የሰው ልጅ ህልውና/መኖር ሲታሰብ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሬት ነው። መሬት ለሰው ልጅ ሁለንተና መገለጫው ነው። መኖሪያው፤ የምግብና የእስትንፋስ ምንጩ፤ የምንነትና የማንነት መታወቂያው ነው። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በአብዛኛው የህዝባቸው የኑሮ መሰረት በግብርና ላይ ለተመሰረተ አገሮች መሬት ትልቅ ፋይዳ ያለው ጉዳያቸው ነው። በመሆኑም አግባብ ባለው መልክ ሊያዝ ይገባዋል። በአ.ፌ.ዴ.ሪ. ህገመንግሥት ድንጋጌ መሰረት የገጠርም ሆነ የከተማ መሬት እና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት መብት የመንግሥትና የህዝብ ብቻ ነው። በዚህ ህገመንግሥትም የፌዴራል መንግሥቱም ሆነ ክልሎች አብዛኛው መብታቸው ይህንን የማስተዳደር ነው የሚሆነው፤ ይሁን እንጂ፤ በተግባር የሚገለጠው የተገላቢጦሹ ነው።
ህገመንግሥቱ የመሬትን የባለቤትነት መብት ለህዝቦች ይስጥ እንጂ እንዴት ያስተዳድሩት፤ የሐላፊታቸው ደረጃስ ምን ያህል ይሁን የሚለው ተቆጥሮ ስርዓት አልተበጀለትም። በዚህም የተነሳ እስከአሁን ድረስ በገጠርም ይሁን በከተማ ከመሬት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጥያቄዎችና ችግሮች መቋጫ አላገኙም። በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ በየነጋው የሚነሳው የመሬት ጥያቄና የይዞታ አቤቱታ እስከወዲያኛው በሚባል ደረጃ የሚፈታበት መንገድ አልተዘረጋም። በተለይ በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር እየጨመረ፤ ከገጠር ወደከተማ የሚፈልሰው የሰው ኃይል መጠኑ እየናረ በመጣ ጊዜ የከተሞችን መስፋትና መስፋፋት የግድ ብሎታል። የከተሞች መስፋትና መስፋፋት ደግሞ ያለመሬት አይሆንምና ሁልጊዜ ችግር እንደሆነ ቀጥሏል።
ግን አንድ ቦታ ላይ መቆም አለበት። ይህንን የከተሞች መስፋፋት ተከትሎና ህገመንግሥቱ መሰረት ተደርጎ የከተሞች ፕላን ፖሊሲ ተቀርጿል። በዚህም ለአረንጓዴ ልማት፤ ለመንገድና ትራንስፖርት፤ እንዲሁም ለግንባታ በሚል 30/30/40 ምጣኔ ቢነደፍም፤ በአዲስ አበባም ይሁን በሌሎች ከተሞች ይህ ምጣኔ ተግባራዊ አልሆነም። እንደ ፖሊሲ ጥናት ምርምር ማዕከል ጥናት ከሆነ ደግሞ የከተማ ልማት ፖሊሲ ሃሳቦች በአብዛኛው አልተፈጸሙም። በገጠርም ቢሆን የአገሪቱ መሬት በይዘት ተለይቶና ለተለያዩ ዓለማዎች እንዲውል ተወስኖ የሚመራበት ፖሊሲ አልወጣም፤ ስርዓትም አልተዘረጋም። ይህም ባለመደረጉ የአዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ የጎንዮሽ የሚታየው መስፋፋት የገጠሩንም የከተማውንም መሬት ይዞታውን፤ አስተዳደሩን ስርዓት አሳጣው።
እንዲህ ዓይነቱ ነባራዊ ሁኔታ ደግሞ መንግሥትን እንደመንግሥት ለማስተዳደር ከተሰጠው ኃላፊነት በላይ የባለቤትነት መብት አጎናጸፈው። የመንግሥት ባለስልጣናትና አጋጣሚውን ያገኙ ግብረአበሮቻቸው የመብቱን አዛዥነት ናዛዥነት ወሰዱ። ችግሩ ግን ለደሃው ከተሜና ለአፈር ገፊው ገበሬ ተረፈው። አዎን ኢትዮጵያ የከተማም ሆነ የገጠር መሬት አያያዝና አስተዳደር ፖሊሲ የላትም። ፖሊሲውን ተከትሎም የሚተገበሩ ሳይንሳዊ የመሬት አጠቃቀምና የመረጃ አያያዝ ስርዓቶች አልተዘረጉም። በከተማ የሚታየው የግንባታም ሆነ የኢንቨስትመንት ሥራ የሚመራው እንደአመቺነቱ በሚወጡ መመሪያዎች ሆኗል። እንዲያም ሆኖ አዲስ አበባ የከተማ መሬት አስተዳደር ደንብና መመሪያ እያላት የፌዴራል መንግሥቱ ሌላ ተደራቢ መመሪያ አውጥቷል።
