ከአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና መመስረቻ ሥምምነት የተገኘው ሰነድ እንደሚያስረዳው፤ የአፍሪካ አህጉራዊ ውህደት ራዕይ እ.ኤ.አ ግንቦት 1963 የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲቋቋም ጀምሮ የነበረ ነው፡፡ ምንም እንኳን ውጤታቸው አመርቂ ባይሆንም ይህንን ራዕይ ዕውን ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶች ተደርገዋል። ከዚህም ባሻገር እ.ኤ.አ. በሰኔ 1991 ዓ.ም በተፈረመው የአቡጃ ስምምነት ላይ የአካባቢያዊ ውህደት ለአፍሪካ ልማት ግቦች ቁልፍ እንደሆነ ጎልቶ ቢቀመጥም በተለያዩ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች የተነሳ ግቦቹን ለማሳካት የተደረጉ ጥረቶች ፍሬ ሳያፈሩ ቆይተዋል፡፡
እነዚህ ሂደቶች እንዳሉ ሆነው ለአፍሪካ በንግድ ቀጣና መተሳሰር የግድ የሚለው ጊዜ ላይ መደረሱን የሚጠቁሙ መረጃዎች በስፋት እየወጡና ነባራዊ ሁኔታዎችም እንደሚያስገድዱ እየተስተዋለ ነው፡፡ ለመሆኑ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ፈተናዎች እና መፃዒ ዕድሎች ምንድን ናቸው? ለስኬቱ ምን መደረግ አለበት? ለአገራትና ለአህጉሪቱ ፋይዳውና ፈተናዎቹስ ምንድን ናቸው? በሚለው ላይ በተለያዩ ወቅቶች ይፋ የሆኑ መረጃዎችን ማጣቀስ ተገቢ ይሆናል፡፡ ቢቢሲ፣ ዓልአይን፣ የአገር ውስጥ የመገናኛ ብዙኃን፣ የባለሙያዎች ትንታኔ፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ የተለያዩ ምሁራን እና የምጣኔ ሀብትን የሚሰንዱ አካላትንና ተቋማትን የመረጃ ምንጮችን በዋቢነት በመጠቀም የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ፈታናዎችና መፃዒ ዕድሎች እንደሚከተለው ይዳሰሳል፡፡
የአፍሪካ አገራት የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናን ዓላማ ለማሳካት በብርቱ በመሥራታቸው እ.ኤ.አ የካቲት 21 ቀን 2018 ዓ.ም የአፍሪካ ኅብረት አባል አገራት መሪዎች በሩዋንዳ በመገኘት የአፍሪካ አህጉራዊ የነፃ ንግድ ቀጣና መመስረቻ ተፈራርመዋል፡፡ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና መመስረቻ ሥምምነት የተገኘው ሰነድ እንደሚያብራራው፤ በአፍሪካ አገራት መካከል የሚካሄደው የእርስ በእርስ ንግድ በእጅጉ ዝቅተኛ በመሆኑና አካባቢያዊ የኢኮኖሚ ማህበረሰቦች የአካባቢያዊ ንግድን ለማጠናከር ቅድሚያ ትኩረት ባለመስጠታቸው ነው፡፡ ባለፉት ሃያ ዓመታት የአፍሪካ የእርስ በእርስ ንግድን ለማሻሻል ጥረቶች ቢደረጉም በአማካይ ከ15 በመቶ በላይ መሆን አልቻለም፡፡ አህጉሩ በዋነኛነት በጥሬ ዕቃዎች ላይ ጥገኛ መሆኑና የኢንዱስትሪው ዘርፍ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ መገኘቱ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ በአማካይ 26 በመቶ የአፍሪካ አገራት አንድ ወይም ሁለት ሸቀጦች 75 በመቶ የሚሆነውን የወጪ ምርታቸውን ይሸፍናል፡፡ 60 በመቶ የሚሆኑት የአፍሪካ አገራት ደግሞ በአምስት ሸቀጦች ብቻ ላይ ጥገኛ መሆናቸውንም ያብራራል፡፡
አፍሪካ ከአንድ ነጥብ 27 ቢሊዮን በ2030 ዓ.ም ወደ አንድ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን እና በ2050 ዓ.ም ወደ ሁለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን የሚያድግ ሕዝብ ሲኖራት፤ አፍሪካ ሁለተኛዋ ትልቅ አህጉር ትሆናለች፡፡ የዚህ ሥምምነት አካል ሆና አፍሪካዊነትን በማቀንቀን ቀዳሚ የሆነችው ኢትዮጵያ በተመሳሳይ ወደ ውጭ ከምትልካቸው ዕቃዎች በአማካይ ከ20 በመቶ የማያንሱት በአብዛኛው የግብርና ምርቶች መዳረሻቸው የአፍሪካ አገራት ሲሆኑ በሌላ በኩል ከአፍሪካ አገራት የምታስገባው የውጭ ንግድ መጠን በአማካይ አራት በመቶ ያልበለጠ ነው።
