መግቢያ
ኢትዮጵያዊያን ከመለያየት ይልቅ አንድነትን፤ ከመራራቅ ይልቅ መቀራረብን እና ከጥላቻ ይልቅ ፍቅርን በመምረጣቸው የሀገራቸውን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ሲባል በተለያዩ ጊዜ በውጭ ወራሪዎች እና ተስፋፊዎች የተቃጣባቸውን አደጋ በጋራ መመከት ችለዋል። ኢትዮጵያ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በተለየ መልኩ ነፃነቷን እና አንድነቷን ጠብቃ መቆየት የመቻሏ አንዱ መስጢር ዜጎቿ በትውልድ ቅብብሎሽ ባልደበዘዘው የሀገር ወዳድነት ስሜት በክፉም በደጉም በአንድነት አብሮ በመቆማቸው ነው (Bahru Zewude, 1991, ዩሱፍ ያሲን, 2009)። ኢትዮጵያዊያን በሀገራቸው ጉዳዮች ላይ አንድነ ታቸው ከብረት የጠነከረ ቢሆንም በውስጣቸው ግን ብዙ ቡድኖችን የያዘ የብዝሃነት አገር አላቸው (Beshir, 1979; Abebaw, 2013)።
በኢትዮጵያ ከነበረው የማህበራዊ እና የፖለቲካ ልዩነቶች እና መስተጋብሮች ምክንያት የታሪክ፣ የባህል፣ የሃይማኖት፣ የቋንቋ እና የብሔር ልዩነቶች ስለምትታወቅ በአንዳንዶች “የህዝብ ሙዝየም” ተብላ ትጠራለች (Wagaw, 1999; Abebaw, 2013)። እንደ ሀገር ይህን ብዙሃነት በአንድነት (Unity with Diversity) ውስጥ የሚስተናገድበት ፍልስፍና እና አተገባበር በሂደት አንድ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ የመፍጠር ግብን ስኬታማነት ይወስናል።
በአገሪቷ በአንድነት የአብሮ መኖር ስልት፤ የታሪክ አገነዛዘብ፤ የግለሰብ እና የቡድን መብቶች አተገባበር፤ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እና ሌሎችን መሰረት በማድረግ የሚነሱ ወቅታዊ የውስጥ ችግሮች የሀገር አንድነት ግንባታ ላይ ጥቁር ጥላ አጠልሽቶባታል። ሀገራዊ አንድነትን እየተፈታተኑ ያሉ የወል ታሪክ ትርክታችን እና አረዳዳችን ልዩነት፤ የብሄራዊ ማንነት እና ሀገራዊ ማንነት እይታዎች የተዛባ መሆን፤የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እና የአሳታፊነት ችግሮች የህዝቦች የእርስ በእርስ መጠራጠርን እና የመገለል ስሜቶችን መፍጠር፤ ከሀገራዊ አንድነት ግንባታ አንጻር የተቋማት ሚና አናሳ መሆን፤ የዴሞክራሲ እና የመልካም አስተዳደር እሴቶች አለመጎልበት ዋና ተጠቃሾች ናቸው (Zahorik, 2011)። ስለዚህ ኢትዮጵያዊነት እንደ አንድ አገራዊ አሰባሳቢ ማንነት እንዲያስተሳስር ከተፈለገ ከሚያለያየን ይልቅ በሚያስተሳስረን ላይ ማተኮር፤ አንድነትን በብዘሃነት ውስጥ ማስተናገድ፤ በወል ታሪክ፣ በመንፈሳዊ እና ቁሳዊ ቅርሶች ዙሪያ መግባባት በመፍጠር በጋራ ማድረግ፤ አንድነትን ለማጠናከር የሚሠሩ ተቋማትን ማጠናከር እንዲሁም የወጣቶች ሀገራዊ የሰብዕና ግንባታ አስመልክቶ በዕቅድና በዓላማ መሥራት ያስፈልጋል። ይህ በኢትዮጵያ አንድ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ የመገንባት ሂደት ላይ ያሉ ጽንሰ ሃሳቦችን፣ በተግባር ያጋጠሙ ስኬቶችን፣ ተግዳሮቶችን እና ችግሮችን በመተንተን ለፖሊሲ ግብአት የሚሆኑ የመፍትሔ ሃሳቦችን ያመለክታል።
