የመንግሥት ትምህርት ቤት ለምን ተናቀ?

በቅርቡ ሕይወታቸው ያለፈው ፕሮፌሰር እንድሪያስ እሸቴ ከ15 ዓመታት በፊት በሸገር ኤፍ ኤም 102.1 የቅዳሜ ጨዋታ ፕሮግራም ላይ ከጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ ጋር ረዘም ያለ ቆይታ አድርገው ነበር። ፕሮፌሰሩ በዚያ ጨዋታቸው ካነሷቸው ሃሳቦች አንዱ፤ የግል ትምህርት ቤት እና የመንግሥት ትምህርት ቤት ጉዳይ ነበር። በእርሳቸው ዘመንም የግል ትምህርት ቤት ነበር ማለት ነው። እርሳቸው የሚማሩት ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ነበር። እናም የግል ትምህርት ቤት ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎች የመንግሥት ትምህርት ቤት ውስጥ በሚማሩት ይቀኑ ነበር። በሚሰጡ ሀገር አቀፍ ፈተናዎች ብዙ ተማሪ የሚያልፈው ከመንግሥት ትምህርት ቤት ነበር። ከግል ምንም ተማሪ የማያልፍባቸው ነበሩ።

ቀደም ባለው ዘመን ተማሪ የነበሩ ሰዎች የጻፏቸውን እንዳነበብነው፤ ሲናገሩም እንደሰማነው፤ እንደ ዳግማዊ ምኒልክ እና ጄኔራል ዊንጌት ያሉ ትምህርት ቤቶች ጎበዝ ተማሪ የሚማርባቸው የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ነበሩ። ተግባረ ዕድን የመሳሰሉት የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ነበሩ። ብዙ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች ከእነዚህ ትምህርት ቤቶች ወጥተዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን የመንግሥት ትምህርት ቤት የድሃ ሆኗል። ትምህርት በአግባቡ የማይሰጥበትና ዝርክርክ አሰራር ያለበት ነው የሚለው ትርክት በብዙዎች አዕምሮ ውስጥ ተገንብቷል። በዚህ ትርክት ምክንያት ወላጆች ልጆቻቸውን በመንግሥት ትምህርት ቤት ማስተማር ልጆችን እንደ መበደል አድርገው እያሰቡት ነው። በሌላ በኩል የዕውቀትና የብቃት ሳይሆን የኑሮ ደረጃ መፎካከሪያ ሆኗል።

ወዲህ ደግሞ፤ ሀገራዊ ኃላፊነት የተሰጣቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት ልጆቻቸውን በግል ትምህርት ቤት ሲያስተምሩ ያያሉ። ይህን የሚያዩ ሰዎች ‹‹ራሱ መንግሥት የናቀውን ታዲያ….›› የሚል ስሜት ይፈጠርባቸዋል። ባለሥልጣንነት ሀገራዊና ሕዝባዊ ኃላፊነት መሆኑ ቀርቶ የደረጃ ማሳያ ሆነ ማለት ነው። አንድ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን በመንግሥት ትምህርት ቤት ውስጥ ያለው ችግር (ችግር አለ ብሎ ካመነ) እንዲስተካከል ከመሥራት ይልቅ ልጁን የግል ትምህርት ቤት ያስተምራል ማለት ነው። ይህ ሰው ግን በየመድረኩና በየሚዲያው ስለመንግሥት ቆራጥነትና ብቃት ይናገራል። ምናልባትም የትምህርት ተቋም ላይ የሚሰራ ከሆነ ደግሞ ይባስ ብሎ ስለትምህርት ጥራት ያወራል፤ የራሱን ልጆች ግን የግል ትምህርት ቤት ያስተምራል።

በየመድረኩ እና በየቴሌቭዥኑ አገር አፍቃሪ መስለው የሚናገሩ ባለሥልጣናት እና ‹‹ምሁራን›› የመንግሥትን ትምህርት ቤት ንቀው የግል የሚያስተምሩ ናቸው። በተለይም የመንግሥት ባለሥልጣናት ግን የበለጠ ይገርማል። ራሳቸው የሚመሩትን ሥርዓት ማስተካከል ሲገባቸው ንቀውት አማራጭ ያጡ ሰዎች መዋያ እንዲሆን አደረጉት ማለት ነው።

እያልኩ ያለሁት የግድ አሁን ባለው ሁኔታ የመንግሥት ትምህርት ቤት ያስገቡ አይደለም፤ ዳሩ ግን የመንግሥት ትምህርት ቤት የተናቀበትን ምክንያት ልብ ይበሉ ነው! አለ የተባለውን ችግር ያስተካክሉ፤ በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ላይ የሚያስተውሉትን ችግር እንዲቀረፍ ይስሩ። የአገር ፍቅር የሚገለጸው አገሩን የሚጠቅም ዜጋ በማፍራት ነው።

ለመሆኑ በግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ ያለው ብቃት እና ጥራት ምን ይሆን?

