ሀገራችን ኢትዮጵያ በረጅም ዘመን ታሪኳ ለሉዓላዊነቷ ውድ ዋጋ የከፈሉና ለዕድገቷ የተጉ በርካታ ውድ ልጆችን አፍርታለች። ለሃገርና ለወገን የሰሩና የደከሙትን ማበረታታት፣ መሸለምና ዕውቅና መስጠት ለተመስጋኙ ከሚሰጠው የአእምሮ ርካታና ከሚያጎናጽፈው ኩራት ባሻገር ተተኪው ትውልድም አርአያነታቸውን ተከትሎ ሃገሩን በትጋትና በታማኝነት እንዲያገለግል ትልቅ አቅም ይሆናል።
ይህንንም እውነታ መነሻ በማድረግም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 80ኛ ዓመት የምስረታ ክብረ በዓልና የዋና መስሪያ ቤት ህንጻ ምረቃ ላይ በኢኮኖሚው ዘርፍ ለሃገራቸው ትልቅ አስተዋጽኦ ላባረከቱ ግለሰቦች ልዩ ሽልማት ሰጥተዋል። ለመሆኑ ተሸለሚዎቹ እነማን ናቸው ያበረከቱት አስተዋጽኦስ ምን ይመስላል? የሚለው እንደሚከተለው በቅደም ተከተል ተሰናድቶ ቀርቧል፦
የብሔራዊ ማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ
ለተከታታይ ዓመታት ዕድገት ሲያስመዘግብ የቆየው የአገራችን ኢኮኖሚ፣ በባለፉት ሁለት ዐሠርት ዓመታት በተከተልነው የልማት ፋይናንስ ሞዴል ጉድለት የተነሣ እንዲሁም የተስተዋሉትን ችግሮች በፍጥነት ለማረም የሚያስችል ዝግጁነት ባለመኖሩ፤ ለከፍተኛ የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ተዳርጎ መቆየቱ የሚታወስ ነው።
በዚህም የተነሣ የኢኮኖሚ ዕድገቱን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ወሳኝ የነበረው የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመምጣቱ፣ የለውጡ መንግሥት ትልቁ ሥራው ኢኮኖሚው ወደ ተባባሰ ቀውስ እንዳይገባ መከላከል እና ቀስ በቀስ እንዲያገግም የማድረግ ተግባር ነበር።
ይህን ሁኔታ ወደኋላ መለስ ብለን ስንመለከት፣ የቀውሱ ዋና መገለጫ ጤናማ ያልሆነ የፋይናንስ ዘርፍ ነበር። ለአብነት እ.ኤ.አ ከ2010 – 2020 ባለው ጊዜ ውስጥ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በገንዘብ ሚኒስቴር ዋስትና የሚወስዱት ብድር በ21 እጥፍ አድጐ ነበር። ይህ ልማትን በንግድ ብድር ፋይናንስ የማድረግ ፖሊሲ፣ ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች ደካማ የፕሮጀክት አፈጻጸም ጋር ተደምሮ የፋይናንስ ዘርፉን ለአደገኛ ቀውስ ዳርጐት ነበር።
የመንግሥት የልማት ድርጅቶቹ ዕዳቸውን ለመክፈል ሲባል ሌላ ዕዳ እንዲወስዱ ይገደዱ ነበር። ይህ ማቆሚያ የሌለው አደገኛ የዕዳ ዝፍቀት አካሄድ እንደ አጠቃላይ በኢኮኖሚያችን ላይ ጤናማ ያልሆነ የፋይናንስ ዘርፍ እንዲፈጠር አድርጓል። በተለይም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን የሀብት ጥራት ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲያሽቆለቁልና የፋይናንስ ህልውናው ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ ምክንያት ሆኗል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ቡድኑ ሲቋቋም ይዞት የተነሣው ዋና ዓላማ ለኢኮኖሚ መዛባቱ እልባት ለመስጠት ነው። ለዚህም ለዓመታት የተከማቸውን እዳ መቀነስና የአገሪቱን የፊስካል አስተዳደር ዘላቂነት ባለው ጽኑ መሠረት ላይ እንዲገነባ ለማድረግ፣ በፋይናንስ የፖሊሲ አማራጮች ላይ ማስተካከያዎችን ለማድረግ ወሰነ። ኢኮኖሚው ከተጋረጠበት ጥልፍልፍ አዙሪት ውስጥ እንዲወጣ ከበጀት ውጪ ያሉ አማራጮችን አሟጦ መጠቀም ግድ ብሏል። ለዚህም እንዲረዳ የልማት ድርጅቶችን ውስጣዊ ዐቅም መፈተሽ፣ የፕሮጀክት አፈጻጸማቸውን መከታተል እና በተሻለ ጥራት ተፈጻሚ እንዲሆኑ ግፊት ማድረግ አስፈላጊ ሆኗል። አዳዲስ የልማት ፕሮጀክቶችም ብድር ለማግኘት ወደ ንግድ ባንክ ከመሄዳቸው በፊት፣ የኢኮኖሚ አዋጭነታቸው በፕላንና ልማት ሚኒስቴር በኩል እንዲገመገም የሚያደርግ አሠራር ተግባራዊ ተደረገ።
