የትምህርት ቤቶችና የንግድ ቤቶች ጉዳይ

ሰሞኑን የዓመቱ የትምህርት ሥራ በመላው ኢትዮጵያ ተጀምሯል፡፡ በመላው ኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎችን ተቀብለው ማስተናገድም ጀምረዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ከሁለት ዓመት በፊት በትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚከናወኑ አዋኪ ድርጊቶችን በመከላከል በሥነ-ምግባር የታነጸ ትውልድ ለማፍራት በትኩረት እንደሚሠራ አሳውቋል፡፡ በዚህም በቂ ነው ባይባልም ተጨባጭ ለውጦችም ታይተዋል፡፡ ይህ የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ መግለጫ በመላው ኢትዮጵያ በሚገኙ ከተሞች ውስጥ ባሉ ትምህርት ቤቶች ግን አሁንም አሳሳቢ ጉዳይ ሆኖ ይገኛል፡፡

የትምህርት ቤቶች አካባቢ ፀጥታ አንገብጋቢ ከሆነው የትምህርት ጥራት ጋር በቀጥታ የሚገናኝ በመሆኑ በጣም አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ በተለይም በከተሞች አካባቢ ይህ ሁኔታ በጣም አሳሳቢ ነው፡፡ እንዴት ተደርጎ ወደ ተግባር ሊቀየር እንደሚችልም ለማወቅ ከባድ ነው፡፡ የሆነ ሆኖ ትምህርት ቤቶች ከሁከት የፀዱ መሆን አለባቸው የሚለው ጉዳይ አከራካሪ አይደለም። ዛሬም ድረስ በከተሞች በትምህርት ቤት ዙሪያ ከትምህርት ሥራው ጋር የሚቃረን ሌላ በርከት ያለ የንግድ ተቋም ይፈለፈላል ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በትምህርት ቤቱ ፊት ለፊት ባር፤ ከጀርባው ሺሻ ቤት፤ ከጎኑ ጭፈራ ቤት፤ ከፍ ብሎ ጫት ቤት፤ እልፍ ብሎ ማሳጅ ቤት፤ ከዛ ደግሞ ፔኒስዮን ወዘተ እያለ ይቀጥላል፡፡ እነዚህ የንግድ ተቋማት ተማሪዎችን ወደ ደንበኝነት ከመሳብ አንስቶ ለሌሎች ሱሶች (ሲጋራ፤ ጫት፤ ሺሻ) እስከማለማመድ ብሎም ሴት ተማሪዎችን ለወሲብ ንግድ እስከ መመልመል የሚደርሱ ናቸው፡፡ ለእነሱ ትምህርት ቤቱ የገበያ ምንጭ ነው፡፡ ለትምህርት ቤቱና በአጠቃላይ በመማር ማስተማሩ ሂደት ግን እነዚህ የንግድ ቤቶች አደጋዎች ናቸው፡፡

እስኪ በዓይነ ልቡናችን የምናውቃቸውን ትምህርት ቤቶች እናስታውስ፡፡ በርካታ ትምህርት ቤቶች በዙሪያቸው ከ10 የሚበልጥ መጠጥ ቤት 500 ሜትር በማይሞላ ርቀት ውስጥ ይዘው ልናስታውስ እንችላለን፡፡ ተማሪው እነዚህን መጠጥ ቤቶች፤ የሚከፍቱትን ሙዚቃ፤ የሚያወጡትን ጠረን እና ሌሎችም ሳቢ ሁኔታዎች ተቋቁሞ ነው ወደ ትምህርት ገበታው የሚገባው፡፡ ይህን ስበት መቋቋም የሚችሉ ይኖራሉ፡፡ ነገር ግን ብዙው ተማሪ ወጣት ነውና ከእድሜም ከብስለት ማነስም ሰንብቶም ቢሆን በዚህ ወጥመድ ውስጥ መግባቱ አይቀርም፡፡ ለዚህ ብዙ ምሳሌዎችን እና ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡

እንዲያው ብዙ ርቀት ሳንሄድ ከጥቂት ዓመት በፊት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለወጣት ጥፋተኞች ማረሚያ የሚሆን አዲስ ዘመናዊ ተቋም ማዘጋጀቱ ችግሩ ምን ያህል እንደደረሰ አመላካች ነው፡፡ ተቋሙ የተስፋፋበት ዋነኛ ምክንያት እድሜያቸው 18 ዓመት ሳይሞላ ከባድ ወንጀል ውስጥ ተሳትፈው የሚገኙ ወጣቶችን ለማረም ተብሎ ነው፡፡ አብዛኞቹ ወጣቶች ወደዚህ የገቡበት አንደኛው ምክንያት ትምህርት ቤት ብለው በወጡበት ወቅት የለመዱት ሱስ ገፊ ምክንያት ሆኖባቸው ነው፡፡ ስለዚህም በነዚህ ልጆች ወንጀል ላይ በትምህርት ቤቶቻቸው ዙሪያ ያሉ መጠጥ ቤቶች፤ ጫት ቤቶች፤ ሺሻ ቤቶች እና ሌሎች ድርሻ አላቸው ማለት ነው፡፡ ከዚህም ባለፈ ዛሬ ላይ በተለያዩ የግል፤ የመንግሥት እና የሃይማኖት ተቋማት በወጣቶች ላይ የሚሠራው ሥራ መነሻ ምክንያቱ ወጣቶች በሱስ እየተጠለፉ እንደሆነ መታየቱ ነው፡፡