የህብረ ብሄራዊ ሀገር ግንባታ ምንነት
ህብረ ብሄራዊ የሀገር ግንባታ (nationbuilding) መንግሥት የማስፈጸም የሥራ ሐላፊነቱን በመጠቀም የብሄራዊ ማንነትን በማዋቀር ወይም በማቀናጀት የሚፈጽመው ሲሆን ዓላማውም በዋናነት በሀገሪቱ ውስጥ ያሉት ህዝቦችን በአንድነት አስተሳስሮ ጠንካራ እና የተረጋጋች ሀገር ለመፍጠር ማገዝ ነው። የሀገር ግንባታ ስኬት እና ሥራዎች እንደየሀገሩ የታሪክ፣ የባህል፣ የኢኮኖሜ፣ የቋንቋ፣ የሃይማኖት እና የልሎች የልዩነት ዓይነቶች እና ጥልቀት የሚለያይ ቢሆንም ጠንካራ እና የተቀናጀ ሥራ የሚፈልግ እና የራሱ ሄደት ያለው ነው። (Kymlicka, 1995፣ Mylonas, 2017)። የተለያዩ ሀገራት ከራሳቸው ነባራዊ ሁነቶች በመነሳት የተለያዩ መርሆችን እና ዶክትሪኖችን በመጠቀም ሀገር ግንባታ ሂደታቸውን ያስኬዳሉ።
በ1950ዎቹ ከሞደርናይዜሽን ቲዮሪ ማብራሪያ መሰረት ሀገር ግንባታ እንደ ውጭ እና ደህንነት ፖሊሲ እንዲሁም እንደ ልማት ፖሊሲ ይታይ ስለነበር የሀገር ግንባታ እና የኢኮኖሚ ልማት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው ብሎ በመውሰድ ሁለቱም ተመሳሳይ የሥራ፣ የጥቅም፣ ተግዳሮቶች፣ ፖሊሲዎች እና ትግበራዎችን የሚጋሩ ናቸው ብሎ ያብራራል (Rivink, 1969)። በሌላ መልኩ ደግሞ የሀገር ግንባታ ሂደትን የድህረ ኮሎኒያሊዝም ጽንሰ ሃሳብ ነው በማለት የሚከራከሩ አካላትም “ሀገር ግንባታ በ1960ዎቹ ነፃ የወጡ አዳዲሶቹ ሀገራት ልክ እንደ አደጉት ሀገራት አዳዲስ ተቋማትን፣ መሰረተ ልማትን፣ የማሟላት እና ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትስስርን የመፍጠር ፍላጎት የወለደው ጽንሰ ሃሳብ ነው ብለው ይገልጻሉ (Atwood, 1994፣ Mylonas, 2017)። በተለያዩ ሀገራት ሦስት ዓይነት የሀገር ግንባታ ሞዴሎች ወይም የፖሊሲ አማራጮች ተተግብረው እናገኛለን።
አንደኛው የመጨፍለቅ ፖሊሲ (Assimilation policy) የሚባለው ሲሆን፣ ይህ በአንድ ሀገር ውስጥ በተለያየ ምክንያት ወይም የታሪክ አጋጣሚ የአንድ ብሔር የማንነት መገለጫዎች የሌሎችም ጭምር ማለትም የሀገር መገለጫዎች እንዲሆን የሚደረግበት እና የሌሎችን ማንነት በማጥፋት ሁሉም ዜጎች ለአንድ ስርዓት ታማኝ ሁነው እንዲኖሩ በማድረግ ሀገር የመገንባት አካሄድ ነው። ይህ ዓይነት የሀገር ግንባታ አካሄድ በሀገራችን በአፄ ምኒልክ የአገዛዝ ዘመን እና በአፄ ሐይለስላሴ የአገዛዝ ዘመን ሲተገበረ የነበረ ቢሆንም ስኬታማ አልነበረም። ሁለተኛው ሞዴል የማጥራት ፖሊሲ (Exclusionist policy) የሚባለው ሲሆን ይህም በአንድ ሀገር ተመሳሳይ ማንነት ያለው ህዝብ ብቻ እንዲኖር የማድረግ እና የተለየ ማንነት ያላቸውን የማስወገድ፣ የማባረር ወይም የማስወገድ አካሄድን የሚተገብር የሀገር ግንባታ ስትራቴጂ የሚጠቀም ነው። ይህን ለማድረግም የሚፈለገውን ማንነት ያለውን ህዝብ ማሰባሰብ፣ የተለየ ማንነት ያላቸውን ማባረር፣ ማፈናቀል እና አልፎ አልፎ ዘርን ለማጽዳት ሲባል በመግደል ጭምር የሚተገበር የሀገር ግንባታ አካሄድ ነው።
