አገራቸውን በሥዕል ከገለጹና አሁንም ሥዕል ኃይል እንደሆነ በተለያየ መድረክና አውደርዕይ ላይ እያሳዩ ያሉ ናቸው። በተለይም ሥዕል ታሪክና ቅርስ እንዲሆን ያለፉት ነገር የለም። ሦስት ተከታታይ መጸሐፍት እንዲወጣና ትውልዱ ስለአገሩ ታሪክና የሥዕል ጥበብ እንዲረዳ አድርገዋልም።
በየጊዜው በሚፈጠሩ አገራዊ ሁነቶች ላይ በመሳተፍ አሻራቸውን በማኖር ይታወቃሉም። አሁንም አገር ፈተና ውስጥ ባለችበት በዚህ ወቅት እርሳቸውን የሚመለከቱ ነገሮች ላይ ፊት መሪ ሆነው ይሳተፋሉ። እንዲያውም ኢትዮጵያ በዓለም ደረጃ ለሚዘጋጀው የሥዕል አውደርዕይ ለሁለተኛ ጊዜ ተመርጣለችና ይህ እንዲሳካ ከሚታትሩት መካከልም ናቸው። በዚያ ውስጥም የጀመሩት አፍሪካን የማስተሳሰር ህልም ያለው የአፍሪካ ሰዓሊያን ማህበር ምስረታ እውን የሚያደርጉበትን መንገድ ቀይሰው እየተንቀሳቀሱ ያሉ ናቸው።
በተለያዩ ሲንፖዚየሞች ላይ በመሳተፍ ኢትዮጵያን ዓለም እንዲያውቃት በእጅ ጥበባቸው ከለፉት መካከል ናቸውም። ለዚህ ደግሞ ብዙዎች አመስግነዋቸዋል። በቅርቡ እንኳን የተደረገላቸውን ብናነሳ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አሕመድ ምስጋናና የምስክር ወረቀት አንዱ ነው። ስለዚህም አርቲስት ግርማ ቡልቲን ከብዙ የሕይወት ተሞክሮዋቸው ልምድን እንቀስም ዘንድ ብዙ አውግተውናልና ለዛሬ በ‹‹ሕይወት ገጽታ›› አምድ እንግዳችን አድርገናቸዋል። በእርግጥ ልምዳቸው አባይን በጭልፋ ነውና ጥቂቱን መራርጠን አ ቅርበነዋል። መልካም ንባብ።
ተተኪው ልጅ
እንግዳችን ተወልደው ያደጉት በኦሮምያ ክልል በአርሲ አቦምሳ ከተማ ውስጥ በ1955 ዓ.ም ነው። አቦምሳ ከተማ ለእርሳቸው ልዩ የተፈጥሮ፣ የማንነት መገንቢያ ምድር ናት። ብዙ የልጅነት ትዝታቸው መፍለቂያም ነች። ምክንያቱም ብዙ ጓደኞች፣ ብዙ ቤተሰቦች፣ ብዙ ባህልና ታሪኮችን ያወቁባትና የተማሩባት ናት። ስለዚህም እርሷን ሲያስቡ የልጅነት ጊዜያቸውን ሙሉ ያስታውሳሉና ደስተኛ ሆነው ነው ስለከተማዋ የሚያወጉት። በእርግጥ ስለ ከተማዋ ሲያወሩ አርበኝነቱ ጭምር ነው የሚታወሳቸው። ምክንያቱም ከተማዋ የተመሰረተችው በአርበኞች ነው። ስለዚህም ብዙዎቹ የወታደር ልጅ በመሆናቸው ሙያውን አውቀውና ወደውት ኖረውበታል።
ለእርሳቸውና መሰሎቻቸው ውትድርና ልዩ የልጅነት ፍላጎታቸው ነው። መሆን የሚሹትና እርሳቸውን ጨምሮ ብዙዎች የሆኑትም ነው። በዚህም ደስተኛ ናቸው። በተለይ ካምፕ ውስጥ የሚያሳልፉት ጊዜ እጅግ ተናፋቂ እንደነበረና ሁልጊዜ ቤቴ ቢሆንልኝ ብለው የሚመርጡት እንደነበር ያስታውሳሉም።
