የአዲስ አበባ ከተማ ስሟን የምትመጥን ትሆን ዘንድ የተለያዩ ጥረቶች በመደረግ ላይ ናቸው።ከዚህም ጎን ለጎን ከተማዋ ላይ የሚስተዋሉ የመኖሪያ ቤት እጥረት የኑሮ ውድነትንና ሌሎች ችግሮች ተፈተው ለነዋሪዎቿ ምቹ ትሆን ዘንድም የከተማ አስተዳደሩ የጀመራቸው ስራዎች ስለመኖራቸው በተለያዩ ጊዜያት ይነገራል ።እኛም ከተማዋ ሰላሟ የተጠበቀ ለነዋሪዎቿ ምቹ እንድትሆን ምን እየተሰራ ነው? ስንል በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ስራ አስኪያጅ ለሆኑት ለአቶ ጥራቱ በየነ ጥያቄዎችን አቅርበናል።
አዲስ ዘመን ፦ አቶ ጥራቱ የሃዋሳ ከተማ ከንቲባ በነበሩበት ወቅት በርካታ የከተማዋን ደረጃ ከፍ የሚያደርጉ ስራዎችን በመስራት ትልቅ ውጤት ማምጣትዎን ብዙዎች ይመሰክራሉ፡፡ አሁን ደግሞ በከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ስራ አስኪያጅ ሆነው በመስራት ላይ ነዎትና ፤ ስራ እንዴት ነው ? ከተማስ ለውጡ ምን ይመስላል በማለት ቃለ ምልልሳችንን እንጀምር?
አቶ ጥራቱ ፦ እሺ በጣም አመሰግናለሁ፤ እንደተባለው የሃዋሳ ከተማ ከንቲባ በመሆን አገልግያለሁ። በቆይታዬም አዲስ አበባ ከተማን ለማገልገል የሚያስችል ልምድ ቀስሜያለሁ ብዬ አስባለሁ። እንደሚታወቀው ሃዋሳ በጽዳትና በውበት በአገራችን ካሉ ከተሞች በጥሩ ሁኔታ የምትነሳና መልካም የሚባል ተሞክሮም ያላት ናት ።በመሆኑም ያንን ከተማ በመራሁበት ወቅት ያገኘሁት ልምድ አዲስ አበባ ከተማ ላይ መጥቼም በምሰራበት ጊዜ የተሻለ ለውጥ ለማምጣት አቅም ጨምሮልኛል ማለት ይቻላል።
አዲስ አበባ የሀገራችን እንዲሁም የአፍሪካ መዲና ናት። የአለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫም ከመሆኗ አንጻር አዲስ አበባን ማገልገልና መምራት ትልቅ ሃላፊነት ነው።አዲስ አበባ ከተማ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚገናኝባት የኢኮኖሚ የፖለቲካ ማዕከል በመሆኗ ከለውጡ በፊት በርካታ ጥያቄዎች ቅሬታዎች ይስተናገዱባት ነበር። እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል ስራን ይጠይቃል። ከዚህ አንጻር ደግሞ ሃላፊነቱ እጅግ በጣም ከባድ ነው ።
እኔም ወደዚህ ከመጣሁ በኋላ ካሉት አመራሮች ጋር በመቀናጀት የከተማዋን ህዝብ ለማገልገል ከተማዋንም የሚጠበቅባትን ወይንም ደግሞ የሚመጥናትን ያህል እንድታድግና ለኑሮ ምቹና ተስማሚ እንድትሆን የአቅሜን ያህል ጥረት እያደረኩ ነው።
አዲስ ዘመን ፦ አዲስ አበባ ከተማ የአፍሪካ መዲና ብትሆንም ዛሬም ድረስ ያልተሻገረቻቸው ብዙ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ያሉባት ናት፡፡ ከዚህ አንጻር ምን እየተሰራ ነው?
አቶ ጥራቱ ፦ አዲስ አበባ ከተማ ላይ ያሉ መሰረታዊ ጥያቄዎች በጣም በርካታ ናቸው።በኢኮኖሚ እና ማህበራዊን ነጣጥለን ብናያቸው ራሱ በርካታ ዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ጥያቄዎች፤ ፍላጎቶች እንዲሁም ብዙ የቤት ሥራዎች ያሉባት ከተማ ናት።ለምሳሌ የአዲስ አበባን ቁልፍ ችግር ሆኖ እየፈተነ ያለው የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ነው።
የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦታችን ከ50 በመቶ የዘለለ አለመሆኑ በጣም ትልቅ ሥራን የሚጠይቅ ነው።የመኖሪያ ቤት ጥያቄ ሌላው የከተማዋ ቁልፍ ችግር ሆኖ ጊዜያትን እያስቆጠረ ነው።ችግሩን ለማቃለል በመንግስት እንዲሁም በከተማ አስተዳደሩ በኩል የሚሞከሩ ስራዎች ቢኖሩም አሁንም ግን ህብረተሰቡ ፍላጎቱ ስላልተሟላለት የተጠናከረ ሥራ መስራትን ይጠይቃል።
በጠቅላላው የከተማዋን ህዝብ በሁሉም ማዕቀፍ ያሉ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮቹን ለመፍታት እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አሉ። በተለይም ከለውጡ በኋላ እነዚህን ሥራዎች በተቀናጀ ሁኔታ ህዝቡን በማሳተፍ መስራት አለብን በሚል ትልቅ ሃላፊነት በመውሰድ ስራዎች ተጀምረዋል። የፌደራል መንግስት እንዲሁም የከተማ አስተዳደሩ በተለይም ባለፉት ጊዜያት ተጀምረው ያልተጠናቀቁ አሁን ላይ የሚጠናቀቁበትን ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ ሥራ ተጀምሯል። በዚህም እየመጡ ያሉ ለውጦች ቢኖሩም አሁንም ከነበሩት ውስብስብ ችግሮች አንጻር ገና ብዙ ይቀራል።
አዲስ ዘመን፦ እርስዎም እንዳነሱት ንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር እስከ አሁንም ልንሻገረው ያልቻልነው ነው፤ ለዚህ ግን ዋናው መንስኤ ምንድን ነው ይላሉ?
