ኢትዮጵያ በየዘመኑ የተፈጠሩና ከዘመን ዘመን እየተሸጋገሩ የመጡ ያልተቃጩ ሃሳቦች፣ በይደር የቆዩ አለመግባባቶች እንዲሁም አገር ትቀጥል ዘንድ ቅድሚያ ተነስቷቸው የቆዩ የማያግባቡ አጀንዳዎች የተሸከመች አገር ናት።
ውይይት የሞት ያህል የሚከብድበት፣ በአመለካከት የሚለዩ በጠላትነት የሚፈረጁበት አገር ሆናም ዓመታትን አስቆጥራለች። ‹‹እኔ ያልኩት ብቻ ካልሆነ ሞቼ እገኛለሁ። እኔ ሁሌም ትክክል ነኝ።›› የሚል የአመለካከትና የባህሪ ችግር ኢትዮጵያን ለረጅም ጊዜ ሲያደማት ከርሟል።
አገሪቱ ልዩነቶችን በውይይት የመፍታት የአሳታፊነት ባህልና ልምድ የሌለባት መሆኑ ደግሞ ችግሮች በቀላሉ ፈጣን ምላሽ እንዳያገኙ፤ ውስጥ ውስጡን እንዲብላሉና ከትላንት እስከ ዛሬ እንዲከተላት ምክንያት መሆኑ በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይታል። በሁሉ ረገድ አማራጭ ሃሳቦችና የጋራ ውይይቶች ዝግ መደረጋቸው ደግሞ ሳይውል ሳያድር ማስተካከያና መፍትሔ ሊሰጥባቸው የሚችሉ በርካታ ጉዳዮች ሳይቀር ተድበስብሰው እንዲቀሩ ከማድረግ ባሻገር የንትርክና የግጭት መንስኤ እንዲሆኑ ሲያደርግም ተስተውላል።
ይሁንና ከሕልውና ባሻገር ስለመጽናትና መቀጠል እንዲሁም ስለ ሁለንተናዊ እድገት ሲታሰብ ለእነዚህን ልዩነቶችና አጀንዳዎች መፍትሔ መስጠት የግድ ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ አንድነቷ ተረጋግጦ፣ ሰላምና መረጋጋት ሰፍኖ የሕዝቧን ቁሳዊና መንፈሳዊ ፍላጎት ማርካት የምትችለው በአንድ በኩል ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት ሲኖራት ነው።
ይህ መንግሥት ምን አይነት ቅርጽ መያዝ አለበት? ምን አይነት የዲሞክራሲ፣ የፖለቲካ፣ የሕግ፣ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ተቋሞች ያስፈልጉናል የሚሉ ትልልቅ አገራዊ ጥያቄዎች መልስ የሚያገኙት ደግሞ ኢትዮጵያውያን ቁጭ ብለው ሲወያዩ ብቻ ነው። በኢትዮጵያ ምድር የውይይት እሳቤ እውን ይሆን ዘንድም በተለይ ባለፉት አምስት አስርተ አመታት ከተለያዩ አካላት ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ሲነሳ ቆይቷል። ‹‹ይሁን›› የሚል መልስ የሰጠ መንግሥት ግን አልነበረም። በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አሕመድ የሚመራው መንግሥትም በአንጻሩ ይህን ታሪክ ለመለወጥ በተለይ ስለ ኢትዮጵያ ቁጭ ብሎ ለመምከር በሩን ክፍት አድርጓል።
ውይይቱ እውን ይሆን ዘንድ በሁሉ ረገድ ፈቃደኛ መሆኑን የሚያመላክቱ እርምጃዎችን እየተራመደም ይገኛል፡ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተቋቁሟል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ከቀናት በፊት ባካሄደው አንደኛ ዓመት 2ኛ አስቸኳይ ስብሰባ፣ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽንን እንዲመሩ በእጩነት የቀረቡ 11 እጩ ኮሚሽነሮችን ሹመት መርምሮ አፅድቋል።
አዲስ ዘመን ጋዜጣም አገራዊ ምክክር ለአንድ አገር ሁለንተናዊ እድገት ምን ትርጉም ይኖረዋል? መሰል መድረኮችንስ እንዴት ውጤታማ ማድረግ ይቻላል? የተለያዩ ሃሳቦች ሊነሱ ቢችሉም ለምክክሩ የሚቀረጹት አጀንዳዎች እንዴት መቃኘት አለባቸው? የባለድርሻ አካላት ሚናስ ምን መሆን ይኖርበታል? የሚሉት ጥያቄዎች በማንሳት ምሑራንን አነጋግሯል። ምሑራኑም፣ አገራዊ የምክክር መድረክ ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ለዘላቂ ሰላም፣ ለተሻለ የፖለቲካ ባህል ግንባታና ለሁለንተናዊ እድገትን እጅግ ወሳኝ ስለመሆኑም አስምረውበታል።