አርበኝነቱና ውትድርናው ብዙ ልጅነታቸው ላይ የሰራባቸው ነገር እንዳለ ሁሉ ከማህበረሰቡና ከቤተሰቦቻቸውም ብዙ ነገር ተምረዋል። በተለይም አገርና ሰውን መውደድን ማንነታቸው ሆኖ እንዲኖር አድርገዋቸዋል። ዛሬ በብሔር ተከፋፍሎ እርስ በእርስ መከዳዳት ባለበት ወቅት እንኳን የማይለያዩ ሰዎችን ማግኘት የቻሉት በዚህ ስብዕና ያደጉ ስለነበሩም ነው። ይህ ባህሪ ያላቸው ብዙ ጓደኞች ስላላቸውም ደስተኛ ናቸው። በእርግጥ መሰረቱ የጸና ልጅ በማንኛውም ጊዜ በቀላሉ አይወድቅም። በዚህም እርሳቸውና ጓደኞቻቸው በተከፈለላቸው ዋጋ ልክ እየኖሩ ስለሆነ የጥንቱን ማንነት ይዘው ለሁሉም በሁሉም ይደርሳሉ እንጂ መከፋፈልን አይሰሙትም። ሕብረታቸውን ከምንም በላይ አጠንክረውም ለአገራቸው ለመሥራት ይታትራሉ።
አርቲስት ግርማ በባህሪያቸው ተግባቢ፤ ሕብረት ያለበት ጨዋታ የሚወዱና ተካፍሎ መብላት የሚያስደስታቸው አይነት ልጅ ሲሆኑ፤ ከሁሉም በላይ ውሸትና ስርቆትን የማይወዱ ናቸው። ከዚህ የተነሳም በቤተሰብ ጭምር እንዲሳቅባቸው ሆነዋል። ምክንያቱም የተነገራቸውን የሚያከብሩና የሚኖሩት በመሆናቸው መንገድ ላይ ወድቆ ያዩትን መቶ ብር ሳያነሱ ትተውት ያልፋሉ። ሁነቱን ደግሞ እቤት እንደገቡ ለቤተሰብ ይናገራሉ። የዚህን ጊዜ ሁሉም የቤተሰብ አባል ‹‹የወደቀን አንሳ የሞተን ቅበር›› የሚለውን አባባል እየተረቱ ሳቁባቸው። ነገር ግን በሁኔታው እንዳይበሳጩ ድርጊታቸውን ሳይኮንኑ ነገሮችን በሚገባ አስረዷቸው። ጊዜውም ምን ማድረግና አለማድረግ እንዳለባቸው የተማሩበት እንደነበር አይረሱትም።
ቤተሰብን ማገዝ ከልባቸው የሚወዱት ባለታሪካችን፤ ከብት በማገዱና ውሃ በመቅዳቱ እንዲሁም የእርሻ ሥራዉን ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ በመከወን ደከመኝ ሰለቸኝን ሳያውቁ ይሠራሉ። ከዚያም አልፈው ከትምህርት ቤት ከመጡ በኋላ ምግብ እንኳን በአፋቸው ሳይዞር የጓሮ አትክልቶቻቸውን ይንከባከባሉ።
ይህ ድርጊታቸውደግሞ ቤተሰቡን ብቻ ሳይሆን ጎረቤትንም ከብዙ ወጪ የታደገና እፎይታን የሰጠ ነበር። በዚህ ደግሞ ሁሉም የሰፈሩ ሰው እንዲመርቃቸው ሆነዋል። ዛሬን ያዩትና ለሕይወታቸው መሰረት የጣሉበትም ምርቃቱና ተግባራቸው እንደሆነም አይዘነጉትም። ምክንያቱም መታዘዝንና ሰውን ማክበርን አስተምሯቸዋልና። በብዙ በረከት የተቀደሱበት እንደነበርም አይተውበታል። ለዚህም ነው ከልጅነታቸው ጀምሮ ‹‹በመስጠት ውስጥ ትልቅ በረከት አለ›› የሚለውን መርህ አድርገውታል፡፡
ህልም እውን ሲሆን
ትምህርታቸውን አሀዱ ብለው የጀመሩት በዚያው በትውልድ ቀያቸው አቦምሳ ከተማ ላይ ነው። ትምህርት ቤቱ አርበኞች የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ይባላል። እስከ ስምንተኛ ክፍልም የተከታተሉበት ነው። ከዚያ በዚያ የመማር እድላቸው አናሳ በመሆኑ ወደ አዲስ አበባ መጡ። ዘመድ ጋር ተጠግተውም እስከ 12ኛ ክፍል ተማሩ። ይህ የሆነውም በአዲስ አበባ በቀድሞ አጠራሩ ጂሴ በአሁኑ ደግሞ አብዮት ቅርስ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ነው። በትምህርታቸው በጣም ጎበዝ ተማሪ ናቸው። ይህ ደግሞ ወቅቱ አስቸጋሪ ቢሆንም ዩኒቨርሲቲን እንዲቀላቀሉ አድርጓቸዋል።
