ልጆች ስለ “የልጆች መጻሕፍት” ምንነት ታውቃላችሁ አይደል? አዎ፣ የልጆች መጻሕፍት ለልጆች ተብለው፣ እናንተን የመሳሰሉ ልጆችን ታሳቢ አድርገው የሚፃፉና ቀለል ተደርገው የሚዘጋጁ መጻሕፍት ናቸው። በተለያዩ ቀለማት የተዋቡ ሲሆኑ ብዙውን ጊዜም በሥዕል የታጀቡ (የተደገፉ) ናቸው። ለምን መሰላችሁ እንደዚህ የሚደረገው፣ እናንተ ደስ ብሏችሁ እንድታነቡ፣ በቀላሉም እንድትረዷቸው ነው።
ልጆች የልጆች መጻሕፍት የት የት እንደሚገኙ ታውቃላችሁ? አዎ ለግዥ ከሆነ በየመጻሕፍት መደብሩ ይገኛሉ። ለንባብ ከሆነ ደግሞ በየቤተ-መጻሕፍት ይገኛሉ። ባለፈው ስለ አብርኆት ቤተ-መጻሕፍት ነግሬያችሁ የለም፣ አስታወሳችሁ? አዎ፣ አዲስ በተገነባው በዚህ ልዩና ዘመናዊ ቤተ-መጻሕፍት ውስጥ አንድ እራሱን የቻለ የልጆች ቤተ- መጻሕፍት አለ። በዚሁ የልጆች ቤተ-መጻሕፍት ውስጥ የተለያዩ የልጆች መጻሕፍት አሉ። እዛ ትሄዳላችሁ አይደል? በቃ፣ እዛ በቀላሉ ታገኟቸዋላችሁና በደንብ አንብቧቸው።
ልጆች፣ እነዚህ መጻሕፍት ቀለል ተብለው የተዘጋጁ ይሁኑ እንጂ የሚይዙት መልእክት ግን ለአዋቂ ተብለው የሚፃፉት መጻሕፍት ከሚይዙት የሚያንስ አይደለም። እንዲያውም አንዳንዴ ሊበልጥ ሁሉ ይችላል። አቀራረባቸው ደግሞ በአፈ ታሪክ፣ በጀግንነት ታሪክ፣ በተረት ወዘተ ነው።
ልጆች እናንተ፣ ወላጆቻችሁ የገዙላችሁ ማለቴ ነው፣ ስንት መጻሕፍት አሏችሁ? ብዙ ነው ያላችሁ አይደል? በጣም ጥሩ። ሁሉንም አንብባችኋቸዋል አይደል፣ ታሪካቸው ደስ ይላል? በጣም ጥሩ። አሁንም ማንበብ እንዳታቋርጡ። ማንበብ ካቋረጣችሁ በጣም ነው የምትጎዱት እሺ፣ ማንበብ በፍፁም እንዳታቋርጡ።
ባደጉት አገራት፣ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑት ወላጆች የልጆቻቸው ትምህርት ከሌሎች የቤተሰብ ወጪዎች የበለጠ አስፈላጊ እንደሆነ ያምናሉ። በመሆኑም ለልጆች መጻሕፍትን በመግዛት ጉዳይ ላይ አይደራደሩም፤ ይገዛሉ፣ ልጆቻቸው እንዲያነቡ፤ አንብበውም እውቀትን እንዲገበዩ ያደርጋሉ። ልጆች የእናንተም ወላጆች እንደዚሁ ናቸው አይደል? በጣም ጥሩ። እናንተሰ ወላጆቻችሁ የሚገዙላችሁን መጻሕፍት ታነባላችሁ አይደል? በጣም ጥሩ።
ልጆች፣ እስከ ዛሬ ድረስ መምህራን ሲናገሩ እንደሚሰማው መጻሕፍትን የሚያነቡ ሕፃናት ከፍተኛ ትምህርት የመቀበል አቅም ያላቸው ናቸው። በደረጃም ከፍተኛውን የሚይዙት እነሱ ናቸው። ፈተና በመድፈን፣ ክፍል ውስጥ ጥያቄ በመመለስ እንዲሁም ሌሎች ትምህርታዊ ተግባራትን በማከናወን በኩል እነዚህ የሚያነቡ ልጆችን የሚያክላቸው የለም።
አዎ ልጆች፣ ወላጆች ለልጆቻቸው የተሻለ የወደፊት ሕይወት እንዲኖራቸው ለማድረግ ጊዜ፣ ጉልበት እና ገንዘብ (መዋዕለ ንዋይ) ማፍሰስ እንዳለባቸው ስለሚያውቁ
ለትምህርት፣ ለጠቅላላ እውቀት የሚያስፈልጓችሁን ሁሉ እንዲገዙላችሁ ጠይቋቸው፤ ይገዙላችኋል። እሺ ልጆች፣ ካልጠየቃችሁ ግን ላያውቁ ስለሚችሉ ላይገዙላችሁ ይችላሉና ሲያስፈልጋችሁ ጠይቁ።
ልጆች፣ በአለም ላይ በጣም ብዙ የአንባቢዎች ስብስብ፣ ለምሳሌ አካባቢያችሁ ወደ’ሚገኝ አንድ ቤተ መጻሕፍት ብትሄዱና አንባቢያኑን ብትመለከቱ፣ ልጆች እና ወጣቶች ናቸው። ይሄ ደሞ ደስ ይላል አይደል። እናንተም ቤተ መጻሕፍትን ቶሎ ቶሎ ትጎበኛላችሁ፣ ታዘወትራላችሁ? ጎበዞች። አዎ፣ አባባ ተስፋዬ ምን ነበር የሚሉት፣ “ልጆች የዛሬ አበባዎች፤ የነገ ፍሬዎች” ነው አይደል የሚሉት፤ አዎ እንደዛ ነው የሚሉት። አንድ ጊዜ እኮ ምን ማለታቸው እንደሆነ ነግሬያችሁ ነበር፤ አስታወሳችሁ?
