ሱስ ልማድ ወይም ጸባይ እንደሆነ ይገለጻል። በዚህም በቀላሉ ለማቆም አስቸጋሪ ነው። ሁኔታው ቀጣይነት ያለው በመሆኑ ደግሞ በሕይወት መኖርን ጭምር የመገደብ ኃይል አለው። ቆሞም ቢሆን ኑሮን የሚያናጋ እንደሆነ በብዙዎች ዘንድ የምንመለከተው ነው። በአካልም ሆነ በስብዕናም ያቆስላል። ከሁሉም በላይ የዝቅተኝነት ስሜትን በማላበስ ማንነትን ያስረሳል። በቃ በዚህ ውስጥ ያለ ሰው ከመሞት መሰንበት ብሎ ነው የሚኖረው። ይህ ደግሞ ከሰውነት ጎዳና ያወጣዋል። በብዙዎች ዘንድም ያስንቀዋል። በተለይ ከሥራ ጋር ተያይዞ ብዙ ነገርን የሚነጥቅ ነው። በእርግጥ ይህ የሚመጣው በተለያየ አጋጣሚ እንደሆነ ይታመናል።
ራሳቸውን ለመርሳት ሲሉ የሚገቡበት እንዳለ ሆኖ ብዙዎች ግን ከችግራቸው ለመላቀቅ ሲሉ በሚያደርጉት መፍጨርጨር ውስጥ የሚገጥማቸው ነው። ከእነዚህ መካከል ደግሞ ለዛሬ በ‹‹ ሕይወት ገጽታ›› አምዳችን ይዘናቸው የቀረብነው አቶ ተሾመ ግርማ አንዱ ናቸው። በሕይወታቸው ላይ ሱሰኝነት ብዙ ፈተና ጋርጦባቸው ነበር። ዓመታትን ሲበጠብጣቸውና በሞት እያሰኛቸው አሳልፈውበታል። ይሁን እንጂ ሥራቸውንና ሕይወታቸውን ሳይነጥቀው ራሳቸውን ማየት በመቻላቸው አምልጠውታል። በዚህም ዛሬ የተሻለውን ሕይወታቸውን እንዲኖሩ ሆነዋል። እናም በተለይ ወጣቱ ከዚህ ሕይወታቸው ብዙ የሚቀስሙት ልምድ አለና ተሞክሯቸውን ተማሩበት ስንል ለንባብ አቀረብንላችሁ። መልካም ንባብ፡፡
ራሱን ያሳደገው ልጅ
ተወልደው ያደጉት በሰላሌ አውራጃ ጅዳ ስርጢ በተባለች ከተማ ውስጥ በ1967 ዓ.ም ነው። ይህቺ ከተማ ለእርሳቸው ብዙውን የልጅነት ጊዜያቸውን ያሳለፉባት ነች። መልካም ምግባርን የቀሰሙባት፣ የተለያዩ ሥራዎችን የለመዱባትና የቦረቁባትም ነች። በእርግጥ አባትና እናታቸው ተለያይተው ስለሚኖሩ ከእናታቸው ጋር ብዙውን ጊዜያቸውን ስላሳለፉ ኖረውባታል። ነገር ግን ልጅነታቸው ሙሉ ለሙሉ በዚያ ስፍራ ብቻ አልተገነባም። ሌሎች ስፍራዎችም አስተዋጽኦ ነበራቸው። ይሁን እንጂ የዚህችን ከተማ ነዋሪ ያክል ያደረገላቸው አልነበረም። እናታቸው ብዙ ነገራቸው ነበሩና ለእርሳቸው የሚሆኑ ተግባራትን ከውነውባታል። ስለዚህም ልጅነታቸው ሲነሳ አብራ የምትነሳው ይህቺ ከተማ እንደሆነች ያስታውሳሉ።
ለእናታቸውም ሆነ ለአባታቸው ሲሠሩ የእርሳቸው አሻራ ቀላል እንዳልነበር ይናገራሉ። በተለይም ለእናታቸው የማይቆፍሩት ድንጋ አልነበረም። ለምሳሌ፡- ሥራ ማስለመዱ አንዱ ነው። ሥራ ወዳድንና በራሳቸው ጥረው ግረው እንዲኖሩ በብዙ መንገድ አስተምረዋቸዋል። እርሳቸው የተለያዩ ሥራዎችን ይከውኑ ነበርና በዚያ ውስጥ ደከመኝ ሰለቸኝን ሳያውቁ ትጉ ሰራተኛ እንዲሆኑም አስችለዋቸዋል። ለዚህም ነው ከቤት ውስጥ ጽዳት እስከ አረቄ ማውጣትና እንጀራ መጋገር የሚደርሱ ሥራዎችን የሚከውኑት።