በአንድ ወቅት በአንድ የመንግሥት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚሠራ የተማሪ ማማከር ባለሙያን ባናገርኩበት ወቅት የተረዳሁት እውነታውም እነዚህ በትምህርት ቤት ዙሪያ ያሉ አዋኪ ተቋማት ቁጥራቸው እየጨመረ እና በተማሪዎች ላይ ያላቸው ተፅዕኖም እያየለ እንደመጣ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ትምህርት ቤት ብለው ወጥተው ሺሻ እና ጫት ቤት የሚውሉት ተማሪዎች ቁጥር እየበረከተ እንደመጣ፤ ብዙ ተማሪዎች እዚያው ትምህርት ቤት በር ላይ የትምህርት ቤት የደንብ ልብሳቸውን እንደሚቀይሩ እና ወደነዚህ ቦታዎች እንደሚገቡ፤ ብዙ ተማሪዎች በተላመዱት ሱስ የተነሳ ክፍል ውስጥ ተረጋግተው ትምህርት መስማት እንደማይችሉ እና ብዙ ተማሪዎች በትምህርት ቤቱ መፀዳጃ ክፍል ሲጋራ እና ሌሎች አደንዛዣ እፆችን ሲጠቀሙ እንደሚያዙ፤ በሚያሳዩት ባሕሪ የተነሳ ከመምህራኖቻቸው ጋር እስከ ድብድብ የደረሰ ጠብ ውስጥ የገቡ ተማሪዎች መኖራቸውን፤ አንዳንድ ተማሪዎችም በሱስ የተነሳ ትምህርት እስከ ማቋረጥ ብሎም ወንጀል ውስጥ ተሳታፊ እስከመሆን እንደደረሱ ወዘተ ነግሮኝ ነበር።

በእርግጥም እነዚህ በትምህርት ቤቶች ዙሪያ ያሉ አዋኪ ተቋማት በተማሪዎች ላይ የሚያስከትሉት ጉዳት እንዲህ በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም፡፡ ከሚያስከትላቸው ጉዳቶች መካከል የተወሰኑትን ብንጠቅስ አንደኛው በተማሪዎች ላይ የውጤት ማሽቆልቆል፤ ከትምህርት ቤት መቅረትና ሌሎች እንቅስቃሴዎች ላይ ተሳታፊ አለመሆን እንዲሁም ትምህርት ማቋረጥ በሱስ ውስጥ ያሉ ወጣቶች የሚያጋጥሟቸው ችግሮች ናቸው፡፡ ሁለተኛው ጉዳት የአካላዊ ጤና መዛባት ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ በከተሞች አካባቢ የሚታዩት አደጋዎች ለምሳሌ ያህል የመኪና አደጋ እንዲሁም እንደ ኤች አይ ቪ ኤድስ ያሉ ተላላፊ በሽታዎች በወጣቶች ላይ የሚከሰቱት በሱስና አደንዛዥ ዕፅ ምክንያት የሚከሰቱ የጤና እክሎች ናቸው፡፡

በሌላ መልኩ በሱስ የተጠመዱ ወጣቶች ከሱስ ነፃ ከሆኑ ወጣቶች ጋር ሲነጻጸሩ ለተለያዩ የአዕምሮ በሽታዎች የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ለምሳሌ ድብት፤ አስቸጋሪ ጠባይ፤ የስብዕና መቃወስ፤ እራስን ለማጥፋት ማሰብና መሞከር እንዲሁም ማጥፋት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ጉዳቱን በማኅበራዊ መልኩ ስናየው ደግሞ ወጣቶቹ የሚያገኙትን ገንዘብ ሁሉ ሱሳቸውን ለማስታገስ የሚጠቀሙበት ሲሆን ያን ማድረግ ካልቻሉ ደግሞ ወደ ወንጀል ሊሰማሩ ይችላሉ፡፡ እንዲህ እንዲህ እያልን በትምህርት ቤት ዙሪያ ያሉ መጠጥ ቤቶች ልጆችን ለምን አይነት ችግር እንደሚጋብዙ መዘርዘር እንችላለን፡፡

ስለዚህም ዘላቂው መፍትሔ በትምህርት ቤት ዙሪያ ያሉ አዋኪ ተቋማትን ማፅዳት መሆን አለበት፡፡ ከዚህም ባለፈ ግን በዚህ ዙሪያ ለተማሪም ለወላጅም ለሌላውም ግንዛቤ መፍጠር እና በጋራ እንዲሠሩ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ አዋኪ ነገሮችን የማፅዳት ሥራው የሌሎችን ሰርቶ የመኖር መብት የማይጋፋ እንዳይሆን፤ እንቅስቃሴውም ትምህርት ቤትን ብቻ ሳይሆን መኖሪያ አካባቢዎችን ያማከለ እንዲሆን ማድረግ ስለሚስፈልግ ሥራው በሕግ የተቃኘ፤ በስትራቴጂ የሚመራ እና ዘለቄታ ያለው ሆኖ መሥራትም አለበት፡፡

ኤልያስ ከቢሾፍቱ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You