ይህ ያለመናበብ ችግር የሚገለጠው እንደህልም ፈቺ በየወቅቱ በሚኖረው አመራር አቅምና ፍላጎት ነው። ግን እስከመቼ? ኢትዮጵያ እንደአገር የከተማ መሬት ይዞታዋንና የገጠር አካባቢዋን የምታስተዳድርበት ሕግና ስርዓት ሊኖራት ግድ ነው። ከዚህ ውጪ በግለሰቦች ፍላጎትና ይሁንታ የሚፈጠረውንና ጦሱ ለሕዝቡ የሚተርፈውን የመሬት ቅርጫ ችግር መፍታት አይቻልም። አዎን መንግሥት በገጠርም ሆነ በከተማ የተዘበራረቀውን የመሬት አጠቃቀም ለማስተካከልና ፍትሐዊ የሆነ ስርዓት ለመዘርጋት ወጥ የሆነ አሠራር (ፖሊሲ ቀርፆ) ተግባራዊ ማድረግ አለበት። ይህ ደግሞ ለነገ የሚባል ጉዳይ ሳይሆን በአስቸኳይ ዛሬውኑ መደረግ ያለበት ነገር ነው።
መሬት የማይሸጥና የማይለወጥ የኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦችና ህዝቦች የጋራ ንብረት ከሆነ፤ ስርዓት ባለው መንገድ ተመዝግቦ ሊያዝ፤ የተያዘውም ስርዓትና አግባብ በሆነ መንገድ ጥቅም ላይ ሊውል ይገባል። ያ ካልሆነ ግን አሁንም የችግርና የግጭት መንስዔ ሆኖ ይቀጥላል። የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግሥታትም በህግ የተሰጣቸውን ሐላፊነት የማስተዳደር አንጂ እንደፈለጉት አየሸነሸኑ ጥቂቶችን ተጠቃሚ አብዛኛውን ህዝብ ደግሞ ተፈናቃይና የበይ ተመልካች እንዲያደርጉት አይደለም። እናም ሐላፊነታቸውን የወሰነ፤ ግዴታቸውንም ያገናዘበ፤ የባለቤትነት ሳይሆን የአስተዳዳሪነት መብት ያላበሰ ስርዓት ሊቀረጽና ሊተገብር ይገባል። እንዲያ ሲሆን በከተማ ዘመናዊ የመሬት አስተዳደር ስርዓት ለማስፈን ይቻላል። ነዋሪውም መብቱንና ግዴታውን ተገንዘቦ በህጋዊ መንገድ መተዳደርን ይለምዳል።
አስተዳደሩም አዲስ ተሿሚ በመጣ ወይም መዋቅር በተቀየረ ቁጥር አፍራሽ ግብረ ሐይል አቋቁሞ የሚሠራውን የዘመቻ ሥራ ያስቀረዋል። ፊቱንም የወጣውን የከተማ ልማት ፖሊሲ 30/30/40 ምጣኔ ተግባራዊ ወደማድረግ ያዞራል። በአጠቃላይ አገራችን ከመሬት ጋር ተያይዞ ከሚነሱና አሁን ላይ ከሚታዩ ችግሮችና ውጥንቅጦች ለመውጣት የምትችለው አንድ ወጥ የሆነ አገራዊ የመሬት ይዞታና አስተዳደር ፖሊሲ ሲኖራት ነውና መንግሥት ይህንን ታሳቢ አድርጎ አፋጣኝ ሥራ መሥራት ይገባዋል። የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግሥታት እስከዛሬ ከነበረው የመሬት ባለቤትነት መብት ወጥተው የአስተዳዳሪነት ሐላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል። እንዲህ ሲሆን በከተማም ይሁን በገጠር የሚታየው የህዝቦች መፈናቀል ይቀራል። መሬትና ተያያዥ ጉዳዮች በስሜትና በፍላጎት ሳይሆን በህግና በስርዓት ብቻ ይተዳደራሉ። በመሆኑም ሁሉም ወገን ለአገራዊው የመሬት ፖሊሲ መውጣትና ሥራ ላይ መዋል የየድርሻውን ተወጥቶ ይህቺን ታሪካዊት አገር በመሬት ሰበብ ከሚመጡ ችግሮች ሊታደጋት ይገባል እንላለን!
አዲስ ዘመን መጋቢት 4/2011