እንግዳችን ጠጅ ቤት ስለነበራቸው ጠጅ የመጣሉን ተግባር በብዙ መልኩ ኃላፊነቱን ወስደው ያከናውናሉም። ጌሾ በመቀቀልማ ማንም አያክላቸውም። ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ የራሳቸውን ገቢ የሚያገኙበትን ሥራ ይሠራሉ። ለምሳሌ ከብት አደልቦ መሸጥ በዋናነት የሚያነሱት ነው። ዶሮም እንዲሁ እያረቡ ከተማ በመውጣት ይሸጣሉ። በቃ የንግዱ ዓለምን የተቀላቀሉት ገና ልጅነታቸው ላይ ሆነው ነው። በዚህ ሥራቸው ደግሞ ከቤተሰብ የሚያጋጫቸው ነገር ይፈጠር እንደነበር ያስታውሳሉ። አንዱና የማይረሱት ከአባታቸው ጋር የሆነውን ሲሆን፤ ከብት ሲያደልቡ ውሃ የሚያስቀምጡበት ሮቶ ይፈልጋሉ። አባታቸውን ግዛልኝ ቢሉትም ፈቃደኛ ሊሆንላቸው አልቻለም። በዚህም ራሳቸውን ለማጥፋት ጭምር ሞክረው እንደነበር ይናገራሉ። ነገር ግን ተሰቅሎ መሞት እንዴት እንደሚደረግ አያውቁምና አንገታቸው ላይ ገመዱን አድርገው ሲዟዟሩ የአካባቢው ሰው አግኝቷቸው የፈለጉትን አድርጎላቸው ሀሳቡን እንደተውት አይረሱትም።
አበበ ቢቂላ ትምህርት ቤት ፊደል ባይቆጥሩ ኖሮ ዛሬ ላይ ስማቸውን እንኳን መጻፍ እንደማይችሉ ያጫወቱን እንግዳችን፤ ቤተሰቦቻቸው ለእነርሱ እንዲያገለግሏቸው እንጂ እንዲማሩ አይፈቅዱላቸውም። የራሴን ሥራ ላከናውን፣ ልንቀሳቀስ ሲሉም ደስተኛ አይሆኑም። በዚህም ሁልጊዜ ይበሳጩባቸው ነበር። እንዲያውም የሚወዷትን ከተማና ቀያቸውን ትተው ወደ አዲስ አበባ የመግባታቸው ምስጢር ይህ እንደነበር ይገልጻሉ፡፡
በባህሪያቸው መጫወት የሚወዱ ግን ከነኳቸው የማይምሩ አይነት ልጅ ሲሆኑ፤ በተለይ ከጓደኞቻቸው ጋር በብዙ ነገር አይመሳሰሉም ነበር። አትንኩኝ ባይነታቸው የጎላና ሱሰኝነትን አጥብቀው የሚጠሉ ናቸው። ያገኙትን ለቤተሰቤ የሚሉና ለራሳቸው እንኳን አስፈቅደው የሚያደርጉም አይነት ልጅ እንደነበሩ ያስታውሳሉ። ጓደኞቻቸው ግን በተቃራኒው ከእናታቸው መቀነት ጭምር ሰርቀው የሚጠጡ ሲሆኑ፤ ከሁነቱ ጋር በተያያዘም እነርሱን ለመለየት ሲሉ እናታቸውን ትተው ወደአባታቸው ጋ ገጠር መውረዳቸውንም አይዘነጉትም። አባታቸው ጋ ከሄዱ በኋላም ቢሆን የፈለጉት ሆኖላቸው አያውቅም። ግን ሁሉንም በድል በመወጣታቸው ደስተኛ ናቸው።
ከቀን ሥራ ወደ ግል
የሥራ ጅማሮዋቸው ከእናታቸው ጋር ሆነው ከብቶችን በማደለብ የሠሩበት ሲሆን፤ ከዚያ አባታቸው ጋ በሄዱበት ወቅትም ቀጥለውታል። ለከብት ማደለቡ የተለየ ፍቅርም ነበራቸው። እንዲያውም ሲያደልቧቸው ብዙ መስዋእትነት ከፍለው እንደነበርም ያስታውሳሉ። ለአብነት ያወፍራቸዋል የሚባለውን ትንባሆ ጭምር ባፋቸው አኝከው በአፍንጫቸው እየሰጡ ይንከባከቧቸዋል። ይህ ደግሞ ራሳቸውን በተደጋጋሚ ስተው እንዲወድቁ አድርጓቸዋል። ግን ለሥራቸው ሲሉ ያደርጉት ስለነበር ምንም እንደማይሰማቸው አጫውተውናል።