በተመሳሳይ ለችግሩ ዘላቂ ዕልባት ለመስጠት ሲባል የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ዕዳ የመክፈል ዐቅም በመገምገም፣ መክፈል ለማይችሉት መክፈል፣ ተሸክመው መቀጠል የሚችሉትን ደግሞ ራሳቸው እንዲከፍሉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት፣ ለዚህም እንዲረዳ ዕዳን እና የመንግሥትን ሀብት ሊያስተዳድር የሚችል ተቋም ማቋቋም፣ ለተቋሙ የሚያስፈልገውን የሕግ፣ የአዋጅ እና የአሠራር ማእቀፍ ሥራን ጎን ለጎን አጠናቆ ተግባራዊ ማድረግ ተችሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከቴሌኮም አዲስ ፈቃድ መስጠት ጋር ተያይዞ የተገኘውን ገቢ በቀጥታ ለአገር ውስጥ ዕዳ መክፈያ በማዋል፣ የንግድ ባንኩን የፋይናንስ ዐቅም ጤናማና ተወዳዳሪ ሆኖ እንዲቀጥል ጉልህ አስተዋጽዖ አድርጓል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ቡድኑ እነዚህንና ሌሎች ጉዳዮችን በተከታታይ በከፍተኛ ሙያዊ ዲሲፒሊን በመመርመርና ውሳኔ በመስጠት፣ ኢኮኖሚው ወደ ተባባሰ ቀውስ አዙሪት ውስጥ እንዳይገባ አድርጓል። ከዚህም በተጨማሪ፣ የአገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ፕሮግራም በመንደፍ ኢኮኖሚውን ወደ ዕድገት ምኅዳር ተመልሶ እንዲገባ ለማድረግ ሲሠራ ቆይቷል። ባለፈው መንፈቀ ዓመት ብቻ በየሳምንቱ ሳያቋርጥ በመገናኘት፣ በ32 የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ወደ 110 የሚደርሱ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል። በአጠቃላይ እነዚህን ችግሮችንና ፈተናዎችን ወደ ዕድል፣ ዕድልን ደግሞ ወደ ድል ለመቀየር ብርቱ ትግል አድርጓል።
የብሔራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴን በመወከል ይህን ልዩ ሽልማት ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እጅ የተቀበሉት አንድ ታላቅ ሰው ናቸው።
እኒህ ታላቅ ሰው፤ በአገራችን የተረጋጋና ጤናማ የማክሮ ኢኮኖሚ ዐውድ ለመፍጠር፣ የግል ዘርፉን ተሳትፎ ለማጐልበት፣ ፍትሐዊ ዕድገትን ለማስቀጠል፣ እንዲሁም በቂና አስተማማኝ የሥራ ዕድልን ለመፍጠር በልምድና በዕውቀት የደረጁ ሃሳቦችን በማቅረብና ብቃት ያለው አመራር በመስጠት ይታወቃሉ።
ከሦስት ዓመታት በፊት በአዲስ መልኩ በተቋቋመው የብሔራዊ ማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ አባልነት፣ የአገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርምና ፕሮግራሞችን ከመቅረጽ እስከ ማስፈጸም ከፍተኛ ሚና ሲወጡ ቆይተዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የኢኮኖሚ ጉዳዮች ክፍል ጀማሪ የኢኮኖሚ ባለሙያ ከመሆን አንሥቶ አሁን እስካሉበት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ ከፍተኛ አማካሪነት ድረስ ታማኝነትን ከብቃትና ትጋት ጋር አጣምረው ላለፉት ዐርባ ዓመታት ኢትዮጵያን አገልግለዋል። በመካከል የመከላከያ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር፣ የኢትዮጵያ ገቢዎች አስተዳደር ኃላፊ ሚኒስትር፣ የኢኮኖሚ ልማትና ትብብር ሚኒስትር፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር፣ በአሜሪካ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር በመሆን ሲያገለግሉ ነበር።
እኒህ ታላቅ ሰው፤ ስንፍናንና የምናገባኝ አስተሳሰብን የሚጸየፉ፣ በሰዓት አክባሪነታቸውና፣ በዲሲፒሊናቸው ሥራን ማዕከል በማድረግ በአርአያነት የሚታዩ የሥራ መሪ ናቸው።
የብሔራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴን በመወከል ይህን ልዩ ሽልማት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እጅ የተቀበሉት እኒህ ታላቅ ሰው፤ በአሁኑ ጊዜ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪና የብሔራዊ ባንክ የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት ክቡር አምባሳደር ግርማ ብሩ ናቸው።
- አቶ ተክለ ወልድ አጥናፉ
ከሦስት ዓመት በፊት የጠቅላይ ሚኒስትር ከፍተኛ የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪ ሆነው ከመመደባቸው አስቀድሞ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ውስጥ ከረዳት የኢኮኖሚ ሪሰርች ኦፊሰርነት አንስቶ እስከ የፋይናንስ ተቋማት ሱፐርቪዥን ዳይሬክተርነት ድረስ ለ30 ዓመት በተለያዩ ቦታዎች አገልግለዋል። ዛሬ የፋይናንስ ተቋማት የሚተዳደሩባቸውን አብዛኛዎችን ሕግጋትና አሠራሮች ከመቅረጽ እስከ ማስፈጸም የሚያደርሰውን ተግባር ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን አከናውነዋል።
