የዛሬ እንግዳችን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እንዲሁም የሥራ፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር ዓባይ ናቸው። በኑሮ ውድነት፣ በጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ፣ በመሰረተ ልማት ግንባታ፣ በከተማ ፀጥታ፣ በህገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በአገልግሎት አሰጣጥና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፡- የከተማ አስተዳደሩ የስድስት ወራት አፈፃፀምና ግምገማ ምን ይመስል ነበር?
አቶ ጃንጥራር፡- ከተማ አስተዳደሩ በስድስት ወራት በብዙ ሥራዎች ስኬታማ ነበር። አልፎ አልፎም የበለጠ ጥረት የሚጠይቁ እንዳሉም ገምግመናል። ጦርነት ላይ ሆነን ጦርነቱን ለመቀልበስ ትልቅ ሃብት የማሰባሰብ እንዲሁም የአካባቢን ሠላም ማስከበር ሥራ ውጤታማ ነበር። ሰራዊታችንን መደገፍ ብቻ ሳይሆን የከተማዋን ሠላም በማስጠበቅ ብሎም ህዝባዊ ሰራዊት በማዘጋጀት ከተማዋን ጭምር የፀጥታ መዋቅሩ እና አመራር በጋራ ብሎም መላው ህዝብ በመናበብ በአንድ በኩል ሠላምን የማረጋጋጥ ሥራ በሌላ በኩል የታቀዱ ሥራዎችን በስኬታማነት ማከናወን ተችሏል። በአጠቃላይ ውጤታማ ነበር።
በከተማዋ ገቢ በማሰባሰብ በመሰረት ልማት ማለትም መንገድ፣ ጽዳትና ውበት፣ ንጹህ የመጠጥ ውሃ፣ አረንጓዴ ልማት፣ ሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ትምህርት ፣ ጤና፣ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅና መጠነ ሰፊ ትርጉም ያላቸውን ሥራዎችን ማከናወን ተችሏል።
ስራዎች በታቀደው መልኩ ስኬታማ ቢሆኑም ብዙ ተጨማሪ ሥራ መሥራት እንደነበረብን ተገምግሟል። ከአገልግሎት አሰጣጥ አኳያ የተገልጋይ ምሬት አለመቀነስና ሌብነት፣ ህገወጥነትና አልፎ አልፎ የሚታየው እንቅስቃሴ ላይ በሰፊው መሥራት እንደሚጠበቅብን ተገንዝበናል። የኑሮ ውድነትና የቤት እጥረት ከፍላጎት አኳያ አቅርቦታችን ተጨማሪ ሥራ እንደሚጠይቀን ገምግመናል። በሚቀጥሉት ጊዜያት የበለጠ ርብርብ ማድረግና ችግሩን ማቃለል ላይም መሥራት አለብን። ንግድና ገበያ ማረጋጋት ላይ የሰራናቸው ሥራዎች ትንሽ ባይሆኑም፤ የኑሮ ማሻቀቡ እልባት ባለማግኘቱ አሁንም ምሬት በመኖሩ እያስተካከሉ መሄድ ይገባል። የጀመርናቸው የተቋማዊ ሪፎርም ሥራዎችንም በቴክኖሎጂ መደገፍ ይጠበቅብናል። በቅርቡ ተራ የተሽከርካሪ አካል መስረቅና የመሳሰሉት ይስተዋላል። እነዚህን ለማስቀረት ክትትልና ወጥ የሆነ የስምሪት ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- ከአፈፃፀሙ በመነሳት የተቀመጠው አቅጣጫ ምንድን ነው?
