እነሆ አሮጌ ዓመትን ጨርሰን አዲስ ዓመት ተቀበልን። አዲስ ዓመት ሲገባ (ስንቀበል) ደግሞ የለመድነውን የዓመተ ምህረት አጻጻፍ ትተን ሌላ አዲስ ቁጥር እንጽፋለን። በእርግጥ ልዩነቱ ያን ያህልም ነው። ከአራት ዲጂት ውስጥ አንዲት ዲጂት ናት የምትቀየረው። ይሄ አጻጻፍ ለአሥር ዓመታት ያህል ይቀጥላል። ለምሳሌ ከ1990 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2000 ዓ.ም ድረስ ሁለተኛ ላይ ያለችዋ (የአሥር ቤት ማለት ነው) 9 ቁጥር ለ10 ዓመታት ያህል ትቀጥላለች፤ 1991፣ 1992፣ 1993 … እያልን ማለት ነው። ከ2001 እስከ 2009 ድረስ ደግሞ 0 ቀጥላለች። እነሆ ከ2010 ጀምሮ ደግሞ ሁለተኛ ላይ ያለችዋ 1 ቁጥር እስከ 2020 ዓ.ም ድረስ ትቀጥላለች። ሦስተኛና አራተኛ ላይ ያሉት (ከቀኝ ወደ ግራ ነው የምንሄደው) ለመቀየር መቶ እና ሺህ ዓመታት ይቆያሉ። የመቶ ቤት የሆነችዋን ‹‹0›› ለመቀየር 83 ዓመታት ይቀሩናል። የአንድ ሺህ ቤት የሆነችውን ‹‹2›› ለመቀየር 983 ዓመታት ይቀራሉ።
አሁን ያለነው ትውልድ የመቶ ቤት የሆነችው ‹‹0›› አብራን ትቆያለች፤ ዕድሜና ጤና ይስጠንና 2100 ዓ.ም ለማየት ያብቃን እያልን ከቁጥር ጨዋታ እንውጣና ወደ ዋናው ትዝብት እንግባ።
እንግዲህ አዲስ ዓመተ ምህረት ሲገባ የመጨረሻዋን ዲጂት መቀየር የተለመደ ነው። እዚህ ላይ ታዲያ አንድ በተደጋጋሚ የሚስተዋል ስህተት አለ። ዓመቱን ሙሉ ስንጽፈው በቆየነው ቁጥር ከመላመድ የተነሳ መርሳት ያጋጥማል። የለመደ እጅ የተቀየረችዋን ቁጥር በመርሳት ያለፈውን ይጽፋል። አሁን አሁን የስብሰባ ማስታወሻዎች ሁሉ ሳይቀር የሚጻፉት በኮምፒተር ስለሆነ እንጂ የእጅ ጽሑፍ በነበረ ጊዜ ደጋግሞ ያጋጥማል። ስህተቱ በኮምፒተር አያጋጥምም ማለት ሳይሆን ቶሎ ለማጥፋት ቀላል ስለሆነ ችግሩን ያቀለዋል። የእጅ ጽሑፍ ሲሆን ግን ስርዝ ድልዝ ይበዛዋል። ለምሳሌ፤ ዓመቱን ሙሉ 2016 እያለ ሲጽፍ የቆየ እጅ 2017 በማለት ፋንታ 2016 ብሎ ሊጽፍ ይችላል።
እነሆ አዲስ ዓመት ተቀበልን። ‹‹2017 ዓ.ም›› ብለን አዲስ ቁጥር ጻፍን። እዚህ ላይ ታዲያ አንድ የምንታዘበው ነገር አለ። ‹‹እኛ ኢትዮጵያውያን የራሳችን የዘመን አቆጣጠር ያለን…›› እያልን እንፎክራለን። የዘመን አቆጣጠራችንን የኮራንበትን ያህል ግን አንጠቀምበትም፤ የውጭው ናፋቂ ነን። በቀላሉ የጓደኞቻችሁን (የራሳችሁንም ቢሆን) ስልክ ተመልከቱ! ሰዓቱ የሚሞላው በፈረንጅኛው አቆጣጠር ነው። ቀኑ እና ዓመተ ምህረቱ የሚሞላው በፈረንጅኛው አቆጣጠር ነው። ስልኩ የኢትዮጵያን አቆጣጠር አይሰራም ይሆን?
