ኢትዮጵያውያን “የተናገሩት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ” ይሉት ብሂል አላቸው። ብሂላቸው ደግሞ ስለ ቃላቸው ታማኝነት በምንም መልኩ በማይደራደሩበት የአብራካቸው ክፋይ እስከመፍረድ ያደረሰ የቃላቸውን መፈጸም ጥብቅነት ያስረገጡበት ነው። ይሄ ሥነልቦናቸውም የተናገሩትን ለመፈጸም፤ ቃል የገቡትን ከዳር ለማድረስ እንዲተጉ አቅም ፈጥሮላቸዋል፤ የእንችላለንን ሰብዕና አላብሷቸው መቻላቸውን በተግባር የገለጡባቸውን የታሪክ ምዕራፎች ፈጥረዋል።
ትናንት ጥቁር የነጭ ተገዢ እንጂ ከነጭ እኩል መብት ሊኖረው አይገባም፤ በሚል ለወረራ የተሰማሩ ነጮችን “እኔ ከናንተ የማንስበት ምንም ምክንያት የለም፤ እናም ልትገዙኝ ልታዙኝ እድል አይኖራችሁም” ብሎ እንቢ አለ። ድንበሩን አልፈው ሲገቡም፤ አትገዙኝም ብሎ ቃሉን ሰጥቶ ነበርና ሊገዙት የመጡትን ነጮች አሸንፎ ያለመገዛት አቅሙን አሳየ። ከራሱም አልፎ ለሌሎች ጥቁር ሕዝቦች የመቻልን ችቦ ለኩሶ አቀበለ።
“ቃል የእምነት ዕዳ ነው” እንዲሉም፤ አንድን ጉዳይ እፈጽማለሁ ብለው ቃል ሲገቡ በሌሎች ላይ የይደረጋል ተስፋና እምነትን የማሳደር ኃይል አለው። እናም አደርጋለሁ ብለው ቃል የገቡትን መፈጸም ማለት ይደረጋል ብለው በሰዎች ላይ እምነት እንዲያሳድሩ ያደረጉትን ነገር ፈጽሞ እምነታቸውን እንዲያጸኑ፤ ለቀጣይም መተማመንን እንዲፈጥሩ የማስቻል አቅምን መግለጥ ነው። በዚህም የኢትዮጵያ ሕዝብ ነጻነቴን አላስደፍርም ብሎ የገባውን ቃል ፈጽሞ የጥቁሮችንም፣ የጭቁኖችንም ልብና እምነት አገኘ።
ይህ ግን አትችሉም ሲሉ ለነበሩት የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ የተጠናወታቸው አገራትን እረፍት የነሳ ነበር። ምክንያቱም በቅኝ ግዛት ይዘው ሊዘርፉና የቅኝ ተገዢ አገራትን የተፈጥሮ ሀብት ሊበዘብዙ የነበራቸውን ሕልም ያመከነ ተግባር ነበርና ነው። ሆኖም ዳግም በጦርነትና በኃይል ሊያሳኩት የማይችሉ መሆኑን ሲገነዘቡ ይሄን የከሸፈ ሕልማቸውን የሚያሳኩበት ሌላ መንገድ ማሰብ ጀመሩ። አስበውም ዘመናዊ ቅኝ አገዛዝን የሚያራምዱበት የኢኮኖሚ ጥገኝነትን ማስፋት ተቀዳሚ ተግባራቸው አድርገው ተንቀሳቀሱ።
በዚህ ረገድ በተለይ የአፍሪካ አገሮችን የእነሱ የኢኮኖሚ ጥገኛ ማድረግ የሚያስችላቸውን መጠነ ሰፊ ዘመቻ ጀመሩ። የእርስ በእርስ ግጭትን እንደ ዋና መሳሪያ አድርጎ በማስፋፋት ሰላም በማስከበርና የሰብዓዊ ድጋፍ በማድረስ ስም የአገራቱን አቅም ማዳከም፤ የጥገኝነት እሳቤት ማላበስ እና በዚህ መሃል የሚፈልጉትን ማሳካት ላይ ተጠመዱ። ይህ አካሄድ ከሞላ ጎደል በበርካታ አገራት ላይ መልካም ውጤት ያስገኘላቸው ይመስላል።
ይሁን እንጂ የቀደመ ቃሏን ያልዘነጋችው፤ የመሸነፍና የጥገኝነት ስሜትን ለመላበስ ተፈጥሮዋ ያልፈቀደላት አገር – ኢትዮጵያ፤ ለዚህ ሴራቸው ልትንበረከክ አልቻለችም። በየጉራንጉሩ አማጽያንን፣ በየመንደሩ ነጻ አውጪዎችን፣ በየሸለቆው ሽምቅ ተዋጊዎችን እየደገፉ ቢፈለፍሉም፤ የኢትዮጵያውያንን እጅ መጠምዘዝ አልተቻላቸውም። በሰብዓዊነት ስም ያሰማሯቸው ተቋማትና ግለሰቦችም ቢሆኑ የተሰጣቸውን ተደራቢ ተልዕኮ በሚፈለገው ልክ ወደ ግባቸው ማስጠጋት እንኳን ሳይችሉ ቀሩ።
በተለይ ከ2010ሩ አገራዊ ለውጥ በኋላ ለቅኝ ገዢዎች ዘመናዊ ቅኝ ግዛት አስተሳሰብ አልገዛም ባይነቷ ጎልቶ በመገለጡ፤ ከእነዚህ አገራት የሚፈጠርባት ጫና በዛው ልክ እያደገ መጣ። ይሁን እንጂ ጦርነት የተደገሰላት ኢትዮጵያ በልጆቿ ሕብረት፣ በአመራሮቿ ብስለት የጦር ወጥመዶቿን በድል ሰባብራ ተሻገረች። ፈራርሳ እንድትዳከም፣ ልጆቿም ተከፋፍለው እንዲለያዩ የተጠነሰሰላት ሴራም ሳይሰምር ባለመለያየት የቃል ኪዳን ድር ተሸምኖ ጸንቶ ቆየ። በማዕቀብ፣ በኢኮኖሚ ጫና፣ በብድር ክልከላና በሌሎችም የፋይናንስ ጉዳዮች ተጽእኖ ሲደረግባትም፣ ሊደረግባት የተሴረውንም መረብ በጣጥሳ የልማት ግስጋሴዋን ቀጠለች።