በሌላ በኩል በአህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና አባልነት ጋር በተያያዘ ሊያጋጥሙ የሚችሉትን ስጋቶች በመቀነስ ረገድ በአገር ውስጥ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች እና አምራቾች ያልተገባ ጫና እና ጉዳት እንዳይደርሳባቸው በስምምነቱ የሚገባውን ግዴታ መጠን በመገደብ፣ ረዘም ባለ የትግበራ ጊዜ በመተግበር፣ አገሪቱ በምትፈልገው መንገድ እና ፍጥነት እንዲሆን እየተሠራ ይገኛል። በዚህም መሠረት ከነፃ የንግድ ቀጣናው የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እየሰፋ የፖሊሲ ነፃነትን በማሳደግ በኢኮኖሚ ላይ የሚያስከትለውን ጫና መቋቋም የሚቻልበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡
የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት ሁሉንም ኅብረተሰብ ክፍሎችና አጠቃላይ ኢኮኖሚው ላይ ባለው ግንኙነት በእስካሁኑ ሂደት የተለያዩ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ክፍሎችን የግንዛቤ ማስጨበጫዎች አቅም በፈቀደ መጠን ተካሂዷል።
የግሉ ዘርፍም ለሂደቱ አስተዋጽኦ በማበርከት ፍላጎቱ እንዲካተት እና ተጠቃሚነቱ እንዲያድግ እንዲሁም ስጋቱ እንዲቀነስ የሚያደርጉ ሀሳቦችን ለማካተት ተሞክሯል፡፡ በተጨማሪም ሥምምነቱ የሚያመጣቸው ዕድሎችን በስፋት ተጠቃሚ ሊያደርጉ የሚያስችሉና ለተወዳዳሪነት ዝግጁ የሚያደርጉና ለቀጣይ ድርድሮች ግብአቶችና ፍላጎቶችን ለማካተት የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችና አሠራሮች ወደፊት በስፋት ተጠናክረው የሚቀጥሉ ይሆናል፡፡
የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ፋይዳዎች የዓለም ንግድ ድርጅት እ.አ.አ በ1994 ከተመሠረተ በኋላ በምጣኔ ሀብታዊ ፋይዳው ታላቅ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ከ1ነጥብ3 ቢሊዮን በላይ ሕዝቦችን ከ3ነጥብ4 ትሪሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ በሆነ የንግድ ትስስር ያጎዳኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ እንደ አውሮፓ ኅብረት ዓይነት ቅርፅ ይዞ ለመንቀሳቀስ እያሰበ ያለው ይህ ቀጣና በአፍሪካ አገራት መካከል ድንበር የማያግዳቸው የንግድ ልውውጦች እንዲካሄዱ እንደሚያግዝ፤ አልፎም ግብር እና አስመጪዎች ላይ የሚጫነውን ቀረጥ በማስቀረት በአህጉሪቱ አገራት መካከል ያለውን ነፃ ዝውውር እንደሚያበረታታ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የወቅቱ ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት በበኩላቸው፤ የአፍሪካ አገራት የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናን ለመመስረት የተፈረመው ሥምምነቱን መልካም ፈተና መሆኑን በመጠቆም የስኬት ጥማት እንዲኖረን እና ድፍረት እንድናዳብር ኃይል ይሰጠናል ይላሉ። ለስምምነቱ መሳካት የአህጉሪቱ አገራት ፖለቲካዊ ልዩነቶቻቸውን ማጥበብ የግድ እንደሚላቸውም ያሳስባሉ፡፡
የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ምጣኔ ሀብት ኮሚሽን የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና መመስረቻ ሥምምነት እየተንደረደረበት ያለውን መንገድ በመመልከት፤ በሥምምነቱ 80 በመቶ በሚሆነው የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑት አነስተኛና መካከለኛ ተቋማት እንዲሁም 70 በመቶ መደበኛ ያልሆነ ድንበር ተሻጋሪ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሴቶች እና ወጣቶች ዋነኛ ተጠቃሚዎች ይሆናሉ የሚል እይታ አለው።
ዩናይትድ ኪንግደም የሌስተር ደሞንትፎርት ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ኤኮኖሚና የሕግ ፕሮፌሰሩ መላኩ ደስታ ዋቢ አድርጎ ትንታኔ ሃሳብን ያቀረበው ዶይች ቬሌ፤ አፍሪካ ወደዚህ መንደርደሯ እጅግ የሚበረታታ እና አህጉራዊ ዕድገትንና ስልጣኔን የበለጠ ለማስቀጠል ትልቅ ሚና እንዳለው ይጠቁማሉ፡፡