ማህበራዊ ሳይንስን የተለየ ትኩረት ይሰጡት ነበርናም ምርጫቸውን አርት በማድረግ የመጀመሪያ ድግሪያቸውን ለመማር በስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ሥር ባለው አለ የሥነጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት አደረጉ። በጥሩ ውጤትም ከዩኒቨርሲቲው መመረቅ ቻሉ። በእርግጥ መሃል ላይ ትምህርቱን አቋርጠውት ነበር። ምክንያቱም ጊዜው ፖለቲካው የተጧጧፈበት ወቅት ሲሆን፤ አብዛኛው ወጣት ደግሞ በዚህ ነገር ውስጥ ይገባ ነበር። እርሳቸውም ብዙም የጠለቀ የፖለቲካ አቅም ባይኖራቸውም ብዙ የሚጋሩት ሀሳብ ስለነበረ ተቀላቅለዋል። እናም በመንገድ ላይ ሆነው እየዘመሩ ሲሄዱ ተይዘው ወህኒ ወርደዋል። በዚህም ምክንያት ትምህርታቸውን መማር አልቻሉም። ነገር ግን ከእስር ከተፈቱ ከሦስት ዓመት የሥራ ላይ ቆይታ በኋላ ዳግም ትምህርቱን እንዲቀጥሉት ሆነዋል።
ሁለተኛ ድግሪያቸውንም ቢሆን ከዚሁ ዩኒቨርሲቲ ሳይወጡ ኮሌጁን ቀይረው ተምረዋል። ይህም ስድስት ኪሎ ግቢ ሲሆን፤ በሙዚዬም ሳይንስ (ሚዚዮሎጂ) የትምህርት መስክ በጥሩ ውጤት የተመረቁበት ነው። እንግዳችን የልጅነት ህልማቸው በሆነው ውትድርናው መስክም ሰልጥነዋል። ይህ የሆነው ግን እንደልጅነታቸው ተመኝተውት አልነበረም። ችግር ውስጥ በመግባታቸው የተነሳ ተማሩት እንጂ። በእርግጥ በመማራቸው ደስተኛ ናቸው። የልጅነት ህልማቸውን ስላሳኩበትም ሌሎቹን ከተማሩበት በላይ በዚህ ሙያ መመረቃቸው ያረካቸዋል።
ወደዚህ ሙያ ስልጠና የገቡት ከላይ እንዳልነው ችግር ውስጥ በመውደቃቸው የተነሳ ነው። በመታሰራቸው የተነሳ ተጠግተው የኖሩበት ሰው ሰምቶ ሁኔታው አሰጋውና ትኩረት እንደዳይሰጣቸው ሆነ። ቤተሰቦቻቸውም በመታሰራቸው ደስተኛ አልሆኑባቸውም። ስለዚህም ትምህርታቸውን አቋርጠው ውትድርናውን ተቀላቀሉ። የመጀመሪያ የስልጠና ቦታቸውን ናዝሬት ላይ አድርገውም መሰረታዊ የውትድርና ኮርስን ወሰዱ። ከዚያ አዋሽ አርባ ማሰልጠኛ ውስጥ በመግባት የታንክ ስልጠናን ተከታተሉ። ሁለቱንም ስልጠናዎች በጥሩ ስብዕናና ተግባር አጠናቀቁ።
ውትድርና ከትምህርቱም በላይ ብዙ ልምድ የሚቀሰምበትና ተሰጥኦን የሚለይበት ቦታ እንደሆነ የሚያነሱት ባለታሪካችን፤ ዛሬም ቢሆን ትምህርት መማር ያለብን ውትድርናው ውስጥ ነው የሚል አቋም አላቸው። በምክንያትነትም የሚያነሱት እያንዳንዱ ትምህርት በፍላጎትና በስብዕና ካልተገነባ ዋጋው ይቀላል። የማሠራትም ሞራል አይኖረውም። በግለኝነት እንጂ በአንድነት ላይ መሰረት ያደረገ ተግባርም አይተገበርበትም። በተለይም ለአገሬ የሚል ነገር በፍጹም አይኖረውም። ሁሉ ነገር ከገንዘብ ጋር እንጂ ከሰውና ከአገር ጋር አይተሳሰርም። በውትድርና ውስጥ ግን መጀመሪያ ሰው ይቀድማል። አገርን ማዳንም የሚታየው ሰውን ከማዳን አንጻር ነው። መቼም ቢሆን ገንዘብ ቅድሚያ አይሰጠውም። ይህ ደግሞ ብዙ ነገራችንን የሚያደላድልልን ነው ይላሉ።