በተጨማሪም የብሔራዊ ባንኩ ምክትል ገዥ ቀጥሎም ገዥ በመሆን ባንኩንና አጠቃላይ የፋይናንስ ዘርፉን መርተዋል። እንዲሁም የዓለም የገንዘብ ድርጅት /IMF/ የገዥዎች ቦርድ /Board of Governors/ አባል በመሆን ለ18 ዓመት አገልግለዋል። በእነዚህ ዓመታት ወሳኝ የሚባሉ ስኬቶችን ለኢትዮጵያ አስመዝግበዋል።
1ኛ/ ለረዥም ዓመታት በጦርነትና በድርቅ ሣቢያ የደቀቀውንና በዝቅተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ የቆየውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንዲያንሠራራና ፈጣን ዕድገት እንዲያስመዘግብ ለማድረግ በተካሄዱት የኢኮኖሚ ዕድገትና ልማት ዕቅዶች ከቀረፃ እስከ መፈጸም ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን የበኩላቸውን አስተዋጽዖ አበርክተዋል፣
2ኛ/ እንደ ዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት /IMF/ ከመሳሰሉ የፋይናንስ ተቋማት እንዲሁም ከለጋሽና አበዳሪ አገራት ጋር የመዋቅርና የዕዳ ቅነሳ ድርድር በማድረግ ከፍተኛ የውጭ ዕዳ እንዲሠረዝ፣ የውጭ ዕዳ ጫና እንዲቀነስና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ ከብሔራዊ ማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ አባላት ጋር በመሆን ጉልህ ሚና ተጫውተዋል፣
3ኛ/ በጣም ዝቅተኛ የሆነው አጠቃላይ የአገር ውስጥ ቁጠባ እንዲያንሠራራ ለማድረግ የሌሎች አገሮች ተሞክሮን በመቀመር በርካታ የፋይናንስ መመሪያዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ አድርገዋል፣ በዚህ ረገድ ለብሔራዊ የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ ተቀርፆ ተግባራዊ መሆኑና ባንኮች ቅርንጫፎቻቸውን በየዓመቱ 25 በመቶ እንዲያሳድጉ በመደረጉ የባንክ ቅርንጫፎች በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።
4ኛ/ ጤናማ፣ የተረጋጋ እና ተደራሽ የፋይናንስ ሥርዓት ለማስፈን በርካታ ሥራዎችን ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን በማከናወናቸው ዛሬ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ የተረጋጋና ጤናማ ሆኖ እየተስፋፋ ይገኛል።
5ኛ/ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪ ሆነው ከተመደቡበት ጊዜ ጀምሮ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰብሳቢነት ለተቋቋመው የብሔራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ አባል ሆነው ከሌሎች የኮሚቴ አባላት ጋር በመሆን የአገር በቀል የኢኮኖሚ ፕሮግራም ከመቅረጽ ጀምሮ በፕሮግራሙ የተቀመጡት ግቦች እንዲሳኩ ድርሻቸውን ተወጥተዋል፤ እየተወጡም ይገኛሉ።
እንደዚሁም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከመንግሥት ልማት ድርጅቶች የብድር አሰጣጥና አመላለስ ጋር በተፈጠረው ችግር እና ሌሎችም ችግሮች ተደምሮበት ለከፍተኛ የገንዘብ እጥረት ችግር (Liquidity Crisis) በመጋለጡ የተነሣ፣ የአገር በቀል የኢኮኖሚ ፕሮግራምን በፋይናንስ ለመደገፍ ተቸግሮ በነበረበት ወቅት፣ ይህንኑ ችግር እንዲያስተካክሉና ባንኩን ሪፎርም (ትራንስፎርም) እንዲያደርጉ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እኒህን ሰው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አድርገው መድበዋቸዋል።
እርሳቸውም ከባንኩ የቦርድ አባላት እና አዲስ ከተሾሙት ፕሬዚዳንትና ከማኔጅመንት አባላት ጋር ሥራዎች በቅንጅት እንዲከናወኑ በማድረጋቸው ከሁለት ዓመት በፊት የባንኩን ህልውና ሲፈታተኑ የነበሩት በርካታ ችግሮች ተፈትተዋል። በዚህም ባንኩ ለአገራችን የኢኮኖሚ ዕድገትና ልማት የሚያበረክተውን አስተዋጽዖ በተገቢ ሁኔታ እየተወጣ እና በሁሉም መስክ የተሻለ አፈጻጸም እያስመዘገበ ይገኛል።