ትፈርሳለች ሲሏት ጸንታ፤ ትደኸያለች ሲሏት ለምታ፤ ተዳክማለች በራሷ አቅም ምንም መስራት አትችልም ሲሏት ጀምራ፤ የጀመረችውን መጨረስ አትችልም ሲሏት የጀመረችውን ጨርሳ ማሳየት ጀመረች። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ዳግም የጥቁር ሕዝቦች የይቻላል ማሳያ፤ የኢትዮጵያውያንም የትብብር መገለጫ ዳግማዊ አድዋ የሆነውም የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የተጋረጠበትን ፈተና አልፎ ሁለት ዙር ውሃ እንዲይዝ የተደረገበትን እና የመጀመሪያው የሙከራ ኃይል ማመንጨት ተግባሩን ለማከናወን ከጫፍ ላይ የደረሰበትን እውነት ማንሳት ይቻላል።
ከዚህ ባለፈ በዚሁ ተዳክማለችና አትችልም በተባለችበት ወቅት ቀድመው የተጀመሩትን ከማጠናቀቅ ባለፈ፤ ግዙፍ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ጀምራ አጠናቅቃለች፤ አብዛኞችኑም ለማጠናቀቅ ከዳር ደርሳለች። ከእነዚህ መካከል ወዳጅነት ፓርክ፣ የአንድነት ፓርክ፣ የእንጦጦ ፕሮጀክት፣ አብርሆት ቤተመጻህፍት እና ትናንት የተመረቀው ግዙፉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሕንጻ ቀዳሚዎቹ ናቸው። እነዚህ ፕሮጀክቶች ለየት የሚያደርጋቸው ግዙፍ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን በተቀመጠላቸው የጥራት፣ የበጀትና የጊዜ እቅድ መሰረት ተከናውነው ለፍጻሜ መብቃታቸው ነው።
እነዚህ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያ እችላለሁ፣ አደርጋለሁ ብላ ከተነሳች የማድረግ አቅም እንዳላት፤ ይሄን ለማድረግ የሚያስችል ሕዝብ እና አመራር ያላት መሆኑን፤ ለዚህ የሚውልም የውጭ እጅ እንድትመለከት የግድ የማይላት ሀብት ባለቤት ስለመሆኗ ያረጋገጡ ናቸው። በተቃራኒው አትችልም ያሏትን አንገት ያስደፋ እና ከኢትዮጵያ ጋር ሊኖራቸው የሚገባውን ትብብርና ግንኙነት ቆም ብለው እንዲከልሱ የሚያስገድዱ፤ ትችላለች ብለው ለተማመኑባት ወዳጆቿም ዳግም እምነት እንዲያደርጉባት፤ ከጎኗ በመሆናቸው እንዲኮሩባት ያደረጉ ናቸው።
ቀድመው የተመረቁት የአዲስ አበባ ፕሮጀክቶችም ሆኑ በመከናወን ላይ የሚገኙት የህዳሴውን ግድብ ጨምሮ የገበታ ለሀገርና ሌሎችም ግዙፍ ፕሮጀክቶች ደግሞ የኢትዮጵያውያንን የእንችላለን ሥነልቡና ውቅር ገላጮች ናቸው። ማሕበራዊ እሴቶቻውም ሆኑ የየእምነቶች አስተምህሮዎቻቸው የመቻል ልዕልና የሚያላብሱ፤ አደርጋለሁ ያሉትን ማድረግ እንጂ ቃልን የማጠፍ ነውርነት፤ በቃል ተገኝቶ ቃልን ፈጽሞ መግለጥን የሚያስረግጡ ስለመሆናቸው እማኝ ናቸው።
ለዚህም ነው አትችሉም ሲሉን እንችላለን ብለን ጀምረን፤ ጅምሮቻችንን እያጠናቀቅን ያሳየነው፤ እያሳየንም ያለነው። በዚህ መልኩ የእንችላለን መንፈሳችን በተግባር ሲደገፍ፤ በላቀ መቻል ታጅበን የላቁ ፕሮጀክቶችን እንድንጀምር፣ ጅምሮቻችንንም ከፍጻሜ እንድናደርስ የአቅም ስንቅ ይሆነናል። መቻላችን ሲገለጽ የገፉን መልሰው እንዲያቅፉን፤ ያቀፉንም አጥብቀው እንዲይዙን የሚያደርጋቸውን ልዕልና እንገነባለን። ይህ እንዲሆን ማድረግ ችለናል፤ እንችላለንም፤ በመሆኑም መቻላችን ሳይቆራረጥ በተግባር ይገለጥ!
በየኔነው ስሻው
አዲስ ዘመን የካቲት 7 ቀን 2014 ዓ.ም