ግብፅ እና ሱዳን የዓባይን ጉዳይ ዳግም በሳይንሳዊ መልኩ ለመመልከት ይዳዳሉ። በተለይ ደግሞ ግብፆች ጉዳዩን ወጣ ባለ መልኩ የደህንነት ጉዳይ አድርገው ምስሉን ማሳደግ ይፈልጋሉ።
በግብፅ የዓባይ ጉዳይ የተሰጠው ለአገሪቱ ብሄራዊ ደህንነት ኤጀንሲ እንጂ እንደ ኢትዮጵያ ለአንድ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት አይደለም። ግብፆች ዋና ዓላማቸው ዓባይን የደህንነት እና ፖለቲካ ጉዳይ ማድረግ ነው።
ይሁንና ኢትዮጵያ በትክክለኛው መንገድ እና ሳይንሳዊ አሰራርን እየተከተለች የግብፅን አካሄድ ትክክል አለመሆኑን አሳይታለች።
ዳሩ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የግብፅ አቋም ቅቡል አለመሆኑን እያወቀ ቢሆንም ከፍትህ ጎን ለመቆም አልቻለም። በዚህ የተነሳ ግብፅ ብዙ ኪሎ ሜትሮችን ርቃ እንድትሄድ እድሉን አግኝታለች። አለፍ ሲልም የጦርነት ጉሰማ በተደጋጋሚ ስታሰማ ነበር። ፍትህን እናውቃለን የሚሉ ሁሉ ከኢትዮጵያ ዘንድ ሲደርሱ ይዘነጉትና ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው ያልፋሉ።
እንደ ምሁራን እይታ፤ ግብፆች የዓባይን ውሃ መነሻ ለምን አንይዘውም ብለው በ1875 እና በ1876 በኢትዮጵያ ላይ ዘመቻ ከፍተው አልሳካ ብሏቸው ተመልሰዋል። የዓድዋ ጦርነትንም ብንመለከት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ተመርጣ ቅድሚያ መያዝ አለባት ተብሎ ነበር፤ ግን ኢትዮጵያውያን ማሸነፍ አልተሳካም። የሱማሊያው መሪ ዚያድ ባሬ ለወረራ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ከዚህ የተነሳ ነው። የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ ያላቸው በኢትዮጵያ ላይ ጥርስ ይነክሱባታል።
የግብፅ እና የሱዳን አካሄድም ከዚህ የዘለለ አይደለም። በአንድ ወቅት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ የግብፆችን የጦርነት ጉሰማ አስመልክቶ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሲጀመር ግብፆች ዝም ብለው ይመለከታሉ ወይ? ተብለው ከሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ጥያቄ ቀርቦላቸው እንደመለሱት ‹‹ዝም ብለው አይመለከቱም ያስፈራራሉ።
ለዚህም መፍትሄው አለመፍራት ነው። አለመፍራት ማለት ደግሞ ገብቶ መተኛት ሳይሆን በቂ ዝግጅት ማድረግ ነው።›› ብለው ነበር። እንደተባለውም ግንባታው ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ ወደ ስልጣን የመጡት የግብፅ መሪዎች የማስፈራራት ሥራ እየሠሩ ቆይተዋል። በወቅቱ ግድቡ ሲጀመር ስልጣን ላይ የነበሩት ሆስኒ ሙባረክ የራሳቸውን ጥረት አድርገዋል። እርምጃ እንወስዳለን ብለውም ዝተው ነበር።