እኒህ ሰው በአሁኑ ጊዜ ባንኩን ሪፎርም (ትራንስፎርም) ለማድረግ ሥራዎችን በታቀደው መሠረት በማከናወን ላይ ይገኛሉ። ምንም እንኳን ብዙ ሥራዎች የሚጠበቁ ቢሆንም፣ እነዚህ የተጠቀሱት አፈጻጸሞች በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲመዘገቡ በማድረግ ረገድ የእርሳቸው ሚና የላቀ ነው።
ባንኩ አሁን ባለበት ጥሩ ቁመና ላይ እንዲገኝ እርሳቸው የአንበሳውን ድርሻ ተጫውተዋል። በተጨማሪ የዋናው መ/ቤት ሕንፃ በተቀመጠለት ጊዜ እና ጥራት እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ ክትትል እና ድጋፍ ሲያደርጉ ነበር።
ኮሚቴው እነዚህን በማገናዘብ በባንኩ 80ኛ ዓመት በዓል እና በምሥራቅ አፍሪካ ተወዳዳሪ እንደሌለው በሚነገረው የዋናው መ/ቤት ሕንፃ ምርቃት ቀን፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ ተሸላሚ ሆነው እና ላበረከቱት አስተዋጽኦ ዕውቅና እንዲሰጣቸው ኮሚቴው ያቀረባቸው እኒህ ታላቅ ሰው ክቡር አቶ ተክለ ወልድ አጥናፉ ናቸው።
- ዶ/ር ተፈራ ደግፌ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በረዥም ታሪኩ ውስጥ ካናዳዊና አሜሪካውያን ኃላፊዎች በበላይነት መርተውታል። ከተለያዩ አገሮች የመጡ ዜጎች (ሕንዳውያን፣ አርመኖች፣ ግብጻውያንና አውሮፓውያን) ባንኩ በተቋቋመባቸው ዘመናት በባንኩ የኃላፊነት ቦታዎችና የተለያዩ የሥራ መደቦች ላይ በተዋረድ በኃላፊነት ሠርተዋል።
የባንኩን የኃላፊነት ቦታዎች ከውጭ አገር ዜጎች እጅ በማውጣት በኢትዮጵያውያን የመተካቱ ሂደት ደረጃ በደረጃ የተከናወነና አገራዊ ፋይዳ የነበረው ከፍ ያለ መስዋዕትነት የተከፈለበት ነው። በዚህ የትግል ሂደት ውስጥ ባስገኙት ከፍተኛ ውጤት ስማቸው የሚዘከር አንድ ታላቅ ሰው አሉ።
እኒህ ታላቅ ሰው፤ ከትምህርት ዓለም በተለያዩ መስኮች ዲፕሎማዎችንና የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ካገኙ በኋላ ሥራቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1958 ዓ.ም ነበር። በካርቱም አዲስ የተከፈተው የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ ሆነው ሥራ ጀመሩ። ይህ ሹመት ቅድሚያ የተሰጠው ሥራዎችን ለማደራጀት እና ተወዳዳሪ ለመሆን ሲሆን ዓላማው በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል የሚደረገውን ንግድ የማስፋፋት መርሐ ግብር መደገፍ ነበር። እ.አ.አ በ1961 ዓ.ም. ወደ የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ ሥራ አስኪያጅነት የሥራ መደብ ዕድገት ያገኙ ሲሆን በዚያ የሥራ መደብ ላይ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ነበሩ።
እ.አ.አ በ1963 ዓ.ም. ሐምሌ ወር በተጠናቀቀው የባንክ ማሻሻያ ላይ በንቃት ተሳትፈዋል። ይህንን ጥናት ተከትሎም እ.አ.አ ታህሣሥ 1963 ዓ.ም የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ ወደ ብሔራዊ ባንክ እና ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተከፈሉ። የመጀመሪያው ተቋም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የማዕከላዊ የባንኪንግ ደንቦችን እና አሠራሮችን የመቅረጽ ኃላፈነት ወሰደ።
ሁለተኛው ተቋም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የባንክ የንግድ ሥራ ጉዳዮች ላይ አተኮረ። እኒህ ታላቅ ሰው በዚህ ጊዜ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ተሾሙ። እ.አ.አ. በ1974 ዓ.ም. የባንኩ ቅርንጫፍ ወደ 100 አደገ። ባንኩም በአገሪቷ ውስጥ እንደ ዋና የፋይናንስ ተቋም የዓለም አቀፍ ዕውቅናን ተቸረ። እርሳቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት ሆነው ሲያገለግሉ እንደ እነዚህ ያሉ በርካታ የአመራር እንቅስቃሴዎች ታይተዋል።
• የኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ምሩቃን ባንኩን በተለያዩ የአመራር ቦታዎች ተመድበው የባንኩን አሠራር ለማዘመን የሚያስችል ዐቅም እንዲኖራቸው አድርገዋል፣