ሦስተኛው የማቀፍ ፖሊሲ (Accomodation policy) ሲሆን የዚህ ዓይነት የሀገር ግንባታ አካሄድ ያሉትን የማንነት መገለጫ ልዩነቶችን ሳያጠፋ ወይም ሳያስወግድ አብረው በጋራ እንዲኖሩ በመስተጋበር የጋራ ማንነት እና ፍላጎት የሚፈጥሩበት እና በሚኖራቸው አስተዳደራዊ ተቋማት ሁሉም ተወክለው የጋራ ሀገር የሚገነባበት የፖሊሲ አማራጭ ነው (Mylonas, 2017)፡ በሀገራችን ከ1991 ዓ.ም ወዲህ እየተተገበረ ባለው የፌዴራል ስርዓት የአንድ የፖለቲካ እና የኢኮኖሜ ማህበረሰብ ከመፍጠር አንጻር በተፈለገው ልክ ውጤታማ ባይሆንም በሂደቱ ግን ቀድሞ ከነበሩት ስርዓቶች የተሻለ ሀገራዊ መግባባት እየፈጠረ መሆኑ ግን የሚካድ አይደለም (Assefa F, 2012)።
ከላይ በተጠቀሱት ማብራሪያዎች መረዳት እንደሚቻለው ሀገራዊ አንድነት ግንባታ ዘርፈ ብዙ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚዊ፣ ማህበራዊ፣ ስነልቦናዊ ወዘተ ትስስሮችን የግድ የሚል እና ለዚህ ደግሞ ተቋማት እና መሰረተ ልማት መሰረታዊ መሳሪያዎች እንደሆኑ መገንዘብ ይቻላል።የተለያዩ ሀገራት ከራሳቸው ነባራዊ ሁነቶች እና ጽንሰ ሃሳቦች በመነሳት የሀገር ግንባታ ፖሊሲያቸውን እና አካሄዳቸውን ይቀርጻሉ። ህብረ ብሔራዊ ሀገር ለመገንባት በሀገራቱ ለሚገኙ ማህበረሰቦች ለሚኖራቸው የባህል፣ የቋንቋ፣ የሃይማኖት፣ የታሪክ እና ሌሎች ልዩነቶች እኩል ክብርን በመስጠት እና አካታች የሆነ የፖሊሲ ዕርምጃዎችን በመውሰድ በሂደት የጋራ ሀገራዊ እሴቶች እና ፍላጎቶች እንዲጎለብቱ ማድረግ ያስፈልጋል።
በኢትዮጵያ የህብረ-ብሔራዊ አንድነት ምስረታ ሙከራዎች
ኢትዮጵያ ለዘመናት መንግሥት መስርተው ነፃነታቸውን ጠብቀው ከኖሩ የዓለማችን ሀገራት ተጠቃሽ ብትሆንም የተሳካ የሀገር-ብሔር ግንባታ ግን በማካሄድ አንድነቷን በጠንካራ መሠረት ላይ ማቆም አልቻለችም። በህዝቦቿ መካከል እንደ ፀጋ ሊታዩ የሚችሉ የብሔር፣ የቋንቋ፣ የሃይማኖት፣ የኑሮ ዘይቤ እና ሌሎች ልዩነቶች ያሉ ቢሆንም ይህ ሳያራርቃቸው የጋራ ዕጣ ፈንታቸውን ለመገንባት በጋብቻ፣ በንግድ፣ እና በእምነት በመሰናሰል በርካታ የጋራ አኩሪ ሀገራዊ እና ከባቢያዊ ታሪኮችን በመፈጸም አብሮነታቸውን አረጋግጠዋል። ህዝቦቿ በበጎዎቹ ነገሮች ብቻ ሳይሆን ችግሮች፣ ስቃዮችና ውድቀቶችንም ሲጋሩ መቆየታቸው ይታወቃል። ይሁን እንጅ በተለያዩ ጊዜያት ሀገሪቷን ያስተዳደሯት ጠንካራ አንድነት በዘላቂነት ከመገንባት ይልቅ ለቆሙለት የግል እና የቡድን ፍላጎት ለማሟላት በሚረዳ መልኩ ሀገሪቷን ሲቀርጹ ቆይተዋል (IDEA, 2010 ዓ.ም፤ Mengisteab K. , 1997)።
በሰሜኑ የሀገራችን ክፍሎች በትግራይ፣ በበጌምድር፣ በጎጃም፣ በወሎ፣ በሀውሳ፣ እና በሸዋ በተለያየ ጊዜ የየአካባቢያቸው መስተዳደር ነበራቸው። በተመሳሳይ መልኩም በደቡቡ የሀገራችን ክፍሎች የግቤ አምስት ነገሥታት፤ የኦሞ ስልጣኔ የሆኑ የከፋ፣ የወላይታ / ንጉሥ ጦና/፣ ሲዳማ፣ ከምባታ እና የም /ጃንጃሮ/፤ የአፋር፣ የሶማሊያና የሀረሪ ኤምሬቶች ነፃ ግዛቶችን በመያዝ እራሳቸው እራሳቸውን ሲያስተዳድሩ ከነበሩ የሀገሪቱ ክፍሎች ተጠቃሽ ሲሆኑ በነዚህ ወቅቶች የተጠናከረ ማዕከላዊ መንግሥት አለመኖሩን በዘርፉ ያሉ ምሁራን ያመለክታሉ (ላፒሶ ጌ. ዴሌቦ, 1983; Bahru Zewude, 1991)። ኢትዮጵያ በተማከለ አስተዳደር እሳቤ የተዳደረችው በንጉሥ ቴድሮስ (በተግባር ባይሳካለትም)፣ በንጉሥ ሚኒሊክ፣ በንጉሥ ሃይለሰላሴና በደርግ መንግሥት ዘመን ብቻ ናቸው።
