በዓለም አቀፍ ደረጃ ውጤታማ የሆኑ አትሌቶችን በማፍራት ከሚታወቁ ስፍራዎች መካከል አንዱ የሆነው ጃንሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ውድድር አትሌቶችን ከህልማቸው በማገናኘት ይታወቃል፡፡ የወቅቱ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ፣ ጌጤ ዋሚ፣ ብርሃኔ አደሬ፣ ወርቅነሽ ኪዳኔ፣ መሰለች መልካሙ፣ ገለቴ ቡርቃ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ ለተሰንበት ግደይና ሌሎችም የዚህ ውድድር ተሳታፊዎች ነበሩ፡፡ በወንዶች በኩልም በተመሳሳይ ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ፣ ገብረእግዚአብሄር ገብረማርያም፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ኢማና መርጋ እንዲሁም ሃጎስ ገብረህይወትም በዚህ ውድድር ውስጥ ካለፉ ከበርካታ አትሌቶች መካከል የሚጠቀሱ ብርቅዬ አትሌቶች ናቸው፡፡
እነዚህን እንቁዎች ያፈራው የጃንሜዳው ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ውድድር ዘንድሮም ጀማሪና ታዋቂ አትሌቶችን በተለያዩ ርቀቶች በማፎካከር ትናንት በጃንሜዳ ተካሂዷል፡፡
ይህ የዘንድሮው ውድድር ግን ከእስከ አሁኖቹ ሁሉ ይለያል፡፡ የሚለየውም ከጃንሜዳ ኢንተርናሽናል አቋራጭ ሻምፒዮና ውድድር በተጓዳኝ የምስራቅ አፍሪካ አገሮች አገር አቋራጭ ቻምፒዮናም ለመጀመሪያ ጊዜ በዚሁ በጃንሜዳ በመካሄዱ ነው፡፡ ይህንን ተከትሎም በውድድሩ ከኬንያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን እና ታንዛኒያ 14 አትሌቶች መሳተፋቸውን ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡ በ10 ኪሎ ሜትር ሴቶች ውድድርም የኤርትራ አትሌት የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ ልትገባ ችላለች፡፡
ባልተስተካከለ የመሬት አቀመማጥ እንዲሁም መሰናክሎች በሚበዛበት ስፍራ በሚካሄደው በዚህ ውድድር የሴቶች አዋቂ 10ኪሎ ሜትር አሸናፊ በመሆን የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ የሆነችው የኦሮሚያ ክልሏ አትሌት ጌጤ አለማየሁ ናት፡፡ አትሌቷ ጥሩ ፉክክር በታየበት በዚህ ውድድር አሸናፊ በመሆኗ መደሰቷን ገልጻለች፤ ከሶስት ዓመት በፊት በዚህ ውድድር ተሳትፋ ሁለተኛ በመሆን ማጠናቀቋን አስታውሳለች፡፡ በጃንሜዳ አሁን ለውድድሩ የተዘጋጀው መሰናክል ውድድሩን ከቀደሙት ጊዜያት ይበልጥ ፈታኝ እንዳደረገው ተናግራ፣ ውድድሩ ግን በጣም አስደሳች መሆኑን አስታውቃለች፡፡
