ኢትዮጵያውያን በአሸባሪ የሕወሓት ቡድኑ ጦርነት ተከፍቶባቸው የህልውና ትንቅንቅ ውስጥ ከገቡ ጀምሮ አያሌ ነገሮችን ተመልክተናል። በዋናነት አገራችን ወዳጅና ጠላቷን ከመለየት ባለፈ የቁርጥ ቀን ልጆች እነማን እንደሆኑም አውቃበታለች። በሂደቱ ላይ በተለያየ የህይወት አጋጣሚ የትውልድ አገራቸውን ትተው በስደት የቆዩ ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን የነበራቸው ተሳትፎና አሁንም ድረስ እያበረከቱት ያለው አስተዋጽኦ አስደናቂ ነው።
በዓለም አደባባይ ድምፅን ከፍ አድርጎ ከማሰማት በዘለለ፣ በጦርነቱ የተጎዱ ወገኖችን ለመደገፍ ያደረጉትና እያደረጉ ያሉት ጥረት ታሪክ በበጎ የጀግንነት የትውስታ መዝገብ ላይ የሚያሰፍረው ነው። ይህ ብቻ አይደለም ከምንም ነገር በላይ ዓለም ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ፊቱን ባዞረበትና ከውሸት ጎን በቆመበት ቅፅበት ባህሉን፣ ማንነቱን እንዲሁም አንድነቱን ጠንቅቆ የሚያውቀው ትውልደ ኢትዮጵያዊ በጭንቅ ግዜ ወደ አገሩ ለመግባት በአንድነት ተነቃንቋል። ይሄ ኢትዮጵያውያን ከጥንትም ጀምሮ የማይናወጥ እሴቶችና ባህላዊ መሰረት ያላቸው በፀና አለት ላይ የቆሙ ህዝቦች መሆናቸውን ያስመሰከረ ነበር።
የአገር አንድነትን ለመጠበቅ ወደ አገራቸው የገቡት ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ደግሞ መንግስት እንግዳን ሳይሆን ልጆችን በሚቀበልበት ፍፁም ባህላዊ እሴቶች “በእቅፍ ውስጥ” በማቆየት ቀድሞውኑም የሚያውቁትን፣ ቢያዩት፣ ቢዳስሱት፣ ቢቀምሱት፣ ቢውረገረጉበት በሚያስደስታቸው “ባህላዊ እሴቶች” አቀባበል ለማድረግ ዝግጅቱን አድርጎ እንደነበር የምናስታውሰው የቅርብ ግዜ ትዝታችን ነው።
ከዚህ የአቀባበል ስነ ስርዓት ውስጥ አንዱ የሆነው ደግሞ በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የሚመራው ዝግጅት ነበር። መስሪያ ቤቱም ከኢስት አፍሪካን ቢዝነስ ግሩፕ እና ከኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማህበር ጋር በመተባበር “በታላቁ ጉዞ ወደ ሀገር ቤት” የመጡትን ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች በሀገር ባህል ወግ ሥርዓት አቀባበል የሚስተናገዱበትና እንግዶችም ተደስተው የሚመለሱበት ዝርዝር መርሐግብሮች አዘጋጅቶ ነበር።
ከዚህም መካከል አንዱና ደማቅ ስነስርአት የነበረው በወዳጅነት አደባባይ የተካሄደው የሙዚቃ የስነ ፅሁፍ፣ የባህል አልባሳት፣ የተለያዩ የእደ ጥበብና ኪነ ጥበብ አውደ ርእይ ነበር። የዝግጅት ክፍላችንም በስፍራው ተገኝቶ አውደ ርእይውን በማቅረብ፣ በማዘጋጀትና ተሳትፎ በማድረግ ከተሳተፉ አካላት ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርጎ ነበር። ከዚህ እንደሚከተለው አጠቃላይ መሰናዶውና ሂደቱ ምን መልክ እንደነበረው ለማቅረብ ወድደናል።
አቶ ዓለማየሁ ጌታቸው በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ውስጥ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት ዲያስፖራው የተደረገለትን ጥሪ አስመልክቶ በተካሄደው አውደ ርእይ ላይ ሁሉም ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ተሳታፊ ሆነዋል። በዚህም ሁሉም ያላቸውን የእደ ጥበብ ምርት፣ ባህላዊ አልባሳት፣ የሙዚቃና ውዝዋዜ፣ የስነ ፅሁፍ ሃብቶች ለዲያስፖራው ማህበረሰብ ማቅረባቸውን ይናገራሉ።