‹‹የወደፊቷ ኢትዮጵያ ምን መምሰል አለባት? የሚለው ላይ ትልቅ አቅጣጫን ያስቀምጣል። የተረጋጋችና በኢኮኖሚ የዳበረች ዲሞክራሲያዊት አገር ለመፍጠር እጅግ ወሳኝ ነው›› ይላሉ።
አሁን ላይ ለሁሉም ችግር ነጋ ጠባ ከመነቃቀፍና ጣት ከመቀሳሰር ተላቀን ለመፍትሔው ቁጭ ብለን መወያየት መጀመር አለብን የሚሉት ምሑራን፤ ከራስ ጥቅም ይልቅ ቅድሚያ ለአገር ማድረግ ከተቻለ መፍትሔ የሚጠፋለት አንድም ችግር እንደማይኖርና ለዚህ እጅግ ወሳኝ ታሪካዊ ሁነት ሁለንተናዊ መሳካትም ሁሉም የበኩሉን መወጣት እንዳለበት አፅዕኖት ይሰጡታል።
‹‹ከምንም በላይ ለብዙ ዓመታት ስንጠይቅ የመጣን ከመሆናችን አንፃር በጣም በጥንቃቄና በጥሩ ዝግጅት መካሔድ አለበት››ይላሉ። በተለይም በምክክሩ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት አካታች በሆነ መልኩ ካልተሳተፉበት ለምክክር መድረኩ እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል ሥጋት አላቸው። አገራዊ ምክክሩ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ባካተተና ባሳተፈ መልኩ መካሄድ ይኖርበታል ይላሉ። በምክክሩ ስለኢትዮጵያ ያገባኛል፣ ይመለከተኛል ወይም ደግሞ ጥያቄ አለኝ የሚሉ በትምህርት ደረጃ፣ በሃይማኖት፣ በዘር፣ በፖለቲካ አመለካከትና በጾታ ሳይገደቡ ማሳተፍና ሃሳቦችን መውሰድ ለውይይቱ ፍሬያማነት ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ያሰምሩበታል።
በጅማ ዪኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ከተቦ አብዲዩም፤ ሕዝብ መንግሥትን ካዳመጠ መንግሥትም ሕዝብን ካዳመጠ ውጤታማ መሆን እና ከችግሮች መውጣት የማይቻልበት ምክንያት እንደሚኖር አፅዕኖት ይሰጡበታል። ለእዚህ ደግሞ አገራዊ ምክክሩ እጅግ ወሳኝ መሆኑን ያነሳሉ።
‹‹አገራዊ የምክክር መድረኩ ውጤታማ እንዲሆን ከተፈለገ ከሁሉ በላይ በሁሉ ረገድ አካታች መሆን ይኖርበታል›› የሚሉት ዶክተሩ፤ ይህን ማድረግ ከተቻለ ውጤታማ የማይሆንበት ምክንያት እንደሌለና አካታች ካልሆነ ግን ውጤታማነቱ አጠያያቂ መሆኑ እንደማይቀር ያስገነዝባሉ። ኢዜማ ፣ ብልጽግናና ኦፌኮን የመሳሰሉ ፓርቲዎች ይህን እሳቤ ይጋሩታል። የሶስቱ ፓርቲዎች ከፍተኛ አመራሮች ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ አገራዊ ምክክሩ አስፈላጊና የኢትዮጵያን መሠረታዊ ችግሮች የሚፈታ በመሆኑ የሁሉም የማኅበረሰብ ክፍሎች አመለካከቶችና አጀንዳዎች መወከልና መካተት አለባቸው የሚል አቋማቸውን አሳውቀዋል። ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ፤ ‹‹ አገራዊ ምክክሩ እስከ አሁን እንደ አገር ለተፈጠሩ አለመግባባቶች ምክንያት የሆኑ ችግሮችን ለመፍታትና ከስምምነት ለመድረስ የሰለጠነ አካሄድ ነው›› ይላል። ምክክሩ የሀሳብ ልዩነቶችን በማጥበብ አገሪቷን እንዴት ማስቀጠልና ዘላቂ ሠላም ማስፈን እንደሚቻል ከስምምነት ለመድረስ ወሳኝ መሆኑንም ያነሳል።
‹‹የተለያዩ ሃሳቦች ሊነሱ ቢችሉም ለምክክሩ የሚቀረጹት አጀንዳዎች በዋናነት ኢትዮጵያን ማዕከል ያደረጉና ዘላቂ ሰላምን የሚያመጡ መሆን ይኖርባቸዋል›› የሚለው አትሌት ኃይሌ፤ አገራዊ ምክክር ስኬታማ እንዲሆን ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች የተወከሉበትና አካታች መሆን እንዳለበትም አፅዕኖት ሰጥቶ ይናገራል። ስለ ውይይት ሲነሳ የተለያዩ ምሑራንና መዛግብት አንድን ምክክር ውጤታማ ለማድረግ፣ ከወገናዊነት ነፃ በመሆን ሚዛናዊ አስተሳሰብን ማራመድ፣ ሁሉም እኩል የሚያሸንፈበት /Win-Win Resolution/ መንገድ መከተል፣ ግልጸኝነት፣ ትእግስት፣ መደማመጥ እና የሌሎችን ሀሳብ ማክበር የግድ እንደሚል ያስረዳሉ። በምክክሩ ወቅት በሰዎች መካከል የአመለካከት ልዩነት ሊፈጠር እንደሚችልና የሃሳብ ልዩነቶች ደግሞ ዓላማንና ግብን የማያስቱ እስከሆነ ድረስ ተፈጥሯዊ ሰውኛ /Humanistic/ መሆናቸውን የሚያስረዱት ምሑራኑ፤ የሃሳብ ልዩነቶችን አቻችሎ ለመቀጠል ከሁሉም በላይ ውይይትን ውጤታማ ለማድረግ ግን በተለይ የሰጥቶ መቀበል መርሕ እጅግ ወሳኝ ስለመሆኑ አፅዕኖት ይሰጡበታል።