በርካታ ታዋቂ አትሌቶች በተሳተፉበት የአዋቂ ወንዶች 10 ኪሎ ሜትር ሩጫ አሸናፊ የሆነው ደግሞ ከዚህ ቀደም ከ20 ዓመት በታች የወንዶች 8ኪሎ ሜትር ውድድር አሸናፊ የነበረው በሪሁ አረጋዊ ነው፡፡ የውድድሩ ባለድል በሰጠው አስተያየት በውድድሩ ጠንካራ አትሌቶች መሳተፋቸውን ጠቅሶ፣ ፉክክሩም ከፍተኛ እንደነበር ጠቁሟል፡፡ ጃንሜዳ የአየር ሁኔታው በራሱ ከባድ መሆኑን የተናገረው በሪሁ፣ ከባድ መሰናክሎች የነበሩበት መሆኑን እሱም አረጋግጧል፡፡ ለዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና ዝግጅት በማድረግ ላይ ሳለ በዚህ ውድድር ተሳታፊ እንደሚሆን ክለቡ ያሳወቀው መሆኑን ተከትሎ ለአንድ ሳምንት ጠንካራ ልምምድ ሲያደርግ መሰንበቱን ጠቅሶ፣ ልምምዱ አሸናፊ ያደረገው በመሆኑ መደሰቱን ይገልጻል፡፡ ይህ ውድድር እንደ እስከ አሁኑ ሁሉ በቀጣይም ጠንካራ አትሌቶች ተሳታፊ እንዲሆኑበት ቢደረግ መልካም እንደሚሆንም ጠቁሟል፡፡
ከውድድሩ ተሳታፊ አገራት መካከል አንዷ የሆነችው የሱዳን አትሌት አለውያ መኪ፤ በ10 ኪሎ ሜትር የአዋቂዎች ምድብ ተሳትፋለች፡፡ የ1 ሺ500 ሜትር ሯጯ አለውያ የምትሮጥበትን ርቀት ለመጨመር እየሰራች ሲሆን፤ ይህንን ውድድር የመረጠችውም ለዚሁ መሆኑን ትገልጻለች፡፡ የሩጫው ተሳታፊ አትሌቶች ጠንካራ እንዲሁም መሮጫውም ከባድ ቢሆንም አስደሳች ውድድር ማድረጓንና ልምድ ማግኘቷንም ጠቁማለች፡፡
በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተሳትፎና ውድድር ዳሬክተር አቶ አስፋው ዳኜ፤ ውድድሩ ትልቅ ፉክክር የተደረገበትና አስደናቂ እንደነበረ ይገልጻሉ፡ ፡ ሜዳውን ለውድድሩ አመቺ እንዲሆን ከማስተካከል ባለፈ ሰው ሰራሽ መሰናክሎችን በመስራት እንዲሁም አትሌቶችን አደጋ ላይ ሊጥሉ በሚችሉ ስፍራዎች ላይ አፈር በመሙላት ጭምር ዝግጅት መደረጉን ያስታውሳሉ፡፡
ዳይሬክተሩ እንዳሉት፤ በውድድሩም በርካታ አዳዲስ አትሌቶች የታዩበት ሲሆን፤ የጃንሜዳ አገር አቋራጭ ቻምፒዮናም የመጀመሪያው የምስራቅ አፍሪካ አገር አቋራጭ ቻምፒዮናም በስኬት ተጠናቀዋል፡፡
በተያዘው ዓመት መካሄድ የነበረባቸው የአህጉርና ዓለም አቀፍ የአገር አቋራጭ ቻምፒናዎች የተራዘሙ መሆናቸውን ጠቁመው፣ ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት እንዲሁም ክለቦች ራሳቸውን እንዲፈትሹ ለማስቻል ውድድሩን መካሄዱን አስታውቀዋል፡፡ በዚህ ውድድር ከወጣቶች ጀምሮ አሸናፊ የሚሆኑ አትሌቶች ዳጎስ ያለ የገንዘብ ሽልማት እንዲያገኙ በማድረግ አትሌቶችን ማበረታታት መቻሉን ተናግረው፣ በቀጣዩ ዓመታትም ውድድሮችን ማዘመን እንዲሁም ዓለም አቀፍ ይዘትን ማላበስ የፌዴሬሽኑ ዕቅድ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡
በወጣት ሴቶች 6 ኪሎ ሜትር፣ ወንዶች 8 ኪሎ ሜትር፣ በሁለቱም ጾታ አዋቂዎች 10 ኪሎ ሜትር፣ 8 ኪሎ ሜትር ድብልቅ ሪሌ እንዲሁም በሁለቱም ጾታ አንጋፋዎች በተደረጉ ውድድሮች አሸናፊ የሆኑ አትሌቶችም በግል ሜዳሊያ እንዲሁም በቡድን ከዋንጫ ሽልማት ባለፈ ከአንድ እስከ ስድስት ባለው ደረጃ ላጠናቀቁት የገንዘብ ማበረታቻ ተበርክቶላቸዋል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን የካቲት 7 ቀን 2014 ዓ.ም