ለ ስፖርቱ ዕድገት ሳይንሳዊ መሰረቱን በያዘ መልኩ ታዳጊዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ስልጠና መስጠት ዋነኛ መፍትሔ መሆኑ በዘርፍ ሊቃውንት ይነገራል። በተለይ በእግር ኳሱ ውጤታማ መሆን የቻሉ አገራት በዚሁ መስመር በመጓዝ የታዳጊና ወጣት ስፖርት ማዕከል ፕሮጀክቶችን እንደ ዋነኛ መፍትሔ በመጠቀም ሠርተውበታል። ፍሬያማ መሆንም ችለዋል። ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ይሄንን መሰረት በማድረግ ፤ «የአምቦ የእግር ኳስ ማሰልጠኛ ማዕከል ጎል ፊፋ» በሚል ስያሜ ለመገንባት በ1999 ዓ.ም የመሰረት ድንጋይ በአምቦ ከተማ አስቀምጠዋል። ማዕከሉ ለሀገሪቱ የእግር ኳስ መጻኢ ጉዞ ውጤታማነት ጉልህ ሚና እንደሚኖረውም ትልቅ ተስፋ ተጥሎበታል። ማዕከሉ እንደተባለው ተገንብቶ ለሀገሪቱ እግር ኳስ ግብዐት የሚሆኑ ታዳጊዎች መልምሎ የማሰልጠን ፕሮጀክቱ የት እንደገባ ሳይታወቅ ቀረ።
የማዕከሉ ግንባታ ከዛሬ ነገ ይጀመራል ቢባልም ሳይጀመር ቀረ፡፡ ለማዕከሉ ከፊፋ የተለገሰው ገንዘብ የት እንዳረፈ የሚናገር ጠፋ። ለማዕከሉ ግንባታ የተዘጋጀው 12 ሄክታር መሬት በተለያዩ የማሰልጠኛ ሜዳዎች ፣ ሳይንሳዊ ስልጠናን የሚሰጥባቸው ማዕከላት ፣ የሰልጣኞች ማደሪያ ፣ መማሪያ ፣ የመዋኛ ገንዳ፤ ለመገንባት የቀረበውን ንድፈ ሃሳብ ከወረቀት ወደ መሬት ለማውረድ ተዘጋጅቷል። ለዚህ ተግባር የተሰናዳው መሬት ሙጃና አረም እንጂ የተባለው ሳይሆን ቀረ። ለማዕከሉ ግንባታ ከፊፋ የተለገሰው ዶላርም ወዴት እንደዋለ አየሁም ሰማሁም የሚል ጠፍቶ «የውሾን ነገር…» በሚለው ተከድኖ ለመቆየት አስገደደ። ዓመታት ከተጓዘ በኋላ የአምቦ ከተማ ህዝብም ሆነ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት የስልጠና ማዕከሉን “ወይ ገነቡልን አልያም እኛ እንገንባው” የሚል ጥያቄን በብርቱ ጠየቁ። ከብዙ ንትርክ በኋላም በክልሉ ሙሉ ወጪ ተገንብቶ በ2006 ዓ.ም ወደ ሥራ ገባ።
የአምቦ ጎል ፊፋ የእግር ኳስ ማዕከል በምን መልኩ እየተጓዘ ይገኛል? በስልጠናው ሂደት ውስጥ ያሉት ተስፋ ሰጪ ነገሮች ፤ በማዕከሉ ሳንካዎችና በሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ስፖርት ዝግጅት ክፍል ከአምቦ ጎል ፊፋ እግር ኳስ ማሰልጠኛ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሊሳ ለሜሳ ጋር ቆይታ አድርጓል። መልካም ንባብ። አዲስ ዘመን ፦ የአምቦ ጎል ፊፋ እግር ኳስ ማሰልጠኛ ማዕከል መቼና እንዴት ነበር የተቋቋመው? አቶ ሙሊሳ፦ የአምቦ ጎል ፊፋ እግር ኳስ ማሰልጠኛ ማዕከል በሀገሪቱ ያለውን የእግር ኳስ ችግር ለመቅረፍ ለታዳጊዎች ሳይንሳዊና ዘመናዊ ስልጠና በመስጠት በብዛት በጥራት እና በዲሲፕሊን የታነጹ የእግር ኳስ ስፖርተኞችን ለማፍራት በማለም በ1999 ዓ.ም የተመሰረተ ነው።