አቶ ጃንጥራር፡- እኔ የምመራው የሥራ፤ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ አምስት ተቋማትን ወደ አንድ አምጥቶ ማለትም የቀድሞ ሥራ እድል ፈጠራ፣ ምግብ ዋስትና፣ አሰሪና ሰራተኛ፣ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ፣ ኢንዱስትሪ ቢሮ እና መስሪያ ቦታዎች ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ አንድ ላይ በመሰብሰብ በአንድ ቢሮ ስራዎች እንዲከናወኑ ሆኗል ። በዚህም የሰው ኃይል ስምሪቱንም በሪፎርሙ መሰረት ሰርተናል፣ አደራጅተናል፤ ሰራተኛም ደልድለናል።
በዚህም የተሳኩ ብዙ ነገሮች አሉ። በስድስት ወር ውስጥ 227ሺ በዓመት ደግሞ 350ሺ ዜጎች ሥራ ዕድል ለመፍጠር አቅደን በግማሽ ዓመቱ 297ሺ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል። በዚህ ዘርፍ ፀጋ ልየታ እና ሥራ ፈላጊዎች ምዝገባ ተካሂዷል። በሌላ መንገድ የዚሁ አካል የሆነው በምግብ ዋስትና እጅግ እልህ አስጨራሽ የማጥራት ሥራ ተከናውኗል። 13ሺ የሚደርሱ የኮሚቴ አባላት የተሳተፉበት የማጣራት ሥራ ሠርተን 109ሺ የሚደርሱ ዜጎች በሁለተኛው ምዕራፍ የምግብ ዋስትና ተጠቃሚ እንዲሆኑና ጥራቱን በጠበቀ መንገድ አከናውነን በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይፋ አድርገን ሥራዎችን አስጀምረናል።
49 ሺ 200 የሚደርሱ ደግሞ የመጀመሪያው ምዕራፍ ሁለተኛው ዙር አስመርቀን ወደ ዘላቂ የኑሮ ማሻሻያ እንዲገቡ የሚያስችል ሥራ አከናውነናል። መስሪያ ቦታዎች ላይ የሚታየውን ሰፊ ክፍተት የማጥራት ሥራ አከናውነን በቂ ባይሆኑም መሰረት ልማት አሟልተንና ህገ ወጦች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ አድርገናል።
ከ900 በላይ ያለአግባብ ተይዘው የነበሩ ይዞታዎችን ለሚመለከታቸው አካላት አስተላልፈናል። በሌላ በኩልም 4 ሺ 197 በላይ ተሸጋግረው ለረጅም ጊዜ ተይዘው የቆዩ ሼዶች በምን ሁኔታ ይተዳደሩ በሚለው ላይ ውሳኔ የተላለፈ ሲሆን ለብዙ ዓመታት መሬት ይዘው የተቀመጡት ላይም በተመሳሳይ ጥናት ተካሂዷል።
በብድር አቅርቦት በኩል አፈጻጸሙ 68 በመቶ ሲሆን ይህም ዝቅ ያለ እንደሆነ አይተናል ። ብድር ማስመለስ ላይም 77 ከመቶ ነው ያሳካነው። ሁሉንም አማራጮችን መጠቀም ላይ ብዙ ርቀት መጓዝ አለብን።
ቀደም ሲል በተዘዋዋሪ ፈንድ ከተሰጠው ካቀድነው ያስመለስነው 44 ከመቶ ብቻ ነው። ብዙ ገንዘብ ቢመለስም ብዙ ይቀራል። እንደሚታወቀው ይህ ገንዘብ ቀደም ብሎ የተሰራጨ ነው። አንዳንዶቹ አድራሻቸውን አጥፍተዋል፤ ሌሎች ደግሞ በመደበኛ መንገድ በወቅቱ እየከፈሉ ነው። ከዚያ ውጭ ኢንተርፕራይዝ በማደራጀት፣ ወደ ሥራ በማስገባት ሽግግር ላይ ብዙ መስራት ይጠበቅብናል።
በስድስት ወር 1 ሺ 800 በላይ ኢንተርፕራይዞችን አደራጅተናል። ከእቅድ አኳያ ግን ዝቅ ያለ በመሆኑ በስፋት መሥራት አለብን። አንዳንዶቹ ሂደታቸው ረዘም ይላል። ለአብነት በከተማ ግብርና መሬት ከማዘጋጀት፣ ማሰልጠን ጀምሮ በቁርጠኝነት የሚገቡበትን መለየት በራሱ ጊዜ ይወስዳል። በቀጣይ ስድስት ወራት ብዙ ኢንተርፕራይዞችን ወደዚህ እናስገባለን።