ከላይ የተዘረዘሩት የብዙዎች የነፃ አስተዳደር ያበቃው በአጼ ሚኒሊክ ስልጣን ዘመን ሲሆን በወቅቱ አፄ ምኒልክ አገዛዝ ወደ ደቡቡ ክፍል በመስፋፋት አዳዲስ የአስተዳደር መዋቅሮችን በመዘርጋት አዲስ የህብረተሰብ ግኑኝነት (Social and political relationship) እንዲፈጠር አድርገዋል (Bahru Zewude, 1991)። የተማከለ አስተዳደር እሳቤ እንደ ብቸኛ አማራጭ ለመተግበር የሞከሩ የአገዛዝ ዘመኖች የተጠናከረ እና የተዋሄደ ማዕከላዊ መንግሥት መመስረት ለሀገር እንድነት (state formation) ወሳኝ እንደሆነ ይወስዱ ስለነበር ይህንም ለማድረግ መንግሥታቶቹ ሁሉም የሀገሪቷ ህዝቦች የሚገለጹበት ወጥ ብሔራዊ ባህል፣ ቋንቋ እና ሃይማኖት ሌሎቹን በመደፍጠጥ ይሠሩ ስለ ነበረ ውጤታማ አልነበረም (Mengie Legesse, and Macklem, Patrick, 2010)።
በአጼ ምኒልክ አገዛዝ ዘመን ሲተገበር የነበረው የአንድ ሀገር፣ የአንድ ባህል፣ የአንድ ቋንቋ ሀገር የመመሰረት ዓላማ በሀገሪቷ ብዝሀነት የደፈጠጠ ቢሆንም ይኽዉ አካሄድ በአጼ ሃይለስላሴ አገዛዝ ዘመንም ተደግሟል (Assefa F, 2012, Merera Gudina, 2006)። በሁለቱም የአገዛዝ ዘመን የአማርኛ ቋንቋ፣ ዘመናዊ ትምህርት፣ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት፣ ጋብቻ እንዲሁም የዜጎች ነፃ እንቅስቃሴን በመጠቀም የብሄረሰቦች እና የህዝቦች የእርስ በእርስ መስተጋብር እንዲኖር እና በዚህ ሂደትም በወቅቱ ያለው አገዛዝ የሚፈልገው የማንነት መገለጫዎች ጎልተው እንዲወጡ ሲሠራ ነበር (Kebede, 2018, Mengisteab K. , 1997)። ይህን የአንድ ብሔር የበላይነት በመቃወም በብሄር የተደራጁ የታጠቁ ነፃ አውጪ ድርጅቶች በኤርትራ፣ በትግራይ እና በኦሮሚያ በመደራጀታቸው እና በነበረው የእርስ በእርስ ጦርነት የደርግ ስርዓት ተገርስሶ በኢትዮጵያ ብዙሐነትን ያመከለ ዴሞክራሲያዊ ሀገራዊ አንድነት የመገንባት ሥራ ተጀመረ (Abebaw, 2013)። ይሁን እንጂ አሁንም የብዙህነት እና የአንድነት ሐይሎች መሀከል የሀገር ግንባታ አካሄድ ላይ መሳሳቦች ይታያሉ። አንዳንዶች ኢትዮጵያዊነት ወይም ሞት በሚለው ላይ ብቻ በማተኮር የሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ማንነት መገለጫዎችን የማይቀበሉ ሲሆን በሌላ መልኩ ደግሞ ሌሎች ለብሔርተኝነት ቅድሚያ በመስጠታቸው ሀገር ግንባታን አስመልክቶ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን አንዱ ወገን የሌላውን ባለመቀበል ምክንያት ውስብስብ እና ውጤታማ እንዳይሆን እያደረገው ይገኛል (አሰፋ ፍሰሃ, 2010)።