“ለሶስት ቀናት ትውልደ ኢትዮጵያውያን በባህላዊ ጭፈራ፣ ምግብና መጠጥ እንዲሁም የተለያዩ እሴቶች እየታደሙ እንዲቆዩ የተሰናዳ ነው” ያሉት ዳይሬክተሩ ይሄም ዲያስፖራው ማህበረሰብ እሴቶቹን በአንድ ስፍራ ላይ አግኝቶ እየተዝናና ስለ ብዝሃ ኢትዮጵያዊነት ጠንቅቆ እንዲያውቅ ትልቅ እድል የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል። በተያያዘ ኢትዮጵያዊ ባህል፣ ስፖርቶችንና መሰል እሴቶችን ከማበልፀግ ፣ ከመጠበቅና ለትውልድ ከማሻገር አንፃር ከእነዚሁ ኢትዮጵያውያን ጋር ሲምፖዚየም መደረጉን አንስተዋል።
“ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ዲያስፖራው ወደ አገር ቤት እንዲመጣ ጥሪ አድርገዋል።
በዚህ አጋጣሚም በጥርና በታህሳስ ወቅት ባሉ ባህላዊ ድባብ እንዲመለከትና ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲያደርግ በማሰብ የተለያዩ መርሃ ግብሮችን አዘጋጅተን ቆይተነዋል” የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ በዋናነትም ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ የሚያሰኛት ይህ ህብረ ብሄራዊ አንድነትና ባህላዊ ሃብቶች መሆናቸውን አጋጣሚውን በመጠቀም ለማስተዋወቅ በማሰብ መካሄዱን ነግረውናል። ቀድሞ ይሄን የሚያውቅ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ይበልጥ እንዲያስታውሰው፤ በዚያ ተወልደው ባህላቸውን እሴቶቻቸውን ለማወቅ እድሉን ያላገኙት ደግሞ እንዲያውቁ የማድረግ ታላቅ አላማን ማንገቡንም ይናገራሉ።
አቶ አለማየሁ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለቀሪው ዓለም የኢትዮጵያን ሀብቶች ለማስተዋወቅ፣ ገበያ ለመፍጠርና የቱሪዝም እንቅስቃሴው እንዲነቃቃ ለማስቻል የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚችሉ ያምናሉ። በዚህም በአውደ ርእይው ላይ የተመለከቱትን ባህላዊ ቁሳቁሶች፣ አልባሳትና ጌጣጌጦች እንዲያስተዋውቁና እራሳቸውም ግብይት አድርገው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ያነሳሉ። ይሄ እድል ደግሞ በውጪው ዓለም የኢትዮጵያውያን የሆኑ ሀብቶች ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እድሉን የማስፋት አቅም እንዳለው አንስተዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር መሰል አውደ ርዕይ እንዲሁም ብዝሃነትን የሚያስተዋውቁ መርሃ ግብሮችን በተመሳሳይ መንገድ ተከታታይነት ባለው አግባብ ለማዘጋጀት ቁርጠኛ መሆኑን የሚናገሩት አቶ አለማየሁ፤ ባህል ያልሆነ ምንም ነገር አለመኖሩን በማስገንዘብ ለአሁን የሚዳሰስ የሚጨበጥና ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ መሰናዶዎች ይቅረቡ እንጂ ሌሎች በልዩ ልዩ መንገድ የሚገለፁ ኢትዮጵያዊ ባህላዊ ሀብቶችን የማስተዋወቅ ስራ እንደሚሰራ ነግረውናል።