በኢንዱስትሪ ዘርፉም ተተኪ ምርቶችን የሚያመርቱ ፋብሪካዎችን ወደ ዘርፉ የማስገባትና ነባሮቹን የማጠናከር ምርት ወደ ውጭ የሚልኩትን ቁጥራቸውን በማሳደግ ረገድ ስንመለከት አፈፃፀማቸው ተስፋ ሰጪ ነው። በአሰሪና ሰራተኛ በኩልም ጥሩ እምርታ አለ። ከኤጀንሲዎችና ማህበራት ጭምር ሠራተኞቻቸው እንዳይበተኑ ውይይት ተደርጓል።
በውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት በኩል ብዙ ሥራ ተሰርቷል፡ በዚህም እንደ አዲስ አበባ ከተማ 600 ለሚሆኑ የውጭ ዜጎች የስራ ፍቃድ ተሰጥቷል ። ይህ ሁሉ ሆኖ ወደ አገልግሎት ዘርፍ የሚያዘነብሉ በመሆኑ ወደ አምራች ኢንዱስትሪ ወይም ዕድገት ተኮር ዘርፍ እንዲገቡ ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል።
በስድስት ወራት ውስጥ የስራ ዕድል የተፈጠረላቸው 297ሺ ዜጎች አጠቃላይ ሁኔታ የሚታወቅ ሲሆን እንደከዚህ ቀደሙ ሪፖርቶች በሀሰት እንዳይቀርቡ ተግባብተን ነው የምንሰራው ። የሀሰት መረጃ የሚያመጣ ማንኛውም አካል ተጠያቂ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- ከተማዋ ውስጥ ካለው ሥራ ፈላጊ አኳያ የተፈጠረው የሥራ ዕድል በቂ ነው?
አቶ ጃንጥራር፡- መተማመን ያለብን የምናየውን ሳይሆን መረጃውን ነው። ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ያጠናው ጉዳይ አለ። በየዓመቱም የሚያስቀምጠው ትንበያ አለ። በእኛ በኩል የ10 ዓመት ፕላን አለን። የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድም እንደዛው ። ከዚህ ደግሞ የሚቀዳ የአንድ ዓመት እቅድ ይወሰዳል። የ10 ዓመት ፕላን ስናዘጋጅ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ያጠናውን መሰረት አድርገን ነው። በዚህም በፈረንጆቹ 2015 ያጠናው ጥናት ነበር። የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ በፈረንጆቹ አቆጣጠር 2022 የአዲስ አበባ ህዝብ ብዛት ስንት ይደርሳል ብሎ ተንብዯል። ከዚህ ተነስተን ተፈጥሯዊ እድገቱ አለ። በሥራ እድል ፈጠራ 2013 በጀት ዓመት እቅድ 280ሺ ነበር። 2014 በጀት ዓመት ደግሞ 350ሺ ነው። ከዚህ በመነሳት የ10 ዓመትም እቅድና ምጣኔ አለ። ከአዲስ አበባ ህዝብ 19ነጥብ3 በመቶ ሥራ ፈላጊ ነው የሚል ጥናት አለን። ይህን ጥናት ወስደን ወደ አንድ ዲጂት እንዴት ማውረድ ይቻላል፣ በዓመት ስንት የሥራ እድል ቢፈጠር ነው በሚለው ላይ ስሌት አለ። ይህ በጥናት ላይ ተመስርቶ ነው። በተፈጥሯዊ እድገቱና የሥራ እድል ፈጠራው እቅድ ችግር የለውም። ነገር ግን ወደ አዲስ አበባ የሚገቡ ወይንም ደግሞ ውስጣዊ ፍልሰቱ ከፍተኛ ነው። የፍልሰት ፖሊሲው ገና ረቂቅ ላይ ነው። ይህን ሁሉ ግምት ውስጥ አስገብተን ሳይሆን ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ መሰረት አድርገን ነው። በዚህ ረገድ ችግር የለበትም።
እኛ እያደረግን ያለው ሥራ ፈላጊ እና ሥራ የተፈጠረለትን እንለያለን። ግን ከአዲስ አበባ ውጪመጥተው ሥራ የተፈጠረላቸው አሉ። እኛ ይህ ለምን ሆነ ብለን አናወራም። በአንድም በሌላም ዜጎች ስለሆኑ ቢጠቀሙ ክፋት የለውም።
አዲስ ዘመን፡- በሥራ ዕድል ፈጠራ አዲስ አበባ እና ዙሪያ ያሉ ከተሞች ትስስር ምን ይመስላል?
