ዛሬ እንደ ወትሮው የተለመደውን ንግግር ለማድረግ ብዙ አቅም የለኝም። ያለፍንበትን ሁለት ሦስት ዓመታት እና ዛሬ የሆነውን ነገር ስመለከት የፈጣሪ ቸርነት እና ርዳታ በእጅጉ ያስደምመኛል። ስለሆነም ንግግሬን የማደርገው በአብዛኛው በምስጋና ላይ ብቻ ያተኮረ ይሆናል፡፡
በመጀመሪያ እጅግ የተከበራችሁ የሥራ ኃላፊዎች፣ አፄ ኃይለሥላሴን እንዳመሰግናቸው እንዲፈቀድልኝ እጠይቃለሁ። አፄ ኃይለሥላሴ፣ በዚያን ጊዜ ማድረግ የሚያስቸግርም ቢሆን፤ መልካም ሃሳብ፣ መልካም ዘር ለልጆቻቸው ማቆየትና ቀጣዩ ትውልድ ሊሠራው እንደሚችል አስበው በዚህ ቦታ ላይ ይሄንን ፕሮጀክት ዲዛይን አሠርተው ቀጣዩ ትውልድ ይገነባዋል የሚል እጅግ ትልቅ ራዕይ በመሰነቃቸው እና ያም ሕልም በልጆቻቸው እውን ስለሆነ ክብር እና ምስጋና ይገባቸዋል፡፡
የእሳቸው ልጅ የሆኑት እና ቀጣዩን ትውልድ የሚወክሉት አቶ መለስ ዜናዊ በሥልጣን ዘመናቸው መጨረሻ አካባቢ ይህ ፕሮጀክት ዓለምአቀፍ ሁኔታው እና የኢትዮጵያ ሁኔታ ምቹ ጊዜ እንደሆነ አምነው ፕሮጀክቱ እንዲጀመር በማድረጋቸው እና በእሳቸው ቆይታ የፕሮጀክቱ እድገት እምብዛም ያላደገ ቢሆንም በማስጀመራቸው እና ከእሳቸው የሚቀጥሉ አመራሮች እንደሚጨርሱት ተማምነው ለጀመሩት ሥራ ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል፡፡
ከእሳቸው በኋላ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ ፕሮጀክቱ በጅምር በቁፋሮ ጊዜ ከነበረበት ተረክበው እስከ ደረሰበት ደረጃ ድረስ ለማድረስ በእሳቸው ጊዜ የነበረው ምቹ ያልሆነ ፖለቲካል አውድ ሳያግዳቸው ላደረጉት ተጋድሎ፤ ከሁሉ በላይ ደግሞ ዕድለኛ ሆነው ዛሬ ከእኛ ጋር ሆነው ይሄንን ለማየት ስለበቁ እጅግ የከበረ ምስጋና እና አድናቆት እንዲሁም እንኳን ደስ ያሎት ልላቸው እወዳለሁ፡፡
ሦስቱ የአገራችን መሪዎች የሚከተሉት እሳቤ፣ አይዶሎጂ፣ የአመራር ሥርዓት፣ የተወለዱበት ከባቢ የተለያየ ቢሆንም፤ ኢትዮጵያውያንን አንድ የሚያደርግና የኢትዮጵያውያንን ልክ የሚያሳየውን ይሄንን ግድብ ሳያቋርጡ ከሃሳብ እስከ ንድፍ፣ ከንድፍ እስከ ጅማሮ፣ ከጅማሮ እስከ ተግባር ስላስኬዱ፤ ይህ የኢትዮጵያ የወደፊት ጉዞም ምልከታ እንዲሆን ስለሚያግዝ ወደኋላ መለስ ብሎ ማመስገንና ማስታወስ ተገቢ ይሆናል።እኛ የጀመሩትን የጨረስን እንጂ ያስጀመርን ስላልሆንን፣ የጀመሩትን አመስግኖ መጀመር ለሚቀጥለው ሥራም አጋዥ ይሆናል፡፡
ከሦስቱ መሪዎች በኋላ ሁለቱን ሚኒስትሮች በተለየ እንዳመሰግን ይፈቀድልኝ።የመጀመሪያው አቶ ዓለማየሁ ተገኑ ሲሆኑ፤ ይሄንን ፕሮጀክት ያስጀመሩ በቅርበት የመሩ ሰው ናቸው።እሳቸውም ዛሬ መታወስ እና መመስገን ይገባቸዋል።ከእሳቸው ቀጥሎ ኢንጂነር ዶክተር ስለሺ በቀለ፣ ሁላችሁም እንደምታውቁት በቅርበት ፕሮጀክቱን ለመምራት ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ መድረክም ጭምር ፕሮጀክቱን በሚመለከት ከፍተኛ ተጋድሎ ያደረጉ ሚኒስትር ናቸው።ሁለቱም ለነበራቸው አገልግሎት የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት፣ እኔም በራሴ ስም የማመሰግናቸው ይሆናል፡፡