አባታቸው ጋ ሳሉ ምቾት አልተሰማቸውምና ዳግም ወደእናታቸው ጋር እንዲመለሱ ሆነዋል። ሌላኛው የሥራ ምዕራፋቸው የጀመረውም እዚህ ላይ ነው። ይህም የቀደመውን ሥራቸውን ሳይሆን ተቀጥረው የሠሩበት ስጋ ቤት ጥብስ የመጥበስ ሥራ ነበር። በቀን ሰባት ብር እየተከፈላቸውም ለወራት ያህል ቆይተውበታል። የለቀቁትም አዲስ አበባ ገብቶ መሥራቱ የበለጠ ውጤታማ እንደሚያደርጋቸው አስበው ነው። በእርግጥ መነሻው ይህ ይሁን እንጂ በንዴት ጭምር ነበር ቦታውን ለመልቀቅ የወሰኑት። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ አባታቸው ናቸው። ሥጋ እየጠበሱ ያጠራቀሙትን ገንዘብ ለባለቤታቸው በአደራ መልክ እንድታስቀምጥላቸው መስጠታቸውን ሲያውቁ እንዳይሄዱባቸው ገንዘቡን እንዳትሰጣቸው አደረጉ። በዚህም አንድ ቀን የሠሩባትን ይዘው ህልማቸውን እውን አደረጉ።
አዲስ አበባን በ19 ዓመታቸው ነበር በሥራ የተቀላቀሏት። ለዚያውም ምንም ብር በሌላቸው ሁኔታ። በቀን ያገኙዋትን ሰባት ብር ይዘው የሦስት ሰዓት የእግር ጉዞው ተጉዘው በስድስት ብር ትራንስፖርት አዲስ አበባ ገብተዋልና የተረፈቻቸው አንድ ብር ናት። በዚህ ደግሞ አይደለም ምግብ ምንም ሊቀምሱ አይችሉም። በጉዞው ደግሞ በጣም ተርበዋል። ስለዚህም ወደ እህታቸው ጋ መሳፈራቸውን ትተው ግንድ ተደግፈው ሰዓታትን እንዲያሳልፉ ሆኑ። ‹‹ሳይደግስ አይጣላ›› እንዲሉ ሆነና አንድ በሰፈር የሚያውቋቸውን መምህር ድንገት ተመለከቱ። እርሳቸውም አይተዋቸው ኖሮ ለምን እንደመጡ ጠይቀዋቸው አምስት ብር ሰጧቸው። በዚያ ብርም ረሀባቸውን አስታገሱ። 25 ሳንቲም በምታስከፍለዋ ባስ ተሳፍረውም ወደ ቄራ እህታቸው ዘንድ አመሩ፡፡
የአዲስ አበባ ሕይወት በአዲስ መልኩ የተጀመረበት ቅጽበት የአምስት ብሯ ስጦታ እንደሆነ የሚያነሱት አቶ ተሾመ፤ እህታቸውን ሲያገኙዋት ሥራዋን አያውቁም ነበር። አዲስ አበባንም የሚያስቡት ሥራ እንደልብ፤ ገንዘብ እንደአፈር የሚታፈስበት አድርገው ነው። ግን የኋላኋላ ነገሮችን ተረዱ። የእህታቸውን ስቃይም ተመለከቱ። በተለይ ገላዋን ሸጣ እንደምታድር ሲያውቁ እጅግ አመማቸው። ምንም እንኳን ሥራን አስበው ቢመጡም በዚያ ፍጥነት እገባለሁ ብለው አልጠበቁም። ምክንያቱም አዲስ አበባን መልመድ ይኖርባቸዋል። ይሁን እንጂ የእህታቸው ነገር ግን አሳስቧቸዋልና የተቻላቸውን ወደ ማድረጉም ገቡ። የመጀመሪያ ሥራቸውንም ጽጌ ሆቴል ውስጥ አደረጉ።
ጽጌ ሆቴል ውስጥ ሲገቡ በቀን ሠራተኝነትና በጥበቃ አገልግሎት ሲሆን፤ ጎን ለጎን የእህታቸውን ልብስ በማጠብ፤ ልጆቿን በመንከባከብ፤ እንጀራ በመጋገርና ወጥ በመሥራት ዋና ተግባራቸው አድርገው ያግዛሉ። በዚህ ደግሞ ደስተኛ ነበሩ። ምክንያቱም እህታቸው ከቆየችበት ስቃይ መጥታ ሌላ ጭንቀት ውስጥ እንዳትገባ አይፈልጉም። በመሆኑም በዚህ እረፍት ይሰጧታል።
የእህታቸው ሥራ የእርሳቸው ትምህርት ቤት እንደነበር የሚያነሱት እንግዳችን፤ ስቃዩዋ በብርታቷ መፍትሄ ያገኝ ነበር። ፊቷን ሳታጠቁር ልጆቿንም ሆነ እኔን ትመግብ ነበር። ከሁሉም በላይ ደግሞ ሌላ አማራጮችን ማየት እንደሚያስፈልግ ለብዙ ሰዎች መካሪ በመሆኗ ብዙዎች ተለውጠውባታልና እኔንም አንቅቶኛል። ምንም አይነት ሥራ ብሰራ ብርታትና እንደምለወጥ እንዳምን የረዳችኝ እርሷ ነች ይላሉ። ሁለቱን ልጆቿን ትታባቸው ስታልፍ ሁሉ ነገር ያልጨለመባቸውም በዚህ ምክንያት እንደነበር ያስታውሳሉ።
