“የአንጪቆረሩ” ፈርጥ

አንጪቆረር ሲባል ሁልጊዜ በአዕምሮዬ የሚመጣው የሆነ ሩቅና አስፈሪ ስፍራ ነው፡፡ ከዛ አስፈሪ ቦታ ሰው በቅሎ በበጎነት መድረክ ተሸለመ ሲባል አንጪቆረር የሀገር ስም ነው እንዴ ብዬ ጠየኩ። ከሀገርም ሀገር መሆኑን ስረዳ አንጪቆረር በሰሜን ሸዋ በሲያደብርና ዋዩ ወረዳ ከደነባ 12ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ታዳጊ ከተማ መሆኗን ተረድቼ ለእናንተም ላካፍላችሁ ወደደኩ።

ይህች ከተማ እና በዙሪያዋ ትርፍ አምራች አርሶ አደሮች ያሉባት፣ በገበያዋ እንቅስቃሴም የተሻለች ከተማ ስትሆን በመሠረተ ልማት ከደነባ፣ ከሞረትና ጅሩ ወረዳ ዋና ከተማ ከእነዋሪ የሚያገናኝ መንገድም ያላት ከተማነች፡፡

አንጪቆረር ከተማ ከ1532 ዓ.ም በፊት የንግድ ማዕከል ሆና ስታገለግል ነበር የሚሉ ሀሳቦችም አሉ። ከ1532 ዓ.ም ወዲህ ባስኬቶ የሚባል ግለሰብ ጦርም አስፍሮባት እንደነበር ምሑራን ይናገራሉ። ከተማዋ መቼ እና በማን እንደተቆረቆረች እስከአሁን አሳማኝ መረጃ አለኝ የሚል አልተገኘም።

እግር ጥሎት ወደዚህች ከተማ ጎራ ካሉ በስንዴና ጤፍ ምርት ገበያዋ ተጨናንቆ ታገኟታላችሁ፡፡ በበሬ የሥጋ ቁርጥም ቀላል የምትባል ከተማ አይደለችም፡፡

ከዚህ ቀደም ስለአንጪቆረር ትርጉም ለማስረዳት የወረዳው ባሕልና ቱሪዝም እንዲሁም ብዙ ግለሰቦችና መጽሔቶች አራት ማስረጃዎችን በማቅርብ ለማስረዳት ጥረት ሲያደረጉም ቆይተዋል። እነዘህ ማስረጃዎች፤ 1ኛ በግራኝ መሐመድ ዘመን በራሱ በግራኝ መሐመድ አማካኝነት ስያሜው እንደተሰጣት ይነገራል። ሆኖም ይህ ብዙም ውሃ የሚቋጥር አይደለም፡፡ 2ኛው የጎንደር ንጉሠ ነገሥት የነበሩት አፄፋሲል የአዳም ዘር የምትባል ሴት ልጅ ነበረቻቸው፡፡ ወደዚህ ቦታ መጥታ በመቅረቷ “አንቺው ቀረሽ” እየተባለች ለረጅም ጊዜያት ስትጠራ ከቆየች በኋላ በጊዜ ሂደት አንጪቆረር ወደሚል መጠሪያ እንደተለወጠችም ይነገራል፡፡ 3ኛው ደግሞ ጤፍ ሲታጨድ የሚቀረው ቃርሚያ ቆረን ይባል ነበር፡፡ ታዲያ በዚህ ጊዜ የመሬቱ ባለቤት አንቺ ቆረን የሚል መጠሪያ እንደሰጡትም ይነገራል፡፡ በ4ኛ. ደረጃ ጠላ ቤት ስለነበረ ጠላ ሻጯን አንጪ ጠላውን ቆረር አድርገሽ በማለት ሰዎች ያዟታል፤ በዚህም የተነሳ አንጪቆረር እንደተባለ የሚያመላክቱ መላ ምቶች መኖራቸው ይነገራል።