ወይዘሮ ባንቺዓለም ውቤ የባህላዊ አልባሳትና በኦፓል ምርት የስነ ጥበብ ውጤቶች አምራችና አቅራቢ ነች። በወዳጅነት አደባባይ ለዲያስፖራው ማህበረሰብ የተዘጋጀ አውደ ርእይ ላይ የስራ ውጤቶቿን ይዛ የመቅረብ እድሉን አግኝታለች። እርሷ እንደምትለው፣ መቀመጫዋን በአዲስ አበባ ከማድረጓ አንፃር ስራዎቿ ብዝሃነትንና ኢትዮጵያዊ ባህልን የሚያሳይ ከመሆኑ ባሻገር ዘመናዊነትን የተላበሰ እንዲሆንና ተጠቃሚው በየእለት እንቅስቃሴው ላይ እንዲጠቀመው ለማድረግ ትሞክራለች።
አልባሳቶቹ የሽመና ውጤት ከመሆናቸው በተጨማሪ የተለያዩ ቀለማትን እንዲይዙና የሁሉንም ፍላጎት ባሟላ መልኩ እንዲሰሩ ማድረጓን ነው የምትገልፀው። የእነዚህ ምርቶች ተጠቃሚ የሆኑት ዲያስፖራዎች፣ የውጭ ዜጎችና የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መሆናቸውን አንስታም አሁን ላይ በልዩ ሁኔታ በበዓላት፣ በሰርግ፣ በሃይማኖትና የህዝብ ፌስቲቫሎች ላይ ተመራጭ መሆናቸውን ትገልፃለች።
“ዲያስፖራም ሆነ የውጭ ዜጎች የኢትዮጵያን ትክክለኛ ባህሎች የሚያንፀባርቁ ስራዎች እንድናቀርብላቸው ይፈልጋሉ። የሚሰጡን አስተያየትም ገንቢ ነው” የምትለው ወይዘሮ ባንቺዓለም ይህን መሰል አውደ ርእይ ላይ መሳተፍ የአገር እሴቶችን ከማስተዋወቅ ባሻገር ጥሩ የገበያ እድል የሚፈጥርና ከቀሪው ዓለም ጋር በስፋት ትስስር ለመፍጠር መንገድ ከፋች መሆኑን ገልጻለች።
ጥሪ ተደርጎላቸው የመጡ ትውልደ ኢትዮጵያውያንም እዚህ ያዩትን መልካም ገፅታ የሚገነቡ ቱባ የኢትዮጵያውያን ባህላዊ አልባሳት፣ ምግቦች፣ ሙዚቃና ጭፈራዎችን ወደየሚሄዱበት አገር በማህበራዊ የድረገፅ የማሰራጫ ዘዴዎች ማድረስ ከቻሉ ማንነታችንን በሚገባ ከማስተዋወቅ ባለፈ በቱሪዝም ሃብቶቻችን የአገራችንን ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባት ይቻላል የሚል እምነት አሳድሮባታል።
ወይዘሮ ባንቺዓለም ከባህላዊ አልባሳት ምርት ውጪ የስነ ጥበብ “የስእል ጋለሪ” ባለቤትም ናት። በጋለሪዋ በዓለም አገራት ተወዳጅነትን ባተረፈውና በኢትዮጵያ በእምቅ ሃብትነቱ በሚታወቀው “የኦፓል” የጌጣጌጥ መስሪያ ተረፈ ምርት ታዋቂ የአገር ባለውለታዎችን ምስል በማሰራት ገበያ ላይ ታቀርባለች። ስእሎቹምየኢትዮጵያን የቱሪዝም ሀብቶች፣ የአገር ባለውለታዎች፣ ታሪካዊ ስፍራዎች፣ ቅርሶች እና መሰል መስህቦችን የሚያሳይ ከመሆኑ አንፃር ኢትዮጵያን የማስተዋወቅ ሰፊ አቅም እንዳላቸው ትናገራለች። በአውደ ርእይው ላይ ለዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ለእይታ ያቀረበቻቸው ሲሆን ሰፊ ተቀባይነትና የገበያ አማራጭም ማግኘት ችላለች።
አቶ ንጋቱ መኮንን ደግሞ ዲያስፖራ ናቸው። በካናዳ ኦታዋ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ ለበርካታ ዓመታት በዚያ ኖረዋል። አሁን መንግስት ያደረገውን ወደ አገራችሁ ግቡ ጥሪ ተቀብለው መጥተዋል። የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ያዘጋጀውን ባህላዊ ግብዣ ለመታደምም በወንድማማቾች አደባባይ ተሳታፊ ሆነዋል። ሙዚቃውን፣ አልባሳቱን፣ ቁሳቁሱንም ሆነ ብዝሃ ባህሎችን በአንድ ቦታ ላይ በማግኘታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ይናገራሉ።