በውይይቱ ወቅት ስለ አገር አስቀድሞ መነጋገርና ሚዛናዊ ሆኖ የሌሎችን ሀሳብ ለማዳመጥ የራስን ሃሳብ ለሌሎች ለማስረዳት መዘጋጀት እንደሚገባ የሚያስገነዝቡት በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶክተር ካሣ ተሻገር፤ ‹‹ሁላችንም ጥግ ይዘን የሌሎችን ሀሳብ በጥርጣሬ የምንመለከት ከሆነ አገራችንን መታደግ አያስችልም።
ስለሆነም የሀሳብ ልዩነቶችን በቅንነት በመመልከት ሌላው የሚያስበውን በሌላው ጫማ ሆነን መረዳትና በትብብር አገርን ለማስቀጠል የየድርሻችንን ኃላፊነት መወጣት ይገባናል›› ይላሉ።
ለአገራዊ ምክክሩ ውጤታማነት የባለድርሻ አካላት ሚና ከፍተኛ መሆኑና ከሁሉ በላይ ከግልና ከቡድን ጥቅም ይልቅ የአገርንና የሕዝብን ጥቅም ማስቀደም የግድ እንደሚልም የተለያዩ ምሑራን ይስማሙበታል። በዚህ ረገድም በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው ይጠቁማሉ። ‹‹የአገር ሕልውና የገዢ ፓርቲ አሊያም የአንድ ፓርቲ ጉዳይ አይደለም። እንደ ዜጋ ወይም እንደ ፓርቲ መንቀሳቀስ የሚቻለው አገር ስትኖር ብቻ ነው። የአገርን አንድነት የሚጠብቁና የአገርን ጥቅም በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ደግሞ የትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ልዩነት ሊኖረው አይገባም ›› ይላሉ።
የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ባይሳ ለታ ይህን እሳቤ አጥብቀው ከሚደግፉት ምሑራን መካከል ናቸው። ለውይይቱ ውጤታማነት የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ የጎላ መሆኑን የሚያነሱት ፕሬዚዳንቱ፤ በዚህ ረገድ በተለይም የፖለቲካ ፓርቲዎችም አገራዊ ጉዳዮችን በማስቀደም እና የእኔ አጀንዳ ብቻ ይፈጸም ከሚል ግትር አቋም በመውጣት አገራዊ ምክክሩን ለውጤት ማብቃት ይኖርባቸዋል ይላሉ። ከዚህ ባሻገር ለአገራዊ ምክክሩ ሁለንተናዊ ውጤታማነትም መንግሥት የጀመራቸውን ጥረቶች ይበልጥ ማስቀጠል፣ ማኅበረሰቡም በምክክሩ ተሳታፊ በመሆን ውሳኔዎችን ለመቀበልም ሆነ ለመተው ራስን ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን ያሰምሩበታል። ዶክተር ባይሳ፤ ለምክክሩ ውጤታማነት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የምሑራን ሚና የላቀ እንደሆነም ያስረዳሉ።
በተለያዩ አገራት የተካሄዱ አገራዊ ምክክሮች ውጤታማ እንዲሆኑ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የማይተካ ሚና መጫወታቸውን የሚያስረዱት ዶክተሩ፣ እንደአገር ሳያግባቡን የቆዩ ጉዳዮች ምን ምን እንደሆኑ በመለየትና የሚፈቱበትን መንገድ በማመላከት አገራዊ ውይይቱ ለውጤት እንዲበቃ የማድረግ አቅማቸው ከፍተኛ ስለመሆኑም ያመላክታሉ።