እንዲሁም ሦስት የመብራት ኃይል ኃላፊዎችን ለማመስገን እወዳለሁ።በመጀመሪያ ዶክተር ምህረት ደበበ፣ የቀድሞው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩ፤ ጊቤ ሦስትን ያሠሩ፤ ይሄንን ፕሮጀክት ያስጀመሩ እና ረዘም ላለ ጊዜ ይሄን ተቋም የመሩ እና አገራቸውን ወደው እንደዚህ ዓይነት ፕሮጀክት እንዲከወን የረዱ ሰው በመሆናቸው፤ ከእሳቸው ቀጥሎም ኢንጂነር አዜብ አስናቀ፣ ይሄንን ተቋም በመምራት እና ጅማሮ ሥራዎችን በማስቀጠል ላደረጉት አስተዋጽዖ፤ እንዲሁም አሁን ያሉትን የመብራት ኃይል ባለስልጣን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ላመሰግናቸው እወዳለሁ፡፡
ፕሮጀክቱን በሚመለከት በጋራ የጀመሩ ሁለት ማናጀሮች፣ በተለይ ዛሬ በመካከላችን የማይገኙትን ኢንጂነር ስመኘው በቀለን በሕልፈታቸው ጅማሯቸው ጥረታቸው ልፋታቸው መና ሳይቀር በወንድማቸው ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ሕልማቸው እና ኃሳቦቻቸው በላቀና በተሻለ መንገድ እንዲፈጸም ስለሆነ፤ ለኢንጂነር ስመኘው በቀለ እና ለኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ከፍ ያለ ምስጋና እንዳቀርብ ይፈቀድልኝ፡፡
ከጅማሮ ጀምሮ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት ሆነው ያገለገሉ ሁሉም የቦርድ አባላት፤ በተለይ ከለውጡ በኋላ ጠንከር ያሉ ውሳኔዎቹን በሚጠይቅ ሥራ ውስጥ የነበሩ የሥራ አመራር ቦርድ በተለይም ዶክተር አብርሃም በላይን እና አቶ ግርማ ብሩን እንዲሁም ጠቅላላ የቦርድ አባላትን እንዳመሰግን ይፈቀድልኝ፡፡
ሕዳሴ ግድብ ላይ የተሳተፉ ሠራተኞች ሥራውን ስለሠሩ፣ በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሕዝባቸውን፣ አገራቸውን ሕልም ስላሳኩ ምስጋና የሚገባቸው ቢሆንም፤ በተለየ መንገድ እኔ ማስታወስ የምፈልገው ከሁለት ወር በፊት በገጠመን ጦርነት በተወካዮቻቸው አማካኝነት የሕዳሴ ግድብ ለአፍታ የሚቆም ከሆነ እዚህ ያለን ሰዎች መጥተን ጦሩን ለመቀላቀል እና ውጊያውን ለመዋጋት የአገራችንን ክብር ለማስጠበቅ ዝግጁዎች ነን ብለው የላኩት መልዕክት ሁሌም ከልቤ የማይፋቅ ነው። እዚህ ያሉት ጀግኖች ወታደሮች እና ሠራተኞች ባደረጉት ተጋድሎ ግድቡን እውን ማድረግ ብቻ ሳይሆን የቁርጥ ቀንም አለኝታ መሆናቸውን ስላሳዩ ከልብ ላቅ ያለ ምስጋና ላቀርብላቸው እወዳለሁ፡፡
እንዲሁም የአገር መከላከያ ሚኒስቴር እና የጸጥታ አካላት በቅርቡ ፕሮጀክቱን ለማስጨረስ በምናደርገው ጥረት በየመንገዱ በነበረው ተጋድሎ መስዋዕትነት እየከፈሉ፣ በእግር ብዙ ኪሎሜትሮችን እየተጓዙ ሲሚንቶ እያጓጓዙ ያሉ የጸጥታ ኃይሎችን በሙሉ ላቅ ያለ ምስጋና እንዳቀርብ ይፈቀድልኝ፡፡
