
አዲስ አበባ፡- የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ በአገሪቱ በክህሎት ላይ ብቻ የተመሰረተ የስራ ቪዛ እንዲሰጥ የሚያዘውን ሕግ አጸደቁ።
አገሪቱ የኢሚግሬሽን ሕጎቿን እያጠናከረች ሲሆን፥ ፕሬዚዳንቱ የተሻሻለውን የወሳኝ ክህሎት የስራ ቪዛ ማፅደቃቸው በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የውጭ አገራት ሰራተኞችን አገሪቱን እንዲለቁ ያደርጋል ነው የተባለው፡፡
በተለይም በውጭ አገር ዜጎች የተያዙት አስተናጋጅነት፣ አነስተኛ ንግዶችን ማስኬድ፣ የሱቅ ንግድ እና በጤና እና ውበት ኢንዱስትሪ ውስጥ መስራትን ጨምሮ አንዳንድ ስራዎች አሁን ለደቡብ አፍሪካ ዜጎች ብቻ የተተዉ ይሆናሉ ተብሏል።
ወደ 3 ሚሊዮን የሚገመቱ የውጭ አገር ዜጎች በደቡብ አፍሪካ ያለ በቂ ሰነድ በህገ ወጥ መንገድ እየሰሩ ነው የተባለ ሲሆን፥ ይህም ከስራ ገበያ እየተገፉ እንደሆነ የሚሰማቸውን የአገሪቱ ነዋሪዎች አስቆጥቷል።
በአሁኑ ጊዜ በቀድሞ የአገር ውስጥ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል ማቩሶ ምሲማንግ የሚመራው የስራ ቪዛ ሥርዓት አጠቃላይ ግምገማ በመካሄድ ላይ ነው ተብሏል።
በዚህ አዲስ የቪዛ ሕግ 200 ሺህ የሚሆኑ ዜጎች በደቡብ አፍሪካ ባላት ዚምባብዌ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እንደሚኖረው ተመልክቷል።
በፀደቀው አዲስ የቪዛ ሕግ መሰረት በአገሪቱ መቆየት የማይችሉ የውጭ አገራት ዜጎች እስከያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት 2022 መጨረሻ ድረስ አገሪቱን ለቀው መውጣት እንደሚጠበቅባቸው ኒውስ 24 ዘግቧል። አዲስ ዘመን የካቲት 7 ቀን 2014 ዓ.ም