አባባ ተስፋዬ “ልጆች የዛሬ አበባዎች፤ የነገ ፍሬዎች” ትልቅ ንግግር ነው ያደረጉት። እንደዚህ ያሉት ደግሞ በእናንተ፣ በዛሬ አበባዎች፣ በነገ ፍሬዎችና አገር ተረካቢና መሪዎች በመተማመናቸው ነው። በእናንተ መተማመናቸው ትክክል ናቸው አይደል? “አዎ” አላችሁ፣ በጣም ጥሩ ልጆች፣ ጎበዞች!!!
ልጆች አንዳንድ ወላጆች በልጆቻቸው ሲበሳጩ ሰምቼ ግርም ብሎኛል። ለምን መሰላችሁ የሚበሳጩት፤ ልጆቹ መጻሕፍት ማንበብን ትተው አይናቸውን ሞባይል ላይ ተክለው ነው ውለው የሚያድሩት በሚል ነው። በእውነት ልጆች እንደዚህ የምታደርጉ ከሆነ በጣም ተሳስታችኋል። ስለሆነም በፍጥነት እራሳችሁን ማስተካከልና ወላጆቻችሁ የሚሏችሁን መስማት አለባችሁ። እንዴ ልጆች፤ ወላጆቻችሁ የሚሏችሁን ካልሰማችሁ ማንን ልትሰሙ ነው?
ልጆች፣ ባለሙያዎች “ኤሌክትሮኒክ ንባብ” በማለት የሚጠሩት ሞባይል ላይ ማንበብ (መጻሕፍት ከሆነ የምታነቡት ማለት ነው) መጥፎ ባይሆንም የወረቀት ንባብን ሊተካ የሚችል ግን አይደለም፣ እሺ ልጆች። “በወረቀት ላይ የተመሠረተ ንባብ በኤሌክትሮኒክ ንባብ የማይተኩ ብዙ ጥቅሞች ስላሉት በወረቀት ላይ የተመሠረተ ንባብ አይጠፋም።” ሲባል አልሰማችሁም፤ አዎ ምንም ቢሆን የመጻሕፍት ንባብ ከ”ኤሌክትሮኒክ ንባብ” የተሻለ ነው።
ስማርት ፎርቲን የተባሉ ጸሐፊ እንደሚሉት ከሆነማ “የወረቀት ንባብ ልዩ እሴት ያለው ሲሆን፤ ለሰዎች (ለአንባቢ) ወደር የማይገኝለት ተሞክሮን (ልምድን) ይሰጣል። በወረቀት ንባብ ሂደት ውስጥ የሰዎች ስሜታዊ ልምዶች ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሊደርሱ እንደሚችሉ ተዘግቧል። ባህላዊ የወረቀት ንባብ በራሱ “በማንበብ” ትርጉም ላይ የበለጠ ያተኩራል፤ አንባቢዎች በእርጋታ እንዲያነቡ በመፍቀድ በእውቀት ላይ ጥልቅ ግንዛቤን ለማግኘት፣ የሥነ-ጽሑፍን ውበት ለማድነቅ፣ ለመለማመድ እና የቋንቋ ጥበብ (ክሂልን) ለማዳበር” እጅጉን ይጠቅማል።
ለዚህም ነው ዛሬ ስለ የልጆች መጻሕፍት ልነግራችሁ የፈለኩት። መጻሕፍትን በፈለግን ጊዜና ሰአት ማግኘት ከመቻላችን ጀምሮ መፃህፍት ጥቅማቸው ብዙ ነው። ስለዚህ ጉዳይ መምህራኖቻችሁን ብትጠይቋቸው ብዙ ነገር ይነግሯችኋልና ጠይቋቸው።
ልጆች ለምን ይመስላችኋል ወላጆቻችሁና መምህራን መጻሕፍትን እንድታነቡ የሚመክሯችሁ? አዎ፣ ይህንን ምክር የሚሰጧችሁ “በልጅነት ጊዜ የልጆችን የወረቀት መጽሐፍ ንባብ ልምዶችን ማዳበሩ በጣም አስፈላጊ” መሆኑን በሚገባ ስለተረዱ ነው። አያችሁ ልጆች፣ ስለዚህ እናንተም ወላጆቻችሁ፣ መምህራኖቻችሁ፣ ታላላቆቻችሁ የሚሏችሁን መስማትና ማድረግ አለባችሁ። የማይስማማችሁ ከሆነ ደግሞ በደንብ እንዲያስረዷችሁ ደግማችሁ መጠየቅን አትርሱ። አዎ ልጆች መጠየቅን የመሰለ ነገር የለም። ዋናው የእውቀት መገኛ ምንጭ መጠየቅ ነውና ጠይቁ። በሉ እንግዲህ ልጆች፣ ሳምንት እንገናኝ። እስከዛው መልካም የትምህርት ሳምንት ይሁንላችሁ።
ግርማ መንግስቴ
አዲስ ዘመን የካቲት 6/2014