አቶ ጥራቱ ፦ እውነት ነው፤ የከተማችንን የውሃ አቅርቦት ችግር በሁለት መንገድ ማየት ይቻላል፡፡ አንዱ የውሃ ሃብት በተገቢው ሁኔታ አልምቶ ለነዋሪው ማድረስ ላይ የገንዘብ አቅም ማነስ አለ፡፡ ሁለተኛው በአቅራቢያችን ያሉ ወንዞች እንዲሁም የከርሰ ምድር የውሃ ሃብታችንን አውጥተን ለመጠቀም ከፍተኛ የሆነ ችግር ይታይብናል። በመሆኑም ሁለቱንም ታሳቢ ባደረገ መንገድ የውሃ ሃብታችንን ከፍ ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶች ተጀምረዋል።
በተለይም ገንዘብ ላይ ያለውን ችግር ለመፍታት ከተለያዩ አገራት ብድርና እርዳታ የማፈላለግ ስራዎች ይሠራሉ። እዚህ ላይ በመሰረታዊነት የአዲስ አበባ ከተማን የውሃ ችግር በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ለመቅረፍ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተቀርጸዋል።ከእነዚህ ፕሮጀክቶች መካከል በ5 ዓመት የሚጠናነቀቁ አሉ።ከዚህም ባጠረ በአንድና በሁለት ዓመት ውስጥ የሚጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ተይዘዋል፡፡ ለአብነት በገርቢ ፕሮጀክት ያሰብነው በአዲስ አበባ ዙሪያ ካሉ የኦሮሚያ አካባቢዎች የሚመጣን ውሃ በመገደብ የመጠጥ ውሃን ለማግኘት የተጀመረው ስራ በአሁኑ ወቅት የገንዘብ ድጋፍ አግኝቶ ወደ ስራ የገባ በመሆኑ በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ ተጠናቆ ህዝቡ ተጠቃሚ ለማድረግ አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ ነው።
በሌላ በኩልም በቀጣዮቹ አምስትና አስር ዓመታት ውስጥ የሚጠናቀቁ ሁለት ትላልቅ ፕሮጀክቶች አሉ። እነዚህ እያንዳንዳቸውም በቀን ከ 5 መቶ ሺ ሜትሪክ ኪዩብ በላይ ውሃ የሚያመርቱ ናቸው፡፡ የዲዛይን ሥራቸው ተጠንቶ የገንዘብ ድጋፍ የማፈላለጉ ስራ እየተሰራ ነው።
ለምሳሌ የገርቢን ፕሮጀክት ያየን እንደሆነ ከ20 ዓመት በላይ ጥናት ሲጠናበት ቆይቷል፡፡ ነገር ግን በገንዘብ እጥረት ምክንያት ወደ ተግባር መግባት ሳይቻል ቀርቷል። ይህ የሚያሳየው ደግሞ ሀብትን አቀናጅቶ በመምራት እንዲሁም ጥናቶች ተጠንተው ውጤታቸው ላይ የማይደርሱበት ሁኔታ እንደነበር ነው፡፡ አሁን ግን በዚህ ዓመት ብቻ በቀን 120 ሺ ሚትሪክ ኪዩብ ውሃ የሚያመርት ለገዳዲ ቁጥር ሁለት ፕሮጀክትን ታሳቢ ተደርጎ እየተሠራ ነው።
በጠቅላላው የውሃ አቅርቦት በከተማዋ ቁልፍ ችግራችን ነው፡፡ ዛሬም ድረስ በሳምንት አልፎም በ15 ቀን ውሃን የሚያገኙ ነዋሪዎች አሉ።ይህ ደግሞ በጣም አሳሳቢ በመሆኑ ችግሩን የሚያቃልል ስራ በከተማ አስተዳደሩ ተጀምሯል ።በመሆኑም በዓመት በሁለትና ሶስት አመት እያለ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት የከተማችንን እድገት ታሳቢ ባደረገ መልኩ ስራዎች እየተከናወኑ ነው።
አዲስ ዘመን፦ አዲስ አበባ ከተማ ሌላው ችግሯ አልፎም መገለጫዋ እስከመሆን የደረሰው የመኖሪያ ቤት ችግር ነው፡፡ ነዋሪዎችን የጋራ መኖሪያ ቤት (ኮንደምንየም) እድለኛ እንሆናለን በማለት ለዓመታት ገንዘብ እየቆጠቡ ተራ ቢጠብቁም በርካቶች የእድሉ ተጠቃሚ አልሆኑም፡፡ በዘለቄታው ይህንን ችግር ሊያቃልል የሚችል በከተማ አስተዳደሩ የተያዘ እቅድ ካለ?
