበር ገልጸዋል። ነገር ግን በዓድዋ ድል ብቻ እየተኩራራን የምንቀመጥ መሆን የለብንም በማለት አሁንም በልማቱ ከዓድዋ ድል ጋር የሚስተካከል ሥራዎችን በመሥራት ድህነትን ታሪክ ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል። ከዓድዋ ጋር ተያይዞ የሚሠሩ ሥራዎች ወደ ገንዘብ መቀየር እንደሚያስፈልግም ገልፀው፤ ሌሎች አገራት አርቴፊሻል ነገር ሠርተው ሲያስጎበኙ እኛ ግን ታላቅ ነገር ይዘን ተቀምጠናል ይላሉ።
ጣሊያኖች ራሳቸው በሮም አደባባይ “ቪቫ ሚኒሊክ ቪቫ ጣይቱ” ብለው እውቅና የሰጡትንና የመሰከሩለትን ድል ሙዚየሞችን በመገንባት ኢትዮጵያን የቱሪዝም ማዕከል ማድረግ ይቻል እንደነበርም አመላክተዋል። በመጨረሻም ይህን የምዕራባውያንን ሴራ በመረዳት ሁሉም ኢትዮጵያዊ አንድነቱን መጠበቅ እንደሚገባው አመላክተው ከዓድዋ የተሻለ አንድነታችንን ለማጠናከር ምሳሌ የሚሆነን ድል የለም ብለዋል።
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2014