• የባንኩን የሪፖርት ሥርዓት አቋቁመዋል፤
• የተለያዩ የባንኪንግ አሠራርና የሥራ ማኑዋሎች አዘጋጅተዋል፤
• የባንኩን ካፒታል ማሻሻያ ከብር 20 ሚሊዮን ወደ 900 ሚሊዮን አሳድገዋል፤
• የቅርንጫፎቹን ቁጥር ከ21 ወደ 100 አሳድገዋል፤
• ለባንክ ባለሙያዎች ማሠልጠኛ ማዕከል እንዲቋቋም የበኩላቸውን አበርክተዋል፤
• የተለያዩ የባንኩ ሠራተኞችን በባንኩ ማሠልጠኛ ማዕከል ሥልጠና እንዲያገኙ አስችለዋል፤
በ1966 ዓ.ም አብዮት በፈነዳበት ወቅት እኒህ የባንክ ፕሬዚዳንት የብሔራዊ ባንክ ገዥ ሆነው ተሾሙ። በወታደራዊ መንግሥት አስቸጋሪ የሽግግር ወቅትም ለአምስት ዓመት ከሰባት ወራት የፖለቲካ እሥረኛ ሆነው ነበር። እ.አ.አ በ1982ዓ.ም ከኢትዮጵያ የወጡ ሲሆን፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በስደት በውጭ አገር ኖረዋል። እ.አ.አ. በ1994 ዓ.ም በ68 ዓመታቸው ጡረታ ከመውጣታቸው በፊት እ.አ.አ. ከ1982 እስከ 1994 ዓ.ም በስዋዚላንድ እና በዚምባቡዌ ውስጥ የፋይናንስ አማካሪ እና የባንኪንግ አማካሪ ሆነው ሠርተዋል።
ማንበብ ስለሚወዱ፤ በአማርኛ፣ በእንግሊዝኛ፣ በፈረንሳይኛ፣ በጣሊያንኛ እና በሩሲያኛ ቋንቋዎች የተዘጋጁ ብዙ መጽሐፍት አሰባስበዋል። ለንግድ እና ለሙያ ጆርናሎች ሙያዊ ጽሑፎችን ከማበርከት በተጨማሪ በዓለም አቀፍ የባንኪንግ እና የኢኮኖሚ መድረኮች ላይ በተደጋጋሚ ንግግር አድርገዋል። እ.አ.አ በ1959 ዓ.ም “Capital Formation in Ethiopia” የሚል ድርሰት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ድጋፍ የጻፉ ሲሆን ድርሰቱ ጠቃሚ ሃሳቦች ቀርበውበታል። እኒህ ታላቅ ሰው የሦስት መጻሕፍት ደራሲ ናቸው፡- A Guide to Serve – a collection of speeches; A Tripping Stone – an Ethiopian prison diary; and Minutes of an Ethiopian Century – recollection of key events in Ethiopia and a life of service.
እኒህ ታላቅ የኢትዮጵያ ባንክ ባለውለታ እ.ኤ.አ በመጋቢት 8 ቀን 2015ዓ.ም በ89 ዓመታቸው አርፈዋል። ሁለቱ ልጆቻቸው በካናዳ አገር የሚኖሩ ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማ በ3,600 ስኩየር ሜትር ላይ የሚገኘውን የመኖሪያ ሕንፃቸውን ልጆቹ በአባታቸው ቃል መሠረት ለሐምሊን የፊስቱላ ሆስፒታል በስጦታ አበርክተውላቸዋል። ልጆቻቸው አባታቸውን ወክለው በዚህ የባንካችን ታላቅ በዓል እንዲገኙ ያደረግነው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።
በመሆኑም ለአገራችን ዕድገት እና ኢኮኖሚያዊ ልማት እንዲሁም ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁለንተናዊ ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋጽዖ በማበርከታቸው ኮሚቴው በ80ኛ ዓመት በዓልና በዋናው መ/ቤት ሕንፃ የምረቃ ቀን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እጅ ልዩ ሽልማትና ዕውቅና እንዲሰጣቸው ያቀረባቸው እኒህ ታላቅ የኢትዮጵያ የባንክ ዕድገት ባለ ውለታ ዶክተር ተፈራ ደግፌ ይባላሉ።
- አቶ ዓለሙ አበራ
በቀድሞው የሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት በባሌ አውራጃ ጊኒር ከተማ ተወለዱ። የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በጊኒር መኩሪያ ተሰማ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። በዘመኑ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በአካባቢው ባለመኖሩ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ካዛንችስ አካባቢ በሚገኘው በቀድሞው የአስፋው ወሰን 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ተምረው ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ወደ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ገቡ። በዩኒቨርሲቲውም በቢዝነስ ትምህርት ክፍል ከመጀመሪያዎቹ ተማሪዎች አንዱ ሆነው በንግድ ሥራ አመራር እና በሕግ ዲግሪያቸውን አገኙ። ለተጨማሪ ትምህርት ወደ ስዊድን በመሄድም በባንኪንግ የትምህርት መስክ ተጨማሪ ዕውቀት ቀስመው ተመልሰዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በወቅቱ ከዩኒቨርሲቲ በላቀ ውጤት የሚመረቁ ተማሪዎች ለማግኘት የሥራ ዕድል ይሰጥ ስለነበር የመጨረሻ ዓመት ተማሪ ሳሉ ባገኙት የትርፍ ሰዓት የሥራ ዕድል አማካኝነት ከባንኩ አሠራር ጋር ለመተዋወቅ ቻሉ። በመስከረም 1959 ዓ.ም የባንኩ ቋሚ ሠራተኛ ሆነው በኦርጋናይዜሽን እና ሜተድስ ክፍል ውስጥ ጀማሪ የባንክ ባለሙያ ሆነው ተቀጠሩ።
