ዓመተ ምሕረት ከቀየርን እነሆ ዛሬ 19ኛ ቀናችን ነው። መስከረም ዘመን የሚቀየርበት ወር ስለሆነ ሙሉውን ‹‹አዲስ ዓመት›› ተብሎ ይጠራል። በታሪክ ውስጥ ደግሞ ዓመተ ምሕረት ትልቅ ቦታ አለው። በምንጠቅሳቸው ታሪኮች ውስጥ ‹‹ከ…ዓመታት በፊት›› የምንለው ቁጥሩ እየጨመረ ይሄዳል ማለት ነው። በሌላ በኩል አዳዲስ ተጨማሪ ታሪኮች ይኖራሉ ማለት ነው። ለምሳሌ፤ ከሦስት ዓመት በፊት በዚህ ሳምንት የሙዚቃው ንጉሥ ጥላሁን ገሠሠ ይታሰብ ነበር። እነሆ ከ2015 ዓ.ም ወዲህ ደግሞ አርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅ ተጨመረ ማለት ነው። አንደኛው በውልደት አንደኛው በሞት የዚህ ሳምንት ክስተቶች ይሆናሉ ማለት ነው። ‹‹ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም›› የሚባለው ለታሪክ ክስተቶች ነው።
ከዘመናት በፊት የተከሰቱ የዚህ ሳምንት የታሪክ ክስተቶችን ስናስታውስ ቅይጥ ሆነው እናገኛቸዋለን። ለዛሬው አንዱን ብቻ መርጠን በዝርዝር ከማየት ይልቅ የሁሉንም አጠር አጠር አድርገን ማየት መረጥን። በቀናቸው ቅደም ተከተል መሠረት እንያቸው።
ከ78 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት መስከረም 15 ቀን 1939 ዓ.ም የመጀመሪያው የአማርኛ ረጅም ልብወለድ መጽሐፍ (‹‹ጦቢያ››) ደራሲ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ገብረኢየሱስ ዘብሄረ ዘጌ አረፉ። አፈወርቅ ገብረኢየሱስ በሀገርኛ ቋንቋ በመጻፍ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመጀመሪያው ጥቁር አፍሪካዊ የተባሉ ናቸው። በፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት ‹‹የኢጣሊያ መንግሥት መልዕክተኛ ሆነው አገልግለዋል›› ተብለው የዕድሜ ልክ እስራት የተፈረደባቸው፣ የእቴጌ ጣይቱ ዘመድ (ግን ደግሞ እቴጌዋ በአንድ የስዕል ሥራ ምክንያት የጠሏቸው) ናቸው። አፈወርቅ ገብረኢየሱስ የኢጣሊያ መንግሥት መልዕክተኛ ሆነው በማገልገላቸው ከመታሰራቸውም ባሻገር በታሪካቸው ‹‹ባንዳ›› የሚል ወቀሳ አትርፈዋል።
‹‹ጦቢያ›› በሚለው መጽሐፋቸው የመጀመሪያው ረጅም ልቦለድ ጸሐፊ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። መጽሐፉ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ‹‹አጤ ምኒልክ›› የሚለውን በመጨመር ሁለት መጽሐፍ አንድ ሆኖ (በማዟዟር) በገበያ ላይ ይገኛል። በብዙ የሥነ ጽሑፍ መድረኮችና ውይይቶችም ‹‹ጦቢያ›› የሥነ ጽሑፍ መነሻ ተደርጋ ትጠቀሳለች።
