
የሊቢያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር መሾሙን አስታወቀ፡፡
ምክር ቤቱ ፋቲ ባሻጋን በአብደል ሃሚድ አል ዲቤይባ ምትክ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ በአብላጫ ድምጽ መሾሙን ቃል አቀባዩ አስታውቀዋል፡፡
ቃል አቀባዩ ካድ አል ቢባስ የተባሉ እጩ ራሳቸውን ከውድድሩ ማግለላቸውን ተከትሎ ባሻጋ ያለምንም ተቀናቃኝ ብቸኛ እጩ ሆነው መቅረባቸውንና በጠቅላይ ሚኒስትርነት መመረጣቸውንም ነው የተናገሩት፡፡ ባሻጋ በዲቤይባ አስተዳደር ስር በአገር ውስጥ ደህንነት ሚኒስቴርነት በማገልገል ላይ ነበሩ፡፡ ሆኖም ዛሬ ዲቤይባን ተክተው የሊቢያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነዋል፡፡
አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አገሪቱን ወደ ተረጋጋ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ሁኔታ ሊመልስ የሚችል መንግሥት ያዋቅራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ከአል ዐይን ጋር ቆይታ ያደረጉ ተንታኞች ገልጸዋል፡፡
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አግባቢነት ከአንድ ዓመት በፊት ጊዜያዊ መንግሥትን መስርተው ሲመሩ የነበሩት ዲቤይባ በበኩላቸው የፓርላማውን ውሳኔ እንደማይቀበሉ አስታውቀዋል፡፡
እሳቸውን ያለ ምርጫ ከሥልጣን ለማስወገድ የተደረገ እንደሆነም ነው በመናገር ላይ ያሉት፡፡ ምርጫ ተካሂዶ አሸናፊው እስከሚታወቅ ድረስ መንግሥታቸው በሥልጣኑ እንደሚቆይም ተናግረዋል፡፡
ሆኖም ባሳለፍነው ታህሳስ ወር ለማካሄድ ቀነ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው አገራዊ ምርጫ በተለያዩ ምክንያቶች መራዘሙ ይታወሳል፡፡ ዲቤይባ ከተቃጣባቸው የግድያ ሙከራ ተረፉ መባሉ አይዘነጋም፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን የካቲት 6/2014