በዚሁ ጊዜም በፊፋና ብሄራዊ ፌዴሬሽኑ ትብብር በቀድሞ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት አቶ አባዱላ ገመዳ የመሰረት ድንጋይ ተጣለ። የማዕከሉን ግንባታ ወጪ ዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማህበር በጀት መመደቡ ተገልጿል። የማሰልጠኛ ማዕከሉ ግንባታም ከአንድ ዓመት በኋላ ተጀመረ። ግንባታው ይጀመር እንጂ ካለበት ሳይነቃነቅ ሶስት ዓመታት ተቆጠሩ። ማዕከሉ ይጠናቀቃል ተብሎ በተያዘለት ጊዜ ለመጠናቀቅ ይቅርና ሊገነባ የተቀመጠው ንድፈ ሃሳብ መሰረት ተደርጎ የመተግበሩ ሁኔታ ራሱ ጥያቄ ውስጥ መግባት ጀመረ። የማዕከሉን ግንባታ በኃላፊነት የተረከበው አካል በአግባቡ መስራት ስላልቻለ ክልሉ ራሱ ለማሰራት ጥያቄ ለማቅረብ ተገደደ። የህዝቡም ጥያቄ በተመሳሳይ ሁኔታ እንዲንጸባረቅ ሆኗል። ይሄንኑ ተከትሎ ከብዙ ውዝግብ በኋላ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ተረከበው። ክልሉ በራሱ በጀት ግንባታውን ያከናወነ ሲሆን፤ ሰው ሰራሽ የማሰልጠኛ ሜዳውን ደግሞ ፊፋ በራሱ ወጪ በማሰራት ግንባታው በ2002 ዓ.ም ተጠናቀቀ።
አዲስ ዘመን ፦የማዕከሉ ግንባታ ሂደት በዚህ መልክ ከተጠናቀቀ በኋላ ወደ ስራ የገባበት ሁኔታን እንዴት ያስታውሱታል ?
አቶ ሙሊሳ፦የስልጠና ማዕከሉ ግንባታው ከተጠናቀቀ በኋላ በፍጥነት አገልግሎት መስጠት አልጀመረም። ከጅምሩ የነበሩ ልክ ያልሆኑ አካሄዶች እንደነበሩ ሁሉ፤ ወደ አገልግሎት ለመግባትም ተመሳሳይ ችግሮች አጋጥመው ነበር። ይሁን እንጂ በ2005 ዓ.ም ክልሉ በመወሰኑ ስራ ጀመረ። ማዕከሉ ባለው መሰረተ ልማት፣ የማሰልጠን አቅም ስራ ሊጀምር ይገባል ተባለ። የሰራተኞች ቅጥር መፈጸም፣ ለሰልጣኞች የሚያስፈልገውን ቁሳቁስ ማሟላትና ሌሎች ተግባራትን ማከናወን ተቻለ። በተጨማሪም ወደማዕከሉ የሚገቡትን ሰልጣኞች ምልመላ አከናውኗል። በዚህም፤ በ2005 ዓ.ም በሀምሌ ወር በኦሮሚያ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አዘጋጅነት በሻሸመኔ ከተማ ለተካሄደው ውድድር ከ17 ዓመት በታች እድሜ ያላቸው ሰልጣኞች ተመለመሉ። የተመለመሉትም ልጆች 27 ወንዶች እና 22 ሴቶች ናቸው። በ2006ም ዓ.ም እነዚህኑ ታዳጊዎች በማዕከሉ በማቀፍ ስልጠና ጀምሯል። ሂደቱ ይሄን ይመስል ነበር።
አዲስ ዘመን ፦ማዕከሉ ከተከፈተበት ግዙፍ አላማ አኳያ ያለፉት ዓመታት እንቅስቃሴው ምን መልክ አለው?