አሁን ደግሞ 358 ዓመታትን ወደኋላ እንሂድ። በዚሁ ሳምንት መስከረም 15 ቀን 1659 ዓ.ም ከጎንደር ነገሥታት አንዱ የነበሩት አፄ ፋሲል አረፉ። የአጼ ፋሲል ታሪክ ከጎንደር ነገሥታት ሁሉ ጎላ ብሎ ይታወቃል። አጼ ፋሲል ከ18 የጐንደር ነገሥታት አንዱ ሲሆኑ የአጼ ሱስንዮስ ልጅ እና የአጼ ዮሐንስ አዕላፍ ሰገድ አባት ናቸው። አጼ ፋሲል በታሪክ ውስጥ ዛሬ ድረስ ሕያው እንዲሆኑ ካደረጓቸው ነገሮች አንዱ የዓለም ቅርስ የሆነው የፋሲል ግንብ ነው። አጼ ፋሲል ፋሲለደስ እየተባሉም ይጠራሉ። በዚህም ምክንያት በስማቸው ትምህርት ቤቶችና እና ክፍለ ከተሞች ተሰይመዋል።
ከ95 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት በደመራ ዕለት መስከረም 16 ቀን 1922 ዓ.ም ‹‹ሞገደኛው›› ደራሲና ጋዜጠኛ መንግሥቱ ገዳሙ ተወለደ። መንግሥቱ ገዳሙ በርካታ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች አሉት። መንግሥቱ ‹‹ሞገደኛው›› የሚለው ሥያሜ የተሰጠው ከልጅነቱ ጀምሮ ችኩል፣ ቁጡና ስህተቶችን የማይታገስ ስለነበር ነው ይባላል። በዚህም ምክንያት ሞገደኛ የሚል ቅጽል ስም ተሰጥቶት ያ ስም አብሮት ዘለቀ። ካደገ በኋላም የሰውየው ባሕሪ ወጣ ያለ የሚባል ነበር። በሕይወት እያለ ‹‹መንግሥቱ ገዳሙ ሞቷል›› ብሎ በራሱ ላይ መርዶ ያስነገረ ደፋር ነው። በተደጋጋሚ ሚስት እያገባ በመፍታት ‹‹የሴቶችን ባሕሪ ለማወቅ ነው›› በማለት በራሱ ሕይወት ላይ ጥናት ያደርግ ነበር። የሚሠራበት መሥሪያ ቤት ውስጥ በርኖስ ለብሶ በመግባት ‹‹ኧረ ባክህ የሥራ አለባበስ ሥነ ሥርዓት አይደለም›› ሲሉት ‹‹ባሕሌን ለማስተዋወቅ ነው›› በማለት ይሟገት ነበር። በአጠቃላይ በእነዚህ ባሕሪያቱ ‹‹ሞገደኛው›› የሚል ቅጽል ስም አትርፏል።
ከ108 ዓመታት በፊት የመስቀል ዕለት መስከረም 17 ቀን 1909 ዓ.ም ልጅ ኢያሱ ከሥልጣን ተሽረው፣ ዘውዲቱ ምኒልክ ‹‹ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ›› ተብለው በአባታቸው፣ በዳግማዊ ምኒልክ፣ ዙፋን ተቀመጡ። ደጃዝማች ተፈሪ መኮንንም ‹‹ራስ ተፈሪ›› ተብለው አልጋ ወራሽ ሆኑ። ሙሉ ዝርዝሩን በጥቅምት ወር የሰገሌ ጦርነትን በምናስታውስበት ታሪክ እናስነብባችኋለን።
ከ84 ዓመታት በፊት ልክ የመስቀል ዕለት መስከረም 17 ቀን 1933 ዓ.ም ዝነኛው ድምፃዊ ጥላሁን ገሠሠ ተወለደ። ታሪክህ ከበዓል አይራቅ የተባለው ጥላሁን ገሠሠ የመስቀል ዕለት ተወልዶ ከ68 ዓመታት በኋላ በፋሲካ በዓል ዕለት አረፈ። ፋሲካ የሚውልበት ቀን ስለሚለያይ በየዓመቱ የፋሲካ ዕለት ላይታወስ ይችላል። ሆኖም ግን ያረፈበት ሚያዚያ 11 ቀን 2001 ዓ.ም ይታወሳል። ጥላሁን ገሠሠ በየዓመቱ በብዙ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሲታወስ አስተውያለሁ።
መስከረም 17 ቀን በዓመቱ ጥላሁን ገሠሠን እያስታውስን ሳለ፤ አርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅም የዚሁ ታሪክ አካል ሆነ። አርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅ በድንገት ሕይወቱ ያለፈው ከሁለት ዓመት በፊት መስከረም 17 ቀን 2015 ዓ.ም ነበር።