እኒህ ሰው በከፍተኛ አመራርነት የባንኩን ተቀማጭ ገንዘብ ለማሳደግና የቅርንጫፎች ሥርጭት ለማስፋፋት ያደረጓቸው ጥረቶች የሚጠቀሱ ናቸው። በኃላፊት ዘመናቸው ባንኩ ገጥሞት የነበረውን ከፍተኛ የሠለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ለመቋቋም የተለያዩ አማራጮችን ሥራ ላይ በማዋል አገልግሎት እንዳይስተጓጎል ማድረጋቸው ይታወቃል። ከእዚህም ባሻገር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የውጭ አገር የባንክና የንግድ አገልግሎቱ በተሻለ ደረጃ ውጤታማ እንዲሆን የተደረገው ጥረት ከፍተኛ ሲሆኑ ለእዚህም የተለያዩ ተቋማት ለባንኩ ዕውቅና መስጠት አስችሏቸዋል።
እርሳቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት በነበሩባቸው ጊዜያት በርካታ ሥራዎችን አከናውነዋል። ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል:-
- ከደርግ መንግሥት በፊት የግል ባንኮች የነበሩት በደርግ ተወርሰው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር እንዲዋሐዱ ሲደረግ የተለያዩ የሥራ ዲሲፒሊን እና አሠራር ይዘው የመጡትን ሠራተኞችና የማኔጅመንት አባላት አንድ በማድረግ የባንክ ሥራ እንዲቀጥል በማስቻል በኩል ከፍተኛ የመሪነት ሚና ተጫውተዋል፣
- በጣም ጥቂት የነበሩት የባንክ ቅርንጫፎች እንዲስፋፉ ጥረት አድርገዋል።
- የደርግ መንግሥት የሶሻሊስት ርእዮተ ዓለም እከተላለሁ ሲል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሌሎች ዓለም አቀፍ ባንኮች ጫና ደርሶበት፣ በጥሩ ሁኔታ ላይ የነበረው የባንኮች ግንኙነት (Correspondent Banking Relation) እንዳይበላሽ ለማድረግ ልዩ ጥበብ በመጠቀም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጠንካራ የCorrespondent Banking Relation እንዲኖር ከፍተኛ ሥራ ሠርተዋል።
- በርካታ የባንኩ ሠራተኞች እና የማኔጅመንት አባላት በዓለም አንቱ በተባሉ የንግድ ባንኮች ኢንስትቲዩሽኖች ውስጥ የአጭርና የመካከለኛ ጊዜ ሥልጠና እንዲያገኙ እንዲሁም on the job training program ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርገዋል። በመሆኑም የባንኩ ማኔጅመንት እና ሠራተኞች ከዓለም አቀፍ የባንክ ሥራ ጋር እንዲለማመዱ እና ዕውቀታቸውን እንዲያጎለብቱ ረድቷቸዋል።
- እንደዚሁም ኤክስፖርት እና ኢምፖርት ካለምንም እንከንና ጥርጣሬ በተቀላጠፈ መንገድ በውጭ ትላልቅ ባንኮች በኩል እንዲስተናገዱ አድርገዋል።
እኒህ ታላቅ ሰው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከነበራቸው የአገልግሎት ዘመን በመቀጠል የዳበረ የባንክ ሥራ ልምዳቸውን ለተለያዩ የአፍሪካ አገሮች በማጋራት የመሪነት አሻራቸውን ማኖር ችለዋል። በደቡባዊ አፍሪካ የሌሴቶ ብሔራዊ ባንክ ሥራ አስኪያጅ ሆነው በመሥራት አገሪቱ የነበረባትን የፋይናንስ ችግር ማስተካከል ችለዋል። የዩጋንዳ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት በነበሩበትም ወቅት ባንኩን ከገባበት ቀውስ በማውጣት ትርፋማ ሆኖ እንዲቀጥል አስችለዋል። በታንዛንያም የብሔራዊው ባንክ ገዥ ዋና አማካሪ በመሆን ለ8 ዓመታት አገልግለዋል።
