”የመጨረሻው መጀመሪያ‘!!
«ይህ ትውልድ» ወይም «እኛ» በእርግጥም ለበጎና አገርን ለመገንባት ለሚጠቅም ተግባር በሙሉ፤ በእርግጥም ከጊዜ እና ታሪክ ጋር ግብግብ ለመግጠም ጊዜ የማናባክን ይልቁንም ከጊዜ ጋር የታረቅን የእናቶቻችንና የአባቶቻችን ልጆች ነን!!!
አስቀድሜ ይህንን የኢትዮጵያውያንና የመላው አፍሪቃውያንን አልሞ የማድረግ ብቃት በታላቅ ከፍታ ያስቀመጠ ግዙፍ ፕሮጀክት ወደ መገባደጃው የመድረሱን መጀመሪያ በሚያበስረው የመጀመሪያው ምዕራፍ የኃይል ማመንጨት መርሐ ግብር ሥነሥርዓት ላይ ተገኝቼ፤ ይህንን በታሪክ የሚሰጥ ልዩ ዕድል የኢኤኃ የሥራ አመራር ቦርድን ወክዬ ንግግር እንዳደርግ ዕድል ለሰጠኝ ለፈጣሪ፣ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት እንዲሁም ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አሊ ምስጋናዬን ሳቀርብ ደስታዬ ወደር የለውም።
«እኛ አሁን ለመገንባት አቅሙ ላይኖረን ይችል ይሆናል ነገር ግን ዛሬ እኛ በምናስቀምጠው ራእይና አቅጣጫ፤ ነገ ከነገ ወዲያ ልጆቻችን ይገነቡታል»፤ – ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ 1957 ዓ.ም የተናገሩት፤
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድባችን ከጥንስሱ አሁን እስከ የደረሰበት የአፈፃፀም ምዕራፍ በርካቶች በየደረጃው ለአገራቸው እድገት፣ ልዕልና እና ፍትህ ለሰፈነበት የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ያላቸውን ጥልቅ ቁጭትና ቁርጠኝነት በየዘመናቸው ያንፀባረቁበት ይህንንም ቁጭት በተግባር ወደሚታይ ውጤት ለመለወጥ መስዋእትነት የከፈሉበትና በአመራር ትውልዶች ቅብብል እየተገባደደ ያለ ፕሮጀክት መሆኑን ቀደም ሲል ከጠቀስኩት የንጉሡ ንግግር እንዲሁም ፕሮጀክቱን በይፋ በ2003 ዓ.ም ባስጀመሩበት ወቅት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ካደረጉት ታሪካዊ ንግግር እና ሌሎችም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ በተለያዩ ጊዜያት የቀረቡ ልዩ ልዩ መልዕክቶችን በመመርመር መረዳት እንደሚቻለው፤ በእርግጥም «ይህ ትውልድ» ወይም «እኛ» ለበጎና አገርን ለመገንባት ለሚጠቅም ተግባር በሙሉ፤ በእርግጥም ከጊዜ እና ታሪክ ጋር ግብግብ ለመግጠም ጊዜ የማናባክን፤ ይልቁንም ከጊዜያችንም ይሁን ከአባትና እናቶቻችን ዘመን ጋር የታረቅን፤ የእናቶቻችንና የአባቶቻችን ልጆች የመሆናችን እውነታ ጥርት ብሎ ይታያል!!!
የህዳሴው ፕሮጀክት ግንባታ በኃይል ማመንጨት የኢንጂነሪንግ ሙያ ዘርፍ አገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት አመታት እያካበተች የመጣችውን ልምምድና የላቀ የሙያ ሽግግር ወደ ከፍተኛ ደረጃ ማድረስ ያስቻለ፤ የአገር ውስጥ የሙያ አቅምን ለመገንባት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያስገኘ ወሳኝና ታሪካዊ ፕሮጀክት ነው።
ፕሮጀክቱ ከኃይል ማመንጨት ኢንጂነሪንግ ከፍተኛ የእውቀት ሽግግር ሥራዎች ጋር በተጓዳኝ በምህንድስና እና የግንባታ ዘርፍም ውስብስብ የሲቪል ምህንድስና እንዲሁም የኤሌክትሪካልና ኤሌክትሮሜካኒካል ሥራዎች የተከናወኑበት ግዙፍ ፕሮጀክት መሆኑ ይታወቃል።