አቶ ጃንጥራር፡- ሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ እቅድ ስናቅድ አዲስ አበባን ማዕከል አድርገን ነው። አዲስ አበባ ከዙሪያዋ ተጠቃሚ ትሆናለች፤ አዲስ አበባ ዙሪያ ያሉትም በዚያው መጠን ተጠቃሚ ናቸው። ወደ አዲስ አበባ ያለው ፍልሰት ከአዲስ አበባ ዙሪያ ብቻ ሳይሆን ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ነው። ትልቁ የኢኮኖሚ ከተማ በመሆኗ ይህን ሁሉ አስቦ መስራት ያስፈልጋል ። እንደ ሀገር የሚሠራበትም ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- አሁን በጥናቱ መሰረት ሥንት ሥራ አጥ አለ?
አቶ ጃኝጥራር፡- በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2012 የአዲስ አበባ ህዝብ 6 ነጥብ 8 ሚሊዮን ነው ተብሎ ይታሰባል። ከዚህ ውስጥ አንድ ሚሊዮን በላይ ሥራ ፈላጊ አለ ተብሎ ይታሰባል። እኤአ 2017 ጥናት ተካሂዶ ነበር። ሥራ ፈላጊ የነበረው 780 ሺ ነበር። በሂደት የሥራ ዕድል እየፈጠርን ይህን አሃዝ እየቀነስን እንሄዳለን።
አዲስ ዘመን፡- ኢንተርፕራይዞች የመሸጋገሪያ ጊዜ አጠናቀው የማይሸጋገሩ ሌሎችን ደግሞ መሸጋገር እየፈለጉ መሰረተ ልማት ባለመሟላቱ በዚያው እየዳሁ ነው። በዚህ ላይ ምን እየተሠራ ነው?
አቶ ጃኝጥራር፡- ከዚህ በፊት የተሸጋገሩት የት ናቸው፤ አሁን መሸጋገር ያለባቸው ምን ላይ ናቸው፣ ምን የሥራ ዕድል ፈጠሩ የሚለውን አይተን ውሳኔ ወስነናል። ዝም ብሎ የተወሰደ ሳይሆን ጥንቃቄ የተሞላበት ነው። የኢኮኖሚ፤ የሀገርና የቤተሰብ ጉዳይ ነው። ከዚህ አኳያ በንግድ፣ አገልግሎት እና በማኑፋክቸሪንግ ላይ የተሰማሩ አሉ። የእነሱን የሽግግር ጊዜ ታሳቢ በማድረግ እና ለሌሎች ሥራ ፈላጊዎችም ዕድል እንዲሰጡ ታሳቢ በማድረግ ወስነናል ተግባራዊም ይደረጋል።
በርካታ ችግሮች አሉ። ለምሳሌ ኢንተርፕራይዞች አምስት ዓመት ሲሞላቸው ቀጥሎ ወደሚጠበቅባቸው ደረጃ ሲሸጋገሩ ምን ይሁን ለሚለው መልስ አልነበረም። በወቅቱ ወደ ሥራ መግባታቸውና መሠረተ ልማት መሟላቱም የትንታኔው አካል ሆኖ ይታይል። አንዳንዶች ቦታ ወስደው የሚያከራዩ፣ የሚጠፉና ላልተፈለገ አገልግሎት የሚያውሉ አሉ። ውሳኔዎችን ስንወስን በተቻለ መጠን በመረጃ ላይ ተመስርተን ለሁሉም ጠቃሚ በሆነ መንገድ ነው። ከክፍለ ከተማ መረጃዎችም ሲመጡ በሶፍት ኮፒ ብቻ ሳይሆን በሃርድ ኮፒ ተፈርመው እንዲመጡ ነው የምናደረገው። አንዳንዶች መሸጋገሪያ ጊዜያችን ሳይደርስ መስሪያ ቦታ ልቀቁ ተብለናል እያሉ ነው፤ ሌሎች ደግሞ ብዙ ዓመት ቦታውን ይዘው ይቀመጣሉ። ለዚህም በበቂ መረጃ ላይ ተመስርተን ነው መወሰን ያለብን። የዘርፉ ችግሮች ግን አንድና ሁለት ተብለው የሚጠቀሱ ብቻ አይደሉም።
አዲስ ዘመን፡- እየተባበሰ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለመቀነስ ምን እየተሠራ ነው?
