አሜሪካ የትራምፕ የምርጫ ዘመቻ መረጃን መንትፈዋል ያለቻቸውን ሦስት ኢራናውያን ከሰሰች

አሜሪካ ከዶናልድ ትራምፕ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ቅስቀሳ መረጃዎችን ከመመንተፍ ጋር በተያያዘ ሦስት ኢራናውያን ላይ ክስ መሰረተች።አቃቤ ሕግ የኢራን እስላማዊ አብዮት ዘብ አባላት ናቸው ያላቸውን ማሱድ ጃሊል፣ ሰይድ አሊ አግሃሚሪ እና ያሳር ባላጋሂ “መረጃ በመመንትፍ እና ሰነድ በማሹለክ” ተግባር ላይ “ይኹነኝ ተብሎ” በስም ያልተጠቀሰን የምርጫ ዘመቻ ለማጣጣል ሲሰሩ ነበር ብሏል።

ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ ባለስልጣናት የኢራን መረጃ መንታፊዎች ከዶናልድ ትራምፕ የምርጫ ዘመቻ አስተባባሪዎች የወሰዱትን ሰነድ ከባይደን የምርጫ ዘመቻ አስተባባሪዎች ጋር ግንኙነት ላላቸው ሰዎች መላካቸውን ገልጸው ነበር። ሦስቱ የመረጃ መንታፊዎች የተከሰሱት በ18 ወንጀሎች መሆኑ ተገልጿል።

በነሐሴ ወር ላይ የትራምፕ ምርጫ ቅስቀሳ ቡድን የውስጥ ግንኙነት ልውውጡ በኢራን መረጃ መንታፊዎች መሰረቁን ገልጾ ነበር። በወቅቱ የኢራን ባለስልጣናት በመረጃ ምንተፋው ላይ እጃቸው እንደሌለበት በመግለጽ አስተባብለዋል። ከጥቂት ቀናት በኋላ የፌዴራሉ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ወደ ትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ኢራን ሰርጋ መግባቷን አረጋግጧል።

የአሜሪካ የፌዴራል ወንጀል ምርመራ ቢሮ ባለፈው ነሐሴ ወር ላይ ኢራን በመጪው የአሜሪካ ምርጫ ላይ ክፍፍልን ለመፈጠር እንዲሁም ዜጎች በአሜሪካ መንግሥታዊ ተቋማት ላይ ያላቸው እምነት እንዲሸረሸር ለማድረግ እንደምትጥር አስጠንቅቆ ነበር። ባለሥልጣናቱ ኢራን ይህንን ዓላማዋን ለማሳካት እና የዲሞክራቶች እንዲሁም የሪፐብሊካኖች የምርጫ ማስተባበሪያዎችን በቀጥታ ለመበርበር “ማኅበራዊ ምህንድስና” የተባለ እና ሌሎች ስልቶችን ስትጠቀም ነበር ብለዋል።

ይህንን ስልት ኢራን እና ሩሲያ በሌሎች አገራት ላይ የሚተገብሩት እንደሆነም አንስተዋል። ቢሮው አክሎም “በዚህ የምርጫ ወቅት ኢራን ይህንን ድርጊቷን በስፋት እንደቀጠለችበት ይታያል” ሲል አስጠንቅቋል። 37 ገጽ የያዘው የመረጃ መንታፊዎቹ ክስ ዝርዝር እኤአ ከ2020 ጀምሮ ከፖለቲካ ምርጫ ጋር ተያይዞ የአሜሪካ መንግሥት፣ የደህንነት ባለስልጣናትን፣ መገናኛ ብዙኃንን፣ እንዲሁም ከምርጫ ቅስቀሳ ጋር የተገናኙ ግለሰቦች ላይ ትኩረት አድርገው ሲሰሩ ነበር ይላል።

በ2024 ግንቦት ወር ላይ የፍትህ ቢሮ ሦስቱ መረጃ መንታፊዎች “የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ 1” ላይ ትኩረት በማድረግ ማሴር ጀምረዋል ሲል ይወነጅላቸዋል። ተጠርጣሪዎቹ በምርጫ ዘመቻ ላይ የሚሳተፉ ግለሰቦችን ኢሜል ለማግኘት በሚል ሀሰተኛ የሆነ አድራሻ በመጠቀም እና ራሳቸውን የአሜሪካ ባለስልጣን በማስመሰል ሰነዶችን እና የመረጃ ልውውጦችን ሰርቀዋል ሲል ወንጅሏቸዋል።

