ከታላላቅ ውድድሮች በኋላ የአትሌቶች ስሜት መረበሽ

እንደ ኦሊምፒክ ያሉ ታላላቅ ውድድሮች ከመሄዳቸው አስቀድሞ በአትሌቶች ዘንድ ጠንካራ ዝግጅት ማድረግ የተለመደ ነው። በጠንካራ ተፎካካሪነት ሰንደቅን ለማስከበር በአካልና በአዕምሮ ይተጋሉ። በውድድሩ ወቅትም የተቻላቸውን በማድረግ እንዳለሙት ሜዳሊያ ሊያሳኩ ወይም በተለያዩ ምክንያት የተጠበቀው ውጤት ላይገኝ ይችላል። ከሳምንታት ደማቅ የኦሊምፒክ ቆይታ በኋላም ወደየሃገራቸው የመልስ ጉዞ ያደርጋሉ። እንዳገኙት ውጤትና አስቀድሞ ቃል በተገባላቸው መሠረትም በአቀባበል፣ በሽልማት እንዲሁም በተለያዩ መድረኮች እየተገኙ ልምዳቸውን በማካፈል መርሐ ግብር እንደተጠመዱም ሞቅታው ለተወሰኑ ቀናት ይቆያል። ከዚያ በኋላስ የአትሌቶች ሕይወት በምን መልኩ ይቀጥላል?

ለረጅም ወራት የሚኖረው ከባድ የዝግጅት ጊዜ እና ውድድር እጅግ አድካሚ በመሆኑ ተገቢውን እረፍት ማድረግ የግድ ነው። ነገር ግን በዚህ የእረፍት ጊዜ አትሌቱ በአካልና በአዕምሮ ሠላማዊ ጊዜን አሳልፎ ለቀጣዩ የውድድር ዘመን ራሱን ያበቃል? ይህ ሁኔታ በእርግጥም ከስፖርት ቤተሰቡ የራቀ በባለሙያዎች ዘንድ ግን የታወቀና በእጅጉ እገዛ የሚያስፈልገው ድምጽ አልባ ችግር ነው። ምክንያቱ ደግሞ በውድድሩ እና ውድድሩን አስቀድሞ የነበሩ እንቅስቃሴዎች መቋረጣቸው አትሌቶችን ከእረፍት ይልቅ ለስሜትና አእምሮ መቃወስ የሚዳርግ በመሆኑ ነው።

በበርካታ የስፖርት ቤተሰብ ዘንድ እምብዛም የማይታወቀው የአትሌቶች የስሜት ለውጥ ‹‹ፖስት ኦሊምፒክ ብሉስ›› በሚል መጠሪያ የሚታወቅ ሲሆን፤ ከውድድር በኋላ በሚኖሩት ጥቂት ቀናት አሊያም ሳምንታት ሊከሰት ይችላል። ይኸውም ድብርትን፣ ግራ መጋባትን እንዲሁም ስለራስ አሉታዊ አስተሳሰብን ወደማዳበር የሚከት ነው። ጉዳዩ የሚከሰተው ውጤታማ በሆኑትም ሆነ ባልተሳካላቸው አትሌቶች ላይ መሆኑ ደግሞ ጉዳዩ ትኩረት የሚሻ መሆኑን ያመላክታል።

በቅርቡ በተካሄደው የፓሪስ ኦሊምፒክ በሴቶች 800 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ያጠለቀችው እንግሊዛዊቷ ኬሊ ሆድሰን ፋይናንሺያል ታይምስ ከተሰኘው ጋዜጣ ጋር በነበራት ቆይታ ልምዷን አካፍላለች። ከውድድር ውጪ በምትሆንበት ወቅት የጊዜው መርዘም እንዲሁም ቀጣይ ሁኔታን ማሰብ ከአንድ ወር ለበለጠ ጊዜ ግራ መጋባት ውስጥ እንደሚከታት ነው ያንፀባረቀችው። በዲስከስ ውርወራ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት የሆነችው ሌላኛዋ አትሌት ቫለሪ አለምን በበኩሏ ‹‹ስለ ኦሊምፒክ ማሰብ አትሌቶችን በክብር ብቻም ሳይሆን እንደ ልብ መሰበር ያሉ የተለያዩ ስሜቶችን እንዲያስተናግዱ ያደርጋል። በመሆኑም እርስ በእርስ ሃሳብን መካፈል የሚኖረውን ግፊት ሊያስቀር ይችላል›› ስትል ትጠቁማለች።

ዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጉዳዩ ላይ ባካሄደው ጥናት መሠረት ሁኔታው 35 ከመቶ የሚሆኑ አትሌቶች ላይ ሊደርስ የሚችል መሆኑን አረጋግጧል። የስፖርት ሥነልቦና ባለሙያዎች አስፈላጊነትም በውድድር ወቅት የአትሌቱን በራስ መተማመን ከማዳበር ባለፈ በመሰል ሁኔታዎች ላይ እንደሆነም እርግጥ ነው። በአውስትራሊያ የስፖርት ማዕከል ውስጥ የአዕምሮ ጤና እና ክሊኒካል ሳኮሎጂ ቡድን መሪ የሆኑት ኒኮል ቡራቲን ‹‹ጉዳዩ የግንዛቤ ለውጥ እንደሚያስፈልገውና በግልጽ መነገር ቢጀምር ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ይጠቁማሉ። ይህ ችግር የሚፈጠረው እንደ ኦሊምፒክ ያሉ ታላቅ ውድድሮች ድምቀትና ግርግር ሲቀዛቀዝ ሲሆን፤ ሳምንታት ወይም ወራትን ሊቆይም ይችላል። ውጤታማ መሆን ያልቻሉና ጉዳት የገጠማቸው አትሌቶች ላይ ደግሞ ሁኔታው ለረጅም ጊዜ ሊቆይ ይችላል።

የስፖርት ሳይኮሎጂ ባለሙያዋ ዶክተር ካረን ሆዌልስ በበኩሏ፤ ከስሜት ለውጥ ባለፈ የአዕምሮ መናጋትን ሊያስከትል የሚችልና በሥነልቦና ባለሙያዎች ርዳታ ሊደረግበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ለኒው ዮርክ ታይምስ ጠቁማለች። እስካሁንም በኦሊምፒክ ተሳትፎ ይህን ዓይነት ጉዳይ ያላሳለፈ አትሌት እንዳልገጠማትም እንዲሁ። በአሜሪካ የኦሊምፒክ እና ፓራሊምፒክ ኮሚቴ የሥነልቦና ባለሙያ የሆኑት ጄሲቻ በርትሌ ደግሞ ሁሉም አትሌት ሊደርስበት የሚችለው ጉዳይ አለመሆኑን ይጠቁማሉ። ጉዳዩ ውስብስብ ቢሆንም ስሜቱ ግን በእርግጥም አለ። እአአ በ2023 የተደረገ ጥናት የሆላንድ ብሔራዊ ቡድንን ወክለው በኦሊምፒክ ከተሳተፉ 49 አትሌቶች መካከል 40 ከመቶ የሚሆኑት ይህንን ሁኔታ የተጋፈጡ መሆኑን ያረጋግጣል። በኦሊምፒኩ ውጤታማ የነበሩ አትሌቶችንም የሚያጠቃልል ነው።

ይህ ሁኔታ በአስተሳሰብም ሆነ በቴክኖሎጂ በዘመኑ አትሌቶች ዘንድ በዚህ ልክ የሚከሰት ከሆነ በማደግ ላይ ባሉ የአፍሪካ ሃገራት ደግሞ ምን ዓይነት መልክ ሊኖረው እንደሚችል መገመት አያዳግትም። በመሆኑም በጉዳዩ ላይ ግንዛቤ እንዲፈጠርና አትሌቶች ላይ ሲያጋጥምም ምን ማድረግ እንደሚገባ ማሳወቅ ተገቢ ነው። የባለሙያዎቹ ምክርም አትሌቶች እና አሠልጣኞቻቸው ከሥነልቦና ባለሙያዎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማጥበቅ እንደሚያስፈልግ የሚጠቁም ነው። ባለሙያዎቹም ቢሆኑ ከውድድር በኋላ አትሌቶችን ቀርበው መከታተልና ማማከርም ተገቢ ነው።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን መስከረም 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You