አቶ ጃንጥራር፡- የግሽበቱ ዋናው ምክንያት ምንድን ነው ?ስንል ጥናቶች መልስ ሊሰጡ ይችላሉ። እንደ አዲስ አበባ ችግር ስናይ በመሰረታዊነት አቅርቦትና ፍላጎት አልተጣጣመም። በተለይ ከግብርና ምርት አኳያ የሚፈለገው መጠን ሲቀርብ ዋጋው ዝቅ ማድረግ ይቻላል። ይህን ለማረጋጋት የከተማ አስተዳደሩ አንድ ቢሊዮን ብር መድቦ ማህበራት ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የግብርና ውጤቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያቀርቡ ሃብት መድበናል።
ለሸገር ዳቦ በየጊዜው የዋጋ ንረቱን በማሰብ ድጎማ እየተደረገ ነው። የከተማ አስተዳደሩ በስድስት ወራት ብቻ ለሸገር ዳቦ 309 ሚሊዮን ብር ድጎማ አድርጓል። ግን ይህ እርካታ ፈጥሯል ወይ ሲባል ገና ብዙ መሥራት ይጠይቃል።
ገበያው አንዴ ከተሰቀለ የመቀነስ አዝማሚያው በሚፈለገው ደረጃ አይደለም። የገበያ ዋጋ እና ንፅፅርም መታየት ያለበት ከባለፈው ወይንም ቅርብ ዓመታት አኳያ እንጂ የዛሬ 10 ዓመት እንደ መነሻ በመውሰድ አይደለም። አሳሳቢ እየሆነ ያለው የኑሮ ውድነቱ የሚቀንሰው ምን ቢደረግ ነው ?የሚለው ሳይንስ ነው። ሀገራዊ መፍትሄ ከክልሎች ጋር በመቀናጀት ለመፍታት እየተሰራ ነው። የዓለም ገበያ እየተረጋጋ ካልሄደ የኑሮ ውድነቱ እየፈተነን ይሄዳል።
አዲስ ዘመን፡- ብዙ ውሳኔዎች ሳይንሳዊ ከመሆን ይልቅ ፖለቲካዊ በመሆናቸው ለችግሮች መፍትሄው እየራቀ ነው ይባላል። እርስዎ ምን ይላሉ?
አቶ ጃንጥራር፡- ፖለቲካዊ ውሳኔ ሲባል ምን ማለት ነው?፤ ሳይንሳዊ ውሳኔስ? ለአዲስ አበባ ኑሮ ውድነት ለመቀነስ ሳይንሳዊ ውሳኔና ትንታኔ የሚያቀርብ ካለ በራችን ክፍት ነው በጣም ጠቃሚ ስለሆነ ። ከምንም በላይ እንደግፈዋለን፤ የእኔ ቢሮም ይደግፈዋል። ከዚህ በላይ የምንፈልገው የለም። ለዳቦ ከመደጎም ውጪ ሌላ ሳይንስ አለ የሚል አካል ካለ በጣም ደስ ይለናል። ስንዴን የሚተካ እና በአጭር ጊዜ የሚደርስ ምርት አለ ብሎ ሳይንሳዊ ትንታኔ የሚሰጠን ካለ ከዚህ በላይ ወርቃማ ዕድል የለም። ይህን የሚሠራ ካላ ለድጎማ የምናውለው አንድ ቢሊዮን ብር ሌላ መሠረተ ልማት እንሰራበታለን። በዘርፉ ብዙ እውቀት ያለውን በደስታ እንቀበለዋለን።
አዲስ ዘመን፡- የመኖሪያ ቤት፣ የትራንስፖርትና አገልግሎት አሰጣጥ ችግርም የከተማዋ ነዋሪዎች ቀዳሚ ጥያቄ ነው። ምን እየተሠራ ነው?