ይሁን እንጂ ሁሉም መላምቶችና አፋዊ ታሪኮች እስካሁን የሰነድ ማስረጃ እንደሌላቸው ያስረዳሉ፡፡ አፈታሪኮች አንድ የታሪክ ማስረጃ መሆናቸው ምንም እንኳ ባይታበልም ትክክለኛ እና እውነተኛ ናቸው ብሎ ለመናገር ግን ጉልበት ያንሳቸዋል፡፡ በሰነድ ቢደገፉ ግን የተሻለ የማስረዳት አቅም ይኖራቸዋል በማለት ከሰነድ መረጃ ፈልገናል፡፡

ታዲያ ስለአንጨቆረር ሰነድ ላይ የት እናገኛለን? ከተባለ በሰነድ ላይ ስለአንጪቆረር ሰፍሮ የምናገኘው “የጥላሁን ብረሃንሥላሴ” የታሪክ መጽሐፍ ገፅ 10 ላይ ነው፡፡ በዚህ መጽሐፍ ላይ አንጪቆረር የሚለው ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ በ19ኛው ክፍለ ዘመን /1806 እስከ 1840/ዓ.ም ዘመን በዘመነ ንጉሥ ሣሕለሥላሴ ሸዋን በሚያስተዳድሩበት ዘመን ነበር፡፡ በወቅቱ ምንም እንኳን የዛሬዋን የሲያደብረና ዋዩ ወረዳ የምትገኘዋን አንጪቆረር ታዳጊ ከተማ ባያስተዳድሯትም ንጉሥ ሳሕለሥላሴ የሸዋ ዝነኛና ታዋቂ ስለነበሩ “በሸዋ የነበሩት ባላባቶች ዝነኛ መሆን ጀምረው ስለነበረ አማርኛ ቋንቋ ውስጥም አንዳንዶቹ ስም መደባለቅ ጀምረው በሸዋ አማርኛ የሚከተሉትን ዘይቤዎች ተለመዱ፡፡

ሩቅ ለማለት———-አንጪቆረር፤

ታች ለማለት———-እንጦሮጦስ፤

ጥንት ለማለት———የስብስቴ ጊዜ፤ ድሮ ለማለት——የአምኃየስ ጊዜ” እያሉ እንደተሰየሙ ያስረዳናል፡፡

ከዚህ በላይ ባጭሩ በተገለጸችውና በልምላሜዋ በታወቀችው በሰሜን ሸዋ አስተዳደር ልዩ ስሙ አንጪቆረር የተባለ ስፍራ በ1949 ዓ.ም ነው እንግዲህ ደረጄ ገብሬ (ረዳት ፕሮፌሰር) የተወለዱት። እኛም እኚህን ምሑርና የበጎ ሰው ሽልማት የማኅበራዊ ጥናት ዘርፍ ተሸላሚ የዛሬ የሕይወት ገጽታ ዓምዳችን እንግዳ ያደረግናቸው።

1(ስለ አንጪቆረር አመሠራረት አንዱ አፈ ታሪክ ከግራኝ አሕመድ ወረራ ቀጥሎ በተደረገው የኦሮሞ ፍልሰት/ መስፋፋት ምክንያት የዋዩን አካባቢ ያስተዳድር የነበረው የዋዩ የተባለ መሪ ነበር በእርሱ ስር ደግሞ ቦኪሳ የሚባል ጭፍራ አለ፡፡ የአንጪቆረር ገበያን የመሠረተውም ቦኪሳ ነው፡፡ የኛ ወላጆች ገበያውን የቦኪሳ ገበያ አድባሯንም የቦኪሳ አድባር ይሉ ነበር፡ )

ልጅነት

ደረጀ ገብሬ (ረዳት ፕሮፌሰር) በ1949 ዓ.ም ነው አንጪቆረር ላይ የተወለዱት። ለትንሽ ጊዜ የቄስ ትምህርትን ተምረው የተወሰኑ ፊደሎችን ከለዩ በኋላ ነበር የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸው በዋዩ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀመሩ።