ከእርሳቸው በመቀጠል ወደ ስልጣን የመጡት ፕሬዚዳንት መሐመድ ሙርሲ በተመሳሳይ እ.ኤ.አ ሰኔ 2013 ለደጋፊዎቻቸው ባደረጉት ንግግር ‹‹የግድቡ ግንባታ መካሄዱ አግባብ አይደለም›› ብለው ዛቻ አድርገው ነበር። ምንም እንኳን ለአባይ ውሃ ምንም ድርሻ ባያበረክቱም ‹‹ከድርሻችን አንድ ጠብታ ውሃ መቀነስ የለበትም›› ብለው ማስፈራራታቸው ይታወሳል።
በአሁኑ ወቅት ግብፅ እያስተዳደሩ ያሉትና በመፈንቅለ መንግስት ወደ መንበረ ስልጣን የመጡት ፕሬዚዳንት አልሲሲ በተደጋጋሚ የዓባይ ጉዳይ የሞት ሽረት ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል። ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ለአፍታም ከዓላማዋ ዝንፍ ባትልም፤ አንዳንድ ጊዜ በፖለቲካ ሞቅታ ውስጥ ሲገቡ ደግሞ በዓባይ ጉዳይ ጦርነት ይነሳል በማለት በከባድ ቃላቶች የጦርነት ጉሰማውን ያቀጣጥሉታል።
የስትራቴጂክ ጉዳዮች ተመራማሪው ዶክተር ወሂበእግዜር ፈረደ እንደሚሉት፤ የግብጽ እና ሱዳን አካሄድ ወትሮም ከፍትህ ሳይሆን ከፖለቲካ ፍላጎት ብቻ የመነጨ በመሆኑ ሊገርም አይችልም።
የግብፅ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በሦስት ጉዳዮች ላይ ያጠነጥናል። ከአማራጮች ውስጥ የመጀመሪያው ከአፍሪካ አባል አገር በመሆኗ በዚያ መንገድ ፍላጎቷን ለማስጠበቅ መመኮር ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ የአረብ አገራት ሊግ አባል በመሆኗ በዚህ በኩል ያላትን ተሰሚነት፣ ለአሜሪካና የተወሰኑ አውሮፓ አገራት ስትራቴጂክ አጋር መሆኗን በማሰብ ዓረቡ ዓለም ከኢትዮጵያ ጋር ሆድና ጀርባ እንዲሆን መውተርተር ነው። ሦስተኛው አማራጭ ደግሞ በአገሬው ካሉ የእስልምና እምነት ተከታይ ጋር ማበርና ኢትዮጵያን ማዳከም የሚለው እንደ ስትራቴጂ የሚጠቀሙትና ኢትዮጵያ በማናቸውም መንገድ ለማደግ የምትከተለውን መንገድና ህልም ማኮላሸት ነው።
በዓባይ ላይ የሚደረጉ ጥናቶች በርከት ያሉ ናቸው። ዋነኛ የጥናትና የምርምር ሥራዎቻቸው ማጠንጠኛ ዓባይ እና ኢትዮጵያ ሲሆን ከጥቅማቸው ውጭ ሌሎችስ ምን ይጠቀሙ? የሚለው አይገዳቸውም። በተመሳሳይ መንገድ የሱዳን ምሁራንም ደጋግመው የሚሰጡት አስተያየት የኢትዮጵያን ዕድገት የሚነቅፍና ከክፋት የመነጨ ብቻ ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ቀውሶችና ግጭቶች የግብፅ እጅ እንዳለበትና ኢትዮጵያን ለማዳከም ሴራ ጠንሳሽ መሆኗን ይጠቁማሉ። ህዳሴ ግድብ እየተገባደደ በመሆኑ አማራጮችን ሁሉ ተጠቅመው ኢትዮጵያን የማፍረስ ዘመቻ ውስጥ ናቸው።