ባለፉት ዓመታት ፕሮጀክቱ በየደረጃው በርካታ ውስብስብና አሳሳቢ የፕሮጀክት የአፈፃፀም ችግሮች፣ የኮንትራት አስተዳደርና የፕሮጀክት አመራር ጉድለቶች ያጋጠሙትና እነዚህንም ውስብስብ ችግሮች፤ በትእግስትና በብስለት በተለያዩ ጊዜያት የማስተካከያ እርምጃዎች በመውሰድ ለዛሬው የመጀመሪያ ምዕራፍ ኃይል ማመንጨት ሥራ መብቃቱን መመልከት ለታደልን ሁሉ እጅግ የሚያስደስት ሲሆን፤ ለፕሮጀክቱ መሳካት በቅንነትና በኃላፊነት ብዙ ለጣሩ፣ ለደከሙና ይህንን መጨረሻ አስቀድመው በምናባቸው ላዩ የዚህ ፕሮጀክት ጥንስስና አመራር ሰፊ ተዋናዮችም በሙሉ ይህ የመጀመሪያ ምዕራፍ ኃይል የማመንጨት ሥራ ማስጀመሪያ (የመጨረሻው መጀመሪያ) ሥነ ሥርሥት በእርግጥም ቃላቸው ተግባራቸው እና መስዋዕትነታቸው በዚህ ትውልድም ተከብሮና ተጠብቆ ክፍተቶቻቸው ደግሞ በሚገባ ታርመው፤ ፕሮጀክቱ ከፖለቲካ መጠቀሚያነት አስወጥቶ ወደ እውነተኛ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሥራ የቀየረና የዛሬውን ፍሬ እንድናይ ያደረገ ለሕዝብ እና ለእውነት የቆመ መንግሥት መኖሩን ያረጋገጠ፤ ፕሮጀክቱን ፍሬያማ ለማድረግ የቆረጡ በአገራችን የኃይል አቅርቦትና ልማት የምህንድስና ዘርፍ ለአገራቸውና ለራሳቸው ጉልህ አበርክቶ ባደረጉ በእነ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ እና መሰል ጓደኞቻቸው እግር የተተኩ፤ አዲስ የፕሮጀክትና የአገር አመራር ትውልድ መፈጠሩን የሚያበስር ኩነት መሆኑን በሙሉ ልብ ማረጋገጥ እችላለሁ።
እዚህ ላይ በተለይም ባለፉት ሦስትና አራት አመታት ውስጥ በፕሮጀክቱ አመራርና የመሬት ላይ አፈፃፀም በተመለከተ ቀደም ብለው ተከስተው የነበሩ ጉልህ እና ውስብስብ የፕሮጀክት አያያዝና የአመራር ክፍተቶች የታረሙበትና መልሶም ፕሮጀክቱን ከስም አልፎ ዛሬ ለበቃበት ደረጃ ለማድረስ የተሰሩ ውስብስብ ሥራዎችን መላው የአገራችን ሕዝብ እንዲገነዘበው ማድረግ ያስፈልጋል።
በፕሮጀክቶች አያያዝና ጉልህ የቀደሙ እክሎች ምክንያት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢፈጠሩም ያለምንም ድንጋጤ ችግሮችን ከመሸፋፈን ይልቅ፣ ችግሮችን ተቀብሎ በጊዜያዊነት በማስተዳደር በመጋፈጥና በአፋጣኝም የፕሮጀክቱን አያያዝና አፈፃፀም የሚቀይሩ፣ የተጠኑና በንድፈ ሀሳብ ጭምር የተደገፉ እርምጃዎችን መውሰድ ያስገደዱ ቅርቃሮችም በየሥራው ዘርፍ በስፋት አጋጥመው እንደነበር ለማስታወስ እወዳለሁ።
ፈረንጆቹ ፤ When you are going through the hell, don’t stop /Keep Going/!! ይላሉ፤ ወደ አማርኛ ሲመለስ ከሞላ ጎደል “በሲኦል ጉሮሮ ውስጥ በምትሔድበት ጊዜ ሁሉ የሚሻልህ ያለመቆም ነው”፤ የሚል ነው፡፡ በእነዚህ የቀውስ ጊዜያት የተወሰዱ ቁልፍ እርምጃዎችም በፕሮጀክት አመራር ሥራዎች ጥናትና መስክ የፕሮጀክት ሥራ ተግዳሮቶች ቅልበሳ “project turnaround “ ልዩ ልምምድ የተቀመረበት በመሆኑ፤ በየትኛውም ደረጃ ለሚያጋጥሙ የፕሮጀክት አያያዝና አፈፃፀም ችግሮች ተጠቃሽ ማሳያነቱን እንደ አስፈላጊነቱ፣ በሚመለከታቸው የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ተመራማሪ አካላት ጥናት ቢደረግበት ጠቃሚ ይሆናል የሚል ፅኑ እምነት አለኝ።
የሕዝባችንና የአገራችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶች በቀጣይነት ለማሟላት እና በየአመቱ በአማካይ በ13 በመቶ እያደገ የመጣው የአገራችን የኃይል ፍላጎት መመለስ እንድንችል አሁን ካሉን እና እየገነባን ካለናቸው የኃይል ማመንጫዎች በተጨማሪ ሌሎች አዳዲስ ተጨማሪ የኃይል ምንጮች እና ፕሮጀክቶች ቀርፆ መተግበር እንደሚያስፈልግ መረዳትም ያስፈልጋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ በአመት 15ሺህ 760 ጅጋ ዋት ሰዓት ኃይል በማመንጨት የአገር ውስጥና የኤክስፖርት ፍላጎቶች ለማስተናገድ ከፍተኛ ድርሻ ይኖረዋል።