አቶ ጥራቱ ፦ የከተማችን ቁልፍ ችግር ከሆኑት ነገሮች መካከል የመኖሪያ ቤት ችግር በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል።በቀጣዮቹ ዓመታት ደግሞ ይህንን የሚቀይሩ ስራዎች በመሰራት ላይ ናቸው።ይህንን ስራም በተገቢው ሁኔታ እንዲመራ ለማድረግ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ ያሉ የቢሮ ሃላፊም ጭምር በመመደብ ስራዎች እየተሰሩ ነው።
እንግዲህ የመኖሪያ ቤት ችግርን ይቀርፋል ተብሎ የተያዘው አንዱ እቅድ ነባር ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቁ ማስቻል ነው።እዚህ ላይ ግን ትኩረት ሊያገኝ የሚገባው ነገር የጋራ መኖሪያ ቤቶች ቀደም ሲል በባንክ ብድር የተጀመሩ ናቸው፡፡ ነገር ግን በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ባለመጠናቀቃቸው እንዲሁም በስራው ላይ በነበሩ ብክነቶች በብድር ለቤት ግንባታው ወጥቶ የነበረው ገንዘብ ህንጻዎቹን ማጠናቀቅ ሳይችል ቀርቷል። አሁን ላይ ያለው ችግር ያንን ሁሉ ገንዘብ ወጥቶበት መጠናቀቅ ያልቻለን የጋራ መኖሪያ ቤት ቀሪ ሃብት ከባንክ ወስዶ ማጠናቀቅን ይጠይቃል።ለዚህም የሚሆን ንግግር ከባንክ ጋር እየተደረገ ነው።ነገር ግን አሁን አገራችን ያለችበት ችግር ያስከተለው የገንዘብ እጥረት ስራውን ማስቀጠል አላስቻለም።
በሌላ በኩል ገንዘቡን ቆጥቦ ተራውን እየጠበቀ ላለው ነዋሪ በተያዘው ዓመት ተጠናቀው የሚተላለፉ ቤቶች እንዲኖሩም እየተሞከረ ነው። እስከ አሁን የሄድንበት ማለትም በመንግስት ጥረት ከባንክ ገንዘብ እየተበደሩ የሚደረገው ስራ ብዙ ውጤት ያመጣ ስላልሆነ የግል ሴክተሩ ከመንግስት ጋር አጋር በመሆን የሚሰራበት። የግል ቤት አልሚዎች የሚፈልጉትን የመሬት አቅርቦትና ሌሎች ነገሮች ተሟልተው በአነስተኛ ወጪ ሊገነቡ የሚችሉ ቤቶችን እንዲገነቡ የተቀመጠ አቅጣጫም አለ።
በተለይም ገንዘብ እየቆጠቡ ቤት ይደርሰናል በማለት እየተጠባበቁ ያሉ ነዋሪዎች የተጀመሩት ተጠናቀው አልያም አዳዲስ ቤቶች ተጀምረውና እስኪያልቁ ረጅም ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ ከተማ አስተዳደሩ መሬት አመቻችቶ ነዋሪዎች በማህበር ተደራጅተው በራሳቸው መንገድ ኮንትራክተሮችን ቀጥረው እንዲያሰሩ የማመቻቸት ስራ እየተሰራ ነው ።ይህ በተለይም እየቆጠቡ ረጅም አመት ቤት ያላገኙ ነዋሪዎችን ችግር ያስታግሳል ተብሎ የታመነበት ነው። በሌላ መልኩ ደግሞ በዝቅተኛ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን በኪራይ ቤቶች እንዲቀርቡላቸው ለማድረግ በተያዘው ዓመት 5ሺ በአነስተኛ ወጪ የሚገነቡ ተገጣጣሚ ህንጻዎችን ለመገንባት ውል ታስሮ ወደ ስራ ተገብቷል።
በመሆኑም የቤት አቅርቦትን በመንግስት ብቻ እየገነቡ መሄድ አዋጭ ስላልሆነ የግሉ ዘርፍ እንዲሁም ተጠቃሚው ህብረተሰብም ተሳታፊ ሆኖበት ችግሩ በዘላቂነት እንዲፈታ አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ ነው።
አዲስ ዘመን ፦ እዚህ ላይ ግን ሰዎች የሚያነሱት ጥያቄ የጋራ መኖሪያ ቤት ባይመዘገቡ እንኳን በሚሰሩበት መስሪያ ቤት አልያም በሌላ መንገድ ተደራጅተው ቦታ አግኝተው ቤት ገንብተው የሚኖሩበትን ሁኔታ አስመልክቶ የሚነሳ ጥያቄም አለ፡፡ ይህስ መሆን ያልቻለው ለምንድን ነው?
