የሀላባ ዞን የተለያዩ ተፈጥሮአዊና ባህላዊ እንዲሁም ሰው ሰራሽ የሆኑ መስህቦች ባለቤት ናት፡፡ ዞኑ ከመዲናችን አዲስ አበባ በሻሸመኔ 313 ኪሎ ሜትር እንዲሁም በቡታጅራ 245 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሲገኝ ከሀዋሳ ከተማ ደግሞ በ87 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ የዞኑ ዋና ከተማ ሀላባ ቁሊቶ ሲሆን በከተማዋም ውስጥ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችና እምነት ተከታዮች በመከባበርና በመቻቻል ለብዙ ዘመናት አብረው የሚኖሩባት ከተማ ናት ፡፡ ዞኑ የተለያዩ ሰብሎችን አምራች ሲሆን ከነዚህም ውስጥ በርበሬ ፣ በቆሎ ፣ ስንዴ፣ጤፍ፣ቦለቄ፣ድንችና የተለያዩ ሌሎችንም ምርቶች በማምረት በአጎራባች ዞኖች እና በተለያዩ የሀገሪቷ ክፍሎች ባሉ ገቢያዎች በማቅረብ ይታወቃል፡፡ በበርበሬ ምርትና በሀገር ደረጃ ከመርካቶ ቀጥሎ ትልቁ እንደሆነ የሚነገርለት የሐሙስ የሜዳ ላይ ገበያ የምትታወቅበት ዋና የገቢ ምንጮቿ ናቸው፡፡
የዝግጅት ክፍላችን ለዛሬ በሀላባ የሚገኙ ባህላዊ፣ ተፈጥሯዊና ሌሎች የቱሪዝም መስህቦችን ከዚህ እንደሚከተለው ያቀርብላችኋል።
የሀላባ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ መንገሳ (ሴራ በዓል)
በወረሃ መንገሳ በየአመቱ በወረዳ ደረጃ በየሁለት ዓመቱ በዞን ማዕከል የሚከበረው የሀላባ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ በዘንድሮ ዓመት ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታዎችን በማገናዘብ በሲምፖዚየም ተከብሮ ማለፉን እናስታውሳለን፡፡
የሀላባ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ሱልጣን ሁሴን እንደሚናገሩት “የዘንድሮው ሴራ በዓል ከወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታዎች ጋር ተያይዞ በቀበሌ ደረጃ በተለያዩ ባህላዊ ክንዋኔዎች ሲከበር መቆየቱን አንስተዋል፡፡
በዞን ማዕከል በሲምፖዚየም መከበሩን የተናገሩት ኃላፊው “የዘንድሮውን ሴራ በዓል የሀላባን ሴራ በአለም አቀፍ ዩኔስኮ ለማስመዝገብ እንቅስቃሴ በተደረገበት ወቅት መከበሩ ልዩ ያደርገዋል” ይላሉ።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር መሀመድ ኑርዬ፤ የሀላባ ብሔረሰብ በረጅም ዘመን ታሪኩ የራሱ የሆነ የዘመን አቆጣጠር ያለው ሲሆን ይህም በወርሃ መንገሳ በተለያዩ ባህላዊ ክንዋኔዎች ሲከበር የቆየና እየተከበረ የሚገኝ መሆኑን ይገልፃሉ። በዘንድሮ አመትም በዞን ማዕከል ተከብሮ ያለፈው የመንገሳ ዘመን መለወጫ ሴራ በዓል እንደ ሀገር ከሚስተዋለው ነባራዊ ሁኔታ አኳያ በባህል ቋንቋና ሲምፖዚየም መከበሩ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም በዞኑ እና ከዞኑ ውጭ በመላው አለም