“ከመጣሁ ጀምሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ጨምሮ በርካታ ቦታዎችን ተመልክቻለሁ” የሚሉት አቶ ንጋቱ ልጆቻችን ምንም እንኳን በዚያ ቢወለዱም ኢትዮጵያዊ ባህልን እንዲረዱና በእሴቱ ተኮትኩተው እንዲያድጉ ፍላጎት እንዳላቸው ይናገራሉ። ለዚህ ደግሞ መሰል ሁነቶች ላይ መሳተፍ፣ ባህሎቻቸውን የሚያውቁበት ዝግጅቶች ላይ እንዲታደሙ ማድረግ፣ ምግቦቹን፣ ሙዚቃዎቹን፣ አልባሳቶቹን እንዲጠቀሙ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለባቸውና እርሱን በመወጣት ላይ እንደሚገኙ ይናገራሉ።
“መንግስት መሰል ጥሪዎችን አድርጎ ስለጋበዘን ደስተኛ ነኝ” የሚሉት አቶ ንጋቱ፤ ይህን እድል አሊያም አጋጣሚ ያልተጠቀሙ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተለያየ ጊዜ ወደ አገራቸው መምጣት እንዳለባቸው ይናገራሉ። በተለይ ትውልዱ የኢትዮጵያ እሴቶችን ማወቅና በዚያም ማደግ ስለሚገባው ይህን ኃላፊነት ወላጆች ወስደው ማሳወቅ፣ ማስተማር ይገባቸዋል የሚል አስተያየት ይሰጣሉ።
ኢትዮጵያውያን ውብ ድብልቅ ማንነት ያለን ከቀሪው ዓለም የሚለየን በርካታ ባህላዊ እሴቶች የያዝን ነን። አስተውሎ አገራችንን ለመረዳት የሞከረ ሁሉ በህዝቦች ህብረት፣አስተሳሰብ፣ አብሮ የመኖርና የመቻቻል፣ የቋንቋ፣ የአለባበስ፣ አመጋገብና የተለያዩ የሃዘንና የደስታ ግዜ ስርአቶቻችን እጅግ ማራኪና ከእኛ ውጪ በሌላ አገር የማናገኛቸው ናቸው። የጎዳና ላይ የጥምቀት፣ የጨምበላላ እና ሌሎችም ልዩ ልዩ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ስርአቶቻችን እኛነታችን ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ እሴቶቻችን ናቸው። እነዚህን ሀብቶቻችን ከበርካታ ሺ ዘመናት በላይ ማህበረሰቡ ሳይበረዙና ሳይጠፉ ጠብቆ ለአዲሱና መጪው ትውልድ ማስተላለፍ ችሏል።
በውጭ አገራት በርካታ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ለስራ፣ በስደትና በተለያየ አጋጣሚ መኖሪያቸውን አድርገዋል። ቤተሰብ መስርተውም ልጆቻቸውን በዚያው አፍርተዋል። ምንም እንኳን እነርሱ በኢትዮጵያውያን ባህል፣ ስርዓትና ማንነት ተቀርፀው ወደዚያ ቢሄዱም ልጆቻቸው ግን የኢትዮጵያን ባህላዊ ሃብቶች ለማወቅ ያሉበት ነባራዊ ሁኔታ ይገድባቸዋል። በመሆኑም ወላጆች ይሄን ክፍተት ለመሙላት ታላቅ ሃላፊነት ይወድቅባቸዋል። በቀዳሚነት እነርሱ ለዓመታት ጥለውት የቆዩትን ባህላቸውን ከማስታወስ በዘለለ ልጆቻቸው በዚህ ኢትዮጵያዊነትን ጠንቅቀው እንዲረዱ የማድረግ የቤት ስራ ያርፍባቸዋል። ታዲያ ይህን መሰሉን ከባድ ኃላፊነት ለመወጣት ወደ ወገናቸውና ወደ አገራቸው ማማተር፣ በተደጋጋሚ ተመላልሰው መምጣትና ልጆቻችውንም በዚህ የስብእና ልእቀት መቅረፅ አለባቸው።
ይህን መሰሉን ድርሻቸውን በቀላሉ እንዲወጡ ለማስቻል ደግሞ መንግሥት በቅርቡ ከዲያስፖራው ማህበረሰብ ጋር የፈጠረው መናበብና አብሮ በጋራ መስራት ትልቅ ጫናን እንደሚያቀል ይታመናል። ከሁሉም በላይ ግን ኢትዮጵያዊነት በቀላሉ ሲፍቁት የሚለቅ የግድግዳ ቀለም አለመሆኑን ይሄ ህብረታችን ለቀሪው ዓለም ቁልጭ አድርጎ የሚያመለክት በመሆኑ “ይበል በዚሁ ይቀጥል” የሚል መልእክት እንድናስተላለፍ አድርጎናል። ሰላም !
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን የካቲት 13/2014