አገራዊ ውይይቱ ያለውን ፋይዳ በመረዳት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለጉዳዩ ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ አፅዕኖት የሚሰጡት ዶክተር ባይሳ፣ ለአገራዊ ምክክሩ ግብዓት የሚሆኑ ሃሳቦችን በጥናትና በምርምር በማዳበር እና ልዩ ልዩ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት ኅብረተሰቡ ተገቢውን ግንዛቤ እንዲይዝ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ነው ያስገነዘቡት።
የአምቦ ዩኒቨርሲቲ አገራዊ ምክክሩ ውጤት እንዲያመጣ የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማድረግ መዘጋጀቱን ኅብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲኖረው የሚያስችሉ ሥራዎችን በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ነው ያስታወቁት።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አፀደወይን፤ ‹‹ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የምሑራን መፍለቂያ እንደመሆናቸው መጠን በዚህ አገራዊ ውይይት ላይ ሚናቸው እጅግ የጎላ በመሆኑ የመፍትሔው ባለቤት መሆን አለባቸውም። ›› ይላሉ። የተሳሳቱ ትርክቶችን ማስተካከልን ጨምሮ በጥናትና ምርምር በመታገዝ የመፍትሄ ሀሳቦችን ማፍለቅ ብሎም መንገዱን በማሳየት ረገድ ታሪካዊ ተልዕኳቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸውም አፅዕኖት ይሰጡታል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ውይይቱን ውጤታማ የሚያደርጉና ወደ ብሔራዊ የመግባባት መንገድ የሚወስዱ ቅድመ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ በቀጣይ ኮሚሽኑ በሚያወጣው እቅድና መመሪያ መሠረት ማኅበረሰቡን የማንቃትን ጨምሮ የተለያዩ ተግባራት በማከናወን አገራዊ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ነው ያረጋገጡት። አገራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን የወጣቶች ሚና ግዙፍ እንደሆነም ይታመናል።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ሠላምና ብልጽግና ተልዕኮ ሊግ ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ በቀለም ይህን እሳቤ ያጠናክራሉ። የአገራዊ ምክክሩ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ትልቅ ሚና እንዳለው የሚገልጹት ፕሬዚዳንቱ፤ ለውጤታማነቱ እያንዳንዱ ዜጋ በምክክሩ በመሳተፍ አገራዊ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባልም።›› ይላሉ።
ሊጉ በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ሰላማዊ እንዲሆን ከ200,000 ሺህ በላይ ወጣቶችን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በማሠማራትና በማሳተፍ የበኩሉን ሚና መጫወቱን የሚታወስ ነው። በዚህ አገራዊ ምክክርም ሚናው የጎላ እንደሚሆን ይታመናል። ፕሬዚዳንቱ እንደሚያስረዱት ከሆነ እንደ አገራዊ ምርጫው ሁሉ አገራዊ ምክክሩንም ውጤታማ በማድረግ ሂደት ሊጉ በየደረጃው ለሚገኙ የወጣት አደረጃጀቶች ስልጠናና የውይይት መድረኮች ከማዘጋጀት ጀምሮ የተለያዩ እገዛዎችን የሚያደርግ ይሆናል። ለአገራዊ ምክክሩ የመገናኛ ብዙሃን ሚናም የሚያጠያይቅ አይደለም።