በተደጋጋሚ ሲባል እንደሰማነው የግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ ያለው የትምህርት ጥራት እና ብቃት የእንግሊዘኛ ቋንቋ አቀላጥፎ መናገር ነው። የዚህም ዋና ጥቅሙ የፈረንጅ አገልጋይ ለመሆን ነው። የአንድ ባለሥልጣን ልጅ የፈረንጅ አገልጋይ መሆኑ ለራሱና ለቤተሰቦቹ ይጠቅም ይሆናል እንጂ እንደ አገር የሚጠቅመው ነገር አይኖረውም። ኢትዮጵያ የተጎዳችው የተማሩ ልጆቿ የፈረንጅ አገልጋይ በመሆናቸው ነው። የወላጆች ፍላጎት ደግሞ ራሳቸውን እና ራሱን እንዲጠቅም እንጂ አገሩን እንዲጠቅም አይደለም። ‹‹ደግሞ ለዚች አገር!›› እያሉ ነው የሚያስተምሩት፤ እነዚህ ሰዎች ግን በየመድረኩና በየሚዲያው ‹‹አገሬን እወዳለሁ!›› እያሉ ያታልላሉ።

የግል ትምህርት ቤቶች ከስያሜያቸው ጀምሮ ኢትዮጵያዊ ይዘት የላቸውም። የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ግን ቢያንስ ስማቸው እንኳን አንድ የትምህርት አይነት ነው። በኢትዮጵያ ጀግኖችና ባለውለታዎች የተሰየሙ ናቸው። በኢትዮጵያ ታሪካዊ ክስተቶች እና የድል ታሪኮች የተሰየሙ ናቸው። ኢትዮጵያዊ ሁሉ የሚያውቀው ትርጉም ያላቸው ናቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ውብ ቦታዎችን የሚያስተዋውቁ ናቸው።

የግል ትምህርት ቤቶች ግን ስማቸው ራሱ ኢትዮጵያዊ ትርጉም ያለው አይደለም፤ ምኞታቸው ሁሉ የውጭ ነው። በዚህ ትምህርት ቤት ውስጥ የሚማሩ ልጆች ምን አይነት ስነ ልቦና ተላብሰው እንደሚያድጉ ማሰብ ቀላል ነው። እነዚህ ልጆች የአገራቸውን ታሪክ፣ ባህልና ወግ የሚያውቁበት ዕድል አይኖራቸውም፤ ስለዚህ አገራቸውን አያውቋትም ማለት ነው! አገሩን የማያውቅ ዜጋ ታዲያ ለአገሩ ምን ሊጠቅማት ይችላል? በእርግጥ የሚማሩትም አገራቸውን ለመጥቀም ሳይሆን የሰለጠነ አገር ሄደው የፈረንጅ አገልጋይ በመሆን ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን መጥቀም ነው።

ቤተሰባቸውን መጥቀም በተዘዋዋሪ አገርን መጥቀም ነው ሊባል ይችላል። ራስን እና ቤተሰብን ብቻ መጥቀም ግን እንደ አገራዊ ጥቅም ሊታይ አይችልም። ለቤተሰቦቻቸው ገንዘብና ልብስ መላክ፣ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች መላክ፣ ግፋ ቢል የቤተሰብ አባላትን ወዳሉበት አገር መውሰድ…. አገራዊ ጥቅም ሊሆን አይችልም። ይህ ቤተሰባዊ ጥቅም ብቻ ነው። ‹‹እኔ ስለአገር ምን አገባኝ!›› ቢሉ ግን እውነቱን ስለተናገሩ ያስማማል!