በኢትዮጵያ ዘላቂ እና ጠንካራ የሀገር-ብሔር ግንባታ ባለመሠራቱ ሀገሪቷ ከጊዜ ወደ ጊዜ አዳጊ የህልውና ስጋት ተጋርጦባታል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሕግ የበላይነት አለመከበር፣ ከፖለቲካ ተሳትፎ የመገለል ስሜት፣ ኢፍትሓዊ የሀብት ክፍፍል ጥያቄዎች፣ የማንነት ጥያቄዎች በአግባቡ አለመስተናገድ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና የወጣቱ ሥራ አጥነት ተደማምረው ሀገሪቷን እንዳትረጋጋ አድረጓታል (Zahorik, 2011, አሰፋ ፍሰሃ, 2010)። ይህን ችግር ለመቅረፍ ለዘላቂ አንድነት ግንባታ የሚያግዙ ተገቢ ለውጦችና ማሻሻያዎች ማድረግ ያስፈልጋል። አገራዊ የዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባታ ዋና ዋና ተግዳሮቶች እና አስቻይ ጉዳዮች በሀገራችን ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባታ ሂደት ወሳኝ ሚና ያላቸው ዋና ዋና ጉዳዮች አሉ። ከዚህ አንጻር የወል ታሪክ አተረጓጎም፣ የኢሊቶች ሚና፣ እና የብዝሃነት አያያዝ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ናቸው።
የኢትዮጵያ ታሪክ ትርክት እና አረዳድ ልዩነቶች
ኢትዮጵያ በረዥም ዓመታት ውስጥ እጅግ በርካታና ተለዋዋጭነት ያላቸው ፖለቲካዊ ድርጊቶችንና ክንውኖችን አሳልፋለች። በእነዚህ ክንውኖች ዓላማ እና ውጤት ላይ ብዙ መግባባቶች እንዳሉ ሁሉ ከዚያ የማይተናነሱ መግባባት ያልተደረሳባቸው እና አጨቃጫቂ የሆኑ ጭምር አሉ (አሰፋ ፍሰሃ, 2010፣ Bahru Zewude, 1991፣ ላፒሶ ጌ. ዴሌቦ, 1983)። እነዚህ የልዩነቶች ታሪካዊ ዳራና መዋቅራዊ ምንጮቻች በአግባቡ ባለመመርመራቸው እና ለሃሳብ ሙግት የተመቻቸ ምህዳር ባለመኖሩ ለሀገራዊ ዴሞክራስያዊ አንድነት ግንባታ ተግዳሮቶች ሆነዋል። ከወል ታሪካችን የሁላችን የወል ተዘክሮ ሆኖ ለዴሞክራሲያዊ አንድነታችን ማለትም እንደ አንድ አስተሳሳሪ አበርክቶ አንዲኖረው ተደርጎ አልተሠራበትም (Abebaw, 2013)።
በአወዛጋቢው ታሪካችን ላይ የወል ባለቤትነትን ለማረጋጋጥ አወዛጋቢዎቹን የታሪካችን ምዕራፎች ለይቶ ዕርቅ በመፍጠር የተሳካ የሀገር- ብሔር ግንባታ በማከናወን የሁላችን የወል ሀብት ማድረግ ያስፈልጋል (Endalamaw Chekol, 2015)። የሀገሪቱ ታሪክ ምሉዕ እንዲሆን የሰለሞናዊውን ዘውዳዊ ስርዓት ስልጣኔን እና የክርስቲያን ወገኑን ባህልና እሴት ከመዳሰስ አልፎ የሌሎች ሃይማኖቶችንና ነባር እምነቶችን ማካተት ይገባዋል (Abebaw, 2013፣ ላፒሶ ጌ. ዴሌቦ, 1983)። እስከአሁን ያለው አመዛኙ የታሪክ ዘገባ ወደቀድሞ ነበረ ያጋደለና የኋለኛውን በበቂ ደረጃ ያላካተተ ሆኖ ቆይቷል። ስለሆነም በእስከዛሬው የታሪክና ባህል ጉዞ ያልተዳሰሱትን ማለትም፣ ከማዕከላዊው መንግሥት ጋር የጠበቀ ትስስር ያልነበራቸውን ኢትዮጵያውያንን ታሪክ በመመርመር፣ ታሪካቸውን በቅጡ በማጥናት መዘገብ፣ መተረክና ማስተዋወቅ ያስፈልጋል (IDEA, 2010 ዓ.ም፣ ሀብታሙ አለባቸው, 2009 ዓ.ም)።
የብሄራዊ ማንነት እና የሀገራዊ ማንነት መስተጋብር እና አተገባበር ብዥታዎች
