ዛሬ በታላቅ የድል ስሜትና መንፈስ ተከብሮ የሚውለውን የአንድ መቶ ሃያ ስድስተኛውን የዓድዋ ክብረ በዓል በተመለከተ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጀላ መርዳሳ ጋር ቆይታ አድርገን ነበር። በዚህም ድሉ የሚከበርበት መንፈስ፤ ታሪካዊ ምክንያት፣ ለኢትዮጵያውያን ስላመጣው ትሩፋትና መላው የጥቁር ሕዝቦችና አፍሪካውያን ክብረ በዓሉን እንደራሳቸው በምን መልኩ ሊያከብሩት እንደሚገባ በሚመለከት ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተውናል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ቀጀላ መርዳሳ የዓድዋ ድል ለተከታታይ ዓመታት ሲከበር እንደነበር በማስታወስ፤ ዛሬ ተከብሮ የሚውለው 126ኛ ክብረ በዓል መሆኑን ይናገራሉ። ጦርነቱ የተካሄደው በፋሺስት ጣሊያንና በኢትዮጵያ መካከል እንደመሆኑ በርካታ ያልተጠበቁ ውጤቶች የመጡበትና የዓለምን እይታ ከመሠረቱ የቀየረ ድል እንደሆነም ይገልፃሉ።
የጦርነቱ መነሻና ውጤቶች
“በዚህ ጦርነት ጣሊያኖች ድባቅ ተመትተውና ሽንፈትን ተከናንበው ጀግኖች ኢትዮጵያውያን አሸንፈው ለአፍሪካውያን ትልቅ ምሳሌ መሆን ችለዋል” ሚኒስትሩ፤ ጥቁር ሕዝቦችም ለመጀመሪያ ጊዜ ነጮችን በአፍሪካ ምድር በጦርነት ያሸነፉበትና ነፃነታቸውን ያስከበሩበት ድል መሆኑን ይገልፃሉ። ለዚህ ነው ይሄ ድል ትልቅ ቦታ የሚሰጠው በማለትም፤ ይህ ጦርነት ከኢትዮጵያውያን ባሻገር በአፍሪካውያን ዘንድም ትልቅ ትርጉም እንዳለው የሚያነሱት። የጦርነቱ መነሻ የሆነው በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ በተለይም ደግሞ ከ1850ዎቹና 1860ዎቹ አካባቢ ካፒታሊዝም በከፍተኛ ደረጃ የተሸጋገረበት እና ያደገበት ነበር።
የአውሮፓ አገራት ወይንም ካፒታሊስቶቹና ኢምፔሪያሊስቶች ግዛታቸውን ለማስፋፋት “sphere of influence” ፣ ለኢንዱስትሪያቸው ጥሬ እቃ ለመፈለግ፣ ለምርት ውጤታቸው ደግሞ ገበያን ለመፈለግ ሲሉ የቅኝ ግዛት አሊያም “የኮሎኒያሊዝም” ዘመንን ለማስፋፋት፤ በተለይ ደግሞ አፍሪካን ለመቀራመት የተንቀሳቀሱበት ግዜ ነበር። በተለይም ደግሞ ከ1884-1885 የበርሊን ኮንፍረንስ አድርገው በግልፅ “አፍሪካን መያዝና መከፋፈል አለብን” የሚል ውሳኔ ላይ መድረሳቸውን ያስታውሳሉ። ይህን ዓላማቸውን ለማስፈፀም በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ደግሞ እርስ በራሳቸው መዋጋት እንደማይኖርባቸው ተስማምተው እንደነበር አቶ ቀጀላ ይገልፃሉ።
እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ፤ በስምምነታቸው መሠረት ቀድሞ የደረሰ አንድን በሚገባ በቁጥጥሩ ስር ያደረገ ቅኝ ገዢ ያንን አካባቢ በአግባቡ ለመቆጣጠሩ ግልፅ መረጃ መቀያየር አለበት ። ያንን ካደረገ ያ ስፍራ ወይም ከአፍሪካዊ አገር አንደኛው ግዛቱን ለተቆጣጠረው ቅኝ ገዢ ሁሉም አውሮፓውያን እውቅናን ይሰጡ ነበር። በዚህ መልክ ነበር እነ ንጉስ ሊዮፖልድ ወደ ኮንጎ አካባቢ በመሄድ የራሳቸውን ግዛት የመሰረቱት። እንግሊዞች እነ ጋናን፣ ናይጄሪያን እንዲሁም እነ ኡጋንዳን የመሳሰሉትን በቅኝ ግዛታቸው ስር አድርገው እንዲያውም አንዳንዶቹ “በኢምፔሪያል ትሪኬሪ” ወይም ደግሞ ልዩ ልዩ መንገዶችና ዘዴዎችን ተጠቅመው አፍሪካውያንን በማታለል ጭምር ነበር ከላይ ያነሳነውን ፍላጎታቸውን ለማሳካት ጥረት የሚያደርጉት።
በዚህ አካሄዳቸው ስምምነቶችን በማስፈረም አሳሪ ሕግ ውስጥ ያስቀምጧቸው ነበር። በዋናነት ስምምነቱን ሲያዘጋጁና አፍሪካውያን መሪዎችን ሲያስፈርሙ በልዩ መንገድ ረቂቁን ሰነድ ክፍተት እንዲኖረው በማድረግ እንዲሁም በሚፈልጉበት ግዜ ለመከራከሪያነት ቀዳዳ እንዲያገኙ ያደርጓቸው ነበር። በዚህ አካሄድ የአካባቢው ነገሥታት፣ መሪዎች አሊያም የጎሳ አባላትን በመቅረብ ስምምነት ያደርጋሉ። እንደ እንግሊዝ ያሉት በተዘዋዋሪ ወይም “ኢንዳይሬክት ሩል” ለመግዛት የተለያዩ አገራትን ይይዙ ነበር። አንዳንድ እምቢተኝነታቸውን ያሳዩ የአፍሪካ አገራት ደግሞ ውጊያ በማድረግ ፍላጎታቸውን ያሳኩ ነበር።
“የኢትዮጵያም የወቅቱ ነባራዊ ሁኔታ ከዚህ የተለየ አልነበረም” የሚሉት ሚኒስትሩ፤ አገራችንን ለመውረር ፍላጎት ያሳየችው ጣሊያን ግን በተለየ ሁኔታ ወደ ቅኝ መግዛት ሥርዓትና ፍላጎት ውስጥ ከመግባቷ በፊት የኢትዮጵያ ወዳጅና በልዩ ልዩ የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ትስስር ፈጥራ የምትሠራ ነበረች ይላሉ። በተለይ ከንጉስ አፄ ምኒልክ ጋር አንኮበር ላይ እነ አንቶነሊ ለረጅም ጊዜ ቆንፅላ ነበሩ። ለልዩ ልዩ ፍላጎትና ሕግን ለማስከበር የሚውል መሣሪያም ንጉሡ የሚያገኙት ከጣሊያን ነበር። ይሁን እንጂ በጣሊያን፣ ፈረንሳይና እንግሊዝ መካከል ፉክክሮች ነበሩ። በተለይ ይህ ፉክክር በኢትዮጵያና በምስራቅ አፍሪካ ላይ የነበረ ነው። ይህን ተከትሎ ጣሊያኖች ቱርክ ለረጅም ግዜ ተቆጣጥራው የቆየችውን የኤርትራን ደጋማ ቦታዎች በመቆጣጠር ቀደም ብለው እዚያ አካባቢ የመቆጣጠር ሙከራዎች ማድረግ ጀመሩ።
“በጊዜው የኢትዮጵያ እንደ አሁኑ የግዛት አንድነቷና ዳር ድንበሯ ተጠናክሮ ስላልነበር ምፅዋም ለዘመናት በቱርኮች እጅ ስለነበር በዚያ በኩል ያገኙትን ክፍተት ተጠቅመው ተጠናክረው ፍላጎታቸውን ለማሳካትና ኢትዮጵያን በቁጥጥራቸው ስር ለማድረግ እንቅስቃሴ ጀምረዋል” በማለት ለወረራ ምቹ የሆኑ አጋጣሚዎችን የሚገልፁት ሚኒስትሩ ፤ ፈረንሳዮችም በጅቡቲ አድርገው የሚያደርጉትን ጫና ተከትሎ በእነዚህ አገራት መካከል ፉክክሮቹ እየጠነከሩ የመጡበትን መንገድ ተፈጥሯል ይላሉ። ጣሊያኖችም ከኢትዮጵያ ጋር ወዳጅ በመምሰል ውል ለማስፈረም ጥረት አድርገዋል። በውጫሌ የውል ስምምነት ላይም በአማርኛውና በእንግሊዘኛው ጽሑፍ ላይ አሻሚ የሆነ ትርጉም በማስገባት ለማታለል አሊያም ለማጭበርበር ያደረጉት ሙከራ ባለመሳካቱ ምክንያት ለጦርነቱ እንደ ዋነኛ መነሻ ምክንያት ሊሆን ችሏል።