የአገር ጥቅም ማለት የአገራቸውን ታሪክ፣ ወግና ባህል አውቀው በአገራቸው ዓውድ ችግር ፈቺ ፍልስፍናዎችን ሲያመጡ ነው። ኢትዮጵያ የምትጠቀመው፣ ተፈጥሯዊ ፀጋዎቿን ተመራምረው የሚያዘምኑላት ቢፈጠሩ ነበር። እንደ አገር ጥቅም የሚኖረው ይህን ምቹ አየር፣ እምቅ የተፈጥሮ ሀብት… ወደ ዘመናዊ ሥልጣኔ እና ምርት የሚቀይሩ ተመራማሪዎች ቢፈጠሩ ነበር። እየሆነ ያለው ነገር ግን በተቃራኒው ይህ እንዳይፈጠር የሚያደርግ ነው! ‹‹እንዴት?›› የሚለውን እንመልከት!

የመንግሥት ትምህርት ቤቶች በቂ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገባቸው አይደለም። በኑሮ ውድነት ናላው የዞረ መምህር የግል ኑሮውን ማሸነፊያ ወከባ ላይ ነው። ተረጋግቶ ስለትምህርትና ስለትውልድ የሚያስብበት ስነ ልቦና የለውም። የሚያስተምረው ከልቡ ሳይሆን ያችኑ የሚያገኛትን ደመወዝ ለማግኘት ነው፤ ሥራው የግብር ይውጣው ነው። በዚህ በኩል መንግሥት በቂ ክትትልና ቁጥጥር እያደረገ አይደለም፤ ትምህርት የሚገባውን ያህል ትኩረት አላገኘም።

የግል ትምህርት ቤቶች ደግሞ ከኢትዮጵያ ታሪክና ተፈጥሮ የራቁ ናቸው። ከውጭውም ከአገር ውስጡም ያልሆኑ የምናብ ዓለም መሃል ሰፋሪዎች ናቸው። ምኞታቸውም የውጭ ቋንቋ ችሎ የሰለጠነ አገር መሄድ እንጂ የኢትዮጵያን ተፈጥሮ መመራመር አይደለም፤ ይህን ለማድረግ የሚያስችል አሰራር ብቻ ሳይሆን ምኞትም ያላቸው አይመስሉም።

ዞሮ ዞሮ የዚሁ ሁሉ ችግር መውደቂያው ራሱ መንግሥት ላይ ነው። በየጊዜው ‹‹ይህን ያህል የግል ትምህርት ቤቶች መስፈርቱን ስላላሟሉ ተዘጉ…›› ሲባል እንሰማለን። ምን እንዳላሟሉ ግን አይታወቅም። ለመሆኑ የትኞቹ የግል ትምህርት ቤቶች ናቸው ኢትዮጵያዊ ይዘት ያለው ትምህርት የሚሰጡት? ከመዘጋታቸው በፊት ፍትሐዊ ክትትል እና ቁጥጥር ተደርጓል ወይ? የሚሉት ጥያቄዎች ልብ መባል አለባቸው።

በዋናነት ግን የመንግሥት ትምህርት ቤቶች በልጠው መገኘት አለባቸው። የግል ትምህርት ቤቶች የመንግሥትን ጫና ለመቀነስ እና ተደራሽትን ለማስፋት እንጂ ሙሉ በሙሉ ብቸኛ አማራጭ እንዲሆኑ መደረግ የለበትም! የመንግሥት ትምህርት ቤት የድሃ መጣያ መሆን የለበትም። አማራጭ ያጡ ሰዎች የሚማሩበት ሳይሆን የሚመረጥ መሆን አለበት። የመንግሥት ትምህርት ቤት የሚማሩ ልጆች የበለጠ ኩራት የሚሰማቸው እንጂ የሚሸማቀቁበት መሆን የለበትም። ትልቅ አገራዊ ኃላፊነት ያለበት መንግሥት ሆኖ ሳለ፤ በነጋዴ መበለጥ የለበትም።

ይህን ለማድረግ ደግሞ በቂ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ፣ የመምህራን ኑሮ እና የሙያ ብቃት ላይ ከፍተኛ ትኩረት መስጠት፣ ብቁ ተማሪዎችን ማበረታቻ በመስጠት ለሌሎች አርዓያ ማድረግ… ያስፈልጋል። በአጠቃላይ፤ የመንግሥት ትምህርት ቤት የበለጠ የሚፈለግና ልጆች የሚመኙት እንጂ የተናቀ መሆን የለበትም! መንግሥት ለዚህ ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን መስከረም 8/2017 ዓ.ም

Recommended For You