ውትድርና ውስጥ መማር ሲጀመር ሌላው የሚገኘው ነገር በአገር ውስጥ ብቻ አለመወሰንን ነው። ውጪ ድረስ ሄዶ መማርም መሥራትም የሚቻልበት ሙያ ነው። ምክንያቱም ትኩረቱ ሰው ነው። እናም በዚህ ቦታ ላይ ገብቶ መሰልጠን ማለት እውነትም ሰው መሆን ነው ይሉታል። መሆን የማንችል የሚመስለን ሁሉ እንደሚሆንልን የምናረጋግጥበት ቤትም እንደሆነ ይናገሩለታል። ትዕግስትን፣ ሰውኛባህሪንና አገር መውደድን ለመማር የሚፈልግ ሁሉ ውትድርናን ይቀላቀልም ሲሉ ይመክራሉ።
የእናትም የአባትም ስጦታ
የሥዕል ትምህርትቤታቸው እናትና አባታቸው ናቸው። ከእነርሱ ጋር ሲጫወቱ ልዩ እንክብካቤያቸው የሚጀምረው ጭቃ አቡክተው በሚሰሩላቸው ልዩ ልዩ ቁሳቁስ ነው። አባታቸው ወታደር ስለሆኑ ከጭቃ የሚሰሩላቸው መጫወቻዎች ሁልጊዜ ከውትድርናው ጋር የተያያዘ ሲሆን፤ ለምሳሌ ፈረስ፣ ወታደርና መሳሪያ የመሳሰሉት ናቸው። እናታቸው ደግሞ ብዙ የገጠር ላይ ቁሳቁሶችን ከጭቃ ሰርተው ያጫውቷቸዋል። ብልሁ አርቲስት ግርማም የሁለቱን ሥራ በጥልቀት በማየት በየቀኑ ይለማመዱ ነበር። ልምምዳቸውና ልዩ ትኩረታቸው ደግሞ ያሰቡትን እንዲሰሩ አግዟቸዋል። እንዲያውም ከእነርሱ ልቀው ወደ ወረቀት የመቀየሩን ምስጢር ተራቀውበታል። ይህ ደግሞ የዛሬ እንጀራቸውን በር ከፍቶላ ቸዋል።
በእነ አርቲስት ግርማ ቤት ሁሉም የራሱ ተሰጥኦ ነበረው። እንደርሳቸው የሥዕል ሙያ ያለው ግን አልነበረም። እናትና አባታቸው ሁሉንም ልጆች ሲያጫውቱ በጭቃ የተለያዩ ቁሳቁሶችን እየሰሩ ቢሆንም ማንም ትኩረት ሰጥቶት አያውቅም። ከእርሳቸው በስተቀር። ይህ ደግሞ የሚያሳየን ልዩ ሥጦታችንን የምናገኘውና የምንለምደው በተለያየ መንገድ እንደሆነ ነው።
ወሰን የሌለው አገልጋይነት
ውትድርናው የልጅነት ህልም መጀመሪያቸው ብቻ አልነበረም፤ የሥራ ፊደል አስቆጣሪያቸውም እንጂ። በዚህም ሥራን ‹‹ሀ›› ብለው የጀመሩት በሙያው ሰልጥነው በናዝሬት አራተኛ ታንከኛ ብርጌድ አራት መቶ አንደኛ ሻለቃ ውስጥ ነበር። ለሦስት ዓመት ያህል በቦታው ላይ አገልግለዋል። ብዙው አገልግሎታቸው ግን በአስተዳደር ሥራ ላይ ያለፈ ነው። ስለዚህም ውጊያ ውስጥ ገብተው እንደማያውቁ ያነሳሉ። ግን ሙያዊ ተግባሩንና ተልዕኮውን በተሳለጠ ሁኔታ እንደተገበሩት አይረሱትም። ምክንያቱም ወታደር መሆን መሳሪያ ይዞ፣ ጦር ምሽግ ውስጥ ገብቶ፣ ተዋጊ መሆን ብቻ አይደለምና። እናም ሦስት ዓመታትን ናዝሬት፣ አዋሽ አርባና አዲስ አበባ መከላከያ ውስጥ በማለት አሳልፈውታል። ብዙ ስንቅ ይዘውም እንደወጡበት ያስታውሳሉ።