በኢትዮጵያ የብሄራዊ ማንነት እና የሀገራዊ ማንነት በጋራ እና በተናጥል ማስተናገድ በአግባቡ ያልተመለሰ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ደም አፋሳሽ የሆነ የፖለቲካ ትግል የተካሄደበትም ጭምር ነበር። ይህም ሁኔታ የተፈጠረው ‹‹በመሬት አንድነት›› እና ‹‹በህዝቦች አንድነት›› አስተሳሰብ አራማጆች መካከል የማይታረቅ ቅራኔ ውስጥ በመግባታቸው ነው (Bahru Zewude, 1991; Assefa F, 2012)። የማይሸራረፍ የመሬት አንድነት ጥያቄ ወይስ የማይሸራረፍ የህዝቦች መብት ጥያቄ መመለስ የሚችል አንድነት የሚለው አተካራ ግን ዛሬም ቢሆን የተዘጋ አጀንዳ አይደለም። ዛሬም ‹‹የፍፁማዊ አንድነት ተከታዮች ዘመን›› ተመልሶ ይመጣል የሚለው ሃይል አስተሳሰብ አለ። በሌላው ፅንፍ ‹‹የፍፁማዊ ነፃነት›› አቀንቃኝም ጥያቄውን አላነሳም።
በተመሳሳይ ከሙግቶቹ ጋር በተያያዘ መልኩ በማንነት ላይ በተመሰረቱ ፌዴሬሽኖች በአንድነት ግንባታ ረገድ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶችም አሉ (Assefa F, 2012፣ Merera Gudina, 2006)። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ህብረ ብሄራዊ በሆኑ ፌዴሬሽኖች ውስጥ በማንነት ላይ ያተኮሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች መበራከታቸው እና እርስ በርስ የሚፎካከሩ አጀንዳዎች ይዘው እንደሚመጡ ይታወቃል። እንዲህ ዓይነቱ ችግር በተለይ ፕሮፖርሽናል የምርጫ ስርዓት በሌላቸው ፌዴሬሽኖች ለሀገራዊ አንድነት ግንባታው ሌላው ተግዳሮት ሊሆን ይችላል(Beshir, 1979)። ይህም ማለት የአብላጫ ድምፅ አሸናፊነትን የሚከተለው የምርጫ ስርዓት ብዙዎቹን ፓርቲዎች የማሸነፍ ዕድል ስለማይሰጣቸው እንወክለዋለን የሚሉት ማንነት እንደተገለለ በመቁጠር እና ይህንኑ ለሚወክሉት ማንነት በመንገር ሀገራዊ አንድነት ግንባታው ላይ በጎ ያልሆነ ተጽእኖ ይፈጥራሉ። ህንድ ዛሬ ከደረሰችበት ደረጃ ከመድረሷ በፊት አጋጥመዋት ከነበሩ ተግዳሮቶች አንዱ የብሔራዊ ማንነትንና ሀገራዊ ማንነትን አቀናጅቶ መሄድ አለመቻል ነበር። እንደሚታወቀው ህንድ ዘርፈ ብዙ ብዝሀነት የሚስተናገድባት ፌዴራላዊ ሀገር ነች። በህንድ ህንዳዊነት የተገነባው እርስ በርስ የማይጋጩ እንዳውም አንዱ ላንዱ ግብአት በሆኑ ለአንድነት እውቅና የሚሰጥ ብዝሀነት እና ብዝሀነትን የሚያከብር አንድነትን የሚቀበል አንድነት ህንዳዊነትን ለመገንባት እና ለማጎልበት ሲባል በአግባቡ ሥራ ላይ አውለውታል (Gagiano, 1990፣ Mengie Legesse, and Macklem, Patrick, 2010)።
የዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ አሳታፊነት እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች
የኢትዮጵያ ህዝቦች ረጅም የትግል ታሪክ በውል እንደሚያስረግጠው የትግሉ ቁልፍ አጀንዳዎች የእኩል ተጠቃሚትና ተሳታፊነት ጥያቄዎች ሲሆኑ በመደባዊ ጭቆናና በብሄራዊ ጭቆና መልክ የሚገለፁ ነበሩ። በህዝቦች እና በክልሎች መሀከል የሚፈጠር የኢኮኖሚ ዕድገት አለመመጣጠን የእርስ በእርስ መጠራጠሮችን እና የመገለል ስሜትን በመፍጠር የአንድነት ግንባታውን ጎድቷል (ላፒሶ ጌ. ዴሌቦ, 1983; Zahorik, 2011)። ክልሎች ከክልልሎችም