ውጫሌና የስምምነት መዘዙ
ሚኒስትሩ አቶ ቀጀላ መርዳሳ እንደሚገልፁት፤ የውጫሌ ውል ስምምነት ዋነኛው ያለመግባባቱ አንኳርም “ኢትዮጵያ ከሌሎች የዓለም አገራት ጋር ግንኙነት ማድረግ ከፈለገች በጣሊያን በኩል ብቻ ነው” የሚለው ነበር። ይህ ስምምነት በኋላ ላይ ሲፈተሽ ከቅኝ አገዛዝ ያልተለየ እንደሆነ በመታወቁ በንጉስ አፄ ምኒልክና በአጠቃላይ ሥርዓታቸው ውሉን አንቀበልም መፍረስ ይኖርበታል የሚል እሰጣ ገባ ተጀመረ። ሌሎች የአውሮፓ አገራት ከአፍሪካ የተለያዩ አገራት የድርሻቸውን በመውሰዳቸው ጣሊያኖችም ተመሳሳይ ፍላጎት ኢትዮጵያ ላይ ቢያሳድሩም ይህ መሆን አልቻለም ነበር።
በዚህ ምክንያት ፋሽስት የመጀመሪያው አማራጭ ሊሳካ ባለመቻሉ በሁለተኛው የኃይል አማራጭ ለመሞከር ኢትዮጵያን የወረሩ ሲሆን ይህም በኢትዮጵያውያን ጠንካራ ክንድ ተመክተው ዳግም በጦርነት ድል ማድረግ ቻሉ። ከኢትዮጵያ አካባቢዎች ያልዘመተ ኃይል አልነበረም። ሁሉም ኢትዮጵያውያን በአንድነትና በኅብረት በጦር፣ በጎራዴ በነፍስ ወከፍ መሣሪያ እንዲሁም በፈረሰኞች ጭምር በመታገዝ ድል አድርገዋል። በግዜው ጣሊያኖች የኢትዮጵያ ጦርና ሥርዓተ መንግሥት ጠንካራ መስሎ አልታያቸውም ነበር። ውጊያው በቁርጠኝነት የተካሄደ በመሆኑ ጦርነቱን ዓድዋ ላይ አሸንፈው በድል መመለስ ችለዋል።
“የዓድዋ ድል በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካም ሆነ በዓለም ታሪክ ትልቅ ድል ነው። በዚህ ምክንያት በታሪክ መዝገብ ላይ ሁሌም ሊዘከር እና በየግዜው ሊከበር የሚገባው ነው። በዚህ ምክንያት የዓድዋ በዓልን አከባበር በባለቤትነት በመያዝ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በርካታ ሥራዎችን ሰርቷል” የሚሉት የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ፤ የዚህኛው ዓመት መሪ ቃል “ዓድዋ ለኢትዮጵያውያን ኅብረት፤ የአፍሪካ የነፃነት ጮራ” የሚል እንደሆነ ይገልፃሉ። በዋናነት ዛሬ እየተከበረ የሚገኘው ዓድዋ ኢትዮጵያውያንን ከየአቅጣጫው በማሰባሰብ ያስተባበረ በመሆኑና አንድነታቸውም እንዲጠናከር በማስቻሉ ሲሆን ለሌሎች አፍሪካውያን በቅኝ የተያዙ አገራት ደግሞ ድሉ ተስፋና ተምሳሌት ስለሆናቸውና ከጭቆና ቀንበር ለመውጣት ከፍተኛ ትግል እንዲያደርጉ መነሻ መሠረት በመሆኑ ጭምር ነው። ክብረ በዓሉን በማስመልከት ይፋ በሆነው ሎጎ ውስጥ የአፍሪካውያንን አንድነት እንዲሁም “የፓን አፍሪካኒዝም” ንቅናቄን የሚደግፍ ጥቁር ክብ ቀለም እንዲኖር በማድረግም ድሉ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን አፍሪካውያንም የሚጋሩት የክብራቸው ተምሳሌት መሆኑን ለማሳየት በማለት አጠቃላይ ይዘቱን ያብራራሉ።
