ሶሬሳው

“ቦሄም አሰናናሁም!” ይላል ጉራጌ። እንኳን አደረሳችሁ! እያልኩ መኮላተፌ ነውና … “ለምኑ?” ያላችሁ እንደሆን ለመስቀርና ልበል እንደጀመርኩት። “መስቀር መስቀር ቲሰራካ…” መግባባቱ አይሳነንምና መስቀል የመስቀሉ በዓል በደረሰ ቁጥር ሁሉ … ሶሬሳው ቢሆን ኖሮ “ቤተና ሙራ” ባለኝ ነበር። የጎመን ድስት ወጥቶ የምንቸቱ መግባቱ መቼም ቤታችን ሙሉ ቢሆን ነው። “መስቀር ሰና ገኛይ አናርነዴ…” እንሂድ በማለት መስከረም ጠብታ ላደረሰችው የመስቀል በዓል በጉጉት ወደ ቀዬው እየገሰገሰ “የተንቢ!” ሲባል ለመስማት ይናፍቃል። ቀዬው እንደሆን በመስቀል ደስታ ነው። ፌሽታ ነው። የቤተ ጉራጌ ልጆች መስቀልን ወደ ቀዬ ሲሉ ከበሬው ቀጥሎ የማይዘነጓቸው ሦስት ልማዶች አሏቸው። አንደኛው መስቀልና ከእናት አባት ቤት መቅረት ነውር ነው። ሁለተኛው ለቤተሰቦቻቸው የሚሸክፉት ስጦታ ነው። ሦስተኛው ደግሞ የመስቀል ማድመቂያ የቴፕ ማጫወቻ ነው። እናም ከከተማ ቴፑን ገዝቶ፣ ሚሞሪውን አስጭኖ አልያም የካሴት አስቤዛውን አጭቆ ይገባል። በተለይ ወጣቱና ሕጻናት ልጆች ከሥራ ቀጥሎ ፍቅራቸው ለሙዚቃና የባሕል ጨዋታ ነው። ይህቺንም የሚያጣጥሟት በመስቀል በዓል ላይ ነው። በዚህ ውስጥም ከመስቀል ሙዚቃ ጋር ከፍ አድርገው በናፍቆት የሚያስታውሷቸው የሙዚቃው ባለቤቶች አሏቸው። እስቲ ማንን አስታወስክ ብላችሁ እያንዳንዱን ብትጠይቁ ውዱን ልጃቸው ሶሬሳውን ሳይጠቅስ የሚያልፍ አንድም አይኖርም።

“ዝ ሻዶ ሾርካ”፣ “የገንየ”፣ “ቤተና ሙራ”፣ “ህርም ህርም”፣ “ቲያርስና ዝሾታ”፣ “አትከታ የሟኒም አትከታ”፣”አርቴ ያዥመና”፣ “ኸጨዋ ገኘ ሰብ ጨዋ” እኚህና ሌሎችም የእርሱ መታወሻ የመስቀል መድመቂያዎቻቸው ናቸው። አንጋፋው የጉራጊኛ ሙዚቃ ድምፃዊ፣ እንዲሁም የግጥምና ዜማ ደራሲው ደምሴ ተካ (ሶሬሳ) ፍቅርና ክብር የሚደርቡለት ብዙዎችም “አጋዝ” ይሉታል። ይህን ታላቅ ስም ያሰጠው ሥራው ነው። መስቀር መስቀር ቲሰራካ…ደምሴ ተካን አለማስታወስ፣ ከዚም ከዚያም የቴፕ ድም! ድም! የእርሱን ድምፅ ሳይሰሙ ለሰዓታት እንደምን ተብሎ ይቻላል…ወደ የትኛው የቤተ ጉራጌ መንደር ቢያቀኑ በመስቀል ያለ ሶሬሳው ደምሴ ተካ ሙዚቃዎች ቢላው እንኳን ለአራጁ አይታዘዝም። በሠርግ ከሚዜው እስከ ሠርገኛ፣ ሙሽራና ሙሽሪት “ሀይ ሎጋ ሆ ምሽራ ሀይ ሎጋ ሆ…” የምትለዋን ድምፀ ቅላፄውን ካልሰማ በስተቀር ሠርጉም ሠርግ አይመስለው። “ሀይ ሎጋ ሆ” አንዲት ነጠላ ዜማ ብቻ ሳትሆን ከሀገር ምድሩ ጋር የተዋወቀባት ምርጥ የካሴት ሥራው ናት። እስካሁን ከአሥር በላይ የሆኑ አልበሞችን በመሥራት የማይነቀነቅ የባሕል ምሰሶ ሆኗል።