እኒህ ታላቅ የባንክ ሰው አሁንም በሥራ ላይ ናቸው። ዕረፍት የማያውቁት ብርቱ ሰው ሥራ በቃኝ አላሉም። በጎረቤት አገር ደቡብ ሱዳን ከሚገኙት የአገሪቱ ባንኮች አንዱ የሆነውን ቡፋሎ ንግድ ባንክ በፕሬዚዳንትነት እየመሩ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሥራዎች በደርግ መንግሥት ወቅት እንደ ሌሎች የሶሻሊስት አገሮች ባንኮች ከዓለም አቀፍ ባንኮች እንዳይነጠል አድርገውታል። ከመነጠል ይልቅ የተጠናከረ ግንኙነት እንዲኖረው በማድረጋቸው ከደርግ ውድቀት በኋላ ምንም ችግር ሳይገጥመው International Banking Business እንዲቀጥል አስችለውታል። በዚህም አገራችን በወቅቱ ከገጠማት ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንድትወጣ ከፍተኛ ድርሻ በመጫወት ለኢኮኖሚ ልማት የበኩላቸውን አስተዋጽዖ በማበርከታቸው ኮሚቴው በ80ኛ ዓመት በዓልና በዋናው መ/ቤት ሕንፃ ምረቃ ቀን በጠቅላይ ሚኒስትር እጅ ልዩ ሽልማትና ዕውቅና እንዲሰጣቸው ያቀረባቸው እኒህ ታላቅ የባንክ መሪ ክቡር አቶ ዓለሙ አበራ ይባላሉ።
- አቶ ጥላሁን ዓባይ
በቀድሞው ትግራይ ጠቅላይ ግዛት በአብርሃ ወአጽብሐና በዱግም ቀበሌ መካከል በምትገኘው ዐቢይአዲ በምትባል መንደር ውስጥ ተወለዱ። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በአሰላ የራስ ዳርጌ ት/ቤት፤ የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በይርጋለም የራስ ደስታ ት/ቤት ተከታትለዋል። አዲስ አበባ በመምጣት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተከታትለው በከፍተኛ ውጤት አጠናቅቀዋል።
በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተከፍቶ ስለነበረው የቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን በመደበኛ ተማሪነት ተመዝግበው በሐምሌ 1956 ዓ.ም በቢዝነስ ማኔጅመንት ተመረቁ።
እኒህ ሰው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የማኔጅመንት ሠልጣኝ ደረጃ በ1957 ዓ.ም ተቀጠሩ። በነበራቸው የሥራ ትጋትና ታታሪነት በተለያዩ የባንኩ ክፍሎች የኃላፊነት ደረጃዎች ከባለሙያነት እስከ ፕሬዚዳንትነት ደረጃ በዘለቀ ስኬት ለ37 ዓመታት አገልግለዋል።
እኒህ ታላቅ ባለሙያ ባንኩን ለ11 ዓመታት ያህል በፕሬዚዳንትነት መርተዋል። በእዚህ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊነት ላይ ሳሉ የተለያዩ አሠራሮችን በመተግበር ባንኩ በዕድገት ጎዳና እንዲጓዝ አድርገውታል። ከዚህም በላይ ዛሬ ላይ ለተደረሰበት ደረጃ የራሳቸውን አስተዋጽዖ እንዳኖሩ በርካቶች ይመሰክራሉ። የመጀመሪያው ኢትዮጵያ ባንኮች ማህበር ፕሬዚዳንት በመሆንም ለ10 ዓመታት ሠርተዋል።
እኒህ ታላቅ ሰው፤ በአገልግሎት ዘመናቸው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሌላ የተለያዩ ተቋማትንና ድርጅቶችን መርተዋል። የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) አገራት የባንኮች ማህበራትን ከምሥረታ ጀምሮ የቦርድ ዳይሬክተር በመሆን ለአምስት ዓመታት አገልግለዋል።
የመተሐራ ስኳር ፋብሪካና የቀድሞው የኢትዮጵያ መርከብ ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ ሆነው ከመሥራታቸውም በላይ መቀመጫውን ካይሮ ባደረገው የአፍሪካ ኤክስፖርትና ኢምፖርት ባንክ የቦርድ ዳይሬክተር፣ የኢንቨስትመንትና የቅርንጫፍ ሥርጭት ቦርድ አባል ሆነው ለ9 ዓመታት አገልግለዋል። ኢኒህ ታላቅ ሰው፤ ላበረከቱት የረዥም ዘመን የላቀ አስተዋጽዖ የአፍሪካ ኤክስፖርትና ኢምፖርት ባንክ የወርቅ ሜዳሊያ ሽልማት አበርክቶላቸዋል።
እኒህ ታላቅ ሰው፤ ዛሬም ለባንክ ኢንዱስትሪ የሚቻላቸውን በማበርከት ላይ ይገኛሉ። በምሥረታ ላይ ያሉ የተለያዩ ተቋማትንም በፋይናንስ አማካሪነት፣ በፕሮጀክት ኮሚቴና በቦርድ አመራር አባልነት በቅርበት ያማክራሉ።
እርሳቸው ለኢትዮጵያ የባንክ ዕድገት ካበረከቱት መካከል ጥቂቱን ለመጥቀስ ያህል፡-
- ፕሬዚዳንት ከመሆናቸው በፊት ባንኩ ብድሮችን በአዲስ አበባ እና በሌሎች ጥቂት ትላልቅ ከተሞች ለተወሰኑት ትላልቅ ነጋዴዎችና ሥራ ፈጣሪዎች ይሰጥ ነበር። እርሳቸው ግን ይህንኑ አካሄድ በመቀየር ብድሩ በሁሉም ቅርንጫፎች በኩል እንዲሰጥ ከማድረጋቸውም ባሻገር የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ፣ የመካከለኛ እና ከፍተኛ ኢንተርፕራይዞች፣ በአገር ውስጥና በውጭ ንግድ የተሠማሩ ነጋዴዎች የመለስተኛ፣ መካከለኛ እና ከፍተኛ ኮንትራክተሮች፤ ለግለሰብ የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ብድሮች እንዲሰጡ በማድረግ የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋፋት ጥረት አድርገዋል።