ለሚገኙ የሀላባ ተወላጆችና ወዳጆች ለዘንድሮው የሀላባ ሴራ በዓል በዞኑ ተገኝተዋል፡፡ የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሙህዲን ሁሴን “ሴራችን ለሰላማችን እና ለህብረ ብሄራዊ አንድነታችን” በሚል መሪ ቃል ለተከበረው የሀላባ ሴራ በዓል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። “የሀላባን ሴራ በዩኔስኮ ለማስመዝገብ የሚደረገው ርብርብ ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም ባለድርሻ አካል የበኩሉን አስተዋጾ በአግባቡ ሊወጣ ይገባል” በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ሆገቴ ባህላዊ ሃብት
እንደ ‹‹ሴራ›› አይነት ከትውልድ ወደ ትውልድ የተሸጋገሩ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊቶች ሕዝቦች በሰላም፣ በአንድነትና በፍቅር ተሳስበውና ተቻችለው እንዲኖሩ ያስቻሉ ሀብቶች መሆኑን ይናገራሉ። የሀላባ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ የ‹‹ሴራ›› በዓል ለአስረኛ ጊዜ በሀላባ ዞን ተከብሯል፡፡ የሀላባ ብሔረሰብ ካሉት ትውፊቶች ውስጥ አንዱ የሆነው ጥንታዊ የዳኝነት ስርዓት ‹‹ሆገቴ›› በአካባቢው ሰላምና ፍትህ መስፈን ላይ እየተጫወተ ያለው ሚና ሳይደነቅ የሚታለፍ አይደለም። በአገራችን ለሚከሰቱ አለመግባባቶችም ከዚህ አይነት ልምድ መማር እንደሚገባ የሚያሳይ ነው።
በቅርቡ በዞኑ ተከስቶ በነበረው ችግር የባህሉ መሪ አባቶችና የሃይማኖት አባቶች ከአጎራባች ክልልና ብሔረሰብ መሪዎች ጋር በመሆን እርቅ እንዲወርድ አድርገዋል። ይህን ሲከውኑ ባህላዊ ስርአቱ ታላቅ አስተዋፆኦ ማድረጉን መረጃዎች ያሳያሉ። በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አካባቢዎች በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ወይም
ከሀላባ ባህላዊ ጭፈራ በጥቂቱ፤
አፍራሽ ተልዕኮዎችን ተቀብለው እንደ አገር የተያዘውን የእድገትና ልማት ጉዞ ለማስተጓጎል በእምነቶችና በብሔሮች መካከል ግጭቶችን ለመፍጠር ሙከራዎች እየተደረጉ እንደሚገኙ ይታወቃል። ታዲያ የሀላባን ባህላዊ የዳኝነትና እርቅ ስርአት የመሰሉ በርካታ እሴቶቻችንን ተጠቅሞ ሰላም ማስፈን ይቻላል።
የሀላባ ሕዝብ በሰላም ወዳድነቱ፣ በአቃፊነቱ እንዲሁም ሐዘንና ደስታን ማስተናገድ የሚችል እንደሆነ ይነገራል፤ የሀላባ ቁሊቶ ከተማ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ ትንሿ ኢትዮጵያ ስትሆን ነዋሪዎቿ ያለምንም ልዩነት ተዋደውና ተፋቅረው የሚኖሩባት የሰላምና የፍቅር ከተማ ነች። ለዚህም በሀላባ ብሔረሰብ ዘንድ ‹‹ሆገቴ›› ተብሎ በስፋት የሚታወቀው ፍፁም ዲሞክራሲያዊ የሆነው ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት የድምፅ ብልጫና የሃሳብ የበላይነት የሚንጸባረቅበት መሆኑ አስተዋፅኦው ከፍተኛ ነው።