አቶ ጃንጥራር፡- ሦስቱም ጉዳዮች ትክክለኛ የከተማችን ችግሮች ናቸው። አገልግሎት አሰጣጥ ችግር እኛም በምክር ቤቱ ውይይት አድርገንበታል። በየደረጃው ህዝብ እጅ መንሻ ይጠይቃል፤ ኔት ወርክ አለ በሚል የህዝብ ቅሬታ በየደረጃው ይቀርባል። ይህ ለምን አይፈታም ብለን በተደጋጋሚ እናነሳለን። ይህ የአመራርና ባለሙያው የአገልጋይነት መንፈስና አስተሳሰብን ይፈልጋል። ከሰው ንክኪ ነፃ የሆነ ቴክኖሎጂ ያስፈልገዋል። የእኛ አካሄድና ህዝብ ፍላጎት አልተጣጣመም። በሌላ ዓለም ያለውን ምርጥ ተሞክሮ እየወሰድን የህዝቡን ፍላጎት ለመጠበቅ እየሠራን ነው። በዚህ ላይ ዋናው ነገር ሥርዓት መዘርጋት፣ በቴክኖሎጂ ማዘመንና በአስተሳሳብ ማደግ ነው። ከአሁን በኋላ በጅምላ ንግግር የሚፈታ ችግር የለም። ችግር የሚፈጥረውን ለይተን እርምጃ እንወስዳለን። ህዝቡ ሊያግዘን ይገባል። ሚዲያውም ይህን ማጋለጥ አለበት። የተወሰኑ የመንግስት አመራሮች ብቻ አይፈቱትም።
በትራንስፖርት በኩል ሸገር ድጋፍ ሰጪ አስገብተን እየሰሩ ጥሩ ለውጥም አለ። ተጨማሪ አውቶቡሶችን የግዥ ሂደት እየተከናወነ ነው። የመንገድ መሰረተ ልማትንም ማስፋፋት ሌላው መፍትሄ ነው። የመንገድ መሰረተ ልማታችን ከእቅድ አኳያ ጥሩ ቢሆንም ከፍላጎት አንጻር በቂ አይደለም። ይህ ታስቦበት እየተሠራ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ሌሎች አዳዲስ አማራጮችንና ትራፊኩን ለማሳለጥ የሚጠቅሙ ተግባራትን እየተገበርን ነው። በአንድ ጊዜ ችግሩን መፍታት ባይቻልም መፍትሄ እየሰጠን እንሄዳለን ። ወደፊት ስትራቴጂካል ሆኖ ማሰብም ይጠይቃል።
ከቤት ልማት ጋር ያለው ብዙ ጊዜ ተጠይቄ ብዙ ግዜ ምላሽ ሰጥቼበታለሁ። አንዳንድ ጊዜ ጥያቄው ተደጋግሞ ሲመጣ ለመመለስ ትንሽ መፍትሄ አበጅተህ፤ ትንሽ ውጤት አሳክተህ በሚሆንበት ጊዜ ላትቸገር ትችላለህ። ቤት ላይ ያለን ‹‹ዲፊሲት›› እና ህዝቡ ፍላጎትና አቅርቦት አለመጣጣም ችግር በህዝቡ ውስጥ ያለውን ምሬትና ህመሙን እናውቀዋለን። በተደጋጋሚ ያስተላለፍኩት መልዕክት ቤት ላይ ያለን ሥራ ብዙ ጥረቶች አድርገን አሁንም ተጨባጭ የሆነ ‹‹ማስ›› የሆነ የቤት ልማት ሥራ ውስጥ ከመግባት አንፃር ጥረቶች አሉ።