አቶ ጥራቱ ፦ አሁን በማህበር አደራጅተው ቤት እንዲገነቡ እናደርጋለን ያልነው ቤት ተመዝግበው ሲቆጥቡ የነበሩትን ብቻ ነው።ይህንን ያደረግነውም ፍትሃዊ ለመሆን ነው።ቀደም ብለው ተመዝግበው ገንዘባቸውንም እየቆጠቡ ያሉ ነዋሪዎች ተጠቃሚ ሳይሆኑ አዲስ ለሆኑ ሰዎች በማህበር አደራጅቶ ቦታ መስጠት ከፍትሃዊነትም አንጻር ትክክል አይሆንም።ስለዚህ አሁን እየተደረገ ያለው ቤት ለማግኘት የተመዘገቡ ቁጠባቸውንም ያላቋረጡና ፈቃደኛ የሆኑ ነዋሪዎች በማህበር ተደራጅተው እንዲሰሩ ቅድሚያ ይሰጣል።
አዲስ ዘመን ፦ በከተማዋ ከመሬት ጋር ተያይዞ የሚነሱ በርካታ ቅሬታዎች አሉ፡፡ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከተማዋ ዙሪያ የአርሶ አደር ልጆች እየተባለ መሬት እየተሸነሸነ መሰጠቱ ላይ የብዙዎች ቅሬታ ነውና እርስዎ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
አቶ ጥራቱ ፦ በጣም ጥሩ ይህንን ጉዳይ ሰፋ አድርጎ ማየቱ ጥሩ ነው። የከተማ አስተዳደሩ በተለይም ከለውጡ በፊት ከመሬት ጋር የተያያዙ ህገወጥነቶች ስር የሰደዱበት ሁኔታ በመኖሩ ይህንን ለመከላከል የሚያስችሉ ስራዎችን እየሰራ ነው።ሁላችሁም እንደምታውቁት ይህ ለውጥ እንዲመጣ ትልቁን ሚና የተጫወተው ወይም ደግሞ እንደምክንያት ሊነሳ የሚችለው በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ አርሶ አደሮች በልማት ስም ከመሬታቸው መፈናቀላቸው ነው ።በመሆኑም ከለውጡ በኋላ አርሶ አደሩ የመሬቱ ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያስችሉ የህግ ማዕቀፎችን የማረጋጋጥ ስራ ተሰርቷል።
ከዚህ ቀደም አርሶ አደሩ በመሬቱ ላይ የባለቤትነት መብት ኖሮት ማረስ፤ አቅም ካለው ደግሞ ኢንቨስት ማድረግ፤ ለልጆቹም ሆነ ለራሱ የሚሆን መኖሪያ ቤት መገንባት ሳይችል ቆይቷል፡፡ ይህ ደግሞ አርሶ አደሩ መሬቱን ለደላሎች በአነስተኛ ዋጋ የመሸጥ አልያም መንግስት የሚሰጠውን ዝቅተኛ የካሳ ክፍያ ተቀብሎ መፈናቀል እጣ ፋንታው ነበር።
አሁን አዲስ አበባ እየሰፋች ነው፡፡ ከከተማው መስፋትና መዘመን ጋር ተያይዞ ደግሞ የአርሶ አደሩ እድገት ያንን ሊመጥን ይገባል፡፡ በመሆኑም ይህንን ታሳቢ ያደረገ መመሪያ ከሌለ አርሶ አደሩ ዳግም ችግር ውስጥ ይገባል፡፡ ልጆቹም ጎዳና ይወጣሉ ።በመሆኑም የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መመሪያ በ2013 ዓ.ም አውጥተናል።
ሌላው አርሶ አደሩ ከዚህ ቀደም ከመሬቱ ተነስቶ እንኳን ይሰጠው የነበረው ካሳ ህይወቱን ሊለውጥ ቀርቶ ለተወሰኑ ጊዜያት እንኳን ሊያቆየው የሚችል አልነበረም። በመሆኑም አሁን አርሶ አደሮች መነሳት ካላባቸው በዘላቂነት እንዴት ይቋቋማሉ? ልጆቻቸው ምን ዓይነት የስራ እድል ያገኛሉ? የሚለውን ያገናዘበ መመሪያም ተዘጋጅቷል።ይህ ተግባራዊ መሆን የጀመረውም በ2013 ዓ.ም ነው።
አዲስ ዘመን፦ ይህም ቢሆን ግን አሁንም ህገወጥነቱ አልቀነሰም ፤መሬት ይወረራል አለ አግባብ ይታጠራል፡፡ ከአርሶ አደሩ በአነስተኛ ዋጋ ይገዛል ፤ መመሪያው ይህንን ሁሉ ማስተካከል ይችላል?