የዳያስፖራ አባላት ገንዘብ በማዋጣት ብቻ ሳይሆን አስፈላጊ በሆነበት ሁሉ ድምጽ በማሰማት እና የኢትዮጵያ ጥቅም የሚከላከል ኃይል ሆነው ላበረከቱት አስተዋጽዖ፤ ዳያስፖራውን ከሁሉም በተለየ በሕዳሴ ግድብ ላይ ባላቸው ኮሚትመንት (ቁርጠኝነት) እና አስተዋፅዖ ላቅ ያለ ምስጋና እንዳቀርብላቸው ይፈቀድልኝ፡፡
የቴክኒክ ኮሚቴ ሆነው ያገለገሉ፣ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ላይ ያገለገሉ፣ በተለያየ ዓለምአቀፍ ሚዲያ አገራቸውን ወክለው የሠሩ፤ በተለይም በአረብኛ ቋንቋ ምንም ክፍያ ሳይከፈላቸው በግል ፍላጎትና ተነሳሽነት ከተለያየ አገር ሆነው ተናበው የሠሩ፤ ዛሬም በመካከላችን የሚገኙ የሕዳሴ ግድቡ አምባሳደሮች በመሆን ለመላው የአረብ ሕዝብ ይህ ውሃ ተገድቦ የሚቆም ሳይሆን ኃይል ብቻ እያመነጨ የተፈጥሮ ፍሰቱን ጠብቆ የሚጓዝ መሆኑን በማስገንዘብ ደረጃ ከፍተኛ ተጋድሎ ስላደረጉ እነዚህንም እንዳመሰግን ይፈቀድልኝ፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ በጥቅሉ ስላመነን፣ ገንዘቡን ስላዋጣ፣ አስፈላጊ በሆነበት መድረክ ሁሉ ለዚህ ፕሮጀክት ድምጽ ስለሆነን፤ ይህ ፕሮጀክት ደግሞ የአንድነታችን፣ የመነሳታችን፣ የመላቃችንና የአይበገሬነታችን ምልክት ስለሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ ላደረገው ሁለንተናዊ ተጋድሎ ከፍ ያለ ምስጋና እንዳቀርብ ይፈቀድልኝ፡፡
እስካሁን ካመሰገንኳቸው አካላት ሁሉ እጅግ በላቀና ከልብ በመነጨ እና በከፍተኛ ትህትና በተለየ ሁኔታ ፈጣሪዬን ላመሰግን እወዳለሁ። ፈጣሪ ባይታከልበት ኖሮ ይህ ፕሮጀክት ዛሬ የደረሰበት ደረጃ ደርሶ በዚህ ሁኔታ ልናስጀምረው እንደማንችል በሂደት ውስጥ ያለፍን ሰዎች ሁሉ እናውቀዋለን፡፡
ይህ ፕሮጀክት እጅግ ፈታኝ የነበረ ብቻ ሳይሆን፤ የገዛነውን ዕቃ ማስገባት የማንችልበት፣ የቀጠርነውን የውጭ ሠራተኛ ማሠራት የማንችልበት፣ ጫናው ፍልሚያው ተጋድሎው እጅግ አስመራሪ የሆነበትን ጊዜ ሁሉ ፈጣሪ ማከናወንን ሰጥቶን ከማሳካትም ባሻገር፤ ዛሬ እንኳን እንግዶቻችን በፀሐይ እንዳይመቱ ውብ ደመና በመስጠት በከፍተኛ ድምቀት እንዲከወን አስችሎናል።ይህ ደግሞ ምድራዊ ብቻ ሳይሆን ሰማያዊ ቅቡልነት መሆኑን ዳግም ስላረጋገጠልን ፈጣሪያችንን እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ፡፡
በመጨረሻም የታችኛው ተፋሰስ አገራት ወንድም የግብጽ እና የሱዳን ሕዝቦች ዛሬ የተጀመረው የኃይል ማመንጨት ሥራ ለእናንተም በረከት ነውና እንኳን ደስ ያላችሁ ልላችሁ እፈልጋለሁ።ባልተገባ ሁኔታም ቢሆን ለፈጠራችሁት ተጽዕኖና ፈተናም እጅግ አድርጌ አመሰግናችኋለሁ፡፡