አሁን የጀመርነው 5ሺ ቤት አለ። ያሉትን የማጠናከር ጉዳይም እንደዛው። ይህ ለምን ተፈጠረ ብለን ወደ ኋላ ሄደን ስናጣራ ብዙ ችግሮች አሉበት። አራብሳ ላይ 40ሺ በላይ ቤት ባለበት ‹‹ትሪትመንት ፕላንት›› አብሮ ዲዛይን ተደርጎ አልተሰራም፤ ውል ሆኖ አልተሰጠም። በምን ያህል ገንዘብ ይከናወናል የሚለውም በተመሳሳይ አልተሰራም። ይህ በመሆኑ የመሰረተ ልማት ሥራዎች በሁሉም የጋራ መኖሪያ ቤቶች በ40/60 ሆነ 20/80 አካባቢ የውል አካል አልነበሩም። ይህን የከተማ አስተዳደሩና እኛ ከመጣን በኋላ ብዙ ቢሊዮን ብር መድበን ለኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ሰጥተን ነው ያስጀመርናቸው። መሰረተ ልማት ሳይሟላ ቤቶችን ማስተላለፍ አይቻልም። በእርግጥ በወቅቱ ግፊት ስለነበር እኔም ከተማ ልማት ሚኒስቴር እያለሁ የተላለፉ ቤቶች ነበሩ። የነበረው እሳቤ ቀሪ ሥራዎችን ነዋሪ የሚያጠናቅቅበት ሁኔታ ካለ እናወያይ በሚል ነው። አሁን ላይ ግን መሰረተ ልማት አሟልቷን ለማስተላለፍ በስፋት እየሠራን ነው። ቀሪዎቹንም አጠናቀን እናስተላልፋለን። አዳዲስ ቤቶችን ለመጀመር ከባንክ ብድር አልተፈቀደልንም። ለጊዜው የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ 5ሺ ተገጣጣሚ ቤቶችን ለመሥራት እየተጋን ነው። የውጭ አልሚዎችን ከደቡብ አፍሪካ እና ናይጄሪያ ጋብዘን በስራው ላይ እንዲሳተፉ ጥረቶች ቢኖሩም ባሰብነው ልክ አልሆነም። ብዙ ውስብስብ ችግሮች በመኖራቸው በቀጣይ ይህን ለማቃለል እየሠራን ነው።
አዲስ ዘመን፡- የኢንተርፕራይዞችን ችግር ለማቃለል ሲባል የክላስተር ልማት እንደሚገነባ ተነግሮ ነበር። ከምን ደረሰ?
አቶ ጃንጥራር፡- የክላስተር ልማት ዲዛይን አጠናቀን ጨረታ አውጥተን በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ 93 ሄክታር መሬት ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ እየተገባ ነው። በመጀመሪያው ዙር በተፈቀደው መሬት ላይ ነው እየተሰራ ያለው። መሬቱን ነፃ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው። ይህ ክላስተር ስማርት የሆነ የማይክሮ߹ መካከለኛ እና አነስተኛ ኢንዱስትሪ ከተማ በሚል እሳቤ እየተሰራ ነው። ለኢንተርፕራይዞች ሽግግር ጠቃሚ አድርገን እንወስዳለን። ይህ ከስማርት ከተማ የመነጨ ሃሳብ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዲስ አበባ ህገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር መዳረሻ የማድረግ አዝማሚያ እየታየ የመጣው ለምንድ ነው?