ከ64 ዓመታት በፊት መስከረም 17 ቀን 1953 ዓ.ም ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት በልዩ ልዩ መንገዶች ለኢትዮጵያ አጋርነታቸውን ያሳዩት እንግሊዛዊቷ የኢትዮጵያ ጠበቃና ባለውለታ ወይዘሮ ሲልቪያ ፓንክረስት አረፉ። ሲልቪያ ፓንክረስት የታዋቂው የታሪክ ምሑርና ልክ እንደርሳቸው ሁሉ የኢትዮጵያ ባለውለታ የነበሩት የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት እናት ናቸው።
ከ160 ዓመታት በፊት መስከረም 19 ቀን 1857 ዓ.ም በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ቁንጅና ውድድር ተካሄደ። ብዙም ሲነገርለት ስለማይሰማ፤ የጳውሎስ ኞኞን አጤ ቴዎድሮስ መጽሐፍ ዋቢ በማድረግ ዘርዘር አድርገን እንየው።
የመስቀል በዓል በዋለ በሁለተኛው ቀን፣ ከልደታ ምሥራቅ ለአበራ ጊዮርጊስ ሰሜን ከሆነችው በቀሃ ወንዝ አጠገብ፣ አጤ ሰቀላ ላይ ከምትገኘው ኮረብታ ላይ የንጉሠ ነገሥቱ ሸራ ድንኳን ተተከለ። ከጧቱ ሦስት ሰዓት ጀምሮ የከተማውና የገጠሩ ሕዝብ በዓሉ ወደሚከበርበት ሜዳ ይጎርፍ ጀመር።
ከረፋዱ አራት ሰዓት ሲሆን ምርጥ መሣሪያ የያዙ ወታደሮችና አጋፋሪዎች ሰልፈኛውን ለማስተናበርና ፀጥታውን ለማስከበር በበዓሉ ሜዳ ተሰማሩ። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ፊታውራሪ ገብርዬ በሠራዊታቸው ታጅበው ሰንደቅ ዓላማ እያውለበለቡ አጤ ሰቀላ ደረሱና የዙፋኑን አቀማመጥ ተመለከቱ።
ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ንጉሠ ነገሥቱ ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ በፈረሶች በሚሳብ ሰረገላ ላይ ተቀምጠው ሊቀ መኳስ ዮሐንስ ቤል ባሠለጠናቸው ወታደሮች ታጅበው መጥተው በዙፋናቸው ላይ እንደተቀመጡ እምቢልታና መለከቱ ተብላላ፤ አጅብር አጅብር፣ ውጋው ውጋው እያለ ነጋሪት ይጎሰም ጀመር።
ዘፋኞች ይዘፍናሉ፤ አዝማሪዎች ይዘምራሉ፤ ወታደሮች ይጨፍራሉ። በዚህ ዓይነት ይዞታ ተድላና ደስታ ሆኖ ሲደባለቅ በመካከሉ ለውድድሩ የታጩት ወይዛዝርት ጥልፍ ቀሚሳቸውን እያንሰረተቱ፣ ተቀብተውና ተኳኩለው ወደተዘጋጀላቸው ቦታ ያልፋሉ።
ቀጥሎም ምርጫው በሚፈፀምበት ጎል እየገቡ ውበታቸውና ደም ግባታቸው፣ የላሕየ ገፃቸው አወራረድ፣ የፀጉራቸው ስሬት፣ የቁንዳላቸው ርዝመት፣ ሽንጣቸው፣ ዳሌያቸውና ተረከዛቸው እየተመረመረ የምርጫው ሥነ ሥርዓት ይጀመራል። እንዲህ እየተደረገም ከሰቀልት ወረዳ ከመቋሚያ ማርያም የመጣችው ትውልዷ ከመቄት አዝማቾች ወገን የሆነችው የደጃዝማች ይልማ አሰፋ ልጅ፣ ጣይቱ ይልማ አንደኛ ስትሆን፣ ከጎንደር አዲስ ዓለም የመጣችው የመሐመድ ኩርማን ሚስት የሼህ መሐመድ ጌታ ልጅ፣ ተዋበች መሐመድ ደግሞ በፀጉሯ ማማር፣ በቁንዳላዋ አወራረድና መርዘም ሁለተኛ ደረጃን አገኘች።