በከፋ ሕይወት ውስጥ ቢሆኑም እናታቸውን ያረሱት አቶ ተሾመ፤ እርሷ የሰጠቻቸው ጥንካሬ ከአዲስ አበባ ወደእናታቸው ጋ ሲሄዱ እረፍት ሳያደርጉ በብዙ መንገድ እንዲያግዟቸው ሆነዋል። ከግቢ ጽዳት ጀምሮ በተለመደው ሥራቸው ይደግፏቸዋል። እናታቸው ግን በተቃራኒው ሆነውባቸው እንደነበር ይናገራሉ። በከፋቸው ጊዜ አልደረሱላቸውም። በጣም የቆረጠላቸው ደግሞ የወደዷትንና ከችግራቸው ያላቀቀቻቸውን ባለቤታቸውን ሊወዱላቸው አለመቻላቸው ነው። ይባስ ብለውም ከባለቤታቸው ጋር ተለያይተው ዓመት ከሦስት ወር ሲቆዩ አይዞህ እንኳን አላሏቸውም። ለምን ተለየሃትም ብለዋቸው አያውቁም። እናም በእርሳቸው ምትክ ባለቤታቸውን እንዲያኖሩ ሆኑ።
‹‹ሰው በቁሙ ካልተደጋገፈ ከሞተ በኋላ መውረስ ጥቅም የለውም›› የሚል እምነት ያላቸው አቶ ተሾመ፤ አባታቸው በፈለጓቸው ጊዜ ስላልደረሱላቸው የእርሳቸውን ገንዘብ አልፈለጉም። ለዚህም ማሳያው ሲያርፉ የንብረታቸው ተካፋይ አለመሆናቸው ነው። ልውረስ ቢሉ የቀንድ ከብት ብቻ 37 ነበራቸው። ሌሎቹን ከብቶች ሳይጨምር። መሬቱም በጋሻ ነው። ውርሱም ከፍተኛው ድርሻ የእርሳቸው ነው። ሆኖም አልተቀበሏቸውም። እንዲያውም ስሙን አስጠሩበት ብለው ትተውላቸዋል። በዚህ ደግሞ ደስተኛ ናቸው። ምክንያቱም ለልጆቻቸው መጀመሪያ መስጠት ያለባቸው አባትነታቸውን እንደሆነ ያምናሉ። በላቤ የሠራሁትን በፍቅር ስሰጣቸው ይባረክላቸዋልም ብለው ያስባሉ።
በውርስ ሳይሆን በሥራ መለወጥ እንደሚያረካም እምነት ያላቸው ባለታሪካችን፤ ጽጌ ሆቴል ውስጥ እያሉ የቄራ ሥራን እንዲጀምሩ ሆነዋል። የማረድን ሥራ ያስጀመራቸው ግን ማረሚያ ቤት እንደነበር ያነሳሉ። ይህም በ1983 ዓ.ም ኢህአዴግ ሲገባ በማያውቁት ነገር ታስረው ነው። ታማኝ እስረኛ ሆነው ለዓመታት ሲቆዩም ሥራውን ወደውት የእስር ጊዜያቸውን እስከመርሳት ደርሰውበታል። ይህ ደግሞ መጥፎውንም ጥሩውንም አሳይቷቸዋል። ጥሩ ብለው የሚጠቅሱት የዛሬ እንጀራቸውን የከፈተላቸውን ከብት የማረድ ሥራ ሲሆን፤ በተመሳሳይ በሁሉም የሥራ መስክ አቅማቸውን ያጎለበቱበት ነው። ከሁሉም በላይ ግን ምንም እንኳን ትንሽ ቢሆኑም ከብት በማረድ ጥበብ የተካኑበት መቼም የማይረሳቸው ነው።
ሙያቸውን ይዘው አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ የሆቴሉን ሥራ ሳይለቁ ጎን ለጎን አቻችለው በሦስት ብር ከ50 ሳንቲም አምስት ዓመታትን በጊዜያዊነት አገልግለዋል። ሴፍትኔት ውስጥ ሲገቡ እንኳን በሆቴሉ ያለውን ሥራ ለቀቁ እንጂ የቄራውን ሥራቸውን አላቋረጡትም። ሴፍትኔቱ ሁለት ዓመት ሞልቶት ሲቋረጥ ቋሚነቱ ተሰጥቷቸው ነበርና ከሥራው ጋር ውህደትን ፈጥረው ወደውትም እንዲቆዩ እድል ሰጥቷቸዋል። ከዚያ በቋሚነት 14 ዓመት እንዲሰሩ ሆነዋል። በቀን 52 በሬ አርደው እንደሚያውቁና ለረጅም ጊዜ ሪከርዱን እንደያዙ ያስታውሳሉም። በዚህ ደግሞ ሁልጊዜ ተሸላሚና ጥቅማጥቅም ቀድሞ አግኚ ነበሩ።
በጥሩ ስነምግባርና ታማኝነት ማገልገልና ሥራ ላይ ሁሌ ቆራጥ መሆን ብዙ ነገርን በራስ ላይ ይለውጣል የሚሉት ባለታሪካችን፤ ተቋሙም ሆነ ሰራተኛው እንዲመርጧቸው፤ እንዲደሰቱባቸው፤ ለእርሳቸው
