እኛና መስከረም …

አዲስ ዓመት ለአብዛኞቻችን ድባቡ ደስ ያሰኛል። ይህ ጊዜ ክረምት አልፎ ፀሐይ፣ ጭቃው ደርቆ ብራ የሚሆንበት ነውና ስሙ ብቻውን በተስፋ የሚያሳድር ነው፡፡ ለእኛ ለኢትዮጵያኖች ደግሞ አውደ ዓመት ይሉት ወግ ልማድ ትርጉሙ ሰፊ ሆኖ ይገለጣል፡፡ ወቅቱ የወዳጅ ቤተሰብ መተያያ፣ የጎረቤት አብሮነት መገለጫ እንደሆነ ዘመናትን ተሻግሯልና፡፡

አዲስ ዓመት መስከረም ላይ በድምቀት ይከሰታል። ዕንቁጣጣሽ በአደይ አበባ ተውቦ በወሩ ደማቅ ፀሐይ ፈንጥቆ ብቅ ሲል ደስታን ያቀብላል፡፡ ከዘመን ዘመን መሻገሪያ አዲስ ተስፋን መቀበያ ነውና በምስጋና ፈጣሪን ማሰብ የተለመደ ነው፡፡

አዲስ ዓመትን በርካቶች በብሩህ ተስፋ ይቀበሉታል፡፡ አውደ ዓመት ሆኖ ሲመጣ ደግሞ በረከቱ ለአንድ ወገን ብቻ አይደለም፡፡ ሙስሊም ክርስቲያኑ በእኩል ይጋራዋል፡፡ ባልተለየ አንደበት በተመሳሳይ ዜማ የ‹‹እንኳን አደረሰን፣ አደረሳችሁ›› ምኞቱን የሚያደርሰው አብሮነቱን እያሰበ ነው፡፡

ለኢትዮጵያውን የመስከረም ወር ሲታሰብ የአዲሱ ዓመት በዓልም አይቀሬ ሆኖ ነው፡፡ በወሩ አጋማሽ ላይ በድምቀት የሚከበረው የመስቀል በዓልም ሌላው የወቅቱ መገለጫ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ልክ እንደዚህ ግዙፍ አውደ ዓመት ሁሉ በዚህ ወር ከውዴታ የሚገቡ ግዴታዎች ጭምር አንድ ሁለት ብለው ይዘረዘራሉ፡፡

እንደሚታወቀው መስከረም ከደስታና እልልታም በላይ ይሻገራል፡፡ አውደ ዓመት ሁሌም በዓል ብቻ ሆኖ አይመጣም፡፡ ወቅቱን ተከትለው ብቅ የሚሉ ችግሮችም በየተራ ይሰለፋሉ፡፡ በዚህ ወቅት አቅምን የሚያንገዳግድ ኪስና ጓዳን የሚያሟጥጥ ወጪ መከሰቱ ግድ ነው፡፡ ለአዲሱ ዓመት የበዓል ዝግጅት ቤት ጓዳን ለመሙላት ገበያው የዋዛ አይሆንም፡፡

ዓመቱን በደስታ ጀምሮ፣ ወሩን በሙላት ለመሻገር የሚሹ ሁሉ ከአቅማቸው በላይ ይተጉበታል፡፡ የመስከረምን ወር፡፡ እውነቱን ለመነጋገር የዚህ ወቅት የማር ወለላ ጊዜ የመጀመሪያዎቹ ቀናት ብቻ ሊሆኑ ይችላል፡፡ ውሎ አድሮ ጣፋጩ ጊዜ እያለቀ ወደሌላው መራር እውነታ ማሻገሩ አይቀሬ ነው፡፡

ችግሩ ግን እንዲህ መሆኑ ላይ ብቻ አይደለም፡፡ ሁሌም በዓሉን ሰበብ አድርገው ዋጋን የሚያንሩ አንዳንድ ነጋዴዎች ጊዜውን እንደልዩ ሲሳይ ይጠቀሙበታል። በግልጽ እንደሚታየው በየጊዜው በሸማቹ ላይ የሚያደርሱት ጫና የገደብ ልጓም የለውም፡፡