“በዛሬው ቀን ዓድዋንና ፓን አፍሪካኒዝምን አያይዘን ነው የምንዘክረው” ብለውም፤ ይህን ንቅናቄ ለማጎልበት ዓድዋ በጣም ትልቅ ሚና ይጫወታል። ለፓን አፍሪካኒዝም መነሻ ምሰሶ ነው። መላው የጥቁር ሕዝቦች በዓል እንዲሆንም ይሠራል። ይህን ለማጎልበት የሚያስችሉ የኪነጥበብ የባህልና የታሪክ ዝግጅቶችም ተደርገው በመላው ኢትዮጵያ ውስጥና ከኢትዮጵያ ውጪ ባሉ የድሉ ባለቤቶች ዘንድ እየተከበረ ነው። በሁሉም የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ሚሲዮኖችም እየተከበረ ይገኛል ብለዋል።
አፍሪካና ዓድዋ
ሚኒስትሩ አቶ ቀጀላ መርዳሳ እንደሚገልፁት፤ አፍሪካውያን ዓድዋን ማክበር ብቻ ሳይሆን በአንዳንድ አገራት እስከ ማምለክ ደረጃም (እንደ አንድ እምነት እስከማየት ደረጃ) ደርሰዋል። ደቡብ አፍሪካ ውስጥ “የኢትዮጵያ ሴክት ” የሚባል ከዓድዋ ጋር የተያያዘና ኢትዮጵያ የሚባለውን እስከማምለክ የተደረሰበት ደረጃ አለ። አሁን ላይ ደግሞ ከፓን አፍሪካኒዝም ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ እያስተዋወቀችውና እያበረታታች ስለሆነ የበለጠ ይጎላል። በተለይ ይህ ንቅናቄና ፅንሰ ሃሳብ ዓድል በኋላ የመጣ ሲሆን በተለይ በ1950ዎቹ ውስጥ ይበልጥ እንደተቀጣጠለ ይታመናል።
በተለይ ጋና ነፃነቷን አግኝታ እነ ፕሬዚዳንት ንኩሩማ ንቅናቄ ጀምረው አፍሪካውያን ነፃ መውጣት ሲጀምሩ “ስለ ፓን አፍሪካኒዝም አመሠራረትና” የአህጉሪቱን መፃኢ እድል ለመወሰን የሚያስችሉ ምክክሮችና ውይይቶች እርስ በእርስ ይደረግ ነበር። ይሄ የሆነው የዓድዋ ድልን መነሻ በማድረግና ለጥቁር ሕዝቦች ስነልቦናዊ መጠናከርና አንድነት እርሾ በመሆኑ ጭምር ነበር። በአሁኑ ግዜም በግዜው የነበረው የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ እንዲጠናከር እንቅስቃሴዎች በመኖሩ ዓድዋን እንደ ዋነኛ መሠረት በማድረግ የመላው አፍሪካውያንና ጥቁሮች ድል ሆኖ እንዲከበር ይሠራል። ዓድዋም ሁል ግዜም ቢሆን በፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ውስጥ እንደሞተር የሚያገለግል ነው።
“አፍሪካውያን አደባባይ ወጥተው ባያከብሩትም ይዘክሩታል” ያሉት ሚኒስትሩ፤ ዛሬ ላይ እያከበርነው ያለውን የዓድዋ ድል ኤምባሲዎች እና የተለያዩ የውጪ አገራት ድርጅቶች እዚህ ያሉም የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ ለብቻቸው ዓድዋን በተመለከተ ሲምፖዚየም እንደሚያደርጉና የሁሉም የድል በዓል ሆኖ በታሪክ እየተዘከረ እንዲሄድ መሠረት ለመጣል እንደሚሠሩ በማጠቃለያ መልዕክታቸው ላይ አስቀምጠዋል። ይሄ ውሳኔ የተደረገውም አብሮ የማክበር ስሜቱን ለማምጣት በማሰብ መሆኑን አንስተዋል። ድሮ ቤታቸው ሆነው የሚያስታውሱት መላው የጥቁር ሕዝቦችና አፍሪካውያን የነበሩ ቢሆንም አሁን ግን ወጥተው ጽሑፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበት እንዲያከብሩ እየተደረገ መሆኑን እንደ በጎ ጅምር የሚታይ መሆኑን ነው የሚያነሱት።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2014