በተለይም መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶችና የግል ተቋማት ውስጥ በሚሰሩ ጓደኞቼ ደግሞ ከዚህም በላይ የታዘብኩት ነገር አለ። የኢትዮጵያ የቀን አቆጣጠር ጭራሹንም ይጠፋባቸዋል። ‹‹ዛሬ ቀን ስንት ነው?›› ተብለው ቢጠየቁ ‹‹መስከረም 4›› ከማለት ይልቅ ‹‹ሴፕቴምበር 14›› የሚለው ቶሎ ትዝ ይላቸዋል። ምክንያቱም የሥራ እንቅስቃሴዎቻቸው ሁሉ ከፈረንጅኛው አቆጣጠር ጋር ነው የሚቀራረቡት። ደብዳቤዎችና ሌሎች የሥራ ሰነዶች የሚጻፉት በእንግሊዘኛ ቋንቋ ነው። የወር ደመወዛቸውን የሚቀበሉት በውጭው አቆጣጠር ነው። በእነዚህ ተፅዕኖዎች ምክንያት ከኢትዮጵያው አቆጣጠር ይልቅ ለውጭው ይቀርባሉ።
የመንግስት ተቋማት ሆነውም የውጭው አቆጣጠር ተፅዕኖ ያለባቸው አሉ። እንዲያውም ከመገናኛ ብዙኃን በስተቀር አብዛኞቹ በውጭው አቆጣጠር የሚጠቀሙ ናቸው። ለምሳሌ ባንኮች ደረሰኝ ላይ ቀን የሚጽፉት በውጭው አቆጣጠር ነው። ትምህርት ቤቶች ውስጥ ቀንና ዓመተ ምህረት የሚጻፈው በውጭው አቆጣጠር ነው። በተለይም ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚለጠፉ ማስታወቂያዎች ሁሉ በውጭው አቆጣጠር ነው። በእርግጥ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የማስተማሪያ ቋንቋውም እንግሊዘኛ ስለሆነ ከተፅዕኖው ነፃ መሆን አይቻልም፤ ቢሆንም ግን ቢያንስ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በሚወጡና በአገር ውስጥ ቋንቋ በሚጻፉ ማስታወቂያዎች የኢትዮጵያን መጠቀም ይቻል ነበር።
ይሄ የዘመን አቆጣጠርን እያደበላለቁ መጠቀም ለመረጃ ስህተትም ይዳርጋል። አንድ በተደጋጋሚ የሚስተዋል ስህተት ላስታውሳችሁ። እንደሚታወቀው በእንግሊዘኛ ጽሑፍ ውስጥ የሚገኝ ዓመተ ምህረት በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ነው። በእንግሊዘኛ ስንጽፍም ይህንኑ ዓመተ ምህረት ነው መጠቀም ያለብን። ምናልባት የኢትዮጵያን ዓመተ ምህረት መጥቀሱ አስፈላጊ ከሆነ ደግሞ E.C የሚለው የተለመደ አገላለጽ አለ። ልብ ብላችሁ ከሆነ ግን ይሄን ሳይጠቀሙ በኢትዮጵያ ዓመተ ምህረት በእንግሊዘኛ የሚጽፉ አሉ። ይሄ ነገር ለስህተት ይዳርጋል። ምክንያቱም ጽሑፉ የእንግሊዘኛ ከሆነ ሰዎች የሚረዱት በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ነው፤ አማርኛ ከሆነ ደግሞ በኢትዮጵያ አቆጣጠር ነው።
ለምሳሌ ዓመተ ምህረቱ ያለፈ ከሆነ የሰባት ወይም የስምንት ዓመት ልዩነት ተሳስተናል ማለት ነው። ምናልባት ዓመተ ምህረቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ገና ወደፊት ከሆነ ግን ከጽሑፉ ዓውድ ልንረዳው እንችላለን። ለምሳሌ ‹‹በ2018 በተደረገው…›› የሚል የሆነ ሁነት ብናነብ የኢትዮጵያ 2018 ገና ወደፊት ስለሆነ በአውሮፓውያኑ ነው ማለት ነው። ‹‹በ2008 በተደረገው… ›› ቢል ግን የአውሮፓውያኑም የኢትዮጵያም 2008 ስላለፈ አንጠረጥርም፤ ምናልባትም ጉዳዩ በብዙዎች ዘንድ የሚታወቅ ሆኖ ከነ ዓመተ ምህረቱ ካላስታወስነው በስተቀር!