ሆነ ክልሎች ከማዕከላዊው መንግስት ጋር የነበራቸው የእርስ በርስ ግንኙነት መርህ አልባነት፤ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ስርጭት እና አተገባበር ኢፍትሐዊነት መብዛት፤ የኮንትሮባንድ እና የህገወጥ ንግድ መበራከት፤ የተደራጀ መንግሥታዊ ሙስናና ሌብነት እንዲሁም ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሀገራዊ የፖለቲካ አሳታፊነት የቀጨጨ እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን በማሳነስ የመገለል ስሜትን በመፍጠር የሀገራዊ አንድነት ግንባታ ሂደቱን አሉታዊ ጫና አሳድሮበታል (Abebaw, 2013፣ Endalamaw Chekol, 2015)።
ሀገራዊ የአንድነት ግንባታ ሥራዎች ስኬታማ እንዲሆን ከተፈለገ ጠንካራ የኢኮኖሚ ትስስር የተለያዩ ብሄራዊ ማንነቶች የጋራ ጥቅሞች እና ፍላጎቶች እንዲዳብሩ በማድረግ ወደ ትብብር እንዲመሩ ማድረግ ያስፈልጋል (Endalamaw Chekol, 2015):: በህብረ ብሄራዊ ፌዴሬሽኖች ሀገራዊ አንድነትን የበለጠ ለማጎልበት ከክልሎችም ከማእከላዊ መንግሥቱም ሊነሱ የሚችሉ አጀንዳዎች ላይ ቀጣይነት ባለው መልኩ ውይይቶች፣ ክርክሮች፣ ድርድሮች እና ሰጥቶ መቀበል በማድረግ ፌዴሬሽኑን አባላት ፍላጎት እና ጥቅሞች ማካተት ተገቢም የግድም ነው። በሌላ አገላለጽ በጥቂት ልሂቃን ብቻ አግላይ በሆነ መልኩ የሚወሰኑ እና የሚወሰዱ እርምጃዎች ብዙሃኑን የፌዴሬሽኑን አባላት ያስኮርፍና የአንድነት ግንባታውን ሂደት እንዳያስተጓግል መሥራት ያስፈልጋል (Abebaw, 2013, Zahorik, 2011)።
ከሀገራዊ አንድነት ግንባታ አንጻር የተቋማት አቅም ውስንነት
በማንነት ላይ በተመሰረተ ፌዴራሊዝም ብዙውን ጊዜ በአንድነት እና በልዩነት ዕሴቶች መካከል የመሳሳብ ዝንባሌ መታየቱ አይቀሬ ነው (Atwood, 1994):: ይህን መሳሳብ በተመለከተ የተለያዩ ተቋማት አንድነትን እና አብሮ መኖርን የሚያጠናክሩ ህብረብሔራዊ እሴቶችን በማጎልበት መሥራት አለባቸው። በሀገራችን የነበሩ መሰረታዊ ህግጋቶች እና ተቋማት ህብረ ብሔራዊ ስርዓቱን ከማጠናከር ይልቅ በተግባር የአንድ ብሄር ወይም የተወሰኑ ብሄረሰቦች ጥቅሞችን እና ፍላጎቶችን በማጎላት አብሮ በመኖር ውስጥ ብዙን ጊዜ የሌሎችን ውክልና ወይም ጥቅም ማስጠበቅ ላይ የተኣማኒነት ችግር ጎልቶ ይታይባቸዋል (Merera Gudina, 2006; Mengisteab, 2001)። ሀገራዊ አንድነትን በዘለቄታነት ለመገንባት የተቋማት የማድረግ አቅምና የፖለቲካ ዝግጅት እና ፍላጎት ወሳኝ ሚና መጫወት እንደሚችሉ የሚታወቅ ቢሆንም በሀገራችን የፌዴራል ተቋማት እና የክልል መንግሥታት ተቋማት ህብረ-ብሔራዊ በመሆን ዴሞክራሲያዊ አንድነትን ለማጠናከር እየሥሩ ያሉት ሥራዎች ደካማ ናቸው።