አቶ ጥራቱ፦በ2013 ዓ.ም ከመሬት ጋር በተያያዘ ሁለት ጊዜ የኦዲት ስራ ተከናውኗል።እያወጣን ያለነው መመሪያ ህገወጥነቱን እየተከላከለ ነው ወይ? የጸጥታ አካላት እንዲሁም መዋቅራችን በስራው ላይ የነቃ ተሳትፎን እያደረጉ ነው ወይ? የሚለውን አይተናል።
በዚህም በ2013 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ በተደረገው የመጀመሪያ ዙር የኦዲት ስራ በርካታ ሄክታር መሬት በግለሰቦች ተወሮ እንደነበር አረጋግጠናል።አለአግባብ የአርሶ አደሮችም መሬት ተይዞ እንደነበር ተረጋግጧል። ይህንን መነሻ በማድረግ የተለያዩ የማስተካከያ ስራዎች ተሰርተዋል።
በ2013 ዓ.ም 6 ተኛውን አገራዊ ምርጫ ተከትሎ ሰፊ የመሬት ወረራዎች እንደሚኖሩ በጥናት ለይተን ስለነበር አስቀድመን ግብረ ሀይል በማቋቋም የማጥራትና የመከላከል ስራ ለመስራት ተሞክሯል።
አዲስ ዘመን ፦ እዚህ ላይ ግን በተለይም አርሶ አደሩን የመሬቱ ተጠቃሚ ለማድረግ የወጣው መመሪያ ምን ያህል ውጤታማ ነበር? የታለመለትን ግብ መቷል ማለት ይቻላል?
አቶ ጥራቱ፦ አዎ የወጣውን የአርሶ አደር መመሪያ ባልተገባ መንገድ በማዛባት አርሶ አደር ያልሆኑ ግለሰቦች የመሬት ባለቤትነት ካርታ የወሰዱበት ሁኔታ ተገኝቷል። የአርሶ አደር ልጆች ሳይሆኑም በተመሳሳይ የማጭበርበር ስራ የሰሩበት ሁኔታ ታይቷል። ይህ ሁኔታ ለመፈጠሩ ደግሞ በመዋቅር ውስጥ ያሉ አመራሮች ። የክፍለ ከተማ ስራ አስፈጻሚዎች ። ደላላሎች እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ የስራ ድርሻ ያላቸው አካላት ተሳታፊ ነበሩ።በዚህም አመራሮች እንዲሁም ከ 88 በላይ የመንግስት ሰራተኞች ከስራ ሃላፊነታቸውና ከስራቸው ተባረው በህግም እንዲጠየቁ የማድረግ ሥራ ተሠርቷል።
ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ በህገ ወጥ ሁኔታ የተያዘ ከ 2 መቶ 20 ሺ ካሬሜትር በላይ ቦታ ወደ መሬት ባንክ ገብቷል።በጠቅላላው ከመሬት ጋር በተያያዘ ያሉ ጉዳዮች በመንግስት ደረጃ ጠንከር ያለ ሥራ እየተሰራባቸው ነው።በቀጣይም ይህንን መሰል ህገወጥነት ለማስወገድ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ያስፈልገናል በማለት በየሰፈሩ የብሎክ አደረጃጀቶችን በመጠቀም እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል።
ህጋችን ባዶ መሬት አይሸጥም አይለወጥም ቢልም መሬት እየተሸጠ ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ነገሮችን ከስራቸው ለማድረቅ የህብረተሰቡ ተሳትፎ እንዳለ ሆኖ እንደ ከተማ አስተዳደር የአሰራር ስርዓት መዘርጋት በቴክኖሎጂ የተደገፈ ስራ መስራት እንዳለብን በማመን የተጀመሩ ሥራዎች አሉ። ከዚህ ጎን ለጎንም መዋቅሩን በአዲስ መልክ አደራጅተን በመሬት ዙሪያ ይሰሩ የነበሩ ሶስት ተቋማትን ወደ አንድ እንዲመጡ ሆኗል።በጠቅላላው የከተማ አስተዳደሩ በመሬት ዙሪያ የሚሰሩ ህገወጥ ተግባራትን ለመከላከል ጠንካራ አቋም ይዞ እየሰራ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።
በነገራችን ላይ አገር በዚህ መሰሉ የጦርነት ሂደት ውስጥ ሆና ህገወጥ ተግባርን የመከላከል ሥራ መስራት ከባድ ቢሆንም እኛ ግን አላቋረጥንም ከዚህ አንጻር ብዙ መሬቶች ከወረራ አድነናል።
አዲስ ዘመን ፦ እዚህ ላይ ግን ከተማ አስተዳደሩ ህገወጥነትን ይህንን ያህል ርቀት ሄጄ እየተቆጣጠርኩ ነው ቢልም፤ በከተማዋ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ አሁንም ድረስ የሚታጠሩ መሬቶች አሉ፡፡ ከፍተኛ የሆነ የደን ሃብት ያለባቸው መሬቶች ሳይቀሩ እየታጠሩ ነው፡፡ ይህ በከተማ አስተዳደሩ እውቅና ያለው ይሆን?