የደስታ ምንጭ ከመሆን አልፎ ቤታቸው ሙሉ እንዲሆንላቸው የሆነው በእነዚህ ነገሮች እንደሆነ ያስረዳሉ። ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ጭምር በመግባት የከብት አራጅነቱን ተግባር እየከወኑ ለዓመት ከዘጠኝ ወር ያህል ሲቆዩ ሁሉም የሚንሰፈሰፍላቸው በምንም ምክንያት ሳይሆን በባህሪያቸው እንደሆነ ይገልጻሉ። እናም የሥራ ምንጩ ራስን አሸንፎ ሌሎችን ማክበር ነውና ሰዎች ይህንን እንዲያደርጉ ይመክራሉ።
እንግዳችን አሁንም በዚያው በቄራ ቦታውን ሳይለቁ ከተቀጣሪነት ወጥተው በግላቸው እየሠሩ ይገኛሉ። ግን ከሁለት ዓመት በፊት አንድ ነገር እርሳቸውንም ሆነ ቤተሰቡን ደስተኛ አያደርጋቸውም። በጣም ይረብሻቸውም ነበር። ይህም ሱሰኝነታቸው ሲሆን፤ ቤተሰባቸውን ጭምር የበጠበጠ እንደነበር አይረሱትም። እንደውም ስለዚህ ባህሪያቸው ሲያነሱ ‹‹እኔ ሳልሆን ሱሱ መጥፎ ነበረ›› ይላሉ። ምክንያቱም በባለቤታቸውና በእርሳቸው ቆራጥነት ሱሱን ሲያቆሙ ሁሉም ነገር ተለውጦላቸዋል። ሙሉ ሆነዋልም። ከዚያም በላይ ሌሎችን የሚያዩና የሥራ እድል ፈጣሪ አድርጓቸዋል። አሁን በሥራቸው ከስድስት በላይ ሰራተኞችን ቀጥረው እንዲያስተዳድሩ የሆኑት በዚህ ምክንያት ነው።
ራስን የማከም ምስጢር
‹‹ሱስ በሰዎች ላይ አካላዊና ስነልቦናዊ የጥገኝነት ስሜት በመፍጠር ለመነቃቃት፤ ድብርትን ለማስወገድ፤ ጀብዱ ለመስራት ፤ ህመምን ለማስታገስ፤ ከፍተኛ የሆነ የደስታ ስሜትን ለመጎናጸፍ ተብሎ እያጨሱ፣ እየሳቡ፤ እየቃሙና በደም ስራቸው እየወሰዱ የሚለምዱት ነው። በተለይ የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴን ለመምራት ወሳኝ ሆኖ የሚታያቸው ብዙ ናቸው። ይህ ደግሞ ሳይታሰብ የሚተገበር ግን በቀላሉ ለመውጣት የምንቸገርበት ነው። እኔም የሆንኩት እንዲህ ነበር›› የሚሉት ባለታሪካችን፤ ማረሚያ ቤት ሳሉ ብርዱን ለመቋቋም በሚል ነበር የጀመሩት። ሰዎችን ማየታቸውና ከሰዎቹ ጋር መላመዳቸው እንዲሁ ተግባሩን አስተምሯቸዋል። የቄራ ሥራ ደግሞ ሌሊት የሚከወን በመሆኑ ሙቀት ይፈልጋልና እንዲያደርጉትም ተገደዋል፡፡
ከማረሚያ ቤት ከወጡ በኋላም ቢሆን ማቆም ያልቻሉት ከማረዱ አልፈው በየስጋ ቤቱ ስጋ ተሸክመው በማድረሳቸው ምክንያት ከሥጋው የሚመጣው ቅዝቃዜ ከአየሩ ጋር ተዳምሮ ውስጣቸውን እረፍት ይነሳዋል። ስለዚህም በአገኙት አረቄ ቤት መግባት ግድ ይሆንባቸዋል። አለያም ሲጋራ ማጨስን ምርጫ እንዲያደርጉ ያስገድዳቸዋል። ጫቱ ደግሞ ለእንቅልፍ መድኃኒት ነው በሚል የሚወስዱት ነው። ስለዚህም በእነዚህ ምክንያቶች ሱሰኝነቱ በላያቸው ላይ እንዲነግስ ፈቅደዋል። ይህ ደግሞ ብዙ ነገራቸውን የነጠቃቸው እንደነበር ያነሳሉ። ዛሬ ድረስ የሚጸጸቱበትን ነገር ፈጥሮባቸዋል። በተለይ ጊዜና የሥራ አቅማቸውን መንጠቁ በጣም ያበሳጫቸዋል።