ደምሴ ተካ የተወለደው በ1960 ዓ.ም በኸዣ ወረዳ ውስጥ ነበር። ከዚህ በኋላ ደምሴ አዲስ አበባን ለመርገጥ የፈጀበት ሰባት ዓመታት ብቻ ነበሩ። ደምሴ 12 ዓመት ሲሞላው ያመራው ወደ መርካቶ አልነበረም። በአጎቱ መሪነት በቀጥታ ወደ ደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት ክርስቲያን አምርቶ ድቁና ላይ ደረሰ። በድቁናው ሳለም 1979 ዓ.ም በሀገራዊ ግዳጅ ወደ ብሔራዊ ውትድርና ገባ። የገባበት የባሩድ ሜዳ ግን እንዲሁ እንደዋዛ የሚያልፈው አልነበረም። ፈታኙን የሥልጠና አጥር እየዘለለ በሄደ ቁጥር ሰውነቱ ከሕመም ጋር መፋተግም ጀመረ። የወታደርነቱ ካባ አልሆንህ እያለው ከውስጡ ጋር ብዙ እሰጣ አገባ ውስጥ ሳይገቡም አይቀርም። በዚያ የጦር ደጃፍ ላይ እያለ ጠላትን ከጠመንጃ ይልቅ በድምፅ የሚማርክ ዓይነት መሆኑን ያወቁለት ቀላል አልነበሩም። ከመውዜሩ ቃታ የሙዚቃውን ማይክ ቢጨብጥ የተሻለ አበርክቶ ሊኖረው እንደሚችል መቼም አለቆቹም ያወቁት ይሆናል።

ደምሴ ድምፁ ለሙዚቃ የሰጠ ነበር። በኋላ ላይ ተመልሶ አዲስ አበባ ላይ ተገኘ። እንደተመለሰም ሆነ ከተመለሰ በኋላ የእርሱ ሀሳብ ሙዚቃ ላይ አልነበረም። ሲያስብ ሲፈልገው የነበረው ቀደም ሲል ጥሎት የሄደውን ድቁና ነበር። ሊሆንለት ግን አልቻለም። ወደ ቤተ ክርስቲያኗ ተመልሶ ደጅ ሲጠና ከአንድ ዓመት በላይ ለደርግ መንግሥት በውትድርና ያገለገለ ተመልሶ ለድቁናው አይታጭም ተባለ። ግራ የገባው ደምሴም ቀድሞውኑ ወደ ውትድርናው ዓለም ወደ ላከው አጎቱ ሄዶ ሁኔታውን ነገረው። አጎትም ለዛሬው ደምሴ ፍኖት ለመሆን ወደ በቃውና የቲያትር ባለሙያ ወደ ሆነው ጀንበሬ በላይ ዘንድ አቅንቶ ጉዳዩን አጫወተው። በኔ ጣለው ያለው ጀንበሬ በላይም ደምሴን ይዞ ወደ ብሔራዊ ቲያትር ወሰደው። ሲደርስም እርሱን ሲጠብቅ የነበረ ይመስል በጊዜው በድምፃዊነት ሲያገለግሉ የነበሩ አንድ ሰው በጡረታ ተገልለው ቦታው ክፍት ነበር። ፈታኞች ፊት ለፈተና የቆመው ደምሴ ተካም “ጀማዬ ነይ ነይ፣ ጀማዬ ነይ ነይ..” እያለ ቢዘፍን ጊዜ፤ ትፈለጋለህና አንተም ና! ተብሎ ከዚያው ቀረ። በፈተና ሰዓት ከ”ጀማዬ” አስከትሎ የተጫወተው “ሌዎሌ” የተሰኘው የተሾመ ወልዴ ሙዚቃ፤ ዜማና ግጥሙን ሠርቶ የሰጠው ራሱ ደምሴ ተካ ነበር።