እንደዚሁም በአማርኛ ጽሑፍ ውስጥ አቆጣጠሩ የውጭ ከሆነ እ.ኤ.አ ብሎ መግለጽ የተለመደ ነው። አንዳንድ ጊዜ ግን ይህን ሳይጠቀሙ በውጭው አቆጣጠር ይጽፋሉ። ይሄም ከላይ የገለጽኩትን አይነት ስህተት ያስከትላል። አንድ እንደ ምልክት የሚያገለግል ነገር ደግሞ አለ። ‹‹ዓ.ም›› የሚል ካለው አቆጣጠሩ በኢትዮጵያ ነው፤ ከሌለው በአውሮፓውያኑ ነው የሚባል ነገር አለ። ይሄ አከራካሪ ስለሆነ አስተማማኝ አይሆንም! የውጭውም ‹‹ዓ.ም›› ይባላል የሚሉ አሉ። ምክንያቱም በእንግሊዘኛ B.C እና A.D የሚባል ነገር ስላለ A.D ‹‹ዓ.ም›› እንደማለት ነው ብለው የሚከራከሩም አሉ፤ ለማንኛውም ይሄኛው ዘዴ የማሳሳት ዕድሉ ሰፊ ነው።
በነገራችን ላይ ጉዳዩ የሀገር ውስጥ ሆኖ የውጭውን አቆጣጠር እንዲንጠቀም የሚያስገድዱን ነገሮች አሉ። ይሄውም በራሳችን መዘናጋት የመጣ ነው። ብዙ ነገሮቻችን በውጭዎች የተጻፉ ናቸው። ስለዚያ ጉዳይ መረጃ ፈልገን ወደ በይነ መረብ (ኢንተርኔት) ስንገባ በእንግሊዘኛ የተጻፈ ታሪክ እናገኛለን። በሀገር ውስጥ ቋንቋ ስንፈልገው ግን ዘረኝነትና የፖለቲካ ብሽሽቅ ነው የሚያመጣልን። ለምሳሌ የአንድ ታዋቂ ሰው ስም አስገብታችሁ ብትፈልጉ፤ ‹‹የእገሌ ስውር ሴራ፣ የእገሌ ገመና ሲጋለጥ…›› የሚሉ አሉቧልታዎችን ነው የሚያመጣልን። በእንግሊዘኛ ስትፈልጉ ደግሞ የሕይወት ታሪኩን፣ የሰራቸውን ሥራዎች፣ የትምህርት ደረጃውን… ይነግረናል። በእነዚህ ምክንያቶች እንግሊዘኛውን ለመጠቀም እንገደዳለን።
እንዲህ የውጭውን አቆጣጠር የመለማመዳችንን ያህል ግን ለምን ወደ አገርኛ መተርጎም አልቻልንም? ቀኑ እና ወሩ ከተጠቀሰ በውጭ አቆጣጠር የተጻፈን ጽሑፍ በኢትዮጵያ አቆጣጠር ማስቀመጥ በጣም ቀላል ነው። በእያንዳንዱ ወር ውስጥ ያለን የቀን ልዩነት ይታወቃል። ያለን የዓመተ ምህረት ልዩነት ይታወቃል። ለምሳሌ ከመስከረም እስከ ጥር ባሉት ወራት ውስጥ የሰባት ዓመት ልዩነት ነው ያለን። በእንግሊዘኛ ጽሑፍ የተገለጸው ወር ከመስከረም እስከ ጥር ባሉት ከሆነ ከዓመተ ምህረቱ ላይ ሰባት መቀነስ ነው። ከጥር በኋላ የፈረንጆች ዓመት ስለሚታደስ ከጥር እስከ ነሐሴ ባሉት ወራት ደግሞ ልዩነታችን ስምንት ስለሆነ ስምንት መቀነስ ነው። ቀኑም ልክ እንደዚሁ! ለምሳሌ ባለፈው ነሐሴ ወር የነበረው ልዩነት ስድስት ሲሆን አሁን በመስከረም ወር ደግሞ 10 ነው።
ይሄኛው አቆጣጠር ወሰብሰብ ስለሚል ሁሉም ይጠቀመው ማለት አይቻልም፤ ቢያንስ በምርምር ላይ ያሉ ሰዎች ግን እንዴት ይሄ ይጠፋቸዋል? እሺ ይሄም ይቅር! አገራዊ ሁነትን በራስ አቆጣጠር ቢጻፍ ምን ችግር አለው? ምናልባት መሰልጠን እየመሰለን ወይም ስንፍና ነው። ሰው እንዴት የራሱ አኩሪ ታሪክ እያለው የሌላው ይናፍቀዋል? ደግሞ እኮ ባለፉት ዓመታት ‹‹የኩራት ቀን›› እያልን ስናከብር ነበር።
በዚህ መዘናጋትችን የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር የመረሳት ዕጣ ፋንታ እንዳይገጥመው ያስፈራል። በራሳችን እንኩራ!
መልካም አዲስ ዓመት!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን መስከረም 4/2017 ዓ.ም