የፔፕሲ አዲስ አበባ የክለቦች አትሌቲክስ ቻምፒዮና ለ39ኛ ጊዜ በመካሄድ ላይ ይገኛል:: የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከሚያዘጋጀቸው ውድድሮች መካከል አንዱ የሆነው የክለቦች ቻምፒዮና በሜዳ ተግባራትና በመም ውድድሮች አትሌቶችን ያፎካክራል::
ስመጥር እና በርካታ ክለቦችን የሚያቅፈው የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከሚያካሂዳቸው ዓመታዊ ውድድሮች መካከል አንዱ የፔፕሲ አዲስ አበባ ክለቦች አትሌቲክስ ቻምፒዮና ነው:: መነሻውን በ1975 ዓ.ም ያደረገው ውድድሩ በርካታ ክለቦችን በማሳተፍ የሚታወቅ ሲሆን፤ ከ1991 ዓም ጀምሮም በሞሃ የለስላሳ መጠጦች ኢንዱስትሪ ስፖንሰር አድራጊነት ቀጥሏል:: ዘንድሮም ለ39ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ዓመታዊ ቻምፒዮናውን በማካሄድ ላይ ይገኛል::
ውድድሩ በአትሌቲክስ ስፖርት በመም ከአጭር እስከ ረጅም ርቀት እንዲሁም የሜዳ ተግባራትንም ያጠቃልላል:: ዋነኛ ዓላማውም አዲስ አበባን ወክለው በኢትዮጵያ አትሌቲክ ቻምፒዮና የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎችን መምረጥ መሆኑ ታውቋል:: በቻምፒዮናው ላይም በፌዴሬሽኑ ስር ከሚገኙ ሰባት አንደኛ ዲቪዚዮን ክለቦች እና 13 ሁለተኛ ዲቪዚዮን ክለቦች በድምሩ ከ20 ክለቦች የተወጣጡ 1ሺ200 አትሌቶች በሁለት ምድብ ተከፍለው ፉክክር ያደርጋሉ:: ከየካቲት 15 እስከ 20/2014 ዓ.ም በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ በሚካሄደው ውድድር አዳዲስና ወጣት አትሌቶች ተሳታፊ ይሆናሉ::
ውድድሩ ክለቦች የአትሌቶቻቸውን አቅም የሚለኩበትና በአገር አቀፉ ቻምፒዮና ከተማ አስተዳደሩን ተወዳዳሪ የሚያደርጉበት ከመሆኑም ባለፈ ከፍተኛ ፉክክር እና ክብረ ወሰንም የሚመዘገብበት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል:: ትናንት በውድድሩ የመክፈቻ ዕለት በርካታ የግማሽ ፍጻሜና የፍጻሜ ውድድሮች ተከናውነዋል:: ፍጻሜ ካገኙ ውድድሮች መካከልም በአንደኛ ዲቪዚዮን 10ሺ ሜትር ውድድር መከላከያ አሸናፊ ሆኗል::
ጠንካራ ፉክክር በተደረገበት በዚህ ውድድር ሁሰዲን ማህመድ 29:14.05 በሆነ ሰዓት ሲገባ፤ የኢትዮ ኤሌክትሪክ አትሌት የሆነው እንየው ንጋቱ ጥቂት ማይክሮ ሰከንዶችን ዘግይቶ 29:14.53 በሆነ ሰዓት የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል:: የፌዴራል ማረሚያው አትሌት ማስረሻ በፌ 29:16.78 በሆነ ሰዓት ሶስተኛ ሆኗል:: በሁለተኛ ዲቪዚዮን ሴቶች የ10ሺ ሜትር ውድድር ደግሞ፤ ኩባ አለሙ ከአዲሱ ገበያና አካባቢው አንደኛ ስትሆን፤ ቆንጂት ጫላ ከዳሎል እንዲሁም ጌጤ ምንዳዬ ከአልሚ ኦላንድ ክለቦች ተከታትለው በመግባት የሜዳሊያ ተሸላሚዎች ሆነዋል::
በዛሬው መርሃ ግብር መሰረትም በርዝመት ዝላይ ወንድ፣ አሎሎ ውርወራ ሴት፣ 10ሺ ሜትር 1ኛ ዲቪዚዮን ሴት እና 2ኛ ዲቪዚዮን ወንድ፣ በ100 ሜትር ሴት 1ኛ እና 2ኛ ዲቪዚዮን ሴት እንዲሁም በ110 ሜትር ወንድ 1ኛ አና 2ኛ ዲቪዚዮን የፍጻሜ ውድድሮች ይካሄዳሉ::
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን የካቲት 16/2014