ከአዲስ አበባም ወደ ብሔራዊ ቲያትር እያንኳኳ ገብቶ ለመቀጠር ቻለ። በብሔራዊ ቲያትር መድረኮች ላይ ድምፁን እያስረቀረቀ በጉራጊኛ ሙዚቃዎቹ ምርኮኛዎቹን ሲያበዛ የተመለከተው መልካሙ ተበጀ ሌላ መንገድ አስመለከተው። አልበም ቢሠራ የተሻለ መሆኑን ከምክር ቢጤ ጋር ጣል አደረገለት። የመልካሙ ተበጀ ቃላት በወኔ ያጋሉት ደምሴ ተካም ዓይኑን ሳያሽ ወደ መርካቶ ገሰገሰ። ከሙዚቃ ቤት ወደ ሙዚቃ ቤት፣ ከአንዱ አሳታሚ ወደ ሌላው እያለ ለሥራው ሰው ፍለጋ ብዙ ኳተነ። የካሴት አልበሙን ሊሠራለት ተስማምቶ ሙዚቃዎቹን የተቀበለው አንዱ ባለሙያ፤ ተቀብሎ ስድስት ወር ያህል ከጎለታቸው በኋላ መልሶ ሀሳቡን ቀየረ። ተስፋ ያልቆረጠው ደምሴ እንደገና ለሌላኛው ሰጠው። 12 የጉራጊኛ ሙዚቃ ሳምፕሎችን ሰጥቶ በሌላኛው ጊዜ ለምላሹ ሲመጣ፤ ከሦስቱ በስተቀር ሁሉም ሙዚቃዎች በሌላ መቀየር አለባቸው ሲል ከመርዶ ያልተናነሰውን ምላሽ ሰጠው። ፈተናው አለቅህ ብሎ አንገት የተናነቀው አልበም አሁንም ወደ ሦስተኛው ሰው ተላለፈ። ግን ሦስተኛውም ከእጅ አይሻል ዶማ ሆነ። አንድ ዓመት ያህል ካቆየው በኋላ፤ ማስተሩን የሚሠሩት እነ እገሌ ወደ አሜሪካን ስለሄዱ እስኪመለሱ ለስድስት ወር ያህል ጠብቅ የሚለውን ምላሽ ሲሰማ ግን እልህና ንዴት እየተናነቀው ከዚህ ቀደም ሠርቶለት ወደ ነበረ ሰው ተመለሰ። ወለል ያለችውን የሙዚቃ ስኬት ጎዳና የረገጠው ከዚህ ሁሉ የአሳር ቁጥቋጦና ጥሻ ውስጥ አምልጦ ነበር።

እንዲያው ጥቂት አክሮባት ሠርተን ወደ ኋላ ምልስ ስንል ደምሴ ተካ ምንም እንኳን ድቁናውን ይዞ ስለመቀሰስ እያሰበ የነበረ ቢሆንም አንድ ያላስተዋለው ነገር ነበር። ምንም ማርከሻ የማይገኝላት የሙዚቃ ንብ እዝዝ! ጥዚዝ! እያለች ከአናቱ ላይ እየሾረች ትርኩስ አድርጋ የነደፈችው ገና ያኔ ጨቅላ ሳለ ነበር። እስከ ሰባት ወይም ስምንት ዓመቱ ድረስ የነበረው ክፍለ ሀገር እንደመሆኑ በውል ያላስተዋላቸው ጥቂት የመስቀል በዓልና ሠርጎችን ታድሞ ጨፍሮባቸዋል። ታላላቆቹ ከበሮ እየመቱና ግጥም ዜማ በድምፅ እያወጡ ሲጫወቱ ተከትሏቸዋል። በአንድ የጉራጌ መንደር ውስጥ ልጆች ከልጆች ጋር ሰብሰብ ብለው ከአቻዎቻቸው ጋር እንዳሻቸው እንዲጫወቱ ነፃነት የሚነፍጋቸው የለም። በዝግጅቶች ላይም ቢሆን የአቅማቸውን ቢጨፍሩ ቢያዜሙ ማንም “እረፉ” እያለ የሚያስደነግጣቸው አይኖርም። ማራኪውን የባሕል አጨፋፈር ስልትና የሙዚቃን ጣዕም የሚያጣጥሙት በዚህ የልጅነት ነፃነት ውስጥ ነው። ደምሴ ተካም የተመለከቱትን ሁሉ መሞከር ደስ በሚያሰኘው ዕድሜ ውስጥ ሆኖ በትንሹም ቢሆን ከመንደሩ ልጆች ጋር ይህን ተጋርቷል። እንደ አብዛኛዎቹ ልጆችም በዚያ ጨቅላነት ስለ ሙዚቃ ሳያውቅ ሙዚቃ ግን ነድፋው ነበር። ሳይረዳው የቆየውም ያንን ጊዜ ነው። ግን የያዘ አይለቅምና ምን ቅስና ምን ጵጵስና ቢመኝም ውስጡ በማያውቀው ነገር ሲንቀለቀል ዘግይቶ ይሰማው ጀመረ።