መስከረም የአዲስ ዓመት መግቢያ ነውና ብዙ እውነታዎች ይከወኑበታል፡፡ የተማሪዎች ትምህርት መጀመሪያ ዓመት እንደመሆኑ ከልብስ ጫማ ጀምሮ እስከ ትምህርት መሳሪያዎች፣ ማሟላት ግድ ይላል። የደንብ ልብስና የመመዝገቢያ ግዴታዎችም አይቀሬ የሚባሉ ናቸው፡፡ እነዚህ ወጪዎች በርከት ያሉ ልጆች ባሉበት ቤተሰብ ላይ ሲታሰቡ ደግሞ የኑሮ አቅምን ያንገዳግዳሉ፡፡ ሕይወትን በእጅጉ ይፈትናሉ፡፡

የመስከረም ወር ጣጣው ብዙ ነው፡፡ በዓላት ይከታተሉበታል፡፡ ይህ ማለት አይቀሬ ይሏቸው ወጪዎች በእጥፍ ይጨምራሉ ማለት ነው፡፡ ብድርና ዕዳዎች ይበዛሉ፡፡ ሃሳብ ትካዜዎች አንገት ያስደፋሉ፡፡ አንዳንዴ ግን አንዳንዶች ለዚህ ዓይነቱ መጨናነቅ ተጠያቂነትን የሚጥሉት በራሱ በጉዳዩ ባለቤት ላይ ይሆናል፡፡

መቼም ‹‹ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ፣ ምክርና ቡጢም ለሰጪው ቀላል ነው›› ይባላል፡፡ መካሪዎቹ ግን ለዚህ ዓይነቱ ተረት መስሚያ ጆሮ ያላቸው አይመስልም። እነሱ እንደሚሉት መስከረም ላይ የበዙ ጉዳዮች ያሉባቸው ቤተሰቦች አስቀድመው ሊጠነቀቁና ሊያስቡ ይገባል፡፡

በእነሱ እሳቤ ተከታትለው የሚመጡ በዓላትን ሸንቀጥ አድርጎ ማክበር ይቻላል፡፡ አንድ ሰው ከፊት ለፊቱ የተማሪዎችን ምዝገባ፣ አልባሳትና ጥቂት የማይባሉ ወጪዎችን ደራርቦ ከምሮ ከወዲሁ ደግሞ ለአውደ ዓመት ድግስ በሰፊው መንጎዳጎድ አይጠበቅበትም፡፡

ርግጥ ነው አውደ ዓመት ለኢትዮጵያውያን የተለመደና አይቀሬ ይሉት ሁነት ነው፡፡ እንዲያም ቢሆን ‹‹ሰው እንደ ቤቱ እንጂ እንደ ጎረቤቱ›› ሊኖር አይገደድም። እከሌ ቤት ለአውደ ዓመቱ በግ ገባ ተብሎ በሌላው ጓዳ ባለቀንድ ሙክት ይጎተት አይባልም፡፡ እነዚህ ታዛቢዎች እንደሚሉት በተለይ ከመስከረም መጥባት ጋር ተከትሎ የሚግተለተሉ ችግሮች ብዙ ናቸው፡፡ በተለይ ደግሞ በዓልና የትምህርት ቤት ወጪዎች የሚነጣጠሉ ሆነው አያውቁም፡፡

እንዲህ በሆነ ጊዜ ጫናው ይበዛል፣ ሃሳብ ትካዜው ይበረክታል፡፡ ታዛቢዎቹ ግን ይህ ዓይነቱ ችግር እንዳይለመድ መፍትሔ የሚሉትን አማራጭ ያኖራሉ፡፡ በግልጽ መንገድ ያኖራሉ፡፡ ይህን የሚሞክር ጎበዝ ቢኖር ደግሞ ስኬታማ እንደሚሆን ርግጠኞች ናቸው፡፡

እነሱ በተለይ ከትምህርትና ተማሪዎች ፍላጎት ጋር የሚከሰቱ ጫናዎችን ለመንቀስ ከብዙ ዕቅዶች አንዱን ብቻ የመነጠል ተገቢነትን ያምኑበታል፡፡ ለምሳሌ እስከዛሬ በሆነ ቤት ለበዓል በግ ይታረድ ከሆነ በመጪው ጊዜ በዶሮ መተካት ይቻላል፡፡