በተለይም ከተጽዕኖ ነጻ መሆናቸው ወሳኝ እንደሆነ በርካቶች ይስማሙበታል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ስነ ተግባቦት ትምህርት ቤት መምህር ዶክተር አንተነህ ጸጋዬ ይህን እሳቤ ከሚደግፉት ምሁራን አንድ ናቸው። ‹‹አገራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን መገናኛ ብዙኃን በገለልተኝነት ማገልገል አለባቸው›› የሚሉት ዶክተር አንተነህ፤ በአገራዊ ምክክር ወቅት የሚዲያ ትልቁ ሥራ ተጨባጭ የሆነውን መረጃ መዘገብ መሆኑንም ያስገነዝባሉ። በእያንዳንዱ ሥራቸው መገናኛ ብዙኃኑ ራሳቸውን ከአሸማጋዮች ነጻ ማድረግ እንዳለባቸውም ያሰምሩበታል።
አገራዊ ምክክሩ የታለመለትን ግብ እንዲመታ የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ገለልተኝነት ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመው፣ ኮሚሽኑን የሚመሩ ሰዎች ከወገንተኝነት ነጻ መሆን እንደሚገባቸው ሳያስገነዝቡ አላለፉም።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ፤ ከቀናት በፊት የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን የሥራ መጀመሪያ ትውውቅ ፕሮግራም በተካሄደበት ወቅት ኮሚሽኑ ሥራውን በገለልተኝነት በመሥራት የተሰጠውን ሕዝባዊ ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል። ፖለቲካ ከአገር በላይ ስላልሆነ ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ መሠረት የተሰጠውን ኃላፊነት ገለልተኛ በመሆን ታሪካዊ ሥራ ሠርቶ ማለፍ እንደሚገባውም አፅእኖት ሰጥተውታል።
የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያም፤ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን አባል ሆነው እንዲሠሩ ኃላፊነት የሰጣቸው ሕዝቡ በመሆኑ ሙሉ ጊዜያቸውን ሰጥተው በኃላፊነት መንፈስ ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን እና ከሚዲያውና ሌሎች አካላት ጋር በጋራ እንደሚሠሩም ነው የተናገሩት። የአስፈፃሚው አካል ወይም የመንግሥት ጣልቃ ገብነት እንደማይኖር እምነታቸው መሆኑን ጠቁመው፤ በኮሚሽኑ አሠራር ውስጥ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት የሚኖር ከሆነ ግን ኃላፊነታቸውን በፈቃዳቸው እንደሚለቁ አሳስበዋል።
የኮሚሽኑ አባላትም ኮሚሽኑ ለሚሠራው አገራዊ ምክክር ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ተሞክሮዎችን በማካተት እና በሕዝቡ መካከል ብዙ የባህል ትስስሮች ስላሉ ዕድሉን ለሕዝቡ በመስጠት እንዲሁም በማወያየት በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አለመግባባቶች በውይይት በሚፈታበት ሁኔታ ላይ አበክረው እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሶስተኛ አስቸኳይ ስብሰባ ላይ፤ ‹‹ኢትዮጵያውያን አገራዊ ምክክሩን ቀለል አድርገው ሊያዩት አይገባም ›› ሲሉ አሳስበዋል። ‹‹በኢትዮጵያ ጉዳይ የሚወስነው በኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ነው››ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ድርድሩ የሚካሄደው በሥልጣን ክፍፍል ጉዳይ ላይ ሳይሆን በቆሰሉ ታሪኮቻችን ሕክምና ላይ እና በምንገነባው ነገ ላይ ነውም ብለዋል።
የምንገነባው ነገ ከሥልጣንና ከፓርቲ በላይ ስለሆነ ማረቅ ያለብን ጉዳይ እንኳን ካለ ለመጪው ትውልድ ስንል ለማድረግ ዝግጁዎች ነን ሲሉም አክለዋል። ምክክሩ ጠቅላላ ሂደቱ ግልፅ፣ ሁሉን ማኅበረሰብ የሚያካትትና ሕዝብ የሚያሳትፍ መሆን እንዳለበት ሳያሳስቡ አላለፉም።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን የካቲት 22 /2014