126ኛ አመቱ ሊዘከር በዋዜማው ላይ ነው:: ኢትዮጵያውያን በወራሪው ጣልያን ላይ የተቀዳጁት ታላቅ ድል :: አድዋ:: በኢትዮጵያውያን ጠንካራ አንድነትና የሀገር ፍቅር ስሜት የተገኘው ይህ ድል ኢትዮጵያን መድፈር፣ ለመድፈር መሞከር ምን ያህል ዋጋ አንደሚያስከፍል አለምን በተለይም ምእራባውያንን በሚገባ ያስተማረ ነው:: አድዋ ለኢትዮጵያውያን የነጻነት ጮራና የድሎች ሁሉ አልፋና ኦሜጋ፣ አንድ ስንሆን ማሸነፍ አንደምንችል ትምህርት ሰጥቶ ያለፈ ሲሉ ኢትዮጵያውያን ይገልጹታል::
አድዋ በኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን፣ በወቅቱ በቅኝ ግዛት ውስጥ ሲማቅቁ ለነበሩ መላ አፍሪካውያን ብቻ ሳይሆን በመላ አለም ለሚገኙ ጥቁሮችም ልዩ ትርጉም ነበረው:: የአድዋ ድል ብዙዎቹን በቅኝ ግዛት ስር የነበሩ አፍሪካውያን ለአውሮፓውያን ውጋት መሆን አንዲጀምሩ ቀስ በቀስም ገዝግዘው እንዲጥሉዋቸው የትግል እርሾ ሆኖ አገልግሏል:: ነጮች አንደማይሸነፉ አርገው ይቆጥሩ የነበሩ አፍሪካውያንን በአንድነት አነቃቅቶ ለፍልሚያ አነሳስቷል፤ የይቻላል መንፈስን ዘርቷል፤ ባለድልም እስከ ማድረስ ደርሷል::
አድዋ ከጥቁሮችና ከአፍሪካውያን እንዲሁም ከሰው ዘር አኳያም ብዙ ትርጉም ተሰጥቶታል:: ጥቁር ህዝብን ከመጥፋት የታደገ ሲሉ የሚገልጹት አሉ:: ለአፍሪካውያን ነጻነትን ያጎናጸፈና ለሰብአዊ መብት መከበርም መሰረት ተብሎም ይገለጻል::
ለጣልያን ደግሞ መቼም ከውስጧ የማይወጣ ዝንተ አለም የሚያንገበግብ ታሪክ ነው:: ሽንፈቱ የውስጥ እግር እሳት ሆኖባት ኖራለች፤ በአውሮፓውያንና በአፍሪካውያን ፊት ቆመው መሄድ ሳያሳፍራቸው አንዳልቀረ መገመት አይከብድም:: 40 አመታትን ቂም አርግዛ ቆይታ በበቀል ስሜት ከፍተኛ ዝግጅት አድርጋ ያን የውርደት ካባ አውልቃ ለመጣል በ1928 አም ኢትዮጵያን የወረረችውም ለእዚህ ነው:: ሂሳብ ልታወራርድ!
አድዋ በመላ አውሮፓና አለምም ይታወሳል:: አውሮፓውያን አፍሪካን የመቀራመት እቅዳቸው እየከሸፈ መሆኑን አድዋ በሚገባ አላረዳቸውም ማለት አይቻልም፤ በቅኝ ግዛት ከያዙዋቸው ሀገሮች አንድ ቀን ጓዛቸውን ጠቅልለው ተዋርደው ሊወጡ አንደሚችሉ ከአድዋው የኢትዮጵያውያን ድል በሚገባ አልተገነዘቡም ተብሎ አይወሰድም::
እናም አድዋ ትልቅ ድል ነው:: በመላ አለም በየቤተመጽሀፍቱ በመጽሀፍ በመጽሀፍ ሆኖ ተሰንዶ በስፋት ይገኛል:: ስለ አድዋ ብዙ ተጽፏልና:: በሀገር ደረጃ የሚካሄደውን አመታዊውን የአድዋ ድል ቀን አስመልክቶ ለቀናት በሚካሄዱ ዝግጅቶች ጥናታዊ ስራዎች፣ የግንዛቤ ማስጨበጫዎችና ውይይቶች ሲካሄዱ ኖረዋል:: አያሌ የአደባባይ ስነስርአቶችም ተካሂደዋል::
በአዲስ አበባ በየአመቱ የአድዋ ድል የሚከበረው በዘመኑ የሀገሪቱ መሪና የጦርነቱ አዝማች ለነበሩት ለዳግማዊ አጼ ምንሊክ አራዳ ጊዮርጊስ አጠገብ በቆመው ሀውልት ነው:: አደባባዩ አድዋ አደባባይ በሚልም ይታወቃል::
አዎን በአዲስ አበባ በአድዋ ስም የሚጠራ ድልድይ አለ:: ከአዋሬ ወደ መገናኛ በሚወስደው መንገድ ቀበና ወንዝ ላይ የሚገኝ ድልድይ አድዋ ድልድይ ይባላል:: ድልድዩ እግረኞችን ብቻ የሚያሻግር ነው:: ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ለመውረር የመጣውን ጣልያንን ለመፋለም ወደ አድዋ ሲሄዱ በእዚህ ድልድይ ላይ ተሻግረው አንደሄዱ ይነገራል:: በመንግስት ይሁን በግል ይዞታ የሚታወቅ ዱሮ አዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት አጠገብ ሲኒማ አድዋ ነበር ይባላል:: አካባቢው ሲጸዳ እሱም ተነሳ፤ በዚያው ቀረ ይባላል::