ነገር ግን ይህን ለማሳካት አፍሪካ ዘርፈ ብዙ ፈተናዎች እንዳሉባትም ያብራራሉ፡፡ ለአብነትም ሸቀጦች የተመረቱበትን አገር በማረጋገጥ በነፃ የንግድ ቀጣናው ለግብይት የሚቀርቡበትን ሥልት የሚደነግገው ሥርዓት (Rules of origin) በድርድር ከሥምምነት ያልተደረሰበት ቁልፍ ጉዳይ በመሆኑ አፍሪካን የሚፈታተናት አብይ ጉዳይ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ሌላኛው አፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ፈተና ደግሞ፤ የንግድ ቀጣናን የምሥራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) ከመሳሰሉት ክፍለ አህጉራዊ ተቋማት ጋር የማጣጣም ጉዳይም እጅግ ፈታኝ እንደሚሆን ያስረዳሉ፡፡ ክፍለ አህጉራዊዎቹ ተቋማት በተቀናጀ መንገድ ወደ አንድ አቅጣጫ ሔደው የአፍሪካን የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መፍጠር አለመቻሉንም ከተግዳሮቶቹ ውስጥ መሆናቸውን ፕሮፌሰሩ ያብራራሉ፡፡ በተመሳሳይ የአፍሪካ አገራት ወጥ የገበያ ሥርዓት የሚፈጥረው ሥምምነት ስኬታማ ይሆን ዘንድ ከአውሮፓ፣ ቻይና እና አሜሪካ በተናጠል የተፈራረሟቸው የንግድ ሥምምነቶች እና ወደፊት የሚያበጇቸው ተመሳሳይ ግንኙነቶች ምን መልክ እንደሚኖራቸው መፍትሔ ማበጀት አስፈላጊ መሆኑንም ያስገነዝባሉ።
ከዚህ ባሻገር ከታሪፍ ጋር በተያያዘ የማይገናኙ ጉዳዮች እና ፖለቲካዊ እንቅፋቶችም ፈተና መሆናቸው አይቀሬ ነው፡፡ በሙስና የተዘፈቁ ባለሥልጣናት አካባቢዎች ሕጋዊ ሰነድ የማግኘት ሒደትን ሊያዘገይ እንደሚችልም ምሁራን ይገልፃሉ፡፡ የአቅም ማነስ እና የክህሎት ጉዳይ ከፈተናዎቹ አንዱ ነው፡፡ ሁኔታዎች የታሪፍ ክፍያ ሥርዓት ወጥ ከሆነ በኋላ ሙስና የመፈጸም ዕድሉ ይቀንሳል። ነገር ግን የአቅም ማጣት እና የክህሎት ጉድለት የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናን የወደፊት ተግባራዊነት እና ስኬታማነት የሚገዳደሩ ፈተናዎች ሆነው እንደሚቀጥሉ ያመለክታል፡፡
የአፍሪካ አገራት የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናን ለመመስረት በሚደረገው መውተርተርና እልህ አስጨራሽ ትግሎች ውስጥ፤ አፍሪካ በቅኝ ግዛት የንግድ ሞዴል ተጠምዳ መቆየቷ እጅግ ፈታኝ ያደርገዋል እንደ ምሁራን ገለፃ፡፡ አፍሪካ ከዓለም ምጣኔ ሀብት ያላት ድርሻ ሦስት በመቶ ብቻ ሲሆን ወደ 55 ቦታ ተበጣጥሶ በመቆየቱ ለፈጣን አህጉራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ፈተና ሆኖ ቆይቷል፡፡ ቀኝ ግዛት ጠባሳም በአፍሪካ ላይ ጥሎ የሄደው ብዙ የቤት ሥራዎች ሲኖሩ፤ አገራት እርስ በራሳቸው ጥሩ ግንኙነት የሌላቸው በመሆኑ አንዱ በሌላው ላይ ድንበሮቻቸውን የዘጉ አገሮች ከአንዳች ውሳኔ ላይ መድረስ ግድ ይላቸዋል፤ ይህ ካልሆነ ግን ‹‹ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ ይሆናል›› ይላሉ የአፍሪካ አገራት የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናን ምስረታ መፃዒ ዕድሎችን በአንክሮ የሚከታተሉ ምሁራን፡፡
ታዲያ እነዚህን ፈተናዎችን መወጣት ከተቻለ እና የመፍትሄ ሃሳቦችን ወደ ተግባር መቀየር ከተቻለ፤ አፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ለኢትዮጵያም ሆነ ለአፍሪካ አገራት ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች እንዳሉትም ምሁራንና ተቋማት ይጠቁማሉ፡፡ በተለይም ለወጪ ምርቶች አስተማማኝ እና ሰፊ የገበያ ዕድሎችን መፍጠር፣ አማራጭ ምርቶችን በተሻለ ዋጋ እና ጥራት ማግኘት፣ የአካባቢያዊ የምርት ትስስር በመፍጠር በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪነት መጨመር፣ የአገር ውስጥ ኢንቨስትመንት መጠናከር እና ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰትን መጨመር የንግድ ቀጣናው ከሚሰጣቸው ዋና ዋና ጥቅሞች መካከል ስለመሆናቸው ያብራራሉ፡፡
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን የካቲት 8/2014