በሰኔ ወር ላይ ደግሞ የተሰረቁትን መረጃዎች ለመገናኛ ብዙኃን እንዲሁም “ከአሜሪካ ምርጫ ዘመቻ 2” ጋር ለተገናኙ ሰዎች በማሹለክ “እንደ መሳሪያ ሊጠቀሙበት” መሞከራቸውን ጠቅሶ ይከስሳቸዋል። ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ አንቶኒ ሜሪክ ጋርላንድ የባይደን የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን መረጃዎቹን ተጠቅሞባቸው እንደሆነ ተጠይቀው “ ምንም ዓይነት ፍንጭ አላገኘንም” ሲሉ መልሰዋል።

እንዲሁም ኤፍቢአይ ከትራምፕ እንዲሁም ከባይደን በኋላም ካማላ ሃሪስ ከተረከበው የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን አባላት “ጥሩ ትብብር” ማግኘቱን ገልጸዋል።የካማላ ሐሪስ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን ከሕግ አስከባሪ አካላት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።

“ምንም ዓይነት ሰነድ በቀጥታ ለቅስቀሳ ዘመቻው መላኩን አናውቅም፤ የተወሰኑ ግለሰቦች በግል የኢሜል አድራሻቸው አሳሳች መልዕክቶች የሚመስሉ ተልኮላቸዋል” ብለዋል የካማላ ሓሪስ የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ፀሀፊ ቃል አቀባይ ሞርጋን ፊንክልተይን።

የክሱ ዝርዝር እንደሚያ ስረዳው ከሆነ “የቀድሞ፣ መደበኛ ያልሆ ኑ የትራምፕ የፖለቲካ አማካሪ” ኢሜል በዚህ የመረጃ መንታፊዎች መረብ ውስጥ ወድቋል። እንዲሁም ስሙ ያልተጠ ቀሰ በምርጫ ዘመቻው ላይ ተሳትፎ ያለው ኃላፊ እና እርሱን የሚወክል ጠበቃ ኢሜልም እንዲሁ በመረጃ መንታፊዎቹ እጅ ገብቶ ነበር። የኤፍ ቢአይ ዳይሬክተር ክርስቶፈር ውሬይ በመግለጫቸው ላይ“ዛሬ ለኢራን መንግሥት ኤፍ ቢአይ መላክ የሚፈልገው መልዕክት እናንተ እና መረጃ መነታፊዎቻችሁ ከኮምፒው ተራችሁ ጀርባ ተደብቃችሁ አትቀሩም የሚል ነው” ብለዋል።

በተጨማሪም ክሶቹ “ኤፍ ቢአይ ለረዥም ጊዜ ክትትል ያደረገባቸው እና በሚገባ ያደራጀው ማጠቃለያ የቀረበበት ነው” ብለዋል። ኢራን በእጇ አስገብታዋለች ከተባለው ሰነድ መካከል ከፕሬዚዳንት ትራምፕ ጋር ለምክትል ፕሬዚዳንትነት የሚወዳደሩት እጩ ጄዲ ቬንስ መረጃዎች ናቸው።

እነዚህ ሰነዶች እና ሌሎች መረጃዎች ለበርካታ የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን የተላኩ ሲሆን፤ በስፋት የተሰራጩት ግን ሐሙስ ዕለት ኬን ክሊፔኒስቴይን የተባለ ጋዜጠኛ በግል ጦማሩ ላይ ካጋራቸው በኋላ ነው። ክሊፔይንስቴይን “ሮበርት” የተባለ ግለሰብ ሰነዶቹን እንደላከለት የገለጸ ሲሆን፤ ወዲያውኑ ከኤክስ ገጹ ላይ ታግዷል። ኤክስ ባወጣው መግለጫም የግለሰብን መረጃ ይፋ በማድረግ ላይ ያለውም መመሪያ ጥሷል ማለቱን ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን መስከረም 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You