ጋሽ ደረጀ የአስኳላን ደጅ ከረገጡ በኋላ ትምህርት ቤት መሄድ ጠልተው የአንድ ዘመዳቸው እርሻ ውስጥ ተኝተው ውለው እንደተማረ ሰው ከተማሪዎች ጋር ተቀላቅለው ቤት መግባት ጀመሩ። “ይህ ልጅ እየተማረ ሳይሆን እርሻ ውስጥ ተኝቶ ነው የሚውለው ለምንድን ነው? የማይማረው” የሚለው ወሬ ቤተሰብ ጋር ደረሰ።” መማር ካልፈለገማ….” ተብሎ ብላቴናው ደረጀ ወደእረኝነት ሥራ እንዲሰማራ በቤተሰብ ተወሰነበት።

ለተወሰኑ ዓመታት ከነቡሬ ጋር ሜዳውን ሲያካልሉ የቆዩት ትንሹ ደረጀ የቀመሷት ፊደል ጣዕም ከውስጣቸው ስላልወጣች ወደትምህርት ቤት መመለስ ፈለጉ፡፡ በኋላም ፍላጎታቸው ተሳክቶ ተመልሰው የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በንቃት በትጋት መከታተል ጀመሩ።

የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸው አመርቂ በሚባል ሁኔታ ያጠናቀቁት ጋሽ ደረጀ የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃን በደነባ ት/ቤት፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በደብረብርሃን ኃይለማርያም ማሞ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታተሉ። “የነብርን ጭራ አይዙም ከያዙም አይለቁም” በሚለው ብሂል ጋሽ ደረጀ በርትተው በመማር የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሚገባ ካጠቃለሉ በኋላ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ (ማትሪክ) ፈተና ወስደው ውጤት መጣላቸው፤ ይህንን ተከትሎም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን የመቀላቀል ዕድል አገኙ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋና ሥነጽሑፍ ትምህርት ክፍል ገብተውም በኢትዮጵያ ቋንቋዎች የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አገኙ። በመቀጠልም በአማርኛ ቋንቋ የማስተማር ሥነ ዘዴ የሁለተኛ (ማስተማርስ) ዲግሪ አገኙ።

በትምህርት መስክ ያመጡት አጥጋቢ ውጤት ደግሞ ሌሎችን አስተምሮ ለመቅረጽ ዕድል ፈጠረላቸው። በዚህም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር አድርጎ እዛው አስቀራቸው። እነሆ እስከ ዛሬዋ እድሜያቸው ድረስም በዩኒቨርሲቲም የመምህርነት አበርክቷቸውን በአግባቡ እየተወጡ ይገኛሉ።

በታላቁ ቤት የተገኘ ታላቅ ዕድል

የአንጪቆረሩ ልጅ አድገው በአዲስ አበባው ዩኒቨርስቲ መምህር ከሆኑ በኋላ ከእረኝነት ቀጥሎ በተዋወቁት ሥራ በመምህርነት እድሜ ዘመናቸውን ቆተዋል። በዩኒቨርሲቲው በመምህርነት ከማገልገላቸውም በተጨማሪ፤ የተከታታይ ትምህርት ፕሮግራም አስተባባሪ በመሆን አገልግለዋል።

በዩኒቨርስቲው የሚዘጋጅ ዜና መጽሔት ላይ ማኔጂነግ ኤዲተር፤ የአማርኛ ቋንቋ የሥነ ጽሑፍ እና ፎክሎር ትምህርት ክፍል ሊቀመንበር ነበሩ ።

ጋሽ ደረጀ ከማስተማሩ ጎን ለጎን የተለያዩ ጥናትና ምርምሮችን ያደርጋሉ። ከምርምሩም በላይ “ሀ” ተብላ በፊደል የተጀመረችውን የሥነ ጽሑፍ ክህሎት አሳድገው በርካታ መጽሐፍትን ለአንባቢያን ማበርከት የቻሉ መምህር ተመራማሪ ናቸው።