አቶ ጥራቱ ፦ አዎ እየታጠሩ ያሉ መ ሬቶች አሉ ። በኦዲት ስራችን ትኩረት አድርገን ስንሰራ የነበረው የአረንጓዴ ቦታዎች። በከተማው ዳርቻ ላይ ያሉ የደን አካባቢዎች ተወረዋል አልተወረሩም? የሚለውን የማጣ ራት ሥራ ነው ። ከዚህ አንጻርም ተወረው ያገኘናቸው ቦታዎች አሉ። ለምሳሌ ኮልፌ ላይ የአረንጓዴ ፓርክ ተብሎ የተለየ ቦታ ተይዟል። በዚህም ወደ አገልግሎታቸው እንዲመለሱ የማድረግ ሥራ እየሰራን መጥተናል።በሌሎች ቦታዎች ላይም ተመሳሳይ ችግሮች እንዳሉ አረጋግጠናል።
አሁንም መሬት ይታጠራል ። ዛፎች ይቆረጣሉ። ቤቶች ይገነባሉ እኛም ይህንን የመከላከል ሥራ እየሰራን ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የከተማ ደኖቻችን ለልማት መዋል አለባቸው ብለን እንደ እንጦጦ አይነት ፓርኮችንም መጠቀም ጀምረናል።በመንግስት የሚታጠሩት ባሉበት ሁኔታ የተፈጥሮ ሃብትነታቸውን ሳይለቁ ለቱሪዝም ሥራው የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ይሠራል።
አዲስ ዘመን ፦ ባለፉት ስድስት ወራት ህገወጥነትን ለመከላከል በሚል እንደ ሰነዶች ማረጋገጫ አይነት ተቋማት በተለይም መሬት ነክ የሆኑ አገልግሎቶችን እንዳይሰጡ ተዘግተው ቆይተዋል፡፡ ከተማ አስተዳደሩ በሠራው የማጣራት ሥራ ምን ዓይነት ውጤት አገኘ?
አቶ ጥራቱ ፦ በከተማው መሬት ነክ አገልግሎቶች ቆመው ነበር፡፡ አገልግሎቶቹ ቆመው የነበሩበት ዋናው ምክንያት ህገወጥነትን መከላከል በጣም አስፈላጊ ስለነበር ነው። በተለይም መሬት፣ ህንጻና ቤት ያላቸው አካላት ንብረታቸውን በመሸጥና በማሸሽ ለጦርነት ግብዓት እንዲውል ሽብርተኛውን ቡድን ሲደግፉ ነበር። አገልግሎቱ መቋረጡም ይህንን ታሳቢ በማድረግ ነው።
ሌላው ሀገር ጦርነት ውስጥ ስትገባና ሁሉም ሰው ትኩረቱ አንድ ነገር ላይ በሚሆንበት ጊዜ ያለተገባ የመሬት ወረራ ይፈጸማል፡፡ ይህንን ለመከላካል የሚያስችሉ ሥራዎችን ለመሥራትም መዝጋቱ አስፈላጊ ነበር። በመሆኑም እነዚህን አግደን አሠራራችንን የመፈተሽ፣ ተቋማቱን የማሻሻል ስራ ተከናውኗል። ምን ውጤት መጣ? ላልሽው ቀደም ብለው ታትመው የነበሩ ከ 4 መቶ ሺ በላይ የበርካታ ዓመታት ካርታዎች በሁሉም ክፍለ ከተሞች ተገኝተዋል፡፡ እነዚህ ካርታዎች ህጋዊ ናቸው፡፡ ነገር ግን ለህገ ወጥ ተግባር ተዘጋጅተው በየባለሙያው እጅና በወረቀት መደርደሪያዎች ላይ የተገኙ ናቸው። እነዚህ ሁሉ ካርታዎች ተሰብስበው እንዲወገዱ ሆነዋል።
አሁን አገልግሎቱን ስንጀመር አዲስ በምናሳትመው የራሱ መለያ ቁጥር (ኮድ)፣ የመቆጣጠሪያ ሚስጥራዊ ቁጥር ባለው ካርታ ነው።በመሆኑም ከዚህ በኋላ ካርታ የሚፈልጉ ሰዎች ቀደም ያለውን ይዘው ቢገኙ ህገወጥ ናቸው ማለት ነው።በመሆኑም የተዘጋበት ጊዜ እንዲህ አይነት የተዝረከረኩ አሰራሮቻችንን እንድንፈትሽና ጠንከር ያለ የአሠራር ስርዓት እንድንዘረጋ ያስቻለን ነበር።በመሰረቱ አገልግሎት በመቋረጡ በአገር ኢኮኖሚ ላይ የፈጠረው ጫና ከፍተኛ ነው ፡፡ ነገር ግን ካስገኘው ጥቅም አንጻር ስንመዝነው አገርን የታደግንበት በመሆኑ ትክክለኛ ውሳኔ ነው ማለት ይቻላል።
አዲስ ዘመን ፦ ሌላው የከተማዋን ነዋሪዎች እየፈተኑ ካሉ ነገሮች መካከል የኑሮ ወድነት ይጠቀሳል፡፡ ከተማ አስተዳደሩ ይህንን ለማቃለል እየተሰራ ያለውን ስራ እንዴት ይገልጹታል?