ሱስ እያደገ ሲሄድ በርካታ ችግሮችን እንደሚፈጥርባቸው በሕይወታቸው አይተዋል። ከደነዘዙ በኋላ ለመሞት ደቂቃ ብቻ እንደሚበቃም ያውቁታል። በዚህም ሱስ ቤታቸው ውስጥ ምንም እንዳይጎል በገንዘብ ቢደጉሙም ማንም የሚያመሰግናቸው ግን አልነበረም። በዚያ ላይ የማስታወስ ችግር፣ ተስፋ መቁረጥ፤ ራስን መቆጣጠር እንዳይችሉ ሆነው ዓመታትን እንዲኖሩበት አድርጓቸዋል። በተለይም እቃ መሰባበርና ቤተሰብን መጨቃጨቁማ አይነሳ። በተደጋጋሚ ወድቀው ባለቤታቸው ጠዋት የምታነሳቸውም እንዲሁ እጅግ አማራሪ ነበር። በዚህም ይህንን ባህሪዬን አይመልስብኝ ሲሉ ዘወትር ይጸልያሉ።
‹‹ሙሉ ለቤት የሚሆኑ ነገሮችን ገዛዝቼ ወደቤት ባመራም ሰክሬ ነው። ተቀብለውኝ ከገባሁ በኋላ ደግሞ እቀየርባቸውና እነርሱን ከመነጀስ አልፌ ኤሌክትሪክ ገመድ ሳይቀር በጣጥሼ አድራለሁ። በዚህም ይገለናል ብለው ስለሚሰጉም ጎረቤት የሚያድሩበት ጊዜ ጥቂት አልነበረም። ጠዋት ሲነጋ ግን የተለየ ሰው እሆናለሁ። የተሰበረውን እና ይዤ የመጣሁትን እቃ እያየሁ እጸጸታለሁ። ማንንም የማናገርም ሆነ የማየት ወኔ አልነበረኝም። ለራሴ ከዚህ በኋላ አላደርገውም ብዬ ምዬ ተገዝቼም አውቃለሁ። ግን ሲመሽ ሌላ ነኝ። ሁለትቀን እንኳን መቆየት አልችልም። እናም የሱስን ጠላትነት ዘርዝሬ ልጨርሰው አልችልምና አይድገምብኝ፤ ለማንም አይስጠውም ከማለት ውጪ የምለው የለኝም›› የሚሉት እንግዳችን፤ ቆም ብሎ ማሰብና የኑሮን ሁኔታ ማሰላሰል እንዲሁም ተደጋጋሚ የሆነ የራስን ወቀሳ መስማት ከችግር ሁሉ ያወጣል። በተለይም ከሱስ ለመውጣት አካባቢን መመልከትና ማንነት ማስታወስ ተገቢ እንደሆነ ያስገነዝባሉ።
አሁን ከልጅና ባለቤታቸው ጋር በፍቅርና በደስታ የማሳለፋቸው ምስጢር፤ ሙሉ ሰው እንደሆኑ የመሰማቱ ሁኔታ የመጣው፤ የልጃቸው ጓደኞች ሳይቀሩ አባታችን የሚሏቸው፤ ጎረቤቶችም እንዲሁ እርሱ ካለ ችግር እንደማይኖር የሚናገሩላቸው የሆኑት ከምንም የመነጨ አይደለም። እራስን ከመመልከት የመጣ ነው እንጂ። ለመለወጥ መጀመሪያ የግለሰቡ ቁርጠኝነት ከምንም በላይ ያስፈልጋል። ከዚያ በተጓዳኝ አጋዥ ሰው ሊኖር ይገባል። ስለዚህም እንደ ባለቤታቸው አዲስ ሰው ሰሪ ካለና ሱስን ለመተው መወሰን ከተቻለ የማይናድ ተራራ የለም ይላሉ።
መጀመሪያ የቀደመውን ማንነትና የአሁኑን አወዳድሮ መመልከት ይገባል። የትኛው የተሻለ እንደሆነም ውሳኔን ይጠይቃል። ከብዙ ነገር ያራቀንን ልምድ ለመተው የገባንበትን ሁኔታ ማወቅ ይኖርብናል። በዚህም ነው የትናንቱን ትቼ የዛሬውን የተቀበልኩት። ይህ ደግሞ ብዙ ነገሮቼን ገንብቶልኛል፤ መልካም መንገዶቼንም አብርቶልኛል። በመቀበል ውስጥ ያለውን እውነት እንድረዳውም አድርጎኛል። ምክንያቱም በመቀበል ውስጥ መኖር አለ፤ በመቀበል ውስጥ ተስፋና የተሻለ እድልን መገንባት ይቻላል። በመቀበል ውስጥ ከተጣሉት ጋር መታረቅም ቀላል ነው። በመቀበል ውስጥ መኖር አዲስ ማንነትን ለመላበስም ያስችላል። ኑሮን ማደላደልና ደስተኛ ለመሆንም ያግዛል። ይህንን ሁሉ አይቼበታለሁና ሰዎችም አዲስ ለመሆን ሲያልሙ በተለይ ሱስ ውስጥ ያሉ መጀመሪያ የመቀበልንና የመወሰንን ትርጓሜ ይረዱ። ከዚያ አይሆንም የሚላቸው የለም፤ ሁሉን ነገር አሸንፈው በደስታ ፈረስ እንደሚጋልቡ ይመክራሉ።