አቶ ሙሊሳ፦ ማሰልጠኛ ማዕከሉ ሳይንሳዊና ዘመናዊ ስልጠና በመስጠት በብዛት፣ በጥራት እና በዲሲፕሊን የታነጹ የእግር ኳስ ስፖርተኞችን ማፍራት ዓላማው አድርጎ ነው የተነሳው፤ ከዚህ አኳያ ባለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት ቆይታው ጅምሩ ተስፋ ሰጪ እንደሆነ ይታመናል። ለዚህ ደግሞ ማዕከሉ አቅሙን ባገናዘበ መልኩ ስልጠና ይሰጣል። ይሄንኑ ለማብራራት ያክል፤ ማዕከሉ ለሰልጣኞቹ ሳይንስን መሰረት ያደረገ የተግባርና የንድፈ ሃሳብ ስልጠና ይሰጣል። በሳምንት አራት ቀናት የሁለት ሰዓት የተግባር ስልጠና ይሰጣል። ሰልጣኞች በማዕከሉ በሚኖራቸው የአራት ዓመታት ቆይታ ይሄንኑ መንገድ በመከተል ያላቸውን ተፈጥሯዊ ችሎታ በሳይንሳዊ ስልጠና እንዲያጎለብቱት ይደረጋል። በዚህ ሂደት ውስጥ ከአመጋገብ፣ ከአካላዊ እንቅስቃሴ፣ ቴክኒካልና ታክቲካል በሆኑና ስፖርቱን በሚያግዙ ተያያዥ ጉዳዮች ላይ መሰረታዊ እገዛ መስጠትንም ታሳቢ በማድረግ ጭምር ነው። በተጨማሪም፤ በስልጠናው ምን ያህል ክህሎታቸውን አዳብረዋል? ምን ያህል ራሳቸውን ለውጠዋል? የሚለውም አብሮ በተግባር ይታያል።
የወዳጅነት ጨዋታዎችን በማድረግ፣ በክልልና በሱፐር ሊግ የውድድር መድረኮች በማሳተፍ ራሳቸውን በሚገባ እንዲፈትሹ ይደረጋል። ይህ ደግሞ የስልጠናው ሂደት በሚገባ እየተፈተሸና እየተመዘነ እንዲጓዝ ይረዳል። ይሄም ሰልጣኞቻችንን በሚገባ ረድቷቸውና አግዟቸው የተመለከትን ሲሆን፤ ሰልጣኝ የነበሩ ታዳጊዎቻችን ለዚህ ምስክር ይሆናሉ። ማዕከሉ ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ በመጀመሪያ ዙር ከ17 ዓመት በታች 27 ወንዶች እና 22 ሴቶችን ለሁለት ዓመት በማሰልጠን በድምሩ 49 ሰልጣኞችን በ2008 ዓ.ም. አስመርቋል። በዚህም የመጀመሪያ የውጤቱን ፍሬ ተመልክቷል። ከማዕከሉ የተመረቁት ሰልጣኞችም ተፈላጊ ናቸው።
ሰልጣኞቹ በተለያዩ ክለቦች በመፈረም የመጫወታቸው ስኬት በቀጣይ ለሚሰራው ስራ ሞራል የገነባና ማሻሻል የሚገባውን ጉዳይም እንዲመለከት ያስቻለው ነበር። ማዕከሉ በዚህ ራሱን ተመልክቶና ማሻሻያዎች አድርጎ በአሁኑ ወቅት የወቅቱን ዘመናዊ የስፖርት ሳይንስ ያማከለ ካሪኩለም አስቀርጾ 15 እና 17 ዓመት የሆናቸውን 30 ወንዶች እና 24 ሴቶች በድምሩ 54 ልጆች እያሰለጠነ ይገኛሉ። ስልጠናቸውን ከአንድ ዓመት በኋላ የሚያጠናቅቁት እነዚህ ሰልጣኞችም ሲመረቁ በመጀመሪያ ዙር እንደነበረው ሁሉ በክለብ፣ ብሎም በብሄራዊ ቡድን ደረጃ እስከ መመረጥ ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል። ስለዚህ በቀጣይ የሚመረቁ ተጫዋቾች በዚህ ሂደት ውስጥ ያልፋሉ የሚል እምነት በመያዝ እየተሰራ ይገኛል።
አዲስ ዘመን ፦ በማዕከሉ የመጀመሪያ ዙር የተመረቁ ሰልጣኞች ውጤታማነት እንዴት ይገለጻል?
አቶ ሙሊሳ ፦ በማዕከሉ በመጀመሪያው ዙር ሰልጥነው የወጡ ታዳጊዎች በተለያዩ ክለቦች ይጫወታሉ፤ ብሎም በብሄራዊ ቡድን ደረጃ እስከ መመልመል ደርሰዋል። ከዚህ አኳያ ማዕከሉ ለክልልና ለሀገር ያበረከተው አስተዋጽኦ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከ17 ዓመት በታች 4 ሴቶች፣ በመላው ኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች ውድድር ኦሮሚያን የሚወክሉ ወንዶችና ሴቶች ማስመረጡ፤ ለመላው ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ኦሮሚያን የሚወክሉትን ወንዶችና ሴቶች ማስመረጡ ማሳያዎች ናቸው። ከሰልጣኞቹም መካከል ወደተለያዩ ክለቦች የተዘዋወሩ አሉ። ስለዚህ ማዕከሉ ያሉበትን ችግር ከቀረፈና የሚመለከተው አካል ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ ከቻለ በሁለቱም ጾታ አሁን ከታየው በላይ ለሀገር ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ተጫዋቾችን ማበርከት ይቻላል የሚል ሙሉ እምነት አለኝ ።
አዲስ ዘመን ፦ማዕከሉ በጥሩ መስመር እንደተጓዘ ቢሆንም ችግሮች አሉ ብለዋልና ችግሮቹን ዘርዘር አድርገው ቢነግሩን ?