ከዚህ በኋላ ፊታውራሪ ገብርዬና ሊቀ መኳስ ዮሐንስ ቤል የምርጫውን ውጤት ለንጉሠ ነገሥቱ ለመንገር ወደ ዙፋኑ ቀረቡ። ወዲያውም ጣይቱ ይልማ አንደኛ፣ እንዲሁም ተዋበች መሐመድ ጌታ ሁለተኛ መሆናቸውን ከገለፁ በኋላ ተመራጮቹ ከዙፋኑ ፊት በመቅረብ እጅ እየነሱ ሽልማታቸውን ተቀብለው የበዓሉ ፍፃሜ ሆነና እንደተለመደው በሰባት ሰዓት ለመሳፍንት፣ ለሊቃውንት ለመኳንንትና ለካህናት የምሳ ግብዣ ተደረገ።
ከውድድሩ በኋላ ኦርማኤል (ወርመር) የተባለው በጋፋት የመድፍ ሠራተኞች አለቃ አንደኛ የወጣችውን ጣይቱ ይልማን በሚስትነት አግብቶ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ወልደዋል። ጋይንት ውስጥ አሁንም በኦርማኤል ስም የሚጠራ መሬት አለ።
በምዕራቡ ዓለም ደግሞ ዘመናዊ የቁንጅና ውድድር መካሄድ የጀመረው በ1831 ዓ.ም በስኮትላንድ እንደሆነ የታሪክ ማስረጃዎች ያሳያሉ። በወቅቱ ተደርጎ በነበረው ውድድር ያሸነፈችው ከገዢ መደብ አባላት የሆነች ሴት እንደነበረች ተፅፏል።
በ1847 ዓ.ም በአሜሪካ የቁንጅና ውድድር ለማድረግ ተሞክሮ ብዙ ሳይጓዝ መቋረጡም ይነገራል። የቁንጅና ውድድር በመላው ዓለም በስፋት እየታወቀ የመጣው ግን በ1881 ዓ.ም በቤልጂየም ከተካሄደው የቁንጅና ውድድር ወዲህ እንደሆነ ማስረጃዎቹ ያመለክታሉ። ለማንኛውም ኢትዮጵያ የቁንጅና ውድድርን የጀመረችው ከ159 ዓመታት በፊት ነው።
ከ89 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት መስከረም 23 ቀን 1928 ዓ.ም ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ወረረች። ይህም የአምስት ዓመቱ የፋሽስት ጣሊያን ቆይታ መጀመሪያ ሆነ ማለት ነው።
ከ108 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት መስከረም 24 ቀን 1909 ዓ.ም ንጉሥ ሚካኤል ዓሊ በልጃቸው፣ ልጅ ኢያሱ ከሥልጣን መወገድ ምክንያት ተበሳጭተው ጦራቸውን አስከትተው ወደ ሸዋ እየገሰገሱ እንደሆነ የሰሙት የማዕከላዊው መንግሥት ሹማምንት (የሸዋ መኳንንት) ለንጉሥ ሚካኤል ደብዳቤ ጻፉላቸው። ደብዳቤውም ይህ ነበር።
‹‹..ይድረስ ከንጉሥ ሚካኤል። ዘሥልጣኑ ጽሑፍ ዲበ መትከፍቱ ንጉሠ ጽዮን።
ልጅዎ ልጅ ኢያሱ አልጋ ወራሽ ከሆኑ ጊዜ ጀምሮ እስከዛሬ የሚሠሩት ሥራ ሁሉ የልጅ ሥራ እንደሆነ ንጉሡም ያውቁታል። እኛም መክረን ተቆጥተን እናሳድጋለን ብለን ብናስብ ባንድ ስፍራ የማይቀመጡ ስለሆነብን ጊዜ አላገኘንም። አንዳንድ ጊዜም እያገኘን ብንመክራቸው አልተቀበሉንም። እኛም ምናልባት ከነገ ሣልስት የመንግሥታቸውን ጥቅም፤ የራሳቸውን ማዕረግና ክብር እያወቁ ይህን የልጅነት ሥራቸውን ይተውት ይሆናል በማለት ሰውነታቸው እንዳይሳቀቅ ታግሰን ብንጠብቃቸው የልጅነት ሥራ መሥራታቸው አልበቃ አላቸው። … ይህንንም ሁሉ ታግሰን ሁላችንም ባንድነት ሆነን ሊቀ ጳጳሱንና እጨጌውን ጨምረን ለማናቸውም ቢሆን ለእንቁጣጣሽ (ላዲሱ ዓመት) ወደ አዲስ አበባ ይምጡ ብለን ደብዳቤ ጽፈን ብንልክላቸውም ሳይመጡ ቀሩ። ይህንም ሁሉ ለንጉሥ መጻፋችን አጼ ምኒልክን እኛንም ሁሉ እንዲወዱ እናውቃለንና አሳብዎ ከአሳባችን ሳይለይ በአንድነት እንድንቆም እንጂ በተለየ ንጉሥ እንዲቀየሙና ልጅ ኢያሱ እንዲጎዱ ብለን ያደረግነው አይደለም። መስከረም 24 ቀን 1909 ዓ.ም…››