ሌላው ከሱስ ጋር በተያያዘ ያነሱት ነገር ራሳቸውን የለወጡበትን ገጠመኛቸውን ሲሆን፤ ‹‹ አንድ ቀን የሆነው ነገር አዕምሮዬንም እኔንም መልሶኛል›› ይላሉም። ይህ ክስተትም አንድ አረቄ ቤት ገብተው 600 ብር የከፈሉበት ጊዜ ነው። ለዚያውም መለኪያው 75 ሳንቲም በነበረበት ወቅት። እናም ምን ያህል እንደጠጡና ራሳቸውን እንደሳቱ በዚያን ቀን አይተውታል። ጠዋት ተነስተው ጭምር ያልባቸው እንደነበረም አይረሱትም። ምንም ቢያደርጉ ራሳቸውን ማከም ተስኗቸው እንደነበረም ሁሌም ያስታውሱታል። ለመተው ቦታ ቀይረው ጭምር ይጠጡ እንደነበርም አይረሱትም። ነገር ግን በሂደት ጉዳቱ ሲበረታባቸው፤ እንጀራቸውን ሊነጥቃቸውና ቤተሰባቸውን ሊያጡ እንደሆነ ሲሰማቸው ነገሮች ላይ ቁርጠኛ ሆው ገቡበት። የዛሬ ሕይወታቸውንም አገኙበት።
የሕይወት ፍልስፍና
ሥራን ሥራ ከሚያደርገው አንዱ ነገር ታማኝነት ነው። በምግባር መስራትም ለበለጠ ነገር ያሳጫል የሚል አቋም አላቸው። በተጨማሪም ሥራ ክብርን ያቀዳጃል፤ ማንነትን ያንጻል። ከምንም በላይ ሰውኛ ባህሪን ያላብሳልም ብለው ያምናሉ። ምክንያታቸውን ሲጠቁሙም በሚሰሩበት ሁሉ ትርፋማ መሆናቸውን በማንሳት ነው። የከብት አራጅ ቢሆኑም አንድም ቀን በገንዘብ ተቸግረው አያውቁም፤ የቀን ሰራተኛ ሆነውም እንዲሁ። ለዚህ ደግሞ በስነምግባር ውስጥ ታማኝነትን አካተው መስራታቸው የሰጣቸው እንደሆነ ይናገራሉ።
‹‹መራራን ካልበሉ ጣፋጭ አይመጣም›› መርሃቸው የሆነው ባለታሪካችን፤ ሰዎች ችግርን በተለያየ መልኩ ማየት አለባቸው ባይ ናቸው። ምክንያቱም ክብርና መፍትሄን ከዚያ መከራ ውስጥ ያገኛሉ። ሰርቶ መለወጥንም ይማራሉ። ከሁሉም በላይ ስለሰው ልጅ ማሰብን ያውቃሉ። ለሌላም መራራት የሚመጣው ይሄ ጊዜ ሲታይ ብቻ ነው። ጊዜው ወደኋላ ይመልሰናልና ከዚያ ችግር የሚወጡበትን መንገድ እናፈላልጋለን። እናም ሁሌም የመከራን ጊዜ ማሰብና መቅመስ ተገቢ ነው ብለው ያስባሉ።
ማንኛውም አለቃ አለቅነቱን ማሳየት ያለበት በባህሪም በተግባርም ነው የሚለው ሌላው ፍልስፍናቸው ነው። ከላይ ያለውን ሳይሆን ታችኛውን እያዩ መሥራት ተገቢም ነው። ይህ ሲሆን ደግሞ የበለጠ ከፍ ለማለት እንጂ ወደታች ለመውረድ አይደለም። የራስን ሥራ አድምቶ መከወን ከምንም በላይ አስፈላጊ ነው። የዛን ጊዜ ማሸነፍም ማየልም ይመጣል። ካልተደረገልኝ አላደርግም የሚል አስተሳሰብም ይወገዳል። ሰውን በሰውነቱ ማክበር ይጀመራል የሚል እምነትም አላቸው።
ሌላው የህይወት መርሃቸው ሀዘን ደጋግመን የምናየው እንዲያልፍ ለመስራት ዝግጁ አለመሆናችንና የሚያልፍ ስለማይመስለንም ነው የሚለው ነው። ችግርን አልፎ ለማየት ጊዜውን ቀና አድርጎ ጎንበስ ብሎ ማሳለፍ ይገባል ብለው ያምናሉ። በዚያ ውስጥ ደግሞ መገንባት፤ መጠንከርና መማር የሚባሉት ነገሮች ተደራርበው ይፈጠራሉ። ለሕይወታችንም የማይናድ አለት ይሆናሉ የሚል አቋም አላቸው።