ሱዳን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ኢትዮጵያን ለማዳከም የምትፈልግና ለኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ምሽግ ሆና ስታገለግል የቆየች አገር መሆኗዋንም ተመራማሪ ይናገራሉ። በግብፅ ውስጥ የፖለቲካ አመራሮችና ስርዓቶች ቢቀያየሩም በአባይ ወንዝ ያላቸው የተሳሳተ አቋም ያመሳስላቸዋል። የግድቡን ግንባታ ሆነ የውሃ ሙሌት ለውስጣዊ ችግሮቻቸው የመፍትሄ ቁልፍና ማረጋጊያ ለማድረግ እየጣሩ መሆኑንም ምሁራን በስፋት እየተናገሩ ነው። በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1929 እንዲሁም በ1959 ግብጽና ሱዳን ውሃውን በብቸኝነት መጠቀም የሚያስችላቸው የቅኝ ግዛት ስምምነት ፈጽሞ እንዲሸራረፍ አይፈልጉም።
የአፍሪካን ችግር በአፍሪካዊ መፍትሄ መፍታት በሚለው መርህ መሰረት ሶስቱ አገሮች በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ለችግሮቻቸው መፍትሄ ለማፈላለግ ስምምነት ላይ ቢደርሱም ሱዳንና ግብጽ በየወቅቱ በሚፈጥሯቸው ችግሮች ግድቡ አሁን ኃይል ማመንጨት በጀመረበት ሰዓት እንኳን ድርድሩ መቋጫ ማግኘት አልቻለም ይላሉ ተመራማሪው የግብፅና የሱዳን ያልተገባ አካሄድ በመተቸት።
በዓባይ ጉዳይና በዓረቡ ዓለም ላይ ሰፊ ልምድና እውቀት ያላቸው ፕሮፌሰር አደም ካሚል እንዳሉት፤ ሦስቱ አገራት እ.ኤ.አ 2015 በተደረገው ሥምምነት መሰረት ግብፅ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሃብቷ የመጠቀም መብት እንዳላት ያመነችበት ወቅት ነው።
ዳሩ ግን ግብጽ ስለ ስምምነት ብታወራም እንዲተገበር አትፈልግም። በህዳሴ ግድቡ ግንባታ የሶስትዮሽ ድርድር ግብፅ የዓባይ ወንዝ ከኔ ውጭ ማንም መጠቀም የለበትም የሚል አቋም እያንፀባረቀች ነው። በሱዳን በኩልም ቋሚ የሆነ አቋም የለም። ይህ ለኢትዮጵያ ፈተና ሆኖ ቀጥሏል። በኢትዮጵያ በኩል ግን የግድቡ ሥራ በመርህ ላይ ተመስርቶ በመቀጠል ኃይል ማመንጨት ጀምሯል።
ግብፆች ዓባይን የተመለከቱ 560 ጥናቶችን ያካሄዱ ሲሆን አንዳቸውም ፍትሐዊ የውሃ ሀብት አጠቃቀምን ማዕከል ያላደረጉና ከሳይንሱ ያፈነገጡ መሆናቸውን ያብራራሉ። ኢትዮጵያ በግድቡ ግንባታና ተጠቃሚነት ዙሪያ ዓለም አቀፍ ህጎችን አክብራና የጎረቤት አገራትን ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ ሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት ስታከናውን እጅግ ከፍተኛ ጩኸት እንደነበርም ያስታውሳሉ። በግድቡ ግንባታ ድርድር እየተካሄደ ቢሆንም በግብፅ በኩል የሚሰነዘሩ የጦርነት ጉሰማዎች ቀደም ሲል የነበሩ የማስፈራሪያ አካል አንዱ መሆኑንም ገልጸዋል።
ግድቡ ግንባታ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ የአገሪቱ መሪዎች ኢትዮጵያ ላይ ዘርፈ ብዙ ጫና ለመፍጠር ሲታትሩ መቆየታቸውንና የጦርነት አማራጭ መጎሰማቸውን አስታውሰው፤ ይህ በዚህ ዘመን የማይታሰብ የማስፈራሪያ መንገድ መሆኑንም ተናግረዋል። ሌላው ቀርቶ ግብፅ እና ሱዳን በተደጋጋሚ የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ማድረጋቸው ይታወቃል።