በወቅቱ ሲያገለግል ከነበረበት ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ የ08 ቀበሌ ከፍተኛ የኪነት ቡድን ነበር። ደምሴ ደግሞ ማታ ማታ ትምህርቱን ይከታተል ነበር። ከትምህርት ቤት ጨርሶም ሆነ ሾልኮ እየወጣ የሚፈረጥጠው ወደ ቤት ሳይሆን ወደ’ዚያ የቀበሌ ኪነት ነበር። ድቁናውን በማዕረግ ሙዚቃን በልቡ ይዞ የኪነት ቡድኑን ሲመለከት የማምሸቱ ነገር ከቤተ ክርስቲያን አባቶቹ ጆሮ ደርሶ፤ ኧረ እባክህን አንተ ልጅ! ታስወቅሰናለህ… እዚህ ጊዮርጊስ እየቀደስክ እንደገና እዚያ ልትዘፍን ነው…ቢሉ፣ ቢመክሩት አንድ ጊዜ ተይዟልና ወይ ፍንክች አለ። ይባስ አብሮ ልምምድ ሁሉ ማድረግና መዝፈኑን ጀመረ። የሙዚቃ ስሜቱ ወደ ጡዘት እያሻቀበ ግጥምና ዜማ ሁሉ መድረስ ጀማመረው። ከዚያን ወዲህ የሚያቆመው አልተገኘም። ከሠራቸው ግጥሞች መካከልም አንዱን ለተሾመ ወልዴ አቀበለው። ቀጥሎም ወደ ደምሴ የመጣው ኬኔዲ መንገሻ ነበር። “ሙናናዬ” የሚለውን ግጥምና ዜማ ተቀብሎ ኬኒዲ በመጀመሪያው አልበሙ ውስጥ አካቶታል።

በአቀበት ቁልቁለቱ ሲጓዝ ሙዚቃን ከመሥራትም አልፎ አንጋፋዎችንም ሲያሠራ ብዙ የተጓዘው ሶሬሳው በብሔራዊ ቲያትር ውስጥ ቆይታው የድምፃዊነት ብቻ አይደለም፤ ጎን ለጎን በተለያዩ ውስጣዊ ኃላፊነቶች ውስጥም ትልቅ ሚና ሲጫወት ቆይቷል። የጉራጊኛን ሙዚቃ የሚያዳምጡና ቋንቋውን የሚችሉ ብቻ ሳይሆን እንዲሁ በአጋጣሚዎች ስለ እርሱ የሰሙ ሁሉ አድናቂዎቹ ናቸው። የጉራጌን ባሕልና ሙዚቃ ከፍ አድርጎ በማስተዋወቅ ደረጃ ሶሬሳውን የሚስተካከል ሙዚቀኛ አለ ለማለት ያዳግታል። ከእርሱ በኋላ ለመጡ ለበርካታ የጉራጊኛ ሙዚቀኞች ጥላ ከለላ ሆኗቸዋል። መቼም የማይዘነጉትን የጥበብ መንገድ መርቶ አሳይቷቸዋል። በርካታ ሙዚቀኞችም የሙያ አባታቸው አድርገው ተቀብለውታል። ለአብነትም ተወዳጁ ኃይሉ ፈረጃና ሞክሼው ደምሴ መርሻ በሙያው ውስጥ የሰጣቸውን በልተው፣ የነገራቸውን ሰምተው ያደጉ የአባታቸው ልጆች ናቸው። ደምሴ ተካ ዛሬ ላይ የጉራጊኛ ሙዚቃ የባሕል አምባሳደር ነው።