መልእክት
የኢትዮጵያ ችግር እኛ ነን። ምክንያቱም ጆሯችን ሁልጊዜ የሚፈልገው ተቃራኒ የሆነውን እንጂ መልካሙን አይደለም። ኮሽታና ጸብ መርጠን ከመስማት አልፈን እንተገብረዋለን፤ አስተላላፊ ጭምር እንሆናለን። ጭላንጭሉ ስህተታችን እንዲጎላ የማንቦረቡረው ድንጋይ የለም። ይህ ደግሞ መለያየት ውስጥ እንድንገባ አድርጎናል። በብሔር የማሰባችንን ሁኔታም አስፍቶብናል። በቀላሉ ከችግር ለመውጣት ያልቻልነውም ለዚህ ነው። ባህልና ወጋችንን የረሳነውም ይህ ስለገነነብን ነው። እናም ዛሬ ልቦናችንን መለስ አድርገን ልናይ ይገባናል ምክራቸው ነው።
ሌላው ያነሱት ነገር ኢትዮጵያዊያን ባህላቸውን
ዘርዘር አድርገው ቢመለከቱትና ያላቸውን ማየት ቢጀምሩ ብዙ ዳይመንድ እንዳላቸው፤ ዘላለም የሚያቆማቸውም ማዕድን ባለቤት እንደሆኑ፤ እስከዛሬ ያቆሙን ነገሮች እነዚህ እንደነበሩ ያስረዱበት ነው። ነገር ግን ብልጫውን ለሌሎቹ ሰጥተን ስላለን ኑሯችን ሌሎችን ሆኗል። ለዚያውም ገና ዳዴ እያሉ ያሉ አገራት። ስለሆነም ጊዜው አሁን ነው እኛነታችንን መፈለግ አለብን ይላሉ። አሁን እየደረሰብን ያለው መከራና ፈተና ከምንም የመጣ ሳይሆን ራስን ካለመመርመርና ካለመጠቀም የመጣ መሆኑን መገንዘብ እንዳለብን ይመክራሉ።
አሁን ባለው ሁኔታ ኢትዮጵያውያን በሁሉም መልክ አሻራቸውን የሚያሳርፉበት ወቅት ነው። ተከላካይ መሆን አለባቸው፤ መከታነታቸውን ማረጋገጥም ይጠበቅባቸዋል። ግን ይህ ሲሆን በጦር ሜዳ ብቻ ሳይሆን በተሰማሩበት ሙያ ሁሉ መሆን ይገባዋል። ትንሽ ነው የምንለው ሊኖር አይገባም። ምክንያቱም ትንሿ ትልቅ ትሆናለችና። ለምሳሌ፡- አንድ ሰው በተጠቀመው ነገር ሁሉ ሪሲት ማስቆረጥ ቢጀምር ለአገር ገቢ ያመነጫል። ከዚያም አልፎ ለራሱ ኑሮ መደጎምም ይችላል። ምክንያቱም በዚህ ሁኔታ የኑሮ ውድነቱን ይቀንስበታል። መንግሥት የሚሰራውን ሥራም ያሰፋል። ስለዚህም የምናደርገውን ነገር ሳንንቅ ለአገራችን ሲባል ጠጠር መወርወርን መጀመር አለብን ሲሉ ይመክራሉ።
በቀልም ሆነ ጥላቻ ለማንኛውም ሰው የሚበጅ አይደለም። ምክንያቱም ሁልጊዜ አሳምሞ በሽተኛ ያደርጋል። በየቀኑ የሚገል ጥይትም ነው። ራስን የማታለልና ሰላምን ያለመፈለግ መንገድም ነው። ምክንያቱም ክፉ ያደረገብንን በክፉ ለመመለስ እንቅልፍ አንተኛም፤ አንበላም አንጠጣምም። ከሰዎች ጋር ጭምር ተግባብቶ ለመቆየት ይሳነናል። እናም ሰላም አደፍራሺ እንጂ አምጪ አንሆንም። እናም እየደረሰብን ያለው ሀዘን መራር ቢሆንም ይቅርታና ሰላም እንዲሁም ደስታ ስለሚገባን በቀለኛ መሆንን መተው ይገባናል። ምክንያቱም እነርሱን መግደል እረፍት መስጠት ነው፤ ለራስም ጸጸት ማምጣት ነው፤ ማንነትንም ማስወሰድ ነው። ስለሆነም ሥራቸው ለማንም የሚገባ አይደለምና ቅጣታቸውን ቆመው በአደረጉት ነገር እየተሰቃዩ እንዲከፍሉት እናድርጋቸው በማለትም መልእክታቸውን ያስተላልፋሉ።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን የካቲት 13/2014