አቶ ሙሊሳ ፦ ማዕከሉ የተለያዩ ችግሮች አንቀው ይዘውታል። በመጀመሪያ ደረጃ ከመሰረተ ልማት ጋር ተያይዞ ያለው ችግር ነው። በማዕከሉ ንድፍ ላይ ሶስት አራት የመጫወቻ ሜዳዎች፤ የመዋኛ ገንዳ፣ ጂም፤… ወዘተ. እንዳሉት ያመለክታል። ነገር ግን፤ ማዕከሉ በአሁኑ ሰዓት አንድ ሜዳ ብቻ ነው ያለው፤ እሱም ሰው ሰራሽ (አርቴፊሻል) ሜዳ፤በዚህም ሰልጣኞቹ በውድድር ጊዜ በተፈጥሮ ሜዳ ላይ ሲጫወቱ ችግር ፈጥሮባቸዋል። የጂም፣ የመዋኛና ሌሎች ጉዳዮችም በተመሳሳይ ተጽእኖ ያሳደሩ ይገኛሉ። ከበጀት ጋር ተያይዞ ያለው ችግርም በሌላው ማዕዘን ይጠቀሳል። ለስልጠና ማዕከሉ የሚበጀተው በጀት እጅግ አነስተኛ ነው። በማዕከሉ በርካታ ሰልጣኞችን ለማሰልጠን የሚያስችል አይደለም። የሰል ጣኞችን ቁጥር ከፍ ለማድረግ እቅድ ቢኖረንም የበጀት ጉዳይ እንቅፋት ሆኖብናል። በማዕከሉ ያሉትን ሰልጣኞች በተስፋፋ መልኩ ይዞ ለመጓዝ የሚያስችል ራሱ በቂ አይደለም። ለሰልጣኞችም ሆነ ለአሰልጣኞች ትጥቅ በበቂ ሁኔታ ለማቅረብ ችግር ሆኗል። ምክንያቱም የትጥቁ በጀት በጣም ትንሽ ነውና፤ ሌላው የማዕከሉ ሳንካ የተሽከርካሪ ችግር ነው።
ሰልጣኞች ከቦታ ቦታ ተጓጉዘው የአቋም መለኪያ ጨዋታዎችን ለማድረግ የመጓጓዣ አውቶቡስ ችግር ሆኖብናል። ሰልጣኞች ህመም ሲገጥማቸው ወደህክምና የሚወሰዱት በባጃጅ ነው። ምክንያቱም ማዕከሉ የራሱ የሆነ ሰርቪስም ሆነ ተሽከርካሪ የለውም። እነዚህ ችግሮች ማዕከሉ በሚያደርገው ግስጋሴ ላይ ሳንካ እየፈጠሩ ይገኛሉ። አዲስ ዘመን፦ ማዕከሉ ያለበትን የበጀትም ሆነ ተጓዳኝ ውስንነቶች እንዲ ቀረፉለት ለሚመለከተው አላሳወቀም? አቶ ሙሊሳ ፦ የማዕከሉን ችግሮች ለሚመለከተው አካል አቤት ብንልም ምላሽ ማግኘት ግን አልተቻለም። የኦሮሚያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ማዕከሉን በመጎብኘት፣ ትጥቅና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ አጋርነታቸውን አሳይተዋል። የማዕከሉ ጉዳይ በቀጥታ የሚመለከታቸው አካላት ግን ዘወር ብለው አልተመለከቱንም። በተለይ ደግሞ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ኃላፊነቱን ራሱ አልተወጣም።
አዲስዘመን፦እነዚህ«የሚመለከታቸው አካላት የተባሉት» እነማን ናቸው ?