አቶ ጃንጥራር፡- ከህገ ወጥ መሳሪያ ዝውውር ጋር በተያያዘ ከተማዋ የፀጥታ መዋቅሩ፣ አመራሩ እና ህዝብ በመቀናጀት መጠነ ሰፊ ሥራ እያከናወኑ ነው። ቁጥሩን ማንሳት ባያስፈልግም ብዙ መሳሪያ መቁጠር ይቻላል። አዲስ አበባን ለምን ማዕከል አደረጉ የሚለው መሳሪያ አዘዋዋሪቹ መልስ መስጠት አለባቸው። ግን የምንገምታቸው ነገሮች አሉ። የሀገሪቱ ዋና ከተማ እና የኢኮኖሚ ማዕከል በመሆኗ፤ ዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ ተቋማት በብዛት ከመገኘታቸው አንጻር እንደሚታወሰው በአሸባሪ ኃይል አጀንዳ ተደርጎ አዲስ አበባን በአጭር ጊዜ እንበጠብጣለን ብሎ ከማሰብ አንጻር ነው።
ጦርነቱን አዲስ አበባ አድርገን መንግስትን በአጭር ጊዜ እናስወግዳለን የሚለውን ፕሮፓጋንዳ አሸባሪው ሕወሓት ሲጠቀምም ነበር ፤ ግን እንዳሰበው አልሆነለትም። አሁንም ቢሆን ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ መተላለፊያ የማድረጉ ሙከራ መኖሩ አይቀርም። ሌላው አዲስ አበባ ወደ ሁሉም የሀገሪቱ አቅጣጫ ለመተላለፍ መስመር እና ማዕከል ስለሆነች ነው። አዲስ አበባን ሠላም በማሳጣትም የሚፈልጉትን አጀንዳ መፈፀምም ሌላኛው እቅዳቸው ነው። በኢትዮጵያ ላይ ሲደረግ የነበረው ዘመቻ ይታወሳል። በተደጋጋሚ መግለጫ ያወጡና ከፍተኛ ቅስቀሳ ያደረጉ ሀገራት ነበሩ። እኛ ግን የተለያዩ ዲፕሎማቶችን በመሰብሰብና እውነታውን በማስረዳት ሁኔታውን ማለፍ ችለናል። ፀጥታ መዋቅሩና ህዝቡ ጋር በመሆን አዲስ አበባ ሠላማዊ ከተማ መሆኗን ማሳየት ተችሏል። ይህ ማለት ግን ህገ ወጥነት አሁንም የለም ማለት አይደለም። አልፎ አልፎ ተራ ስርቆቶች አሉ። ይህን መቆጣጠር የሚያስችል ስርዓት ተቋቁሟል።
የከተማ አስተዳደሩ ዋና ሥራው ህገ ወጥነትን መከላከልና ዜጎች በሠላም ወጥተው እንዲገቡ ማድረግ ነው። መሰረተ ልማቶችን ማሟላት፣ የኑሮ ውድነትን ማረጋጋት ቀዳሚ አጀንዳ ሆኖ ይቀጥላል። ህገ ወጥ መሬት ወረራ ማስቆም፣ ሥራ ዕድል መፍጠር፣ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር መቆጣጠር በየጊዜው እየተከታተሉ መፍትሄ የሚበጅለትና የከተማ አስተዳደሩ ቀዳሚ አጀንዳ ሆኖ የሚቀጥል ይሆናል።
አዲስ አበባ፡- የከተማዋ ፈተና ከሆኑት አንዱ ለተቋማት የቢሮ ኪራይ ክፍያ ነው። እርስዎ ያሉበት ቢሮ ጨምሮ ከፍተኛ ሃብት የሚወጣበት ነው። ይህን የሃብት ብክነት ለማስቀረት ምን እየተሠራ ነው?
አቶ ጃንጥራር፡- ይህ ጥያቄ በምክር ቤትም ተነስቷል፤ ለቢሮ ኪራይ ከፍተኛ ሃብት ይወጣል። ቀደም ብሎ ቢሮ መገንባት ነበረበት። በዚህ ዓመት እቅድ ይዘን ዲዛይን አሰርተን ቦታ ምርጫ አከናውነናል። ወደፊት እንገነባለን። ነገር ግን ሁሉንም በአንድ ጊዜ ማጠናቀቅ አይቻልም በመሆኑም ለተወሰነ ጊዜ ቢሮ ኪራይ እየከፈልን መቀጠላችን አይቀሬ ነው። ሁሉንም ተቋማት የሚያቅፍ ህንፃ ለመገንባት ወደ ሥራ ገብተናል። እኛ ፈልገን አይደለም ተገደን ነው ወደ ኪራይ የገባነው። ሌላው ቀርቶ ከግለሰብ ስንከራይ እንደፈለግን ዲዛይን አንቀይርም። በመሆኑም ሃብት መባከን ስለሌለበት ግንባታ ለማከናወን አቅደናል።
አዲስ ዘመን፡- የዝግጅት ክፍላችን እንግዳ ስለሆኑ እናመስግናለን።
አቶ ጃንጥራር፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን የካቲት 21 ቀን 2014 ዓ.ም