ዶሮውም ሳይቻል ቀርቶ አቅምን ከፈተነ ደግሞ አሁንም ልክን በሚመዝን ወጪ በኪሎ ሥጋ አቻችሎ ዕቅድን ወደ ትምህርት ዓላማ ማጋደል ግድ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ በተለይ መስከረም ወር ላይ የነጋዴዎች ዕቅድ በስሌት ይለወጣል፡፡ አስቀድመው በርካሽ ያስገቧቸውን ዕቃዎች በመደበቅ መስከረም መጥቢያው ሲዳረስ በዋጋ ሰቅለው ለገበያ ያቀርባሉ፡፡ ይሄኔ ምርጫው የሌላቸው ወላጆች ያለ ክርክር አጋብሰው ይገዟቸዋል፡፡

ታዛቢዎቹ በዚህ ዓይነቱ ግብይት ተወቃሽ የሚያደርጉት ሸማቹን ህብረተሰብ ነው፡፡ እንደ እነሱ እምነት ሁሌም የአትራፊ ነጋዴዎች መቀለጃ ከመሆን አስቀድሞ መዘየድ ይቻላል፡፡ እያንዳንዱ ሰው ገንዘቡን በቁጠባ ባሕልና በጊዜ አግባብ መጠቀም ቢችል ጥቅሙን በክፉ ነጋዴዎች እጅ አይነጠቅም፡፡

እስከዛሬ አብዛኞቻችን አለመድነውም እንጂ ጊዜው ሳይደርስ የመዘጋጀትን ልማድን ብንተገብር ከተደራራቢ ችግሮች መዳን ይቻለናል፡፡ በየጊዜው በአትራፊዎች ከመበዝበዝና አማራጮችን ከማጣትም እናመልጣለን። እስከዛሬ ደጋግመን እንዳስተዋልነው ግብይት ላይ የአንድ ወገን አሸናፊነት ጎልቶ ይስተዋላል፡፡

ሁሌም ቢሆን በገበያው ልቆ የሚራመደው ሸማቹ ሳይሆን አትራፊው ነጋዴ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ እውነታ በስፋት የሚታየው ደግሞ ሁላችንም በእኩል በምንጋረው የመስከረም ወር ላይ መሆኑ ዕሙን ነው። በዚህ ወር አበባ ብቻ ሳይሆን ችግሮችም በግልጽ ይፈነዳሉ፡፡ ጭቃው ደረቀ ፀሐይ ፈነጠቀች በሚባልበት ወቅት አብዛኞች ደግሞ ከማይወጡት የኑሮ ማጥ ገብተው ሲዳክሩ ይታያሉ፡፡

ታዛቢዎች እንደሚሉት ግን እኛና መስከረምን አፈራርቶ፣ በስጋት ከሚያዘልቀን ችግር አስቀድሞ መውጣት ይቻላል፡፡ ወሩን ከብዙዎች አስታርቆ ለመጓዝም የራስን መላና ዘዴ መቀየስ ያስፈልጋል፡፡ በተለምዶ እንደሚባለው መስከረም የወጪና የችግር ወር ነው እያሉ መቀጠል ብቻ ጎዶሎን አይሞላም፣ ችግርን አይፈታም፡፡

የኋላው ወደ ኋላ አልፏል፡፡ በወደፊቱ መንገድ በስኬት ለመራመድ ግን ከወዲሁ የራስ መላ ፈጥሮ ከኑሮ ጋር መስማማት በእጃችን ነው፡፡ ጊዜውን ልጠቀም፤ አስቀድሜ ልዘይድ የሚል ቢኖር ዛሬውኑ ‹‹አንድ›› ብሎ ይጀምር፡፡ እነሆ ! መስከረም ሊጠባ አዲስ ቀንም ሊመጣ ሁለት ቀን ብቻ ቀርቶታል፡፡ መልካም ብሩህ ዓመት፡፡

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ሰኞ ጳጉሜን 4 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You