መላው የዓለም ሕዝብ እንዲገነዘብ የሚያስፈልገው ይህ ውሃ ኃይል እያመነጨ ቀደም ሲል የሚያደርገውን ተግባር በመፈጸም ወደ ሱዳን እና ወደ ግብጽ የሚሄድ እንጂ፤ በአሉባልታ ሲነገር እንደነበረው የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት ውሃውን ገድበው የወንድም ግብጽን እና ሱዳን ሕዝብን የማስራብም የማስጠማትም ፍላጎት እንደሌላቸው ስንናገር የነበረውን ዛሬ በተግባር ያሳየንበት ቀን ስለሆነ ሁሉንም የግብጽና የሱዳንን ብቻ ሳይሆን መላ የአፍሪካ ወንድም እና እህት ሕዝቦች እንኳን ደስ አላችሁ እላለሁ። ሃሳባችን የቀና ተግባራችን አድካሚም ቢሆን ፍሬያችንም ያማረ ነውና ሁላችሁም የእኛን መንገድ ተከትላችሁ ከልመና በመውጣት ሕይወታችሁንና የሕዝባችሁን ሕይወት ለመለወጥ እንድትሠሩ አደራ ልላችሁ እፈልጋለሁ፡፡
የሕዳሴ ግድብ አሁን ያለበትን ደረጃ በቀላል ምሳሌ ለመግለጽ፡- አንድ ሰው ሃያ ክፍል ያለው ሆቴል ለመገንባት ቢነሳ በመጀመሪያ እንግዳ መቀበያውን፣ ሬስቶራንቱን፣ አጠቃላይ የሆቴሉን ውቅር ከሠራ በኋላ፤ አምስት መኝታ ቤቶች አጠናቅቆ ለምርቃት ወዳጆቹን ቢጠራ ሆቴል አስመርቃለሁ ብሎ እንደሚጠራው ሁሉ፤ ከሁለትና ሦስት ወር በኋላ ስድስተኛውን፣ ሰባተኛውን፣ ስምንተኛውን፣… መኝታ ክፍል እየጨረሰ ቢያስገባ መኝታ ክፍል ባደሰና ባዘጋጀ ቁጥር ሆቴል አያስመርቅም፡፡
መጀመሪያ ላይ ሬስቶራንቱን ከጨረሰው የአልጋ ቁጥር ጋር ካስመረቀ በኋላ በየሁለትና ሦስት ወሮች አዳዲስ መኝታ ክፍሎች ሊጨመሩ ይችላሉ፤ የተተከሉ ዛፎች ሊበቅሉ ይችላሉ፤ አዳዲስ አሠራሮች ሊጨመሩ ይችላሉ፤ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓቱ ሊዘምን ይችላል፤ በየጊዜው ግን ምርቃት አይካሄድም።ዛሬ የመጀመሪያው ክፍል፣ ሬስቶራንትና አገልግሎት መስጠት የሚችለው ሆቴል ተመርቋል፡፡
ከዚህ በኋላ የሚኖረው ሥራ አዳዲስ ክፍሎችን እንደመጨመር፣ አዳዲስ አገልግሎት እንደመጨመር የሚታይ ሥራ ስለሆነ በሕዳሴ ጉዳይ፤ በዚህ ውሃ ጉዳይ መነታረክ ትተን በትብብር መንፈስ፣ በሚያግባባ መንፈስ፣ ግብጽን በሚጠቅም፣ ሱዳንን በሚጠቅም፣ ሌሎች ተፋሰስ አገራትን በሚጠቅም፣ እኛንም በሚጠቅም መንገድ የጋራ ትብብር እንድናደርግ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡
የኢትዮጵያ ፍላጎት ይሄንን ኃይል በማምረት የጎረቤት አገራትን መጥቀም፤ ውሃውንም ወደ ግብጽና ሱዳን መላክ ብቻ አይደለም። አሁን በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ገመድ ተቀጥሎ ኃይል እየሸጥንላቸው እንገኛለን።ግብጽ ደግሞ ቀይ ባህርን፣ ሜዲትራኒያንን ተሻግሮ ከሌሎች የአውሮፓ አገሮች ጋር የተገናኘ መስመር አላት።እናም ከሱዳን ወደ ግብጽ ያለውን መስመር ማገናኘት በጣም ቀላል ስለሆነ ተጨማሪ የኃይል ማመንጫዎች እየሠራን አውሮፓ ላይ ያለውን የጋዝ ኃይል ማመንጫ እና ከባቢ አየርን እየበከለ ያለውን ነገር ለመቀነስ ከዚህ ወደ አውሮፓ ኃይል ኤክስፖርት(የመላክ) የማድረግ ፍላጎት አለን። የኢትዮጵያ ፍላጎት ይሄ ነው፡፡