የውትድርናውን ሥራ ተማርኩበት እንጂ ሠራሁበት አይሉም። ምክንያቱም እየሠሩ የተማሩት ነገር ይበዛልና። በተለይም ከአንድነት፣ አገርን መውደድና ስነምግባር ጋር ተያይዞ ያገኙት ማንነት መቼም የማይሸረሸርና እንደ አለት የጠነከረ በመሆኑ ከሥራዬ ይልቅ የተማርኩት ይበልጣልና ሰራሁበት ሳይሆን ተሰራሁበት ማለትን እፈልጋለሁ ይላሉ።
ሌላኛው የሥራ ምዕራፋቸው የስዕል ሙያውን በመያዝ የሠሩበት ሲሆን፤ በርካታ ተቋማትን ረግጠውበታል። የመጀመሪያቸው መስሪያ ቤታቸው የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ነው። የስዕል ዲዛይንና ኦዲዮቪዥዋል ባለሙያ ነበሩ። ብዙ ዓመታትም ቆይተውበታል። ከዚያ አሁንም ከአዲስ አበባ ሳይወጡ ማስታወቂያ ቢሮ ውስጥ ተቀጠሩ። ይህም እንደቀደመው በሙያቸው ያገለገሉበት ሲሆን፤ በዋናነት ግን በኦዲዮቪዥዋል ሥራ መሪነት የሚሠሩበት ነበር።
ቀጣይ የሥራ ቦታቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ውስጥ ሲሆን፤ በተለያየ ክፍሎች ውስጥ በመግባት አገልግሎት ሰጥተዋል። ለአብነት የባህል ተመራማሪነትና ሱፐርቪዥን ኦፊሰርነት፤ በሕጻናትና ወጣቶች ቴአትር ቤት በዲዛይንና ኦዲዮቪዥዋል ክፍል ኃላፊነት የሠሩባቸው ዋና ዋናዎቹ ናቸው። ከዚያም ወደ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚዬም በማምራት አሁን እየሠሩበት ያለውን ሙያ ተቆናጠጡ። ይህም በስነጥበብ ኪዩሬትን እያገለገሉ ያሉበት ነው። በዚህ ሥራቸው ስምንት ዓመታትን አስቆጥረዋልም።
ሌላው ከሥራቸው ጋር ተያይዞ የሚነሳው የሌሎች ሰዓሊያንን ታሪክ ማስቀመጥ መቻላቸው ሲሆን፤ ለዚህም ማሳያው ‹‹ የኢትዮጵያ ስነጥበብና ቅርሶች›› በሚል ሦስት መጸሐፍትን ለንባብ ማብቃታቸው ነው። በተመሳሳይ የስዕል ጥበቡን ለማሳደግና ታሪክን ለመትከል በዓመት ሁለት ጊዜ የስዕል ኤግዝቢሽኖችን ያዘጋጃሉ። እንዲያውም በዚህ ዓመት ለ32ኛ ጊዜ ማዘጋጀታቸውን ያስታውሳሉ። ይህ ደግሞ የሚያሳየው ሕዝብን ከአገር ጋር በስነ ስዕሉ ከማስተሳሰር አኳያ አሻራቸውን ሳያስቀምጡ ማለፍ አለመፈለጋቸውን ነው። በአብዛኛው ሥዕሎቻቸው ደግሞ ትኩረት የሚያደርጉት ባህልንና ታሪክን ሲሆን፤ የገጠሩን ሕይወት በስፋት ይዳስሳሉ። በዚህም ሕዝብን ከባህሉና ታሪኩ ጋር ያስተሳስራሉ፤ የማይረሳው ማንነት እንዳለውም ያስተምራሉ።