ከሥነ ጽሑፍ ሥራዎቻቸው በጥቂቱ

ጋሽ ደረጀ የተለያዩ ይዘት ያላቸውን አስተማሪና አመራማሪ መጽሐፍትን እነሆ ብለዋል። ከእነዚህም ቀዳሚው ጠይም ዕንቁና ሌሎች የአጫጭር ልቦለዶች መድበል ሲሆን ፤ መጽሐፉ የመጀመሪያ የምናብ ልጃቸው ሆኖ በ1981 ዓ.ም አዲስ አበባ፤ ንግድ ማተሚያ ቤት ታትሞ ነበር ለንባብ የበቃው፡፡

ይህ መጽሐፍ መንደርደሪያም መነቃቂያም ሆኗቸው ከዛ በኋላ ባሉት ጊዜያት ተግባራዊ የጽሕፈት መማሪያ፤ በተማሪዎች የቤት ሥራ የመምህራንና የወላጆች ሚና፤ የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር፤ የዘመን ቀለማት የግጥም መድበል፤ ታትመውላቸዋል፡ ፡ ከዚያ በኋላ ባሉት ጊዜያት የታተሙላቸው ሥራዎች አብዛኞቹ የልጆችን የማንበብና የመጻፍ ችሎታ ለማዳበር የሚረዱ ናቸው፡፡ እነሱም በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የትምህርት ሚኒስቴር በኩል የታተሙ ናቸው፤ ከእነሱም ውስጥ ጥቂቶቹ፣

ገበያ በገጠርና በከተማ፣ የንባብ መጽሐፍ ለ3ኛ ክፍል፤ 2010፤

መንገድና የመንገድ አጠቃቀም፣ የንባብ መጽሐፍ ለ3ኛ ክፍል፤

ግብርና፣ የንባብ መጽሐፍ ለ3ኛ ክፍል፤ 2010፤

ሥራና የሥራ እቅድ፣ የንባብ መጽሐፍ ለ3ኛ

ባሕል፣ የንባብ መጽሐፍ ለ3ኛ ክፍል፤

ንጉሡና ገበሬው፣የንባብ መጽሐፍ ለ3ኛ ክፍል፤

መጥፎ ተክል ሲነቀል፣ የንባብ መጽሐፍ ለ3ኛ ክፍል፤ 2010፤

ስፖርት፣ ተጨማሪ የንባብ መጽሐፍ ለ4ኛ ክፍል፣

ግለታሪክ፣ተጨማሪ የንባብ መጽሐፍ ለ4ኛ ክፍል፣

መገናኛ ብዙኀን፣ ተጨማሪ የንባብ መጽሐፍ ለ4ኛ ክፍል፣ 2010፤

መዝናኛ፣ ተጨማሪ የንባብ መጽሐፍ ለ4ኛ ክፍል፣

መጓጓዣ፣ተጨማሪ የንባብ መጽሐፍ ለ4ኛ ክፍል፣ 2010፤

የአካባቢ ጥበቃ፣ ተጨማሪ የንባብ መጽሐፍ ለ4ኛ ክፍል፣ 2010፤

ከነዚህ በተጨማሪ ደግሞ ልጆችን በተረት ማስተማር (2011) አዲስ አበባ፤ ሜጋ አሳታሚና ማከፋፈያ ድርጅት፡፡ ተረት እንደገና የማንበብና የመጻፍ ችሎታ ማዳበሪያ አጋዥ፤ 2011፤ አዲስ አበባ፤ ሜጋ አሳታሚና ማከፋፈያ ድርጅት የሚሉ መጽሐፍት የመምህር ደረጄ የአዕምሮ ውጤቶች ናቸው ፡፡

በግል ጥረት ደግሞ፣ መራሔ ንባብ- የማንበብ ክሂል ማበልጸጊያ፤ 2013፤ አዲስ አበባ፤ አፍሪካ ማተሚያ ቤት፡፡ ጀግኖቻችን፣ አጫጭር የታዋቂ ግለሰቦች ታሪክ ለልጆች፤ 2013፤ አዲስ አበባ፤ ከቡክኮርነር ጋር በጋራ በመሆን ለተደራሲ አቅርበዋል።

