በመካከለኛና ረጅም ርቀት የሩጫ ውድድሮች የምትታወቀው አትሌት መሰረት ደፋር በሳምንቱ መጨረሻ በጃፓን ናጎያ በተካሄደው የሴቶች ማራቶን ውድድር አራተኛ ወጣች። በውድድሩ የኢትዮጵያና የኬንያ አትሌቶች ከፍተኛ የማሸነፍ ቅድሚያ ግምት ቢሰጣቸውም ናሚቢያዊቷ አትሌት ሂሊያ ጆሃንስ ሳትጠበቅ ቀዳሚ መሆን ችላለች።
2 ሰዓት ከ22 ደቂቃ ከ25 ሰከንድ የገባችበት ሰዓት ሆኖ ተመዝገቧል። ኬንያውያኑ አትሌት ቪሲሊን ጆፕኪሾ ከ22 ደቂቃ ከ58 ሰከንድ በማስመዝገብ ሁለተኛ ስትሆን፣ ሌላኛዋ የአገሯ ልጅ ቫለሪ ጄምሊ 2 ሰዓት ከ23 ደቂቃ ከ01 ሰከንድ በመግባት ሦስተኛ ደረጃን መያዝ ችላለች። ኢትዮጵያዊቷ መሰረት ደፋር 2 ሰዓት ከ23 ደቂቃ ከ33 ሰከንድ በመግባት አራተኛ ሆና ውድድሩን አጠናቃለች። አትሌቷ በሁለተኛ የማራቶን ወድድሯ የገባችበት ሰዓትም በቀጣይ ውድድሮች ውጤታማ መሆን እንደሚያስቻላት አመላክቷል።
የ35 ዓመቷ አትሌት መሰረት ባሳለፍነው ዓመት ለ12ኛ ጊዜ በተካሄደው የጃፓን ቶኪዮ ማራቶን ለመጀመሪያ ጊዜ ለመሳተፍ ወስና የነበረ ቢሆንም፤ ይህ ሳይሆን ቀርቶ በአምስተርዳም ማራቶን 2 ሰዓት ከ27 ደቂቃ ከ25 ሰከንድ በሆነ ሰዓት ስምንተኛ መውጣቷ ይታወሳል። ከዓመት በፊት በአሜሪካ ሳንዲያጎ ግዛት በተካሄደ የግማሽ ማራቶን ውድድር 1 ሰዓት ከ8 ደቂቃ ከ27 ሰከንድ በሆነ ሰዓት ማሸነፏም ይታወሳል።
አትሌት መሰረት ደፋር በ1999 ዓ.ም በፖላንድ የ3 ሺ ሜትር ዓለም አቀፍ ውድድር አድርጋ ሁለተኛ ከወጣችበት ጊዜ ጀምሮ በ1 ሺ 500፣ በ5 ሺ እና በ10 ሺ ሜትር ውድድሮች ኢትዮጵያን በመወከል የተለያዩ ስኬቶችን ተጎናጽፋለች። በ5ሺ ሜትር ሁለት ጊዜ የኦሎምፒክ የዓለም ሻምፒዮና መሆን ችላለች። በ3,000 ሜ በዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና አራት ጊዜ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ሆናለች። መረጃው የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ማህበር ነው፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 3/2011