ነገሩን ወደ ከረረ አዝማሚያ የመውሰድ ፍላጎት ነበራቸው። ዳሩ ግን የዓባይ ጉዳይ በዚያ መንገድ ከታሰበ ዘርፈ ብዙ ችግር ያመጣል። በመሆኑም ምንም እንኳን ለውስጣዊ ችግሮቻቸውም መፍትሄ ማምጣት ባይችሉም ይህን አማራጭ ከመጠቀም ይልቅ ሌላ አማራጭ ፍለጋ ላይ አተኩረዋል።
ሌሎች መረጃዎችን ዋቢ ስናደርግ፤ በምስራቅ አፍሪካ የጅቡቲ ወደቦችን ተገን በማድረግ አሜሪካ፣ ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ግብፅ ሌሎች የአረብ አገራት የወታደራዊ ቀጣና መስርተው እየተንቀሳቀሱ ነው።
ነገር ግን ከኢትዮጵያ ውጭ ከእነዚህ አካላት ውስጥ አንዳቸውም አልሽባብን ብሎም የአልቃይዳን እንቅስቃሴ መግታት አልቻሉም። በዚህም የተነሳ ኢትዮጵያ ለአሜሪካም ሆነ ለምዕራባውያን ስትራቴጂካዊ አገርና አጋር ሆና ቀጥላለች።
በመሆኑም ግብፅና ሱዳን ኢትዮጵያን ከእነዚህ አጋር አካላት ነጥለው ወዳጅ አልባ ማድረግ አልተቻላቸውም። የግብፅ አቋም መቀያየር እና የተለያዩ አማራጮችን ለመመልከት ማማተሩ ለዘመናት አብሯቸው የቆየ አሰራር በመሆኑ ብዙም የማይደንቅ ነው።
ኢትዮጵያ ታላቁን የህዳሴ ግድብ እየገነባች ብቻ ሳይሆን በዓለም አደባባይ ፍትህ እንዲነግስ እየሠራች ያለች አገር ናት። የዓባይ ውሃም ለትብብር እንጂ ለፀብ ምንጭ አይሆንም፤ ሊሆንም አይገባም። ሆኖም ግብፆች ትንንሽ ቀዳዳዎችን ባገኙ ቁጥር አጋጣሚውን ለራሳቸው ጥቅም ማዋል ይፈልጋሉ።
በተለይም ውስጣዊ ድክመቶች ተከስተዋል ብለው ባሰቡ ወቅት ጣልቃ የመግባት ፍላጎታቸው የላቀ ነው። ይሁንና ኢትዮጵያ ወደ ከፍታ ዘመን ሄዳለች። የካቲት 13 ቀን 2014 ዓ.ም ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በጉባ ታሪካዊ ክስተት ሊሆን ግድ ብሏል።
ምንም እንኳን የግብፅና ሱዳን ጩኸት ቢበረታም ግድቡ ከተጀመረ ከ11 ዓመታት በኋላ ውጤታማ የሆነውን የኤሌክትሪክ ኃይል ማንጨት ስራውን ጀምሯል። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ከፍታ መገለጫ ሆኖ ቀጥሏል።
አሁናዊ መረጃዎችም የሚያሳዩት ይህንኑ ነው። በአሁኑ ወቅት በዚህ ስፍራ እነዚህ ቁጥሮች ትርጉም አላቸው፤ ድምጽ ባይኖራቸውም ትልቅ ስሜት ይፈጥራሉ። አጠቃላይ የግድቡ የግንባታ አፈፃፀም 84 በመቶ፣ እስካሁን ለግድቡ የተደረገ ወጪ 163 ቢሊዮን ብር፣ ግድቡ ማመንጨት የጀመረው ኃይል መጠን 375 ሜጋ ዋት፣ የግድቡ አጠቃላይ የማመንጨት አቅም 5 ሺ 150 ሜጋ ዋት፣ ግድቡ በዓመት የሚያመነጨው ኃይል በሰዓት 15ሺ 760 ጌጋ ዋት፣ በግንባታው ላይ እየተሳተፉ ያሉ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች 7ሺ፣ የግድቡ ግንባታ ሲጠናቀቅ የሚይዘው የውሃ መጠን 17 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ነው።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን የካቲት 15 /2014