አድዋን በድሉ ልክ በታላቅ ታሪክነቱ ልክ ፣ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ለአለምም ባበረከተው አስተዋጽኦ ልክ በቋሚነት በመዘከሩ በኩል ግን ብዙ ይቀራል:: ኢትዮጵያውያን አድዋ የብዙ ውጥን ፣ የብዙ ፈተና የአሸናፊነት ምስጢራቸው መስፈሪያ ማንጸሪያ ነው:: ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን በአድዋ ልክ ይመለከቱታል:: ወራሪ ጠላት ኢትዮጵያን ባሰበ ቁጥር አድዋን ይጠቅሳሉ:: መጠራሪያቸው፣ ጠላትን ልኩን የማሳያቸው መሳሪያቸው ነው:: እናም በእዚህ ሁሉ ልክ በሚገባ ሊዘከር ይገባል::
በኢህአዴግ ዘመን አድዋን ከቀደመው በተለየ መልኩ ለመዘከር ሀሳቡ ነበር፤ በአሉን አድዋ ላይ በደማቅ ስነስርአት ማክበር የተጀመረውም በእዚሁ ስርአት ነው:: አድዋን ከፍ በማድረግ በኩል ይህንንም አንደ አንድ እርምጃ መውሰድ ይቻላል::
በዚሁ ስርአት ወቅት አድዋን እንደ ከፍታው ለመጥራት የሚያስችል የአራዊት ፓርክ በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ለመገንባት ታስቦም ነበር፤ የመሰረት ድንጋይ ሳይቀመጥስ ይቀራል:: ከዚያ በሁዋላ ዞር ብሎ የተመለከተው ግን የለም::
በትግራይም በአድዋ የፓን አፍሪካ ዩኒቨርስቲን በመገንባት ድሉን የሚዘክር ስራ ለመስራት ተጀምሮ ነበር:: የፌዴራል መንግስቱ ለእዚህ ታላቅ ተግባር እርሾ የሚሆን ገንዘብም መድቦ እንደነበር አስታውሳለሁ:: አፍሪካውያንም አሻራቸውን ሊያኖሩበት ቁርጠኝነቱ ነበራቸው::በሀገራችን የዛሬ አራት አመት የመጣውን ሀገራዊ ለውጥ ተከትሎ ለውጡ ያስኮረፈው አልፎም ተርፎ ያሸፈተው እና ወራሪ ያደረገው ከሀዲው የትህነግ ቡድን በሀገሪቱ ላይ በፈጸመው ታሪክ ይቅር የማይለው ጥፋት የትግራይን ህዝብ ፈተና ውስጥ መክተቱን ተከትሎ ተጀምሮ በነበረው አንቅስቃሴ ላይም ቀዝቃዛ ውሃ ቸልሶበታል::
አዲስ አበባ ግን አድዋን በአመት አንዴ ብቻ ከመዘከር በሚያወጣ ታላቅ ስራ ላይ ከተጠመደች አመታት ተቆጥረዋል:: አድዋን ከአመታት በፊት በገባችው ቃል መሰረት የከተማ አስተዳደሩ የአድዋ ሙዚያምን የአድዋን ታሪክ ሊመጥን በሚችል መልኩ መሀል አጠገቡ /አዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት እና ዳግማዊ ምኒሊክ አደባባይ አጠገብ/ ግዙፍ ግንባታ እያካሄደ ይገኛል::
የአዲስ ከተማ አስተዳደር እያከናወነ ያለው ይህ የአድዋ ሙዚየም ግንባታ ፕሮጀክት ግንባታን በአፋጣኝ ተጠንስሶ፣ በአፋጣኝ ወደ ግንባታ የተገባበትና ግንባታው ያለእረፍት እየተካሄደ ያለበት ሁኔታ ይስተዋላል:: ይህ ከአራት ነጥብ ስድስት ቢሊየን ብር በላይ በጀት ተይዞለት ወደ ግንባታው የተገባ ፕሮጀክት፣ ለበርካታ አገልግሎት ሊውሉ የሚችሉ ግንባታዎችን ያካተተም ነው::
ሙዚየሙ የአድዋ ህያው ታሪክ የሚታወስበት ዘመን ተሻጋሪ ቅርስ እንደመሆኑ፤ በጦርነቱ ሂደት የነበሩ ውጣ ውረዶች፣ የታሪክ፣ የድል ቅርሶችና ሌሎች በርካታ በውስጡ የሚካተቱ ቅርሶች ተቀርጸው እንዲቀመጡበት በሚያስችል መልኩ በመታነጽ ላይ ነው::
የአድዋ ሙዚየም ሙዚየም ብቻም አይደለም:: እንደ ሲኒማ ቤት፣ ልዩ ልዩ አዳራሾች፣ ሬስቶራንቶች፣ ቤተመጻህፍት ያሉ ሌሎች አገልግሎት መስጫዎችን ያካተተ ነው:: በርካታ ተሸከርካሪዎችን ማቆም የሚያስችል ፓርኪንግ አንደሚኖሩት የሚጠበቀው ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ አድዋን በሚገባ የሚዘከር አንደሚሆን ይጠበቃል:: የከተማዋን በተለይም የአራዳን/ ፒያሳን አካባቢ/ በወሳኝ መልኩ አንደሚቀይረውም ይጠበቃል::
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለእዚህ ተግባሩ በእጅጉ ሊመሰገን ይገባል:: አድዋን በስሙ ልክ ለማድረግ የጀመረውን ጥረት የአድዋ የአራዊት ፓርክ/ዙ/ንም እውን በማድረግ ሊደግመው ይገባል እላለሁ:: መልካም የአድዋ ድል በአል!
ኃይሉ ሣህለድንግል
አዲስ ዘመን የካቲት 21 ቀን 2014 ዓ.ም