አርቲስት ግርማ ሥዕላቸውን በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም ደረጃ እየተዘዋወሩ ያሳዩና አገራቸውን ያስተዋወቁም ናቸው። ከአሳዩባቸው ቦታዎች ውስጥም ማዘጋጃ ጋለሪ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚዬም፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ የኦሮሞ ባህል ማዕከል፤ ብሔራዊ ቴአትርና በኢትዮጵያ ባሉ የውጪ ኢምባሲዎችና ባህል ማዕከላት ላይ በዋናነት ይጠቀሳሉ። በፓን አፍሪካን ጋላሪና ኳታር ዶሃ ከተማም እንዲሁ ስዕሎቻቸውን ካሳዩባቸው መካከል የሚነሱ ናቸው። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያን ዓለም እንዲያውቃት ብዙ ከለፉ መካከል እንዲጠቀሱ ያደርጋቸዋል።
በአሳሳል ዘያቸው የተለዩ አርቲስቶችን መርጦ የሚያሳትመው የአፍሪካ ጆርናል መጽሔት በ2012 ዓ.ም በዓለም ከተመረጡ 10 ሥራዎች ውስጥ ኢትዮጵያን ወክሎ እንዲገባ ከተደረገላቸው አንጋፋ ሰዓሊያን መካከል አንዱ የሆኑት እንግዳችን፤ የኢትዮጵያ ሰዓሊያን ማህበርን ከመመስረቱት መካከል ይጠቀሳሉ። የተለያዩ ሥራዎች ላይ ሲሳተፍም በግንባር ቀደምነት ከጎኑ የሚቆሙም ናቸው። የሥዕል ማህበራት በክልልም ደረጃ ሚናቸው እንዲጎላ በማድረግ ፣ ታሪክና ባህልን ለዓለም ጭምር በሥዕሉ ዘርፍ በመሰነድና በማስተዋወቅ ፤ አማተር ሰዓልያንን በማስተሳሰርና ልምዳቸውን ለሌላው እንዲያካፍሉ በማድረግም ያላሰለሰ ጥረት ያደረጉ ናቸው።
እንግዳችን የስነጥበብ ቅርሶች ከሌሎች ቅርሶች እኩል እንዲታዩ ያደረጉና ሰዓሊያንና የሚመለከታቸው አካላትን በማሳመን አሁን ድረስ እየተጉ ያሉ ሲሆኑ፤ የስነ ሥዕል ጥበብ በአገር ደረጃ አንድ እርምጃ ከፍ እንዲል ጠጠር ወርውሪያለሁ ይላሉ። በተለይም በስነጥበብ ዙሪያ ብዙ የተጻፉና የተጠኑ ምርምሮች ባለመኖራቸው ይህ እንዲሆን ብዙ መልፋታቸውን ይናገራሉ። ‹‹የኢትዮጵያ ስነጥበብ ቅርሶች›› በሚል ከጥንታዊው እስከ ዘመናዊው የኢትዮጵያ የሥዕል አሳሳል ጥበብንና የኢትዮጵያ ሰዓሊያንና ሥራዎቻቸው ምን ይመስላሉ የሚለውን የሚያሳይ ሦስት ተከታታይ መጸሐፍት እንዲዘጋጅ ያደረጉትም በዚህ ምክንያት እንደሆነ ያነሳሉ። አሁንም ይህን ሥራ እንደሚያስቀጥሉት አጫውተውናል። ሌላው ለአገሬ አበርክቻለሁ ያሉን ሲሆን፤ በግድቡ፣ በትልልቅ በዓላትና መንግስታዊ ስብሰባዎች ላይ በሙያቸው መሳተፋቸው አገር በምትፈልጋቸው ተግባር ላይ ሁሉ እንዳሉ ያሳዩበት መሆኑን አንስተውልናል።
አሁን ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ለመሞገትም እየሰሩ ይገኛሉ። አንዱ የሚመጡ እድሎችን መጠቀም ሲሆን፤ በቅርቡ ኢትዮጵያ የተመረጠችበትና ዓለምን በተአምረኛነቷ የምትማርክበት ዓለማቀፉ የሥዕል አውደርዕይ ነው። እናም ይህንን ከመጠቀም አንጻር እርሳቸውና ሌሎች አጋሮቻቸው ብዙ እየለፉ መሆኑን ያስረዳሉ። እርሳቸው እንዳሉን፤ ይህ ሲንፖዚዬም ለአገራችን ትልቅ ትርጉም ያለው ነው። ብዙ ነገራችንን የምንሸጥበትና የኢኮኖሚ በራችንን የምንከፍትበት ነው። ፖለቲካውንም ቢሆን ለማረጋጋት ሰፊ እድል ይሰጠናል። ስለዚህም እንጠቀምበታለን ብለውናል።