ከመጽሐፍቱ በተጨማሪ

“በልጆች ላይ የሚነገሩ ምሳሌያዊ ንግግሮች ናሙናዊ የይዘት ትንተና፤ በአማርኝ፣ በኦሮምኛና በትግርኛ ምሳሌነት”፤ የሚል የጥናት ጽሑፍ፤ “በኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ክረምት መርሐ-ግብር የክሬዲት ሰዓት ሥርዓት ትርጓሜና ተግባራዊነት ትንታኔ” የተዘጋጀ ጥናት “ኩርኩም ከጠፋ ልጅም አይፋፋ”፤ ታዛ መጽሔት፣ ደብረ-ያሬድ አሳታሚ ድርጅት፡፡ ግንቦት 2012፣ ቀጽ 3 ቁ. 32፣ ፅፈዋል።

“ለአማርኛ ማስተማር ሥነ ዘዴ (ቲም) መርሐ-ግብር ከ1985–96 የቀረቡ የዲግሪ ማሟያ ጽሑፎች (ዲማጾች) አጭር ቅኝት፤ የቋንቋዎች ጥናት ተቋም አሥራ ሰባተኛው ዓመታዊ ጉባኤ፤ ግንቦት 1997፣ (ገጽ 133– 150)

“በ1998 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ክፍለ ትምህርት አዲስ የተመደቡ ተማሪዎች የመጀመሪያ ጽሑፍ ገጽታ”፤ ለ18ኛው የቋንቋዎች ጥናት ጉባኤ የቀረበ ጥናት (ከአቶ ግርማ ገብሬ ጋር በጋራ የተሠራ፣ በመድበለ ጉባኤ ለመታተም በሂደት ላይ ያለ)

“ስለ ባሕላዊ የዘፈን ግጥሞቻችን ጥቂት የመወያያ ሀሳቦች”፤ ታኅሣሥ 14 ቀን 1999 ዓ.ም. በግሎባል ሆቴል ለሙዚቀኞች ማኅበር የቀረበና በብሌን ቁጥር 4 የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር መጽሔት፤

‹‹የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ዓላማዎች፣ ተግዳሮቶችና ጥቂት የመፍትሔ ሀሳቦች››፤ ብሌን፣ የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር መጽሔት ቁ.7፣ ሰኔ 2003፣ ገጽ 10-13፡፡

በአማርኛ ድርሰት የመጻፍ ችሎታ ግምገማ” ለ19ኛው የቋንቋዎች ጥናት ጉባኤ የቀረበ፤ ሰኔ 1999 (ከአቶ ግርማ ገብሬ ጋር በጋራ የተሠራ፣ በመድበለ ጉባኤ በአ.አ.ዩ. ድረ ገጽ የታተመ)

“አጉል አስተያየቶች የሚያሽቃብጡ ዓይነት ከሆኑ ጭራሽኑ ሊገፈትሩ ይችላሉ”፤ ጠብታ መጽሔት፤ ቅጽ 1፣ ቁጥር 11 ( በመጽሐፍት የጀርባ ገጽ ላይ ስለሚሰጡ አስተያየቶች ቃለ መጠይቅ)፤

“ንባብ የእውቀት ምንጭ”፤ ስምዐ ጽድቅ፣ ዘኦርቶዶከስ ተዋሕዶ፤ ጋዜጣ፡፡ 14ኛ ዓመት፣ ቁጥር 18 ቅጽ 14 ቁጥር 137 እና 138፡፡

የአራተኛ ክፍል ተማሪዎች በአማርኛ ሀሳባቸውን በደረጃው የሚጠበቅባቸውን ያህል በጽሑፍ የመግለጽ ብቃት አላቸው? በሦስት የአዲስ አበባ ት/ቤቶች የተደረገ ናሙናዊ ጥናት The Ethiopian Journal of Education. Vol. 27, Number 1 , June 2007 pp. 1 – 23.

‹‹የንባብ ልምድ ቅኝት በአዲስ አበባ›› Ethiopian Journal of Education (EJE), Vol. 29 No.2 De­cember 2009 Pp. 69- 102.