ከ8 ዓመታት በፊት መስከረም 25 ቀን 2009 ዓ.ም ወደር በሌለው የጦር ሜዳ ጀግንነታቸው የሚታወሱት ብርጋዴር ጀኔራል ለገሠ ተፈራ ወልደሥላሴ አረፉ።
አምስት የሶማሊያ ተዋጊ ሄሊኮፕተሮችን ያጋዩት፣ የሶማሊያን ተዋጊ ጄቶች እርስ በእርሳቸው አላትመው ያነደዱት፣ ጀት አብራሪው እና የበረራ አስተማሪው፣ የሐረር ጦር አካዳሚ ምሩቁ፣ ሳይሰለቹ የመብረር፣ በአየር ላይ የመገለባበጥ፣ ዒላማ የማስገባትና ምንም ጭስ ሳያሳዩ የማረፍ ልዩ ተሰጥዖዎች ባለቤቱ፣ የፕሬዚዳንት ራውል ካስትሮ ልዩ እንግዳና ተሸላሚው፣ ወደር የሌለው የኅብረተሰባዊት ኢትዮጵያ ከፍተኛ የጀግና ሜዳይ ተሸላሚው፣ ‹‹ሸንቃጣው፣ ሽቅርቅሩና መልከ መልካሙ›› የሚባሉት፣ የወይዘሮ አልማዝ አምሐ ባል፣ የነፃነት እና የሉሊት አባት፣ ጀግናው ብርጋዴር ጀኔራል ለገሠ ተፈራ የዚህ ሳምንት የታሪክ አካል ናቸው።
ከ51 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት መስከረም 26 ቀን 1966 ዓ.ም ‹‹የዮም ኪፑር›› ወይም ‹‹የረመዳን›› ጦርነት በመባል የሚታወቀው አራተኛው የዓረብ እስራኤል ጦርነት ተጀመረ።
ጦርነቱ በግብፅ እና በሶሪያ የሚመራው የዓረብ አገራት ጥምረት፣ በእስራኤል የዮምኪፑር በዓል ቀን፣ በእስራኤል ላይ ጥቃት ሲሰነዝር የተጀመረ ሲሆን፣ ውጤቱም የእስራኤልን አሸናፊነትና የዓረቦችን ተሸናፊነት ያሳየ ነበር። በአንዳንድ ተንታኞችም ግብጽ ከጦርነቱ መጠነኛ ጥቅም አግኝታለች ይባላል።
በዚሁ ቀን መስከረም 26 ቀን 1974 ዓ.ም የግብፅ ፕሬዚዳንት የነበሩት አንዋር ሳዳት ተገደሉ። ሳዳት የተገደሉት በመጀመሪያዎቹ ቀናት መጠነኛ ድሎችን ያገኙበትንና ከሞታቸው ቀን ልክ 8 ዓመታት በፊት የተጀመረውን የዮም ኪፑር ጦርነት 8ኛ ዓመት መታሰቢያ እያከበሩ ሳለ ነበር።
በካሊድ እስላምቡሊ የተመሩት የሳዳት ገዳዮች፣ ሳዳት ከዮም ኪፑር ጦርነት በኋላ ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ሜናኽም ቤጊን ጋር የተፈራረሙትን የካምፕ ዴቪድ የሠላም ስምምነትን አምርረው የተቃወሙ ፀረ እስራኤል አክራሪዎች ናቸው።
ከ9 ዓመታት በፊት መስከረም 27 ቀን 2008 ዓ.ም አንጋፋው ጋዜጠኛ፣ ዲፕሎማትና የታሪክ ጸሐፊ አምባሳደር ዘውዴ ረታ ወልደአረጋይ አረፉ። አምባሳደር ዘውዴ ረታ ‹‹የኤርትራ ጉዳይ›› በሚለው ግዙፍ መጽሐፍ እና በሌሎች የታሪክ መጽሐፎቻቸው እንዲሁም በዲፕሎማትነታቸው ይታወቃሉ።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን እሁድ መስከረም 19 ቀን 2017 ዓ.ም