አቶ ጥራቱ፦ ከለውጡ ወዲህ አገራችን ተረጋግታ ወደልማት እንዳትገባ ለውጡን በማይፈልጉ አካላት በርካታ ችግሮ ሲፈጠሩብን ነበር። የጦርነቱ ሁኔታም ሌላው ችግር ነው።ነገር ግን በዚህ ሁኔታ ውስጥ ብንሆንም የከተማችንን ነዋሪዎች የኑሮ ጫና ሊያቃልሉ የሚችሉ ውሳኔዎችን እየወሰንን ቆይተናል።
በተለይም ባሳለፍናቸው ጊዜያት በመሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች ላይ የነበሩትን ጫናዎች ለመከላከል አንደኛ ለሸማቾች የህብረት ስራ ማህበራት በሁለት ዙር 1 ቢሊየን ተዘዋዋሪ ብድር የድጎማ በጀት ለቀናል፡፡ የእዚህ ገንዘብ ዋና አላማም ማህበራቱ ያሉባቸውን የአቅም ውስንነት ቀርፈው ምርቶችን ከአምራች አርሶ አደሮች ገዝተው ለከተማችን ነዋሪዎች እንዲያከፋፍሉ ለማስቻል ነው።በነገራችን ላይ ይህንን ገንዘብ እንዲጠቀሙ የተሰጣቸው ለተመረጡ ማለትም ለጤፍና ለስንዴ ምርቶች ነው።እነዚህን ገዝተው አነስተኛ ገቢ ላላቸው ነዋሪዎች በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ገበያውን ማረጋጋት ተችሏል።
በተጨማሪም የእሁድ ገበያ ብለን የጀመርነው ከባለፉት ጊዜያት ተሞክሮ እየተወሰደበት እየሰፋ የሚሄድ የዋጋ ማረጋጊያ መንገድ ነው፡፡ ውጤቱም ጥሩ እየሆነ ስለመጣ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ሊሰፋ ይገባል በማለት ስራዎች እየተሰሩ ነው።ነገር ግን እነዚህ ገበያዎች እስከ አሁን በመንገድ ላይ ስለሆኑ ይህ ደግሞ ቀጣይነቱ ላይ ችግር ስላለው በዘላቂነት የገበያ ማዕከላት ሆነው እንዲቀጥሉ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ግንባታዎች እየተከናወኑ ነው።
አዲስ ዘመን ፦ እነዚህ የገበያ ማዕከላት ግን ከዚህ ቀደም በከተማዋ አምስት ማዕዘኖች ላይ ይገነባሉ ከተባሉት የገበያ ማዕከላት ይለያሉ?
አቶ ጥራቱ፦ አይ አይለዩም እነሱ ማለት ናቸው።
አዲስ ዘመን ፦ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ቁጥር ከእለት እለት እየጨመረ ነው፡፡ ይህ ምንን ያመለክታል ? አሁን ባለው ሁኔታስ ከተማዋን ሊያግዝ የሚችል ሌላ ከተማ ሊኖራት አይገባም ይላሉ?
አቶ ጥራቱ ፦ አዲስ አበባ የአገራችን ትልቋ ከተማ እንደመሆኗ ኢኮኖሚውም ኢንደስትሪውም ያለው አንድ ቦታ ነው ። በርካታ ቁጥር ያለው ነዋሪም ያለባት ናት።ተቀራራቢ እድገት የሚታይባቸው ከተሞች ማፍራት አለብን የሚለው ነገር በመንግስት በኩልም የሚታሰብ ነው።
በተለይም የክልል ከተሞች ወደዚህ ሁኔታ እንዲመጡ የተጀመሩ ስራዎች አሉ።እነዚህ እያደጉ ሲሄዱ አዲስ አበባ ከአቅሟ በላይ የያዘቻቸው ነገሮች የሚከፋፈሉላት ይሆናል።በተለይም አሁን ያለው ወደ አዲስ አበባ የሚደረግን ፍልሰት ለመቀነስ ተጨማሪ ሌሎች አካባቢዎች ላይ ከተሞች ማደግ አለባቸው።አዲስ አበባ እንደ ሜትሮፖሊታን ከተማ በዙሪያዋ ያሉ ከተሞች ከእሷ ጋር ተቀራራቢና ኢንደስትሪውን የሚሸከም ስራ እንዲሰሩ ይጠበቃል። በመሆኑም አስፈላጊነቱ ላይ ምንም ጥያቄ የለም ።
አዲስ ዘመን ፦ አዲስ አበባ ከተማ ላይ አገልግሎት አሰጣጥ ብዙዎችን እያማረረ ነው። በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ሄዶ እጅ መንሻ መስጠት እንደ ትክክለኛ አሰራር እየተቆጠረ ነው የሚሉ አሉና በዚህ ላይ እርስዎ ምን ይላሉ?
አቶ ጥራቱ፦ ይህ ትክክል ነው ።አሁን እየሰጠን ያለው አገልግሎት ከፍተኛ የሆነ የህዝብ ቅሬታ ያለበት መሆኑን ራሳችን እንደ ተገልጋይም እንደ አመራርም ወርደን ስንፈትሽ የምናየው ሃቅ ነው።ተቋማት አሁንም በጉቦ አገልግሎት የሚሰጡበት ሁኔታ አለ።የቢሮ አደረጃጀታችን የቴክኖሎጂ አጠቃቀማችን ምቹ አይደለም።ይህ ደግሞ አገልግሎት የሚያዛባና በገንዘብ የሚሰራ አገልግሎት ሰጪ እንዲበዛ አድርጓል።በመሆኑም ይህንን መቀየር ቁልፍ ተግባራችን ነው ብለን በዓመቱም በአምስት ዓመቱም እቅዳችን ውስጥ አካተን እየሰራን ነው። ለውጥ ለማምጣት ሰራተኛ በመቅጣት አልያም አመራር ማባረር መፍትሔ ስለማይሆን ትኩረታችንን ተቋማዊ በሆነው ስራ ላይ አድርገናል።ለብልሹ አሰራር ተጋላጭ የሆኑ መስሪያ ቤቶቻችን በቴክኖሎጂ የተደገፈ ስራን መስራት ካልቻሉ ምንም ያህል ጥረት ቢደረግ ከሌሎች አገሮች ጋር አንደራረስም።በመሆኑም ተቋማዊ ለውጥን ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጋር አዋህዶ ለመስራት ጥረቶች አሉ።
አዲስ ዘመን ፦ ከተማችን አሁን በኢትዮጵያ እየሆነ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊ ሁነት መሸከም ችላለች? ጦርነቱስ በከተማዋ ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ እንዴት ይገለጻል?