‹‹አንጪቆረር ድፈሽ››፤ ታዛ መጽሔት፤ አዲስ አበባ፤ ደብረ-ያሬድ አሳታሚ ድርጅት፡፡ ቅጽ 2፣ ቁጥር 13፣ መስከረም-ጥቅምት 2011፤ ገጽ 31-33፡፡

ማኅበራዊ አገልግሎት

በበጎ አድራጎትና ከማኅበራዊ ግልጋሎት መስጠት የሚስደስታቸው እኚህ ሰው “ፕሮጃይኒስት” በተሰኘ ዋና ትኩረቱን በሴቶችና ሕፃናት ላይ ባደረገ ግብረ ሠናይ ድርጅት ውስጥ፣ በቦርድ አባልነት ከ1998 ዓ.ም. ጀምሮ ነፃ ግልጋሎት እየሰጡ ይገኛሉ።

በተጨማሪም “ልሕቀት የንባብ ማዕከል” በተሰኘ ትኩረቱን በንባብ ባሕል መዳበር ላይ ባደረገ በጎ አድራጎት ድርጅትም ውስጥ የነፃ ግልጋሎት ሰጥተዋል። በኢትዮጵያ ራዲዮ፣ በፋና ራዲዮ፣ በሸገር ራዲዮ፣ በአሐዱ ራዲዮ ብዙ ጊዜ ከሙያዬና ከሥራ ልምዴ ጋር በተያያዙ ጥያቄዎችን በመመለስ ልምዴን አጋርቻለሁም ይላሉ፡፡ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በንባብ ልምድ፣ በልጆች ትምህርት፣ እና በመሳሰሉት ልምድና የሥራ የሥራ ተሞክሯቸውን በማቅረቡ በኩልም ሚናቸውን ይናገራሉ፡፡

በፋና ቴሌቪዥን በልዩ ልዩ ጉዳዮች (ማለትም ትምህርት፣ ድርሰት፣ የልጆች ንባብና ትምህርት፣ ስለመጽሐፎቼ ይዘትና አገልግሎት ወዘተ.) ላይ ለቀረቡልኝ ጥያቄዎች የማውቃቸውንና በደንብ የማምንባቸውን ሀሳቦቼን አጋራለሁ በማለትም ስለ ራሳቸው ያብራራሉ ፡፡

“……በተማሪዎች የቤት ሥራ የመምህራንና የወላጆች ሚና በተሰኘው መጽሐፌ ላይ የተንተራሱ በርካታ ገለጻዎችን በግል ትምህርት ቤቶች (በአዲስ አበባና ከአዲስ አበባም ውጪ በአዋሳ፣ በመቂ፣ በሚዛን ቴፒ)፣ በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ደግሞ በሰሜን ሸዋ አንጪቆረር አካባቢ ለሚገኙ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መምህራን ሁለት ጊዜ ልምድ አካፍያለሁ” ይላሉ፡፡

“……በሐምሌ 2016 ዓም በአሻም ቲቪ ላይ “መጽሐፈ ጨዋታ” በተሰኘ መርሐግብር ሙያዊ ገለጻ አድርጌያለሁ፡፡ ነሐሴ 2016 በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን መዝናኛ ቻናል ስለ አንጋፋው ደራሲ ሣሕለሥላሴ ብርሃነማርያም በተሰናዳ የእውቅና ዝግጅት ላይ ሙያዊ ተሳትፎ አድርጌአለሁ”፡፡

በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አዲስ በጀመረው “ብላቴናት” የልጆች መጽሔት ላይ ዓምደኛ በመሆን የረጅም ጊዜ የሥራ የጽሑፍ ልምዳቸውን እያጋሩም ይገኛሉ፡፡

ሽልማቶቻቸው

የተለያዩ የበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ የተሳተፉት ጋሽ ደረጀ በተለያዩ ጊዜያት ልዩ ልዩ ሽልማቶች ከተለያዩ አካላት አግኝተዋል። ለምሳሌም በቅርቡ የተካሄደው የአስራ ሁለተኛው የበጎ ሰው ሽልማት የማኅበራዊ ጥናት ዘርፍ ተሸላሚ አድርጓቸዋል።