ይህ ፍላጎታችን ባዶ ሕልም አይደለም።ይልቁንም በከፍተኛ ቦታ ላይ የምንገኝ፣ ከፍተኛ የዝናብ መጠን የምናገኝና ብዙ ወራጅ ውሃ ያለን አገር በመሆናችን፤ በርከት ያሉ ግድቦች ገንብተን ለእኛም ለሌሎች አገራትም የሚተርፍ ኃይል ማምረትና መሸጥ የምንችል ስለሆንን ነው። የምዕራቡ ዓለም እና ገንዘብ ያላቸው አገራትም አሁን ያለውን የውሃ ፖለቲካ መልክ ቀይረው ከእኛ ጋር በትብብር አዳዲስ ፕሮጀክቶች በመሥራት ለእኛም ከድህነትና ከጨለማ መውጫ፣ ለእነሱም ከጋዝ ብከላ መገላገያ እንዲሆናቸው በቀና እና በአዲስ መንገድ በትብብር መንፈስ እንድንሠራ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡
ኢትዮጵያ ማንንም የመጉዳት ሀሳብ፣ ፍላጎትና ድርጊት የሌላት፣ የኢትዮጵያ ዋነኛው ፍላጎት 60 በመቶ በጨለማ የሚሰቃየውን ሕዝብ፣ አምፖል አይተው የማያውቁ እናቶች፣ በጀርባቸው እንጨት ተሸክመው ኃይል ለማምረት የሚጥሩ እናቶችን ጉልበት ለመከላከልና አሁን ካለንበት ድህነት ለመገላገል ብቻ ያለመ ፍላጎት ነው።ይህም ሲሆን ደግሞ የወንድሞቻችንን ጥቅም በጠበቀና በትብብር መንፈስ መሆኑን ተገንዝባችሁ እስካሁን ለማደናቀፍ የወጣው ጉልበት፣ ጊዜና ገንዘብ ቀርቶ ለልማት በትብብር በጋራ እንድንቆም በታላቅ ትህትና ከአደራ ጭምር ጥሪዬን ላቀርብላችሁ እፈልጋለሁ፡፡
“ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ” ስንል ቆይተናል፤ ባርኳል፣ አስጀምሯል፣ የብልጽግና ጉዞ በር ተከፍቷል፣ ከእንግዲህ ኢትዮጵያን የሚያቆማት ነገር አይኖርም።ኢትዮጵያውያን ልንገነዘብ የሚያስፈልገው ከጥቃቅን አጀንዳ፣ እርስ በእርስ ከመበላላት፣ ከማያስፈልጉ ሽኩቻዎች ወጥተን ተደምረን፣ ተሰባስበን እንደ ሕዳሴው ኢትዮጵያን እንድንሠራ እና በከፍታ ማማ ላይ እንድናስቀምጥ፤ ከመናቆርና ከማያስፈልግ የተንኮል ፖለቲካ እንድንወጣ፤ በይቅርታ ልብ በጋራ እንድንቆም፤ ሕዳሴ መከናወኑ ለኢትዮጵያ ሰላም፣ ለኢትዮጵያ ኅብረት፣ ለኢትዮጵያ አንድነት በር ከፋች ሆኖ እስካሁን የነበርንበት ግጭትና አላስፈላጊ ንትርክ ቆሞ ተባብረን አገራችንን እንድናለማ፤ ወደ ብልጽግና እንድንሸጋገር፤ ፈጣሪ የሰጠንን ዕድልና ጸጋ እንድንጠቀም፤ ከማያስፈልጉ የቅጥረኛ አስተሳሰቦች እንድንወጣ እና ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊ ሆነን እንድንቆም በታላቅ ትህትና ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡
እንኳን ደስ ያላችሁ፤ እንኳን ለዚህ ቀን በቃን፤ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የብልጽግና ጉዞ መጀመሩን ተገንዝቦ በአንድ መንፈስና ልብ በጋራ በመቆም ኢትዮጵያን ወደሚገባት ክብር እንድናወጣት፤ ነፃ ሆና የተረከብናትን አገር ነፃ እና የበለጸገች አድርገን ለልጆቻችን እንድናስረክብ በታላቅ ትህትና አደራ ማለት እፈልጋለሁ፡፡
ስለሆነው፣ ስለሚሆነው ሁሉ ፈጣሪያችን የተመሰገነ ይሁን። አመሰግናለሁ!
አዲስ ዘመን የካቲት 14 ቀን 2014 ዓ.ም