ነቀታ ሴራ (የሴራ ማሰልጠኛ ተቋም)
ጥንታዊ ሀላቦች ሀገረ መንግስቱ የሚተዳደርበት ሴራ በሴራ ቅቡልነት ያገኙ የህዝቡ ባህልና ወግ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ የዘየዱት ዘዴ ቢኖሮ ታዳጊዎች የህፃንነት ዘመናቸውን አጠናቀው ወደ ወጣትነት በሚያደርጉት ሽግግር በየዓመቱ የስድስት ወር ልምምድና የስልጠና ጊዜ እንዲኖሯቸው ማድረግ ሲሆን ይህም ተቋም “የነቀታ ሴራ” ተብሎ ይታወቃል፡፡
ይህም የስልጠና ተቋም ሲሆን ስልጠና የሚሰጠው ከግርዘኝነት ቀጥሎ ባለው 6 ወራት ውስጥ ሲሆን በዚህ ወቅት ግርዘኞች በሀገር መንግስቱ ውስጥ ያለውን የአደረጃጀት አይነቶችን፤ የስልጣን ክፍፍሎችን፤ የዜጎች የስራ ድርሻዎችን፤ ባህላዊ ክዋኔዎችን፤ ስነ ጥበቦችን፤ የሀገሪቱ የሴራ ስርዓቶችን፤ የማዕረግ ስሞችን፤ ጀግና መፍጠሪያ መንገዶችን ባጠቃላይ ሀገረ መንግስቱ ስርዓት እንዴት እንደሚሰራ በመጀመሪያ ሁለት ወር በንድፈ ሀሳብ ቀጥሎ ባሉት አራት ወራት ደግሞ በተግባር በጫወታና በሚያዝናና ሁኔታ እንዲሰለጥኑና እንዲለማመዱ የሚደረግበት ተቋም ነው።
አሁን ላይ የሀላባ ሀገረ መንግስቱ ነባራዊ ሁኔታ በኢትዮጵያ ሀገረ መንግስት ግንባታ የተቀየረ በመሆኑ የጥንታዊ ሀላቦች ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ብለው ታዳጊዎች እንዲማሩበት ያስቀመጡት የሴራ ማሰልጠኛ ተቋም አሁንም እዚህኛው ዘመን ድረስ ደርሷል። ሆኖም ስልጠና የሚሰጠው ከግርዛት ጋር የተገናኘ ስለነበር የሀላባ ኦገቴ በአንድ ወቅት የሴቶች ግርዘት እንዲቀርና ሴቶች ባይገረዙም በክዋኔው እንዲሳተፉ በተወሰነው መሰረት ተሻሽሎ እንደሚከተለው እየተፈጸመ ይገኛል፡፡
የስልጠናው ሂደት
በሀላባ የዘመን መቁጠሪያ ቀመር መሰረት “ኢብጂ” ተብለው የሚታወቁ ያልተገረዙ ወንድ ህፃናት ‘መሰሮ” ሀምሌ ወር መጀመሪያ ቀኖች ይገረዛሉ። ከተገረዙበት ቀን ጀምሮ ለሁለት ወራት ከቤት ሳይወጡ እየተመገቡ፤ “ገዳሞጂ” ተብለው ከሚታወቁ በቅርብ ዓመታት ከተገረዙ ልጆችና ከቤተሰቦቻቸው የንድፈሀሳብ ልምድ እየወሰዱ ይቆያሉ።
“ኢዳራ” (መሰከረም) እና “መሼታ” (ጥቅምት) በአካባቢው በሚገኙ ትላልቅ ዛፍ (ነቀታ) ስር በቲዎሪ ቤት ውስጥ የተማሩትን በአጠቃላይም የህብረተሰቡን የአኗኗር ብሂል ትውፍታዊ አስተዳደር መዋቅር፤ የፆታ ልዩነት መሰረት ያደረጉ ሚናዎችንና የስራ ድርሻዎችን፤ ባህላዊ እሴቶችን፣ ባህላዊ ጭፈራዎችን ፣ ስነግጥሞችን፣ ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያዎችን፣ የሴራ ደንቦችንንና ህጎችን …ወዘተ በጫወታ መልክ መተግባር ይጀምራሉ።
ከነቀታ ቀጥሎ ባሉት ሁለት ወራት “ከአንቶጎታ” ህዳር እስከ “መንገሳ” ታህሳስ አጋማሽ ከአንድ ቤት ወደ ሌላ ቤት እየተንቀሳቀሱ “ሀዌሻ” ድግስ እየተመገቡ ሁለተኛውን የተግባር ልምምድ ይወስዳሉ።
እንዲህ እያለ ለስድስት ወራት የተከናወነው ስርዓት ለተሳታፊ ልጆች በእድሜ ዘመናቸው በፍፁም ከማይረሷቸው መልካም አጋጣሚዎች ትዝታዎችና