አቶ ጥራቱ ፦ ጦርነቱ ከፍተኛ የሆነ ሀብት የሰው ሃይል ጠይቋል፡፡ በኢኮኖሚም ካየነው ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪን ወስዷል፡፡ ይህ ሁሉ ሰራዊት ቀለብ ሀብት ይፈልጋል።ለዚህ ማሟያ ደግሞ በጀት ይፈልጋል፡፡ በመሆኑም እንደ አገር ከፍተኛ የሆነ ወጪ አውጥተናል።እንደ ከተማ ጦርነቱ እንቅስቃሴዎችን ጎድቷል። እኛም አስቀድመን ጦርነቱን ድል ልናደርግ የምንችልበትን ከተማችንም ለመጠበቅ ህዝቡ እንዲነቃና እንዲደራጅ እንዲዘምት ሀብት እንዲያሰባስብ ሠርተናል።ጎን ለጎን ደግሞ በምክትል ከንቲባ ደረጃ ኢኮኖሚው እንዳይዳከም የሚመራ ሀይልም ተዋቅሯል። ይህም ቢሆን ግን ተጽዕኖው ቀላል አይደለም። ሆኖም በተለይ በመንግስት የተያዙ ፕሮጀክቶች እንዳይቆሙ አድርገናል።ለዚህ ደግሞ ከጦርነቱ በኋላ ያስመረቅናቸው ፕሮጀክቶች ማሳያ ናቸው።
አዲስ ዘመን ፦ በከተማ ደረጃ መስቀል አደባባይን ጨምሮ የከንቲባ ጽህፈት ቤት እንዲሁም አድዋ ዜሮ ዜሮ እና ሌሎችም ትልልቅ ሜጋ ፕሮጀክቶች እየተሰሩ ግማሾቹም ለምርቃት በቅተዋል፡፡ በተለይም የከንቲባ ጽህፈት ቤት የወጣበት ወጪ ብዙዎችን ሲያነጋግር ነበርና እንደው በዚህ ላይ እርስዎ ምን ይላሉ?
አቶ ጥራቱ፦ የከንቲባ ጽህፈት ቤት ከሜጋ ፕሮጀክቶቹ መካከል አንዱ ነው ፡፡ ይህ ህንጻም በተለይም ውስጡ በአዲስ መልክ እንዲሰራ ሆኗል፡፡ ህንጻው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የሚስተናገዱበት ነው፡፡ አዲስ አበባ ብለው የሚመጡ እንግዶች እንዲሁም የተለያዩ አገራት ከንቲባዎችና የልዑካን ቡድናቸው የሚመጡት እዚህ ቢሮ ነው፡፡ መጥተው ሲስተናገዱ ቦታው ደረጃውን የጠበቀ ከሆነ ለህዝባችን ለሀገራችን ክብር ይሰጣሉ፡፡ ይህንን ታሳቢ ያደረገም የእድሳት ስራ ተሰርቷል።በመሆኑም የህንጻው ውስጥ የአየር ማቀዝቀዣው (ኤሲ) ን ጨምሮ የቢሮ እቃዎች፣ መወጣጫ ደረጃዎች፣ ወለሉ፣ የእሳት አደጋ መከላከያ በጠቅላላው ደረጃውን የጠበቀ ህንጻ ሊያሟላቸው የሚገባቸውን ሁሉ ያሟላ ነው ።
አዲስ ዘመን ፦ በመጨረሻ እርስዎ ማለት የሚፈልጉት ነገር ካለ?
አቶ ጥራቱ ፦ የከተማችን ነዋሪ ማገልገል ትልቅ እድልም ከባድ ሃላፊነትም ነው።ከተማ አስተዳደሩም ነዋሪዎቹን ለማገልገል በገባው ቃል መሰረት እየሠራ ያለው በርካታ ሥራ አለ።በዚህ ሂደት ውስጥ የከተማው ነዋሪ ሊያግዘን ይገባል፡፡ በተለይም በጦርነቱ ጊዜ የራሱን ሰላም ለማስጠበቅ የወሰደውን እርምጃና የነቃ ተሳትፎ አጠናክሮ መቀጠል አለበት።
አዲስ ዘመን ፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ። አቶ ጥራቱ፦ እኔም አመሰግናለሁ
ዕፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን የካቲት 7 ቀን 2014 ዓ.ም