በትምህርት ቤቶች የሚሰጠው ትምህርት ይዘት እና አቀራረብ ሀገራዊ አንድነትን በሚያጎለብት መልኩ መቀረጽ አለበት፤ሀገራዊ ፖሊሲዎች አብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል በሚያሳትፍ እና በሚያማክል መልኩ መቀረጹ እና ሥራ ላይ ማዋል ያስፈልጋል እና የህግ ስርዓቱ ፍትሐዊ በሆነ መልኩ መተግበሩ ወሳኝ የሀገራዊ አንድነት መገንቢያ መሣሪዎች እንደሆኑ ይተነትናል (Wagaw, 1999)። በተመሳሳይ መልኩ Mylonas (2017 ) የሀገራዊ አንድነት መገንቢያ መሣሪዎችን ሲጠቅስ የቋንቋ ፖሊሲ፣ አስገዳጅ ብሄራዊ ውትድርና አገልግሎት፣ ሀገራዊ ነቁጦች እና በአላት፣ ስፖርት እና ዓለምአቀፋዊ ተሳትፎዎች ጭምር ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው ያብራራል። የጋራ መጠቀሚያ የሆኑ መሠረተ ልማቶች ማለትም የመንገድ አቅርቦት፣ የቴሌኮሚኒክሽን አገልግሎት፣ የገበያ አቅርቦት፣ የጤና ተቋማት ስርጭት እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ሥራዎች የህዝቦችን የእርስ በእርስ ግንኙነት በመወሰን የሀገር ግንባታ ሥራዎችን በማፋጠን ወይም በመግታት ትልቅ ሚና ይጫወታል (Mengisteab K. , 2001)።
የቋንቋ ብዝሀነት ያላት ፌዴራላዊ ሀገር የምትከተለው የቋንቋ ፖሊሲ በተለይ ደግሞ በሥራ ቋንቋ አመራረጥ ላይ የምትወስደው ውሳኔ በሀገሪቱ ህዝቦች መካከል ለሚኖረው ግንኙነት እና አንድነት ግንባታ መሰረታዊ አስቻይ/ነቃይ – ተካይ/ ተደርጎ ይወሰዳል (Zahorik, 2011፣ Assefa F, 2012)። የቋንቋ ፖሊሲ ብዝሃነት በሚታይባቸው ፌዴራላዊ ሀገራት ሊጫወት የሚችለውን ሚና ለመረዳት የሲውዘርላንድ ፌዴሬሽኖችን ተሞክሮ ማየት ይጠቅማል። በሲውዘርላንድ ከሚነገሩ አራት ቋንቋዎች መካከል ሦስቱ ማለትም ጀርመን፣ ፈረንሳይኛ ጣልያንኛ እና ሮማኒሽ በ1848 በህገ መንግሥቱ አኩል እውቅና እንዲያገኙ አደረጉ። የሲዊስ ሊህቃን ከ19ኛው ክፍለዘመን አንድ ሀገር አንድ ቋንቋ ከሚለው አስተሳሰብ በተለየ መልኩ የቋንቋ ብዝሀነትን እኩል እውቅና በመስጠታቸው በተለያዩ ቋንቋዎች ተናጋሪዎች መካከል የባላንጣነት ሳይሆን የትብብር መንፈስ ጎልቶ እንዲወጣ አስችሎታል (Espersen B., 2012፡86)።
እንደመውጫ
ሀገር በርካታ ተያያዥ እና ተከታታይ ሥራዎችን የግድ የሚል፤ ዜጎች በሀገራቸው ልዩ ልዩ የታሪክ፣ የፖለቲካ እና የማህበራዊ ኩነቶች ተቀራራቢ ቢያንስ ደግሞ ጽንፍ ለጽንፍ ሆኖ መደማመጥ ያልተሳነው አተያይ እና አስተሳሰብን እንደ ዋንኛ ግብዓቶች የሚፈልግ እና የሚጠቀም፤ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እንደ ጡብ ተደራርበው እና ተሰድረው የሚገነቡት የጋራ ቤት ነው። ይህን ለማድረግ የምሁራን፣ የፖለቲከኞች እና የሌሎች ተቀዋማዊ እና ግለሰባዊ ተዋንያኖች አስተዋጽኦም ከፍተኛ ነው።
ስለሆንም የምንጽፋቸው፤ የምንናገራቸው እና የምንተገብራቸው እያንዳንዳቸው ጉዳዮች ሀገርን የመገንባት ወይም የማፍረስ አቅም እንዳላቸው መረዳት እና በገንቢ ጎናቸው አስተዋጽኦ የሚያደርጉበትን መንገድ መሻት የግድ እና አሁን መደረግ ያለበት ጉዳይ ነው ብዬ አምናለሁ። ከዚህ አንጻር ለታሪካችን፣ ለቋንቋችን፣ ለባህላችን ወዘተ የሚኖረነረ አረዳድ እና የምንሰጠው ስፍራ ወሳኝ እና ተኪ የሌለው መሆኑን በመረዳት በኃላፊነት መንፈስ መተወን ለራስም ለሀገርም ፈውስ ነው በማለት ላብቃ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 4/2011
በጎሳዬ ቶጎና