በሌላ በኩልም ለደራሲያን ማኅበር የዘመን ቀለማት በሚለው መጽሐፍ ላይ ስላደረጉት አስተዋፅዖ እውቅና የተሰጣቸው ሲሆን፤ በተጨማሪም በበጎ አድራጎት ሥራቸው ከተሳተፉባቸው አብዛኛው የእውቅና ሰርተፍኬት አግኝተዋል።

በሕይወት መንገድ

ጋሽ ደረጀ በሕይወቴ አላሳካሁትም ይቆጨኛል የሚሉት ነገር እንደሌላቸው ይናገራሉ። በትዳር ሕይወታቸው ደስተኛ በሥራቸውም ስኬታማ እንደሆኑ ይገልጻሉ። ለሌሎች ማካፈል እጅግ በጣም የሚያስደስታቸው ተግባር መሆኑን ይናገራሉ።

ሰው ይታይልኝ እየተባለ ለሰው በሚያደርግበት ዘመነ ለተቸገረው ደራሽ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል፤ ያለውን ተካፍሎ የሰውን ሕይወት ማቅለል ተገቢ ነው ብለወም ያምናሉ ።

“….. ለሰው ሳደርግ መልሶ እንዲያደርግለኝ ሳይሆን እሱ ተሳክቶለት ሌላ የሱን እርዳታ የሚፈልግ ሰውን ለማገዝ እንዲችል በመመኘት ጭምር ነው። በዩኒቨርሲቲ ግቢ ለሚኖሩ ለሻይ የሚሆን ሳንቲም ለሚቸገሩ ልጆች የምችለውን ከማድረግ ጀምሮ እስከመመረቂያ ሙሉ ልብስ ድረስ እገዛለሁ። ከዚህም በተጨማሪ በሰሜን ሸዋ አካባቢ ተማሪዎችን የሚያግዝ ድርጅት ውስጥም አገለግላለሁ” በማለት መስጠት ማካፈል የሚሰጣቸውን ደስታ ይናገራሉ።

የተማረ ያስተምር ነፃ የትምህርት አገልግሎት (ስኮላር ሽፕ) ፈንድ የተሰኘ የተቸገሩ ተማሪዎችን የሚረዳ በተለይም ሴት ተማሪዎች ተበረታተው ውጤታማ የሚሆኑበትን ድጋፍ ያደርጋል። ጋሽ ደረጀም በዚህ አሜሪካን ሀገር በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የተቋቋመ በጎ አድራጎት ኮሚቴ ውስጥ ከአስተባበሪዎቹ አንዱ በመሆን አገልግለዋል።

በመጨረሻም

“……ከላይ አንዳልኩት እኔ በሕይወቴ ቀረ የምለው ወይንም ባደርገው ኖሮ ብዬ የምቆጭበት ነገር የለኝም። ባገኘሁት ዕድል ብዙ ወጣቶችን አስተምሬ አብቅቻለሁ። አሁንም እያስተማርኩ ነው። ወደፊትም የሚቀጥል ይሆናል” ካሉ በኋላ ወጣቶች ተምሮ መለወጥን ባላቸው አውቀትና ችሎታ ለሌሎች መትረፍን ቅድሚያ ሊሰጡት የሚገባ ነገር ስለመሆኑም አጥብቄ እናገራለሁ። በጎነት የአንድ መልካም አሳቢ ሰው የብቻ ባሕሪው አይመስለኝም፤ የሌሎችንም በርካታ ተባባሪዎች የሚፈልግ ተግባር ነው፤ በጎነት እንዲቀጥል በጎዎች ይብዙልን፡፡” በማለት ከሰፊው የማስተማርና የሕይወት ልምዳቸው ያገኙትን ዕውቀት በጥቂቱ አካፍለውናል፡፡

አስመረት ብሥራት

አዲስ ዘመን መስከረም 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You