ዛሬ የኃይል ማመንጨት ሥራውን የሚጀምረው የፕሮጀክቱ ክፍል በመጀመሪያው ተርባይን በመጠቀም ኃይል የማመንጨት እቅዳችን የሚያሳካ አፈፃፀም ሲሆን፤ ፕሮጀክቱ ከኃይል ማመንጨት በተጨማሪ በአካባቢ ጥበቃና የቱሪዝም ልማት ዙርያ በቀጣይነት በፕሮጀክቱ የሚካተቱ ግዙፍ ተያያዥ ሥራዎችም በአካባቢው ማህበረሰብ ተሳትፎ ሌላ ጠንካራ የኢኮኖሚ ስበት ማዕከል መፍጠር የሚያስችሉ፣ የጎለበቱ ውጥኖችን ያካተተ መሆኑን በአንክሮ ማስተዋል ይገባል።
ፕሮጀክቱን በሚመለከት ከተለያዩ አቅጣጫዎች ከውስጥም ከውጭም ከቅርብም ከሩቅም፤ ከፕሮጀክቱ ዓላማና እውነታ በተፃራሪ ደም በለበሱ የምቀኝነት ዓይኖች የመታየቱ ምክንያት ምን እንደሆነም በአስተውሎታችን ልክ ሊገለፅልን ይችላል።
ይህ ፕሮጀክት በቀጣይ ተከታታይ ወራት በየምዕራፉ እንዲጠናቀቅ የሚያግዙ በርካታ ሥራዎች ከስር ከስር እየተከናወኑ ያሉ በመሆኑ በተከለሰው የፕሮጀክቱ የማጠናቀቂያ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ፕሮጀክቱ ተጠናቅቆ ወደተሟላ የኃይል የማመንጨት ሥራ የሚሸጋገርም ይሆናል።
ይህ ፕሮጀክት መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዓይንና ልቡን የጣለበት የጋራ ቁጭቱ መቋጫ ጫፍ የሚደርስበት መሆኑን ለአፍታ ሳይዘነጉ፤ በእጅግ አስቸጋሪ የአየር ጠባይና ከፍተኛ ሙቀት ሳይበገሩ፤ ሌት ተቀን ጉልበትና እውቀታቸውን ያለስስት ላለፉት በርካታ አመታት ላበረከቱና እያበረከቱ ለሚገኙ የጉልበት ሠራተኞች፣ በልዩልዩ የግንባታና የቴክኒክ እንዲሁም በአጋዥ አገልግሎት ሥራዎች የተሰማሩ የአገር ውስጥና የውጭ መሐንዲሶች እና ልዩልዩ ሙያተኞችን ከልብ እናመሰግናለን።
ለመላው የአገራችን ሕዝቦች፣ ለኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ለኢትዮጵያ ወዳጆች ይህ ፕሮጀክት እዚህ እንዲደርስ በሀሳብ፣ በገንዘብ፣ በእውቀት ያላችሁን ሁሉ ሳትሰስቱ በማበርከታችሁ ሁሌም በማይፋቅ የታሪክ መዝገብ ውስጥ ተመዝግባችኋልና እንኳን ደስ አለን።
የፌዴራልና የክልል የፀጥታ ኃይሎችና የኢፌዴሪ የመከላከያ ኃይላችንን ደግሞ በተለየ ከልብ እናመሰግናለን።
ልዩ ልዩ የክልልና የፌዴራል መስሪያቤት ኃላፊዎች እና አመራሮች፤ በአጠቃላይ ይህንን ፕሮጀክት እዚህ አመርቂ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ልዩ እገዛ ላደረጉ ሁሉ የላቀ አክብሮትና ምስጋናዬን ሳቀርብ፤ የፕሮጀክቱ ቀሪ ሥራዎች ተገባድደው ወደ መጨረሻ ምዕራፍ እንዲደርስ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ አሁንም እንደ ወትሮው ያልተቋረጠ ድጋፍና ክትትላቸው እንዳይለየን አደራም በማለት ጭምር ነው።
በመጨረሻም መላው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የህዳሴ ግድባችን አፈፃፀም ሂደት የመጨረሻው የመጀመሪያ የሆነውን ይህን የስኬት ምዕራፍ እና ቀጣይ ውጤቶቻችንን በተቀሩት ቁልፍ የአገራችን ጉዳዮች ላይ ለመድገምና ለመደጋገም የሚያስችለን ጥበብ፣ ስክነትና አንድነትን፣ ፈጣሪ እንዲሰጠንና በጥቂት ዓመታት ውስጥ እንደ ሕዝብ ወደ ምንመኘው ክብር እንደምንሸጋገር በሚያረጋግጥ መንገድ ላይ ስለመሆናችን በሚያሳይ ፅኑ እምነትና ፍላጎት ላይ ሆኜ፤ ሁላችንንም በድጋሚ፤ እንኳን ደስ አለን፤ እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እወዳለሁ።
ፈጣሪ አገራችን ኢትዮጵያን እና ሕዝባችንን ይጠብቅ ፤ ይባርክ !
አመሰግናለሁ!!
የካቲት 13 ቀን 2014 ዓ.ም
አዲስ ዘመን የካቲት 14 ቀን 2014 ዓ.ም