ሶሬሳው በጉራጊኛ ሙዚቃ ውስጥ ከብዙዎች ለየት የሚያደርገው አንዲት ነገርም አለችው። ሁሉም ጉራጌ፣ ሁሉም ጉራጊኛ ቢሆንም ቋንቋ ግን ልዩ ኅብርን ይዞ በየአካባቢው የሚነገርበት ዘዬ የተለያየና ከአንዱ የሌላው ወጣ ያለው ነው። ደምሴ ተካም በአንዱና በተመቸው ብቻ ሳይገታ ከክስታኔ እስከ እንደጋኝ፣ ከምሑር እስከ እኖርና ሌሎችም ድረስ በመዝለቅ ከግማሽ በማይተናነሱት ዘዬዎች ሁሉ ሙዚቃ አበርክቷል። ወደ የትኛዎቹም ቤተ ጉራጌዎች ጎራ ቢሉ ደምሴ የሁሉም የልብ ትርታ ነው።

በጉራጊኛ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ጥበብ ከፍላ የማትጨርሰውን ውለታ በመዋል አልበሞች በማይወጡበት ጊዜ ሁሉ አድማጩ ፆም ውሎ እንዳያድር እያከታተለ አጥግቦታል። በተለይ ደግሞ ከ1985 እስከ 1990ዎቹ አጋማሽ ድረስ በነበሩት ጊዜያቶች ያበረከተው እድሜ ዘላለሙን እጁን የሚያስም ነበር። በሠራቸው አሥር አልበሞች ውስጥ ያላነሳው የሀሳብ ቅርንጫፍ፣ ያላበላው የዜማ ትርንጎ የለም። ምግባረ ፀዓዳ፣ ደመ ግቡ የሀገር ፍቅር የተሸከመ ስለመሆኑ እልፍ ምስክር ቢኖረውም ምስክር ግን አያሻውም “ኢትዮጵያ አዶተና” ይላታል ሀገሩን። በብስል ትርጓሜው “እናት ኢትዮጵያ” እንደማለት ነው። ደግሞ “ንዝግድና” ያላት እናትና “አባና” ያለው አባትም አለው። ከሥራ መሐል ተወልዶ፣ በሥራ የኖረ ትጋት አይለዬ እጹብ ማንነት አለውና “ቶቺ ሜና” ሲል የደከመን በወኔ፣ ብርቱውን ወደ ፊት በዜማ ያሰልፈዋል። ከሀገር ባሕል፣ እስከ ኑሮ ዘንቢልና ፌስታል ብቻ በዚያ ስርቅርቅ ድምፁ ያልገባበት የለም። ሲያደምጡት በጆሮና ልብ ስበት የሚማርከው ድምፁ በቴፕና ማጫወቻዎች ውስጥ ቢሆን መድረክ ላይ ፈጽሞ አይለዋወጥም። ተፈጥሮ በጥበብ የቸረችው ነውና በየትኛውም ጊዜና ቦታ ቢሆን እንደ አንዳንዶች የሚያሳብብበት ጉንፋን የለም።