ሥራዎቻቸውን በዚህ ሲንፖዚዬም ላይ ለማቅረብ የሚመጡ ብዙ አገራት ይኖራሉ። ይህ ደግሞ የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታና ታሪክ እንዲሁም ባህልና ሁነት አይተው እንዲመለሱ ያደርጋቸዋል። ከዚያ እነርሱ ብቻ ሳይሆኑ አጋሮቻቸውም ሆኑ ዜጎቻቸው እውነቱን እንዲረዱ ይሆናሉ። ወደፊትም ስለ አገራችን የሚባለውን እንዳያምኑ ያደርጋቸዋል። በዚህም አገር ብዙ ደጋፊ ይኖራታል፤ አጋዥና እርሷን ለማየት የሚጓጓውን ያበረክትላታል። ስለሆነም ሲንፖዚዬሙን እንደ አገር ብቻ ሳይሆን እንደ አፍሪካ ጭምር ለመጠቀም መዘጋጀታቸውን ያነሳሉ።
አርቲስት ግርማ ለዓለም ሲንፖዚዬም ዝግጅቱ ብቻ አይደለም የተዘጋጁት። ቀድመው እየተንቀሳቀሱበት ያለውን የአፍሪካ ሰዓሊያን ማህበር ማቋቋምን እውን ለማድረግም እየተጉ ነው። ምክንያቱም ይህ እድል ብዙዎችን ያገናኛል። በተለይም አፍሪካውያንን በእጅጉ የሚያጣምር ነው። እናም ኢትዮጵያ እንደ አፍሪካ ህብረቱ ሁሉ የአፍሪካ ሰዓሊያን ማህበርን ምስ ታ ቀዳሚነቷን በዚህም እንድትደግመው ለማድረግ ይሠራሉ። ይህ ሆነ ማለት ደግሞ የአህጉሪቱን የእርስ በእርስ ትስስር አሰፉ ማለት ነውና ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ እንደሚሳተፉበት አውግተውናል።
ጥበብ ኃይሏን ገልጣ ብዙዎችን ታናግራለችና የእርስ በእርስ መቃረኖችን ጭምር በውይይት እንድንፈታና ወደ አንድነት እንድንመጣ እንዲሁም ኢኮኖሚያችንን እንድንገነባ ከዚያም ባለፈ ፖለቲካውን በጋራ ተግባር ላይ እንድንመራው ሥራው ያስፈልገናልና እንደ አህጉር አስበን የምንሰራበት ይሆናልናም ብለውናል።
ሽልማቶች
ለአበረከቷቸው ሥራዎች ከበርካታ አካላት ሽልማትን አግኝተዋል። በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አንጋፋ አርቲስቶችን ሲሸልሙ የተሰጣቸው በዋናነት የሚነሳ ነው። በተመሳሳይ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በተለያዩ ጊዜያት ላደረጉት ተሳትፎ ምስክር ወረቀት አበርክቶላቸዋል። የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም፣ ወላቦ ፊልም ፕሮዳክሽንና የአቢሲንያ ሽልማት ድርጅት የተለያዩ ሽልማቶችን ካበረከቱላቸው መካከል ይጠቀሳሉ።
እንግዳችን ጥናትና ምርምርን ለማበረታታት፣ መማር ማስተማሩን ለማገዝ፣ የአገር ቅርሶችን ጠብቆ ለትውልድ በማቆየት ሥራ ላይ በመሳተፋቸውና በግላቸው የሠሩትን ሁለት ሥዕሎች ለተቋሙ በማበርከታቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም የምስክር ወረቀት ከአበረከተላቸው መካከል ናቸው። ይህ ደግሞ አሁንም ያላሰለሰ ጥረት ለአገራቸው እንዲያደርጉ አግዟቸዋል።