- ይህን በማድረጋቸው በአራጣ አበዳሪዎች ሲሰቃዩ የነበሩ በርካታ ዜጎች እፎይታ ከማግኘታቸው ባሻገር፣ ከባንክ አገልግሎት ጋር ብዙ ዜጎች ራሳቸውን እንዲያስተዋውቁ እገዛ አድርጓል። የዚህ ፕሮግራም ተጠቃሚ የነበሩና በወቅቱ በጣም በአነስተኛ ደረጃ የነበሩ ዜጎች በአሁኑ ጊዜ አንቱ የተባሉ ኤክስፖርተሮች፣ ኢምፖርተሮች፣ ኮንትራክተሮች፣ የባለ ኮከብ ሆቴል ባለቤቶች ሆነው ለአገራችን የኢኮኖሚ ልማት ድርሻቸውን እየተወጡ ይገኛሉ።
- ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ባደረገችው ጦርነት ማግሥት የአገራችን ኢኮኖሚ በጣም የደቀቀበት ጊዜ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ከዓለም ባንክና ከዓለም የገንዘብ ድርጅቶች /IMF/ ጋር የነበረው ፕሮግራም የተቋረጠበት እና የዓለም አገራት ጀርባቸውን የሰጡበት ወቅት ነበረ። በመሆኑም የአገራችን የውጭ ምንዛሪ ተቀማጭ (ሪዘርቭ) ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ተሟጦ ነበር። በመሆኑም የውጭ ምንዛሪ ማግኘት የሞትና የሽረት የሆነበት ጊዜ ስለነበር የወቅቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት የነበሩት እኒህ ሰው በጋራ የውጭ ምንዛሪ ብድር ለማግኘት ለተለያዩ የዓለም ትላልቅ ባንኮች ጥያቄ አቅርበዋል፤ ብዙ ወራትን በጉዞ አሳልፈዋል። ነገር ግን ማንም ፈቃደኛ ሊሆን አልቻለም ነበር። በዋናነት ሲያቀርቡት የነበረው ምክንያት ለብድር ማስያዣ የሚሆን ነዳጅ ወይም ወርቅ ወይም ሌሎች የከበሩ ማዕድናት ስለሌላችሁ ብድር ለመስጠት እንቸገራለን የሚል ነበር።
- ሆኖም በመጨረሻ ከአንድ ባንክ ጋር በሚሠራ አንድ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅት /Money Transfer Operation/ በኩል የሚመጣውን /Remittance/ ማስያዣ በመስጠት፣ ከአንድ ትልቅ ባንክ ብዙ መቶ ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ብድር ለማግኘት ተችሏል። የውጭ ምንዛሪ በመገኘቱ እና የብሔራዊ ባንክ መጠባበቂያ ገንዘብ በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ በኢኮኖሚ ልማት ላይ ያንዣበበው አስጊ ደመና እንዲገፈፍ ሆኗል። በዚህ ሂደት እኒህ ታላቅ ሰው የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወስዱ አቶ ተክለ ወልድ ይመሰክሩላቸዋል።
- በወቅቱ ከነበሩት ም/ፕሬዚዳንቶች ጋር በመሆን፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ /successor Program/ በመቅረጽ፣ በሺህ የሚቆጠሩ ወጣት ምሩቃንን በመመልመል፣ አጫጭርና መካከለኛ የሥልጠና ፕሮግራሞችንና /on the job training/ በመንደፍ ተግባራዊ በማድረግ፣ ወደ ሥራ በማስገባታቸው ባጭር ጊዜ ውስጥ የተለያዩ ቦታዎች በሠልጣኝ ምሩቃን እንዲሞሉ በማድረግ የመተካካት ዕቅዱ እንዲሳካ አድርገዋል። የአሁኑ እና የቀድሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንቶች እና አብዛኛዎቹ ም/ፕሬዚዳንቶች እንዲሁም የግል ባንኮች ፕሬዚዳንቶች እና አብዛኛዎቹ ም/ፕሬዚዳንቶች የእኒህ ታላቅ ሰው የምልመላና ሥልጠና ፕሮግራም ውጤቶች ናቸው።
በመሆኑም እኒህ ታላቅ የባንክ መሪ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካበረከቱት አገልግሎት በተጨማሪ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለአጠቃላይ የፋይናንስ ዘርፉ ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋጽዖ በማበርከታቸው፤ እንዲሁም አገራችን የውጭ ምንዛሪ ቀውስ በገጠማት ወቅትም ከቀውስ እንድትወጣ ከፍተኛ ድርሻ በመጫወት ለኢኮኖሚ ልማት የበኩላቸውን ሚና በመጫወታቸው፤ ኮሚቴው በ80ኛ ዓመት በዓልና በዋናው መ/ቤት ሕንፃ የምረቃ ቀን በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እጅ ልዩ ሽልማትና ዕውቅና እንዲሰጣቸው ያቀረባቸው እኒህ ታላቅ ሰው – ክቡር አቶ ጥላሁን ዓባይ ይባላሉ።
አዲስ ዘመን የካቲት 8/2014