ሙዚቃ በደምሴ ተካ ሕይወት ውስጥ ለጥሪ ነብስያው ማረፊያ ከመሆኗም ለኑሮውም መግፊያ ጭምር ናት። ባገኘው የሥራ አጋጣሚ ሁሉ በሠርጎች ላይ እየተገኘ በሠርግ ሙዚቃዎቹ እያደማመቀ አቧራ ሲያስጨስ ይኖራል። በአንድ ወቅት ታዲያ አንድ ሰው ደውሎ በቅርቡ ከውጭ ሀገር መጥታ የምታገባ እህት አለችኝና ተሰናዳ በማለት ይነግረዋል። ሠርጉ የሚካሄደው የትና በምን መልኩ ነው የሚለውን በስልክ ካወጉ በኋላ፤ ለሥራው ቀብዱን የሚከፍልህ አባቴ ነውና እቤት እንድትመጣ በማለት አድራሻውን ሰጠው። ደምሴም ስምምነቱን ለመፈጸም በቀጥታ ወደ ተነገረው ቤት አመራ። በወግ ተቀብለው ከቤት ከገባ በኋላ ምሳ በላ። ጠጣ። ወደ መጣበት ጉዳይ ሲገባም “አባዬ ያው እንግዲ ደምሴ መጥቷል። በቀደም የነገርንህን ነገር ውሉን ይዟልና ቀብዱን ስጠው” ሲሉ ልጆች ለአባታቸው ይነግሯቸዋል። አባትም “የቱ ነው ደምሴ?” ይላሉ። “ዘፋኙ ደምሴ” አባት አሰብ አደረጉና “አላወቁትም” አሉ። ልጆቹም ቤቱ ውስጥ በየፊናው ፈለግ ፈለግ አድርገው የደምሴን ሙዚቃዎች እየከፈቱ አንድ ባንድ አስደመጧቸው። “አሃ! ‘ያሆ ጃማ’ የሚለው ልጅ ነው እንዴ” በማለት ያስታወሱት እየመሰሉ “እና ደምሴ ማለት ይኼ ነው?” “አዎን አባዬ” አሉ ልጆቹ በአንድ ድምፅ። “አይ ደምሴን አውቀዋለሁ ይኼማ እሱ አይደለም። በፎቶ አይቼዋለሁ” በማለት ፈርጠም ብለው አስወጡልኝ አሉ። “ኧረ አባዬ እሱ ራሱ ነው” በማለት በዚህ ቢሉ በዚያ “ዝም በል! ሌባ ተመሳጥራችሁ ገንዘቤን ልትበሉ ነበር! አስወጡልኝ!” ብለው እርፍ! በገዛ ማንነቱ ላይ አንተ አይደለህም ተብሎ ቅንጡን የተመታው ደምሴም እግሬ አውጪኝ ሲል ጥሎ ሄደ።

ሙዚቃ ሕይወት ነው። ሕይወት ደግሞ በውጣውረዶች የታጀበች ትናንት፣ ዛሬና ነገ ናት። ዛሬ ላይ ድንገት ጥቁር ደመና ክልብስ! ሲል ብልጭ የምትል የነገ ተስፋ ደርሳ ታነሳናለች። ለሶሬሳው ደምሴ ተካ ሕይወት የሥራውን ያህል ቀላል ሳትሆንለት ቀርታለች። ዘጠኝ አልበሞችን ከሠራ በኋላ በተደጋጋሚ የሚገጥሙት ነገሮች ትክት ስልችት ቢሉት ጊዜ ከእንግዲህስ አልበም አልሠራም በማለት ለይፋ የተቀራረበ ንግግር አደረገ። የኮፒራይት ጉዳይ እጅግ እንዳንገሸገሸው አልደበቀም ነበር። በቃ ከእንግዲህ አዳዲስ አልበሞቹን ላናደምጥ ነው በማለት ንግግሩን የሰሙ ብዙዎች ተስፋ ቆርጠው ነበር። ነገር ግን ከድቁናው ለይቶ ቅስናውን ያስመለጠው ውቃቤ ሙዚቃ በሀሳብ ቀርቶ መች በፀበልስ የሚለቅ ሆነና… በ2014 ዓ.ም “ሰበና” ሲል አሥረኛውን አልበም በማስደመጥ ሌላ የሙዚቃ ካብ ካበና ተካበ። በጉራጊኛ የአልበም ታሪክ በአሥር የነገሠ የመጀመሪያው በመሆን የንግሥናውን ዘውድ ደፋ። ረዥም እድሜን ከጤና ጋር ለሶሬሳው የጥበብ ልጅ!!

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን መስከረም 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You