መልዕክት
አገር ያለችበት ችግር በማንም ሳይሆን በዜጎች ነው የሚፈታው። በዚህም ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ከዜጎች ይጠበቃል። በመሆኑም ሰዓሊያን በስዕል ጥበባቸው ማህበረሰቡን ማስተሳሰርና በጎ ተግባራቸውን እንዲያጎለብቱ ማገዝ ይኖርብናል። በተለይም የተጎዱ ወገኖችን በተለያየ መልኩ ማገዝ የምንችልበት አቅሙም ሁኔታውም አለንና ይህ ጊዜ ብዙ የምንሰራበት ነው። እናም ችግር ተፈጥሯል እያሉ ከማውራት ወጥተን ራሳችን የችግሩ ተጠቂ እንደሆንን በማሰብ የድርሻችንን ማበርከት ይገባናል። አሁን እንደ አገር እንጂ እንደግለሰብ የመጣ ችግር የለም። ሁሉም ቤት ቁስል አለ። ስለዚህም በጥበብ የማይታከም ህመም የለምና እርስ በርስ እንተካከም የሚለው የመጀመሪያው መልዕክታቸው ነው።
ሌላው ያነሱት ነገር በብሔር ጥላቻ ውስጥ የመግባታችንንና እያስከተለብን ያለውን ችግር ሲሆን፤ መብዛታችን ሊያጋጨን አይገባም ባይ ናቸው። ምክንያታቸውም በብዙ ነገር መብዛት ብዙ ነገር የማግኘት ምስጢር ነው። በብዙነት ውስጥ ብዙ ባህል፣ ብዙ ጥበብ፣ ብዙ ጉልበት፣ ብዙ … አለ። ስለዚህም ምስጢሩን ለሚመረምርና ለሚረዳ ዋጋውን ያገኛል። ነገር ግን በቸልታ የሚያየው ሰው ዋጋውን ይከፍላል። አሁንም በአገራችን ላይ እያጋጠመ ያለው መለያየትና መጠላላት የብዝኃነትን ዋጋ ባለመረዳት ነው። ያንን የማየቱ ጉዳይ ደግሞ የእያንዳንዱ ሰው ግዴታ መሆን ነበረበት። ይሁን እንጂ ብዙነታችን የሰጠንን ጸጋ አልተረዳነውም። እናም ዋጋ እየከፈልን እንገኛለን። ስለሆነም ብዝኃነታችን የተሰጠን ለጥንካሬያችን እንጂ ለድክመታችን መንስኤ እንዲሆን አለመሆኑን ተገንዝበን አገራችንን ማቆም አለብን ሲሉ ይመክራሉ።
‹‹እግዚአብሔር ሲፈጥረን ለሁላችንም የሚሆነውን በእኩል ደረጃ ሰጥቶ ነው። የአንተ ብቻ ያለው ነገር የለም። ነገር ግን ከየት እንዳመጣነው በማይታወቅ ሁኔታ የእኛ የሚለውን ትተን የእኔ ላይ ሰፍረናል። ይህ ደግሞ ግለኝነትን አብዝቶብናል። በዚህም ለሁሉም የምንደርስበት ሁኔታ ተመናምኗል። እናም ዛሬ ካልነቃን መቼም አንለወጥምና እስካሁን የነበሩ ችግሮች ያስተምሩን።›› የሚሉት አርቲስቱ፤ ማንም በቋሚነት የያዘው ምድርም ክልልም የለምና ሁሉም በልክ ይሁን። ሁሉም ለሁሉም የተሰጠ ነው። አገራችንም ስትኖርበት የቆየችው ይህንኑ ባህልና ታሪክ ነው። ስለዚህም በተሰጠን ልክ መጠቀምን ዛሬ እንጀምር። ማስተዋል ሊገዛን ይገባል። አገር ሰላም እንድታገኝ እኛ ሰላም ሰጪ እንሁንላት፤ ለዚህ ደግሞ ጊዜው አሁን ነውና ለአገርም ሆነ ለራሳችን ፈውስ ሲባል ቆም ብለን እናስብ ሌላው መልእክታቸው ነው።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን የካቲት 6/2014