አይረሴ የሕይወት ገጠመኞች መካከል አንዱና ዋነኛ በመሆኑ ግርዘኞች ይሄ የደስታና የክብር የስድስት ወር ጊዜ እንዲሁም የልጅነት ጊዜ እንዲያልቅባቸው አይፈልጉም። ምክኒያቱም ስድስት ወራትን ከፈጀው አስደሳች በጫወታ የታገዘ ክዋኔዎችን ጨርሰው ወደ ወጣትነት ደረጃ፣ ሀላፊነትን ወደ መቀበል የሚሸጋገሩበት የሽግግር ወር በመሆኑ ነው።
ተፈጥሯዊ ሃብት ”የአርቶ ፍል ውሃ‘
ስለ ባህላዊ ሃብቷ ከላይ ካነሳንላችሁ አይቀር በተጨማሪ በውስጧ ስለሚገኙት በርካታ ተፈጥሯዊና እንዲሁም ሰው ሰራሽ መስህቦች መካከል ተፈጥሯዊ በሆነው “የአርቶ ፍል ውሃ” ላይ በማተኮር በውስጡ ያሉትን ድንቅ መረጃ እናስተዋውቃችሁ።
የአርቶ ፍል ውሃ የሚገኘው በአርሾ ቀበሌ ውስጥ ሲሆን ከሀላባ ዞን ዋና ከተማ ቁሊቶ በ10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ይህን ተፈጥሮአዊ መስህብ ከሌሎች መስህቦች ልዩ የሚያደርገው በርካታ ባህሪያት ያሉት መሆኑ ድንቅ አድርጎታል፡፡
ይህ ፍል ውሃ ለብርድ፣ ለቁርጥማት ለተለያዩ ሰውነት ላይ ለሚወጡ ቁስሎችና ለሌሎችም ከጤና ጋር ለተያያዙ በሽታዎች ወዘተ ፍቱን መድኃኒት መሆኑ በአብዛኛው ጎብኝዎች ዘንድ የተመሠከረለት ስለሆነ ልዩ ያደርገዋል፡፡ የአርቶ ፍል ውሃ ሌላው አስደናቂ ነገር ከፍል ውሃው ላይ የተለያዩ ሰብሎች ማለትም እንደ በቆሎ እሸትና የተለያዩ የጥራጥሬ ሰብሎችን በፍል ውሃው ውስጥ በዕቃ/በገመድ በማሰር በሚጨመርበት ወቅት 15 ደቂቃ በማይሞላ ጊዜ ቶሎ በማብሰል የሚታወቅ ነው፡፡ እንዲሁም በአካባቢው ለጉብኝት የመጡ ቱሪስቶች ሻይና ቡናን ለመጠጣት ቢፈልጉ እንኳን የፍል ውሃውን በማንቆርቆሪያ በመቅዳት/በመጨመር/ የተፈጨ ቡና ወይም ሻይ ቅጠልና ስኳር በመጨመር ማፍላት ሳይጠበቅባቸው በዚህ ድንቅ የተፈጥሮ መስህብ መጠቀም መቻላቸው ደግሞ ልዩ ያደርገዋል፡፡
በዚህ መስህብ አካባቢ በፍል ውሃው ለመጠቀም የሚመጣ ጎብኚ በፍል ውሃው ከመታጠቡ ባሻገር በተፈጥሮአዊ ይዘቱ በሚለቀው እንፋሎት በመታጠን የሚያገኘው እርካታ ይበልጥ አስደናቂ አድርጎታል፡፡ የአርቶ ፍል ውሃ በውስጣዊ እምቅ ሀይልና በተፈጥሮአዊ ይዘቱ በመታገዝ ወደ ላይ ከ9 እስከ 12 ሜትር ከፍታ ሲዘል ላየው ምን ያህል አስደሳች እንደሆነ መናገር አያዳግትም። ይህ ክስተት በየቀኑ በ24 ሰዓት ውስጥ አንዴ የሚሆን ነው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ይህ ፍል ውሃ ለሰዎች ከሚሰጠው ፈዋሽ መድኃኒትነቱ ባሻገር ለከብቶችና ለሌሎች ቤት እንስሳት በማጠጣትና አሞሌ ጨውን አብሮ በማብላት ለጤንነታቸው ትልቅ ሚና ያለው ፍል ውሃ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ይህን ፍል ውሃ ከተለያዩ የአጎራባች አካባቢዎችና የሀገሪቱ ክፍሎች እንዲሁም ከዞኑ በየወቅቱ የሚጎበኙት ቱሪስቶች ቁጥር ከፍተኛ ነው፡፡
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን የካቲት 6/2014