አቶ ሙሊሳ ፦ የስልጠና ማዕከሉ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር እንዲያስተዳድረው ነበር የታሰበው፤ በግንባታው ሂደት ላይ ውዝግብ መፈጠሩን ተከትሎ አስተዳደሩን ለመቀየር አስገድዷል። በዚህም ማዕከሉ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት እንዲተዳደር ውሳኔ የተቀመጠ ሲሆን፤ ለወጣቶችና ስፖርት፣ ለብሄራዊ ፌዴሬሽኑ፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የኦሮሚያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት የጋራ ኃላፊነት እንዲወስዱ ነበር የተደረገው፤ ይሄንኑ ተከትሎ ብሄራዊ ፌዴሬሽኑ በቦርድ አባልነት ተካትቶና ኃላፊነት ወስዶ እንዲሰራ በመመሪያ ደረጃ የተቀመጠም ነበር። እነዚህ አካላት በተለይ ደግሞ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ኃላፊነቱን ለመወጣት ምንም አይነት ፍላጎት አላሳየም። በዚህም ምክንያት የስልጠና ማዕከሉ በእጅጉ ተጎድቷል። ከፊፋ ጋር ያለውን ግንኙነትም አሳጥቶታል።
አዲስ ዘመን ፦ ይህ ሁሉ ችግር የብሄራዊ ፌዴሬሽኑ ለመሆኑ ማስረጃው ምንድን ነው?
አቶ ሙሊሳ ፦በመመሪያው የተቀመጠው ብሄራዊ ፌዴሬሽኑ በተለየ መልኩ ድልድይ በመሆን ማዕከሉንና ፊፋን የማገናኘት ስራ እንዲሰራ ነበር፤ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፌዴሬሽን) በስሙ “ፊፋ አምቦ ጎል ፕሮጀክት የእግር ኳስ ስልጠና ማዕከል” በሚል መጠሪያ ማዕከሉን የከፈተው ያለምክንያት አይደለም። አንድ ማሳያ ለመጥቀስ፤ ማዕከሉ ሰው ሰራሽ (አርቴፊሻል) ሳር በመሆኑ በፊፋ አማካኝነት ሜዳውን በዓመት አንድ ጊዜ እድሳት እንዲደረግለት ቃል ተገብቷል። በማዕከሉ የስድስት ዓመት ቆይታ ግን ከአንድ ጊዜ በላይ ሜዳው እድሳት አልተደረገለትም። ፊፋ ለማዕከሉ ከሜዳ እድሳት በተጨማሪ ሌሎች መሰረታዊ ድጋፎችን ማድረግ ይገባው ነበር። ለማዕከሉ የገንዘብ፣ የትጥቅ፣ የሙያ ስልጠና በማድረግ ድጋፍ ለመስጠት ቃል መግባቱ ይታወቃል።
ይህ እየሆነ አይደለም። ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ሳንካ ብሄራዊ ፌዴሬሽኑ ነው። ፊፋ ማዕከሉን እንዲያግዝም ሆነ ማዕከሉ ከፊፋ ጋር እንዲገናኝ ብሄራዊ ፌዴሬሽኑ እንደ ድልድይ ያገለግላል። ይሁንና፤ ብሄራዊ ፌዴሬሽኑ ከፊፋ ጋር ድልድይ መሆን ሲገባው ጭራሹኑ አቆራረጠን። ማዕከሉ ማንኛውንም ግንኙነት የሚያደርገው በብሄራዊ ፌዴሬሽኑ በኩል ብቻ ስለሆነ እኛ ለመገናኘት አልቻልንም።
አዲስ ዘመን ፦በመጨረሻም ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ካለ?
አቶ ሙሊሳ ፦ የስልጠና ማዕከሉ እያደረገ ያለው አበረታች እንቅስቃሴ እያደገ ነው። የማዕከሉን ፍሬያማነት ቀጣይነት እንዲኖረው የሚመለከታቸው አካላት የተጠቀሱት ችግሮች እንዲቀረፉ እገዛ ማድረግ ይገባቸዋል። በእኛ በኩል ለብሄራዊ ፌዴሬሽኑ ተደጋጋሚ ጥያቄና ደብዳቤ ብንጽፍም ምላሽ ማግኘት ግን አልቻልንም። የስልጠና ማዕከሉ ከተነሳበት ሀገራዊ አላማ፤ እያደረገው ካለው በጎ እንቅስቃሴ አኳያ ይህ ችግር አንድ ቦታ መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል። ብሄራዊ ፌዴሬሽኑም የተሰጠውን ኃላፊነት በሚገባ ሊወጣ ይገባል፤ እንላለን።
አዲስ ዘመን ፦ ስለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን።
አቶ ሙሊሳ ፦እኔም እዚህ ድረስ መጥታችሁ ሃሳቤን እንድናገር እድሉን ስለሰጣ ችሁኝ በማዕከሉ ስም በእጅጉ አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን መጋቢት4/2011
በዳንኤል ዘነበ